ዛሬ በየትኛውም የዓለም ማዕዘን ቢቻል በአየር ብንበርር፤ በየብስ ብንጓዝ፤ አሊያም በባህር
ብናቋርጥ ሁሉም በየራሱ ቋንቋ የሚዘምርላት፤ የሚፈልጋትና የሚመኛት
በአማርኛችን ባለሦስት ፊደሏ ቃል፤ ነገር ግን ትርጉሟ እና አስፈላጊነቷን እልፍ ቃላት የማይገልጿት ‘’ሰላም’’ እጅጉን ውድ ሆና ሳለ በአንዳንዶች ዘንድ ተራ የዕቃ
ዕቃ ጨዋታ የመሰለችበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ከጎሮቤት አገሮች ጀምሮ እስከ ሩቅ ምስራቅ፤ መካከለኛው ገቢ ካላቸው እስከበለፀጉት
አገራት ድረስ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ሰላማቸው እየደፈረሰ፤ ህፃናት በጅምላ ጨራሾች እና በአሸባሪዎች ህይወታቸው ሲቀጠፍ፤ ከሞቀ
ቀያቸው እና ተረጋግተው ከሚማሩበት ትምህርት ቤታቸው ተፈናቅለው ሲሰደዱ ማየትና መስማት የማንንም ሰብዐዊ ፍጡር ስሜት የሚነካና
ሕሊና ተሚቆጠቁጥ ተግባር ነው። ይህ የዓለማችን የዕለት ተዕለት ክስተት የሁሉም ሚዲያ ዘገባ አስኳል መሆን ከጀመረ ውሎ አድሯል።
አሁን አሁንማ ከድግግሞሹና ከሰርክ ተፈጻሚነቱ የተነሳ ለሰው ልጆች ሞትና እልቂት መጨነቃችን ቀርቶ የልብ ወለድ ተውኔት ያህል ትኩረት
ሳንሰጠው እየቀረን የአንድ ወቅት የዜና ፍጆታ ብቻ እየሆነ የሚያልፍበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በተለይ በሶሪያ፤ በኢራቅ፤ በሊቢያ፤
በየመን፤ በአፍጋኒስታን… ወዘተ. ያለው የሰው ልጅ እልቂትና እሮሮ ማለቂያ ያጣ ሆኗል።
አገራችን ኢትዮጵያ ከአስራ ሰባት አመት እርስ በርስ እልቂት ተላቅቃ በ1983 ዓ.ም. የሰላም
አየር መተንፈስ ከጀመረች ወዲህ በሁሉም ዘርፍ እመርታዊ ለውጥ እያሳየች መምጣቷ እሙን ነው። ከከፋ ድህነትና ከኋላቀርነት ለመላቀቅ
በምታደርገው እልህ አስጨራሽ ጦርነት ከ50 ሚሊዮን ኩንታል የማይበልጥ የነበረው የምግብ ሰብል ምርት ዛሬ ላይ ከ294 ሚሊዮን ኩንታል
በላይ ደርሷል። ይህም ቢያንስ በነፍሰ ወከፍ ወደ3 ኩንታል የሚጠጋ ድርሻ እንዲኖረን አድርጓል። እናም፤ ከድህነት ወለል በታች ይኖር
የነበረው ሕዝብ መጠን ከ47 ከመቶ ወደ 22 በመቶ ዝቅ ማለት ችሏል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በራሳችን አቅም
መገንባታችንና በውጤቱም ተጠቃሚ መሆን መጀመራችን በአገሪቱ ለሰፈነው ሰላም ጉልህ አስተዋዕኦ ማስረጃዎች ናቸው። በዚህ እየተገባደደ ባለው ዓመት እንኳን በሃምሳ ዓመት ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የገጠመንን
የድርቅ አደጋ በራሳችን የውስጥ አቅም ለመከላከል የቻልነው፤ ሕዝቡ ሰላሙ ተጠብቆ ፊቱን ወደ ልማት በማዞሩና መንግሥትም በዚህ ምቹ
ሁኔታ በመጠቀም አቅሙን በማስተባበር ልማትን የሞት ሽረት ጉዳይ አድርጎ የመሪነቱን ሚና በመጫወቱ ጭምር ነው፡፡
አሁን በተለያዩ የአገራችን ክልሎች በተለይም፤ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በመልካም አስተዳደር እጦት ሰበብና በማንነት
ጥያቄ ምክንያት እየተፈፀመ ያለው ሁከትና ሥርዓት ለመናድ የሚደረግ ብጥብጥ ከላይ ያነሳነውን ሰላም ዋጋ የሚያሳጣ ሲሆን፤ በእጃችን
ያለውነ አጥፍቶ እድገታችንን ወደኋላ የሚጎትት ድርጊት ነው። ሁከቱና ብጥብጡ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ
እጅግ አሳዛኝ ጉዳይ ነው፡፡ እንግዲህ የሰላም ዋጋ ምን ያህል ውድ እንደሆ በዚህ ጊዜ ውስጥ በጠፋው ውድ የሰው ልጅ ህይወትና
በወደመው ንብረት መረዳት ይቻላል፡፡ በአገራችን የሕግ ሁሉ የበላይ በሆነው ሕገ መንግሥት ውስጥ እንደተደነገገው ማንኛውም ዜጋ ወይም
የተደራጀ አካል ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሀሳቡን የመግለፅ፤ የመደራጀትና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት አለው። ይህንን ሲያደርግም
መንግሥት ጥበቃ ያደርግለታል። ነገር ግን ለዚህች አገር ልማትና እድገት አንዳች አስተዋፅኦ ባላበረከቱና ኑሮአቸውን በአውሮፓና በሌሎች
የምዕራብ አገሮች ያደረጉ፤ የመንግሥትን ጥቃቅን የአፈፃፀም ክፍተቶች በመለቃቀምና በማጉላት፤ እንዲሁም በኪራይ ሰብሳቢነት መንገድ
በአቋራጭ ወደ ስልጣን ለመውጣት ከሚፈልጉ የውስጥ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ጋር በመተባበር በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ሕገ-ወጥ ሰልፍ
በመጥራት ተጠምደዋል። በዚህም ስራ ፈላጊውን ወጣት አንዳች ላይፈይዱለት፤ ስሜቱን በመኮርኮር ብቻ አጉል ተስፋ በመስጠት ግርግር
እንዲፈጥር እያነሳሱት ነው። በዚህም በሁከቱና በብጥብጡ ሰላማዊ ዜጎች ይጎዳሉ፤ በአንጣራዊነት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን በጥቂት ቦታዎች
ውጥረት መስፈኑ አልቀረም። ታዲያ፤ በኢትዮጵያ ሰላም የለም ለማስባል በእነዚህ ኃይሎች እየተደረገ ያለውን አደገኛ የአገር ማፍረስ
ዘመቻ ሕዝቡ በንቃት ሊከታተለውና ሊቀለብሰው ይገባል፤ ሁላችንም ሰላማችንን ለማስከበርና አንድነታችንን ለማጠናከር ተግተን መስራት
ይጠበቅብናል፡፡
የሰላም ዋጋ ተመን የለውም !!! ቸር ይግጠመን
No comments:
Post a Comment