ታከለ አለሙ
የደቡብ
ሰዳን ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር የተቆራኘ ብዙ ክስተቶችን አምቆ የያዘ ነው፡፡ ደቡብ ሱዳኖች ከሰሜን ሱዳን ጋር በነበራቸው የረዥም
ጊዜ የሽምቅ ውጊያ ጦርነት ውስጥ አጼ ኃይለ ሥላሴ ሁለቱን ወገኖች ለማስታረቅ ሰፊ ጥረት አድርገዋል፡፡ ሽምግልናው የተሳካ እስኪመስል
ድረስ ሁለቱን ተቃራኒ ወገኖች አዲስ አበባ ላይ አሸማግለው እጅ ለእጅ እንዲጨባበጡ አድርገውም ነበር፡፡
ከሽምግልናው
በኋላ ወደ ወትሮው ግጭትና ጦርነት ነው ያመሩት፡፡ ያኔ የደቡብ ሱዳኑ ንቅናቄ አኛኝያ አንድ የመጀመሪያው ሁለተኛው ደግሞ አኛኝያ
ሁለት ይባል ነበር፡፡ የደቡብ ሱዳን የሽምቅ ተዋጊዎች ይጠለሉ የነበረው ጋምቤላ ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር፡፡ ከጃንሆይ ጊዜ ጀምሮ በኋላም
በደርግ የደቡብ ሱዳን ሽምቅ ተዋጊ ኃይል ሙሉ በመሉ ሲሰለጥን የነበረው በኢትዮጵያ መሬት ውስጥ እንደነበር ይታወቃል፡፡
በደርግ
ዘመን ብቻ 40 ሺህ የደቡብ ሱዳን ሠራዊት የሰለጠነው በኢትዮጵያ ነው፡፡ በህይወት የሌሉት የደቡብ ሱዳን ንቅናቄ መሪ ኮሎኔል ጆን
ጋራንግ የዛሬው የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኬር ምክትላቸው ሬክ ማቻር ሌሎችም መኖሪያቸው ኢትዮጵያ ነበረች፡፡
ኢትዮጵያ
ደቡብ ሱዳን እንደ አገር ራሷን ችላ መቆም ከጀመረችበትም ጥቂት ዓመታት ጀምሮ ሠላምና መረጋጋት ያላት አገር ሆና ልማትና ዕድገቷ
ላይ እንድታተኩር ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች፡፡ ሠላምና መረጋጋት ያላት አገር እንድትሆን ያላትን ቁርጠኝነት ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ
ጊዜ አሳይታለች፡፡
በደቡብ
ሱዳን የነገሰው ኋላ ቀር የጎሳ አስተሳሰብ በፕሬዚዳንቱ ሳልቫኬር ዲንካ ጎሳና በምክትል ፕሬዚዳንቱ ሬክማቻር የኑዌር ጎሣ መካከል
ያለው የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ትንቅንቅና ፉክክር በጥላቻ የተሞላ በመሆኑ በተደጋጋሚ ጦርነት ውስጥ ገብተዋል፡፡ በእነዚህ ኃይሎች
የተቆሰቆሰው ጦርነት ለብዙ ሺህዎች ደቡብ ሱዳናውያን ሞትና ለሚሊዮኖች ደግሞ መፈናቀል ምክንያት ሆኗል፡፡
በኢትዮጵያ
ብቻ በጦርነቱ የተፈናቀሉ የተሰደዱ ከ250 ሺህ በላይ ደቡብ ሱዳናውያን ይኖራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳን ሠላም አግኝታ በተረጋጋ
ሁኔታ እንድትኖር ጦርነቱ ከተካሄደ በኋላም ሰፊ የሽምግልና ሥራ ሰርታለች፡፡ ያለመሰልቸት ሁለቱንም ወገኖች አቀራርባ ሠላምና እርቅ
እንዲፈጠር የበኩሏን ትልቅ ድርሻ ተወጥታለች፡፡
በጉዳዩ
የአፍሪካ ሕብረት፣ የአሜሪካና እንግሊዝ መንግሥታት እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገብተው በደቡብ ሱዳን ሠላምና መረጋጋት
እንዲሰፍን አመራር ላይ ያሉት ኃይሎች ለሕዝባቸውና ለአገራቸው ሠላም ሲሉ ሠላም እንዲያወርዱ ከእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት እንዲወጡ
ከፍተኛ የማሸማገል ሥራ ተሰርቷል፡፡
ጊዜያዊ
እርቅ እንጂ ዘላቂ ሠላም ለማስገኘት አልተቻለም፡ ተስፋ የተጣለበትና ብዙ የተደከመበት እርቅ ውሎ ሳያድር ይፈርሳል፡፡ ከአሸማጋዮቹ
በላይ ለራሳቸው አገርና ህዝብ ማሰብና መቆርቆር የነበረባቸው ደቡብ ሱዳናውያኑ ነበሩ፡፡ አልሆነም፡፡
በቅርቡም
ሠላም የተገኘ በመሰለ መልኩ ሁለቱ ተቀናቃኞች የጋራ መንግሥት መሥርተው እንዲሰሩ ስምምነት ላይ ተደርሶ ሬክ ማቻር ከጋምቤላ ወደደቡብ
ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ ገብተው ጥቂት ጊዜ አገሪቱ በሠላም ውላ ማደር ጀምራም ነበር፡፡
ሁሉም
ወገን የተመኘውና የናፈቀው ሠላምና መረጋጋት ግን ሊገኝ አልቻለም፡፡ ዳግም ሁለቱም ወገኖች ጠመንጃ አንስተው ወደጦርነት ውስጥ ገብተዋል፡፡
የአገሬ ሰው ለያዥም ለገራዥም አስቸገረ የሚለው ዓይነት ሁኔታ ነው የሆነው፡፡
ደቡብ
ሱዳን ነጻነቷን አግኝታ ትንሽ ዓመታትን ያስቆጠረች አገር ነች፡፡ ምንም ዓይነት የመሠረተ ልማት የሌለባት ለመጀመር ደፋ ቀና የሚባልበት
አብዛኛው ህዝብ የኑሮ መሠረቱን በግብርናና በከብት እርባታ ላይ አድርጎ የሚኖርባት አገር ነች፡፡ መብራት፣ ንጹህ ውኃ፣ ጤና፣ ትምህርትና
መንገድ በመጠኑም ጁባ አካባቢ ካልሆነ በስተቀር ጭርሱንም የለም ማለት ይቻላል፡፡
በዚህ
የከፋ ኋላ ቀርነት ድጥ ውስጥ የምትገኝ አገራቸውን ከድህነት ጨለማ ለማላቀቅ ወደ ልማት፣ ዕድገትና ሥልጣኔ እንድታመራ ህዝቡንም
ያለልዩነት በፍቅር፣ በመቻቻልና በመከባበር እንዲኖር የማድረግ ህዝባዊም መንግሥታዊም ኃላፊነት ያለባቸው የደቡብ ሱዳን ሹማምንት
እጅግ ኋላ ቀር በሆነው የጎሣ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ ተደፍቀው እርስ በእርስ መፋጀታቸውና መጫረሳቸው በሌላው ዓለም ዘንድ አፍሪካን
አሳፋሪ ግምት ውስጥ እንድትወድቅ አድርጓታል፡፡
የጎሳ
ፖለቲካ የዓለማችን እጅግ ኋላ ቀሩ ፖለቲካ ነው፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ቀድሞም ለነበሩ አስከፊ ጦርነቶች ሁነኛ መነሻ በመሆን ለአገራቱ
መውደምና ለህዝቦች እልቂት ግዙፉን ድርሻ የተጫወተው አፍሪካ ማደግና መለወጥ በሚገባት ደረጃ እንዳትራመድ ሰቅዞ የያዛትና ለዘመናት
የኋሊት ሲጎትታት የኖረው ይኸው የጎሣ ጦርነት ችግር ነው፡፡
በደቡብ
ሱዳን ውስጥ በተለያየ ጊዜ እያገረሸ ከሚከሰተው የእርስ በእርስ ጦርነት ጀርባ የተለያዩ የውጭ ኃይሎችም እጅ አለበት፡፡ በነዳጅ
ዘይት ሀብታም አገር ብትሆንም ይህንኑ በሠላምና በአግባቡ እንዳትጠቀም የህዝቧም ኑሮ እንዳይሻሻልና እንዳይለወጥ በእርስ በእርስ
ጦርነት ተጠምዳ ስትታመስ በመሀል የአገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት በማግበስበስ ሥራ የተጠመዱ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እንዳሉ ለመገመት
አያዳግትም፡፡
በሌላም
ወገን ኢትዮጵያን ዒላማ ማድረግ የዘወትር ምኞታቸው የሆኑት የግብጽና የኤርትራ ሰዎችም ደቡብ ሱዳንን መረማመጃ በማድረግ እግራቸውን
ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት የሚያደርጉት የማያባራ ሙከራ እንዳለ ሆኖ ደቡብ ሱዳን ውስጥ ገብተውና ሰፍረው በንግድና በተለያየ ሽፋን
ስም ተከልለው እየሰሩ ያለውም ሥራ ግጭቱን የሚያባብስ እንጂ የሚያበርድ አይደለም፡፡
የደቡብ
ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት ጎሣ አባላት የሆኑት ኑዌሮች በኢትዮጵያ ውስጥም ስለሚገኙ ይህንን በተፋለሰ አቅጣጫ እንዲተረጎም በማድረግ
ኢትዮጵያ ኑዌሮችን ትረዳለች የሚል የተዛባ ፕሮፓጋንዳ ሲያዛምቱ መቆታቸውም ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያ
የደቡብ ሱዳን መንግሥት እንደ መንግሥት ራሱን ችሎ ተደማምጦ፣ ተቻችሎና ተከባብሮ ለአገሩና ለህዝቡ ልማትና ዕድገት እንዲቆም እንዲሰራ
የተረጋጋች አገር እንዲፈጠር የጎረቤቶቼ ሠላም የእኔም ሠላም ነው በሚለው የውጭ ጉዳይ መርህ መሠረት ብርቱ ድጋፍና እገዛ አድርጋለች፡፡
አሁንም በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
ደቡብ
ሱዳን የተረጋጋች ሠላም ያላት አገር እንድትሆን ኢትዮጵያ ትናንትም ዛሬም እየሰራች ሲሆን አገሪቷ እንድትበጠበጥና እንድትታመስ የሚያደርጉት
በእጅ አዙር ሚና የሚጫወቱት ወገኖች የደቡብ ሱዳንን አለመረጋጋት በመጠቀም የአገሪቱን ሀብት ለመዝረፍና ለመቀራመት ትግል የሚያደርጉ
ኃይሎች ናቸው፡፡
በደቡብ
ሱዳን እርቅ ለማስገኘት ብዙ ተደክሞበታል፡፡ በተደጋጋሚ እርቅ ቢያደርጉም
ዘላቂ ሠላምን መሬት ላይ ሊያወርዱ አልቻሉም፡፡ በቅርቡም በሁለቱ ወገኖች መካከል በዓለም አቀፍ ሽምግልና የተደረሰበት
እርቅ ፈርሶ ዳግመኛ የተነሳው ጦርነት ለበርካታ ዜጎች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት ሆኗል፡፡ መፈናቀልም አስከትሏል፡፡
የደቡብ
ሱዳን መሪዎች ከነጻነት በኋላ ለሊት ከቀን ወደአገር ግንባታ ሥራ ፊታቸውን ማዞር ሲገባቸው የእርስ በእርስ ጎሣ ጦርነት ውስጥ በመዘፈቃቸው
አገራቸውንም ህዝቡንም እየገደሉት ይገኛሉ፡፡
የደቡብ
ሱዳን መከላከያ ጄኔራሎች ከሁለቱ ተቀናቃኝ ጎሣዎች የተውጣጡ ሲሆኑ በጋራ ስለአገርና ስለህዝባቸው ማሰብና መሥራት ያልቻሉ እጅግ
ኋላ ቀር በሆነ የጎሣ አስተሳሰብ ውስጥ ተነክረው የማያባራ ጥፋትና ውድመት እያደረሱ የሚገኙ ናቸው፡፡ ስለ ጋራ አገራቸው ለማሰብ
ከጎሣ አስተሳሰብ በላይ ርቀው መራመድ አልቻሉም፡፡
ከጎጥና
ጎሣ መንደርተኛ እሳቤ ወጥተው በላቀ አገራዊ ራዕይ እየተመሩ መሠረተ ልማት፣ ትምህርት፣ የጤና አገልግሎት፣ ትራንስፖርት፣ የተለያዩ
ተቋማትን መመሥረት፣ መገንባትና ማሳደግ አልቻሉም፡፡ በአገር ግንባታ ተግባር የመሳተፍ ቁርጠኝነት አላሳዩም፡፡ ገና ከኋላ ቀር አስተሳሰባቸው
አልወጡም፡፡ ልቀትን አልተቀዳጁም፡፡
የደቡብ
ሱዳን ፖለቲከኞች ከሠላምና መረጋጋት ከአገር ግንባታ ልማትና ዕድገት ይልቅ እርስ በእርስ ጎጥ እየለዩ መፋጀቱን ቀዳሚ አጀንዳ አድርገው
ይዘውታል፡፡ ይኼ አካሄድ አስፈሪ ነው፡፡ ችግሩ ለጎረቤት አገራትም ይተርፋል፡፡ ህዝቡ ጦርነቱን በመፍራት የሚሰደደው ወደ አጎራባች
አገራት ነው፡፡
ኢትዮጵያ
ከአቅምዋ በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ የምትገኝ አገር ናት፡፡ ሠላምና መረጋጋት በአገራቸው ቢኖር እዚያው
እየሰሩ በሠላም መኖር ይችሉ ነበር፡፡ ይህ ሊሆን ባለመቻሉ ነው ህይወታቸውን ለማትረፍ ስደትን የመረጡት፡፡
የደቡብ
ሱዳንን ጎጣዊና ጎሣዊ ደም አፋሳሽ ችግር ከመሠረቱ ለማምከን በአጭር ዓመታት የሚቋጭ የሚፈታም አይደለም፡፡ የኅብረተሰቡን አስተሳሰብ
የመለወጥ የአብሮ መኖርና የመቻቻልን ባህል ማሳደግ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በሠላማዊ መንገድ የመፍታትን አገራዊ ጥቅም እንዲረዱት
ለማድረግ ሰፊ የማስተማር ሥራ በመሥራት ብቻ ነው በዓመታት ውስጥ ለውጥ ለማምጣት የሚቻለው፡፡
በደቡብ
ሱዳን ህዝብ ውስጥ ዘመናዊ ትምህርት አልተስፋፋም፡፡ ቀድሞም ቢሆን የደረሰው ለጥቂቶች ነው፡፡ እሱም የመማር እድሉን ላገኙት ብቻ፡፡
ዋናዎቹ በመንግሥት አመራር ላይ ያሉት በትምህርታቸውም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰዋል ተብለው የሚታሰቡት ወገኖች በጎጥና ጎሣ አስተሳሰብ
አንዱ ሌላውን በማጥፋት ደረጃ ጦርነት የሚከፍቱና ህዝባቸውን የሚያፋጁ ከሆኑ ምንም ትምህርት የሌለውና የጫካ ኑሮውን ብቻ የለመደው
በከብት እርባታና በግብርና የሚተዳደረው በሚሊዮኖች የሚቆጠረው ህዝብ ምን እንደሚያስብ ለመገመት አይከብድም፡፡ አደጋው በእጅጉ ያሳስባል፡፡
ይህንን
የተዛባና አንካሳ የሆነ የጎጥ አስተሳሰብና እምነት መለወጥ የሚቻለው ሰፊ የማስተማር ሥራ በመሥራት የኅብረተሰቡን ኑሮና ህይወት
በመለወጥ የምጣኔ ሀብት የትምህርቱ የጤናው አገልግሎት የትራንስፖርት ዘርፉና የመሳሰሉት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ህይወቱን ከመሠረቱ
የሚለውጥ ተጨባጭና መሠረታዊ ርምጃ በመውሰድ ብቻ ነው፡፡
በዚህ
ረገድ የደቡብ ሱዳን መንግሥት በባለቤትነት አጎራባች አገራትና የአፍሪካ ህብረትም ሆነ የመንግሥታቱ ድርጅት በአጋርነት ርብርብ በማድረግ
ሰፊ ሥራዎችን በህብረትና በትግግዝ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በህዝቡ ውስጥም ሆነ በአመራሩ መሠረታዊ ለውጥና የአስተሳሰብ ሽግግር
ሊመጣ የሚችለው በማስተማርና በማስተማር ብቻ ነው፡፡
አሁን
ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በደቡብ ሱዳን ያለው ሠላም በመድፍረሱ ግጭቱም አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ የአፍሪካ ህብረትም ሆነ የተባበሩት
መንግሥታት ድርጅት ሠላምን በኃይል የሚያስከብር ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያና ከሩዋንዳ የተውጣጣ 13000 ሠራዊት በደቡብ ሱዳን እንዲሰማራና
ሠላምን እንዲያስከብር ወስኗል፡፡
ይህ ዓይነቱ
ዓለም አቀፍ የሠላም ማስከበር ግዳጅ አስፈላጊ የሆነበት ትልቁ ሥጋት ሁኔታው እየከፋ ሄዶ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆንና የሚፈራውን
የጎሣና የዘር እልቂት እንዳያስከትል በማሰብ ነው፡፡ ርምጃው ተገቢም አስፈላጊም ነው፡፡
No comments:
Post a Comment