ኢብሳ ነመራ
ማህበራዊ
ሚዲያዎች በተለይ ፌስ ቡክ የተሰኘው ማንም ከኃላፊነትና ከተጠያቂነት ውጭ ሕግንና የሞያ ሥነ ምግባርን ዋጋ ባለመስጠት የሚፈነጭበት
ፌስቡክ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የዘረኝነት
መርዝ የጎረሰ የጦርነት ክተት ሲያውጁ ነበር። በተቃውሞ ሰልፍ ሽፋን፤ የፌስቡኩ ከተት አንዱ ብሔር በሌላው ላይ ጥቃት እንዲሰነዝር
ግልጽ አዋጅ ነበር ሲያስተላልፍ የነበረው። የክተቱ አጋፋሪዎች ደግሞ ያስፈራራሉ፤ የፎክራሉ፤ ያቅራራሉ፤ አንዱ ብሔር ተቆጥቶ በሌላው
ላይ እንዲነሳ ጸያፍ ዘለፋዎችን ይሰነዝራሉ። ይህን የተቃውሞ ሰልፍ የተባለ በዘር ጥላቻ የተለወሰ የጥቃት ዘመቻ ጥሪ የሚያስተላልፉት
እንማን እንደሆኑ አይታወቅም። ኦሮሞዎች ቅዳሜ ሐምሌ 30 ቀን አማሮች ደግሞ እሁድ ነሃሴ 1 ቀን 2008 ዓ.ም አደባባይ እንዲወጡ
ነበር ጥሪ ሲተላላፍ የቆየው።
በዚህ
የአደባባይ ተቃውሞ በግልጽ ተለይቶ በተገለፀ ብሔር ተወላጆች ላይ ጥቃት እንዲሰነዝሩ መልዕክት ተላልፏል። የፈጠራ ወሬ ይሁን የእውነት
ባይታወቅም “በዚህ አካባቢ አንድ የወያኔ ሰላይ በጀግናው የእከሌ ህዝብ
ተገደለ” እየተባለ የማደፋፈሪያ ወሬም ይለቀቅ ነበር። ከጸጥታ
አስከባሪ ኃይል አባላት ላይ መሳሪያ እንዲነጥቁ ግልፅ ትእዛዝ ሲተላለፍ ነበር። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀውን
ኦነግና ትምክህተኛ ብሔረተኞች መለያቸው ያደረጉትን አረንጋዴ ቢጫ ቀይ ቀለማት ያሉት አርማ እንዲያውለበልቡ፤ በሌላ በኩል የኢፌዴሪን
ሰንደቅ ዓላማ እንዲያወርዱ መልእክት ሲተላላፍ ነበር። ይህን ድርጊት ለማበረታታት የኢትዮጵያ ልብስ ሰፊዎች ባንዲራ በመስፋት ሥራ ተጠምደዋል፤ የሚል የኦነግንና የትምክህተኞችን
አርማ የሚያሳዩ ምስሎች የያዘ የፌስቡክ ዜና ተለቅቋል፤ አርብ ሐምሌ 29፤
በሌላ
በኩል በግልፅ ኢትዮጵያን የማተራመስ ስትራቴጂ ነድፎ እንደሚንቀሳቀስ የሚታወቀው፤ በአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጨነት በሚመራው የኤርትራ
መንግሥት በሚሰጠው አቅጣጫ እንደሚሰራ የሚታወቀው ኢሳት የተሰኘ የቴሌቪቭዥን ስርጭት በአገር ውስጥ እንዲታይ የተደረገበት ምክንያት
ለብዙዎች ግልፅ ባይሆንም ቴሌቪዥኑ በየቤቱ የዘረኝነትና የመተላለቀቅ ቅስቀሳውን ሲለፍፍ ነበር የሰነበተው፤ በነገራችን ላይ፤ ኢሳት
የተሰኘው የቴሌቪዥን ቻናል የሚሰራጨው Horn TV በተሰኘ የኤርትራ መንግስት ምሥራቅ አፍሪካን ለማተራመስ በከፈተው የቴሌቪዥን
ጣቢያ ነው።
በርካታ
ኢትዮጵያውያን ይህ የዘረኝነትና የእልቂት ቅስቀሳ አሳስቧቸው ሰንብተዋል። ማህበራዊ ሚዲያዎች ለመተላለቅ ምክንያት የሚሆን ቅስቀሳዎችን
ማሰራጨት እስኪያቆሙ ቢዘጉ ይሻላል የሚል አቋም የነበራቸው በርካቶች ነበሩ። የኢሳት በየቤቱ መፈንጨት ደግሞ ከስጋት ባለፈ ብዙዎችን
እጅግ አስገርሞ ሰንብቷል።
ይህን ተከትሎ የኦሮሚያና የአማራ ክልላዊ መንግሥታት
ርእሳነ መስተዳድር መግለጫ ሰጡ። በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚተላለፈው የሰልፍ ጥሪ ሕጋዊ እንዳልሆነ ነበር በመግለጫቸው ያሳወቁት።
በሰላማዊ ሰልፍ አቤቱታ ማቅረብ በሕገ መንግስት የተረጋገጠ መብት መሆኑን አፅንኦት የሰጡት ርእሳነ መስተዳድሮቹ፤ ሰልፎች ሕግና
ሥርዓት ተከትለው መካሄዳቸውን ለማረጋገጥ ሰልፉን የጠራውና የሚመራው አካል አስቀድሞ ሰልፉ በሚካሄድበት አካባቢ ለሚገኝ ጉዳዩ የሚመለከተው
የስልጣን አካል ማሳወቅ እንደሚጠበቅበት፤ ሰሞኑን ለተጠራው ሰልፍ ግን ባለቤት ነኝ የሚል ኃላፊነት ወስዶ ያሳወቀ አንድም አካል
ያለመኖሩን አሳውቀው፤ ሕዝቡ በዚህ ሕገ ወጥ ሰልፍ ላይ እንዳይወጣ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
የፌዴራል መንግሥትም ይህንኑ ነበር ያደረገው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው አርብ ሐምሌ 29/2008 ዓ.ም. ለመገናኛ በዙኃን በሰጡት መግለጫ፤
ሕዝቡ ችግሮችን በዴሞክራሲያዊ እና በሰለጠነ አግባብ መፍታት የሚችልበት ሰፊ ዕድል እንዳለው ገልፀው፤ ባለቤቱ ከማይታወቅ እና በማህበራዊ ድረ ገጽ ከሚመራ ሕገ ወጥ ሰልፍ ጥሪ ራሱን እንዲቆጥብ፤ ሰሞኑን በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች የተካሄዱ እና እየተጠሩ ያሉ ሰልፎችም አግባብነት እንደሌላቸው አሳውቀዋል። በሕገ መንግስቱ መሰረት ሰላማዊ ሰልፍ የመውጣት መብት የተጠበቀ መሆኑንም አስታውሰዋል።
ሰሞኑን በተካሄዱትና በተጠሩት ሰልፎች ከሕዝቡ ጥያቄ ባፈነገጠ አኳኋን ህብረተሰቡን የማይወክሉ የጸረ ሰላም ኃይሎች አቋም ሲንጸባረቅ በአደባበይ መስተዋሉን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ለመግታት መንግሥት ሕግን ለማስከበር እንደሚገደድና ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አሳስበዋል።
ይሁን እንጂ፤ በተቃውሞ ሰልፍ ሽፋን የዘረኝነት
ጦርነት ያወጁት የፌስቡክ አዝማቾች ዐርብ እለት “ሰልፎቹ በታቀደላቸው
መርሀ ግብር መሰረት ይካሄዳሉ” የሚል ቅስቀሳቸውን ገፍተውበታል። በተለያየ ሰው ስም ኦሮሞም፣ አማራም፣ ትግሬም ሆነው
በከፈቷቸው የፌስቡክ አካውንቶች በሚያስታውቅ ሁኔታ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ፤ አንዱ በሌላው እንዲቆጣ የሚያደርጉ
የተቀነባበሩ አስተያየቶችን (comments) በመስጠት የመጠላላቱንና ለመጠቃቃት መፈላለጉን ለማጋጋል ሞከሩ። ልብ በሉ፤ እጅግ
በርካታ ኢትዮጵያውያን ግን አካሄዱ አላማራቸውም። እንዲያው ቀልባቸው እምቢ ብሎ በፌስቡኩ የሁከት ዘመቻ ስር በጎ አስተያያት
የሚሰጡ ሲገኙ ወዲያው “እከካም …፤ ቅማላም …፤” የሚል ጸያፍ
ስድብ ይሰነዘርባቸው ነበር። ይህን አሁንም የፈስ ቡክ የክተት ጥሪ ገጾችን በመመለከት ማረጋገጥ ይቻላል። የሁከትና የመተላለቅ
ጥሪው በተላለፉባቸው ቀናት የቅስቀሳው አጋፋሪዎች የልብ ልብ ተሰመቷቸው ፉከራ ቢጤ ሲቃጣቸው፤ የሁከቱ አደጋ ያሳሰባቸው ደግሞ
በስጋት ተውጠው ቀፍፏቸው ነበር የሰነበቱት፤
ያም ሆነ ይህ ቅዳሜ ደረሰ። የፌስቡክ የሁከትና የመተላላቅ
አዝማቾች ልብስ ሰፊዎችን ፋታ አሳጥቶ ሲሰፋ ሰነበተ የተባለለት የኦነግ አርማ ግን እንደተነገረው በመላ ኦሮሚያ ከተሞች በምድር
አንቀጥቅጥ የተቃውሞ ሰልፍ ሲውለበለብ አልታየም። ጥቂት አካባቢዎች ላይ ግን ኃይል የተቀላቀለባቸው ሁከቶች ተሞክረዋል። ለምሳሌ፤-
በሻሸመኔና አካባቢው፤ በነቀምት በምእራብ ሐረርጌ፤ በአዲስ አበባም እስከ አንድ መቶ የሚደርሱ ሰዎች ከሌላ ቦታ በጭነት መኪና
ተሳፍረው የመጡትን ጨምሮ እስከ 200 በሚደርሱ ሰዎች ሕገ ወጥ የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሄድ ተሞክሮ ነበር። በአጠቃላይ ኦሮሚያ
በዘረኝነት ስሜት በሚነዳ ሁከትና መተላላቅ ሳትናወጥ በአብዛኛው ሰላም ሆና ዋለች። እርግጥ ሁከት በተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎቸ
ጉዳት ደርሷል። በሰው ህይወትም፤ በንብረትም ላይ፤ በተወሰኑ ብሔሮች አባላት ንብረቶችም ላይ ጥቃት የተሰነዘረበት ሁኔታ
እንደነበረ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከቀናት በፊት በጎንደር ከተማ አንድ በወንጀል
የተጠረጠረ ግለሰብ ፍርድ ቤት መቅረቡን አስታክኮ ተቀስቅሶ የነበረውና ሰላም አስከባሪን ጨምሮ ለአራት ሰዎች ህይወት መጥፋት
ምክንያት የነበረን ሁከት “ጀግናው … ከወያኔ ሰራዊት ጋር ገጥሞ
እንዲህ አደረገ፣ ምንትስ ፈጠረ” በሚል አሳፋሪ ወሬ ሲቀሰቅስ ቆይቶ
በኣማራ ክልል የሁከትና የዘረኝነት መተላላቅ እንዲቀጣጣል ጥሪ የተላለፈበት እሁድ ሐምሌ 1 ቀን ደረሰ። በዚህ ዕለት
የዘረኝነትና የጥላቻ ቅስቀሳ መርዝ በተወሰነ ደረጃ በሰረገባቸው የሰሜን ጎንደር አካባቢዎች እንዲሁም፤ ሰማያዊ የተሰኘው ፓርቲ
ኃላፊነት ወስዶ በባህር ዳር ከተማ የጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ በማስታከክ በቦምብና በመሳሪያ የታጀበ ሁከት ተቀስቅሷል። አዋኪዎቹ
ንብረት አወደሙ፤ በሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት ላይም ጥቃት ሰነዘሩ። ሕዝቡ ባይከላከል ኖሮ በከተማዋ በግለሰቦችና በመንግሥት
ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት ሊደርስ ይችል እንደነበረ ሁኔታውን የታዘቡ ሰዎች ይናገራሉ። ይህ ቦምብ በመወርወርና ሽጉጥ
በመተኮስ ጭምር የተካሄደው ሁከት ሊያደርስ ይችል የነበረውን ውድመት ለመከላከል በተወሰደ ሕግ የማስከበር እርምጃ ከአዋኪዎቹም
ወገን የሰው ህይወት ጠፍቷል።
እንግዲህ በዘረኝነት የታጀለው ሁከትና የመተላላቅ
ዘመቻ የተጠራው በመላው አማራ አካባቢዎች ቢሆንም፤ ከላይ በተጠቀሱት በጎንደር ከተማና በአካባባው፤ እንዲሁም በባህር ዳር
ከተቀሰቀሰው ሁከት ውጭ የተቀሩት ሰባት የአማራ ክልል ዞኖችና ከተሞዎቻቻው ፍፁም ሰላም ሆነው ውለዋል።
በዚህ አኳኋን መላው ኦሮሚያና አማራ ክልሎች በእርስ በርስ ግጭት ሲታመሱ ይውላሉ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሞተው ከተሞች በደም
ይጨቀያሉ፤ ጩኸትና ዋይታ ይሆናል፤ ይህም መንግሥትን ያንበረክካል፤ በኢትዮጵያ ሕግና ሥርዓት ጠፍቶ ሥርዓት አልበኝነት ይነግሳል
ብለው ጠብቀው ያለ የሌለ ኃይላቸውን ተጠቅመው ሁከትና እልቂት የደገሱት የቅርብና የሩቅ የኢትዮጵያ ጠላቶችና ድግሳቸውን ሊያወጡ
የሁከትና የእልቂት ክተት ያወጁት ተላላኪዎቻቸው ያሰቡት ሳይሳካ ቀረ። እርግጥ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ደም ያፈሰሰ፤
ንብረት ያወደመ፤ ሰዎች በማንነታቸው ብቻ ለጥቃት እንዲጋለጡ፤ እንዲሸማቀቁና ስጋት እንዲያድርባቸው ያደረገ ጥፋት ደርሷል። ይህ
እጅግ የሚያሳዝን ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ አሁንም ሁከትና እልቂት እንዳጠላ ይገኛል። አጠቃላይ የሁለቱን ክልል ሕዝብ
ሰላም ፈላጊነት ያስተዋለ ግን የሁከትና የመተላላቅ ጥላ በቅርቡ እንደሚገፍፍ መገመት አያዳግተውም።
የሁከትና የእልቂት ቅስቀሳ ሲያካሂዱ የከረሙት
የፌስቡክ አዝማቾች ቅስቀሳቸው የፈጠረው ሁከት ያሰቡትን ያህል እልቂት ባያስከትልም፤ የተገኘውን ያህል ግዳያቸውን በፌስቡክ
ገፃቸው ይዘው መውጣት ጀመሩ። “ጀግናው የ… ህዝብ፣ … እከሌ፣
በለው! ውቃው! . . .” በሚል ቅስቀሳ በትምክህተኞችና በኦነግ አርማ አሸብርቀው የሰነበቱት የፌስቡክ ገፆቻቻው
አስከሬን ይዘው መውጣት ጀመሩ። ያቀዱትን ያህል እልቂት ባያተርፉም የተገኘችዋን፤ በሌላ አገር በማንኛውም ምክንያት መንገድ ላይ
የወደቁ አስከሬኖችን ፎቶግራፍ ጨማምረው መለጠፉን ተያይዘውታል። ተቃውሟቸውን ያሰሙ የእከሌ ሕዝብ ጥይት ዘነበበት፣ ምንትስ ቅብጥርስ በሚል ወሬ አጅበው፤ መድረሻቸው የኦሮሞ ወይም የአማራ ሕዝብ
ጥቅም መጠበቅ ሳይሆን እልቂት ውስጥ ከትተውት የአስከሬኑን ፎቶግራፎች ለፖለቲካ ፍጆታነት መቸርቸር ነበር። አሁን እያደረጉ
ያሉት ይህንኑ ነው።
እንግዲህ እንደታሰበው በሞትና በደም ካልደመቀው የሰሞኑ
የእልቂት ድግስ ጀርባ ጠንሳሽና መሪዎች አሉ። እነዚህ ሆነ ብለው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስና አገሪቱን እንደ ሊቢያ፤
ሶሪያና ኢራቅ የማድረግ ራዕይ ያላቸው ናቸው። እነዚህ ጠንሳሽና መሪዎች የተደገሰውን እልቂት እንዲፈፅሙ የተጠሩትና ለመፈፀም
የሞከሩት ግን የሴራውን ምንጭና ቢሳካ በአገራቸው ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ያልተረዱ የተታለሉ የዋህ የጥፋት አርበኞች
ናቸው። ምንም እንኳን ድርጊታቸው ወንጀል ቢሆንም፤ አብዛኞቹ በአገሪቱ የተጀመረውን ልማት የሚያደንቁና የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ
መሆን የሚፈልጉ፤ የአገራቸው ትልቅና ገናና መሆን የሚያኮራቸውና ይህን ለአገራቸው የሚመኙ ናቸው። ነገር ግን ለእርኩስ ዓላማ
መጠቀሚያ ለመሆን ተጋልጠዋል። የኃይል ርምጃ እንዲወስዱ በማነሳሳት የተመለመሉ የሞት እጩዎች ናቸው። የተደገሰላቸው ሞት ከተሳካ
የአስከሬናቸውን ፎቶግራፍ እየሸጡና የመንግሥትን ገፅታ የሚያበላሹ፣ በሕዝቡና በውጭ አካላት በጥርጣሬ እንዲታይ የማድረግ ዓላማ
ያላቸው ሪፖርቶች ማድመቂያ እንዲሆኑ የተመለመሉ ምስኪኖች ናቸው። እናም ያሳዝናሉ!
በኢትዮጵያ ወዳለው ነባራዊ ሁኔታ ልመለስ፤ ኢትዮጵያ
ይህ ነው የሚባል እንከን የማይወጣለት፤ ብሔሮቿ፣ ብሔረሰቦቿና ህዝቦቿ በእኩልነትና በመከባባር አብሮ የመኖር ቃል ኪዳን ሆኖ
የሚያገለግል ሕገ መንግሥት ያላት አገር ነች፤ በአፈፃፃም ደረጃ አሁንም አንዳንድ ክፍተቶች መኖራቸው ሳይዘነጋ፤ በዚህ ሕገ
መንግሥት መሠረት የአገሪቱ ሉአላዊ የስልጣን ባለቤቶች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩና በክልላዊ መንግሥታት የተዋቀሩ ብሔሮች፣
ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው። ፌዴራል መንግሥቱን የመሠረቱትም እነዚህ ናቸው። ይህ የፌዴራል መንግሥቱ (የኢፌዴሪ መንግሥት)
ስልጣኑን ያገኘው ከክልላዊ መንግሥታት ነው። ይህ ፌዴራላዊ የመንግሥት ሥርዓት ለዘመናት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች
ማንነታቸው በሕግ ዕውቅና ተነፍጎት፤ ማንነታቸው፤ ቋንቋቸው፣ ባህላቸው፤ ታሪካቸው ተንቆና ተዋርዶ ሲገዙበት የነበረውን አሃዳዊ
ሥርዓት ሸሮ ነው የተገነባው፤
ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ለብሔራዊ መብትና ነጻነት በተካሄዱ ጦርነቶች
የመበታታን ጫፍ ላይ ደርሳ የነበረችውን አገር ከመበታታን ታድጎ በእኩልነትና በመከባባር ላይ የተመሰረተ፤ የወሰን ሳይሆን የሕዝቦች
አንድነት ያላትን አገር መመስረት ያስቻለ ነው። አስታውሱ አገሪቱ ከመበታታን አፋፍ ነው የተመለሰችው፤
በኢትዮጵያ የነበረው አሃዳዊ ሥርዓት አንድ ብሔራዊ
ማንነት መለያው ያደረገ ነበር። (ልብ በሉ፤ የአንድ ብሔር የበላይነት ነበር እያልኩ አይደለም።) ታዲያ፤ የዚህን ያከተመ
የአሃዳዊ ሥርዓት አመለካካት የሚያራምዱ፣ ለተቀሩት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት እውቅና የማይሰጡ ቡድኖች
አሁንም አሉ። እነዚህ የአሃዳዊ ሥርዓት ናፋቂ ትምክህተኛ ብሔረተኞች የዚህ ሥርዓት ተቃዋሚዎች ሆነው ተሰልፈዋል። የተወሰኑት
ይህን አቋማቸውን ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት በሰላማዊ መንገድ ለማራመድ ሲሞክሩ የሚታዩ ቢሆንም፣ ይህ ሰላማዊ አካሄድ
የሚመኙትን አሃዳዊ ሥርዓት መመለስ አያስችልም የሚል እምነት ያደረባቸው፤ ግን ሕገ መንግሥታዊውን ፌደራላዊ ስርአት በኃይል
የመናድ ዓላማ ይዘው በአገር ውስጥ ውስጥ ውስጡን እንዲሁም በውጭ አገራት በይፋ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ።
እነዚህ በተለይ በኃይል ሥርዓቱን ለመናድ የሚንቀሳቀሱ
ትምክህተኛ ብሔረተኞች፤ እነርሱ የሚመኟት አሃዳዊት ኢትዮጵያን መመለስ ካልተቻለ አገሪቱ በእርስ በርስ ግጭት እንድትጠፋ
የማድረግ አማራጭ እንደሚከተሉ የሚያሳዩ እውነታዎች አሉ። ፍፁም አምባ ገነን ከሆነውና ለሰብዐዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ምንም
እውቅና የማይሰጠው፤ በተለይ ኢትዮጵያን ዳግም አገር መሆን በማትችልበት ሁኔታ ለማተራመሰ ስትራቴጂ ነድፎ በሚንቀሳቀሰው፤
በአንድ ግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነት በሚመራው የኤርትራ መንግሥት ስር መግባታቸው ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀስ ይችላል።
በሌላ በኩል አገሪቱ ለብሔራዊ መብትና ነፃነት
በተደረገ ትግል ደርሳበት ከነበረው የመበታታን ጠርዝ ተነስተው፤ ከዚያ በኋላ በእኩልነትና በመከባባር ራስን በራስ እያስተዳደሩ
አብሮ ለመኖር በመስማማት በሕገ መንግሥት የፀናውን አንድነት ችላ ብለው፤ መገንጠል በራሱ መድረሻ ይመስል፣ የመገንጠል ጥያቄ ይዘው
ይህን በኃይል ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች አሉ። ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹ ሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከለላ አድርገው
እንደሚንቀሳቀሱ ይታወቃል። እነዚህ ጠባብ ብሄርተኞች የሚገዙትን ትንሽ ነፃ አገር ለመመሰረት በማንኛውም መንገድ - በጦርነትም
ሆነ በሽብርተኝነት ፌደራላዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ ይፈልጋሉ። ፌዴራላዊ ሥርዓቱን ማፍረስ ከሚፈልግ ማንኛውም ወገን ጋር
እንወክለዋለን የሚሉትን ብሔር የመጨረሻ ጥቅም የሚፃረርም ቢሆን ወዳጅነት ሲመሰርቱ ይታያሉ። ኦነግ፣ ኦብነግና ሌሎች አሥርም፣
ሃያም ሰው ይዘው የኢሳያስ መንግሥት ስር የተጠለሉ ቡድኖችን ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል።
ትምክህተኞቹና ጠባብ ብሔረተኞቹ በዓላማ ፍፁም
ተቃራኒ፣ አንዱ ለሌላው አጥፊ ቢሆኑም አንድ የሚያመሳስላቸው ነገር ግን አለ። ሁለቱም ለየራሳቸው ጥቅምና የጥላቻ ስሜት እርካታ
ፌዴራላዊ ሥርዓቱ እንዲፈርስ፣ ኢትዮጵያ የምትባለው አገር እንድትበታተን ይፈልጋሉ።
በሌላ በኩል ሌሎች ኢትዮጵያ እንድትፈርስ የሚፈልጉ
የሩቅና የውጭ ኃይሎችም አሉ። የኤርትራ መንግስት አንዱ ነው። ሌሎች ከኢትዮጵያ ጋር የተሳሳረ ጥቅም ያላቸው የኢትዮጵያ ማደግና
ገናና አገር ሆኖ መውጣት የጥቅም የበላይነታችንን ያሳጣናል የሚል ስጋት ያሳደረባቸው አካላት መኖራቸውም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ስውር
አይደለም። በይፋ በመንግሥት ደረጃ የተያዘ አቋም ባይሆንም፣ በተለያየ መልክ ይህን አቋም የሚያራምዱ የውጭ ኃይሎች መኖራቸውን
የሚያመለክቱ መረጃዎቸ አሉ። ለኤርትራ መንግሥት፣ ለኦነግና ኦብነገ በስውርና በይፋ ድጋፍ የሚያደረጉ አካላትን ልብ በሉ።
እነዚህ የቅርብና የሩቅ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች
ወደበለጸጉ ሃገራት ተርታ ወደመሰለፍ ሊያደርሳት እነደሚችል በግልጽ እየታየ ያለውን እድገትና ልማት እንቅልፍ ነስቷቸዋል። ይህ
ተጨባጭ የኢትዮጵያ እድገትና ልማት አገሪቱ ከምትከተለው የአካባቢውን ሰላም በማረጋገጥና በመጠቃቀም ላይ የተመሰረተ የውጭ
ግንኙነት ፖሊሲ፣ ይህን ለመተግበር ያደረገችው ጥረትና የደረሰችበት ውጤት የፈጠረላት ዓለም አቀፍ እውቅናና ቀጣይ ገናናነትም
እጅጉን ጎርብጧቸዋል። እናም የተከፋፈለች፣ በእርስ በርስ ግጭት የምትታመስ፣ ድኃና ኋላ ቀር ሊያደርጋት ይመኛሉ። ይህን
ምኞታቸውን በኃይል ማሳካት የሚያስችል እድል የላቸውም። እናም ስውር የእጅ አዙር የጥቃት መንገድ ያስፈልጋቸዋል።
ለዚህ የኢትዮጵያ የቅርብና የሩቅ ታሪካዊ ጠላቶች
የእጅ አዙር ጥቃት ማስፈፀሚያነት ቀድመው የተገኙት ቀደም ሲል በባህሪይ መለያቸው የተመለከትናቸው ኢትዮጵያን የማተራመስና
የመበታተን ህልም ያላቸው ትምክህተኛና ጠባብ ብሄረተኛ ቡድኖች ናቸው። እነዚህ ቡድኖች በቀጥታ በኤርትራ መንግሥትና በተዘዋዋሪ
ከሩቅ ታሪካዊ ጠላቶች በኤርትራ በኩል በሚደረገላቸው ድጋፍ በተለያያ መንገድ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ
ሙከራዎችን አድገዋል።
የሽብር ጥቃት አንዱ ሕዝቡን በማራድና መንግሥትን
በማስገደድ ፍላጎታቸውን ለማሳካት የተከተሉተ ስልት ነበር። ይህ ግን የትም አላደረሳቸውም። በተለይ ባለፉት አስር ዓመታት ከውጥን
ያለፈ አንድም የተሳካ የሽብር ጥቃት መፈፀም አልቻሉም፤ ሙከራዎቻቻው ሁሉ ከሽፈዋል። በሕዝቡ፤ በፌዴራል ፖሊስ የመረጃና
ጸረሽብር ግብረ ኃይል የተባበረ ሰላምን የመጠበቅ እርምጃ ነው የከሸፈባቸው፤
ይህ ስልት የትም እንዳላደረሰ ሲረዱ በአገር ውስጥ
ያሉ የልማት ክንውኖችንና ሌሎች ዴሞክራሲን በማጎለበትና ሕግን በማስከበር ሊስተካካሉ የሚችሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን
ያለወጉ በመተርጎም ሕዝብን በሕዝብ ላይ፤ እንዲሁም ሕዝብን በመንግስት ላይ በማነሳሳት ደም መፋሰስን ዓይነተኛ ስልት
አድርገውታል። ከአራት ዓመት በፊት በወልቃይት መገንባት የጀመረውን የስኳር ፋብሪካ፣ ከዋልድባ ገዳም ጋር በማገናኘት “ሃይማኖት ተደፈረ” በሚል የተካሄደው በሀሰተኛ መረጃ ሕዝብን
በማደናገር የማነሳሳት ሙከራ፤ በተመሳሳይ ጊዜ ተቀስቅሶ የነበረውን የአክራሪነት እንቅስቃሴ በመደገፍና በማበረታታት ያደረጉት
አገር የማፍረስ ሙከራ፤ ከሁለት ዓመት በፊት በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው የመላው ኢትዮጵያ ስፖርት ውድድር ላይ አንድን ብሔር
ነጥሎ የሚያንቋሸሹ ስደቦች በውድድር ስፍራ በይፋ እንዲነገር በማድረግ የተካሄደው የብሔር ግጭት የመቀስቀስ ሙከራ፤ በቅርቡ
የአዲስ አበባንና የፊንፊኔን ዙሪያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን ያለአግባብ በመተርጎም እንዲሁም በሰላማዊ መንገድ ሊጠየቁና ሊመለሱ
የሚችሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ያለወጉ በማራገብ የተቀሰቀሰው የኃይል ተቃውሞ፣ በአማራ ብሔራዊ ክልል ከቅማንት ሕዝብ
የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የተቀሰቀሰው ደም አፋሳሸ የእርስ በርስ ግጭት፣ እስካሁንም ድረስ እየተራገበ የመተላላቀ ምክንያት
እየሆነ የሚገኘው በሕገ መንግሥቱ መሰረት በሰላም ሊጠየቅና ምላሸ ሊያገኝ የሚገባው የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ለሁከትና
ለመተላላቅ መቀስቀሻነት ለማዋል እየተደረገ ያለው ሙከራ ወዘተ. ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።
እነዚህ በሀሰተኛ መረጃና እውነታዎችን በተሳሳተ
መንገድ በመተርጎም ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ ሕዝብን በመንግስት ላይ በኃይል እንዲነሳሳ የማድረግ ሴራ የሚፈፀመው ግን በየዋሀን ኢትዮጵያውያን
ነው። እናም በተለያዩ አጋጣሚዎች የተለያዩ አጀንዳዎችን ይዘው ሕገ ወጥ የኃይል መንገዶችን በመከተል ለሁከት የሚሰለፉና
ራሳቸውን ለመስዋዕትነት የሚያቀርቡ ወጣቶች የዚህ ውጤት ናቸው። የሁከትና የመተላላቅ አዝማቾቹ እሳቱ የማይነካቸው በተደላደለ ስፍራ
ላይ ተቀምጠው የእርስ በርስ ግጭት ቀስቅሰው ሰዎችን እንዲገድሉ፤ ንብረት እንዲያወድሙ፤ ቢቻል ይህ ሁከትና የእርስ በርስ
መገዳዳል በመላው አገሪቱ እንዲያዛምቱ ይቀሰቅሷቸዋል። ይህን ሕገ ወጥ ድርጊታቸውን ለመከላከል በሚወሰድ ሕግ የማስከበር እርምጃ
ሲቆስሉና በአስገዳጅ ሁኔታ ህይወታቸው ሲያልፍ ደግሞ ሰሞኑን እያደረጉ እንዳሉት የቆሰለ አካላቸውን፤ የአስከሬናቸውን ፎቶግራፍ
እየሸጡ፣ የሰብዐዊ መብት አያያዝ ሪፖርት ማድመቂያ እያደረጉ የኢትዮጵያን ገፅታ በዓለም ፊት ለማበላሸትና የበለጠ የእርስ በርስ
ግጭት መቀሰቀሻ የፖለቲካ ትርፍነት ያውሉታል።
ሰሞኑን እየተደረገ ያለው ይህ ነው። እናም ሰላም
ወዳዱና ከኢትዮጵያ ሰላምና ልማት ቀዳሚ ተጠቃሚ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተለይ
ወጣቶች የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችና የተላላኪዎቻቻው የእልቂት መሳሪያ ላለመሆን መጠንቀቅ አለባቸው። እርግጥ ነው በአገሪቱ
ያለው ሁኔታ ያበቃለት ምሉዕ በኩለሄ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ከፊሉ ችግር ከዘመናት ድህነት የተወረሰና በኢኮኖሚ እድገትና ልማት
ብቻ እየተቃለለ የሚመጣ መሆኑን መገነዘብ ያስፈልጋል። የማንነትን ጥያቄ በተመለከተም ሕገ መንግሥቱ የሚፈታበትን ሥርዓት
ማስቀመጡን አስታውሱ! ከኪራይ ሰብሳቢነትና ኪራይ ሰብሳቢነት ከሚፈጥረው
የመልካም አስተዳደርና ፍትሀዊ የኃብት ክፍፍል እጦት የሚወጡትን ችግሮች በተመለከተ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል ብቻ የሚስተካካል
መሆኑን ልብ ማለት ተገቢ ነው። እናም ወጣቶች የጥፋት አዝማቾች ተከታይ ጀሌ ከመሆን ራሳቸውን ይጠብቁ!
No comments:
Post a Comment