ቶሎሳ ኡርጌሳ
እሁድ ነሐሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም። ልክ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ላይ። አዲስ
አበባ መስቀል አደባባይ እምብርቱ ላይ ተገኝቻለሁ። ከሰፈሬ ማልጄ ወደ መስቀል አደባባይ በታክሲ በመሄድ ስፍራው የተገኘሁት በተለያዩ
ማህበራዊ ሚዲያዎች የከተማው ህዝብ ስርዓቱን እንዲያወግዝ በፀረ-ሰላም ኃይሎች የተጠራ ሰላማዊ ሰልፍ ካለ ለማየት ነበር። መስቀል
አደባባይ ፊት ለፊት የሚገኘው የአዲስ አበባ ኤግዚቪሽን ማዕከል በሚያስገባው ደረጃ ላይ አንዳንድ የረፈደባቸው የአካል ማጎልበቻ
ስፖርት የሚሰሩ ሰዎችን ከመመልከቴ በስተቀር በቦታው ምንም ዓይነት ሰልፈኛ ማግኘት አልቻልኩም። አካባቢው ተለምዷዊ እንቅስቃሴ እየተከናወነበት
ነበር። ከአደባባዩ ፊት ለፊት የልማታዊ ስርዓቱ ትሩፋቶች የሆኑት ባቡሮች ደቂቃዎችን እያስቆጠሩ ይተላለፋሉ።
ቦታው የአራት መንገዶች መስቀለኛ በመሆኑም፣ ወደ ቦሌ፣ ወደ መገናኛ፣ ወደ
ስድስት ኪሎ እና ወደ ሜክሲኮ የሚተመው የከተማው ነዋሪ ዕለታዊ ጉዳዩን ለመከወን ስፍራውን አቋርጦ ከማለፉ ውጪ፣ ስለ ሰልፍና ሰልፈኛ
የሚያወጋ ሰው አላጋጠመኝም። በዚያ አካባቢ ያየሁት ህዝብ በፀረ ሰላም ሃይሎች ስለተጠራውና ‘ወጥታችሁ ሁከት ፍጠሩ’ ስለተባለው
ጉዳይ የሰማ አይመስልም። ወይም ውትወታውን ሰምቶ እንዳልሰማ አልፎታል። ሁሉም በየፊናው ይተማል። እርግጥም በትናንትናው ዕለት የአዲስ
አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለህብረተሰቡ በፀረ- ሰላም ኃይሎች የተጠራ ሰልፍ መኖሩን በመግለፅ፣ ህዝቡ እንዲጠነቀቅና ከዕለታዊ ስራው ሳይስተጓጎል
የተለየ እንቅስቃሴ ካጋጠመው በተለመደ ትብብሩ ለፖሊስ እንዲያሳውቅ ያስተላለፈውን ጥሪ የመዲናችን ነዋሪ ተቀብሎት፤ የፀረ-ሰላም
ኃይሎቹን ውትወታ ከመጤፍ አልቆጠረውም ማለት ነው። አደባባዩ ላይ ምንም አይታይም። ሰልፍና ሰልፈኛ ቦታው ላይ የሉም።
እኔም ፀረ-ሰላም ኃይሎቹ በሌላ ሰው እጅ እሳትን ለመጨበጥ የሞከሩበትና
‘ወጥታችሁ ሁከት ፍጠሩ’ ያሉበት ጥሪ ውሃ እንደበላው ለመገንዘብ ብዙም ማሰብ አላስፈለገኝም። ያም ሆኖ ግን “መስቀል አደባባይ
ተገኝተን ለገዥው ፓርቲ ቀይ ካርድ እንስጠው ያሉት የማህበራዊ ሚዲያ አርበኞች የታሉ?” በማለት ራሴን ከመጠየቅ ወደ ኋላ አላልኩም። ምናልባት ለጥያቄዬ ምላሽ አገኝ ይሆን ብዬ ግራና ቀኝ አማተርኩ። ከአላፊ መንገደኛ በስተቀር እጅብ ብሎ የተሰበሰበ
ሰው እንኳን አላየሁም። አዎ! እነዚያ በብዙሃን ሰላም የጥቂቶችን የሁከት አመፅ “እንጀራ” ለመጋገር የፈለጉት ፀረ-ሰላም ኃይሎችን ተከትሎ የወጣ ህዝብ ካለ በማለት በመስቀል አደባባይ ላይ ቆሜ ባማትርም ሰላም ወዳዶቹ አዲስ
አበቤዎች በአራዳ ቋንቋ እንደሚሉት “ወፍ የለም!”።… መቼም ነፍሱን ይማረውና እንደ ክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ሁሉም ነገር በግልፅ በሚታይበት በመስቀል አደባባይ ውስጥ “ፈልጌ አስፈልጌ ያን ሰሞን ያጣኋት…” እያልኩ ላዜም አልችልም። ድምፁም የለኝም፤
ባዶ ሜዳ ላይ በጠራራ ፀሐይ የሌለ ሰውን እንደ ፈላስፋው ዲዩጋን በፋኖስ መፈለጌም ግርምት ላይ ይጥለኛል። እናም አልሞከርኩትም።
እርግጥም እነዚያ ሰዎች የሚገኙት እንደ ፌስ ቡክ ባሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እንጂ እዚህ ሀገር ውሰጥ ባለመሆኑ እንዲሁም እነርሱን
የሚሰማቸው አመዛዛኝ ህዝብም ሊኖር ባለመቻሉ ለከሸፈ ነገር ማዜምም ይሁን የሌለን ሰው ፍለጋ መኳተን እንደማይጠበቅብኝ ለመገንዘብ
ብዙም ጊዜ አልወሰደብኝም።
ታዲያ እዛው መስቀል አደባባይ
ባሉት የስፖርት ማዘውተሪያ ደረጃዎች ላይ ቁጭ ብዬ ፌስ ቡክን የመሳሰሉ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ለአፍታ አሰብኳቸው። በእዝነ ልቦናም
የኋሊት የዛሬ 11 ዓመት ገደማ ተጓዝኩ፤ 1997 ዓ.ም። ነገሩ እንዲህ ነበር።…የዛሬዎቹ የማህበራዊ ሚዲያ ተዋናዮች፤ ያኔ ህገ-መንግሥቱንና ህገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን በአመፅ ለመጣል የጎዳና ላይ ነውጥ ማቀጣጠላቸውን አንዘነጋም። በነውጥ ስልጣን ካልያዝን ምንም ዓይነት የምርጫ ውጤትን አንቀበልም ማለታቸውንም እንዲሁ።
በወቅቱ የምዕራቡን ዓለም አክራሪ ኒዮ- ሊበራሎችን ‘በእናንተው መጀን ይሁን፣ ለዙፋን አብቁን’ በማለትም “አንጋሽ” ፍለጋ ተሯሩጠዋል። “አንጋሾቹም” ያለ ሃፍረት በአንዲት ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት፤ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የሪፖርት ጋጋታ በማውጣት የተላኪዎቻቸውን እንባ ለማበስ ሞከሩ። ይሁንና ህዝቡ ግን “በሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነቴ ውስጥ ምን ዶላችሁ?” በማለት እጢያቸውን ዱብ አደረገው። “አንጋሽ ፈላጊዎቹንም
ታዘባቸው፤ ስለሚያወሩት ነገርም ጆሮውን ነፈጋቸው። ያም ሆኖ
እነዚያ ፀረ-ሰላም ሃይሎች ግን ተስፋ አልቆረጡም— ውጭ ሀገር በገሃዱ ዓለም ላይ ሆነው ሀገር ቤት ውስጥ መከናወን ስላለበት ነገር ምናባዊ እምቢልታቸውን ቀጠሉበት።…
…ይህ የምናብ ዓለም እምቢልታቸው
ብዙም አልቆየም። ስድስት ዓመት ቆይቶ ብቅ አለ—ግንቦት 20 ቀን 2003 ዓ.ም።…በዕለቱ ልክ እንደ ዛሬው መስቀል አደባባይ ተገኝቼ ነበር። ያኔም እነ አሸባሪው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ፅንፈኛ ቡድኖችና አንዳንድ የቀድሞው ስርዓት ናፋቂዎች፤ የሀገራችን ደመኛ ጠላት የሆነውና በዕድገታችን እርር-ድብን በማለት የሚቀናው የኤርትራ መንግሥት ተላላኪ ሆነው “በመስቀል አደባባይ ግንቦት 20ን በመቃወም በፌስ ቡክ ላይ ተቃውሞ አውጀናል፤
ሶስት ሺህ የሚጠጉ ዜጎችም ሰልፉን ለመቀላቀል ድረ ገፅ ላይ ፈርመውልናል” ብለው ሽር ጉድ ሲሉ መክረማቸውን አስታውሳለሁ። ጥሪው የተካሄደው ውጭ ሀገር ተሁኖ ሲሆን፤ በዕለቱ የግንቦት 20 ክብረ-በዓል
ላይ ለመታደም የተገኘው የአዲስ አበባ ነዋሪ ግን ልክ እንደ ዛሬው ስለ ጥሪው የሰማ አይመስልም። እኔም እንኳንስ ሶስት ሺህ ቀርቶ
ሶስት የሚሆን ሰውም ዕለቱን ለመቃወም ሲወጣ አላየሁም። እናም የተባለውን ምናባዊ ቁጥር እምጥ ይግባ ስምጥ በወቅቱ ላገኘው ባለመቻሌ
ለራሴ ግርምትን አጭሮብኝ ነበር። በስተመጨረሻም በዕለቱ ግንቦት 20ን ለማክበር የወጣው የመዲናችን ነዋሪ ለሰላም፣ ለልማትና ለዴሞክራሲ
ያበቃውን ዕለት አክብሮና ለህዳሴው ግድብ የሚሰጠውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ቃል ገብቶ ወደ መጣበት በሆታና በጭፈራ መመለሱን አስታውሳለሁ።…
…ዛሬስ?...እርግጥ ዛሬም እንደ ትናንትናዎቹ የጥሪው ባለቤት የሆኑትና የሀገራችንን
ለውጥ እንዲሁም ዕድገት የማይደግፉ የውጭና የውስጥ ፀረ ሰላም ኃይሎች ቅንጅታዊ የሁከት ጥሪ ሰሚና አዳማጭ አላገኘም፤ በአዲስ አበቤዎች።
እናም በሁኔታው በመደመም የአዲስ አበባ ህዝብ ለሰላም ያለውን ቀናዒ ፍላጎት ዛሬም አረጋገጥኩ።…ግና አንድ ጥያቄ ውስጤን ሰቅዞ
ያዘው—‘የመዲናችን ነዋሪ ለፀረ-ሰላም ኃይሎች የሁከት ጥሪ የሰጠው ብስለት የተሞላበት ምላሽ ምክንያቱ ምንድነው?’ የሚል። እንደ
‘ኢሳት’ ዓይነት የሽብር ቡድን ልሳኖች፣ እንደ “ቪኦኤ” የአማርኛው ክፍል ዓይነት የኢህአፓ፣ የደርግና የቅንጅት ቅሪቶች፣ በፅንፈኛ
ድረ ገፆችና በፌስ ቡክ ገፆች ላይ በመደጋገም የቀረበው የ‘ሁከት ፍጠሩ’ ጥሪ መምከኑስ ምንን ያሳያል? ስልም ራሴን መጠየቄ አልቀረም።…
…እናም ብዙም ሳልቆይ ለጥያቄዎቼ ምላሽ የሚሆኑ ሶስት ምክንያቶችን አገኘሁ።
በእኔ እምነት አንደኛው፣ ነዋሪው ከሰላም እንጂ ከሁከት የሚገኝ ትርፍ የሌለ መሆኑን ማወቁ፤ ሁለተኛው፣ የከተማዋ ነዋሪ የሚፈጠሩ
ችግሮችን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ተወያይቶ መፍታት እንደሚቻል መገንዘቡ ሲሆን፤ ሶስተኛው ደግሞ አሁን ያለው መንግስት ችግሮችን
በማንኛውም ጊዜ የመፍታት አቅምና ብቃት ያለው መሆኑን ካለፈባቸው ተግባራዊ ሂደቶች ማወቅ መቻሉ ነው። ሶስቱም ምክንያቶቼ በአንድም
ይሁን በሌላ መልክ የከተማውን ህዝብ አተያይ ሊወክሉ የሚችሉ ይመስለኛል።
እስቲ ውድ አንባቢያን ሃሳቤን ይረዱልኝ ዘንድ ሶስቱንም ምክንያቶቼን አፍታትቼ
ልዘርዝራቸው። የአዲስ አበባ ነዋሪ እንደ ማንኛውም ህዝብ የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን ነገር ለይቶ ያውቃል። ከሰላም እንጂ ከነውጥና
ከሁከት ምንም እንደማይገኝ በሰከነ ሁኔታ ይገነዘባል። ማንም በቀደደለት የፀረ-ሰላምነት ቦይ ዝም ብሎ የሚፈስ አለመሆኑን “ለፌስ
ቡክ አብዩተኞቹ” በሚገባ ነግሯቸዋል። ትናንት ‘ምናልባትም ኢትዮጵያ ውስጥ አመፅ ካስነሳን፣ በግርግር የስልጣን ኮርቻን ልንፈናጠጥ
እንችላለን’ በሚል በየማህበራዊ ሚዲያው ሲጋልቡት የነበረው የተሳሳተ የቀቢፀ ተስፋ- ምኞትን በውል ተገንዝቦ ከምኞት እንዳይዘል
ያደረገው ሰላም ወዳዱ የመዲናችን ነዋሪ፣ ትናንት “እባካችሁ እኛ የህዳሴያችን ሩጫ ላይ ስለሆንን፣ ይህን ‘ማሪንጌ ቻቻችሁን’ እዛው
በምዕራቡ ዓለም የምሽት ክበቦች ውስጥ ደልቁት” በማለት የማያሻማ ምላሽ የሰጣቸው አዲስ አበቤ፤ ዛሬም በሰከነ ሁኔታ ነገሮችን አገናዝቦ
የፌስ ቡክ አርበኞችን “ፌዘኞች” ብሏቸዋል። ለእኔ የተሰማኝ የከተማችን ነዋሪ ምላሽ ይኸው ነው።
የአዲስ አበባ ህዝብ የመጣበትን መንገድ ወደ ኋላ ዞር ብሎ ይመለከታል እንጂ፣
እንደ “ፌዘኞቹ” በስሜት የሚነዳ አይደለም። ሁሉንም ነገር በትዕግስት የሚያጤን ህዝብ ነው። ባለፉት 25 ዓመታት በፌዴራል ስርዓቱ
የተመዘገቡትን ድሎች ይገነዘባል። ልማትና ዴሞክራሲ በሂደት እንጂ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ዕውን እንደማይሆኑ የሚያውቅ
ሩቅ አሳቢ ህዝብ ነው። ከትላንት ዛሬ፣ ከዛሬ ደግሞ ነገ፣ ከነገ ደግሞ ከነገ ወዲያ እንደሚሻል ይገነዘባል። ከስሜት ይልቅ ለትዕግስት
ቦታ ይሰጣል። ትዕግስት ጊዜውን ጠብቆ የሚያፈራ ማር መሆኑንም ያውቃል። የኦሮሞ አባቶች “obsaatu damma gnaataa”
/ኦብሳቱ ደመ ኛታ/ (“የታገሰ ማር ይበላል” የማለት ያህል ነው) እንደሚሉት ከትዕግስት የሚገኘውን ጣፋጭ ፍሬ የሚያውቅ ህዝብ
ነው። እርግጥም ለዚህ አስተዋይና ሚዛናዊ ህዝብ ከአንዴም ሁለቴ…ከሁለቴም ሶስቴና አራቴ ብሎም አምስቴ…ቆሜ ባጨበጭብለት ቢያንስበት
እንጂ የሚበዛበት አይመስለኝም።
አዎ! በውጭና በውስጥ ፀረ- ሰላም ኃይሎች የተቀናጀ ሴራ የተጠራው ሁከት
የህዝቡን ብሶቶች ለማራገብም ሞክሯል። የአዲስ አበባ ህዝብ ግን ያለፉትን 25 ዓመታት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ እመርታዎችን
ስለሚያውቅና ነገሮችን የሚያገናዝብ ብሎም ፍትሃዊ በመሆኑ፤ የፌስ ቡክ ፌዘኞችንና ጥቂት የውሰጥ አጫፋሪዎቻቸውን “የቁራ መልዕክተኛነት”
ሊቀበል አልፈቀደም። የመዲናችን ህዝብ በሀገሪቱ ውስጥ የተፈጠሩትና ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዘው የሚነሱት ተግዳሮቶችና ሌሎች
መሰል ጉዳዩች መንግሥት እያስመዘገበ ባለው ዕድገት ላይ ያጋጠሙ ጊዜያዊ ችግሮች መሆናቸውን ይገነዘባል።
ይህ ህዝብ ባለፉት ጊዜያት መንግሥት “አደርገዋለሁ” ብሎ የገነባውን ቃል
እንዳላጠፈው ሁሉ፤ ዛሬም የሚነሱ ችግሮችን እርሱ ብቻ እንደሚፈታለት እርግጠኛ ነው። የመዲናዋ ህዝብ በመንግሥት ትክክለኛ የልማት
አቅጣጫዎችና ፖሊሲዎች ተመርቶ ተጠቃሚነቱን በየደረጃው ከጊዜ ወደ ጊዜ ማረጋገጥ ላይ የሚገኝ በመሆኑም “የነገ ሰው” እንደሚሆን
ተስፋን የሰነቀ ነው። በእንዲህ ዓይነት የተስፋ ባቡር ላይ የተሳፈረ ህዝብ ደግሞ ተጠቃሚነቱን ለመሸርሸር የሚሹ ፀረ-ሰላም ሃይሎችን
“ወግዱ!” ቢላቸው ተገቢና ትክክል ይመስለኛል።
ምን ይህ ብቻ! ይህ ለሰላም ቀናዒ የሆነና አመዛዛኝ ህዝብ ለፀረ-ሰላም ሃይሎችና
ለፅንፈኞች ሲል ያለፈው አረመኔያዊና ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ጫንቃው ላይ እንደ አዲስ እንዲጫንበት አይፈልግም። ከሁለት አስርታት
በላይ የተጎናፀፈው የሰላም እፎይታ ፀዳልን ፀረ ሰላም ሃይሎች እንዲያደፈርሱበትና ህይወቱ ምስቅልቅል እንዲሆንበት አይሻም። የአዲስ
አበባ ህዝብ ከሌሎች የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመሆን በልዩነት ውስጥ ባለ አንድነት ተከባብሮ የመሰረተው ልማታዊና
ዴሞክራሲያዊ ስርዓትም፤ ለሀገራችን በጎ በማይመኙ የውጭና የውስጥ ፀረ-ሰላም ሃይሎች እንዲሁም ባለፈው ስርዓት ባለሟሎችና አጫፋሪዎቻቸው
ሳቢያ የኋሊት እንዲቀለበስበት አይፈልግም።
በትምክህተኞችና በጠባቦች ምክንያትም እያራመደ ያለው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነቱ
እንዲሸረሸር ቦታ አይሰጥም። እርግጥም እነዚህን የስርዓቱን ትሩፋቶች እያጣጣመ ያለው የመዲናችን ነዋሪ፤ ሰላሙን በማወክ ኑሮውን
ለማሽቆልቆል ያሴሩበትን፣ በእርሱ ደምና በህይወት ክፋይ ስልጣንን በአቋራጭ ለማግኘት የሚሹ የባህር ማዶ የድረ ገፅ ህልመኞችን የሁከት
ጥሪ ሊሰማ የሚችልበት ጆሮ የለውም። በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ይመስለኛል—የመዲናችን ነዋሪ ፀረ-ሰላም ሃይሎች በማህበራዊ ሚዲያዎች
ላይ ያቀረበውንና ‘ውጡና ሁከት ፍጠሩ፣ ለስርዓቱም ቀይ አሳዩት’ የሚል ጥሪን “ጆሮ ዳባ ልበስ” ብሎ ቀይ ካርዱን ለራሳቸው መልሶ
የሰጣቸው። እናም የእሁዱ የሁከት ጥሪ መክሸፉ የግድ ነበር።…
ያም ሆነ ይህ ግን እኔ እንደ ማንኛውም ዜጋ ሰላም ወዳድና አስተዋይ ለሆነው፣
የፀረ- ሰላም ኃይሎችን የሁከት ጥሪ መና ላስቀረው እንዲሁም ‘በሰላሜ አትምጡብኝ’ በማለት በቅጥፈት ወሬ ላልተታለለው ለአዲስ አበባ
ህዝብ ያለኝን የላቀ አክብሮት ለመግለፅ፤ እነሆ ከተቀመጥኩበት መስቀል አደባባይ ብድግ ብዬ በአክብሮት ባርኔጣዬን አነሳሁ!...ሰዓቴንም
ተመለከትኩ—ከረፋዱ አምስት ሰዓት ከአስር ደቂቃ ይላል።…ፊቴን ወደ መጣሁበት የታክሲ መስመር አዞርኩ።…
No comments:
Post a Comment