Wednesday, 31 August 2016

ስለሰላማችን 11ኛውን ሰአት ማለፍ አይገባም !!


ስሜነህ
ሃገሪቱ ትልቅ የሆነውን የአገር ጉዳይ በረሱ እና፣ ለአቋራጭ የፖለቲካ ሥልጣን ብቻ በሚደረግ ኃላፊነት የጎደለው አጓጉል ድርጊት በተጠመዱ በውጭ ሃይሎች ሰላሟ አደጋ ለይ እየወደቀ ለመሆኑ ማህበራዊ ሚዲያዎችን እና እነርሱን ተከትሎ የሚተጋተገውን ህብረተሰብ በመመልከት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በእርግጥ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚተላለፉት መልእክቶች በሙሉ ግለሰቦቹን ይወክላሉ ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም የነዚሁ ቅጥረኞችም በስፋት በተለያየ ስም እንደሚቧጭሩ ከመልእክቶቹና በውጭ ከሚገኙት ሃይሎች መሰረታዊ ባህሪ ለመገንዘብ ስለማያዳግት። በዚህም ተባለ በዚያ መነጋገርንና መደማመጥን እርም ያለውና ምክንያታዊነት የጎደለው የነዚህ ሃይሎች ሰበካ በየማህበራዊ ድረገጹ የፈጠረው ሽኩቻ ለአገር ህልውና የሥጋት አደጋ የመደቀኑ እውነትነት ነው፡፡ ዴሞክራሲ ከሌለ ሰላም የለም፡፡ ሰብዓዊ መብት ካልተከበረ መረጋጋት አይታሰብም፡፡ መነጋገርና መደማመጥ ከሌለ ጉልበተኞች ይበዙና ለዕልቂት የሚዳርግ ቀውስ ይከተላል፡፡ በዚህ ላይ ብሔርን፣ ማንነትን፣ የፖለቲካ አመለካከትን፣ ሃይማኖትንና መሰል ልዩነቶችን በመንተራስ ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የጥላቻ ንግግሮች መሰራጨታቸው በይዘትም በመጠንም ቀጥለዋልና አንድ ነገር ካልተባለ እና ህዝቡም ከዝምታ ወጥቶ የመፍትሄው አካል መሆን ካልጀመረ አደጋው ከባድ ነው፡፡
ቀልድና ብሽሽቅ ይመስሉ የነበሩት የጥላቻ መልእክቶች ላይ በውጭ የሚገኙት ምቾት ያንዘላዘላቸው ሃይሎች ሌላ ጥላቻ እየደመሩበት ለአገርና ለሕዝብ ምንም ዓይነት ፋይዳ የሌላቸው የጥፋት ድግሶች እየተዘጋጁ መሆኑንም ህዝቡ ማጤንና አቋሙን ማሳወቅ ያለበት ሰአት አሁን ነው፡፡ አሁን እኮ ፈጽሞ ኃላፊነት የማይሰማቸው ወገኖች ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመቆጣጠር አገር የሚበትኑ ፕሮፓጋንዳዎችን እየነዙ እንጂ የሃገርን ሰላም ለመጠበቅ አንዳች ፋይዳ ያላቸውን ቃላት እየሰነዘሩ አይደለም ፡፡ በዚህ ዓይነቱ ጊዜ ደግሞ ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ወሳኝ ሆነው መውጣት አለባቸው፡፡
በሃገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ባለቤት የሌላቸው በርካታ የተቃውሞ ሠልፎች ተካሂደዋል፡፡ አሁንም በውጭ ሆነው ኬክ በሚያኝኩና ውስኪ በሚያንቆረቁሩ ሃይሎች ስለዳቦ እና ስለንጹህ መጠጥ ውሃ የሚተጉ ሃይሎችን ባለቤት አልባ ወደሆነው አደባባይ እየገፉ መሆኑ በግልጽ ሊታወቅ ይገባል።
እንዲህ ዓይነቶቹን የተቃውሞ ሠልፎች የሚመራቸው አካል ስለመጥፋቱ እና ባለቤት አልባ ስለመሆናቸው በአደባባዮቹ ላይ ያየናቸው የጥያቄዎቹ አቀራረብ ገጽታቸው እየተለወጠ ለዜጎች ሕይወት ሕልፈት፣ ለአካል ጉዳትና ለንብረት ውድመት ምክንያት ከመሆናቸው በላይ አስረጅ የለም፡፡ ሰላማዊ ተቃውሞ ህገ መንግስታዊ መብትና በሂደቱም የህይወትና የንብረት ውድመት አይኖርም፤ ምክንያቱም ባለቤት ስላለው በስርአት ይመራል፤ ተጠያቂነት ባለበት ቦታ ላይ ሃላፊነት ስለሚኖር ።
በጥያቄዎቹ አቀራረብ ስሜታዊነትና ዘረኝነትን የሚያቀነቅኑ በመሆናቸውም ሳቢያ ከዜጎች ጉዳት በተጨማሪ ለአገር ህልውና ጠንቅ የሆኑ ሥጋቶች ተፈጥረዋል፡፡ የዜጎች ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች በአግባቡ ቀርበው መፈታት ሲገባቸው፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎች በሚቀሰቀሱ የጥላቻ ንግግሮች እየተዋጡ፣ አንዳንዴም የጥያቄዎቹ መልዕክት በሚገባ ሳይተላለፍ ውጤቱ ትርምስና ውድመት እየሆነ ነው፡፡ ጥያቄ ባላቸው ወገኖችና ምላሽ መስጠት በሚገባው መንግሥት መካከል መኖር የሚገባው የመተማመን ድልድይ ተሰብሮ አየሩን የሞሉት በማንነት፣ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አቋምና በመሳሰሉት ላይ ያጠነጠኑ የጥላቻ ንግግሮች ናቸው፡፡ ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ድምፅ ጠፍቶ የአጥፊዎች ድምፅ በጉልህ እየተሰማ ነው፡፡ ለአገር ህልውና ለሕዝቡ በሰላም አብሮ መኖር ጠንቅ የሆነ የጥፋት ድምፅ እንዲህ ሲስተጋባ ደግሞ ሁሉም ዜጋ አደባባይ ወጥቶ ሃይ ሊላቸውና ትክክለኛውን አቅጣጫ ሊያሳውቃቸው ይገባል፡፡
አገርን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶችና ከሚቃጡ አደጋዎች መጠበቅ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የጥፋት ሃይሎቹ እናት፣ አባት፣ ወንድም፣ እህት ወዘተ….የሁሉም ዜጎች የጋራ ኃላፊነት ነው፡፡ ለአገር ነፃነት፣ ሰላምና ብልፅግና መመኘት፣ ምኞትንም ወደ ተግባር መለወጥ የሚቻለው ዜጎች ለአገራቸው በተገቢው መጠን አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ብቻ ነው፡፡ ዜጎች በገዛ አገራቸው ጉዳይ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸውና አስፈላጊውን አስተዋጽኦ በምልዓት እንዲያበረክቱ ደግሞ፣ ከምንም ነገር በላይ ብሔራዊ መግባባት አስፈላጊ ነው፡፡ መንግሥት እንደ መንግሥትነቱ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሲወጣ፣ የተለያዩ አቋሞች ያሉዋቸው የፖለቲካ ኃይሎች በነፃነትና በኃላፊነት ሲንቀሳቀሱና የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች ሁሉ ከስሜት የፀዱና ምክንያታዊ ሲሆኑ እንጂ ታዋቂነትን እና አዋቂነትን ከለላ አድርገው ለከርሳቸው በሚማስኑ የውጭ ጥገኛ ሃይሎች አለመሆኑንም ህዝቡ ተገንዝቦ ማስገንዘብ ግድ የሚለው ሰአት ቢኖር አሁን ነው። የመንግስት እንደተጠበቀ ሆኖ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ዕድሉ የሚኖረውና እያንዣበበ ካለው የአደጋ ሥጋት መውጣትም የሚቻለው ህዝቡም በዚህ መልኩ ሃላፊነቱን ሲወጣ ብቻ ነው።
ስለሁሉም መሻታችን የሕግ የበላይነት ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ሲኖር የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ይከበራሉ፡፡ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ተጠቃሚነት ይኖራል፡፡ ቅሬታዎች ሲኖሩ የሚፈቱበት ሕጋዊ አሠራር ይሰፍናል፡፡ የመልካም አስተዳደር ዕውን መሆን ብቻ ሳይሆን ፍትሕ ለሁሉም ተደራሽ ይሆናል፡፡ ሙስና አከርካሪው ይሰበራል፡፡ ሕገወጥነት አደብ ይገዛል፡፡ ለአሉባልታና ለሐሜት የሚዳርጉ እኩይ አሠራሮች ይወገዳሉ፡፡ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር፣ ከሽኩቻ ይልቅ መነጋገር፣ ከኩርፊያ ይልቅ መደማመጥ፣ ከጠባብ ፍላጎቶች ይልቅ የአገር የጋራ ጥቅሞች ይቀድማሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ የተቀደሱ ተግባራት አደጋ ላይ ወድቀዋልና ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ሁሉ አቋማቸውን አደባባይ ወጥተው ሊገልጹና የጥፋት ሃይሎቹን ሴራ ሊያጋልጡና አንሰማችሁም ሲሉ ሊያረጋግጡ ይገባል፡፡
የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ምሁራን፣ አርሶ አደሮች፣ ሠራተኞች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ፖለቲከኞች ወዘተ ከስሜታዊነት ይልቅ በምክንያታዊነት የሚመራ የአስተሳሰብ ልዕልና ይፈጠር ዘንድ አደባባይ ወጥተው ድምፃቸውን ሊያሰሙ ከተገባ ትክክለኛው ሰአት አሁን ነው፡፡ ዜጎች በመንግሥት ላይ የሚሰማቸውን ማናቸውንም ዓይነት ቅሬታዎች ሲያቀርቡ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ልዩነቱ እና አደባባይ መውጣት እንዲገባን ግድ የሚሆንብን ምክንያት ግን  ይህን መብታቸውን የሚጠቀሙበት አግባብ ነው ።
እዚህ ጋር ነገሩ እየከፋ ስለመጣ ድርሻውን ለህዝብ ብናደርግም፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ዕውቅና የተሰጣቸው መሠረታዊ መብቶች እንዲከበሩና የሚያቀርቡት ሕጋዊና ሰላማዊ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ያገኝ ዘንድ መንግሥት ሁሉን ነገር ጨርሷል ለማለት እንዳልሆነ ጸሃፊው እንዲሰመርለት ያሻል፡፡ ከህዝቡ ተሳትፎ እና ሃይ ባይነት ጎን ለጎን በተለይ  የሕዝብ ጥያቄዎች መደራረብ የፈጠረው ችግርና አሁንም ለሚቀርቡ ጥያቄዎች እየተሰጠ ያለው  ዘገምተኛ ምላሽ፣ እንዲሁም ችግሮችን አቃልሎ ማየት በመንግስት በኩል ከፍተኛ ትኩረት የሚያስፈልገው መሆኑንም በተመሳሳይ፡፡
በዚህ ከተግባባን ምክንያታዊነት እየጠፋ ስሜታዊነት አገርን ችግር ላይ እንዳይጥል ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች አደባባይ ወጥተው  የጥፋት ተልእኮውን በብርቱ ሊያወግዙ  በመገባቱ ላይ ልዩነት አይኖርም፡፡ በተለይ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት አገርንና ሕዝብን ከሚያስመርሩ አጓጉል ድርጊቶች ውስጥ በፍጥነት ለመውጣትና በጋራ ጉዳዮች ላይ ለመምከር፣ ሁሉም ዜጎች አገራዊ ግዴታቸውን የሚወጡበት መድረክ ማመቻቸት የሚጠበቅበት መሆኑን ማስመር ይገባዋል፡፡
ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና የመሳሰሉት ያልገደቡት ልዩነት ኢትዮጵያዊያን በፈጠሩት የሚያኮራ የትስስር እሴት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ስለሆነም የሚያስፈልገን የተቃውሞ ሰልፍ ለእንዲህ ዓይነቷ ታላቅ አገር የሚመጥን እንጂ ጥላቻና ልዩነትን የሚያደምቅ አይደለም፡፡ የሚያስፈልጉን ፓርቲዎችም ይህንን ሕዝብ የሚመጥኑቱ እንጂ የውጭ ተላላኪዎች አይደሉም፡፡ ለዚህ ደግሞ አሁንም ደግሞ ደጋግሞ ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ አገር ትሁን ማለት ያስፈልጋል፡፡ ዜጎቿ በእኩልነት የሚኖሩባት አገር ትሁን ማለት ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የመላ ዜጎቿ ኩራት፣ የሰላምና መረጋጋት፣ የዴሞክራሲና የብልፅግና ማማ ትሆን ዘንድ ዜጎች ሁሉ አደባባይ ወጥተው በከፍተኛ ኃላፊነት መንቀሳቀስ ካለባቸው ትክክለኛው ሰአት አሁን ነው፤ 11ኛውን ሰአት ማለፍ ዋጋው የበዛ ነውና።


No comments:

Post a Comment