ኢብሳ
ነመራ
በ2007
ዓ.ም. የተከሰተው ኤልኒኖ የተሰኘው የአየር ንብረት መዛባት በኢትዮጵያ ላይ ያስከተለው የምግብ እጥረት ተጽእኖ ይፋ ከተደረገ ሰኔ
2008 ላይ አንድ ዓመት አለፈው። ያለፈው ዓመት ድርቅ ያስከተለው የግብርና ሥራ መሰተጓጎል ከ10 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ
የሚሆኑ ዜጎች የአስቸኳይ ግዜ እርዳታ ጠባቂዎች እንዲሆኑ አድርጎ መቆየቱ ይታወቃል። ይህ ሁኔታ አሁን መቀየር ጀምሯል።
የበልግና የክረምት ዝናብ በመጠንም በስርጭትም በመስተካካሉ ነው ሁኔታው መቀየር የጀመረው። በተለይ ባለፈው በልግ የነበረው
የተስተካካለ ሊባል የሚችል የዝናብ ሁኔታ በበልግ አብቃይ አካባቢዎች የነበረውን የተረጂዎች ቁጥር እንዲቀንስ ማድረጉን የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ
ባለፈው አርብ ነሃሴ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣
ከሚመለከታቸው አባላት ጋር በመሆን በበልግ አብቃይና አርብቶ አደር አካባቢዎች የምግብ ዋስትና ጥናት ማድረጉን አስታውቋል። ጥናቱ በሰብል አብቃይ አካባቢዎች ከግንቦት 28 እስከ ሰኔ 12 2008 ዓ.ም ድረስ፤ እንዲሁም በአርብቶ አደር አካባቢዎች ከግንቦት 28 እስከ ሰኔ 18 2008 ዓ.ም ድረስ ነበር የተካሄደው፤
በጥናቱ የዝናብ ሁኔታ፤ የእርሻ ስራ እንቅስቃሴ፤ በማሳ ላይ ያለዉ የሰብል ሁኔታ፤ የምርት ግምት፤ የግጦሽ እና የዉሃ አቅርቦት፤ የእንስሳት አቋም እና ምርት ሁኔታ፤ የሰው እና የእንስሳት ጤና እንዲሁም በወቅቱ እየቀረበ የሚገኘው ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎች የስርጭት ሁኔታ እና የማህበረሰቡን የምግብ ዋስትና ሁኔታ መገምገሙን ኮሚሽኑ አስታውቋል። በዚህ ግምገማ ውጤት መሰረት ቀደም ሲል 10 ነጥብ 241 ሚሊዮን የነበረው የአስቸኳይ ገዜ እርዳታ ጠባቂ ቁጥር ቀንሶ ለቀጣይ 5 ወራት ማለትም፤ ከነሐሴ 2008 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2009 ዓ.ም. ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶች እርዳታ የሚያስፈልገው ሕዝብ ቁጥር 9,741,576
መሆኑ በጥናቱ ተረጋግጧል። የተረጂዎቹ ቁጥር በግማሽ ሚሊዮን ገደማ ቀንሷል ማለት ነው።
የዳሰሳ ጥናቱ ሰብል አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ማለትም፤ በአማራ፤ በኦሮምያ፤ በደቡብ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች፤ በአፋር እና በሶማሌ ክልሎች ለ15 ቀናት 19 አጥኝ ቡድኖችን በማሰማራት ነበር የተከናወነው።
በአርብቶ አደር አካባቢዎች ደግሞ ማለትም በአፋር፣ በሶማሌ ክልሎች እንዲሁም በኦሮምያ ክልል በቦረና እና በጉጂ ዞን ለ21 ቀናት። በ6 ክልሎች በሚገኙ 38 ዞኖች በተከናወነ ጥናትም 210 ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
በጥናቱ ላይ በብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስተባባሪነት የፌዴራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፤ የክልል ሴክተር ቢሮዎች፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች፤ የሁለትዮሽ ስምምነት ያላቸውና ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መሳተፋቸውን ከኮሚሽኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
ያለፈው ዓመት የድርቅ ተጽእኖ እየቀነሰ እንዲመጣ በማድረግ ረገድ ፈጥነው
የሚደርሱ ሰብሎችን በመዝራት ምርት እንዲገኝ መደረጉ ጉልህ
አስተዋጽኦ እንዳለው የብሔራዊ
የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አመልክቷል። በአማራ ክልል ፈጥነው የሚደረሱ ሰብሎችን በመዝራት በሶስት
ወራት ውስጥ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱ ለዚህ ማሳያነት እንደሚጠቀስም ኮሚሽኑ አስታውቋል።
የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ እደላው እስከ መጪው ታህሳስ ማለትም የመኸር ምርት
እስከሚሰበሰብበት ጊዜ እንደሚቀጥል ያመለከተው ኮሚሽኑ፤ ለዚህም አሁን በክምችት ብቻ 451 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ እንደሚገኝ፤ በያዝነው የነሃሴ ወር
ወደብ ላይ የሚደርስ 499 ሺህ 536 ሜትሪክ ቶን ስንዴ በግዢ ሂደት ላይ መሆኑንም አስታውቋል። ከጥራጥሬ፤ ከዘይትና መሰል ምርቶች ጋር ተያይዞ ምንም ዓይነት እጥረት እንደሌለም ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
እንግዲህ
ባለፈው አንድ ዓመት ድርቅ ያስከተለው የምግብ እጥረት ለኢፌዴሪ መንግሥት ትልቅ ፈተና ነበር። ይሁን እንጂ፤ ድርቁ ባስከተለው
የምግብ እጥረት ሳቢያ የአንድም ሰው ህይወት ሳይጠፋ እነሆ የምግብ እጥረት ተጋላጮቹ ቁጥር ለቀንስ ችሏል። ድርቁ ያስከተለው
የምግብ እጥረትና የምግብ እጥረቱን ተጽእኖ ለመቋቋም መንግሥት ያደረገውን ጥረት ለመረዳት ያለፈውን አንድ ዓመት ክራሞት መለስ
ብለን እናስታውስ።
በኤልኒኖ
ክስተት ምክንያት የተፈጠረው የበልግ ዝናብ መጥፋት ያስከተለው የምግብ እጥረት ተጽእኖ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የተደረገው ከአንድ
ዓመት በፊት ሰኔ 2007 ዓ.ም. ላይ ነበር። ሰኔ 2007 ዓ.ም. ላይ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዜጎች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸው ይፋ
ሆነ። የኤልኒኖው ክስተት ተጽእኖ ቀጥሎ፤ ከበልግ በተጨማሪ የክረምቱም ዝናብ የስርጭት መዛባትና እጥረት ገጠመው። የበልጉ ተጽዕኖ
ከክረምቱ ጋር ተዳምሮ ነሃሴ ላይ ለምግብ እጥረት የተጋለጡት
ሰዎች ቁጥር ወደ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ከፍ አለ። ጥቅምት 2008 ዓ.ም. መግቢያ ላይ ለምግብ እጥረት የተጋለጡ የአስቸኳይ ግዜ
እርዳታ ፈላጊዎቹ ቁጥር 8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ደረሰ። በዚህ አላበቃም፤ የመኸር ምርት በሚሰበሰብበት በጥር ወር ላይ የአስቸኳይ ጊዜ
እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ደረሰ። ባለፈው ሳምንት ይህ አሃዝ በግማሽ ሚሊዮን መቀነሱ እስከተነገረበት ጊዜ
ድረስ ለተከታታይ ሰባት ወራት ያህል ጊዜ የአስቸኳይ ግዜ የምግብ እርዳታ ይቀርብላቸው የነበሩ ዜጎች ቁጥር 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን
ነበር።
ያለፈው
ዓመት ኤልኒኖ ያስከተለው ድርቅ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ካገጠሙት ሁሉ የከፋ ነበር። ይሁን እንጂ፤ የኢፌዴሪ መንግሥት ድርቁ
የምግብ ተፅእኖ ማስከተል እንደጀመረ ጉዳቱን ይፋ አድርጎ በድርቁ ምክንያት የአንድም ሰው ህይወት መጥፋት የለበትም፤ የሚል
ግልጽ አቋም ይዞ በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ ርብርብ አድርጓል።
ድርቁ
የምግብ እጥረት ማስከተል በጀመረበት ሰኔ 2007 ዓ.ም. ላይ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ለማቅረብ የሚውል ለመነሻ በቂ
የሆነ የመጠባበቂያ የእህል ክምችት ነበር። የምግብ እጥረቱ ማጋጠም በጀመረበት ወቅት 451 ሺህ ሜትሪክ ቶን (4 ሚሊዮን 451
ሺህ ኩንታል) የመጠባበቂያ የእህል ክምችት ነበር።
እስካሁን
ባለው ሁኔታ ድርቁ ያስከተለውን የምግብ እጥረት በመቋቋም ረገድ የኢፌዴሪ መንግሥት የመሪነቱን ድርሻ ወስዷል። ለዚህም 400
ሚሊዮን ዶላር ወይም ከስምንት ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ወጪ አድርጎ ድርቁ ላስከተለው ተፅዕኖ ምላሽ ሰጥቷል። የፌደራል መንግሥት
ከክልላዊ መንግሥታትና ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር የፈጠረው የድርቁን ተፅዕኖ የመመከት አቅሙ ከዚህ ቀደም ከተከሰቱ ተመሳሳይ
አጋጣሚዎች አኳያ ሲመዘን በከፍተኛ መጠን ጨምሮ እናገኘዋለን። ለጋሾች ቃል ከገቡት ውስጥ እስካሁን መስጠት የቻሉት ብዙም
ከግማሽ የዘለለ አይደለም። ይሁን እንጂ፤ በተለይ ባለፉት 13 ዓመታት የተመዘገበው ዕድገት ቀጣይነት በድርቁ ተፅዕኖ ምክንያት ሳይደነቃቀፍ
መቀጠል እንዲችል የለጋሾች የውጭ ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት እርዳታውን ለማግኘት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ሰኔ 21 ቀን 2008 ዓ.ም. የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም
በኒወዮርክ ከተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ፀሃፊ ስቴፈን ኦብሪዮን ጋር የለጋሽ ተቋማት ተወካዮች
በተገኙበት በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።
በዚህ ውይይት ዶ/ር ቴድሮስ አድሓኖም ድጋፍ ሰጪ አካላት ለድርቁ ቃል ከገቡት ውስጥ የለገሱት 54 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልፀው፤ ቃል የተገባውን እርዳታ በሙሉ መስጠታቸው አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው ነበር። በአንዳንድ ቆላማ አካባቢዎች
ሊያጋጥም የሚችለውን የዝናብ እጥረት ተፅእኖ ለመቀነስ የውሀ እቀባና ተያያዥ የዘላቂ ልማት ሥራዎች ለማከናወን፤ እንዲሁም በያዝነው ክረምት ከመጠን ያለፈ ዝናብ ሊጥል የሚችልበት ሁኔታ መኖሩ ስለተተነበየ፤ በዚህም ምክንያት
ሊያጋጥም የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመቋቋም ድጋፎች እንዲጠናከሩ፤ የተባባሩት መንግሥታት ድርጅትም እገዛ እንዲያደርግ አሳስበው ነበር።
እንግዲህ፤ በፅሁፉ መግቢያ ላይ የብሔራዊ
የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ሰሞኑን ያወጣውን
መግለጫ ጠቅሰን እንደተመለከትነው፤ በበልግ የዳሰሳ ጥናት የተረጂዎች ቁጥር በግማሽ ሚሊዮን ቀንሷል። የዘንድሮ የመኸር እርሻም በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች በፍጥነት እንዲያገግሙ የሚያስችል መሆኑን የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር በሰኔ ወር ላይ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል። አጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ
የምግብ እርዳታ አሰጣጡ የመኸር ምርት ከተሰበሰበ በኋላ ሙሉ በሙሉ ይቆማል ተብሎ ይጠበቃል። ከጥር 2009 በኋላ። የሴፍቲ ኔት
እርዳታ ግን ይቀጥላል።
የሴፍቲ ኔት እርዳታ በድርቅ ምክንያት የተፈጠረ ሳይሆን በቤተሰበ ደረጃ የምግብ
ዋስትና ያልተረጋጋጠ በመሆኑ የተፈጠረ ነው።
በልግ በጥሩ ሁኔታ እንዳለፈ ሁሉ የክረምቱም የዝናብ ስርጭት የተሰተካከለ እንደሚሆን
የሚቲዮሮሎጂ ትንበያ አመልክቷል። የተስተካከለውን የክረምት ዝናብ በአግባቡ በመጠቀም ጥሩ የመኸር ምርት ለማግኘት ዝግጅት
እየተደረገ ይገኛል። በመኸር እርሻ 14 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈንና 301 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ ነው። የዝናቡን ስርጭትና የአርሶ አደሩን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በማቅረብ እቅዱን ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አስታውቋል።
የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር በዘንድሮው የመኸር እርሻ ለሶስት
ዘርፎች ሊውሉ በሚችሉ ሰብሎች ላይ ትኩረት መደረጉን በሰኔ ወር ላይ ማስታወቁ ይታወሳል። እነዚህም
ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ፤ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ እና ለምግብነት የሚውሉ ሰብሎች ናቸው። ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶች ተለይተው በተመረጡ አካባቢዎች በከፍተኛ ደረጃ ምርታማነትን እና ጥራትን ከገበያ ጋር ለማስተሳሰር የሚያስችል እቅድ ተነድፎ ወደ ትግበራ ተገብቷል። እንዲሁም ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ በተለይም ሰሊጥ እና ጥራጥሬ ሰብሎችን እያንዳንዳቸውን በእቅድ በመያዝ የሚመረትባቸውን አካባቢዎች በመምረጥ የተለየ ድጋፍ፤ የግብዓት አቅርቦት እና የክትትል ሥርዓት ከፌዴራል እስከ ቀበሌ በመዘርጋት እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።
በተጨማሪም በሄክታር ሊገኝ የሚችለውን ምርት የማሳደግ ግብ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን ያመለከተው ሚኒስቴሩ፤
ይህም የአርሶ አደሩን ገቢ በመጨመር ተጠቃሚነቱን እንደሚያሳድግ፤ በተለይ የኤልኒኖ
የአየር ክስተት በአለፈው ዓመት ምርት ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ በመቀነስ ረገድ የላቀ ሚና እንደሚኖረው አመልክቷል።
ይኸው ከእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከላይ
የተገለፁትን የመኸር የእርሻ ሥራ እቅዶች ለማሳካት የዝናብ ስርጭትን መሰረት ያደረገ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተከናውኗል። በዘንድሮው ክረምት የዝናቡ ስርጭት በአንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ መጠን ሲኖረው፤ በተወሰኑ ቆላማ አካባቢዎች ደግሞ ዝቅተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል። የዝናቡ ሁኔታ የተስተካከለ የሆነባቸውን፤ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ የሚያገኙ እንዲሁም እርጥበት አጠር የሆኑ አካባቢዎችን መሰረት በማድረግ ለባለሙያዎችና ለአርሶ አደሮች ስልጠና ተሰጥቶ ወደ ተግባር ተገብቷል። ዝናብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ውኃን ከማሳ ውስጥ ማጠንፈፍ የሚያስችል፤ ውኃ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ደግሞ በማሳ ላይ ውኃን ማቆየት የሚያስችል ስልጠና ነው የተሰጠው፤
በተሻሻለ የግብርና ቴክኖሎጂ ስርፀት ረገድ ባለፉት ዓመታት በተግባር የተገኙ ተሞክሮዎችን ሁሉም አርሶ አደሮች በጋራ በሚያደርጉት የተቀናጀ እና የተደራጀ የሰብል ልማት እንቅስቃሴ ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛሉ። ለዚህም የየአካባቢውን የአፈር የማዕድን ይዘት ጉድለት በመሙላት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችል 650 ሺህ ሜትሪክ ቶን አምስት ዓይነት ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ በመሰራጨት ላይ ይገኛል።
የምርጥ ዘር አቅርቦትን በተመለከተም፤ በየክልሎቹ
ከሚቀርበው በተጨማሪ በፌደራል መንግስት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርጥ ዘር ተዘጋጅቶ ለአርሶ አደሮች
ተሰራጭቷል።
አርሶ አደሩ በቁጠባና ብድር ተቋማት አማካኝነት ማዳበሪያና ምርጥ ዘር የሚያገኝበት ሥርዓት መዘርጋቱንና በተለይም በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ብድር በስፋት እንዲቀርብላቸው መደረጉም ታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ ቀደም ሲል የወሰዱትና ያልከፈሉት ብድር ያለባቸው አርሶ አደሮች የመክፈያ ጊዜያቸው እንዲራዘምላቸው ተወስኗል።
እንግዲህ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገለፅ እንደቆየው፣ ያለፈው ዓመት ድርቅ
ያስከተለውን የምግብ እጥረት ተጽእኖ መቋቋም ተችሏል። በተለይ ኤልኒኖ የተሰኘው የአየር ንብረት መዛባት ክስተት በአመዛኙ ከሰው
ቁጥጥር ውጪ በመሆኑ በቀጣይ ዓመታትም ሊያጋጥም ይችላል። በ2007 ዓ.ም. የተከሰተውና በአስከፊነቱ በሃምሳ ዓመታት ውስጥ ታይቶ
የማይታወቅ የተባለው ኤልኒኖ ያስከተለውን የምግብ እጥረት ተጽእኖ በሰው ህይወት ላይ ምንም ጉዳት ሳያስከትል መቋቋም መቻሉ
ለመከላከል ያለውን ብቃት ከማረጋገጥ ያለፈ በቀጣይ ተመሳሳይ ችግር ቢከሰት ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ትምህርት ሰጥቶ
አልፏል። ድርቅም ሆነ ሌላ የተፈጥሮ አደጋ የሚያስከትለውን ተፅእኖ በተደራጀና በተቀናጀ አሰራር መከላከል የሚያስችል ልምድ
ማካበትም አስችሏል።
No comments:
Post a Comment