Friday, 19 August 2016

በመኸሩ በምርት ለመንበሽበሽ…!




ዮናስ
ኢትዮጵያ እጅግ ሠፊና የተለያየ ስነ-ምህዳር ያላት አገር በመሆኗ በኢትዮጵያውያን የተለመዱና የኢትዮጵያ ብቻ የሆኑትን ጤፍ፤ ገብስ፤ እንሰት፤ ጫት እና ሌሎችም አገር በቀል ሰብሎች መኖራቸው ሲታይ መልማት የሚችል እምቅ ሀብት እንዳለን ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ፤ የግብርናው ሥራ ኋላ-ቀር በመሆኑ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም ሆነ በየጊዜው ከአየር ንብረት መዛባት ጋር ተያይዞ የሚገጥሙንን ችግሮች በአስተማማኝ መልኩ ለመቋቋም አላስቻለንም፡፡
ሕዝቡን ከድህነት የሚያላቅቅ፤ በሂደትም የበለፀገ አገር ለመገንባት የሚያስችልና የግብርናን ልማት የሚያፋጥን ፖሊሲና ስትራቴጂ ወጥቶ በሁሉም አካላት የጋራ ርብርብ ተግባራዊ ማድረግ የተጀመረ ሲሆን መንግስትም ለግብርናና ገጠር ልማት ሥራዎች ንዲሁም ለገጠሩ ህብረተሰብ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ባለፉት ዓመታት ስብርብራችንን በማውጣት የሚታወቀውን ድርቅ በዚህ ዓመት የተቋቋምንበት ደረጃ ላይ መድሳችን በራሱ አብይ አስረጅ ነው፡፡ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ያለንን የልማት አቅም፤ ማለትም ሰፊ ጉልበት፤ መሬትና ውኃ እንዲሁም ውስን ካፒታል በቁጠባ ለመጠቀም የሚያስችል በመሆኑም፤ በሂደት ግብርናው የኢንዱስትሪ ግብዓትን፤ የካፒታል ክምችትን፤ የገበያ ዕድልንና የጉልበት አቅርቦትን በማረጋገጥ ለከተማውና ለኢንዱስትሪው ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት መቻሉም አያጠያይቅም፡፡
የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተነድፎ ወደ ተግባር ሲገባ የተለያዩ መነሻዎች የነበሩት ሲሆን፤ ዋናውጀንዳ ግን ተከታታይነት ባለው ሁኔታ መመዝገብ የጀመረውን የግብርውን ምርትና ምርታማነት ዕድገትም ሆነ ፈጣኑን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስቀጠል የአርሶ አደሩን፤ ብሎም የመላውን ሕዝብ ተጠቃሚነት ወደላቀ ደረጃ ማሻጋገር ነው፡፡ በዚህም በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ ላይ በግብርናው ዘርፍ 6 ነጥብ 6 በመቶ አማካይ ዕድገት የተመዘገበ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላስመዘገበው 10 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት ግብርናው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ይታወቃል፡፡ ያም ሆኖ ግን፤ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ይህ እድገት እንዳይዋዥቅ የተጠናከረ ሥራና ትጋት የሚጠይቅ መሆኑ አያከራክርም።
ይህ ትርክትም በተለይ ዘንድሮ ገጥሞን ከነበረው ድርቅና ጎርፍ ጋር ተያይዞ፤ የሚጠበቀውን ከባድ ዝናብ በምን አግባብ እንደምንቆጣጠረውና ለተሻለ ጠቀሜታ እንደምናውለው ሳይንሱን ከተሞክሮ ጋር አዋህዶ መረጃ የሚሰጥ ነው።
በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ከተቀመጡ ግቦች አንጻር አፈጻጸሙ ሲታይ  95 በመቶ በላይ የሚሆነው የግብርና ምርት የተመረተው በአነስተኛ አርሶ አደር ማሳ ላይ ነው። ይህም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንና አዳዲስ አሰራሮችን በአነስተኛ አርሶ አደር ማሳ ላይ በመተግበር የግብርናን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እንደሚቻል የሚያረጋግጥ በመሆኑ፤ መላው አርሶ አደር በዚህ የመኸር ዝግጅት ወቅት ሊከተለው የሚገባ የመጀመሪያው አቅጣጫ ነው፡፡  
በተፈጥሮ ሀብት ልማት ረገድም፤ በዕቅድ ዘመኑ መነሻ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር የነበረውን በተለያዩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የተሸፈነ ማሳ 8 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ማድረስ ስለመቻሉ መረጃዎች ያመላክታሉ።ይህ ከሆነ ደግሞ፤ ከዚህ ስኬት በስተጀርባ ያለው ምስጢር ለዚህ መኸር ጠቃሚ ተሞክሮ ይሆናል። ይኸውም የህብረተሰቡ ሰፊና የተደረጃ ንቅናቄና ተሳትፎ ነው፡፡ የተፋሰሱልማት ሥራ እንስሳትማድለብ፤ በግና ፍየል በመሞከት፤ ንብ በማነብና በመሳሰሉት ዘርፎች በሚሊዮን ለሚቀጠሩ የገጠር ወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ይህ ሥራ በስፋቱም ሆነ ህብረተሰቡን በማሳተፍና ተጠቃሚነተቻውን በማረጋገጥ ረገድ በአህጉራችንም ሆነ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በምርጥ ተሞክሮነት የሚጠቀስ ነው፡፡
በግብርናው ዘርፍ የሚታዩትን ውስንነቶች ከመፍታት አኳያ፤ አርሶና አርብቶ አደሩን ማኅበረሰብ በአመለካከትና በክህሎት የማብቃት ተከታታይ ሥራ በመስራት ምርታማነቱን የማሳደግ፤ እነዚህን የልማት አቅሞች ከተግባር ጋር በማስተሳሰር የማብቃት፤ አደረጃጀቶቹን የማጠናከርና የልማት አቅሞቹን የማነቃነቅ፤ እንዲሁም ውጤታማ ተሞክሮዎችን እየቀመሩ የማስፋት ሥራ ማከናወን መኸሩን ውጤታማ ያደርግልናል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎንም ተፋሰስን መሠረት ያደረገ የግብርና ልማት ሥራ መስራት ለዚህ መኸርም ሆነ ዘላቂነት ላለው ልማት ወሳኝ ነው። ሰፋፊና አነስተኛ የመስኖ አውታሮች ተገንብተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው፤ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት፤ የግብዓትና ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎች አቅርቦት መሻሻሉን፤ በተጨማሪም የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋንና ተደራሽነት እየጨመረ መምጣቱን ታሳቢ ያደረገ የአኗኗር፤ የአመራረትና የአረባብ ዘይቤ ጭምር መቀየር ያስፈልጋል፡፡
ግብርናችን ያለማቋረጥ እያደገ በመምጣቱ ለአደጋ ተጋላጭነታችንና ድርቅን የመቋቋም አቅማችን እንደ አገር እየተገነባ የመጣበት እውነታ ከላይ በተመለከተው አግባብ ቢኖርም ከአካባቢ አካባቢ የተለያየ አፈፃፀም አለው። አሁንም ለአየር ንብረት መዛባት ተጋላጭነት ያላቸው አካባቢዎች ያሉን መሆኑን ታሳቢ ያደረገ፤ ይልቁንም ጠንከር ያለ ድርቅ ቢከሰትንኳን ችግሩን ተቋቁሞ የማለፍ አቅማችንን የሚጨምር ዝግጅት ከወዲሁ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ የተሟላ አቅም መገንባት ገና የሚቀረን መሆኑም ግንዛቤ ተይዞበት ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የግብርና ዕድገት እየተመዘገበ ባለበት ልክ የድርቅ መቋቋምና የአደጋ መከላከል አቅማችንን ማሳደግ እንደሚገባን ሊሰመርበት ይገባል፡፡
ከውቅያኖሶች ሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ የተከሰተው የአየር መዛባት ያስከተለው አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። እንደዚህ ዓይነቱን ክስተትም ሆነ ተያያዥ ችግሮችን መቋቋም የምንችለው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት ስንችል ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም። የተጀመረውን የተፈጥሮ ሀብትና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ከመስኖ ልማቱ ጋር አስተሳስሮ በላቀ ቁርጠኝነት በመፈጸም የግብርናን ምርትና ምርታማነት ዕድገት ማስቀጠል ወደ ኢንዱትራላይዜሽን የምናደርገውን ሽግግር በሚያቀላጥፍና አገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ የያዘችውን የህዳሴ ጉዞ በሚያሳካ መንገድ ለመፈጸም ያስችላል።
ስለሆነም አርሶ አደሮች በልማት ቡድን ተደራጅተው ለመኸር ሰብል እንክብካቤ ማድረግ ግድ ይላቸዋል፡፡ ይኸውም በማሳ ላይ ያለውን ሰብል የማረምና የመኮትኮት ሥራ የሚያጠቃልል ነው፡፡ የአረሙንና የኩትኳቶውን ሥራ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች በማሳተፍና በግብርና ባለሙያዎች በመታገዝ ጭምር ማከናወን ደግሞ የበለጠ ውጤታማ ያደርጋል። ይህም በዚህ መኸር ሁሉም ሊከተለው የሚገባ አቅጣጫ ነው፡፡ የልማት ቡድኖችን በማጠናከር ከዘር ጀምሮ እስከ ምርት ስብሰባ ድረስ በጋራ መስራትም ተገቢና ሊዘነጋ የማይገባው ተግባር ነው፡፡ በልማት ቡድኖች አደረጃጀት የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች በተናጠል ከሚከናውኑት በበለጠ ጊዜና ጉልበት ይቆጥባሉ፡፡ በጋራ የሚከናወነው ሥ ከሰብል ልማት በተጨማሪም የችግኝ ተከላና እንክብካቤ የሚያካትት መሆን አለበት፡፡ በቡድን ስራ ላይ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ልምዳቸውን የሚያካፍሉበትን አሰራር መዘርጋት ለመኸሩ እርሻ ውጤታማነት አስፈላጊ ነው፡፡
የክረምቱ ዝናብ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት በመጠንና በስርጭት እየተጠናከረ እንደሚሔድ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የሰጠውን መረጃ ማስታወስ ተገቢ ነው። ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ አሁን እየታየ ያለው ዝናብ በአብዛኛው የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ በመጠንም ሆነ በስርጭት እየተጠናከረ ይሔዳል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም በአገሪቱ ሰሜናዊ አጋማሽ ላይ የተሻለ ርጥበት ሊታይ እንደሚችል ይጠበቃል። አልፎ አልፎ በፀሐይ ታግዘው ከሚፈጠሩ ጠንካራ ደመናዎች ቅፅበታዊ ጎርፍና የወንዞች ሙላት ሊያስከትል የሚችል ከባድ ዝናብ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሊኖር ይችላል ብሏል።
በተጨማሪም የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አንዳንድ የአገሪቱ ሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች የዝናቡ አወጣጥ በመጠኑ ሊዘገይ እንደሚችል ነው፤ ኤጀንሲው በትንበያው የገለፀው
ስለሆነም ይህ የአየር ሁኔታ በመኸር ወቅት ለሚመረቱ ለመካከለኛና የረዥም ጊዜ ሰብሎች ዕድገት፤ ለቋሚ ሰብሎች የውሃ ፍላጎት፤ ለአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የመጠጥ ውሃና ለግጦሽ ሳር አቅርቦት አዎንታዊ ገጽታ እንዳለው ማጤንና በጥቅም ላይ ማዋል ይገባል
ከዚህም ባሻገር እንደትንበያው፤ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ርጥበቱ ከመጠን በላይ ሊሆን ስለሚችል በዚህ ምክንያት ውሃማሳ ላይ እንዳይተኛ ቦይ በማውጣትና በማንጠፍጠፍ የመከላከል ሥራ ማከናወን ከመኸር ዝግጅቶቻችን ዋናው ሊሆን ይገባል። ከግብርና ባለሙያዎች በሚገኙ ምክረ ሐሳቦች በመደገፍ አረምን በወቅቱ በማረም፤ ፀረ-አረምና ፀረ- ተባይ ኬሚካሎችን በወቅቱ በመጠቀም ጥንቃቄ ማድረግም በተመሳሳይ በትንበያው መሠረት በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ በሚጠበቅባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሩና የሚመለከታቸው አካላት በሰብሎችና በእንስሳት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ተገቢውን ጥንቃቄ ከማድረግ ሊቦዝኑ አይገባም። በአንፃሩ፤ በቆላማ የአገሪቱ አካባቢዎች የተገኘውን ርጥበት በአግባቡ በመጠቀምና የውሃ እቀባ፤ የኩሬ ማጎልበትና የዝናብ ውሃ መሰብሰብ ስራ ማከናወን የመኸር ዝግጅቱ ቁልፍ ተግባራት ሊሆኑ ይገባል።




No comments:

Post a Comment