ዘአማን በላይ
ሁከትና
ብጥብጥ በየትኛውም መስፈርት ህጋዊ ሊሆን አይችልም። የህግ የበላይነትን ይጣረሳል። የህግ የበላይነት ከሌለ ደግሞ ስለ ሰላም ማውራት
ከጉንጭ አልፋነት የሚዘል አጀንዳ ሊሆን አይችልም። ሰላም ከሌለ እንኳንስ በመንግስት ደረጃ ቀርቶ ግለሰቦችም ቢሆኑ ምንም ነገር
ሊከውኑ አይችሉም። በህይወት የመኖር ዋስትናቸም አደጋ ላይ ይወድቃል። ጉልበተኞች ባሻቸው ጊዜ የፈቀዱትን ጉዳይ ያደርጋሉ። መብት
ሰጪና ነሺ በመሆንም ያሻቸውን ይፈፅማሉ። አብዛኛው ሰላማዊ ነዋሪም የእነዚህ ጉልበተኞች ሰለባ መሆኑ አይቀርም።
በተለይም
ህዝቡ መብቱን በሚጠይቅበት ወቅት አጀንዳው በፅንፈኛ ኃይሎች እጅ ከወደቀና ከተጠለፈ የህግ የበላይነት ከምንጊዜውም በላይ አደጋ
ላይ መውደቁ አያጠያይቅም። እነዚህ ሃይሎች በአንድ ወቅት ጀምረውት ያልተሳካላቸውን ሀገርንና ህዝብን የማሸበር ተግባራቸውን በማናቸውም
ወቅቶችና አጋጣሚዎች ሊጠቀሙበት ይችላሉ። እናም የህዝቡ የመብት ጥያቄዎች በእነዚህ ሃይሎች ተጠልፈው የሀግ የበላይነት አደጋ ላይ
እንዳይወድቅ ህዝቡ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል። አሊያ ግን በምንም ዓይነት የማይገናኙት ፅንፈኞች አጀንዳውን እየተቀባበሉ የራሳቸውን
ህገ ወጥ መንገድ ያራምዱበታል።
እርግጥ
ህዝቡ በተለያዩ የመንግስት አሰራሮች ላይረካ ይችላል—በተለይም እንደ መልካም አስተዳዳር ባሉ ጉዳዩች ላይ። ይህ እውነት ነው። ሆኖም
ሀገራችን ውስጥ በህገ መንግስቱ አማካኝነት ዕውን የሆኑ በህግ አግባብ የተዘረጉ ማዕቀፎች አሉ። እነዚህ ህጋዊ ማዕቀፎች ለሁከትና
ለብጥብጥ ቦታ የሚሰጡ አይደሉም። በመሆኑም ህዝቡ የሚያቀርባቸውን ማናቸውንም የመብት ጥያቄዎች ከራሱ ፍላጎት አኳያ እንጂ በፅንፈኛ
ኃይሎች ተታልሎ ምንም ነገር ማድረግ ያለበት አይመስለኝም።
እንደሚታወቀው
ፅንፈኛ ኃይሎች ለጊዜያዊ የጥፋት ተልዕኮ ጋብቻ ካልሆነ በስተቀር ዘላቂ ስምምነትም ይሁን አንድነት የላቸውም። በተለይም የትምክህትና
የጥበት ኃይሎች የሆድና የጀርባ ያህል የማይገናኙ የጥፋት ቡድኖች መሆናቸውን ህብረተሰቡ ሊገነዘበው የሚገባ ይመስለኛል። በአማራ
ክልል ፌዴራላዊ ስርዓቱን የሚቃወሙ ትምክህተኞች ትናንት የከሰረ ፖለቲካቸውን እዚህ ሀገር ውስጥ እውን ለማድረግ ያልቻሉ ናቸው።
የእነዚህ ኃይሎች “ከእኛ በላይ ለአሳር” የሚል ያረጀና ያፈጀ ተረትን ይዘው ሌላውን የህብረተሰብ ክፍል ያጥላላሉ። በተለይም በአማራውና
በሌላው የህብረተሰብ ክፍል መካካል ትልቅ መጋረጃን በመጋረድ አጥር ለማበጀት ይሞክራሉ። ሃቁ ግን የአማራው ህዝብ እንደ ማንኛውም
የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ ባለፉት ስርዓቶች የግፍና የስቃይ ሰቆቃን ሲቀበል የነበረ ነው። በስሙ ከመነገዱ በስተቀር ለእርሱ
ጠብ ያለለት ነገር የለም። ተጠቃሚዎቹ በአማራ ህዝብ የሚነግዱ ጥቂት ኃይሎች ናቸው።
እነዚህ
ሃይሎች ቀደም ሲልም ይሁን በምርጫ 97 ወቅት የተገኘውን አጋጣሚ በመጠቀም የህዝቡን አጀንዳ ቀምተው በጎዳና ላይ ነውጥ ስልጣን
ለመያዝ የሞከሩ የከሰሩ ፖለቲከኞች መሆናቸውን ህዝቡ በሚገባ ያውቀዋል። ይሁንና ዛሬም ይህ ትምክህተኛ ሃይል በክልሉ ውስጥ ፌዴራላዊ
ስርዓቱን በመፃረር የህዝቡን የመልካም አስተዳደር አጀንዳዎችን በመቀማት ለሁከት ተግባር ሲጠቀምበት ይስተዋላል። በጎንደርና በአካባቢው
በሰላማዊ ሰልፍ ሰበብ የተከሰቱት ችግሮች በእነዚሁ ሃይሎች የተቀነባበረ መሆኑን በወቅቱ ከታዩት መፈክሮች ለመረዳት የሚከብድ አይመስለኝም።
አዎ!
ሰልፎቹ ላይ የተመለከትናቸው መፈክሮች ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን የሚያጥላሉና በስርዓቱ ላይ የሚነዙ አሉባልታዎችን
ጭምር የያዙ ናቸው። የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተንተርሰው ነገር ግን ጽንፈኛ የፖለቲካ አስተሳሰቦች የተራመዱበት ሰልፍ
ነበር። በጥቅሉ የትምክህተኞቹ ቅስቀሳዎች ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ የታለሙ እንደነበሩ ግልጽ ነው።
ያም ሆኖ
ግን እዚህ ላይ ግንዛቤ መያዝ ያለበት አንድ ጉዳይ ያለ ይመስለኛል። እርሱም በየትኛውም መስፈርት ቢሆን የፅንፈኝነት ፖለቲካ አራማጆች
ለአማራ ህዝብ አሁን ካለው ህገ መንግስታዊ ስርዓት የተሻሉና ወገንተኛ ሊሆኑ አይችሉም። የአማራ ህዝብ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር
በመሆን ይህን ስርዓት ለማምጣት የታገለና ያታገለ ነው። ይህ ስርዓት የእርሱው ትግል ውጤት ነው። ከስርዓቱም ተጠቃሚ መሆኑን በተግባር
አረጋግጧል። በስርዓቱ ውስጥ በነባራዊነት ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች ቢኖሩም፤ ዛሬም እንደ ትናንቱ እነዚያን ችግሮች በውይይትና በመነጋጋር
ማስተካካልና ማረም ያለበት እርሱ እንጂ ያለፉት ስርዓቶች ተጠቃሚ የነበሩ ጥቂት ፅንፈኛ ፖለቲከኞች ሊሆኑ አይገባም። እናም ፅንፈኛ
ፖለቲከኞች ዛሬም መልካም አስተዳደርን የመሳሰሉ ችግሮቹን ጠልፈውበት ስርዓቱን አደጋ ላይ እንዲጥሉበት መፍቀድ ያለበት አይመስለኝም።
በተለይም ጽንፈኛው የትምክህት ሃይል ስርዓቱን ለማፍረስ በምንም የማይጣመረውን የጥበት ሃይልን እስከ መደገፍ የሚደርስ ተግባርን
እንደሚከተል ባህሪውን ጠንቅቆ ማወቅ የሚገባ ይመስለኛል።
እርግጥም
የትምክህትና የጥበት ኃይሎች የእሳትና ጭድ ዓይነት ግንኙነት ያላቸው ናቸው። በአንዱ ውስጥ አንዱ ሊኖር አይችልም። ሁለቱም እንደ
ዜሮ ድምር ጨዋታ የሚጠፋፉ ሃይሎች ናቸው። የሚያመጡት ጥምረትም ሃሳባቸውን በዜሮ የማባዛት ያህል ነው። ትምክህተኛው “እኔ ነኝ
የበላይ” የሚል ፍፁም ኢ-ዴሞክራሲያዊነትን ሲያቀነቅን፣ ጠባቡ ሃየል ደግሞ ሌሎች ብሔሮችን በጠላትነት በመፈረጅ ራሱን በመነጠል
ያቀነቅናል። ሁለቱም በፀረ-ዴሞክራሲያዊነት መንገድ ላይ የሚተሙ በመሆናቸው በመቻቻል አብሮ ስለ መዝለቅ የሚዘምሩ አይደሉም። እናም
ቁርኝታቸው ጊዜያዊና “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚል ትስስር የተያያዘ መርህ አልባ “ወዳጅነት” ነው። በጎንደር ላይ የታየውም
ይኸው ነው። ትምክህተኛው በዚህ የእከክልኝ ልከክልህ መርህ በመመራት ጠባቡን ቡድን የሚደግፍ መፈክር ይዞ እስከ መውጣት ደርሷል።
ይሁንና
ቀደም ሲል በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በታየው ሰላማዊ ያልሆነ ሰልፍ ላይ ጠባቡ ቡድን በሀገሪቱ ውስጥ በአሸባሪነት የተፈረጀውን
ኦነግ ባንዴራን ይዞ ወጥቷል። ይህ የጥበት ቡድን ደግሞ ፍላጎቱ ትምክህተኛው የሚፈልገውንና ይዞት የወጣውን የቀድሞውን የአሃዳዊ
ስርዓት ባንዴራን የሚፃረር ነው። ይህም የሁለቱ ቡድኖች ፍላጎት ሆድና ጀርባ መሆኑን ያሳያል። ያም ሆኖ ግን እነዚህ ሃይሎች ለአንድ
ቀንም ቢሆን በጥፋት ጎዳና አብረው የመሰለፍ አዝማሚያ ያላቸው መሆኑን በገሃድ አሳይተዋል። የዚህ ድምር ውጤትም ህገ መንግስቱን
በመፃረር ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን የመናድ ፍላጎት መሆኑን ህዝቡ ሊገነዘበው የሚገባ ይመስለኛል።
እርግጥ
ትምክህተኛውም ይሁን ጠባቡ ቡድን በህዝቡ ሰላማዊና በህገ መንግስቱ መሰረት ሊፈቱ በሚችሉ አጀንዳዎች ላይ እየተረማመደ የህግ የበላይነትን
ከመጣሱም ባሻገር ህዝቡ ዕለታዊ ኑሮውን እንዳይመራና ከህግ ጋር እንዲጋጭ ከማድረግ አይቦዝንም። ቀዳዳ የተገኘ መስሎ ሲታየው ጥቂት
ተከታዮቹን በማቀፍ የህዝቡን የዕለት ተዕለት ኑሮን በእኩይ ሴራው ከማወክ አይመለስም። ለዚህ ደግሞ ሰሞኑን በጎንደር ከተማ ላለፉት
ሶስት ቀናት የተካሄደው ራስን የማቀብ ተግባር ተጠቃሽ ይመስለኛል።
ይህ የእቀባ
ድርጊትም ዜጎችን ከተለምዷዊ የአኗኗር ዘይቤያቸው የሚያግድና የቤታቸው እስረኛ እንዲሆኑ የሚያደርግ ያልተገባ ተግባር ነው። እርግጥ
የትኛውም ህዝብ ሁከትን ሊደግፍ አይችልም። ከለመደው የአኗኗር ሁኔታ ውጪ ሆኖም በኑሮው ላይ ስንክሳር እንዲፈጠርበት አይሻም። ከሁሉም
በላይ ደግሞ በውይይት ካልሆነ በስተቀር፣ በሁከትና ራስን በማቀብ መብትን ማረጋገጥ እንደማይቻል ያ ህዝብ በሚገባ የሚያውቅ ይመስለኛል።
ስለሆነም የህዝብን ጥቅም የማያረጋግጡ የፅንፈኛ ፖለቲከኞችን የጥፋት ቁርኝት መንገድን በመረዳት ህዝቡ የእነዚህን ሃይሎች ፍላጎት
ሊዘጋው ይገባል እላለሁ።
No comments:
Post a Comment