ታከለ አለሙ
ደቡብ
ሱዳን እንደ አገር ከተመሠረተችበት ከጥቂት ዓመታት ጀምሮ ሠላምና መረጋጋት አግኝታ መኖር አልቻለችም፡፡ ዋነኛውና መሠረታዊ ምክንያቱ
የመሪዎቹ በጎጥና በጎሣ መከፋፈል የመንግሥትና ህዝብ የአገሪቷን ሀብት ያለአንዳች ይሉኝታ በመዝረፍ ወደር በሌለው የሙስና ተግባር
ውስጥ መዘፈቃቸው ነው፡፡ ደቡብ ሱዳን ለገላጋይ ባስቸገረ መልኩ በመሪዎቿ ምክንያት በመንግሥታዊ ሙስናና ዘረፋ እየተናጠች፣ እየፈረሰችና
በጦርነቱም ምክንያት ህዝብ እያለቀና እየተሰደደ ያለባት አገር ነች፡፡
እንደጎረቤት
የደቡብ ሱዳን ሠላም ማጣትና እርስ በርስ ጦርነት ኢትዮጵያን ያሳስባታል፡፡ ይመለከታታልም፡፡ በአሁኑ ወቅት 250 ሺህ ስደተኞች
የሚኖሩት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ የእርስ በርስ ጦርነቱም ዋና መንስዔ ሙስና ዘረፋ የአገር ሀብት ቅርምት ነው፡፡ ደቡብ ሱዳንን
ሙስናና ዘረፋ እያፈረሳት ያለች አገር ብሎ መግለጽም ይቻላል፡፡
ኢትዮጵያ
ለደቡብ ሱዳን ሠላምና መረጋጋት ያላደረገችው ጥረት ያልሞከረችው ሽምግልና የለም፡፡ ዋናው የጉዳዩ ባለቤቶች ራሳቸው ደቡብ ሱዳናውያን
እንደመሆናቸው መጠን ስለህዝባቸውና ስለአገራቸው ሲሉ ቆም ብለው ማሰብ ችግራቸውን በሥርዓቱ መፍታት ያለባቸው እነሱውና እነሱው ብቻ
ናቸው፡፡ ጉዳዩ አሳሳቢ በመሆኑ ነው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያና ሌሎች ሦስት የአፍሪካ አገራት በፒስ ኢንፎርስመንት ሠላም አስከባሪነት
ደቡብ ሱዳን ውስጥ እንዲሰማሩ የአፍሪካ ህብረት የወሰነውና ጉዳዩም ዓለም አቀፍ እውቅናን ያገኘው፡፡
የመጀመሪያው
የተባበሩት መንግሥታት የሠላም ማስከበር ተልዕኮ የተጀመረው በ1948 እ.ኤ.አ ነው። የፀጥታው ምክር ቤት በእሥራኤልና በዐረብ ጎረቤቶቿ
መካከል በነበረው ጦርነት የተባበሩት መንግሥታት ወታደራዊ ታዛቢዎች በቦታው እንዲሰማሩ በማድረጉ ነው፡፡ በቀጣይም ስድሳ ዘጠኝ ዓለም
አቀፍ የሠላም ማስከበር ግዳጅ አሰማርቷል፡፡ ሃምሳ ስድስቱ ከ1988 ጀምሮ ነው፡፡
ከዚያን
ጊዜ ጀምሮ ባሉት ዓመታት በመቶ ሺህዎች ወታደሮች በብዙ አሥር ሺህዎች ፖሊሶችና ሲቪሎች ከ120 አገራት ተውጣጥተው በዓለም አቀፍ
የሠላም ማስከበር ግዳጅ ተሰማርተዋል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ባንዲራ ሥር ሲያገለግሉ ከአሥር አገራት የተውጣጡ 3326 ሠላም አስከባሪዎች
ሞተዋል፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት 60 ዓመታት በሠላም ማስከበር ግዳጅ አሳልፏል፡፡ ኢትዮጵያም በነዚህ ሁሉ ረዥም ዓመታት የራሷን
ዓለም አቀፍ ድርሻ በተገቢው ሁኔታ ተወጥታለች፡፡
አሁን
ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ሠላም ማስከበር ግዳጅ እንድትገባ የተጠየቀችው በፒስ ኢምፎርስመንት ነው፡፡ ይህም በኃይል አስገዳጅነት የሠላም
ማስከበር ተልዕኮ ውጊያ ውስጥ የመግባት ግዳጅን ያጠቃልላል፡፡
የዲፕሎማቲክ
ጥረቶችን በማገዝ በተቀናቃኞች መካከል ሠላም እንዲሰፍን ለማስገደድ ሠላም አላሰፍን ካሉ ገለልተኛ ሆኖ የማይመለከት ኃይል ነው፡፡
ተቀናቃኞቹ ውጊያ ውስጥ ከገቡ ኃይል በመጠቀም ተኩስ አቁም እንዲፈጠር ያደርጋል፤ ያስገድዳል፤ ለሰለባዎቹ የተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈጠር ይሰራል ማለት ነው፡፡
ፒስ
ኢንፎርስመንት ሠላም አስከባሪው ኃይል ታጣቂዎች በሚዋጉበትና ሠላም በሌለበት ሁኔታ ውስጥ የሚሰማራ ሠላምን ለማስፈን ኃይልን የሚጠቀም
ነው፡፡ ከመደበኛው ሠላም አስከባሪ የሚለየው በሁለቱም ተቀናቃኝ ወገኖች በኩል መግባቱ የማይደገፍ መሆኑ ነው፡፡ በተለያዩ አገራት
ጥምረት የሚካሄድም ነው፡፡ ግቡን ለማሳካት በቂ ወታደራዊ መሣሪያዎችን መታጠቅ ያለበት ነው፡፡ ተቀናቃኞችን ወደ ድርድር ጠረጴዛ
እንዲመጡም የማስገደድ አቅም አለው፡፡
ደቡብ
ሱዳን በራሷ መሪዎች ለገንዝብ ማግኛነት የተጠለፈች በራሷ ልጆች አስተዋይነት ማጣትና ራስ ወዳድነት ለአገር ሳይሆን ለግል ጥቅማቸው
ሲሉ በአገር ሀብት ዘረፋ ላይ በተሰማሩ አሳፋሪ ሹማምንት የተነሳ ሠላሟን ያጣች በጦር አለቆች ዘረፋና ውንብድና በጎሣና በጎጥ እየተከፋፈሉ
እርስ በእርስ የሚጫረሱባት ህዝቡንም ለእልቂትና ለስደት የዳረጉባት አገር ናት፡፡
የደቡብ
ሱዳን መንግሥት በመሠረታዊ ደረጃ ማህበራዊ አገልግሎት መስጠት፤ ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግ፤ ሠላምና መረጋጋት መፍጠር፤ የህግ የበላይነትን
ማክበር ማስከበር አልቻለም፡፡ የደቡብ ሱዳን ሁኔታ እየተሸጋገረ ያለው ወደ ከፋ ጥፋትና የእልቂት ወንጀል ነው፡፡ መንግሥቱ የመሪዎቹን
ፍላጎት ብቻ ለማስጠበቅ የተመሠረተ የንግድ ኢንተርፕራይዝ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡
የደቡብ
ሱዳን ባለሥልጣናትና ዙሪያቸው ያሉ ግለሰቦች ብቻ በአገሪቱ የተፈጥሮ እምቅ ሀብት እንዳሻቸው ሲጫወቱበት ሌላው ዜጋ የሚያገኘው ምንም
ጥቅም የለም፡፡ ለህዝቡ የተረፈው እነሱ በጥቅምና በጎሣ በተጋጩ ቁጥር ሞትና ስደት ብቻ ነው፡፡ ይኼ ነው ኢትዮጵያንም ዓለም አቀፉን
ኅብረተሰብንም እያሳሰበውና እያስጨነቀው ያለው፡፡ እንደነዚህ ዓይነት መሪዎች አገራቸውን ብቻ ሳይሆን መላውን አፍሪካ የሚያሰድቡ
ከሰብዓዊነት ይልቅ የአውሬነት ባህርይ የተላበሱ አስገራሚ ፍጡራን ናቸው፡፡
በደቡብ
ሱዳን የገዢው ፓርቲ ተፎካካሪ አንጃዎች ራሱን መንግሥትንና መንግሥታዊ መዋቅሩን ጠልፈውታል፡፡ ተቋሞቹን በኃይል አስገድደው ይጠቀማሉ፡፡
ፋይናንስ በማድረግ መረባቸውን ያጠናክራሉ፡፡ ዓላማቸው በግል መክበር ወይም የፖለቲካ ሥልጣን መያዝ ብቻ ነው፡፡ ያልተገደበ ህግና
ሥርዓት የማይገዛው ስግብግብነት ነው በደቡብ ሱዳን ላለው ግጭት አንዱ ምክንያት፡፡ ይህንን ዓለም አቀፍ ተቋማት ዝርዝር ጥናት አድርገው
በማስረጃ ደርሰውበታል፡፡
በዓለም
አቀፉ የሠላም ጥረት ውስጥ በአግባቡ ያልታየውና ትኩረት ያልተሰጠው አሁን ግን በታላላቆቹ መንግሥታትና ለጋሽ አገራት ልዩ ትኩረት
ያገኘው ጉዳይ ይኸው የመሪዎቹ በከፍተኛ ሙስናና ስግብግብነት ተዘፍቀው
የመገኘታቸው ጉዳይ ነው፡፡ የደቡብ ሱዳን ህዝቦች በምድራችን የመጨረሻዎቹ ድሆች ናቸው፡፡ አገራቸው ደግሞ በተፈጥሮ ሀብቷ እጅግ
በጣም ሀብታም አገር ናት፡፡ ሀብቱን የሚመዘብሩትና የሚጫወቱበት የፖለቲካ መሪዎቹ ናቸው፡፡
ለደቡብ
ሱዳን መሪዎች የፖለቲካ ሥልጣን መያዝ ማለት መገመት ከሚቻለው በላይ ተመንጥቆ መክበር ማለት ነው፡፡ በ2013 ነጻነቷን ካገኘች
ከዓመት በኋላ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ከመንግሥት ካዝና ተዘርፏል፤ አራቁተውታል፡፡
አሜሪካዊው
ዓለም አቀፉ ኢነፍ ፕሮጀክት የሚል መጠሪያ ያለው ተቋም በደቡብ ሱዳን የሚካሄደውን መንግሥታዊ ዘረፋና የመሪዎቹን ውንብድና በተመለከተ
ሰፊ ማጣራትና ምርመራ በማድረግ ሙሉ ሪፖርት አቅርቧል፡፡ በመንግሥቱ ውስጥ ማሰብም መገመትም ከሚቻለው በላይ ግዙፍ ምዝበራና ዘረፋ
ማጭበርበሮች እንዲሁም የአገሪቱ ሀብት ተቆጥሮ በማይዘለቅ መልኩ መዘረፉን አረጋግጧል፡፡
በደቡብ
ሱዳን ባንክ ለአገሪቱ መሪዎቹና በየደረጃው ላሉ ሹሞች ቅርብና ቤተኛ የሆኑ ሰዎች ፕሮጀክት እንዲሰሩ እየተደረገ ባላቸው ግንኙነት
በሚሊዮኖች ዶላር ይወስዳሉ፡፡ የተባሉት የፕሮጀክት ሥራዎች ደግሞ በፍጹም አይሰሩም፡፡ የመንግሥትን ሀብት ይዘርፋሉ፡፡ አቻ የሌለው
ጥፋትና ውድመት ያደርሳሉ፡፡ የተዘረፈውን የመንግሥትና የአገር ሀብት ባህር ማዶ ወደሚገኙ ባንኮች ያሸጋግራሉ፡፡
በደቡብ
ሱዳን በአጭር ጊዜ ቋሚ ሠላም ይመጣል ብሎ ማሰብ የማይታሰብ ነው የሚሆነው፡፡ የሚቀሰቀሰው ጦርነት በአገር ሀብት ዘረፋ ላይ በመንተራስ
የሚካሄድ በመሆኑ ከመሠረቱ በመለወጥ አገራዊና ህዝባዊ ኃላፊነት ተጠያቂነት ያላቸው ኋላ ቀር ከሆነው የጎሣ ፖለቲካ የተላቀቁና ለህዝባቸው
ታላቅ ራዕይ የሰነቁ መሪዎች እስካልተተኩና እስካልተፈጠሩ ድረስ ግጭቱና ጦርነቱ አንዴ ቀዝቀዝ አንዴ ሞቅ እያለ ይቀጥላል፡፡
የህግ
ተጠያቂነት ግልጽነት እስካልሰፈነ ድረስ በመንግሥት ባለሥልጣናት የሚካሄደው የቆሸሸ የሙስና ተግባር ህገ ወጥ ዘረፋም ሆነ ገንዘብ
ዝውውሩ ለእርስ በርስ ጦርነቱና ለጎሣ ክፍፍሉ ዋና ምክንያት በመሆን እንደትናንቱ ሁሉ ይቀጥላል፡፡ በአገሪቱ ላይ ጦርነት ጥፋትና
አደጋ ያመጡትም እነዚሁ ኃይሎች ናቸው፡፡ ፖለቲካዊ ፈቃደኝነትና የፖሊሲ ራዕይ የላቸውም፡፡
ታላቅ
መንግሥታዊ ዘረፋና ውንብድና ሙስና ነው ደቡብ ሱዳንን ባለፉት ሁለት ዓመታት ጦርነት ውስጥ የከተታት፡፡ የ2015 የአፍሪካ ህብረት
የደቡብ ሱዳን አጣሪ ኮሚሽን በሪፖርቱ ላይ 34 ጊዜ ነው ሙስናን የጠቀሰው፡፡ ለቀውሱ መፈጠር እርግጠኛ ምክንያት መሆኑን በመግለጽ፡፡
ሀብት ለዜጎቿዋ በእኩል ያለመከፋፈሉ የተለያዩ ቡድኖችን በማግለል የአገሪቱን አንጡራ መዋዕለ ንዋይ በብቸኝነት መዝረፍ ከፍተኛ ቅሬታን
በሁለቱ መሪ ፓርቲዎች ውስጥ በመፈጠሩ ነው ግጭትና ጦርነቱ የሚካሄደው፡፡
አንዱ
ከሌላው የፖለቲካ ሥልጣን ለመንጠቅ ሠራዊት አሰልፈው እርስ በርስ የሚዋጉትም ለዚሁ ነው፡፡ በጦርነቱ የተነሳ ዩኤስኤይድ እንደሚለው
2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ደቡብ ሱዳናውያን ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ረሀብ አለ፡፡ በተለይ በጦርነቱ
አካባቢዎች፡፡ ከጦርነቱ ጀምሮ አሜሪካና ሌሎችም ለጋሾች በቢሊዮን የሚቆጠር ዕርዳታ አድርገዋል፡፡ ችግሩ ግን እንደቀጠለ ነው፡፡
ጦርነቱ
እንዳይቆም የሚፈልጉ የውጭ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች፣ ደላላዎችና የማፍያ ቡድኖችም ጓዛቸውን ጠቅልለው ደቡብ ሱዳን ከገቡ ዓመታት
ተቆጥረዋል፡፡ የእርስ በርስ ጦርነቱ የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት አውድሞታል፡፡ በሁለቱም ተቀናቃኝ ወገኖች ያሉ ሙሰኛ ባለሥልጣናት በአገሪቱ
ጦርነት ውስጥ መግባትና ሠላም ማጣት ከብረውበታል፡፡
ባለሥልጣናቱ
ከዓለም አቀፍ የጦርነት አትራፊዎች ጋር ተቀናጅተው ይሰራሉ፡፡ አስገራሚው ነገር የደቡብ ሱዳን መሪዎች በጎረቤት አገራትና በተለያዩ
የዓለም ክፍሎች የቅንጦት ንብረቶች አላቸው፡፡ ልጆቻቸውን ባህር ማዶ ልከው እጅግ ውድና ምርጥ በተባሉ የግል ትምህርት ቤቶች ያስተምራሉ፡፡
ህዝቡ እነሱ አልጠግብ ብለው በቆሰቆሱት ጦርነት ይረግፋል፡፡ ሠላሙን አጥቶ በጥይት እየተቆላ በሲኦል ውስጥ ይኖራል፡፡ ሁለቱም ተቀናቃኝ
ወገኖች በከፍተኛ ደረጃ ወታደራዊ ኃይልና የጦር መሣሪያ ይጠቀማሉ፡፡ ለፖለቲካ ዓላማቸው ሲሉ የጎሣ ግጭቱን ያቀጣጥላሉ፡፡ እንዲቆምም
አይፈልጉም፡፡
በደቡብ
ሱዳን ሁለቱም ወገኖች በሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲሉ የጅምላ ግድያና ውድመት ይፈጽማሉ፡፡ ሲቪሎችን በገፍ ይገድላሉ፡፡ ሰብዓዊ ሠራተኞችን
ጭምር፡፡ ዓለም አቀፍ ቢሯቸውን ይዘርፋሉ፡፡ የገዘፈው ሙስናና ምዝበራ በሱዳን መንግሥት ውስጥ ሥር በመስደዱ ነው ይህ ሁሉ ጥፋትና
ውድመት በአገሪቱ ላይ የነገሰው፡፡ ለሰው ልጅ ህይወት አክብሮት የላቸውም፡፡
በደቡብ
ሱዳን የነገሱት ጦረኞች የመንግሥትን ገንዘብ መዝረፍ፣ የአገሪቱን ህግ መጣስና የጦር ወንጀል መፈፀም ይቻላል ብለው ያምናሉ፡፡ መፍትሄው
መንግሥታዊ ተቋማትን ከጠለፉት ወንጀለኞች በማጽዳት የህግ የበላይነትን ማስፈንና ተጠያቂነት ያለው ሥርዓት መዘርጋት መቻል ብቻ ነው፡፡
የደቡብ
ሱዳን መንግሥት ለዜጎቹ መሠረታዊ አገልግሎት መስጠት አልቻለም፡፡ ቢኖርም እንደሌለ የሚቆጠር መንግሥት ነው፡፡ የህዝብ አገልግሎት
ሠራተኞች ደመወዝ የላቸውም፡፡ የህዝብ ጤና አገልግሎት፣ የትምህርት ፕሮግራሞችና መሠረተ ልማት የሚባል ጭርሱንም የለም፡፡ ዓለም
አቀፉ ማኅበረሰብ ዕርዳታና እገዛ ቢያደርግም በመሪዎቹ እጅ ወድቆ ይቀራመቱታል፡፡ ባህር ማዶ ያሻግሩታል እንጂ ለህዝብ አገልግሎት
ስለመዋሉ ማረጋጋጫ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የለም፡፡
በተለይ
የአፍሪካ ህብረትና የምዕራባውያኑም የቅርብ እገዛና ትብብር ግፊትና ጫና እስካልተደረገ ድረስ መሪዎቹ ያለው ጦርነትና ምስቅልቅል
የተመቻቸው በመሆኑ የሚሰሩት የግል ሀብታቸውን ለማሳደግ እንጂ ለህዝቡ የሚጠቅም ሥራ አይደለም፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት
ከፍተኛ በሆኑ የደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት ላይ ስለህዝቡና ስለአገሪቷ ሲባል ልዩ ማዕቀብ መጣል አለበት የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡
የመንግሥትን
ንብረት በከፍተኛ ደረጃ በሚዘርፉት፣ አመጽ በሚያቀጣጥሉትና በህዝቡ ላይ ይህ ቀረው የማይባል የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሚፈጽሙት የደቡብ
ሱዳን ባለሥልጣናት ላይ የዝውውር እገዳ መጣል በጎረቤት ኬንያ ባንክ
የመንግሥታቸውንና የህዝባቸውን ሀብት በመዝረፍ በብዙ ሚሊዮን ዶላር ያካበቱትን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ገንዘቡን እንዳይጠቀሙበት
ማድረግ መልሶም ለአገሪቱ ልማት ማዋል ተገቢ መሆኑን የሚገልጹ አስተያየቶችም ይደመጣሉ፡፡
በተለይ
የሜጀር ጄኔራል ማርያል ቻንኡዎንግ ዮልማንጎክ እንዲሁም ሌተና ጄኔራል ጋብሬል ጆክ ሪያክ በኬንያ ንግድ ባንክ ውስጥ በብዙ ሚሊዮን
የሚቆጠር ዶላር አካውንት ያላቸው መሆኑን በመግለጽ የኢነፍ ፕሮጀክት መሥራች ዳይሬክተር በሴኔቱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የአፍሪካ የዓለም
ጤና፣ ሰብዓዊ መብት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ንዑስ ኮሚቴ ፊት ቀርበው ደቡብ ሱዳን ለሠላምና ደህንነት ያላት እድሎች በሚል ባቀረቡት
ሪፖርት ውስጥ በስፋትና በዝርዝር ገልፀውታል፡፡
በዚህም
መሠረት የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ መሪዎች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሚገኙ ባንኮች ከደቡብ ሱዳን ህዝብና መንግሥት ዘርፈው ያከማቹት
ሀብትና ንብረት በምርመራ ከተጣራ በኋላ እንዳይንቀሳቀስ ይደረጋል፡፡ ኤፍ ቢአይና የአገር ውስጥ ደህንነት ምርመራውን መምራት አለባቸው
ሲሉ የኢነፍ ዓለም አቀፍ ፕሮጀክት ዋና ዳይሬክተር ገልፀዋል፡፡
የደቡብ
ሱዳን መሪዎች በአገሪቱ ከሚካሄደው በጭካኔ የተሞላ ጦርነት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ እነሱ ብቻ አይደሉም እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው
ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮችና ብዙ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችም በጦርነቱ ለማትረፍ ደቡብ ሱዳን ይገኛሉ፡፡
በዚህ
ሁኔታ ውስጥ ነው የአፍሪካ ህብረት ኢትዮጵያና ሌሎች ሦስት የአፍሪካ አገራት አስፈላጊ ሲሆን ኃይል መጠቀም በሚችል የሠላም ማስከበር
ግዳጅ ደቡብ ሱዳን ውስጥ እንዲሰማሩ የወሰነው፡፡ ደቡብ ሱዳን ልቅ በሆነ መንግሥታዊ ሙስናና ዘረፋ እየፈረሰች ያለች አገር መሆኗ
የዘመናችን አስገራሚ ክስተት ነው፡፡ ሁኔታውም ውስብስብ ገጽታ አለው፡፡
No comments:
Post a Comment