በአገራችን ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ የበጎ
አድራጎትን ሥራ በአግባቡ የሚመራ የሕግ ማእቀፍ አልነበረም፡፡ አዋጅ 621/2001 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት በአገሪቱ
የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ያላቸውን ሚና ለመደገፍ እና ለማሳለጥ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ
አዋጅ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 31 ለዜጎች የሰጠው የመደራጀት መብት ተግባራዊ እንዲሆን ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ሲሆን
ዜጎች ተደራጅተው በአገራቸው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና በልማት ሥራዎች ላይ ያለምንም ገደብ እንዲሳተፉ ግልጽ በሆነ መልኩ
ደንግጓል፡፡ በአዋጅ 621/2001 መሠረት የተቋቋመው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት
እንዲስፋፉና ተልዕኳቸውን በሕግ መሠረት እንዲወጡ፤ ብሎም ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሠራር እንዲጎለብት ዓላማ አንግቦ እየሰራ
ይገኛል፡፡ ኤጀንሲው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በአገሪቱ 3115 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ተመዝግበው በሥራ
ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 416 የውጭ አገር በጎ አድራጎት ድርጅቶች፤ 2646 በኢትዮጵያ ውስጥ የተደራጁ በጎ አድራጎት
ድርጅቶችና ማኅበራት፤ እንዲሁም 53 ኅብረቶች ናቸው፡፡
ኤጀንሲው እነዚህ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ
621/2001 በሚፈቅደው መሠረት በሕዝብ ስም ያገኙትን ሀብትና ንብረት በተገቢው መንገድ ሥራ ላይ በማዋል የተቋቋሙለትን ዓላማ
ከግብ እንዲያደርሱ በሚያግዝ መልኩ የድጋፍና የክትትል ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ለምሳሌም፤- በ2008 በጀት ዓመት ኤጀንሲው
የ2756 በጎ አድራጎት ድርጅቶችንና ማኅበራትን ፋይል በመመርመር ዓመታዊ እቅድ፣ ሪፖርት እና የፕሮጀክት ስምምነት ገምግሟል፡፡
ይህንን መነሻ በማድረግም 824 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ላይ የመስክ ክትትል አድርጓል፡፡ በተደረገው ክትትል ሕግን
የተላለፉ 206 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የሚደርስ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የበጎ
አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ከታዩባቸው ችግሮች መካከል ከተቋቋሙለት ዓላማ ውጭ መንቀሳቀስ፤ ያለኤጀንሲው ፈቃድ የባንክ
አካውንት መክፈት፤ የገቢ ምንጫቸውን አለማሳወቅ፣ ዓመታዊ የሥራና የኦዲት ሪፖርት በወቅቱ አለማቅረብ፤ የቋሚ ንብረት ዝርዝር አለማሳወቅ፤
የፕሮጀክት ስምምነት ሳይፈራረሙ መሥራት፤ አስተዳደራዊ ወጪዎችን ከዓላማ ማስፈፀሚያ ወጪዎች ጋር መቀላቀል፤ ከ30% በላይ ለአስተዳዳራዊ ወጪ መጠቀም፤ ልማትን ከሀይማኖት ጋር
ቀላቅሎ መስራት፤ ያለፈቃድ የገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ መሰማራት ለዓብነት የሚጠቀሱ ግኝቶች ናቸው፡፡
በ2008 በጀት ዓመት 122 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ተዘግተዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ 119 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት በራሳቸው ጥያቄ፤ ፈንድ በማጣት እና ለሦስት ዓመታት ምንም እንቅስቃሴ
ባለማድረጋቸው ምክንያት የተዘጉ ናቸው፡፡ በተጨማሪም፤ ባክነር አዶፕሽን ኤንድ ማተርኒቲ ሰርቪስ፤ ግሎባል ኢንፋንቲል እና ሜዲስን
ዱሞንድ የተባሉ 3 የውጭ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በፈፀሙት የሕግ ጥሰት ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ያሉባቸውን ችግሮች ባለማስተካከላቸው
ተዘግተዋል፡፡ አብዛኞቹ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከጅምሩ አቅም ፈጥረው ወደ ሥራ ያልገቡ በመሆናቸው መዘጋታቸው በአገር ላይ የሚያስከትለው
ጉዳት የለም፡፡ የገንዘብ እጥረት ያጋጠማቸው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አዋጁ በፈቀደላቸው በተለያየ የገቢ ማስገኛ ሥራ ላይ ተሰማርተው
ዓላማቸውን ለማስቀጠል ምንም ጥረት አላደረጉም፡፡ በሌላ መልኩ፤ በ2008 በጀት ዓመት መስፈርቱን ያሟሉ 187 አዲስ የበጎ
አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ተመዝግበዋል፡፡ ለ803 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የፈቃድ ዕድሳት ተሰጥቷል፡፡
በአዋጅ 621/2001 መሠረት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ከሚያገኙት
ገቢ ከ70% የማያንሰውን ለዓላማ ማስፈፀሚያ (በቀጥታ ለተጠቃሚው የሚደርስ) እንዲሁም፤ ከ30% የማይበልጠውን ለአስተዳደራዊ
ወጪ እንዲያውሉት ይደነግጋል፡፡ ሆኖም፤ በርካታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ይህንን ሕግ ጠብቀው እየሰሩ አይደለም፡፡
ኤጀንሲው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ሕግን አክብረው
እንዲሰሩ የተለያዩ የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሰርቷል፡፡ ኤጀንሲው ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶም
በዋናነት ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ የቆየው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት በዘርፉ የወጣውን ሕግ አውቀው እንዲተገብሩ መስመር
የማስያዝና የማስተማር ተግባር ቢሆንም፤ በድርጅቶቹና በማኅበራቱ በኩል ሕግን በተሟላ መልኩ አክብሮ በመስራት ላይ አሁንም ብዙ
የሚቀሩ ነገሮች ይታያሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን፤ ኤጀንሲው መፍትሄው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን መዝጋት ነው ብሎ አያምንም፡፡ የበጎ
አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት የሚዘጉት መስራት የሚችሉባቸው ሁሉም አማራጮች ተፈትሸው መቀጠል የማይችሉ መሆናቸው ሲረጋገጥ ብቻ
ነው፡፡
እውነታው ከላይ በዝርዝር የቀረበው ሆኖ እያለ አንዳንድ የአገር
ውስጥና የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የጠራ መረጃ ሳይይዙ፤ ኤጀንሲው በርካታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን እየዘጋ ነው ሲሉ ዘግበዋል፡፡
ለምሣሌ፤- በፍሪደም ሀውስ እና በዶቼ ቬሌ ሬዲዮ ጣቢያ ላይ ኤጀንሲው ከ200 በላይ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ያለአግባብ እንደዘጋ
ተደርጎ የተዘገበው ይጠቀሳል፤ ይሁን እንጂ የተባለው ጉዳይ ሀሰት ነው፡፡ በ2008 በጀት ዓመት በተለያዩ ምክንያቶች የተዘጉ
የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው 122 ብቻ ናቸው፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ሕግን
አክብረው እስከሰሩ ድረስ እንዲዘጉ የሚደረግበትም ሆነ የተደረገበት ሁኔታ የለም፡፡
በተጨማሪም እነዚህ ሚዲያዎች አዋጅ ቁጥር 621/2001 የበጎ
አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት በአገሪቱ ዴሞክራሲ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ እንዳይሰሩ ገደብ አድርጓል፤ የሚል የፈጠራ ሀሳብ በስፋት
አንፀባርቀዋል፡፡ ይህ አስተያየት ሕጉን በአግባቡ ካለመረዳት የመነጨ ነው፡፡ በአዋጅ ቁጥር 621/2001 መሠረት ከ10% በላይ
ገቢ ከአገር ውጭ የሚያገኙ በኢትዮጵያ ውስጥ የተቋቋሙ የነዋሪዎችና የውጭ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት በዴሞክራሲ ሥርዓት
ግንባታ እና በዜጎች መብት ነክ ጉዳዮች ላይ መሥራት አይችሉም፤ ሲል ይደነግጋል። በሌላ መልኩ፤ አዋጁ እነዚህ በጎ
አድራጎት ድርጅቶች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ፈቅዷል፡፡ የገቢ ምንጫቸው 90% ከአገር
ውስጥ እንዲሁም፤ 10% የማይበልጠውን ከውጭ የሚያገኙ በአገሪቱ ዜጎች የተቋቋሙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት በልማት፣ በዴሞክራሲ
ሥርዓት ግንባታና በመብት ነክ ጉዳዮች ላይ መስራት ይችላሉ፡፡ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ የዜጎችን መብቶችና
ጥቅሞች ማስከበር ለኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ብቻ የተሰጡ ናቸው፡፡ አገር በቀል የሙያና የብዙኃን ማኅበራት የሚቋቋሙት
ይህን ዓላማ እውን ለማድረግ ነው፡፡ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ መብት እና ጥቅም ለማስከበር የሚሰራው ሥራ እንደልማቱ ትልቅ ሀብት
የሚጠይቅ አይደለም፡፡ በመሆኑም በዜጎች ብቻ ሊሰሩ የሚችል ነው፡፡ በአጠቃላይ፤ አዋጁ ሁሉም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት
በልማት ሥራዎች ውስጥ እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ አዋጁ የአገርን ደህንነትና ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ
ተቃኝቶ የተዘጋጀ ነው፡፡ ከምንም በላይ ለሠፊው ሕዝብ ጥብቅና የቆመ ሕግ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡
ምንም እንኳን ክፍተቶች ቢኖሩም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ግን
በልማቱ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽዖ እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የኅብረተሰባችንን ችግር በመቅረፍ ረገድ እያደረጉት ያለው ተግባርም
ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት በማመንጨት ክፍተት በሚታይባቸው የልማት ሥራዎች ላይ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በዚህ
ረገድ፤ የኤጀንሲው ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያመለክተው በ2008 በጀት ዓመት 641 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ብቻ
19,155,771,263 ብር ( አስራ ዘጠኝ ቢሊዮን አንድ መቶ ሀምሳ አምስት ሚሊዮን ሰባት መቶ ሰባ
አንድ ሺህ ሁለት መቶ ስልሳ ሶስት ብር) በጀት ይዘው ወደ ስራ ገብተዋል መግባታቸው እንደማሳያ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ይህ ሲታይ በዘርፉ
በሕዝብ ስም የሚመጣው ሀብትና ንብረት በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ መዋል ከቻለ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት በጥቅሉ
ሊያበረክቱት የሚችሉት አስተዋኦ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል በቀላሉ መረዳት አያዳግትም፡፡
ነገር ግን፤ “ሁሉም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ሕግ በሚፈቅደው አግባብ ከአገር ውስጥ እና ከውጭ አገር
የሚሰበስቡትን ገንዘብ በትክክል ለሚፈለገው ዓላማ እያዋሉት ነው ወይ?” የሚለው ጉዳይ የሁሉንም ወገን ጥብቅ ክትትል
የሚጠይቅ ነው፡፡ ለአገር ዕድገትና ብልፅግና የሚሰሩ ድርጅቶችና ማኅበራት እንዳሉ ሁሉ፤ ልማትን ሽፋን
በማድረግ በአቋራጭ ለመክበር የሚንቀሳቀሱ አካላት መኖራቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በአገሪቷ ያሉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ተልዕኳቸው ስኬታማ የሚሆነው
ግልፅነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት መልኩ ተንቀሳቅሰው በቀጥታ ኅብረተሰቡ ከልማት ሥራቸው ተጠቃሚ መሆን ሲችል ነው፡፡ ይህ እውን የሚሆነው ደግሞ፤ ሕግ በአግባቡ ተግባራዊ ሲደረግ
ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ለአገር ካላቸው ጠቀሜታ አንፃር ተገቢው ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ሕግን ተረድተው በአግባቡ እዲሰሩ ድጋፍ
ከተደረገላቸው አቅም ፈጥረው አገሪቷ ሁለተኛውን የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ እውን ለማድረግ በምታደርገው ርብርብ ላይ የበኩላቸውን
አስተዋፅኦ ማበርከት ይችላሉ። እንላለን!
No comments:
Post a Comment