Tuesday, 16 August 2016

ልክ ያለፈው ማንጎላጀት ዋጋ እንዳያስከፍለን!!




ስሜነህ
የሽግግሩ ዘመን በርካታ አወንታዊ ተግባራት የተከናወኑበት ቢሆንም ከሁሉም ልቆ የሚጠቀሰው ታላቁን የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት የማርቀቅና የማፅደቅ ተግባር የተፈፀመበት ጊዜ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የወቅቱ የኃይል አሰላለፍ ዓይነተኛ መለያ የነበረውም የብሔር ብሔረሰቦች መብት ጥያቄ መሆኑም በተመሳሳይ የሚታወቅና የማይዘነጋ ነው፡፡ በተለይ የእስከ መገንጠል መብት ዓይነተኛ የፍልሚያ ርዕስ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያዊነት ፈቅደውና ወድደው የሚጎናፀፉት፤ የኢትዮጵያ አንድነትም በሕዝቦቿ መፈቃቀድና መልካም ፈቃድ ላይ የሚመሰረት እንጂ፤ በኃይልና በግዴታ የሚጫን መሆን የለበትም የሚለው አዲስ አስተሳሰብ የበላይነትን ይዞ ፋይሉ በቀጣይ አተገባበሮች ተደምድሟል፡፡ በዚህ ወቅት ታዲያ የትምክህት ኃይሉ የተለመደ የመከፋፈልና የመለያየት ስጋቱን ከፍ አድርጎ በማሳየት ብዙዎችን ለመማረክ መሞከሩም የማይዘነጋ ነው፡፡ የዚህ ተረክ አጀንዳም የከሸፈ የመሰለው አጀንዳ ዛሬም አቧራውን አራግፎ አቧራ እያስነሳ መሆኑን በተለያዩ ተጠየቆች መሞገት ነው።
በሕገ-መንግስቱ መግቢያ እንደተገለፀው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በአገራቸው ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ማህበራዊ ዕድገታቸው እንዲፋጠን፣ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን ተጠቅመው በነፃ ፍላጎታቸው በሕግ የበላይነት እና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት ቁርጠኝነታቸውንና መተማመናቸውን የገለፁበት የቃል ኪዳናቸው ሰነድ ሆኖ ፀድቋል፡፡
ሕገ-መንግሥት የማፅደቁ ሂደት በምልዓተ-ሕዝቡ ሰፊ ውይይትና ተሳትፎ ያለፈ፤ በየደረጃው ከፍ ያለ የሀሳብ ትግል የተካሄደበትና ዴሞክራሲያዊ የነበረ ቢሆንም፤ የትምክህቱ እና የጠባቡ የመከፋፈል አጀንዳ የሚጀምረውም ከዚሁ ከአሳታፊነት ጋር በተያያዙ የማስመሰል አስተሳሰቦች መሆኑን ስለአጀንዳችን አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ያም ሆኖ ግን መሰረታዊ አቋሞቻቸው ተቀባይነት ያላገኙ ወገኖች የመጨረሻ ምሬታቸውን በሂደቱ በዴሞክራሲያዊነት ላይ ለማሳበብ ቢኖክሩም እዚህም ላይ ተሸንፈው ይውደቁ እንጂ አሁን አቧራውን አራግፈው ተነስተዋል፡፡  
የመጀመሪያው የኢፌዴሪ መንግሥት የሥራ ዘመን ሕገ-መንግሥታዊ ዕውቅና ያገኙትና ለዘመናት አገሪቱን የኋሊት ሲያጓጉዟት የቆዩትን ችግሮች የገቱት መሠረታዊ ባህርያት የሚታይ ውጤት ያመጡበትና በተግባር የተረጋገጡበት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የአገራቸው ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት መሆናቸውና እኩልነታቸው መረጋገጡ በመላ አገሪቱ ዳር እስከ ዳር ሰላምን ከማስፈኑም ባሻገር፤ ለአዲስ ኢትዮጵያዊነት ግንባታ መሠረት የጣለ መሆኑ ዛሬ በትምክህቱ እና በጠባቡ መንደር በአደባባይ እየተካደና የአዲሲቱ ኢትዮጵያ መገለጫ የሆነው ባንዲራ እየተረገጠ የሚገኘው በወቅቱ ተሸንፈው የነበሩ ኃይሎች አቧራውን አራግፈው በመነሳታቸው መሆኑን መላው ሰላማዊ እና የአገሩን ብልጽግና የሚፈልግ ዜጋ ሁሉ ጠንቅቆ ሊገነዘብ ይገባል፡፡
ከመንግሥት ምስረታ በኋላ የትምክህትና የጠባብነት ኃይሎች የፅንፈኝነት አጀንዳቸውን ቢያራግቡም የሚቃጠል ነገር ማግኘት አልቻሉም። እናም ዛሬ በሂደት የተፈጠረውን እና በእርግጥም ለውጥ ማምጣት ያልተቻለበትን የመልካም አስተዳደር አጀንዳ ያሰቃየውን ሕዝብ ለትምክህትና ለጠባብነት አጀንዳቸው አቧራ ማስነሻ እያዋሉት ነው፡፡  
በሰፈነው ዴሞክራሲ፤ በነፃነት የመናገርና ሀሳብን  የመግለፅ መብት ኢ-ዴሞክራሲያዊ ቅስቀሳቸውን ለዴሞክራሲያዊ ፕሬስ ቦታ እስኪጠብብ ድረስ ያጧጧፉትና መድረኩን በጩኸት የሞሉት የደርግ ፀሃፌ ትዕዛዞችና ትምክህተኞች የቱንም ያህል ዕሪታ ቢያቀልጡ የሚፈልጉትን ሰሚ ጆሮ በወቅቱ አላገኙም። ዛሬ ደግሞ በነኢሳትና በፌስቡክ አብዮት አቧራውን ለማስነሳት ስለመትጋታቸው ሰሞንኛዎቹ ሁከቶች በቂ ማሳያዎች ስለመሆናቸው መጠራጠር አይገባም፡፡
በመሠረቱ በሕዝቡና በመንግሥት የተጠናከረ ተሳትፎ የተገኘው ሰላምና መረጋጋት፤ እንዲሁም የአርሶ አደሩ ዕርካታ ይልቁንም የትምክህት እና የጠባብነት ኃይሉ መኮላሸት የመንግሥትን ስልጣን የተቆጣጠረው መሪ ድርጅት ባለበት እንዲያንጎላጅ ያደረገው ስለመሆኑና እነዚህ ኃይሎች አቧራውን አራግፈው እንደገና አቧራ እንዲያስነሱ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑንም መቀበል የመፍትሄው መጀመሪያ ነው፡፡ ምክንያቱም በዚያ ይኸ ኃይል ተኮላሽቶ በነበረበትም ወቅት የማንነትና የመሬት ጥያቄው በብቃት የተመለሱለት አርሶ አደር ሕዝብ ጎትጓችና ቀስቃሽ ሆኖ አለመገኘቱ መሪው ድርጅት ወደፊት ያለመንቀሳቀስ ብቻ ሳይሆን ባለበት ለመበስበስ አደጋ አጋልጦት የነበረ መሆኑ ይታወሳልና፡፡
በኢትዮጵያ የተጀመረው እና በመገንባት ላይ የሚገኘው የብሔር፣ ብሐረሰቦችን መብትና እኩልነት ያረጋገጠ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እፎይታ የማይሰጠው ለመሆኑ በብዙ ማሳያዎች ለተረጋገጠለት የሻዕቢያ መንግሥት አቧራ አራጋፊዎቹ እና መወለካከፉ ምቹ ሁኔታዎች የፈጠሩለት ለመሆኑም ሰሞንኛ በነበሩት ሁከቶች ላይ ሁሉ የተንጸባረቁት መፈክሮች እና ድንፋታዎች በቂ ምስክሮች ናቸው፡፡
ኢህአዴግ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት አየር ላይ የተንጠለጠለና ሕዝባዊ መሠረት ያልገነባ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ለደረሰው ሻዕቢያ እንዲህ ዓይነት መወለካከፎች ዋጋ እንከፍል ዘንድ ምቹ ሁኔታዎች መሆናቸውንም መዋጥ ሌላኛው የመፍትሄ መጀመሪያ ነው። የማያሽረውን ዋጋ እንዳንከፍል የመፍትሄው መጀመሪያ ከሆኑቱ በሁለተኛው ምእራፍ ላይ መቀመጥ የሚገባው ደግሞ በሥርዓቱ ውስጥ የፋፋውን ንቅዘት በተገቢው መንገድ ለይቶ የይስሙላ ሳይሆን አስተማማኝና ዘላቂነት ያለው እርምጃና ትግል ማካሄድ ተገቢ መሆኑን የተመለከተው ነጥብ ነው።
በኢህአዴግ እና በመላው ሕዝብ ውስጥ ስለተፈጠረው ማንጎላጀት እና በዚህም አገርና መላው ሕዝብ ዋጋ እንዳይከፍል ስለተፈጠረው ስጋት ዋናው መገለጫ የሥርዓቱ  ማህበራዊ መሠረት የሆነው አርሶ አደር መሰረታዊ ጥያቄዎቹ /ማለትም የማንነትና የመሬት ጥያቄዎች/ ስለተመለሱለት ለጎትጓችና ለቀስቃሽ ኃይል ተጋላጭ አይሆንም የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ መያዙና በሥርዓቱ ፊት አውራሪዎች ዘንድ ያቆጠቆጠው የአስተሳሰብ ንቅዘት ሊታገሉት ወደሚከብድ ኪራይ ሰብሳቢነት አድጎ ድርጅቱ መልኩን እየለወጠ እንዲመጣ ያደረገው መሆኑ ነው፡፡ ይህ ችግር በተለይ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ጎልቶ የወጣና በወቅቱ እና በተገቢው መንገድ ካልተቋጨ አደጋው ከባድ እንደሚሆን ታምኖበት ሲያበቃ እንደገና ማንጎላጀቱ ይኸው ሰሞነኛ ከነበሩት ሁከቶች በስተጀርባ ለነበሩት አቧራ አንሺዎች ምቹ መደላድል መሆኑ ተስተጋብተው በነበሩት መፈክሮች ተረጋግጧል፡፡
ስለሆነም ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ እያፈነገጠ የመጣው የንቅዘት ኃይል ከአዲስ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ግንባታ ጋር የሚጋጩ እና የሻቢያን ሴራ የሚያንቆለዻጵሱ መፈክሮች ይዞ በፌስቡክ አብዮተኞቹ አደባባይ በግልጽ የታየው ሥርዓቱ በወቅቱና በተገቢው መንገድ ስላላረመው ወይም ለመቅጨት ጊዜ ወስዶ በማንጎላጀቱ እንደሆነ አምኖ መቀበልም የመፍትሄው ሁለተኛ ምእራፍ ነው፡፡ በሁከት አደባባዮች ሲስተጋቡ ከነበሩት መፈክሮች እና ጩኸቶች መገንዘብ የሚቻለው አብይ ቁም ነገር የድርጅቱ ዋና መለያ የሆነውን የሕዝባዊነትና ሰላማዊ አማራጭን የማስቀደም አብዮታዊነት እንደ ክህደትና ልፍስፍስነት የተቆጠረ የመሆኑን የማንጎላጀት ውጤት ነው፡፡ የሁሉም ምንጭ ሥርዓቱም አምኖ የተቀበለው እና የአግዙኝ ጥሪ የተላለፈበት ንቀዘት ነው ፡፡ 
ከካፌ ጨዋታም ልቆ ኢህአዴግ ስለመልካም አስተዳደር በዘረጋቸው መድረኮች ላይ ሁሉ በራሱ በመሪ ድርጅቱ ማንጎላጀት መነሾ ኪራይ ሰብሳቢነት  የድርጅቱን ዴሞክራሲያዊነት እየተበተበው መሆኑን አረጋግጠው የነበረ መሆኑንም ለሁከት ተጋላጭ ላለመሆን አስታውሶ መትጋት የግድ የሆነበት ሰዐት ላይ መሆናችንንም አምኖ መቀበል ሌላኛው እና ስለመፍትሄው በሁለተኛው ምእራፍ ላይ መቀመጥ የሚገባው፤ ግን ደግሞ ዝቅ ብዬ ከተመለከትኩት አንደኛው ነጥብ ጋር ተያይዞ መፈጸም ያለበት መሠረታዊ ነጥብ ነው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት ውስጥ የገቡ አባላትን ጭምር ዋና የሁከት አራማጅ አድርጎ የተንቀሳቀሰው  ሰሞነኛው ኃይል፤ ሥርዓቱ ባለበት መቆም ብቻ ሳይሆን ወደኋላ መመለስም ይገባው ነበር ከማለት ያልተለየ አቋሙን በግልፅ እና በየሁከቶቹ አደባባይ ያሳየው ሥርዓቱ በራሱ ስላንጎላጀጀ ነው፡፡ ከዚህም ጋር አብሮ ፀረ-ዴሞክራሲ አቋሙ አዲስ ገዢ መደብነትን እስከመሻት የሚደርስ መሆኑን የሚያጠይቁ መፈክሮች እስከማሰማት የደረሰው መንግሥት ብቻ ሳይሆን እኛም ስላንጎላጀጅን ነው፡፡ ባናንጎላጅጅማ ሊንቀሳቀስ አንድ እርምጃ እንኳን እንዳይጓዝ ቅርቃር ውስጥ መግባቱ ተረጋግጦ የነበረው የትምክህትና የጠባብነት ኃይል አቧራውን አራግፎ አቧራ ማስነሳት ባልተቻለው ነበር፡፡ 
ስለሆነም ለእንደዚህ ዓይነት ዋጋ የሚያስከፍሉ ሁከቶች ላለመጋለጥ በሰላማዊና በውይይት ሊፈታ የሚችለውን ችግርና ለአቧራ ማንሻ ከለላ የተደረገውን ምክንያት ማስወገድ ተገቢ ነውና ሥርዓቱ ሊተጋበት ቁርጠኛ መሆኑን የገለጸልንን የጸረ ኪራይ ሰብሳቢነት ዘመቻ  ከራሱ ሥራ አስፈፃሚና ከማዕከላዊ ኮሚቴ  አባላቱ ጀምሮ  ወደመላው  አባላቱ በማውረድ ውጤቱን ለሕዝብ ይፋ ማድረግም የመፍትሄው ሁለተኛ ምእራፍ ላይ መቀመጥ የሚገባው መሰረታዊ ነጥብ ነው፡፡ በተለይ የመሪ ድርጅቱ አባላት ስለአገራቸው እድገትና ሰላም   በኔትወርክ ተጠምደው ከመጠዛጠዙ ይልቅ ድርጅታቸው በማንጎላጀቱ ለትምክህትና ለጠባብነት ኃይሉ ቀዳዳዎች የሰፉለት መሆኑን፤ እውነተኛ የመፍትሄው አካል መሆንም ግድ የሚላቸው ሰዐት ላይ ስለመሆናቸው አምኖ መቀበልም ሌላኛው የመፍትሄው ሁለተኛ ምእራፍ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ እንደቀድሞው የተሟሟቀ የትግል መድረክ አለመኖሩና ሀሜት ስለመስፈኑ ሁሉንም በየአካባቢው እያነጋገረ መሆኑንም ስለመፍትሄው አምኖ መቀበልን ይጠይቃል፡፡ ድርጅቱ ከፍተኛ አመራር አባላት መካከል የሚካሄደው ትግል በአብዮታዊው ኃይል የበላይነት እየተመራ ወደ አባሉ ሲደርስ የበለጠ መሠረቱን እያሰፋና ዳር እስከ ዳር ንቅናቄን ፈጥሮ ክፍት የሆኑት ቀዳዳዎች ሁሉ የመደፈናቸው ነገር አያጠራጥርምና፡፡ 
ይህን ማድረግ አንድን ድርጅት ወይም ኢህአዴግን ማደስ ብቻ ሳይሆን አገርን ከጥፋትና ከትርምስ የማዳን ጉዳይ መሆኑም ላይ ግልፅ ግንዛቤ ሊኖርና አቋም ሊያዝም ይገባል፡፡  እዚህ ላይ ግን ይኼ የቀናት ወይም የሳምንታት ተግባር ሳይሆን በተራዘመ ጊዜ የሚፈጸምና ተከታታይ ተግባራትን የሚጠይቅ እንደሆነም ሕዝቡ ሊገነዘብ እና በስራ ሂደት ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ አጀንዳዎችን በማራገብ ለሚታወቁት ሃሳዊ መሲሆች ሰለባ እንዳይሆን ማጤን ያስፈልጋል ፡፡
በዚህ ሂደት አደጋው ከመጣ ጦሱ የሚተርፈው በየደረጃው ያለው ፈፃሚና እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል በስፋት መሳተፍ የሚገባው መሆኑን ለአፍታ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ይህ የውስጥ ድርጅትን ዴሞክራሲ፤ በአጠቃላይም የዴሞክራሲን መፋዘዝና የመተጋገል እጦትን ለም መሬት አድርጎ የሚፋፋው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የፖለቲካል ኢኮኖሚ መሰረት እንዳለው በሰሞንኞቹ ሁከቶች አረጋግጧልና፡፡
ሌላው እና አቧራውን እያራገፈ ብቅ የሚለውን የትምክህትና የጠባብነት ስብስብ አጀንዳ የማሳጣት ተግባር እውን የሚሆነው በየደረጃው ያለውን አመራርና ፈፃሚ የሕዝባዊነት አመለካከት እና የማስፈፀም አቅም በመገንባት መሆኑንም ባለመዘንጋት እና ባለማንጎላጀት ነው፡፡ የድርጅቱ ሕዝባዊነት ዋና መገለጫ ለሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት፣ የሕዝብን ጥቅም መሠረት አድርጎ መወሰን፣ ለዚህም አስፈላጊውን መስዋዕትነት መክፈል መሆኑ ይታወቃልና፡፡ ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተገነባ ባለው የነፃ ገበያ ሥርዓት አመራሩ እንዲሁም ፈፃሚው ራሱን አገልጋይ በማድረግ ኃብት ያለውን አርሶ አደር እንዲሁም አገራዊ ባለኃብት መፍጠር ተልዕኮው አድርጎ ሲሰራ በአቋራጭ ለመክበር አደጋ እንደሚጋለጥ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ባለችው ስልጣን፣ ኃላፊነትና ሙያ ለኪራይ ሰብሳቢነት የመዳረግ ዕድሉ እጅጉን ሰፊ ነው፡፡ ይህንን መግታት የሚችለው ሕዝባዊነቱንና የዓላማ ፅናቱን የሙጥኝ በማለት ብቻ በመሆኑ በአመለካከት ጥራትና ግንባታ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ማድረግም የመፍትሄው ሁለተኛ እና ሁነኛ ምእራፍ ነው። ከግለሰቦች አቅም ግንባታ ባሻገር አሰራሮችንና አደረጃጀቶችን ምቹና ዘመናዊ ማድረግ እንደዚሁ የመፍትሄው አካል ነው፡፡ 
አገሪቱ ያሏት እና በተጨባጭ በእጇ የሚገኙት ኃብቶቿ ሰፊ የሰው ኃይሏና መሬቷ እንደመሆናቸው፤ ይህንን በተጨባጭ መጠቀም በሚችል ይልቁንም ለአቧራ አራጋፊው እና አንሺው ምክንያት እና ምቹ ሁኔታ መሆኑ የታመነበትን በከተሞች የሚታየውን በአቋራጭ የመክበር አስተሳሰብ ሰርቶና ጥሮ ግሮ ኃብት በማፍራት አስተሳሰብ ለመተካትና እዚያው እያለም ሰፊውን ወጣት ኃይል በአምራች ኃይልነት ለማሰማራት እንደሚያስችል የታመነበትን የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ማጠናከር ተገቢ ይሆናል፡፡ 
ሌላው ጉዳይ ዴሞክራሲ የሕልውናና የልማት አጀንዳ መሆኑ ላይ አገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ማድረግ ነው፡፡ የብዝሃነት ምድር በሆነችውና ልማቷ በሕዝቦቿ በጎ ፈቃድና ፍላጎት በሚያፈሱት ጉልበት ላይ በተመሰረተው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የሕልውና ጉዳይ መሆኑ ያለማቅማማት እንዲታመን መስራትም ሌላኛው ስለመፍትሄው መወሰድ ያለበት እርምጃ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብትና እኩልነት መረጋጥ፤ የቡድንና የግለሰብ መብቶች የሚከበሩበት ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓት ከልባዊ ዴሞክራሲ ውጪ ዕውን መሆን እንደማይችል አድምቆ ማስመርም ያስፈልጋል፡፡ የአገራችን ዴሞክራሲ ለፕሮሲጀር ሳይሆን ከልባዊነትና ከሕዝባዊ ወገንተኝነት የሚመነጭ፤ ለሕዝብ ጥቅም የሚቆም እርግጠኛ ዴሞክራሲ መሆኑና ሊሆንም እንደሚገባው  በመንግሥትም ሆነ በመሪ ድርጅቱ በግልፅ ተቀምጧልና፡፡
በምልዓተ ሕዝቡ ተሳትፎ ፈጣን፣ ፍትሃዊ እና ሁሉንም በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርግ ልማትን ማረጋገጥ ዓላማ ያደረገው ሥርዓትና መስመሩ አገራችንን ከጥፋትና ከትርምስ የሚታደገው ይኸው ፈጣን ልማት ብቻ መሆኑን አምኖ ተቀብሏልና፤ እምነቱ መሬት ይይዝ ዘንድ ሲያንጎላጅጅ እየቀሰቀስነው፤ እኛም ስናንጎላጅጅ እያነቃን ከላይ በተመለከቱት እና ተያያዥ መንገዶች ከፈሰስን የትምክህት እና የጠባብነት ኃይሉ ቀዳዳዎች ሁሉ ላይሸነቆሩ በዘላቂነት ይደፈናሉ፡፡ 

No comments:

Post a Comment