Wednesday, 31 August 2016

ፌዴራላዊ ሥርዓቱን ከትምክህተኞችና ከጠባብ ብሄረተኞች መጓተት እንጠብቅ!




ኢብሳ ነመራ
ኢትዮጵያ ከ80 በላይ የተለያየ ማንነት ያላቸው ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች አገር ነች። እነዚህ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች አንዱን  ከሌላው የሚለያቸው ቋንቋ፤ ባህልና ወግ፤ ታሪክ… ባለቤቶች ናቸው። የዚያኑ ያህል፤ በተለይ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ጀምሮ በአንድ አሃዳዊ ሥርዓት ስር በተዳዳሩባቸው ዓመታት በክፉም ይሁን በደግ ያፈሯቸው የጋራ እሴቶች አሏቸው። ለምሳሌ፤- በከተሞች አካባቢ የሚኖሩ የሁሉም ብሄር ብሄረሰብ አባላት ቢያንስ ለመግባቢያ ያህል አማርኛ ቋንቋ ያውቃሉ። በሌላ በኩል፤ የኢትየጵያ የተለያዩ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ማንነት ግን በጥናታዊ ፅሁፎች፤ በመጻህፍት ላይ ከመጠቀስ ያለፈ ሕጋዊ እውቅና ተነፍጎት ነበር የቆየው፤ ከተጠቀሰው ጊዜ በኋላ አሁን ያለው የአገሪቱ ወሰን በዘውዳዊ ሥርዓት መተዳደር ከጀመረ በኋላ ባለው አንድ ክፍለ ዘመን ያህል እድሜ፤
የሕግ እውቅና ተነፍጓቸው ነበር ማለት በቋንቋቸው ፍትህን ጨምሮ የመንግሥት አገልግሎት የማግኘት መብት፤ ቋንቋቸውን ለትምህርት መስጫነት የመጠቀም  መብት አልነበራቸውም ማለት ነው። ይህም ብቻ አይደለም፤ ታሪካቸው ሥርዓቱ የወሰን አንድነቱን ለማጽናት ባነጸው መሰረት ነበር ሲነገር የነበረው፤ እውነተኛ ታሪካቸው ተሸሽጎ ነበር። ባህላቸው አልፎ አልፎ ለይስሙላ ያህል ወይም ጭፈራ ለማድመቅ ያህል ጣል ጣል ከሚደረጉ ዘፈኖችና ጭፈራዎች የዘለለ ብዙም ዋጋ አልተሰጠውም ነበር። በአጠቃላይ የባህል ትንሽ ያለው ይመስል ዝቅ ተደርጎ ነበር የሚታየው፤
ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች አባላት በማንነታቸው እንዲሸማቀቁ፣ ማንነታቸውን እንዲደብቁ ያደረገ አስገዳጅ ሁኔታ ፈጥሯል። ማንነታቸውን የሚገልጸውን ስማቸውን ይቀይሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።
ዘውዳዊው ሥርዓት ይህን ሲያደርግ የነበረው በአጋጣሚ ወይም በየዋህነት ስህተት አልነበረም። ሆን ተብሎ ብዘሃነትን በማቅለጥ ሥርዓቱ የአገዛዙን ቅቡልነት ለማረጋጋጥ የእኔ ነው ብሎ በያዘው አንድ ብሄራዊ ማንነት፤ ቋንቋ፣ ባህል . . . ቀጥቅጦ ለመቅረፅ ታስቦና ስትራቴጂ ተነድፎለት የተካሄደ ነበር።
ዘውዳዊው ሥርዓት አቅልጦ፤ በአንድ ብሄራዊ ማንነት ቀጥቅጦ ለመቅረፅ የሞከረው የብሄር ብዝሃነትን ብቻ አልነበረም። ይልቁንም፤ የሃይማኖትንና የአመለካከትን ብዝሃነት ጭምር እንጂ፤ ዘውዳዊው ሥርዓት መንግሥታዊ ሃይማኖት ነበረው። በአገሪቱ የሚገኙ ሌሎች ሃይማኖቶች ሕጋዊ እውቅና አልነበራቸውም። ለምሳሌ፤- ሙስሊሞች እንደ ኢትዮጵያዊ አይቆጠሩም ነበር። በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሙስሊሞች ነበር የሚባሉት፤ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አይባሉም። የአመለካከት ብዝሃነትም ክልክል ነበር። ማንኛውም ዜጋ የዘውዳዊውን ሥርዓት ምሉዕ በኩለሄነት የሚክድ ወይም የሚጻረር አቋም የመያዝ፤ የማራመድ፤ የመግለጽ፤ በዚህ አመለካከት የመደራጀት መብት አልነበረውም።
የዘውዳዊው ሥርዓት ፖለቲካል ኢኮኖሚ ፊውዳሊዝም ነበር። የፊውዳሊዝም ኢኮኖሚ መሰረት የሆነው መሬት በመሳፍንቱ፤ በመኳንነቱና በሌሎች ሥርዓቱ በተለያያ ደረጃ በሚሾማቸው ቢሮክራቶችና ዳኞች ይዞታ ስር ገሚሱ በርስትነት፤ የተቀረው በጉልትነት ነበር። በተለይ የሥርዓቱ ቢሮክራቶችና ዳኞች ጉልተኞች ነበሩ። ሥርዓቱ ቀደም ሲል በነበረው ጊዜ ለቢሮክራቶች ደመወዝ የሚከፍለው በገንዘብ ሳይሆን በጉልት ነበር። የሥርዓቱ መሳፍንት፤ መኳንንት፤ ቢሮክራቶችና ሌሎች በርስትነትና በጉልት የያዙት መሬት የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች አቅንተው ይኖሩበት የነበረውን ነው። በተለይ ዘውዳዊው ሥርዓት በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ላይ ወሰኑን በማስፋት ያካተታቸው የመካከለኛው፤ የደቡብ፤ የምስራቅና ምዕራብ የአገሪቱ አካባቢዎች ባለአገሩ መሬቱን ተነጥቆ በገዛ መሬቱ ላይ በንጉሠ ነገሥቱ ትእዛዝ መሬት በርስትነትና ጉልት ለተሰጣቸው መሳፍንት፤ መኳንንትና ቢሮክራቶች ገባር ጭሰኛነት ተዳርገዋል። ምርታቸውንና ጉልበታቸውን ለባለርስቶችና ለባለጉልቶች የሚገብሩ ምንም የሌላቸው ያጡ የነጡ ደሀ ገባር ጢሰኛ አርሶ አደሮች ሆነው ነበር።
ይህ የአገሪቱን የብሄር፤ የሀይማኖት፤ የአመለካከት ብዝሃነት እውቅና የነፈገና ብዝሃነትን አቅልጦ በአንድ ማንነትና አመለካከት የመቅረጽ ስትራቴጂ የነበረው ዘውዳዊ ሥርዓት ስትራቴጂውን አሳክቶ አንድ የተለየ ማንነት ያላቸው ዜጎች መፍጠር አልቻለም። ከዘውዳዊው ሥርዓት መንግሥታዊ ሃይማኖት ውጭ የሆኑ ሃይማኖቶች ምንም ያህል ቢገፉ የተወሰኑ ወደሥርዓቱ መጠጋት የፈለጉ ሰዎች ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ ከማድረግ ያለፈ ሃይማኖቶቹን ግን ማደብዘዝ አልቻለም። ሰዎች የማሰብ ችሎታቸው እስካለ ደረስ ነባራዊውን ዓለም ከሚረዱበትና ከሚተነተኑበት የገሃዱ ዓለም አተያይ ወይም ርዕዮተ ዓለም አልቦ ሆነው መኖር ስለማይችሉ የአመለካከት ብዝሃነትን ከማዳፈን ያለፈ ማጥፋት አልቻለም።
የተለያያ ማንነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ይህንን በማንነታቸው ላይ የተጫነ ቀንበር በጸጋ ተቀብለው አያውቁም። በመጀመሪያ ለዚህ የዳረጋቸውን ነባራዊ ሁኔታ በመርህ ተንትኖ በሥርዓት ደረጃ (system) መረዳት የሚያስችል ግንዛቤ ስላልነበራቸው ተቃውሟቸው በሥርዓቱ ላይ ሳይሆን፤ ይልቁንም በተበታታነ ሁኔታ አጠገባቸው በነበረ አስገባሪ ወይም ቢሮክራት ላይ ያተኮረ ነበር። ይህ የተቃውሞና የትግል አካሄድ አርሶ አደሮቹን ለሞት፤ ለእስር፤ ለአደባባይ ግርፋትና ለውርደት ከመዳረግ ያለፈ ጭቆናቸውን ግን ከላያቸው ላይ ሊያወርድላቸው አልቻለም። በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተካሂደው የነበሩ “የገበሬ አመፅ” የሚባሉ የአርሶ አደር ንቅናቄዎችን ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል።
እየከረመ፤ ዘመናዊ ትምህርት ወደሕዝቡ እየዘለቀ፤ የተለያዩ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች አባላት የሆኑ ልሂቃን አየተፈጠሩ ሲመጡ፤ ፊውዳላዊውን ዘወዳዊ ሥርዓት ምንነት በመተንተን የጭቆናውን ምንጭ መለየት ተቻለ። ይህን ተከትሎ በሥርዓቱ ላይ ያተኮረ ተቃውሞ መቀሰቀስ ጀመረ። የአገሪቱን አርሶ አደር ከገባር ጭሰኝነት ለማላቀቅ የመሬት ለአራሹ ጥያቄ ሲቀርብ፤ ከዚሁ ጋር የብሄርና የሃይማኖት እኩልነት ጥያቄ ጎልቶ መውጣት ጀመረ። ይሄኔ ነበር ተቃውሞው በሥርዓቱ ላይ ያተኮረው።
ይሁን እንጂ ይህ ትግል የልሂቃን ማፍሪያ በሆኑ የ2ኛ ደረጃና ጥቂት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተገደበ ነበር። ትግሉም የተደራጀና መደረሻውን የሚያውቅ አልነበረም። በመጨረሻ ይህ የተማሪዎችና የልሂቃን ተቃውሞ ስርአቱን መነቅነቅ ቢችልም የተነቃነቀውን ስርአት አስወግዶ በህዝባዊ መንግስት መተካት ግን አልቻለም። ይህ የሆነው ትግሉ የተደራጀና መድረሻውን አንጥሮ የሚያውቅ ሰላልነበረ ነው። አናም በወቅቱ የተፈጠረውን የስልጣን ክፍተት ለመድፈን የሚያስችል አደረጃጃትና አቅም የነበረው ያንኑ ዘውዳዊ ስርአት ሲያገለግል የነበረው መለዮ ለባሹ ነበር።
መለዮ ለባሹ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ወደስልጣን ሲመጣ፤ የሥርዓት ለውጥ የማምጣት ዓላማ አልነበረውም። በጥገናዊ ለውጥ ሥርዓቱን ማስቀጠል ነበር ዓላማው፤ ይሁን እንጂ፤ በወቅቱ ጎልቶ የወጣውን 90 በመቶ ገደማ የአገሪቱን ሕዝብ በሚወከለው አርሶ አደር ላይ የተጫነውን የገባርነት ጭቆና በጥገና ማለፍ የሚያስችል ሁኔታ አልነበረም። በመሆኑም ታሽቶ ታሸቶ ወደስልጣን በመጣ በስድስተኛው ወር የመሬት ለአራሹን አዋጅ አወጣ። በዚህ አዋጅ የኢትዮጵያ አርሶ አደር በባለርስትና በባለጉልት ተጭኖበት የነበረው የገባርነት ጭቆና ተነሳለት። የራሱ መሬትም ኖረው፤
ወታደራዊው ቡድን አስከፊነቱ ጎልቶ ወጥቶ ለነበረው ኢኮኖሚያዊ ጭቆና ምላሸ ቢሰጥም የኢትዮጵያን የብሄር፤ የአመለካከትና የሃይማኖት ብዝሃነት ማክበር ግን አልፈቀደም። የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች እውቅና መነፈጋቸው ቀጠለ። በቋንቋቸው የመንግሥት አገልግሎት አያገኙም። ልጆቻቻውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማስተማር አይችሉም። ቋንቋቸውንና ባህላቸውን ማሳደግና ማስተዋዋቅ፤ ትክክለኛ ታሪካቸውን ማውጣትና መንከባከብ፤ በሚኖሩበት ወሰን ውስጥ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት መነፈጋቸው ቀጠለ።
ጭቆናው ሲቀጥል ትግሉም ቀጠለ። በወቅቱ ሃያ ገደማ የሚሆኑ በብሄራዊ ማንነት ተደራጅተው ወታደራዊውን ሥርዓት ለማስወገድ የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ የነበሩ የብሄራዊ ነፃነት ድርጅቶችን የፈጠረው ይህ ነባራዊ ሁኔታ ነው። በአመለካካት ተደራጀተው ሥርዓቱን ለማስወገድ የሞከሩና በውጭ አገር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ድርጅቶችም ነበሩ። ወታደራዊውን አገዛዝ ለመጣል በተካሄደው ትግል ውስጥ የነበራቸው ድርሻ የአንዳቸው ከሌላው የተለያየ መሆኑ ባይካድም፤ ወታደራዊው ደርግ ለውድቀት የበቃው በዚህ የነፃነት ትግል ነው።
ወታደራዊው ደርግ ተወግዶ ግዙፉ ሰራዊቱ ሲበተን አገሪቱ በተለያየ አቅጣጫ የነፃነት ትግል ሲያካሂዱ በነበሩ ኃይሎች ተቦጫጭቃ ለመበታተን በሚያበቃ ሁኔታ ለአደጋ ተጋልጣ ነበር። ይሁን እንጂ፤ ሁሉም በብሄር ላይ ተመስርተው የተደራጁና በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩት ሌሎችም ኃይሎች በየአቅጣጫው አገሪቱን ከመቀራመት ይልቅ፤ ተጭኖባቸው የነበረውን ጭቆና አስወግደው አብረው መኖር ይችሉ እንደሆነ በአንድ አዳራሽ ታድመው መከሩ። እናም አሃዳዊውን የመንግሥት ሥርዓት ሸረው ብዝሃነትን የተቀበለ፤ ሕዝቦች በፈቃዳቸው የሚሳተፉበትና በእኩልነት አብረው የሚኖሩበት መንግሥት ለመመስረት ተስማሙ። ወደዚህ የሚያደርሳቸውን የሽግግር መንግሥትም አቋቋሙ። 
የሽግግር መንግስቱ ዋና ተግባር የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በመፈቃቀድ፤ በእኩልነት፤ በመከባባርና በመቻቻል የሚኖሩበት፤ የወሰን ሳይሆን የሕዝቦች አንድነት ያላት አገር መመሰረት የሚያስችል ሕገ መንግሥት በሕዝብ ተሳትፎና ውሳኔ እንዲዘጋጅ ማድረግ ነበር። የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የተዘጋጀውና የጸደቀው፤ የኢፌዴሪ መንግሥትም የተመሰረተው በአጭሩ ይህን ሂደት ተከትሎ ነበር። ይህን የኢፌዴሪ መንግሥት ምስረታ ሂደት ጠቅለል አድርጌ ያቀረበኩት የቅርብ ጊዜ ታሪካችን አካል በመሆኑ ሁሉም ለአካለ መጠን የደረሱ ኢትዮጵያውያን ያውቁታል በሚል እምነት ነው።
እንግዲህ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ባለቤቶች ማንነታቸውን እንደጠበቁ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በፈቃዳቸው ከሌሎች አቻዎቻቸው ጋር ኢትዮጵያ የምትባል አገር ዜጎች ሆነው በእኩልነት ለመኖር የተስማሙ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው። ይህን እውን ማድረግ የሚያስችለው የመንግሥት አወቃቀር ደግሞ ፌዴራላዊ አወቃቀር ነው። በዚህ መሰረት በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 1 “የኢትዮጵያ መንግሥት ስያሜ” በሚል ርዕስ ስር፤ ይህ ሕገ መንግሥት ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አወቃቀርን ይደነግጋል። በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ በሚል ስም ይጠራል። የሚል ድንጋጌ ሰፍሮ እናገኛለን።
ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለኢትዮጵያ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የአገሪቱ ህልውና መቀጠል ወይም ያለመቀጠል ጥያቄ ነው። አገሪቱ የብሄርና የአመለካከት ብዝሃነቷን ጠብቃ እንድትቆይ ከተፈለገ ምትክ የሌለው አማራጭ ነው።
እንግዲህ፤ ፌዴራሊዝም የየራሳቸው የስልጣን ወሰን ያላቸውን የሁለት መንግሥታት ሥርዓት አጣምሮ የያዘ ነው። ማለትም ማዕከላዊውን ወይም የፌዴራል መንግሥቱንና እንደየአገራቱ ነባራዊ ሁኔታ የተዋቀሩ የግዛት ወይም የክልል መንግሥታትን የያዘ ነው። በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ የፌዴራሉ አካል የሆኑት ክልላዊ መንግሥታት የተዋቀሩት በአመዛኙ በብሄር አሰፋፈር ላይ በመመሰረት ነው። የክልልን አወቃቀር በተመለከተ ሕገ መንግሥቱ “ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፋር፤ ቋንቋ፤ ማንነትና ፈቃድ ላይ ነው” ሲል ይደነግጋል። በዚህ መሰረት የፌደራል መንግሥቱ አካላት የሆኑ ዘጠኝ ክልሎች ተወቅረዋል። የፌዴራል መንግሥቱ ማለትም፤ የኢፌዴሪ መንግሥት በእነዚህ ክልሎች የተዋቀረ ብቻ ሳይሆን ስልጣኑም የመነጨው ከእነዚህ ክልሎች ነው። የፌዴራል መንግሥቱ ከክልሎቹ የተነጠለ የራሱ ህልውና የለውም።
በክልሎች የተዋቀረው ፌዴራላዊ መንግሥት ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት አስገኝቶላቸዋል። በሚኖሩበት ክልል፤ ዞን ወይም ወረዳ በመረጧቸው ወኪሎቻቸው አማካኝነት ይተዳደራሉ። በቋንቋቸው የመንግሥት አገልገሎት ያገኛሉ። ልጆቻቻውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ያስተምራሉ። ታሪካቸውን ይንከባከባሉ። ባህላቸውን ያሳድጋሉ። በወሰናቸው ውስጥ ያለውን እምቅ የኢኮኖሚ  አቅም ለሕዝባቸው የተሻለ ህይወት ጥቅም ላይ ያውላሉ። ወዘተ. ሁሉም ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳደሩና ፌዴራል መንግሥቱን የመሰረቱ የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የፌዴራል መንግሥቱ ከፍተኛ የስልጣን አካል በሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕዝባቸው ቁጥር ልክ ስልጣን ይጋራሉ። ሕገ መንግሥታቸውን የመተርጎም ስልጣን ባለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውስጥም ውክልና አላቸው። አበስፈጻሚው አካል ውስጥም በተመሳሳይ የብሄር ተዋጽኦንና ብቃትን ታሳቢ ባደረገ አኳኋን ይሳተፋሉ።
በኢፌዴሪ የመንግሥት ሥርዓት ውስጥ አንድ ብሄር የበላይ ሆኖ ሌሎችን ከፈቃዳቸው ውጭ መግዛት፤ ወይም በክልላዊ ጉዳያቸው ውስጥ ጣልቃ መግባት የሚያስችል እድል የለም። ኦሮሚያን የሚያስተዳድሩት ኦሮሞዎቸ ናቸው። አማራን፤ ትግራይን፤ የኢትዮጵያ ሶማሌን፤ አፋርን፤ ወዘተ. የሚያስተዳድሩት ክልሎቹን የመሰረቱት ብሄሮችና ብሄረሰቦች ናቸው። አማራ ወይም ትግራይ የኢትዮጵያ ሶማሌን ወይም ኦሮሚያን ወይም አፋርን በበላይነት ማስተዳደር የሚያስችላቸው አንድም መንገድ የለም። ይህ አሁን በአገሪቱ በተጨባጭ እየታየ ያለ ዕውነታ ነው። እናም በአገሪቱ የአንድ ብሄር ወይም አንድን ብሄር የሚወክል ፓርቲ የበላይነት አለ ብለው በግድ እመኑ የማለት ያህል የሚጨቃጨቁ፤ በተለይ አሃዳዊ ሥርዓት የመመሰረት ህልም ያላቸው ተቃዋሚ ቡድኖች ወሬ መሰረተ ቢስ መሆኑን ያሳያል።
ያም ሆነ ይህ፤ ኢትዮጵያ በአገሪቱ የነበረውን መሰረታዊ ቅራኔ፤ ማለትም የብሄርን ቅራኔና ብዝሃነትን ታሳቢ በማድረግ የአገሪቱ አንድነት ተጠብቆ እንዲዘልቅ ያለአማራጭ ተመራጭ ሆኖ የተዋቀረው ፌዴራላዊ ሥርዓት ግን ሥራ ላይ በቆየባቸው ያለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ተቃውሞዎች ገጥመውታል። ቀዳሚዎቹ የፌደራላዊ ሥርዓቱ ተቃዋሚዎች የአገሪቱን ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች አቅልጠው ማንነታቸውን አጥፍተው በአንድ መለያ ማንነት የመግዛት ህልም ያላቸው የአሃዳዊ ሥርዓት አራማጆች ናቸው። እነዚህ ቡድኖች ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት አገሪቱ ተከፋፈለች፤ ተበጣጣሰች፤ አንድነቷ ጠፋ ወዘተ. እያሉ ውዥንብር ሲነዙ፤ ለዚህም ተጠያቂ ያሉትን ወገን በጠላትነት ፈርጀው ሲያወግዙና ሕዝብ እንዲነሳበት ሲቆሰቁሱ ቆይተዋል። እነዚህ ቡድኖች አገሪቱ በብሄር ላይ ወደተመሰረተ ፌዴራላዊ ሥርዓት የመጣቸው የአገሪቱ ህልውና ዘላቂ እንዲሆን ብቸኛው አማራጭ ስለሆነ መሆኑን አያውቁም ወይም ማወቅ አይፈልጉም። አገሪቱን ወደአሃዳዊ ሥርዓት መመለስም መድረሻው መበታተን ብቻ መሆኑን ማሰብ አይፈልጉም። በእርግጥ  ከቅርብ ግዜ ወዲህ እኛ የምንመኘው አሃዳዊ ሥርዓት መምጣት ወይም መመለስ ካልቻለ አገሪቱ ትጥፋ የሚል አቋም የያዙ ይመስላሉ። ኢትዮጵያን እርስ በርስ በማተራመስ ለመበታተን ስትራቴጂ ነድፎ በሚሰራው የኤርትራ መንግሥት ስር በትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚነት የተሰለፉ የአሃዳዊ ሥርዓት ተስፈኞች ለዚህ በአስረጂነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። እነዚህ የአሃዳዊ ሥርዓት ተስፈኞች በጥቅሉ ትምክህተኛ ብሄረተኞች ናቸው። ብዝሃነትን ጨፍልቀው አንድ ማንነት የበላይ መሆን አለበት የሚል እምነት ያላቸው ትምክህተኞች፤
ሌላው ፌዴራላዊ ሥርዓቱን በመቃወም የተሰለፈው ወገን በብሄር ላይ የተደራጀ ጎራ ነው። በዚህ ጎራ ያሉ ቡድኖች እንወክለዋለን የሚሉትን ብሄር በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከተረጋጋጠው የሕዝብን ፍላጎት መሰረት ያደረገ መንገድ ውጭ አንድን ብሄር ገንጥለው የመግዛት ፍላጎት ያላቸው ናቸው። እነዚህ ቡድኖች መገንጠልን መድረሻ ያደረጉም ናቸው። በመሰረቱ መገንጠል መብትና ነፃነት ወደተረጋገጠበት ሥርዓት መሸጋገርን የሚያረጋግጥ አካሄድ አይደለም። ኤርትራን ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል። የኤርትራ መገንጠል የኤርትራውያንን መብትና ነፃነት ማስከበር አልቻለም። መገንጠል ብቸኛ አማራጭ የሚሆነው በተለይ አሃዳዊ ሥርዓት የሚኖሩ ብሄሮች መብትና ነፃነታቸውን ማረጋገጥ የሚያስችል ምንም አማራጭ ሲጠፋ ብቻ ነው። ያኔ መገንጠል የመጨረሻ አማራጭ ነው። ከእነዚሀ ሁኔታዎች ውጭ የአንድን ብሄር መገንጠል የሚፈልጉ ቡድኖች በአብዛኛው ጠባብ ብሄረተኞች ናቸው። ይህን ከሕዝብ ፈቃድ ውጭ እንወክለዋለን የሚሉትን ብሄር ገንጥለው ለመግዛት የሚፈልጉ ቡድኖችም እንደአሃዳዊው ሥርዓት ተስፈኞች ሁሉ በኤርትራ መንግሥት ስር ኢትዮጵያን የማፈራረስ ስትራቴጂውን ለማስፈፀም ተሰልፈው እናገኛቸዋለን።
ከሁሉም የሚያስገርመው እነዚህ ፍፁም ተቃራኒ የሆኑ፤ ምንም የጋራ ነገር የሌላቸውና ሊኖራቸውም የማይችል ትምክህተኛ ብሄረተኞችና ጠባብ ብሄረተኞች በኤርትራ መንግሥት ትእዛዝ ግንባር ፈጥረው በየፊናቸው አገሪቱን እየጎተቱ የአገሪቱን አንድነት ማስጠበቅ የሚችለውን ብቸኛ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለማፈራረስ ሲፍጨረጨሩ ይታያሉ። ሰሞኑን በተወሰኑ የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች በማህበራዊ ሚዲያ በሚነዛ ውዥንብር የተቀሰቀሱት ሁከቶችና ሊቀሰቀሱ የታቀዱ ብጥብጦች አገሪቱን ከሁለት ከማይታረቁ ፅንፎች እየጎተቱ በእርስ በእርስ ብጥብጥ ፌዴራላዊ ሥርዓቱን የማፈራረስ ፍላጎትና ሙከራ ውጤት ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በዴሞክራሲያዊ ብሄረተኝነት መርህ ላይ በመመስረት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ያጸናውን ፌደራላዊ ሥርዓት ማፍረስ ማለት አገሪቱን ማፍረስ መሆኑን ተገንዝቦ ፌደራላዊ ሥርዓቱን ከትምክህተኛናከ ጠባብ ብሄረተኞች መጓተት መጠበቅ አለበት።

እነሆ ለአዲስ አበቤዎች በክብሮት ባርኔጣዬን አነሳሁ!




                                                  ቶሎሳ ኡርጌሳ
እሁድ ነሐሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም። ልክ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ላይ። አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እምብርቱ ላይ ተገኝቻለሁ። ከሰፈሬ ማልጄ ወደ መስቀል አደባባይ በታክሲ በመሄድ ስፍራው የተገኘሁት በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የከተማው ህዝብ ስርዓቱን እንዲያወግዝ በፀረ-ሰላም ኃይሎች የተጠራ ሰላማዊ ሰልፍ ካለ ለማየት ነበር። መስቀል አደባባይ ፊት ለፊት የሚገኘው የአዲስ አበባ ኤግዚቪሽን ማዕከል በሚያስገባው ደረጃ ላይ አንዳንድ የረፈደባቸው የአካል ማጎልበቻ ስፖርት የሚሰሩ ሰዎችን ከመመልከቴ በስተቀር በቦታው ምንም ዓይነት ሰልፈኛ ማግኘት አልቻልኩም። አካባቢው ተለምዷዊ እንቅስቃሴ እየተከናወነበት ነበር። ከአደባባዩ ፊት ለፊት የልማታዊ ስርዓቱ ትሩፋቶች የሆኑት ባቡሮች ደቂቃዎችን እያስቆጠሩ ይተላለፋሉ።
ቦታው የአራት መንገዶች መስቀለኛ በመሆኑም፣ ወደ ቦሌ፣ ወደ መገናኛ፣ ወደ ስድስት ኪሎ እና ወደ ሜክሲኮ የሚተመው የከተማው ነዋሪ ዕለታዊ ጉዳዩን ለመከወን ስፍራውን አቋርጦ ከማለፉ ውጪ፣ ስለ ሰልፍና ሰልፈኛ የሚያወጋ ሰው አላጋጠመኝም። በዚያ አካባቢ ያየሁት ህዝብ በፀረ ሰላም ሃይሎች ስለተጠራውና ‘ወጥታችሁ ሁከት ፍጠሩ’ ስለተባለው ጉዳይ የሰማ አይመስልም። ወይም ውትወታውን ሰምቶ እንዳልሰማ አልፎታል። ሁሉም በየፊናው ይተማል። እርግጥም በትናንትናው ዕለት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለህብረተሰቡ በፀረ- ሰላም ኃይሎች የተጠራ ሰልፍ መኖሩን በመግለፅ፣ ህዝቡ እንዲጠነቀቅና ከዕለታዊ ስራው ሳይስተጓጎል የተለየ እንቅስቃሴ ካጋጠመው በተለመደ ትብብሩ ለፖሊስ እንዲያሳውቅ ያስተላለፈውን ጥሪ የመዲናችን ነዋሪ ተቀብሎት፤ የፀረ-ሰላም ኃይሎቹን ውትወታ ከመጤፍ አልቆጠረውም ማለት ነው። አደባባዩ ላይ ምንም አይታይም። ሰልፍና ሰልፈኛ ቦታው ላይ የሉም።
እኔም ፀረ-ሰላም ኃይሎቹ በሌላ ሰው እጅ እሳትን ለመጨበጥ የሞከሩበትና ‘ወጥታችሁ ሁከት ፍጠሩ’ ያሉበት ጥሪ ውሃ እንደበላው ለመገንዘብ ብዙም ማሰብ አላስፈለገኝም። ያም ሆኖ ግን “መስቀል አደባባይ ተገኝተን ለገዥው ፓርቲ ቀይ ካርድ እንስጠው ያሉት የማህበራዊ ሚዲያ አርበኞች የታሉ?” በማለት ራሴን ከመጠየቅ ወደ ኋላ አላልኩም። ምናልባት ለጥያቄዬ ምላሽ አገኝ ይሆን ብዬ ግራና ቀኝ አማተርኩ። ከአላፊ መንገደኛ በስተቀር እጅብ ብሎ የተሰበሰበ ሰው እንኳን አላየሁም። አዎ! እነዚያ በብዙሃን ሰላም የጥቂቶችን የሁከት አመፅ “እንጀራ” ለመጋገር የፈለጉት ፀረ-ሰላም ኃይሎችን ተከትሎ የወጣ ህዝብ ካለ በማለት በመስቀል አደባባይ ላይ ቆሜ ባማትርም ሰላም ወዳዶቹ አዲስ አበቤዎች በአራዳ ቋንቋ እንደሚሉት “ወፍ የለም!”።መቼም ነፍሱን ይማረውና እንደ ክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ሁሉም ነገር በግልፅ በሚታይበት በመስቀል አደባባይ ውስጥፈልጌ አስፈልጌ ያን ሰሞን ያጣኋት…” እያልኩ ላዜም አልችልም። ድምፁም የለኝም፤ ባዶ ሜዳ ላይ በጠራራ ፀሐይ የሌለ ሰውን እንደ ፈላስፋው ዲዩጋን በፋኖስ መፈለጌም ግርምት ላይ ይጥለኛል። እናም አልሞከርኩትም። እርግጥም እነዚያ ሰዎች የሚገኙት እንደ ፌስ ቡክ ባሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እንጂ እዚህ ሀገር ውሰጥ ባለመሆኑ እንዲሁም እነርሱን የሚሰማቸው አመዛዛኝ ህዝብም ሊኖር ባለመቻሉ ለከሸፈ ነገር ማዜምም ይሁን የሌለን ሰው ፍለጋ መኳተን እንደማይጠበቅብኝ ለመገንዘብ ብዙም ጊዜ አልወሰደብኝም።
ታዲያ እዛው መስቀል አደባባይ ባሉት የስፖርት ማዘውተሪያ ደረጃዎች ላይ ቁጭ ብዬ ፌስ ቡክን የመሳሰሉ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ለአፍታ አሰብኳቸው። በእዝነ ልቦናም የኋሊት የዛሬ 11 ዓመት ገደማ ተጓዝኩ፤ 1997 ዓ.ም። ነገሩ እንዲህ ነበር።…የዛሬዎቹ የማህበራዊ ሚዲያ ተዋናዮች፤ ያኔ ህገ-መንግሥቱንና ህገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን በአመፅ ለመጣል የጎዳና ላይ ነውጥ ማቀጣጠላቸውን አንዘነጋም። በነውጥ ስልጣን ካልያዝን ምንም ዓይነት የምርጫ ውጤትን አንቀበልም ማለታቸውንም እንዲሁ።
በወቅቱ የምዕራቡን ዓለም አክራሪ ኒዮ- ሊበራሎችንበእናንተው መጀን ይሁን፣ ለዙፋን አብቁንበማለትምአንጋሽፍለጋ ተሯሩጠዋል።አንጋሾቹምያለ ሃፍረት በአንዲት ሀገርውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት፤ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የሪፖርት ጋጋታ በማውጣት የተላኪዎቻቸውን እንባ ለማበስ ሞከሩ። ይሁንና ህዝቡ ግን በሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነቴ ውስጥ ምን ዶላችሁ?” በማለት እጢያቸውን ዱብ አደረገው። “አንጋሽ ፈላጊዎቹንም ታዘባቸው፤ ስለሚያወሩት ነገርም ጆሮውን ነፈጋቸው። ያም ሆኖ እነዚያ ፀረ-ሰላም ሃይሎች ግን ተስፋ አልቆረጡም— ውጭ ሀገር በገሃዱ ዓለም ላይ ሆነው ሀገር ቤት ውስጥ መከናወን ስላለበት ነገር ምናባዊ እምቢልታቸውን ቀጠሉበት።…
…ይህ የምናብ ዓለም እምቢልታቸው ብዙም አልቆየም። ስድስት ዓመት ቆይቶ ብቅ አለ—ግንቦት 20 ቀን 2003 ዓ.ም።…በዕለቱ ልክ እንደ ዛሬው መስቀል አደባባይ ተገኝቼ ነበር። ያኔም እነ አሸባሪው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ፅንፈኛ ቡድኖች አንዳንድ የቀድሞው ስርዓት ናፋቂዎች፤ የሀገራችን ደመኛ ጠላት የሆነውና በዕድገታችን እርር-ድብን በማለት የሚቀናው የኤርትራ መንግሥት ተላላኪ ሆነው “በመስቀል አደባባይ ግንቦት 20ን በመቃወም በፌስ ቡክ ላይ ተቃውሞ አውጀናል፤ ሶስት ሺህ የሚጠጉ ዜጎችም ሰልፉን ለመቀላቀል ድረ ገፅ ላይ ፈርመውልናል” ብለው ሽር ጉድ ሲሉ መክረማቸውን አስታውሳለሁ። ጥሪው የተካሄደው ውጭ ሀገር ተሁኖ ሲሆን፤ በዕለቱ የግንቦት 20 ክብረ-በዓል ላይ ለመታደም የተገኘው የአዲስ አበባ ነዋሪ ግን ልክ እንደ ዛሬው ስለ ጥሪው የሰማ አይመስልም። እኔም እንኳንስ ሶስት ሺህ ቀርቶ ሶስት የሚሆን ሰውም ዕለቱን ለመቃወም ሲወጣ አላየሁም። እናም የተባለውን ምናባዊ ቁጥር እምጥ ይግባ ስምጥ በወቅቱ ላገኘው ባለመቻሌ ለራሴ ግርምትን አጭሮብኝ ነበር። በስተመጨረሻም በዕለቱ ግንቦት 20ን ለማክበር የወጣው የመዲናችን ነዋሪ ለሰላም፣ ለልማትና ለዴሞክራሲ ያበቃውን ዕለት አክብሮና ለህዳሴው ግድብ የሚሰጠውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ቃል ገብቶ ወደ መጣበት በሆታና በጭፈራ መመለሱን አስታውሳለሁ።…
…ዛሬስ?...እርግጥ ዛሬም እንደ ትናንትናዎቹ የጥሪው ባለቤት የሆኑትና የሀገራችንን ለውጥ እንዲሁም ዕድገት የማይደግፉ የውጭና የውስጥ ፀረ ሰላም ኃይሎች ቅንጅታዊ የሁከት ጥሪ ሰሚና አዳማጭ አላገኘም፤ በአዲስ አበቤዎች። እናም በሁኔታው በመደመም የአዲስ አበባ ህዝብ ለሰላም ያለውን ቀናዒ ፍላጎት ዛሬም አረጋገጥኩ።…ግና አንድ ጥያቄ ውስጤን ሰቅዞ ያዘው—‘የመዲናችን ነዋሪ ለፀረ-ሰላም ኃይሎች የሁከት ጥሪ የሰጠው ብስለት የተሞላበት ምላሽ ምክንያቱ ምንድነው?’ የሚል። እንደ ‘ኢሳት’ ዓይነት የሽብር ቡድን ልሳኖች፣ እንደ “ቪኦኤ” የአማርኛው ክፍል ዓይነት የኢህአፓ፣ የደርግና የቅንጅት ቅሪቶች፣ በፅንፈኛ ድረ ገፆችና በፌስ ቡክ ገፆች ላይ በመደጋገም የቀረበው የ‘ሁከት ፍጠሩ’ ጥሪ መምከኑስ ምንን ያሳያል? ስልም ራሴን መጠየቄ አልቀረም።…
…እናም ብዙም ሳልቆይ ለጥያቄዎቼ ምላሽ የሚሆኑ ሶስት ምክንያቶችን አገኘሁ። በእኔ እምነት አንደኛው፣ ነዋሪው ከሰላም እንጂ ከሁከት የሚገኝ ትርፍ የሌለ መሆኑን ማወቁ፤ ሁለተኛው፣ የከተማዋ ነዋሪ የሚፈጠሩ ችግሮችን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ተወያይቶ መፍታት እንደሚቻል መገንዘቡ ሲሆን፤ ሶስተኛው ደግሞ አሁን ያለው መንግስት ችግሮችን በማንኛውም ጊዜ የመፍታት አቅምና ብቃት ያለው መሆኑን ካለፈባቸው ተግባራዊ ሂደቶች ማወቅ መቻሉ ነው። ሶስቱም ምክንያቶቼ በአንድም ይሁን በሌላ መልክ የከተማውን ህዝብ አተያይ ሊወክሉ የሚችሉ ይመስለኛል።
እስቲ ውድ አንባቢያን ሃሳቤን ይረዱልኝ ዘንድ ሶስቱንም ምክንያቶቼን አፍታትቼ ልዘርዝራቸው። የአዲስ አበባ ነዋሪ እንደ ማንኛውም ህዝብ የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን ነገር ለይቶ ያውቃል። ከሰላም እንጂ ከነውጥና ከሁከት ምንም እንደማይገኝ በሰከነ ሁኔታ ይገነዘባል። ማንም በቀደደለት የፀረ-ሰላምነት ቦይ ዝም ብሎ የሚፈስ አለመሆኑን “ለፌስ ቡክ አብዩተኞቹ” በሚገባ ነግሯቸዋል። ትናንት ‘ምናልባትም ኢትዮጵያ ውስጥ አመፅ ካስነሳን፣ በግርግር የስልጣን ኮርቻን ልንፈናጠጥ እንችላለን’ በሚል በየማህበራዊ ሚዲያው ሲጋልቡት የነበረው የተሳሳተ የቀቢፀ ተስፋ- ምኞትን በውል ተገንዝቦ ከምኞት እንዳይዘል ያደረገው ሰላም ወዳዱ የመዲናችን ነዋሪ፣ ትናንት “እባካችሁ እኛ የህዳሴያችን ሩጫ ላይ ስለሆንን፣ ይህን ‘ማሪንጌ ቻቻችሁን’ እዛው በምዕራቡ ዓለም የምሽት ክበቦች ውስጥ ደልቁት” በማለት የማያሻማ ምላሽ የሰጣቸው አዲስ አበቤ፤ ዛሬም በሰከነ ሁኔታ ነገሮችን አገናዝቦ የፌስ ቡክ አርበኞችን “ፌዘኞች” ብሏቸዋል። ለእኔ የተሰማኝ የከተማችን ነዋሪ ምላሽ ይኸው ነው።
የአዲስ አበባ ህዝብ የመጣበትን መንገድ ወደ ኋላ ዞር ብሎ ይመለከታል እንጂ፣ እንደ “ፌዘኞቹ” በስሜት የሚነዳ አይደለም። ሁሉንም ነገር በትዕግስት የሚያጤን ህዝብ ነው። ባለፉት 25 ዓመታት በፌዴራል ስርዓቱ የተመዘገቡትን ድሎች ይገነዘባል። ልማትና ዴሞክራሲ በሂደት እንጂ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ዕውን እንደማይሆኑ የሚያውቅ ሩቅ አሳቢ ህዝብ ነው። ከትላንት ዛሬ፣ ከዛሬ ደግሞ ነገ፣ ከነገ ደግሞ ከነገ ወዲያ እንደሚሻል ይገነዘባል። ከስሜት ይልቅ ለትዕግስት ቦታ ይሰጣል። ትዕግስት ጊዜውን ጠብቆ የሚያፈራ ማር መሆኑንም ያውቃል። የኦሮሞ አባቶች “obsaatu damma gnaataa” /ኦብሳቱ ደመ ኛታ/ (“የታገሰ ማር ይበላል” የማለት ያህል ነው) እንደሚሉት ከትዕግስት የሚገኘውን ጣፋጭ ፍሬ የሚያውቅ ህዝብ ነው። እርግጥም ለዚህ አስተዋይና ሚዛናዊ ህዝብ ከአንዴም ሁለቴ…ከሁለቴም ሶስቴና አራቴ ብሎም አምስቴ…ቆሜ ባጨበጭብለት ቢያንስበት እንጂ የሚበዛበት አይመስለኝም።
አዎ! በውጭና በውስጥ ፀረ- ሰላም ኃይሎች የተቀናጀ ሴራ የተጠራው ሁከት የህዝቡን ብሶቶች ለማራገብም ሞክሯል። የአዲስ አበባ ህዝብ ግን ያለፉትን 25 ዓመታት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ እመርታዎችን ስለሚያውቅና ነገሮችን የሚያገናዝብ ብሎም ፍትሃዊ በመሆኑ፤ የፌስ ቡክ ፌዘኞችንና ጥቂት የውሰጥ አጫፋሪዎቻቸውን “የቁራ መልዕክተኛነት” ሊቀበል አልፈቀደም። የመዲናችን ህዝብ በሀገሪቱ ውስጥ የተፈጠሩትና ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዘው የሚነሱት ተግዳሮቶችና ሌሎች መሰል ጉዳዩች መንግሥት እያስመዘገበ ባለው ዕድገት ላይ ያጋጠሙ ጊዜያዊ ችግሮች መሆናቸውን ይገነዘባል።
ይህ ህዝብ ባለፉት ጊዜያት መንግሥት “አደርገዋለሁ” ብሎ የገነባውን ቃል እንዳላጠፈው ሁሉ፤ ዛሬም የሚነሱ ችግሮችን እርሱ ብቻ እንደሚፈታለት እርግጠኛ ነው። የመዲናዋ ህዝብ በመንግሥት ትክክለኛ የልማት አቅጣጫዎችና ፖሊሲዎች ተመርቶ ተጠቃሚነቱን በየደረጃው ከጊዜ ወደ ጊዜ ማረጋገጥ ላይ የሚገኝ በመሆኑም “የነገ ሰው” እንደሚሆን ተስፋን የሰነቀ ነው። በእንዲህ ዓይነት የተስፋ ባቡር ላይ የተሳፈረ ህዝብ ደግሞ ተጠቃሚነቱን ለመሸርሸር የሚሹ ፀረ-ሰላም ሃይሎችን “ወግዱ!” ቢላቸው ተገቢና ትክክል ይመስለኛል።
ምን ይህ ብቻ! ይህ ለሰላም ቀናዒ የሆነና አመዛዛኝ ህዝብ ለፀረ-ሰላም ሃይሎችና ለፅንፈኞች ሲል ያለፈው አረመኔያዊና ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ጫንቃው ላይ እንደ አዲስ እንዲጫንበት አይፈልግም። ከሁለት አስርታት በላይ የተጎናፀፈው የሰላም እፎይታ ፀዳልን ፀረ ሰላም ሃይሎች እንዲያደፈርሱበትና ህይወቱ ምስቅልቅል እንዲሆንበት አይሻም። የአዲስ አበባ ህዝብ ከሌሎች የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመሆን በልዩነት ውስጥ ባለ አንድነት ተከባብሮ የመሰረተው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትም፤ ለሀገራችን በጎ በማይመኙ የውጭና የውስጥ ፀረ-ሰላም ሃይሎች እንዲሁም ባለፈው ስርዓት ባለሟሎችና አጫፋሪዎቻቸው ሳቢያ የኋሊት እንዲቀለበስበት አይፈልግም።
በትምክህተኞችና በጠባቦች ምክንያትም እያራመደ ያለው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነቱ እንዲሸረሸር ቦታ አይሰጥም። እርግጥም እነዚህን የስርዓቱን ትሩፋቶች እያጣጣመ ያለው የመዲናችን ነዋሪ፤ ሰላሙን በማወክ ኑሮውን ለማሽቆልቆል ያሴሩበትን፣ በእርሱ ደምና በህይወት ክፋይ ስልጣንን በአቋራጭ ለማግኘት የሚሹ የባህር ማዶ የድረ ገፅ ህልመኞችን የሁከት ጥሪ ሊሰማ የሚችልበት ጆሮ የለውም። በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ይመስለኛል—የመዲናችን ነዋሪ ፀረ-ሰላም ሃይሎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ያቀረበውንና ‘ውጡና ሁከት ፍጠሩ፣ ለስርዓቱም ቀይ አሳዩት’ የሚል ጥሪን “ጆሮ ዳባ ልበስ” ብሎ ቀይ ካርዱን ለራሳቸው መልሶ የሰጣቸው። እናም የእሁዱ የሁከት ጥሪ መክሸፉ የግድ ነበር።…
ያም ሆነ ይህ ግን እኔ እንደ ማንኛውም ዜጋ ሰላም ወዳድና አስተዋይ ለሆነው፣ የፀረ- ሰላም ኃይሎችን የሁከት ጥሪ መና ላስቀረው እንዲሁም ‘በሰላሜ አትምጡብኝ’ በማለት በቅጥፈት ወሬ ላልተታለለው ለአዲስ አበባ ህዝብ ያለኝን የላቀ አክብሮት ለመግለፅ፤ እነሆ ከተቀመጥኩበት መስቀል አደባባይ ብድግ ብዬ በአክብሮት ባርኔጣዬን አነሳሁ!...ሰዓቴንም ተመለከትኩ—ከረፋዱ አምስት ሰዓት ከአስር ደቂቃ ይላል።…ፊቴን ወደ መጣሁበት የታክሲ መስመር አዞርኩ።…












የኤርትራ መንግሥትና ሽብርተኝነት…!




አባ መላኩ
አንዳንድ የአገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጸረ ዲሞክራሲያዊና ሕገወጥ አካሄድ አላማቸውን ለማስፈጸም ሲሉ ከለየላቸው ጸረ ሰላም  ሃይሎች ጋር ቁርኝት ፈጥረው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። በአገራችን የፖለቲካ ስልጣን መያዝ የሚቻለው በምርጫ ብቻ መሆኑ በተረጋገጠበት ሁኔታ ውስጥ  በምርጫ ተወዳድረው ማሸነፍ ባለመቻላቸው በአቋራጭ ወደ ሥልጣን ሊያሸጋግረን ይችላል ብለው የሚያስቡትን ማንኛውንም ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ በመደገፍና እንዲያም ሲል ራሳቸውም ዋነኛ ተዋንያን ሆነው ሲንቀሳቀሱ የሚታዩበትን ሁኔታ እየታዘብን ነው።
በዚህ ቅኝት መንቀሳቀሳቸውም በአገሪቱ ውጤት እያስመዘገበና ሕብረተሰቡን በየደረጃው ተጠቃሚ እያደረገ ያለውን ዘላቂ ልማት የማደናቀፍ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን ሳይገነዘቡት ቀርተው ነው ለማከለት አይቻልም።  ለዚህ አንዱ ማሳያ ደግሞ በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ ያላቸው የተዛባ አመለካከት ነው።
አገሪቱ ያላትን የውሃ ሃብት በተገቢው መንገድ ለመጠቀም የቻለችበት ሁኔታ አልነበረም። የተፈጥሮ ጸጋዋን ወደ ጥቅም መለወጥ ያልቻለችው ኢትዮጵያ ህዝቦቿ በርሃብ ሲናጡ፣ ለስደትና ለስቃይ ሲዳረጉ፣ የአባይ ወንዝን መጠቀም ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ በማሳብ በቁጭት ሲቃጠሉ ኖረዋል።  የኢትዮጵያ ህዝብ ያለምንም ልዩነት "እንደጀመርነው ዳር እናደርሰዋለን" በሚል ከጅምሩ አንስቶ በንቃት እየተከታተለው ያለውን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ እያነሱ ካሉት ሃሳብ አንዱ ግድቡ የማን እንደሆነ አናውቅም የሚል ነው። 
 በኢትዮጵያ ህዝብ ገንዘብና  በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብት እየተሰራ ያለን ትልቅ ልማት "የማን እንደሆነ አናውቅም፣" ማለት ከፌዝነቱ ፣እጅግ በዘቀጠ ሁኔታ በሕዝብና በሃገር ከመሳለቅም ባለፈ ሃላፊነት የጎደለው የሚያሳፍር ክህደት  ነው።


ትውልድ ትውልድን እየተካ ህዝብና አገር ሁሌም ይኖራሉ። በአንድ አገር የሚሰሩ የልማት አውታሮችም የህዝቡ ሆነው ይቀጥላሉ። ከዚህ በመነሰት የሰማያዊ ፓርቲና የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ባለቤት ማን እንደሆነ አናውቅም ማለታቸው የማን እንደሆነ ጠፍቶአቸው ሳይሆን በሕብረተሰቡ መካከል ውዥንብር በመፍጠር የአገሪቱን ልማት ለማደናቀፍ አንዲያም ሲል እየተመዘገበ የመጣውን ዕድገት በጭፍን ጥላቻ በማጣጣል-ለማጥቆር  እንደሆነ አያጠያይቅም።
እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ጥብቅ ቁርኝት በመፍጠርና የገንዘብ ድጋፍ በማሰባሰብ በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ የፖለቲካ አጀንዳን ለማራመድ በሚል ሽፋን ተደራጅተው ሕገመንግስቱን ሲተላለፉና በአገሪቱ አመጽና ብጥብጥ ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ አልፈው ተርፈውም የሃይማኖት አክራሪነት ለማስፋፋት፣ ሽብርተኝነትንና ሁከትን ለማንገስ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያን ልማት ከማይፈልጉ ጸረ ሰላም ኃይሎችና ኤርትራን ከመሳሰሉ መንግስታት ጋር ሆነውም በመስራት ላይ ይገኛሉ።
የኤርትራ መንግስት ባድመን በመውረር ኢትዮጵያ ተገዳ ወደ ጦርነት እንድትገባ ቢያደርግም በመጨረሻ ላይ ግን ወረራውን ቀልብሳ በፍጹም አሸናፊነት የወጣችበት  ሁኔታ ይታወሳል። ይሁንና የኤርትራ መንግስት የሃፍረት ሸማ በመከናነቡ ከስህተቱ ከመማር ይልቅ አሁንም በሌላ መልክ ኢትዮጵያን ለማተራመስ መንቀሳቀሱን ቀጥሏል። 
ኢትዮጵያ በሶማሊያ ስር ሰዶ የነበረውን የሽብር ቡድን በመታችበት ወቅትም የቡድኑ አመራሮችና ከጦርነቱ የተረፉ አባላት ወደ ኤርትራ ሄደው በመጠለል በየጊዜው ከኤርትራ መንግስት በሚያገኙት የስልጠናና የገንዘብ ድጋፍ የአፍሪካ ቀንድ ሰላምን ለማወክ የተለያዩ ጥረቶችን አድርገዋል።
ከአሸባሪዎች ጋር በሚያደርገው ትብብር የተነሳ ዓለም አቀፍ ሕብረተሰብ ያወገዘውና አልፎም ማዕቀብ የጣለበት የኤርትራ መንግስት ጄኔራሎችና መኮንኖችም  ሶማሊያ በመግባት ከአልሸባብ ጋር ተባብረው ኢትዮጵያን ተዋግተዋል። 
ለሰዎች ህይወት የማይሳሱት የሽብር ቡድኖች በአንዳንድ አካባቢዎች ጅምላፍጨፋ አካሂደዋል። በህዝብ መጓጓዣዎች ላይ ጥቃትን ፈጽመዋል። ከዚህም አልፈው በገበያ ቦታዎችና በህዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች ላይ  ተደጋጋሚ ጥቃቶችን አቀነባብረዋል።
የኤርትራ መንግስትና የሽብር ቡድኖች በተለያየ ጊዜ ለመፈጸም ያቀዷቸው የተያዩ የሽብር እቅዶች በሕብረተቡ ጥረት ክሸፋዋል። የዚህ እንቅስቃሴ መክሸፍን በተገነዘቡ ወቅትም ተስፋ ቆርጠው አርፈው አልተቀመጡም። ሌላ ስልት መቀየስን መረጡ እንጂ።
ቡድኖቹ ሌላ የተጠና የሽብር ተግባር መፈጸሚያ መሳሪያ ይሆናል ያሉትን ይዘው በሌላ መልክ ብቅ ማለትን ነበር የመረጡት። በዋናነት አገር ውስጥ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ሙሉበሙሉ የሽብር ፈጻሚ አካላት ማድረግን ማዕከል ያደረገ እንቅስቃሴ አደረጉ።
ይህ እንቅቃሲያቸው በተወሰነ ደረጃ ውጤት ያስገኘላቸው ተግባር ነበር። በአገሪቱ ያለውን ፖለቲካዊ፣  ማህበራዊና ኢኮኖያዊ እንቅስቃሴ በማጣጣልና ጥላሸትን በመቀባት የጀመረው የእነዚህ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ውሎ እያደረ ሲመጣ ደግሞ በቀጥታ በሽብር ተግባራት የሚሳተፉበት ሁኔታ በማመቻቸት ቀጥተኛ የሆነ የሽብር ተግባርን መፈጸሙን ተያይዘውታል።
መንግስት በአገሪቱ ሊደርሱ ከሚችሉ የሽብር ተግባራት ለመከለከልና በደረሱበት ወቅትም በሕግ ለማስተናገድ ባለው ቁርጠኝነት መሰረት በሕግ አውጪው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸረ ሽብር ሕግ ወጥቶ እንዲፀድቅ አድርጓል። 
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እውን ከሆነ ሁለት ዓስርት ዓመታት ተቆሯዋል፡፡ የአገሪቱ ሕገመንግስት መጽደቅን ተከትሎ የብሄር ቤረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት ተረጋግጧል፤ የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት እውን ሆኗል፤ የፕሬስ ነጻነት ተከብሯል፤ የሃይማኖት ነጻነት ተረጋግጧል። ይህ ደግሞ ባለፉት 20 ዓመታት ሲተገበር ቆይቷል፡፡
ከደርግ ውድቀት ማግስት  የተረጋገጠው የሃይማኖት ነጻነትን  በመጠቀም  አንዳንድ የደርግ ስርዓት ትርፍራፊዎች   ህቡእ አጀንዳቸውን በሃይማኖት ሽፋን ለማራመድ በሁሉም የሃይማኖት አማኞች መካከል መሰግሰግን  ነበር የመረጡት። 

የኢህአዴግ መንግስት የክርስትና እምነት ሊያጠፋ ለሌሎች ሃይማኖቶች ነጻነትን ሰጥቷል የሚል ማደናገሪያ ይዘው በክርስትና ሃይማኖት ሽፋን የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማናጋት   ቀላል የማይባል ጥረት አድረገዋል።  
በእምነት በዓላት  ህዝበ ክርስቲያኑ ለጸሎትና ሃይማኖታዊ ተልእኮ  በሚሰበሰብበት ወቅት ብጥብጥና ሁከትን  በማንሳት ሰላምን ለማደፍረስ ሙከራ ቢያደርጉም   ምእመናን የፖለቲከኞቹ ድብቅ ሴራ እየተገነዘቡ  በመምጣታቸው  ዓላማቸው ሊከሽፍ ችሏል፡፡   ይሁን እንጂ    ተስፋ ሳይቆርጡ ስልታቸውን እየቀያየሩ  ጥረታቸውን ቀጥለዋል።
በአገሪቱ ባለፉት ሃያ አምስት  ዓመታት በተለያየ ስልትና በተለያየ ሃይማኖት ሽፋን የተደረጉ ጥረቶች ተጽእኖ አላሳደሩም ማለት ባይቻልም ሃይማኖታዊ ተልእኮ እንዳልነበራቸው  እርቃናቸው እየወጡ በመምጣታቸው በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት አልቻሉም።
 የኢትዮጵያ ህዝብ ቀንደኛ ጠላቱን በመለየቱ ድህነትን ለማጥፋት  ቀና ደፋ እያለ ይገኛል።  አስተማማኝ የኢኮኖሚ መሰረት ያላት አዲስቷን ኢትዮጵያ ለመገንባትም  ቆርጦ ተነስቷል፡፡
ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የተመዘገቡትን የልማት ውጤቶችና የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን ለማስፋትና ሙሉእ ለውጥን ለማረጋገጥ መንግስት በአምስት ዓመታት ለመተግበር የነደፈውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ ህዝቡ ሰፊ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛል።