አብኬሞዳ
‹‹ልጅነት
ዕዳ ነዉ›› ይሉ ነበር አያቴ፡፡ ዕድሜ ቢያስተምራቸው እንደሆነ የገባኝ በጉርምስና በር ካለፍኩ ነዉ፡፡ ምንም እንኳን ህይወቱን
በጥልቅ ዕዉቀትና ፍልስፍና የሚመራ ወጣት የለም ባይባልም፤ ወጣት ስትሆን ከእርጋታና ከአርቆ አሳቢነት ይልቅ ሞቅታ ይሞላሀል፡፡
ከነገ ዕጣ ፈንታ ይልቅ የዛሬ ጎርፍ ይገፋሀል፡፡ ባይሆንማ ኖሮ፤ ምንም
አያትና ቅድመ አያቶቻችን ያለፉትን የፈተና ዘመን ለማየት ባንችል እንኳን፤ አሻራውን በአባቶቻችን ባየነዉ ነበር፡፡ የአባቶቻችንን
የክፉ ቀን ዓርማ ለማየት ቢሳነን እንኳን በባህር ላይ ጉዞ ወቅት
እንደዋዛ ሰምጠው በወጀቡ ተተፍተው በባህር ዳርቻ የወደቁ የሶሪያ ህፃናትን ብቻ ማስታወስ በቂ ነበር፡፡ በሆስፒታል ያለጊዜያቸው
ተወልደው በሙቀት ክፍል ውስጥ የገቡ እንቦቃቅላ ህፃናት ዕድል ስለምን እንደራቀቻቸው እና ሳይተነፍሱ
እንደሞቱ በተገነዘብን ነበር፡፡
የሰላምን
ትርጉም ለማወቅ በስቃይ የሚዳክሩ፤ የሞት ጽዋ የሚጎነጩ ብዙኃንን ማየት ይኖርብን ይሆን? የሰቆቃ ድምጽና የስጋት ህይወት መምራትስ?
ስለምን ሰላማችንን አሳልፈን እንሰጣለን? ስለምን ክብራችንን እንሸጣለን? ስለምን በሴረኞች ገመድ ተተብትበን እንወድቃለን? ስለምን
ከአንድነትና ከፍቅር ይልቅ ወደ ጥርጣሬና ጥላቻ ጎራ እናመራለን? ስለምን በዓላማ የለሽና መሪ አልባ ሰልፍ ዘምመን እንወድቃለን?
ለመሆኑ ከስሜት ለበስ ግንፈላ ማን አትርፎ ይሆን? ሊቢያ? ሶሪያ?
የመን? ኧረ ማን አተረፈ? ዛሬ ለሊቢያውያን አምባገነኑ ጋዳፊ፤ ለሶሪያውያንም መሪያቸው ከነችግሩ፤ ለየመናውያንም ፕሬዚዳንታቸው
ከነ ህፀፁ፤ ቢዘልቅላቸው በስንት ጣዕሙ በተሻላቸዉ ነበር፡፡ ግን፤ የእነዚህ አገራት ሕዝቦች ትናንት ዓይናችሁ ላፈር ሲሏቸዉ የነበሩ
መሪዎቹንም ሆነ ትናንት የሚያውቋትን አገራቸዉን፤ ብሎም በህይወት የተለዩ ልጆቻቸዉን፤ አባቶቻቸውን፤ እናቶቻቸውን፤
ወንድሞቻቸውን፤ እህቶቻቸውን፤ ዘመዶቻቸዉን እና ወገኖቻቸውን ሊያገኟቸው አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ማፍረስ እንደመገንባት፤
ሰላምን ማስፈን እንደ ነዉጥ መፍጠር ቀላል አይደለምና ነዉ፡፡
እርግጥ
በገዢዉ ፓርቲም ሆነ በመንግሥት የሚስተዋሉ ችግሮች ይኖሩ ይሆናል። መንግሥትም ሆነ ገዥው ፓርቲ ችግሩን ለመቅረፍ ከዝግጁነት እስከ
መዝመት የደረሰና በርካታ ችግሮች የፈታ ቢሆንም አሁንም ያልተፈቱ ችግሮች ይኖሩ ይሆናል፡፡ ይኖራሉም። ይሁንና ችግሮቹን ለመቅረፍ
የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ መንገዶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው፤ ችግር እንደፈጠረ የሚታሰበው እና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰገው የኪራይ
ሰብሳቢነት የፖለቲካል ኢኮኖሚ እንዲያከስም መንግሥትን መገፋፋት፤ መደገፍና በአብሮነት መቆም ነው፡፡ ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ፤ በሕዝብ
ድምፅ ስልጣን የተቆናጠጠው መንግሥት ችግሩን መፍታት ከተሳነው ጊዜው ሲጠናቀቅ ሕዝብ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለሚፈልገዉ ወገን ድምጹን
መስጠት የሚችልበት በሕገ መንግስቱ የተረጋገጠ መብት አለ፡፡
ሊዮናርድ
ሩቢኖ የተባለ ሰዉ << Show me a person who doesn’t make mistakes
and I’ll show you a person who doesn’t do anything >> ብሎ ነበር፡፡ ሥራ ካለ ስህተትም
ይኖራል፡፡ ተኝቶ መዋልና ማደር ካለ፤ ተንቀሳቃሽ እንደማይኖር ሁሉ ተመልካችና ወቃሽም አይኖርም፡፡ ዛሬ በአገራችን የተፈጠረው የጠያቂነትና
የተጠያቂነት ትንቅንቅ ዕድገት የወለደው ነው፡፡ የስህተቶቹ ምጣኔና ሚዛን ምንም ያህል ይቅለሉም ይክበዱ መነሻቸዉ ከድህነት ጋር በተደረገው
ትንቅንቅ፤ በተገኘው ዕድገት የተፈጠረ ቀዳዳ ነው፡፡ ታዲያ ይህንን ዕውነታ
ካመንን ዘንዳ፤ በለውጥ ማዕበል ያጥለቀለቀ ፓርቲና መንግሥት የኪራይ ሰብሳቢነትን የፖለቲካ ኢኮኖሚ ስረወ መሰረት ገንድሶ
እንደሚጥል የሚጠራጠር ማን ይሆን? ውሃ የተሞላበትን በርሜል እያንከባለለ
ከፍታውን የወጣ ፓርቲና መንግሥት፤ ባዶውን በርሜል ወደታች ማንከባለል ይሳነዋል ብሎ የሚጠራጠር ማን ይሆን? ለለውጥ መቆምና ማገዝ ድንቅ ነው፤ ለነውጥ መቆም ግን ረመጥ ይሆናል፡፡ ወገን
የማታውቀውና እየተመለከትከው ያለኸው መንገድ የት ይሆን የሚያደርስህ?
አባቶች ‹‹ ማሰላሰል ደግ ነዉ ›› ይሉ ነበር፤ አዎ ማሰላሰል ደግ ነዉ፡፡ አሰላስሎ የሚጓዝ ረጅም ርቀት ይጓዛል፡፡
No comments:
Post a Comment