Friday, 19 August 2016

የዛሬ የሰንደቅ ዓላማ ንቀት ለነገ አደጋ አለው!



ብ.ነጋሽ
በአንድ ሰው አምባገነንነት ከሚተዳዳረው የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያን የማተራመስ ውክልና ወስደው የሚንቀሳቀሱ የኢሳያስ ምንደኞችና በኢትዮጵያ ተቃዋሚነት ሽፋን የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚዎች በማህበራዊ ሚዲያ ያለ የሌለ ኃይላቸውን ተጠቅመው በኢትዮጵያ፤ በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ሁከት ለመቀስቀስ ያጠመዱት ሴራ እየከሸፈ ይመስላል። ከአሁን በኋላ ላይቀሰቀስ አክትሟል ማለት ግን አይደለም። አሁንም በከባዱ እንዳጠላ ነው።
ኢትዮጵያን ዳግም አገር ልትሆን በማትችልበት ሁኔታ በእርስ በርስ ግጭት የማተራመስ ስትራቴጂ ነድፎ የሚመራው የኤርትራ መንግስትና ሌሎች የሩቅ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በምንደኛ ወኪሎቻቻውና ተቃዋሚ ነን በሚሉ ወገኖች፤ እንዲሁም በተወሰነ ደረጃ በአሜሪካ መንግሥት በጀት በሚንቀሳቀሰው የአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ የአማርኛ ፕሮግራም በመታገዝ ያካሄዱት የብሔር ግጭት የመቀስቀስ ዘመቻ እስካሁን ባለው ሁኔታ ግቡን ባይመታም ብዙዎችን ያሳዘነ ቀላል የማይባል ጉዳት ግን አድርሷል። በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች በሰላማዊ ሰልፍ ሽፋን ሕጋዊ እውቅና የሌላቸው በኃይል እርምጃ የታጀቡ የጎዳና ላይ የሁከት ተቃውሞዎች ተካሂደዋል። በተለይ በአማራ ክልል በጎንደር ከተማና በአካባቢው፤ በባህርዳር፤ በኦሮሚያ በምእራብ አርሲ፤ በነቀምትና በሌሎችም አካባቢዎች የተቀሰቀሱት ሁከቶች የኤርትራ መንግሥት፤ የሩቅ የኢትዮጵያ ጠላቶችና ተላላኪዎቻቻውን ግዳይ መጣል አስችሏቸዋል። በኤርትራ መንግሥት ወኪሎች ቅስቀሳ ተወናብደው በሰላማዊ ዜጎችና በሰላም አስከባሪ ኃይል አባለት ላይ የኃይል ጥቃት የሰነዘሩ፤ መሳሪያ ለመንጠቅ የሞከሩ፤ ቦምብ የወረወሩ፤ የኢፌዴሪን ሰንደቅ ዓላማ ለማወረድ የሞከሩ፤ በግለሰቦች፤ በህዝብና በመንግሥት ንብረት ላይ የጥፋት እርምጃ ለመውሰድ የሞከሩ በቅስቀሳው የሰከሩ እምቢተኛ ወጣቶች ህይወት ያለፈበት ሁኔታ አለ። በተባራሪ ጥይት የሞቱና የቆሰሉም አልጠፉም። ከሰላም አስከባሪ ኃይል አባላትም መካከል እንዲሁ የቆሰሉና የሞቱ አሉ።
እርግጥ የሞቱትና የቆሰሉት ሰዎች ቁጥር የኤርትራ መንግሥት ወኪሎችና የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚዎች የሚያወሩትን ያህል አይደለም። እነዚህ አካላት ስኬታቸውን የሚለኩት በሞተውና በቆሰለው ሰው ቁጥር፤ በወደመው ንብረት ልክና ሁኔታው በፈጠረው ፍርሃትና ስጋት መጠን ስለሆነ አጋንነው መናገራቸው የሚጠበቅ ነው። ግዳያቸውን ከፍ ለማድረግ መሞከራቸው የሚገርም አይደለም።
የዘር ጥላቻ በመንዛት የመገዳዳል ጥሪ ሲያስተላልፉ ሰንብተው፤ ሁከቱ ጋብ እንዳለ ካለፈው ሳምንት መግቢያ ጀምረው የእውነት ይሁን የውሸት ያልተረጋጋጠ፤ በምን ሁኔታ እንደሞቱ የማይታወቅ፤ የኢትዮጵያ ይሁን የውጭ አገር የማይታወቅ በጥይት የሞቱ ሰዎችን አስከሬኖች በፎቶ ግራፍና በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ ሲለጥፉ ነበር የሰነበቱት፤ ይህ ሁኔታ ከሁከቱ ጀርባ ያለውን ኃይል ለሚያውቁ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚያንገበግብ ቁጭት ፈጥሯል። በኃይልና በሽብር ኢትዮጵያን ማጥቃት ያልቻሉና በዲፕሎማሲም የተሸነፉ የኢትዮጵያ ልማትና ታላቅነት እንደ ውስጥ እግር እሳት ያነገበገባቸው፤ በተለይ የኢትዮጵያ ህዳሴ ምልክት ተደርጎ የሚወሰደውና ታላቅ አገራዊ መግባባት የተፈጠረበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቁ አይቀሬ መሆኑን የተረዱ . . . የኤርትራ መንግሥትና የሩቅ ታሪካዊ ጠላቶች እርስ በርስ እንድንጠላላና በጥርጣሬ እንድንተያይ፤ አንዳችን በሌላኛችን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እንድንቃጣ በማድረግ ደም እንዲፈስ ማድረጋቸው ነው ቁጭት የሚፈጥረው፤
እነዚህ የኤርትራ መንግሥት ወኪሎችና የትርምስ ጉዳይ አስፈፃሚዎች ባለፈው ሳምንትም ማለትም ነሃሴ 7 እና 8 - 2008 ዓ.ም. ከአንድ ሳምንት በፊት የነበረው ዓይነት በዘረኝነት የሚነዳ መተላላቅን ያጋተ ሁከት ጠርተው ነበር፤ እንደተለመደው በማህበራዊ ሚዲያዎች፤ በተለይ በእያንዳንዱ ወጣት እጅ ባለው ፌስቡክ፤ በምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ በደብረ ማርቆስ የደገሱት ሁከትና እልቂት በከተማዋ ነዋሪዎችና በክልሉ ሰላም አስከባሪ ኃይል ከሽፏል። በዳንግላ ከተማ ጠርተውት የነበረው ሁከትም እንዲሁ ሕዝቡ ጥሪያቸውን አልቀበልም በማለቱ ሳይሞከር ቀርቷል። የኤርትራ ወኪሎች በደቡብ ወሎ ዞን ዋና ከተማ በደሴ ከፍተኛ እልቂት የሚያስከትል ሁከት ይቀሰቀሳል ብለው ጠብቀው የነበረ ቢሆንም በሕዝቡ እምቢተኝነት ሳይሳካ ቀርቷል።
ታዲያ ይህን ያለፈውን ቅዳሜና እሁድ ሁከት የቀሰቀሱ በአሜሪካ የኤርትራ መንግስት ወኪል የሆነው ኤልያስ ክፍሌ የከፈተው mereja.com የተሰኘ ማህበራዊ ሚዲያና ሌሎች መሰሎቹ እነዳለፈው ሳምንት ሁሉ ግዳይ አለቀናቸውም። የፌስቡክ ገጾቻቻው ላይ የሚለጥፉት የአስከሬን ፎቶ ግራፍ አላገኙም። የውሸት እንዳይለጥፉም ለማስመሰል ያህል እንኳን የሚሆን ሁከት አልተቀሰቀሰም። ዝም ግን አላሉም። 
በኦሮሚያ ክልል ሙሉ በሙሉ ተስፋ የቆረጡ ይመስላሉ። በዚህ ሳምንት ስለኦሮሚያ ያወሩት የሚጠቀስ ነገር ባይኖርም በጥላቻ ስሜት ሊቀሰቀስ ይችላል ብለው የገመቱት የአማራ ክልልን ግን አልለቀቁትም። በዚህ ሳምንት የኢፌዴሪን መንግሥት ገፅታ ለማበላሸትና ወደተቃውሞ ሊያመራ የሚችል የሕዝብ ቅሬታ ለመፍጠር ከአማራ ክልል የተገኙ ያሏቸውን ጥቂት ፎቶግራፎች ለጥፈዋል። ብዙም ትኩረት የሚስቡ ግን አልነበሩም።
የኤርትራ መንግሥት ወኪሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች ጥቂቶች ቢሆኑም፤ በተለይ በአማራ ክልል ሁከት የመቀስቀስ ተልእኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን በሕዝቡ የህገ ወጥ ተቃውሞ እምቢተኝነት ተስፋ እንዳይቆርጡ የሚያበረታቱ መልእክቶችም አስተላልፈውላቸዋል። ከእነዚህ መካከል ሕገ መንግሥቱ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት ቢፈቅድም መንግሥት ከልከሏል፤ የሚል መልዕክትና ይህን ያሳያል ያሉትን ዩኒፎርም የለበሱ በኃያዎቹ የሚቆጠሩ የሰላም አስከባሪ ኃይል አባላትን  ምስል፤ የት አካባቢ እንደሆነና የማን እነደሆኑ የማይታወቁ በወታደራዊ ተሽከረካሪ ፎቶግራፎች የታጀቡ  የአማራ ከተሞች ተወርረዋል የሚሉ መልዕክቶች ተጠቃሾች ናቸው።
እዚህ ላይ የአማራ ክልል ሕዝብ አንድ ማስታወስ ያለበት ነገር በሕገመንግሥት የተረጋገጠው ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ወይም በአደባባይ አቤቱታውን የማሰማት መብት ያልተከለከለ መሆኑን ነው። ሕገ መንግሥቱ ሰላማዊ ሰልፍን በተመለከተ በአንቀጽ 30 “የመሰብሰብ፤ ሰላማዊ ሰልፍ የማደረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት” በሚል ርዕስ ስር፤
·         ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሳሪያ ሳይዝ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው። ከቤት ውጭ የሚደረጉ ስብሰባዎችና ሰልፎች በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች በሕዝብ እንቅስቃሴ ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ ለማድረግ ወይም በመካሄድ ላይ ያለ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ሰላምን፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችንና የህዝብን የሞራል ሁኔታ እንዳይጥሱ ለማስጠበቅ አግባብ ያላቸው ሥርዓቶች ሊደነገጉ ይችላሉ።
·         ይህ መብት የወጣቶችን ደህንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስምን ለማስጠበቅ፣ የጦርነት ቅስቀሳዎች እንዲሁም ሰብአዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎችን ለመከላከል ሲባል በሚወጡ ሕጎች መሰረት ተጠያቂ ከመሆን አያድንም።
የሚል ድንጋጌ ሰፍሯል።
እናም ሰላማዊ ሰልፍ የሚደረገው በዚህ ሕገ መንግሥት ላይ በሰፈረው መሰረትና ሕገ መንግሥቱ በሚያዝዘው መሠረት በወጡ ማስፈፀሚያ ሕጎችና ደንቦች መሠረት ብቻ ነው። የተከለከለው በጎንደርና ባህርዳር እንደተደረገው (በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ቦታዎች ይሄው ተደርጓል) ሕገ መንግሥቱ ከሚያዝዘው ውጭ የጦር መሳሪያ በመያዝ፤ የኃይል ጥቃት በመሰንዘር፤ የግለሰቦችን ክብር የሚነኩ መልዕክቶችን በመያዝ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አብሮነትና እኩልነት የሚወክለውን ሰንደቅ ዓላማ የሚፃረር፤ የማይወክላቸውን ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለብና መሰል ብሔርን ከብሔር የሚያቃቅርና በጥርጣሬ እንዲተያዩ የሚያደረጉ ብሎም ለግጭት በር የሚከፍቱ በሁከት የታጀቡ ሰልፎች ናቸው። የዚህ ዓይነት ሰልፎችን መከልከል ደግሞ ተገቢ ነው። እናም በአገሩ ላይ እንኳን ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄድ በጨዋታ መካከል በመንግሥት ላይ ቅሬታ ማቅረብ አይቀጡ ቅጣት በሚያስከትልበት የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያን እንዲያተራምስ ውክልና የተሰጠው ኤልያስ ክፍሌ የሚመራው mereja.com ለአማራ ሕዝብ ተቆርቋሪ ሆኖ ሕገ መንግሥታዊ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቱን ተነፍጓል፤ የሚል መልዕክት ማስተላላፉ አስገራሚ ነው።
የኤርትራው ወኪል ኤልያስ ክፍሌ የሚመራው mereja.com የተሰኘው ድረገፅ የፌስቡክ ገፁ ካስተላለፋቸው መካከል ብዙዎችን ያስገረመው፤ ነገር ግን ጥቂት ፈገግ ያሰኘው መንግሥት የአዲስ አበባ ወጣቶችን በመፍራት በነፍስ ወከፍ የ10 ሺህ ብር ብድር ሊሰጥ ነው፤ በሚል ያስተላላፈው ዜና ነው። ታዲያ በዚህ መልዕክት ስር የተሰጡት አስተያየቶች፤ እንኳን አደረገ! የሚልና የኤርትራ ተላላኪ መሆኑ እንደተነቃበት የሚገልጹ ነበሩ።
እርግጥ ነው፤ የኢፌዴሪ መንግሥትና የየክልሉ መንግሥታት ሥራ ፈጣሪ ለሆኑ ታታሪ ወጣቶች ከዚህ ቀደም ብድር ብቻ ሳይሆን የመሥሪያ ቦታና የሞያ ድጋፍ ሲሰጡ መቆየታቸው ይታወቃል። ይህ ለዜጎች የሥራ እድል የመፍጠርና ኢኮኖሚው ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግ በሚያስችል አኳኋን እንዲያድግ የማድረግ የመንግሥት የኢኮኖሚ እቅድ አካል እንጂ፤ የኤርትራ መንግሥት ወኪሎችና የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚዎች ሁከት ለመቀስቀስ የከፈቱትን ዘመቻ ተከትሎ የተላላፈ ድንገተኛ ውሳኔ አይደለም።
በአጠቃላይ ያለው ሁኔታ የኤርትራ መንግሥትና የሩቅ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያውያንን በዘርኝነት እርስ በርስ እንዲተላላቁ የማድረጉ ሴራ እስካሁን ባለው ሁኔታ ብዙም የተሳካላቸው አይመስልም። በዚህ ተስፋ ይቆርጣሉ ብሎ መጠበቅ ግን የዋህነት ነው። የዘር ጥላቻ ቅስቀሳቸውን ይቀጥላሉ። በተለይ፤ በአማራ ክልል የሕዝቡን ተገቢ ቅሬታ ያለወጉ አዛብተው በመጥለፍ የኤርትራ መንግሥት ተወካዮች ባካሄዱት የኢትዮጵያ ብሔሮች  በጥርጣሬ እንዲተያዩ የማድረግ ቅስቀሳ ሊሽር የሚችል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ያስቀመጡት ጠባሳ ግን አለ።
ይህም በተለይ ከኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ነው። በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች፤ በተለይ በሰሜን ጎንደር አካባቢዎችና በጎንደር ከተማ በተካሄዱ በጦር መሳሪያ በታጀቡ ሰልፎች ላይ፤ እንዲሁም የአማራ ሕዝብ ደጋፊ መሰለው የጥላው! በለው! መልዕክት የሚያስተላልፉ ማህበራዊ ሚዲያዎችና ኢሳት በተሰኘው የኤርትራ ቴሌቪዥን ብሔራዊ አርማ የሌለው አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ ባንዲራ ሲያውለበልቡ ታይተዋል። ይህን ብሔራዊ አርማ የሌለው ባንዲራ ትክክለኛ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ነው የሚል መልዕክት ሲያስተላልፉና ባለአርማውን ሰንደቅ ዓላማም ሲያጥላሉ እንደሰነበቱም ይታወቃል።
ይህ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የተንፀባረቀው ንቀት፤ የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ላይ እንደተሰነዘረ ንቀትና ጥላቻ የሚቆጠር ነው። የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ ከጥቂት ትምክህተኞች ውጭ በሁሉም ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተቀባይነት ያለው መሆኑ ሊስተዋል ይገባል።
የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሰንደቅ ዓላማው ላይ ያላቸውን አቋም ለማሳየት አንድ እውነታ ላንሳ፤ በአገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ በብሔር ላይ ተመስርተው የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በአካሄድ ላይ ሰላማዊነትንና ሁከትን የማጣቀስ ዝንባሌ የሚንጸባረቅባቸው ጭምር ብሔራዊ አርማ ያለውን የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ የተቀበሉ መሆኑን ልብ በሉ። በብሔር ላይ የተመሰረቱ የተለያያዩ ፓርቲዎችን ያቀፈው መድረክ የተሰኘው የፖለቲካ ፓርቲ ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ ያካሄደውን ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል። ይህ የመድረክ ሰላማዊ ሰልፍ በተለየ ሁኔታ በባለብሔራዊ ዓርማው ሰንደቅ ዓላማ የደመቀ ነበር። ይህ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፅንፍ የያዘ አቋም ያላቸው ጭምር የኢፌዴሪን ሰንደቅ ዓላማ የራሴ ነው ብለው የተቀበሉ መሆኑን ያመለክታል። በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መፈቃቀድ የተመሰረተ የሕዝቦች አንድነት ያላትን ሉዓላዊት ኢትዮጵያ ያልተቀበሉት የመገንጠል ፍላጎት ያላቸው ኦነግን የመሳሰሉት ድርጅቶች ደግሞ ጭራሽ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያለውን ሰንደቅ ዓላማም አይቀበሉም። ሰሞኑን ከተመሳሳይ ቦታ ማለትም ከኤርትራ መንጭቶ በአማራና በኦሮሚያ ክልል የተካሄደውን ሁከት ስንመለከት በአማራ ክልል የኢትዮጵያን ብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አንድነት የማይወክለው ሰንደቅ ዓላማ ሲውለበለብ፤ በኦሮሚያ ደግሞ በሰማያዊ መደብ ላይ ቀይ ኦዳ (ዋርካ) ያለው የኦነግ አርማ ነበር የተውለበለበው፤
ያም ሆነ ይህ፤ ቀደም ሲል በነበሩት አሃዳዊ ሥርዓቶች በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል የነበረውን የተዛባ ግንኙነት በመሻር በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት የተፈጠረባትና ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት የሆኑባት፤ ይህም በሕገ መንግሥት የተረጋገጠበት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ የመንግሥት ሥርዓት ሰንደቅ ዓላማ አርማ አለው። በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 3 “የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ” በሚል ርዕስ ስር፤
·         የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሃል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በመሃሉ ብሄራዊ አርማ ይኖረዋል።

·         ሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚኖረው አርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንጸባርቅ ይሆናል።
ተብሎ ተደንገጓል።
በዚህ መሠረት ማንኛውም ሰው ሕገ መንግሥቱ ላይ ያለውን መንፈስ የሚወክል አርማ አዘጋጅቶ እንዲወዳደር በወጣ ይፋ ማስታወቂያ መሠረት በርካታ ተወዳዳሪዎች ካቀረቧቸው አርማዎች መካከል ተወዳድሮ ያሸነፈው ተመርጦ ነው የሰንደቅ ዓላማው ብሔራዊ አርማ የተወሰነው፤ ይህ አርማም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፀደቀ አዋጅ ጸንቷል። ይህም በመጀመሪያ በ1989 በወጣው አዋጅ ቁጥር 16/1989፤ በኋላም በ2001 ዓ.ም. ተሻሽሎ በወጣው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001 ጸድቋል።
በሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001 አንቀፅ 6 ላይ ደግሞ፤ የሰንደቃላማው ቀለማትና ቅርፅ  በሚል ርዕስ ስር የሚከተለው ተደንግጓል፤
·         ሰንደቅ ዓላማው ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሃል ቢጫ ከታች ቀይ ሆኖ በክብ ሰማያዊ መደብ ላይ የተቀረፀ ብሄራዊ አርማ ይኖረዋል። አርማው መሃከል ላይ የሚያረፈው የክቡ ዙሪያ የአረንጓዴና የቀዩን ቀለማት አጋማሽ አካሎ ይሆናል።
·         ቀለማቱ ብሩህና መሰረታዊ የሆናሉ።
·         ቀለማቱ አግድም የተዋቀሩና እኩል ስፋት የሚኖራቸው የሆናሉ፤ የሰንደቅዓላማው ወርድ የቁመቱ እጥፍ ይሆናል።
·         የአርማው ቅርፅ ክብ በሆነ ሰማያዊ መደብ ላይ፤
ሀ. ከየአቅጣጫው መጥተው የሚገናኙ ቀጥታና እኩል የሆኑ ቢጫ መስመሮች
   ይኖረዋል፤
ለ. ቀጥታና አኩል ከሆኑት መስመሮች የተዋቀረ ኮከብ ይኖረዋል፤
ሐ. ቀጥታና አኩል በሆኑት መስመሮቸ መተላላፊያ ላይ ቢጫ ጨረር ይኖረዋል።
በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 8 ላይ የአርማው ትረጉም ፤ በሚል ርእስ ስር ደግሞ የሚከተለው ተደንገጓል፤
·         ክብ የሆነው ሰማያዊ መደብ ሰላምን ይወክላል።
·         ቀጥታና እኩል የሆኑት መስመሮች፤ የብሄሮችን፣ የብሄረሰቦችንና የህዝቦችን እንዲሁም ሃይማናቶችን አኩልነት ያመለክታል።
·         ቀጥታና እኩል ከሆኑት መስመሮች የተዋቀረው ኮከብ፤ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድ የመሰረቱትን አንድነት ያመለክታል።
·         ቢጫ ጨረር፤ በመፈቃቀድ አንድነት ከመሰረቱት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች የፈነጠቀውን ብሩህ ተስፋ ይፈነጥቃል።
እንግዲህ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የሰፈረውን አርማ መጥላት ወይም መቃወም ቀደም ሲል የነበረውን የተዛባ ግንኙነትና ጭቆና በመሻር የተመሰረተውን የብሔሮች እኩልነትና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት መቃወም ነው። ይህ ደግሞ በየትኛውም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ተቀባይነት የሌለው አቋም ነው። እናም በተለይ የሻዕቢያ ተላላኪዎች በቀሰቀሱት ሁከት ቀመስ ሰልፍ ላይ ብሔራዊ አርማ የሌለው ሰንደቅ ዓላማ እንዲውለበለብ መደረጉ የተቀሩት የኢትዮጵያ ብሔሮች አማራውን በጥርጣሬ እንዲመለከቱት የሚያደርግበት ሁኔታ አለ። ይህ ደግሞ በብሔሮች መካከል አለመተማማንን በመፍጠር አንድ ቀን ግጭት ለመጫር ሆን ተብሎ በኤርትራ መንግሥትና በትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚዎቹ የተደረገ ሴራ ነው።
በመሆኑም የአማራ ሕዝብ ልጆቹን በማደናገር በሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በጥርጣሬ እንዲታይ ለማድረግ የተጠነሰሰው ሴራ ለበኋላ ጥላቻና ግጭት እየተደገሰለት መሆኑን እንደሚጠቁም ከወዲሁ ሊረዳ ይገባል። በተለይ፤ በመላ የኢትዮጵያ ክልሎች ተሰራጭቶ ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር ለሚኖረው የአማራ ሕዝብ ይህ አካሄድ ፈፅሞ መልካም አይሆንም። የአማራ ሕዝብም እንዲህ ዓይነቱን ተግባር የሚፈጽሙ አካላትን ሀይ ሊላቸው፤ በመከባባርና በእኩልነት ላይ የተመሰረተውን የብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለማፅናትም ከሌላው ጊዜ በበለጠ በግንባር ቀደምትነት ሊሰራ ይገባል። የዛሬ የሰንደቅ ዓላማ ጥላቻ ለነገ በብሔሮች መገፋት ጣጣ እንደሚዳርግ ማሰብ ብልህነት ነው።

No comments:

Post a Comment