ኢብሳ ነመራ
ሰሞኑን
2ኛው አገር አቀፍ የዳያስፖራ ቀን “የኢትዮጵያ ህዳሴ በአገር ልጆች” በሚል መሪ ቃል በባህር ዳር ከተማ ተከብሯል። በክልል ደረጃም ለ3ኛ ጊዜ በዚያው በአማራ ክልላዊ
መንግሥት ባህርዳር ከተማ ተከብሯል። የኢፌዴሪ መንግሥት በተለያየ ምክንያት ከአገራቸው ወጥተው በውጭ አገራት ለሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና
ኢትዮጵያውያን ትኩረት ሰጥቷል። በመሆኑም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ
ጉዳዮቸ ፖሊሲ ተቀርፆ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ጥቂት ዓመታት ተቆጠረዋል። የኢፌዴሪ መንግሥት ለዳያስፖራው ትኩረት መስጠት ያስፈለገው
የዳያስፖራውን ማህበረሰብ (ዜግነታቸውን የቀየሩትን ጭምር) ከእናት አገራቸው ኢትዮጵያ መነጠል ፈፅሞ የማይቻል በመሆኑ ነው። ይህን
ጥብቅ የስሜት ቁርኝት መነሻ በማድረግ ዳያሰፖራውም ከሚወዳት አገሩ እንዲጠቀም፤ የሚወዳት አገሩና ህዝቧም ከዳያስፖራው እንዲጠቀሙ
ለማድረግ ነው።
ቀደም
ባሉት ጊዜያት ወደውጭ አገር የሚሰደዱ በማደግ ላይ ያሉ አገራት ዜጎች እንደኪሳራ ነበር የሚታዩት። በተለይ የምሁራን ስደት እንደከፍተኛ
ኪሳራ ነበር የሚታሰበው። ይህ የሆነው አምራች ዜጎችን ያሳጣል በሚል መነሻ ነው። እርግጥ ነው፤ አንድ አገር አእምሯዊና አካላዊ
ብቃት ያላቸው ዜጓቿ በብዛት አገር ለቅቀው ሲሰደዱ መጎዳቷ የማይቀር ነው። ይሁን እንጂ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በበለፀጉና
በሰለጠኑ አገራት የሚኖሩ ዜጎችና ተወላጆች እንደኪሳራ ሳይሆነ እንደእምቅ ሀብት የሚታዩበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
በውጭ
አገር የሚኖሩ ዜጎችና ተወላጆች የንግድ ትስስር፣ የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ምንጭ፣ የቴከኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር ምንጭ መሆናቸው
ከፍተኛ ግምት እየተሰጠው መጥቷል። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በውጭ አገር በሚኖሩ ዜጎች/ተወላጆችና በውጭ ንግድ መካከል ቀጥተኛ
ትስስር ይፈጠራል። በውጭ አገር የሚኖሩ በርካታ ዜጎችና ተወላጆች ያሏቸው አገራት ዜጎቻቸው ከሚኖሩባቸው አገራት ጋር ያላቸው የውጭ
ንግድ ትስስር ከፍተኛ የሆናል። በውጭ የሚኖሩት ዜጎችና ተወላጆች የትውልድ አገራቸውን አምራቾችና ተጠቃሚዎች በሚኖሩበት አገር ከሚገኙት
አምራቾችና ተጠቃሚዎች ጋር ያስተሳስራሉ። በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎችና ተወላጆች የአገራቸው ምርቶች ተጠቃሚዎች ስለሚሆኑም የወጭ
ንግድ መዳረሻ ይፈጥራሉ። ከዚህ በተጨማሪ የአገራቸውን ምርት በሚኖሩበት አገር በማስተዋወቅ የገበያ መዳረሻን ያሳድጋሉ።
በውጭ
አገር የሚኖሩ ዜጎችና ተወላጆች ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ምንጭ የሚሆኑበት ሁኔታም አለ። በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎችና ተወላጆች
በትውልድ አገራቸው ኢንቨስት ከማድረጋቸው ባሻገር መረጃ በመስጠት የሚኖሩበት አገር ባለሀብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ያበረታታሉ።
አገራት በውጭ አገር ለሚኖሩ ዜጎቻቻውና ተወላጆቻቻው የሚያዘጋጁት የመንግስት ቦንድም የካፒታል ምንጭ ይሆናል። በውጭ አገራት የሚኖሩ
ዜጎችና ተወላጆች ከቀጥታ የውጭ ኢነቨስትመንትና ቦንድ ግዢ በተጨማሪ አገር ቤት ለሚገኙ ቤተሰቦቻቻውና ዘመዶቻቻው ገንዘብ በመላክ
የውጭ ምንዛሪ ምንጭም ናቸው።
የዕውቀትና
የቴከኖሎጂ ሽግግር ሌላው በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎችና ተወላጆቸ ለአገራቸው የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ነው። በሰለጠኑት አገራት የሚኖሩ
ዜጎችና ተወላጆች የዚያን አገር ዕውቀትና ክህሎት የታጠቁ ናቸው። ይህን ዕውቀትና ክህሎት በኢንቨስትመንትና በቀጥታ ስልጠና ወደትውልድ
አገራቸው ማሸጋገር ይችላሉ።
ከላይ
በተገለፀው አኳኋን በውጭ አገራት ከሚገኙ ዜጎቻቸውና ተወላጆቻቸው በመጠቀም ረገድ በተለይ ቻይናና ህንድ ተጠቃሾች ናቸው። ሁለቱ
አገራት በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎቻቸው በርካታ ስለሆኑ ይጠቀሳሉ እንጂ፤ በዚህ ረገድ ተጠቃሚ የሆኑ አገራት ቁጥር ቀላል አይደለም።
በዚህ
ዙሪያ ያለውን እውነታ ለመረዳት የቻይናን ተሞክሮ በአጭሩ እንመልከት። የቻይናውያን ወደውጭ አገር የመጓዝ ታሪክ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ
ነው። በተለይ ታይዋን፣ ደቡብ ኮሪያ ፣ ሲንጋፖር፣ ታይላንድ፣ ማሌዢያ፣ ፊሊፒንስ . . . በመሳሰሉ የደቡብ ምስራቅ ኢስያ አገራት
እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ቻይናውያን ይኖራሉ። በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ቻይናውያን ቁጥርም ቀላል አይደለም። እነዚህ በውጭ አገር
የሚኖሩ የቻይና ተወላጆች ምንም ያህል ዓመት በውጭ አገር ቢኖሩ አገራቸውን አይተዉም። በሚኖሩበት አገር ሁሉ ትንሿን ቻይና ሰርተው
ባህልና ወጋቸውን ሳይለቅቁ ነው። ቻይናውያን በውጭ አገር የሚኖሩ ተወላጆቻቸውንና ዜጎቻቻውን ወደአገራቸው ላይመለሱ እንደሄዱ ስደተኞች
አይመለከታቸውም። ስደተኞች ሳይሆሁ ተጓዦች እንደሆኑ ነው የሚያስባቸው፤ አንድ ቀን ወደአገራቸው እንደሚመለሱ ተጓዦች።
ታዲያ
እነዚህ በውጭ አገር የሚኖሩ ቻይናውያንና የቻይና ተወላጆች በአመዛኙ በሚኖሩባቸው አገራት ስኬታማ እንደሆኑ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፤
ታዲያ ከ70ዎቹ ማገባደጃ በኋላ በቻይና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ መደረጉን ተከትሎ በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎቻቸውና ተወላጆቻቸው የቻይና
ኢኮኖሚ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲመነደግ በማድረግ ረገድ ከፈተኛ ሚና ተጫውተዋል። በተለይ ከ90ዎቹ መግቢያ አንስቶ በውጭ አገር
የሚኖሩ የቻይና ተወላጆች ወደትውልድ አገራቸው የሚያደርጉት ቀጥታ ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ደረጃ አድጎ ነበር። በእነዚህ ዓመታት
በዓመት ወደቻይና ይገባ ከነበረው 40 ቢሊዮን ዶላር ቀጥታ የውጭ
ኢንቨስትመንት ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው በትውልደ ቻይናውያን የሚከናወን ነበር።
ትውልደ
ቻይናውያኑ በአገራቸው የሚያደርጉት ኢንቨስትመንት በተለይ በአገራቸው ያለውን ርካሸ የሰው ኃይል ታሳቢ ያደረገና የወጪ ንግድ ምርቶችን
በማምረት ላይ ያተኮረ ነበር። በመጀመሪያ ወደቻይና የገቡት የትውልደ ቻይናውያን ኢንቨስትመንቶች ጫማ፣ በከፊል የኤሌክትሮኒክስ መገጣጣሚያ፣
የተቀነባባሩ ምግቦች፣ ጨርቃጨርቅ፣ የገና ማድመቂያ ጌጣጌጦች፣ አሻንጉሊቶች፣ . . . የመሳሰሉ በውጪ አገራት ገበያ ላይ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸው ምርቶች ላይ ያተኮሩ እንደነበሩ መረጃዎች ያመለከታሉ። በኋላ ላይ ግን የትውልደ
ቻይናውያኑ ኢነቨስትመንት ወደትላልቅ የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ፣ ሪል ስቴት ወዘተ እየዘለቀ መጥቷል። ከ1990 እሰከ 97 ባሉት ዓመታት
የትውልደ ቻይናውያን ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት በየዓመቱ በ44 በመቶ ነበር የሚያድገው።
ይህ
የቻይናውያንና የትውልደ ቻይናውያን ቀጥታ ወደአገራቸወ የጎረፈ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የአገሪቱን ኢኮኖሚ በፍጥነት በማሳደግ ረገድ
ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ታዲያ ትውልደ ቻይናውያኑን በእነዚሀ ዓመታት በውጭ አገር ያፈሩትን ሀብት፣ ዕውቀት ከነኩባንያው ይዘው ወደአገራቸው
እንዲጎርፉ ያደረገ አንድ መሰረታዊ ምክንያት ነበር። ይህመ የቻይና ሪፖብሊክ መንግስት በሀገመንግስቱ በውጭ አገር ለሚኖሩ ትውልደ
ቻይናውያን፣ ቻይናውያንና ወደአገራቸው ለሚመለሱት ልዩ ጥበቃ የሚያደርግ ድንጋጌ እንዲካተትበት መደረጉ ነው።
እንግዲሀ
የጽሁፌ መነሻ ስለቻይና ዳያስፖራ ማውራት ሳይሆን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ በአገሩ ከሌላ ቦታ የማያገኘውን አግኝቶ እንዲጠቀም፣ አገሩንም
እንዲጠቅም የሚያስችለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል መመልከት ነው።
በዚህ
ጽሑፍ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው የኢፌዴሪ መንግስት በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከትውልድ አገራቸው
እንዲጠቀሙና አገራቸውንም እንዲጠቅሙ ማድረግ የሚያስችል የዳያስፖራ ጉዳይ ፖሊሲ ቀርጾ ሥራ ላይ አውሏል። ዳያስፖራው ከአገሩ ጋር
ባለው ቁርኝት በፖሊሲ የተመቻቸለትን እድል ተጠቅሞ ለአገሩ አሰተዋፅዖ ሊያበረክት ለሚችለውና እርሱም ሊያገኝ የሚገባውን ጥቅም እንዲያገኝ
አነሳሸ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ሆኗል። በየዓመቱ በተለያዩ ክልሎች በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ የዲያስፖራ ቀን ማክበር ያስፈለገው
ለዚህ ዓላማ ነው።
በዚሁ
መሰረት የዳያስፖራ ቀን ዘንድሮ ለ2ኛ ጊዜ “የኢትዮጵያ ህዳሴ በሀገር ልጆች” በሚል መሪ ሀሳበ በባህር ዳር
ከተማ ተከብሯል። የኢፌዴሪ የዳያስፖራ ጉዳይ ፖሊሲ ጸድቆ ሥራ ላይ ከዋለና የዳያስፖራ ቀንን በማከበር ዳያሰፖራው በትውልድ አገሩ
ስላለው ተጨባጭ ሁኔታ ግንዛቤው መዳበር ከጀመረ ወዲህ፤ በአገሪቱ ኢኮኖሚና ልማት ውስጥ ያለው ተሳትፎና የሚያበረክተው
አሰተዋፅኦ እያደገ መጥቷል። ይህም አገር ቤት ለሚኖሩ ዘመዶቻቸው በህጋዊ መንገድ በሚልኩት የውጭ ምንዛሪ፣ በቀጥታ የውጭ
ኢንቨስትመንት፣ በዕውቀትና በቴክኖሎጂ ሽግግር የሚገለፅ ነው።
መረጃዎች እንደሚያመለከቱት በ2008 ዓ.ም. በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደአገር ቤት
የላኩት ገንዘብ (remittance) 4 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። ይህ ትልቅ ገንዘብ ነው። አገሪቱ ከቱሪዝም እንዲሁም ከወጪ
ንግድ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሪ የሚበልጥ ነው። ይህ ከውጭ አገር የሚላክ ገንዘብ በ2003 ዓ.ም. 1 ነጥብ 78 ቢ. ዶላር፣
በ2004 ዓ.ም 1 ነጥብ 85 ቢ. ዶላር፣ በ2005 ዓ.ም. 1 ነጥብ 95 ቢ. ዶላር፣
በ2006 ዓ.ም. 3 ነጥብ 4 ቢ. ዶላር፣ በ2007 ዓ.ም 3 ነጥብ 8 ቢ. ዶላር ነበር። በተለይ የዳያሰፖራ ቀን መከበር ከጀመረ በኋላ
ያለው እድገት ቀኑ መከበሩ ዳያስፖራውን ምን ያህል እንዳነቃቃው ያመለክታል።
የዳያሰፖራውን ኢንቨስትመንት ስንመለከት 6 ሺህ ያህል
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኩል የኢንቨስትመንት የማማከር አገልግሎት ያገኙ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል
ከ 3 ሺህ በላይ የሚሆኑት በኢንቨስትመንት ላይ ተሰማረተዋል። የኢተዮጵያ ዳያስፖራ አባላት የተሳተፉባቸውን የኢንቨስትመንት
ዘርፎች ስንመለከት 1458 በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ 1100 በግብርና፣ 400 በአገልግሎት፣ 4 በማዕድን ዘርፍ ሆኖ እናገኘዋለን።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት በዕውቀት ሽግግር
በኩልም ለአገራቸው አሰተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። በቀጥታ
ከኢንቨስትመንት ጋር ይዘውት ከመጡት ዕውቀትና ቴክኖሎጂ በተጨማሪ፤ በተለይ በህክምናው ዘርፍ በውጭ አገር የሚሰሩና የሚያስተምሩ
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀኪሞች ከሌሎች የላቀ ችሎታ ካላቸው የውጭ አገር ዜጎች ጋር በመተባበር ዘመናዊ የህክምና
መሳሪያዎችን ይዘው ወደአገር ቤት በመመጣት የህክምና አገልገሎት ሲሰጡ ቆይተዋል። ይህ ብቻ አይደለም፤ ከኮሌጆችና
ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባባር ስልጠናዎችንም ሰጥተዋል። ይህ ለወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት አገራቸውን በውጭ ምንዛሪ
መደገፈ እንዲችሉ በአገር ውስጥ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ የቁጠባ ሂሳብ እንዲከፍቱ ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸዋል። እስካሁን በዚህ
የውጭ ምንዛሪ የቁጠባ ሂሳብ ተጠቃሚ የሆኑ የዳያስፖራ አባላት 5 ሺሀ ደርሰዋል። የቆጠቡት ሂሳብም 37 ሚሊዮን ዶላር ገደማ
ነው። በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቦንድ ግዥም የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ እያደገ መጥቷል። በ2008 ዓ.ም. አስር ወራት
ብቻ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት የ5 ሚሊዮን ዶላር የቦንድ ግዥ ፈፅመዋል።
ይህ ከላይ ለአብነት ያህል ወስደን የተመለከትነው የኢትዮጵያ
የዳያስፖራ አባላት በአገራቸው ኢኮኖሚ ውስጥ እያደረጉት ያለው ተሳትፎ የዳያስፖራ አባላቱ ራሳቸውን ጠቅመው አገራቸውንም
እየጠቀሙ እንደሆነ ነው። አጠቃላይ የኢተዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ቁጥር 3 ሚሊየን እነደሚሆን ይገመታል። እነዚህ የዳያሰፖራ
አባላት ተወልደው ተምረው ካደጉባት አገራቸው ጋር የስሜት ቁርኝት አላቸው። ይህ ቁርኝት በስሜት አገርንና ሕዝብን ከመወደድ
አልፎ በመጠቃቀም ላይ የተመሰረተ ወደመሆን መሸጋጋር አለበት።
No comments:
Post a Comment