Friday, 30 September 2016

Koottaa hairreefannuu (ኑ እናመስግን)


ኢብሳ ነመራ
ኦሮሞዎች ምሉዕ በኩለሄ አምላክ (Waaqa) ያለፈውን ዓመት በሰላም ስላሳለፋቸው የሚያመሰግኑበትን፤ መጪውን እንዲባርክላቸው የሚማለዱበትን የዘንድሮውን የኢሬቻ (Irreecha) በዐል እንደተለመደው በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሰዲ (አርሰዲ ኃይቅ) ላይ ያከብራሉ። የፊታችን እሁድ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ/ም።
ኢሬቻ መንፈሳዊ ሥርዓት ነው። ኢሬቻ ፈጣሪን ማምለክ ማለት ነው። ኦሮሞዎች ይህን የምሉዕ በኩለሄ ፈጣሪ አምልኮ ሥርዓት በዓመት ሁለቴ ነው የሚከውኑት፤ በጸደይ እና በበልግ መግቢያ ላይ፤ በጸደይ ወር የሚከናወነው ኢሬቻ መልካ ሲባል የበልጉ ደግሞ ኢሬቻ ጋረ ይባላል። ኢሬቻ መልካ በዋናነት የምስጋና ሲሆን የሚከናወነውም በውሃ ዳር ነው። ኢሬቻ ጋረ ወይም ኢሬቻ ከዳ (kadhaa) ደግሞ በልግና ክረምቱ እንዲዘንብ፣ ምድር እንድታፈራ፣ ከብቶች እንዲረቡ፣ እንዲሰቡ፣ . . .ምልጃ የሚከናወንበት ነው።
ይህ የኢሬቻ ሥርዓት የኦሮሞዎች በአንድ ምሉዕ በኩለሄ ፈጣሪ አምላክ (Waaqa) የሚያመልኩበት የዋቄፈና (Waaqeefnnaa) ሃይማኖት ጥንታዊ ሥርዓት ነው። የዋቄፈና ሃይማኖት ከኦሮሞ የመጀመሪያ ልጅ አባ ሙዳ ነቢይነት የሚጀምር መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ። ዋቄፈና በየጨፌው ባሉ አባሙዳ ወደነበረበትና ያረፈበት ቦታ ማለትም ወደ መደ ወላቡ ሃይማኖታዊ ጉዞ ወይም ጂለ (jiila) አካሂደው በአምላክ መንፈስ በሚሞሉ ቃሉ (qaalluu) የተሰኙ የሃይማኖት አባቶች የሚመራ የሃይማኖት ሥርዓት ነው። የሃይማኖቱ ተከታዮች ዋቄፈታ (waaqeefataa) ይባላሉ።
ቃሉ የሚሰኙት የሃይማኖት አባቶች ከመንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ አገልግሎት በተጨማሪ የጨረቃንና የከዋክብትን ኡደት በመከታተል ጊዜን፤ ዓመትን፤ ወቅትንና ወራትን በመቀመር ለገዳ የአስተዳደር ሥርዓት የሎጂስቲክስ ድጋፍ ያደርጋሉ። በገዳ ሥርዓት ውስጥ ያለ እድሜን መሰረት ያደረገ የአኗኗርና የአስተዳደር ሥርዓት በየስምንት ዓመቱ የሚቀያየር ነው። በየስምንት ዓመቱ ኦሮሞዎች ከህፃናት እሰከ አዛውንት የእድሜ እርከን ሽግግር ያደርጋሉ። የአባ ገዳዎች ወይም ቦኩ የስልጣን ሽግግር የሚደረገውም በየስምንት ዓመቱ ነው። ታዲያ አባገዳዎች ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ተግባራትን ሲያከናውኑ ጊዜውን የሚለካውና የዓመቱን መለወጫ ወቅት የሚያሳውቁት ቃሉዎች ናቸው። በገዳ አስተዳደር ሥርዓት ሃይማኖትና መንግሥት ፍፁም የተለያዩ በመሆናቸው ቃሉዎች ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ውስጥ ባይገቡም ወሳኝ የሎጂስቲክስ ድጋፍ ያደርጋሉ። ገዳና ዋቄፈና የዚህ ዓይነት ትስስር ነው ያላቸው፤ በመሆኑም ገዳን ስናነሳ የኦሮሞዎች መንፈሳዊ ህይወት መገለጫና ለአስተዳደሩ የሎጂስቲክስ ድጋፍ የሚያደረግበትን ዋቄፈና ወይም ቃሉዎችን ሳናነሳ ማለፍ አይቻልም።
የኢሬቻ ሥርዓት ለክፍለ ዘመናት ሲካሄድ የቆየ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ቢሆንም፤ በሌሎች ሃይማኖቶች፤ በተለይ በክርስትና እና በእስልምና መስፋፋት ምክንያት እየደበዘዘ የመጣበት ሁኔታ መኖሩ አይካድም። እርግጥ በበርካታ የኦሮሚያ አካባቢዎች፤ በተለይ በቱለማ ኦሮሞዎች አካባቢ ተጽእኖዎችን ተቋቁሞ ሲከናወን ቆይቷል። ከዚህ በተጨማሪ በአጠቃላይ፤ የዋቄፈና ሃይማኖትና በተለይ የኢሬቻ ሥርዓት ከሃይማኖታዊ ትርጉሙ ውጭ የተዛባ ትርጉም እየተሰጠው ኢሬቻ የሚያሸማቅቅ ሆኖ የቆየበት ሁኔታ መኖሩም አይካድም። የእምነቱ ተከታዮች ተገቢ ያልሆነ አምልኮ እንደሚከተሉ ተቆጥረው ይወገዙ ነበር። ኢሬቻ የሚከናወንባቸው ስፍራዎች በተለያየ መንገድ ሥርዓቱን ማከናወን እንዳይቻል የተደረገበት ሁኔታም ነበር።
ያም ሆነ ይህ፤ ኢሬቻ የተሰኘው የዋቄፈታዎች የአምልኮ ሥርዓት ከ1983 ወዲህ ይፋ ወጥቷል። ኢሬቻ በየአካባቢው መልካ የሚከበር ቢሆንም በኦሮሚያ ክልል አቀፍ ደረጃ በቢሾፍቱ አርሰዲ ሃይቅ ላይ እንዲካሄድ ተወስኗል። ላለፉት ሃያ አምስት አመታት ኢሬቻ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኦሮሞዎችና የሌሎች ብሄሮችና ብሄረሰቦች አባላት በሚሳተፉበት ሁኔታ በድምቀት ሲከበር ቆይቷል።
አሁን ኢሬቻ ሲከበር ነባሩን ሃይማኖታዊ ይዘቱን ባይለቅም የሚያከብሩት ግን የዋቄፈታ እምነት ተከታዮች ብቻ አይደሉም። ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በተጓዳኝ የኦሮሞዎች ብሄራዊ ማንነት መለያ እሴት ለመሆን የበቃበት ሁኔታ አለ። እናም ሁሉም ኦሮሞዎችና ሌሎች የኦሮሞዎችን ባህላዊ እሴቶች የሚያደንቁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሚሳተፉበት ሁኔታ የሚከበር ከኢትዮጵያ ደማቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሁነቶች አንዱ ለመሆን በቅቷል።
የዘንድሮው ኢሬቻ የሚከበረው የዓለማችን ቀደምት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገለጫ እንደሆነ የሚነገርለት ገዳ በተባባሩት መንግሥታት የትምህርት፤ የሳይንስና የባህል ድርጅት (The United Nations Educational, Scientific and Cultural Organization  _UNESCO) በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት እውቅና ሊያገኝ ወራት በቀሩት ጊዜ ውስጥ  መሆኑ ልዩ ያደርገዋል። ገዳና ኢሬቻ አያት ቅድም አያቶቻችን አስተዳደራዊና መንፈሳዊ ህይወታቸው ሲመራበት የኖረ፤  ብዙ ጫናዎችን አልፈው ወደዚህ ትውልድ የተሸጋገሩ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የበለጠ እየጎለበቱ የመጡበትን ሁኔታ እናገኛለን። በቦረናና በጉጂ ዞኖች መልኩን ሳይቀይር ተጠብቆ የቆየው፣ በአንዳንድ የቱለማ ኦሮሞዎች ዘንድም መሰረታዊ ይዘቱን ቢስትም በወግነት ተይዞ የቆየው የገዳ ሥርዓት አሁን በመላ ኦሮሚያ አንሰራርቷል። አሁን በሁሉም የኦሮሚያ አካባቢዎች እንዲሁም አንድ ክልል አቀፍ የገዳ ሥርዓት ተዘርግቷል፤ አባገዳዎችም አሉ። ይህ የገዳ ሥርዓት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከመንግሥት ጋር በመደጋገፍ የሚሰራበት ሁኔታም አለ።
ኦሮሞዎች የተቀሩትም ኢትዮጵያውያን የዘንድሮውን የኢሬቻ በዐል ሲያከብሩ  ትልቁ የኦሮሞዎች ዋነኛ መገለጫ የሆነው ገዳ በጥንታዊ የስልጣኔ እሴትነት  የአገራት ድንበር፤ ዘር፤ ቀለም፤ ሃይማኖት ሳይለይ በሰው ልጅ ቅርስነት የሁሉም ሃብት ሊሆን በተቃረበበት ወቅት መሆኑን አስታውሰው፣ የኢሬቻ በዐል ይህን ሊያግዝ በሚችልበት ሁኔታ ባህላዊ ሥርዓቱን ጠብቆ በፍጹም ጨዋነት ለማክበር መዘጋጀት አለባቸው። የገዳ ሥርዓት በሰው ልጅ የማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገብ ለኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆን ይህ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓቶች ሁሉ አንጋፋ የሆነው ሥርዓት እዚች ምድር ላይ የተፈጠረና ተግባራዊ የሆነ በመሆኑ ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የሚያኮራ ነው። እናም ከኦሮሞዎች የላቁ እሴቶች አንዱ የሆነው ኢሬቻ በድምቀት መከበር የኦሮሞዎችን ታሪክ ገናና በማድረግ ገዳንም እንደሚያጎላው እናስታውስ!
እንግዲህ በዋቄፈና እና ኢሬቻ ዙሪያ ያለውን እውነታ በአንድ አጭር ጽሁፍ ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም። በሌላ አጋጣሚ የማውቀውንና ከአዋቂዎች ያገኘሁትን ሰፋ አድርጌ እንደምመለከተው ተስፋ በማድረግ አሁን የዘንድሮው ኢሬቻ የሚከበርበትን ድባብ  አስመልክቶ ጥቂት መረጃዎችን ልስጥ፤
በዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ላይ እስከ አምስት ሚሊዮን የሚደርሱ ተሳታፊዎችና ጎብኝዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህን በዓል ለማስተናገድ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል። የከተማው አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ፤ በዓሉን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን በበቂ ሁኔታ ለማስተናገድ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል። 
የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን የማደስ እና ማስፋፋት ስራዎች ተሰርተዋል።  ከእነዚህ መካከል በዓሉ የሚከበርበትን ሆራ አርሰዲ ኃይቅ ከዋናው መንገድ ጋር የሚያገናኝ የመንገድ ግንባታ መከናወኑ ተጠቃሽ ነው። በኃይቁ አቅራቢያ ለእንግዶች ማረፊያ የሚሆን ስፍራም ተዘጋጅቷል። በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር ይከበር ዘንድም ከከተማዋ ነዋሪዎች እና ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን በቂ ዝግጅት መደረጉም ታውቋል። በዓሉ በርካታ ታዳሚ የሚገኝበት መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ተላላፊ በሽታዎች እንዳይከሰቱ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅትም ተከናውኗል። 
በዐሉን ምክንያት በማድረግ  የኦሮሞን ባህል የሚገልጽ አውደ ርዕይ በቢሾፍቱ ከተማ የተከፈተ ሲሆን፤  በበአሉ ዋዜማ የኢሬቻ የሩጫ ውድድር ይካሄዳል። እስከ ጥቅምት ወር የሚቆይ የንግድ ትርኢትና ባዛርም ተከፍቶ በመካሄድ ላይ ይገኛል። እናም ኢትዮጵያውያን በሙሉ የገዳ ሥርዓት በሰው ልጅ የማይዳሰስ ቅርስነት እውቅና ሊያገኝ በተቃረበበት ወቅት በሚከበረው የዘንድሮ ኢሬቻ ላይ ተገኝተን የኦሮሞዎችን ታሪክ በማጉላት እውቅናውን እውን እናድርግ! በመላ አገሪቱ ያማረ ሰብል እንዲበቅል የሚያደርገውን፤ ከብቶች እንዲጠግቡ አድርጎ በሰላም ከዘመን ወደዘመን የሚያሻግረንን ዋቀዮ እናመስግን! koottaa Waaqayyoo hairreefannuu! (ኑ እግዚአብሄርን እናመስግን!)

No comments:

Post a Comment