ቶሎሳ
ኡርጌሳ
ኢትዮጵያን
ጨምሮ በርካታ ሀገሮች ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር ሥርዓትን ይከተላሉ። ይህን የሚያደርጉትም ከሀገራቸው ታሪክ፣ ተጨባጭ ሁኔታና
ከህዝቦቻቸው ፍላጎት በመነሳት ነው። በዚህ ፅሑፌ ላይም ማስረጃዎችን በማጣቀስ የፌዴራላዊ ሥርዓትን ምንነትና እንደ እኛ ላሉ ብዝሃነት
ለሚያስተናግዱ ሀገራት ሊሰጥ የሚችለውን ጠቀሜታ እዳስሳለሁ። በዚህም ሥርዓቱ በማንኛውም ወቅት የሚፈጠሩ ነባራዊ ችግሮች መፍታት
የሚችልበት የፖለቲካ ምህዳር (political space) ያለውና ጥቅሞቹንም አሟጦ መጠቀም ከተቻለ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ሁነኛ
መፍትሔ መሆኑን ለማመላከት እሞክራለሁ።
እንደሚታወቀው
ፌዴራሊዝም በህዝቦች መካከል የፌዴራል የፖለቲካ ስርዓት የመንግስት ስልጣንና ተግባራት በፌዴራል የመንግስት መስተዳድር እና በክልል
መንግስታት መካከል በሕገ መንግስት በግልፅ የሚከፋፈልበት ስርዓት ነው። በዚህ ስርዓት የመንግስት ስልጣን፣ ኃላፊነት፣ አስተዳደር፣
ግብር የመሰብሰብና የፋይናንስ ሃብት የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት በአንድ ማዕከል ወይም ቦታ ብቻ የተጠራቀሙና የተከማቹ እንዲሆኑ አይደረጉም—በተለያዩ
ቦታ የስልጣን ማዕከላት ወይም ቦታዎች ይከፋፈላሉ እንጂ። ይህም የፌዴራል ስርዓት ዋነኛ መገለጫ ያልተማከለ የመንግስት ስልጣን፣
ኃላፊነት፣ አስተዳደር እና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ያለው መሆኑን ያሳየናል።
የፌዴራላዊ
ስርዓት በአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ የመንግስት መስተዳድሮችን ያዋቀረ፣ ለተወሰኑ ጉዳዮች
በጋራ መስተዳድር (Shared rule) አማካኝነት መስተዳድሮች ተቋማት የራስ አስተዳደርን የሚያቋቁም የስርዓት ዓይነት ነው። በዚህ
ዓይነት የስርዓት አወቃቀር የፌዴራሉ መስተዳድር እና የክልል መስተዳድሮች የበላይና የበታች ግንኙነት የላቸውም።
ምንም
እንኳን በህገ መንግስቱ ተለይተው ለየራሳቸው በተሰጣቸው ጉዳዮች እያንዳንዳቸው ያላቸው ስልጣን የተለያየና የየራሳቸውም ነፃነት የተጠበቀ
ቢሆንም፣ የመንግስት አስተዳደር ስራና ሂደት (governmental process) በሁለቱ መስተዳድሮች መካከል የመደጋገፍና የመቆራኘት
ስራን የግድ ማለቱ አይቀሬ ነው። በመሆኑም በሁለቱ መስተዳድሮች የተወሰነ የኃላፊነት መደራረቦች እና መደጋገፍ ይኖራል። ይህም ሁሉም
የፌዴራል ስርዓቶች የሚጋሩት የወል ባህሪ ነው ማለት ይቻላል።
የፌዴራል
የፖለቲካ ስርዓትን የሚከተሉ ሀገሮች የተፃፈ ሕገ መንግስት ያላቸው ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም የዚሁ ስርዓት ተከታይ ሀገሮች በተለያየ
ሁኔታ ለሕገ-መንግስት የበላይነት መረጋገጥ ልዩ ትኩረት ይሰጣሉ። ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት የፌዴራል ሕገ-መንግስት፣ የፌዴራል
የፖለቲካ ማህበረሰብ ከመገንባት፣ ከሕዝቦች ሉዓላዊነት የስልጣን ባለቤት መሆናቸውን መሰረት በማድረግ የመንግስትን ስልጣን በሁለት
ወይም ከዚያም በላይ ባሉ የመንግስት አስተዳደር ማዕከላት መካከል ያከፋፈሉበት፣ ስላላቸው ስልጣንና ተግባር የወሰኑበት፣ ጥቅሞችን
ማቻቻል መደራደርና ስልጣንን ያከፋፈሉበት፣ የፌዴራል ስርዓታቸውን ያዋቀሩበት፣ ያደራጁበትና ስለ አሰራሩ የደነገጉበት የበላይ ህግ
መሆኑ ብቻ አይደለም። የሀገራቸው አጠቃላይ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊ የፖለቲካዊና የሕግ ስርዓት የሚመረኮዝበትና የሚገነባበት ዋና
የሕግ ማዕቀፍ በመሆኑም ጭምር ነው።
ህገ-መንግስት
በአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ በጋራ ጉዳዮቻቸው የጋራ የመንግስት መስተዳድር ተቋማትን ለማቋቋም፣ ለየራሳቸው ለሆኑ ጉዳዮች
ደግሞ ከሌላው የራስ መንግስት መስተዳድሮን ለማቋቋም ፈቃድና ፍላጎታቸውን የገለፁበት ከፍተኛ የህግና የፖለቲካ ቃልኪዳን ሰነድ ነው።
በዚህም ስርዓቱ እያንዳንዱ መስተዳድር ለህገ-መንግስቱ ተገዥ የመሆን ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል።
በዚህ
ስርዓት ውስጥ ከህገ-መንግስቱ ጋር የሚቃረን ወይም የሚጋጭ ተግባር በህግ ተቀባይነት አይኖረውም። ስለዚህ የህገ- መንግስት የበላይነትን
መቀበል ለፌዴራል ስርዓት መተግበርና ስኬታማነት ቁልፉና ወሳኙ ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል። በፌዴራል ሀገሮች ህገ-መንግስትን የማክበርና
የማስከበር ኃላፊነትን በተግባር የማዋሉን ሁኔታ እጅግ አስፈላጊ የሚያደርገው፤ የፌዴራሉን መስተዳድር እና በእርሱ ስር የታቀፉ አባል
ክልላዊ መስተዳድሮች (States) ማንነትና ህልውና የሚመነጨው እንዲሁም የሚመረኮዘው በህገ መንግስቱ በመሆኑ ምክንያት ነው።
ምንም
እንኳ በፌዴሬሽኖች መካከል እንደ ምሳሌነት ከላይ የተጠቀሱት የጋራ ባህሪያት የሚታዩ ቢሆንም፤ ሁሉም ፌዴሬሽኖች አንድ ዓይነት አወቃቀርን
ሊከተሉ አይችሉም። እርግጥም ፌዴሬሽኖች ግዙፍ ልዩነቶች ሊኖራቸው የግድ ነው። ምክንያቱም ፌዴሬሽኖቹ ስርዓቱን እንዲያቋቁሙ ያስገደዷቸው
የየራሳቸው የታሪክ፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ ነባራዊ ሁኔታዎች የሚለያዩ በመሆኑ ነው።
ብሊንደንባቸር
እና ዋትስ የተባሉ የመስኩ ምሁራን ይህን ዕውነታ አስመልክተው እ.ኤ.አ በ2003 ዓ.ም “Federalism in a changing
world: A Conceptual Framework” በሚል ርዕስ ባቀረቡት መፅሐፋቸው ላይ እንደገለፁት፤ “አንድ ፌዴሬሽን ከሌላው
የሚለየው፤ በባህላዊ ብሔራዊ ልዩነት መጠንና ይህን ለማጣጣም በሚያደርገው ሙከራ፣ በአባላቱ ብዛት፣ አንፃራዊ መጠንና ተመሳሳይነት፣
በመንግስታት መሃከል ያለው ህግ የማውጣትና የአስተዳደር ኃላፊነት፣ ግብር የመሰብሰብ ስልጣን እና የፋይናንስ ሀብት ድልድል፣ የመማከልና
ያለመማከል መጠን እንዲሁም የኢኮኖሚ ውህደት መጠን፣ የማዕከላዊ ተቋማት ዓይነትና ይዘት፣ በመንግስት መስተዳድሮች መካከል የሚነሱ
ግጭቶችን ለመፍታት እና በመካከላቸው የስራ ትብብርን ለማቀላጠፍ የሚጠቀሟቸው ተቋማትና ሂደቶች ብሎም የፌዴራልና የክልል መስተዳድሮች
በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ላይ የሚኖራቸው ሚና ወሳኝ ጉዳይ ናቸው” በማለት ይተነትናሉ። ይህም የተለያዩ ሀገራት የተለያዩ የፌዴራል
አወቃቀር ሂደትን እንደሚከተሉ የሚያሳይ ይመስለኛል።
እርግጥ
ፌዴራሊዝም በተለያዩ የፖለቲካ ክፍሎች ስር የሚኖር፣ ነገር ግን የጋራ ቋንቋና ባህል ያለውን ህዝብ ወይም በጋራ የፖለቲካ ክፍሎች
ውስጥ በአባልነት የመሳተፍን ጥቅም የሚፈልግ ነገር ግን በቋንቋና በባህል የሚለያይ ህዝብን አንድ ለማድረግ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።
በፌዴራሊዝም የሚፈጠረው የአንድነት ውጤት በፌዴሬሽኑ የተካተቱ የአባል መንግስት መስተዳድሮችን የተለየ መሆን የሚያዋህድ ወይም የሚያጠፋ
ሆኖ መወሰድ አይኖርበትም።
ፌዴራሊዝም
አንድነት የሚያራምደው ፌዴሬሽኑን ያቋቋሙትን አካላት የተለየ ማንነት የራሳቸው ለሆኑ ጉዳዮች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበትን፣
እንዲሁም ለጋራ ጉዳዮቻቸው በጋራ መስተዳድራቸው የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ የሚወከሉበትንና የሚሳተፉበትን ተቋማዊ ማዕቀፍ በህገ-መንግስት
ዋስትና የሚሰጥ የስርዓት አወቃቀር ነው። ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት ፌዴራሊዝም የሚያልመው በአንድና በተመሳሳይ ጊዜ አንድነትንና
ህብራዊነትን በመጠበቅና በመኮትኮት ዓላማ ያለው በመሆኑ ነው። በዚህም በፌዴራላዊ ስርዓቱ የጋራ እሴቶችን እና ሁሉ አቀፍ ማንነትን
መገንባት ይቻላል።
ፌዴራሊዝም
ከውጭ የሚመጣ ወታደራዊ ጥቃትን ወይም የጦርነት ስጋትን በመከላከል ሰላም እና ደህንነት እንዲረጋጥ የሚረዳ ስርዓት ነው። በተሳካላቸው
ፌዴሬሽኖች ጀርባ ፌዴሬሽኖቻቸው በተመሰረቱበት የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ይህ ጥቃትንና ስጋትን በጋራ የመከላከል እሴት ይስተዋላል።
ለምሳሌ በአሜሪካ የውጭ ጥቃትን ወይም የጦርነት ስጋትን በጋራ የመመከትና ሰላምና ፀጥታን ማስፈን ዓይነተኛ የፌዴራሊዝም እሴት ሆኖ
አገልግሏል። በአሜሪካ ኮንፌዴሬሽን ውስጥ የነበሩት መንግስታት ፌዴሬሽንን ያቋቋሙት አንዱ አብይ ምክንያታቸው ከውጭ ሊቃጣባቸው የሚችሉ
ጦርነቶችን እና የጦርነት ስጋቶችን ለማምከንና ለመከላከል ጠንካራ የመከላከያ አቅም ለመፍጠር በማሰብ ነው።
በሌላ
ምሳሌ ደግሞ ህንድንና ቤልጂየምን የመሳሰሉ ከዚህ ቀደም አሃዳዊ የመንግስት የፖለቲካ ስርዓት የነበራቸው ቢሆኑም፣ በውጭ ከሚመጣ
ወይም ሊመጣ ይችላል ተብሎ ከሚገመት ስጋት ሳይሆን፣ በውስጣቸው ያሉት የተለያዩ ማህበረሰባዊ ልዩነቶች (Social
diversities) ባላቸው ሕዝቦች የእኩልነት፣ የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት የመሆንና የመጋራት ጥያቄዎችና ትግሎች አማካኝነት ወደ
ፌዴራላዊ የመንግስት የፖለቲካ ስርዓት ሊሸጋገሩ መቻላቸውን መረጃዎች ያስረዳሉ።
እርግጥ
እነዚህ ሀገራት ፌዴራሊዝምን ለመምረጥ የተገደዱበት ምክንያት ስንመለከተው ከውስጣቸው በተፈጠሩት ኃይሎች አማካኝነት አንድነታቸው
እንዳይሸረሸርና እንዳይጠፋ ለመከላከል በማሰብ ሆኖ እናገኘዋለን። ያም ሆነ ይህ ግን በሁለቱም ምሳሌዎቻችን ፌዴራሊዝም ለተጠቀሱት
እሴቶች ማራመጃ ሁነኛ መሳሪያ ሆኖ የሚያገለግል የፖለቲካ ስርዓት መሆኑን ለመገንዘብ አይከብድም።
ከዚህ
በተጨማሪም ፌዴራሊዝም ነፃነትን እና ዴሞክራሲን በማጠናከር ቁልፍ ሚና ይጫወታል። የመንግስትን ስልጣን እንደተለመደው ወደ ጎን በማለት
በህግ አውጪው፣ በሕግ አስፈፃሚውና በዳኝነት አካላት መካከል ብቻ በማከፋፈል ሳይሆን ፌዴራሊዝም የመንግስትን ስልጣን በአግድሞሽ
በፌዴራል መስተዳድሩና በአባል ክልል መንግስታት መካከል በማከፋፈል በመንግስት ስልጣን ላይ ተጨማሪ ገደቦችን በመጣል ለግለሰቦችና
ለማህበረሰቦች የተግባር ነፃነትን እና የፖለቲካ ስልጣን ምህዳርን (political space) የማረጋገጥ ሚናን ይጫወታል። ለአብነት
ያህል በአሜሪካ የሚገኙ ፌዴሬሽኖችን ብንመለከት፤ እያንዳንዱ ዜጋ እና የፖለቲካ ቡድኖች በመንግስት አስተዳደር ችግሮች ላይ ለመወያየት
የሚሳተፉበትን የፖለቲካና የሕግ ምህዳር በመፍጠርና በመኮትኮት እንዲሁም ዜጎች በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ በመንግስት የውሳኔ
አሰጣጥ ሂደት ውስጥ የሚሳፉባቸውን ዕድሎች በማስፋት ይታወቃሉ። ይህም ፌዴራሊዝም የማህበረሰብንም ሆነ የግል ነፃነቶችን ለመጠበቅ
የሚያገለግል ጠቃሚ የመንግስት አወቃቀር መሆኑን የሚያስረዳ ነው።
ከዚህ
በተጨማሪም ፌዴራሊዝም አንድ ሰፊ ገበያን በንግድ እንቅስቃሴ ላይ በውስጥ የሚጣሉ ገደቦችን በማስወገድና የጋራ ኢኮኖሚያዊ አንድነት
በመፍጠር እንዲሁም በመጠበቅ የኢኮኖሚ ልማትን ወይም ዕድገትን ያፋጥናል። ፌዴራላዊ ስርዓት ራስን በራስ የማስተዳደር ስልጣንና ነፃነትን
በህገ-መንግስት መሰረት በመስጠትና በማቋቋም በፌዴሽኖች ውስጥ ያሉት የመንግስት መስተዳድሮች በየአካባቢያቸው ካሉት ህዝቦች ፍላጎቶች
ጋር የሚጣጣሙ የፖሊሲ አማራጮችን እንዲቀርፁና የአካባቢ ባለስልጣናት ለየአካባቢያቸው ህዝብ ቅርብ እንዲሆኑ በማድረግ የህዝብን ፍላጎቶች
እያዳመጡ ለህዝቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል። እንዲሁም የፌዴራሊዝም አደረጃጀት ለፈጠራ ስራዎች በተወሰኑ አካባቢዎች
ለፖሊሲ ሙከራዎች ዕድሎችን በመፍጠር በማህበረሰቡ ውስጥ የላቀ ጠቀሜታን ይፈጥራል። በተለያዩ የስልጣን ማዕከላት መካከል በሚኖረው
በጎ ፉክክሮች ፈጣንና ጠቃሚ ውጤቶች እንዲገኙም በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ ነው።
ፌዴራሊዝም
በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ሊኖሩና ሊፈጠሩ የሚችሉ ልዩነቶችን በማቻቻል አብሮ ለማራመድ እና ልዩነቶችን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች
በሚፈጠሩበት ውቅት ችግሮቹን ለማርገብ አግባብነት ያለው የፖለቲካ ስርዓት ነው። በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ የሚኖሩና ሊነሱ የሚችሉ
ግጭቶችን ለመቀነስ ፌዴሬሽኖች ብዙ የመንግስት ስልጣን ማዕከላትንና የፖለቲካ ምህዳር (political space) ስላላቸው ለሰላማዊ
ድርድር ምቹ ተቋማዊ ማዕቀፍ ይፈጥራሉ። ይህም የፌዴራላዊ ስርዓት ዋነኛው ጠቀሜታ ነው ተብሎ በመስኩ ምሁራን ይገለፃል።
ከዚህ
በተጨማሪም ፌዴሬሽኖች ብሔሮች ብሔረሰቦና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደርና የጋራ ጉዳዮቻቸው በጋራ የማስተዳደር ለጋራ ጉዳዮቻቸው
በጋራ የማስተዳደር መብት ዋስትና በመስጠት የብሔር ብሔረሰብ እና ህዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችል
ተቋማዊ መሰረት አላቸው። ይህን ዕውነታም ላሪ ዳይሞንድ የተሰኙ የመስኩ ምሁር እ.ኤ.አ በ1999 ዓ.ም ባወጡት “Developing
Democracy Towards Consolidaton” በተሰኘው መፅሐፋቸው ላይ፤ “ፌዴራሊዝም ባለ ብዙ ብሔር ሀገርን ብሔራዊነትና
ዴሞክራሲን በማጣጣም የአናሳ (minority) ብሔሮችን ቋንቋ፣ ባህልና ሃይማኖት የመጠበቅና የመጠቀም ዋስትና ይሰጣል። ይህም ፌዴራሊዝም
ከአብዛኛው ብሔር እኩል የመወሰን ነፃነት ስሜት እንዲሁም በአካባቢያዊ ጉዳዮች ስልጣን በመስጠት በአንድነት በባለ ብዙ ብሔር ሀገር
ውስጥ ዕውን እንዲሆን ያስችላል” በማለት ገልፀውታል። ይህ አባባል
እንደ ሀገራችን ባሉ እጅግ በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ላሉ ሀገራት በአንድነት የተሳሰረን ህዝብ በአንድ የፖለቲካል ኢኮኖሚ
ማህበረሰብነት ለማስቀጠልና የሚፈጠሩ የማህበራዊ መስተጋብር ግጭቶችን በመቻቻል ምህዳር ለመፍታት ፌዴራላዊ ስርዓት ጠቀሜታው እጅግ
የላቀ መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል።
እርግጥም
እንደ እኛ ያሉ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሀገራት ከፌዴራሊዝም የመንግስት አወቃቀር ስርዓት ውስጥ፤ ለሁሉም ብሔሮች፣
ብሔረሶችና ህዝቦች ህገ መንግስታዊ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነትንና ውክልናን ማረጋገጥን፣ የውጭ ጥቃትን በጋራ መመከትን፣ ፈጣን
ኢኮኖሚን ማምጣትን፣ የሚፈጠሩና ሊፈጠሩ የሚችሉ ነባራዊ ግጭቶችን መፍታትን እና የጋራ ኢኮኖሚያዊ አንድነት መፍጠርን…ወዘተ. ጠቀሜታዎችን
ማጣጣም የሚቻል ይመስለኛል። ይህም በፌዴራላዊ ስርዓት ውስጥ ዕውን የሚሆኑ ጥቅሞች እስካሉ ድረስ፤ ሥርዓቱ ራሱን በራሱ እያረመና
ከህዝቦች ፍላጎት ጋር እየተራመደ ሊፈጠሩ ለሚችሉ ማናቸውም ነባራዊ ተግዳሮቶች መፍትሔ መሆን እንደሚችል የሚያሳይ ነው። እናም በፌዴራላዊ
ሥርዓት ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ የሚያገኙት በራሱ በሥርዓቱ መሆኑን ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል እላለሁ።
No comments:
Post a Comment