Friday, 19 August 2016

አይበጀንም !!




                                                          ይነበብ ይግለጡ             
                                                                
በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ውስጥ እየታየ ያለው የእለት ተእለት ተለዋዋጭ ሁኔታዎች በእጅጉ ያሳስባሉ፡፡ ትናንትም ሆነ ዛሬ ሀገራችን ባስመዘገበችው ፈጣን ሀገራዊ ልማትና ዕድገት ምስክርነታቸውን ሲሰጡ የቆዩና እየሰጡም ያሉት ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት ሳይቀሩ እየታየ ያለው ችግር በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ አይበጀንም፣ አይጠቅመንም ልንታገለው ይገባል፡፡ ሀገራችንን ከውድቀትና ከጥፋት መታደግ አለብን፡፡
ይህንን ጉዳይ አደባብሰን ወይንም አለባብሰን እንለፈው ቢባል እንደሀገር የሚያስከፍለን ዋጋ ከሚታሰበውም ከሚገመተውም በላይ ነው፡፡ ለመንግሥትም ለህዝብም የሚበጀው የችግሩን መሰረታዊ መነሻ ፈትሾና መርምሮ መፍትሄ ላይ መድረስ ነው፡፡ የሕዝብን ጥያቄ በማዳመጥ መሰረታዊ ምላሽ መስጠት ነው፡፡ ተገቢም የሚሆነው ይኸው ነው፡፡
የሀገሪቱ ሰላምና ደህንነት ተጠብቆ የተጀመረው ልማትና ዕድገት ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል የሁሉም ዜጋ ፍላጎት ነው፡፡ የኢትዮጵያን ውድቀትና መጥፋት ሌት ተቀን ለሚመኙ ሀይሎች ምኞታቸውም ሆነ ህልማቸው መቼም እንደማይሳካ በተግባር ማሳየት መቻል ያለበት ህዝቡ ነው፡፡
የጉዳዩን ጥልቀትና አሳሳቢነት ቀጥለን የምንፈትሸው ቢሆንም ሀገርን ከጥፋትና ከውድቀት የመታደጉ ኃላፊነት በዋነኛነት የህዝብን፣ የመንግሥትን፣ የእውነተኛ ሀገር ወዳድ ዜጎችንም ታላቅ ርብርብ የሚጠይቅ ጊዜና ፋታም የማይሰጠው አጣዳፊና አስቸኳይ ተግባር መሆኑ ሊሰመርበትም ይገባል፡፡
ኢህአዴግ በሚመራው መንግሥት ውስጥ መሠረታዊ የሆኑ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህ፣ የኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና ዐቢይ ችግሮች ሥር ሰደው መንሰራፋታቸውን ይህም ለሥርዓቱ አሳሳቢ አደጋ መሆኑን አምና ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ኢህአዴግ በ10ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ የሁሉም አባል ድርጅቶች አመራሮችና ተዋካዮች የኅብረተሰቡና የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች በታዛቢነት በተገኙበት ጉዳዩን በሰፊው ተወያይቶ መርምሮታል፡፡ ግልጽ  ውይይት ነበር፡፡
በኅብረተሰቡ ውስጥ ገኖ የሰፈነውን የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህ፣ የኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና ችግር ማስወገድ ለድርጅቱ የሞት የሽረት ትግል መሆኑን ሁሉም ድርጅቶች ተማምነውበት የጋራ አቋምም ተወስዶበት ወደተግባር የተገባበት ሁኔታ እንደነበረ ይታወቃል፡፡
በሚገርም ሁኔታ ይኸው በመቀሌ የተካሄደው አሥረኛ ድርጅታዊ ጉባዔ የዛሬ ዓመት ላይ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተከሰቱት ሁኔታዎች አስቀድሞ ሊከሰቱ እንደሚችሉ ከተጨባጩ እውነት በመነሳት መገመትም መተንበይም ችሎ ነበር፡፡ ትንቢት  ይቀድም ለነገር  እንዲሉ፡፡
ኢህአዴግ በዚህ ደረጃ የችግሩን ግዝፈት ተቀብሎ በግልጽ መድረክ አውጥቶ መወያየቱና ርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱ ራሱን ችሎ የሚደነቅ ተግባር ነው፡፡ የተወሰነ ርቀት ያህልም በአደባባይ ከህዝብ ጋር በከፈተው ሰፊ የመወያያ መድረክ የህዝቡን ብሶትና ምሬት መከፋቱን የደረሰበትን በደል በመናገሩ መፍትሄ ለመስጠት ተንቀሳቅሷል፡፡
በእርግጥም ይህ ሥር የሰደደ ችግር ህዝቡን ያስመረረና ያስከፋ ቢሆንም በአንድ ጀምበር ሁሉም መፍትሄ ያገኛል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ጅምሩ ወደ ኋላ ላይ እየተቀዛቀዘ መሄዱ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት አለመቻሉ የድርጅቱን ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡ በአድርባዮች፣ በኪራይ ሰብሳቢዎች ጫናና ተጽዕኖ ሥር ወድቋል፤ መንቀሳቀስ አልቻለም የሚለው የህዝብ አስተያየት ገኖ ይሰማም ነበር፡፡
ኪራይ ሰብሳቢው ኃይል መንግሥታዊና የፓርቲውን መዋቅር በሽፋንና በከለላነት በመጠቀም ጉያው ውስጥ ተሸጉጦ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ነገ በአደባባይ የህግ ተጠያቂ ከመሆኔ በፊት ሰፊ የገንዘብ አቅም ስላለኝ ነውጥና ሁከት መፍጠር አለብኝ በሚል ሰፊ እንቅስቃሴ ያሰበውን ለማድረግ የቻለበት ሁኔታም ታይቷል፡፡ ተሸፋፍኖ እንዲቀር ለማድረግ ማን ማንን ይነካል በሚል አንካሳ አስተያየት ሥር ሲዋኝ ቆይቷል፡፡
በመንግሥታዊ መዋቅሩም ሆነ በፖለቲካ ድርጅቶቹ ውስጥ አቅምና ጡንቻ ያለው ማን ይነካኛል የሚል አጀንዳው እንዲነሳ የማይፈልግ ተድበስብሶ እንዲቀር ጭርሱንም ኢህአዴግ የተለያየ ውጥረት ውስጥ እንዲገባ ግብ ቀርጾ የሚንቀሳቀስ ኃይል እንዳለ ህዝቡ ሳይውል ሳያድር ተረድቶታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአደባባይ በሙሰኞችና በኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ ርምጃ እንደሚወሰድ ለህዝቡ ቢናገሩም ህዝቡም በተስፋ ለውጥና ውጤት ይመጣል ብሎ ቢጠብቅም የተፈለገውን ያህል ለውጥ ሳይመጣ ቀርቷል፡፡ በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ላይ የተወሰዱ ወይም እየተወሰዱ ናቸው የተባሉት ርምጃዎች ታች ባለው ሠራተኛ ላይ ብቻ ያተኮሩ ሆነው በገፍ የማሰር ሁኔታዎች ታይተዋል፡፡ ማስረጃ አልተገኘም በሚል የተለቀቁም አሉ፡፡
እነዚህ የታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል አባላት ሲሆኑ ከኑሯቸውም ከገቢያቸውም ማነስ አንጻር ለትናንሽ ገንዘቦች ሊሸነፉ ይችላሉ፡፡ ሠራተኞች የበላይ አለቆቻቸው ሳያውቁት ወይም የጥቅም ተጋሪ ሳይሆኑ ወይም አይዞህ ባይና የሚያቀብሉት የጥቅም ተካፋይ ሳይኖር ወደ ሙስናና ጎራ ውስጥ ይገባሉ ብሎ ማሰብ ጅልነት ነው የሚሆነው፡፡
ከባዶ ሜዳ ተነስተው ሚሊዮነር አስመጪና ላኪ ለመሆን የበቁት የኦሮሚያንና የአዲስ አበባን መሬት በህገ ወጥነት ተቀራምተው የቸበቸቡት ከአቀባባይ ደላላው ጋር በመሆን ከመንግሥት ቤት ጀምሮ ካርታ እያስለወጡና በግለሰብ ስም እያዞሩ የሸጡት፤ የግለሰቦችን የግል ቤትና የቆየ ይዞታ ሳይቀር በማምከን ለልማት ይፈለጋል ተነሺ ነው በሚል በመንግሥት ስም በመነገድ ከጀርባ ከሀብታሞች ጋር እየተደራደሩ ትንሽ ካሳ በመወርወርና በማስነሳት እነሱ ደግሞ በሚሊዮኖች የዛቁበት ድራማ ነው በሀገርና በህዝብ ላይ የተካሄደው፡፡ ቢመረር ቢከፋ እሪ ቢል ምን ይገርማል?
በኮንዶሚኒየም ቤት ግንባታና ክፍፍል ሽያጭ ህዝቡን ደም እንባ ያስለቀሱት በመንግሥትና በህዝብ ሀብት ላይ ወደር የሌለው ዘረፋና ምዝበራ በማድረግ ጠያቂ ሳይኖራቸው በአንዴ ወደ ኢንቨስተርነት፣ የኮሌጅ ባለቤትነት፣ የእርሻ ባለቤትነት፣ አስመጪና ላኪነት የተቀየሩት እልፍ አዕላፍ ናቸው፡፡ ብዙ ተባዙ የተባሉ ይመስል፡፡
ድሀውን ዜጋና ለፍቶ አዳሪውን ገበሬ በመንግሥት ስም እያፈናቀሉ ትንሽ ካሳ እየሰጡ በማስነሳት ወይም ደልለውት በትንሽ ብር በመግዛት እነሱ ደግሞ በብዙ ሚሊዮን የሸጡት የለወጡት በኔት ወርክ ከባለሥልጣናት እስከ ታችኛው ድረስ በመረብ የተሳሰሩ ህዝብና መንግሥትን የዘረፉ ጉዶች ዛሬም እንዳሻቸው እየፈነጩ እያገሱ ይገኛሉ፡፡
በአዲስ አበባ ሁለት ሦስት ቤት በክልል ከተሞች እንዲሁ ምርጥ ፎቅና ቪላ ንግድ ቤቶች ባለቤቶች የሆኑ ከየት አመጣኸው፣ በምንስ ገቢህ ሰራኸው ተብለው የማይጠየቁ በመንግሥትና ህዝብ ሀብት ዘረፋ የከበሩ የደለቡ ማን ይነካናል ባዮች ህዝቡም ለይቶ የሚያውቃቸው በስምም እከሌ ብሎ ሊጠራቸው የሚቻለው ስንትና ስንቶች ከተራ ዜጋ እስከ ሹማምንት ባሉበት ሀገር የሙስናና ፀረ ኪራይ ሰብሳቢ ትግሉን እልፍ አድርገናል ቢባል ሰሚም አድማጭም የለም፡፡ የሀገሪቷን ሠላም መረጋጋት እየናጠው የሚገኘውም ይኸው ኃይል ከጀርባ ሆኖ ነው፡፡
ኢህአዴግ ትግሉን በእርግጠኝነት የጀመረው መሆኑን ህዝቡ ቢረዳም ወሳኝ ለውጦችን ግን ማሳየት አልቻለም፡፡ ሥር ነቀል ርምጃዎችን ለመውሰድ ያላስቻለው በውስጡ የተሰገሰገው በአባልነትና በኃላፊነት የተለያየ ደረጃ ያለው ተመንጥሮ መውጣት ያለበት ኪራይ ሰብሳቢ ሙሰኛና አድርባይ ኃይል ድርጅቱን ተብትቦ ይዞታል የሚለው የህዝብ አስተያየትም በሰፊው ይደመጣል፡፡
የውስጥ መተጋገል እናደርጋለን ሲሉ ከፍተኛ ሹሞች በአደባባይ ቢናገሩም ከቃላትና ከወሬ ያለፈ ሊሆን አልቻለም፡፡ ያሳዩት ለውጥ የለም፡፡ የውኃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል፡፡ ህዝቡ ይህንን ሁኔታ አይቶና ታዝቦ ሲ,ያበቃ ማን ማንን ይነካል የሚል ስላቅ እያሰማ ይገኛል፡፡ በራሱ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ያለው ብክነትና ምዝበራ ዝርክርክነት በማይታወቅና ማስረጃ በሌለው መልኩ የሚባክነው በሚሊዮኖች የሚቆጠር የሀገር ሀብት ከቀድሞ በባሰ መልኩ መቀጠሉን ዘንድሮ የጠቅላይ ኦዲተር ጄኔራል ኃላፊው ለፓርላማው ያቀረቡት ሪፖርት ይገልጻል፡፡
በየመሥሪያ ቤቱ ያለው የዘመድ አዝማድና የጎጥ ስብስብም በአሳፋሪ ሁኔታ ለሌላው ዜጋ ሰርቶ ለመኖርም ሆነ ለማደግ ትልቅ ማነቆ እንደሆነበትም ይታወቃል፡፡ ከገጠር አስከ ከተማ ዓይኑን አፍጥጦና ጥርሱን አግጥጦ ያለምንም ይሉኝታ የተንሰራፋው ሙስና ኪራይ ሰብሳቢነት የፍትህና የመልካም አስተዳደር ችግር በአንድ ሰሞን ስብሰባና ውይይት ብቻ የማይፈታ እንደሆነ ቢታወቅም ጭርሱንም በአሁኑ ጊዜ አጀንዳው በተለያዩ ግርግሮችና ሁከቶች እንዳይነሳ ተደርጎ በባሰ መልኩ በትርምስና ብጥብጥ ተጠቃሚ መሆን እንችላለን በሚሉ ኃይሎች ችግሩ በከፋ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡
መፍትሄ ስለማምጣት መነጋገር ሲያስፈልግ ችግሩን ነቅሶ ማሳየቱ ተገቢ ስለሆነም ነው ነጥቦቹ የተነሱት፡፡ ትልቁ ጎልቶ የታየው ችግር ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት አንሶ መታየቱ ነው፡፡ ስለዚህም ዛሬ ከተፈጠሩት ሀገራዊ አሳሳቢ ችግሮች ዙሪያም የኪራይ ሰብሳቢው ጥገኛ ኃይል ከሌሎች ጋር በመደመር የራሱ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ይታወቃል፡፡
ሠላም ካለ ተጠያቂ እሆናለሁ ብሎ ስለሚያስብ ሁከትና ትርምስ አለመረጋጋት እንዲኖር እንዲቀጥል የሁልጊዜም ምኞቱና መደበኛ ሥራው መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ይህን በተመለከተ ኢህአዴግ ከጉባዔው በኋላ የነበረውን ወርቃማ እድልና አጋጣሚ በአግባቡ አልተጠቀመበትም፡፡ በራሱ ውስጥ ከፍተኛ የማጥራት ርምጃዎችን አልወሰደም፡፡ የህዝቡንም ወሣኝ ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ አላስተናገደም፡፡ ከህዝቡ ለማዳመጥ ቢችልም ሥር ነቀል እርምት አላደረገም፡፡ ይኼም ሰፊ የቅሬታ መነሾ ሆኗል፡፡
ይህንን አጋጣሚ ደግሞ ኢህአዴግ ቢነገረውም ራሱን ለመለወጥና ለማሻሻል የሚፈልግ ድርጅት አይደለም፡፡ ከህዝቡ ይልቅ የራሱን የፖለቲካ ጥቅም ብቻ እያየ ውሣኔዎቹን ተግባራዊ ለማድረግ የሚንቀሳቀስ ቡድኖችንና ግለሰቦችን ተጠቃሚ በማድረግ የሚሰራና የሚያሰራ ድርጅት ነው፡፡ አባል ያልሆነ ሰው በሀገሩ እንደዜጋ ተጠቃሚ አይደለም። የሥራ እድል የለውም ወዘተ…በሚል አፍራሽ ቅስቀሳዎች በብዛት በማሰራጨት ተጠቅመውበታል፡፡
አድሏዊነት፣ መድልዎ፣ ጎጠኝነት፣ ሙስና፣ የፍትህና መልካም አስተዳደር ችግሮች የህዝብና የመንግሥት ሀብት ዘረፋ የሥርዓቱ መገለጫ እስከመሆን ደረጃ አድጓል የሚሉ ሰፊ ቅሬታዎችም ከህዝቡ ይደመጣሉ፡፡ ይህም ራሱ ኪራይ ሰብሳቢውና ሙሰኛው ኃይል በውስጥ ሆኖ ሥርዓቱን ለመታገል ሲል በሰፊው የሚነዛው አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ አንዱ አካል መሆኑ ነው፡፡
ለዚህ ነው ኪራይ ሰብሳቢው ኃይል ፈጣን ርምጃ ሊወሰድበት ካልቻለ ለሥርዓቱ ዐቢይ አደጋ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገለጽ የነበረው፡፡ አሁንም ሙሉ በሙሉ የጨለመ ባይሆንም ባለው ቀዳዳ ኢህአዴግ ይህንን በውስጡ ነግሶ አላንቀሳቅስ ያለውን በቡድንና በማፍያ ድር ተሳስሮ ትርጉም ያለው ሀገራዊ ለውጥ እንዳይመጣ ተብትቦ የያዘውን ኃይል ማራገፍ ካልቻለ የአደጋው ግዝፈት በገሀድ እየታየ መሆኑን ሊረዳው ይገባል፡፡
የሚነሱትን የህዝብ ጥያቄዎች በአግባቡ ማጤንና ማዳመጥ ሠላማዊ እልባትና መፍትሄ መስጠት የሀገሪቱ ሠላምና ደህንነት በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል ትርምሱ ሁከቱና ረብሻው እንዲበርድ፣ ሁኔታዎች ወደቀድሞ ሠላማዊ ሁኔታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ዐቢይ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ኢህአዴግ ለሚፈጠሩት ችግሮች ሁሉ ከአንዱ ወይንም ከሌላው ጋር በማያያዝ ባለቤት ከመስጠት ይልቅ በራሱ ውስጥ ያለውንም ችግር አጣርቶ ቢመለከት ለምን ችግሮቹ ሊፈጠሩ ቻሉ፣ መሠረታዊ ምክንያታቸው ምንድነው፣ መፍትሄውስ ላይ የሚደረሰው እንዴት ነው በሚል ጉዳዩን ከውስጡ ቢፈትሽ፣ ወርዶም ከህዝቡ ጋር በስፋት ቢወያይና ቢመክርበት የህዝቡን ስሜትና ቃል ጠብቆ ቢሄድ እኔ ያልኩት ብቻ እንደ ፈጣሪ ቃል መከበር አለበት የሚል ግትር መስመር ባይከተል ለውጥና ሠላም ማስፈን ይቻላል፡፡
ሁኔታዎችን በማባባስ ሁሉ ነገር ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ እንዲወጣ ሆን ብለው የሚሰሩ ህዝብን ከህዝብ የሚያናቁሩና የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ቀን ከለሊት የሚነዙ በብሄረሰብ ላይ ያነጣጠረ ጥላቻን የሚያራግቡ የማህበራዊ ሚዲያ ድብቅ ሽፍቶች በዚህ ነውረኛ ድርጊታቸው ሀገሪቷ የእርስ በእርስ ጦርነትና የመተላለቅ አውድማ እንድትሆን፣ እንድትጠፋና እንድትወድም ለማድረግ በሰይጣን መንፈስ ተጭነው ከሚነዙት መርዝ ከሚረጩት ቤንዚንና እሣት የማርከፍከፍ አስነዋሪ ድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል፡፡ ይህ አካሄድ ለማንም አይበጅም፡፡ ለሀገርም ለህዝብም አይጠቅምም፡፡
በዚህ አካሄድ ሀገራት ሲወድሙ ህዝብም ሲተላለቅና ሲጠፋፋ እንጂ ሲጠቀም አላየንም፡፡ ለዛሬውም ሆነ ለቀጣዩ ትውልድ ይህ ዓይነቱ አስነዋሪ ድርጊት የሚሰጠው ጥቅምም ሆነ የሚያመጣው ሀገራዊ ፋይዳ የለም፡፡ ዙሪያዋን በታሪካዊ ጠላቶች ተከባ በምትኖረው ኢትዮጵያ ውስጥ ልዩነትን አቻችሎ፣ ተደማምጦና ተከባብሮ ከመኖር ውጪ እርስ በእርሳችን በመባላትና በመጠፋፋት የምንከፍተው ቀዳዳ ወድቀቷን ለሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች ሰፊ በር የመክፈት ያህል መሆኑን መረዳትም ይገባል፡፡
የሰለጠነ በአስተዋይነት የተሞላ፣ ሀገርን ለውድቀት የማይዳርግ፣ ሉዓላዊነታችንን አሳልፎ የማይሰጥ፣ የበሰለና የሰከነ አካሄድን መከተል ብቸኛው አማራጭ ነው፡፡ ከብዙ ሀገራት  ጥፋትና ውድቀትም በተለይም ከሶሪያ ልንማር ይገባል፡፡ በእልህና በማነህ ማነህ ሁሉም ተያይዘው ጠፉ፡፡ ሀገራቸውን እንዳትነሳ አድርገው አወደሟት፤ ህዝቦቿም በእርስ በእርስ ጦርነት አለቁ፡፡ ኢኮኖሚያቸውም ወደመ፡፡
ባዶ አውድማ ብቻ ሲቀር ሁሉም ሀገራቸውን ለቀው ተሰደዱ፡፡ ቤት አልባ ኑሮ አልባ ሀገር አልባ ሆኑ፡፡ በስንትና ስንት ሺህ ዘመንና በትውልድ ቅብብሎሽ እየተገነባች የኖረችውን ሀገራቸውን በፖለቲካ ልዩነትና የተካረረ አለመግባባት እንዲሁም በጭፍን የፖለቲካ ጥላቻ በመሞላት እርስ በእርስ በመተላለቅ ጠፍተው አጠፏት፡፡ ዛሬ ቢፀፀቱ ቢያለቅሱ እሪ ቢሉ ሠላማቸውንም፣ ሀገራቸውንም፣ ታሪካቸውንም አጥተው በውጭው ዓለም በስደትና በመከራ ይኖራሉ፡፡ እብድና አክራሪ ፖለቲከኞች በስተመጨረሻው ራሳቸውም ጠፍተው ትውልድንም ሀገርንም ይዘው ይጠፋሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ይህ እንዲከሰት የሚፈቅድ ዜጋ የለም፡፡ አይበጀንም፡፡ ይህን አጥፊ ድርጊት አጥብቀን ልንታገለው  ይገባል፡፡ ግዴታም ነው፡፡

No comments:

Post a Comment