Wednesday, 31 August 2016

የህዝቡን በሰላማዊ መንገድ የመታገል ፍላጎትን ማጠናከር ይገባል!




                                                      ዘአማን በላይ
ለዚህ ፅሑፍ መነሻ የሆነኝ በሀገራችን አንዳንድ ክፍሎች ውስጥ ህዝቡ እያነሳቸው ያሉት የሰላምና የትግል ፍላጎቶች እንዲሁም ኢህአዴግ ሰሞኑን ያወጣው መግለጫ ነው። የሀገራችን ህዝቦች ከትናንት ጨቋኞች የተላቀቁ ብቻ ሳይሆኑ፣ ከእነዚያ አስከፊ ጭቆናዎች የተማሩና የነገ ተስፋን አሻግረው የሚያዩ ናቸው። ይህ ተስፋቸው በፀረ-ሰላም ሃይሎች እኩይ ሴራ እንዳይደናቀፍና ህልማቸው መንገድ ላይ እንዳይቀር በመንግስት አሰራሮች ላይ የሚያጋጥሟቸውን ግድፈቶች በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ጥረት ጀምረዋል።
ይሁንና ይህ ጥረታቸው ግን በፀረ-ሰላም ኃይሎች እኩይ አጀንዳ የሚጠለፍበት ሁኔታ እንደሚኖር በቅርቡ በጎንደርና በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱት ችግሮች አመላካች ሆነው አልፈዋል።
እርግጥ ህዝቡ እዚህ ሀገር ውስጥ በሚከናወኑ መንግስታዊ ስራዎች የሚያሳየው ያለመርካት ስሜት ለሰላማዊ ትግል ያነሳሳው መሆኑ አይካድም። ይህን ስሜት በሰከነና በተደራጀ እንዲሁም ለሀገርና ለህዝብ በሚጠቅም ስሜት መምራትና የሚጠናከርበትንም መንገድ መቀየስ የሚገባ ይመስለኛል። የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፈቃዳቸው ያፀደቁት ህገ መንግስት፤ ማንኛውም ዜጋ ጥያቄዎችን በተናጠልም ሆነ በህብረት የሚያቀርብበትን አሰራርና መብት እንዳስቀመጠ በሚገባ ያውቃሉ።
በተለያዩ ጊዜያትም ይህን መብታቸውን እየተጠቀሙ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ዳሩ ግን ይህን መብታቸውን በሰላማዊ ትግል የሚያጠናክሩነትን ሁኔታ ማመቻቸትና ለዚህም የህዝቡን ፍላጎት ከፀረ-ሰላም ኃይሎች ድብቅ አጀንዳ ጋር ነጥሎ በመመልከት ሰላማዊ ትግሉን ማጎልበት ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆን የለበትም።
ችግሮችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማቅረብና ህገ መንግስታዊ መፍትሔ መሻት የዜጎች ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ነው። ይህ ዴሞክራሲያዊ መብት በፅንፈኞች እንዲሁም በፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ሃይሎች ተጠልፎ ህገ ወጥ በሆነ መስመር እንዳይጓዝ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።
ለነገሩ ፅንፈኞቹና ፀረ-ሰላም ሃይሎቹ ለህዝቡ ያስገኙለት ምንም ዓይነት ፋይዳ የለም። እነዚህ ሃይሎች ሰላሙን አጥቶ የየዕለት ተግባሩን እንዳያከናውን እንዲሁም በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ በተለይም ባለፉት 13 ዓመታት የተገኙትን ስኬቶች ከማስተጓጎል ውጪ የሚያመጡለት ጠብ የሚል ነገር እንደማይኖርም ያውቃል።
የሀገራችን ህዝብ የዛሬ 15 ዓመት ገደማ የተቀጣጠለው የተሃድሶ ንቅናቄ በመንግስት ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራ ፈጣን በሆነ ሁኔታ የተቀየሰና ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደነበር የሚያውቅና ለዚህ ዕውን መሆንም የተንቀሳቀሰ ነው። ለውጥ ማምጣትም ችሏል። የለውጡን ትክክለኛነትና ጥንካሬን ለማረጋገጥም በ50 ዓመት ታሪካችን ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የድርቅ አደጋ አጋጥሞን፤ ይህ ነው የሚባል የውጭ ድጋፍ ሳይገኝ በራስ አቅም መቋቋም መቻሉ ማሳያ ይመስለኛል።
ከተሃድሶው ወዲህ ባሉት ዓመታት በከተሞች ውስጥ የኢንዱስትሪ ልማት መሰረቶችን ማስፋፋት መቻሉ ከህዝቡ የሚሰወር ዕውነታ አይመስለኝም። በተለይም በከተሞች ውስጥ እየተከናወኑ ያሉት የአነስተኛና ጥቃቅን ፕሮግራሞች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው። ምንም እንኳን በከተሞች ያለው የተጠቃሚነት ሁኔታ በተለያዩ ስንክሳሮች ምክንያት የሚፈለገውን ያህል መጓዝ ባይቻልም፣ ከፕሮግራሞቹ በተለይም ወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ብዙ ርቀት መጓዝ እንደተቻለ ህዝቡ በሚገባ ይገነዘባል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም በእነዚህ ዓመታት በከተሞች ውስጥ ሲከናወን የነበረው የአገልግሎት ዘርፍ ተደራሽነትም ዕድገት ማሳየቱ የሚታበይ አይደለም። የእነዚህ ሁሉ ዕድገቶች ድምር መሰረታዊ ውጤት ማምጣት ችሏል። ሌላውን ትተን የቅርቡን ብናስታውስ እንኳን በ2002 ዓ.ም 377 ዶላር የነበረው የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ በ2007 ዓ.ም ወደ 691 ዶላር ከፍ ብሏል። ይህ የሚያሳየውም መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ልማት ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንቀሳቀሱን ነው።
ዜጎች ከልማቱ በፍትሐዊ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ባለፉት 25 ዓመታት በማህበራዊ መስክ ውጤት የተገኘባቸው ስራዎች መከናወናቸውን የሀገራችን ህዝብ የሚዘነጋቸው አይመስለኝም። በትምህርት፣ በጤና እና በመሰረተ-ልማት አቅርቦት ዘርፍ የተከናወኑት ወሳኝ ስራዎች ለዚህ አባባል ሁነኛ አስረጅዎች ናቸው። በበበበበበበበበበበበበበበበበበበበበበበበ
ከእነዚህ ማህበራዊ መስኮች ህዝቡ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን፣ በአኗኗር ዘይቤው ላይም ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ጥረት ተደርጓል። ማንኛውም ሰው ቅድሚያ የሚሰጠው በህይወት የመቆየት ጊዜውን እንደመሆኑ መጠን፤ በተጠናቀቀው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የልማት ዘመን የዜጎች በህይወት የመቆየት የዕድሜ ጣሪያ 64 ዓመት ሆኗል። ይህም መንግስት ሀገሪቱን ከተቆጣጠረበት 1983 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር ወደ 20  ዓመት የሚጠጋ ልዩነት አለው።
እንዲህ ዓይነቱ ለውጥ እንደ እኛ ባለ በማደግ ላይ ለሚገኝ ሀገር ትርጉሙ ከፍተኛ መሆኑ ግልፅ ነው። ህዝቡም በማያሻማ ሁኔታ ይገነዘበዋል። ምክንያቱም በአንድ ታዳጊ ሀገር ውስጥ የሰዎች በህይወት የመቆየት ጣሪያ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከነበረበት ወደ 20 ዓመት የሚጠጋ ጭማሪ ኖረው ማለት፤ በበኑሮ ሁኔታና በጤናው መስክ ከፍተኛ ስራ መከናወኑን እንዲሁም የሀገሬው ህዝብ ከዚህ ጉዳይ በአያሌው ተጠቃሚ መሆኑን ያረጋግጣል።
እንግዲህ እነዚህ ለውጦች የተገኙት ገዥው ፓርቲና እርሱ የሚመራው መንግስት የህዝብን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ርብርብ በማድረጋቸው ነው። እርግጥ እዚህ ላይ አንድ የማይካድ እውነታ ያለ ይመስለኛል። ይኸውም ባለፉት 25 ዓመታት የሀገራችን ህዝብ ቁጥር በእጥፍ ማደጉና በዚያውም ልክ የወጣቱ ሃይል ቁጥር በመጨመሩ የለውጡ ግዝፈት የተጠበቀውን ያህል ሊሆን አለመቻሉ ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ ዜጎችን ላያረካቸውና ስሜት ውስጥም ሊከታቸው ይችላል። ዜጎች መንግስት እያመጣ ያለውን ለውጥ እያወቁት ቢሆን  በመታተል ተገፋፍተው በፀረ-ሰላም ሃይሎች አጀንዳ እንዲዋጡ ሊያደርጋቸው ይችላል።
ለዚህ አባባሌ በቅርቡ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አሰፋ አብዩ በጎንደርና በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ችግር አስመልክተው ከመሰንበቻው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ “…99 በመቶ የሚሆኑት በህገ ወጥ ሰልፉ የተሳተፉ ዜጎች በቂ ግንዛቤ ሳይኖራቸው በቦታው የተገኙ ናቸው።
ከዚህ አንፃር የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ጥቂት ፀረ ሰላም ሃይሎች በህብረተሰቡ ውስጥ ሰርገው በመግባት ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን የሚፃረሩ ድርጊቶችን ሲፈፅሙ ተስተውለዋል” በማለት የገለፁትን ሃቅ መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል። ምክንያቱም ዜጎች ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዩች በተገቢው አኳኋን ተፈፃሚ አለመሆናቸው ስላስመረራቸው የፀረ- ሰላም ሃይሎቹ አካሄድ ትክክለኛ መስሎ ሊሰማቸው ስለሚችል ነው። ኋላ ላይ ግን መሳሳታቸውን የሚያውቁት ሰላማዊ የመብት ጥያቄያቸው የራሳቸው አጀንዳ ባላቸው ጥቂት የሰላምና የልማት ፀሮች መጠለፉን ሲያውቁና በእነርሱ ሳቢያ የተፈጠረው ሁከት ለአላስፈላጊ የህይወትና የንብረት ውድመት እንዲሁም በተከታታይነት የተጀመረው ተጠቃሚነታቸው ሊስተጓጎል እንደሚችል ሲያውቁት ነው።
ይህ መሰረታዊ ዕውነታም ዜጎች የሚደገፉበት መንገድ ካለ ማንኛውንም ጥያቄያቸውን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለማቅረብና ሁሉም ችግሮቻቸው እዚህ ሀገር ውስጥ የተገኘውን ለውጥ በባመጣው መንግስት አማካኝነት ብቻ እንዲፈታላቸው የሚሹ መሆኑን የሚያሳይ ነው። እናም ይህን የዜጎችን ፍላጎት መደገፍና ማጠናከር የግድ ይላል። ለዚህ ደግሞ የህዝብን ድምፅ መስማትና የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ትላልቅ መድረኮችን መፍጠር ያስፈልጋል።
ይህ ሲሆንም ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ ሃሳቡን እየገለፀ ከመንግስት አስፈፃሚዎች ጋር ህጋዊ ትግል ውስጥ ይገባል። የሚፈጠሩ የአሰራር ማነቆዎችንም ማስወገድ ይቻላል። ይህም ትግሉ በቁርጠኛ አመራር ከታገዘና ህዝቡ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዩች ውስጥ የሚኖረው የተሳታፊነት ሚና ተጠናክሮ ከቀጠለ ሰላማዊ ትግሉን የሚያጎለብተው ይሆናል።
ታዲያ ይህን ፅሑፍ በማጠናቀር ላይ እያለሁ የኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለስድስት ቀናት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ መግለጫ ማውጣቱን ተመለከትሁ። በመግለጫው ላይም “…ምንም እንኳ በድርጅታችንና በመንግስት አመራር ዘንድ ሲከሰት የቆየው ያልተስተካከለ ዝንባሌ ይህ የህዝብ ድምፅ በአግባቡ እንዳይሰማና ችግሮቹም በፍጥነት እንዳይቀረፉ ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም፤ መላ የአገራችን ህዝቦች በየአካባቢው የሚታዩ ስህተቶች ይወገዱ ዘንድ ጠንከር ባለ አኳኋን ያካሄዱት ትግል ስራ አስፈፃሚው ለወሰዳቸው የለውጥ አቋሞች ጠንካራ መሰረት ሆኖ አገልግሎናል” በማለት ድርጅቱ ለያዘው የለውጥ አቋሞች የህዝቡ ሚና የማይተካ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
በእኔ እምነት ይህ የመግለጫው ክፍል የሚያሳየው ነባራዊ ሃቅ ቢኖር፣ ገዥው ፓርቲ የህዝብን ድምፅ ዛሬም ይሆን ነገ የሚያከብርና የሚፈጠሩ ችግሮችን ከህዝቡ ጋር በመሆን ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም ያለው መሆኑን ነው።
እርግጥ ለገዥው ፓርቲ የለውጥ አቋሞች ጠንካራ መሰረት ሆኖ ያገለገለው የህዝብ ትግል በአግባቡ ሊመራ ይገባል። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ህዝቡ እዚህ ሀገር ውስጥ ያሉት ሁለንተናዊ ለውጦች የተገኙት በገዥው ፓርቲና እርሱ በሚመራው መንግስት መሆኑን በሚገባ ይገነዘባል። ይሁንና በየቦታው የሚታዩ የአሰራር ክፍተቶች ሲኖሩ ተጠቃሚነቱን እንደሚያሳጡት በመገንዘብ በፅናት እያወገዛቸው ነው።
ይህ ህዝባዊ በሰላማዊ መንገድ የመታገል ፍላጎት እንዲጠናከርና የሚፈለገውን ሀገራዊ ግብ እንዲያመጣ የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ፍላጎቱ እንዲጎለብትና ከህዝቡ በማንኛውም እርካታ ባላገኛቸው አሰራሮች ሚናው የላቀ እንዲሆን ከተደረገ፤ እዚህ ሀገር ውስጥ የሚነሱ ማናቸውም ጥያቄዎች ሰላማዊና በህዝቡ ፍላጎት ብቻ የሚመሩ መሆናቸው አይቀሬ ይመስለኛል።

No comments:

Post a Comment