ቶሎሳ ኡርጌሳ
ሰላምና ሁከት ሁለት የማይታረቁ ፅንሰ- ሃሳቦች ናቸው። አንደኛው በሌላኛው
ውስጥ ሊገኝ አይችልም። በሁከት ውስጥ ሰላም እንደማይኖረው ሁሉ፤ በሰላም ውስጥም ሁከት ሊታሰብ አይችልም። ስለ ሰላም ስናስብ ሁከትን
በተቃራኒ ገፅታው እየተመለከትነው ነው። ሁከት በህዝብና በሀገር ውስጥ ሊፈጥረው የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖንም እየኮነንነው ነው።
የድርጊቱ ዕውን መሆን የእኛነታችንን በመሻሻል ላይ የሚገኝ ገፅታን ጥላሸት ከመቀባት ባሻገር፣ የእኛ ሰላም መሆንና መታደስ እንዲሁም
የሀገራችን ዕድገትና ብልፅግና ለሚያንገበግባቸው የውጭም ይሀን የውስጥ ኃይሎች ሰፊ በር ይከፍታል። ይህም የብጥብር በርን በርግዶ
በመክፈት የትርምስ ምህዳርን ይፈጥራል። ትናንት ወደ ነበርንበት የጦርነት፣ የድህነትና የኋላ ቀርነት ታሪክ ይመልሰናል።
የሁከት በር አፉ ሰፊ ነው። በተሳሳተ አቅጣጫ የሚጓዝን ዜጋ ሁሉ ያስገባል።
ሚዛናዊነትን አይፈጥርም። ስሜታዊነትን ያነግሳል። በዚህ በር ውስጥ ለማስገባት የሚፈልጉ ኃይሎችም የበሩን ግራና ቀኝ እጀታ ይዘው
በስሜትና በአሉባልታሌገንን ሊያስጋልቡት ይከጅላሉ። የጥፋት አውድንም ይፈጥራሉ። ጥፋቱ ግን የህዝቡን ክቡርና የማይተካ ህይወት ከመንጠቅ
ባሻገር ሃብቶቹንና መጠቀሚያዎቹን ሁሉ ያወድማል። ወደ ኋላ መለስ ብለው ሲያጤኑት ግን ቁጭትን ይፈጥራል።
የሁከት ኃይሎቹ ያላቸውን የቅጥፈትና የአሉባልታ አቅማቸውን ሁሉ አሟጠው በመጠቀም
ህዝቡ ላለፉት ዓመታት ከሰላም ያገኛቸውን ትሩፋቶች ይነጥቁታል። እነርሱ በዚህም ይሁን በዚያ የራሳቸውን ፖለቲካዊ ጥቅም እስካሳካላቸው
ድረስ እዚህ ሀገር ውስጥ የፈለገው ቢሞትና ንብረቱ ቢወድም ጉዳያቸው አይደለም። ባህር ማዶ ሆነው የሚለኩሱት እሳት ወላፈኑ በእነርሱና
በልጆቻቸው ላይ እንደማይደርስ ስለሚያውቁ፤ እሳቱ ሀገር ውስጥ ማንንም ቢያቃጥል ከምንም አይቆጥሩትም። በተገላቢጦሹ በሚፈጠረው የሞትና
የንብረት ውድመት “እልል በቅምጤ” እያሉ በየድረ ገፁ ይጨፍራሉ—“ በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት” እንዲሉ አበው። ብቻ በዚህም
ይሁን በዚያ ህዝቡን አደናግረው የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካት ጥልቅ ጉድጓድ ይቆፍራሉ።
የእነዚህ ሃይሎች ዓላማ ሁለት ይመስለኛል። አንደኛው፤ ሃይሎቹ ከዚህ ቀደም
ሀገር ውስጥ በነበሩበት ወቅት በከሰረ ፖለቲከኝነታቸውና በፀረ-ህገ መንግስታዊነታቸው በህዝብ የተተፉ በመሆናቸው ሳቢያ በህዝቡ እምቢተኝነት
ያጡትን ስልጣን በሁከትና በብጥብጥ ለመያዝ ፍላጎት ያላቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ፤ የሀገራችንን ሁለንተናዊ ዕድገትና የልማት ጎዳና
ማየት የማይሹ አንዳንድ የውጭ ሃይሎች እያዘዟቸውና ገንዘብ በገፍ እያሸከሟቸው ሰላማችንን እንዲያደፈርሱ ታዘው በተለያዩ ማህበራዊ
ድረ ገፆች ሁከትን መቀመር ነው።
እነዚህ ጥቂት ሃይሎች ይህን ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ እዚህ ሀገር ውስጥ
በስውር ያደራጇቸው የጥፋት ቀማሪዎች የሉም ማለት አይቻልም። ይሁንና በመንግስት በኩልም መልካም አስተዳደርንና ሌሎች የህዝቡን እርካታ
የማያረጋግጡ ምክንያቶች በወቅቱ ተገቢ ምላሽ አለመሰጠቱ የሁከት ኃይሎቹን ፍላጎት በማገዝ ረገድ የበኩሉን ሚና መጫወቱ አይካድም።
በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች አንዳንድ ቦታዎች ላይ የተከሰተው ሁከት የመፍጠር ሁኔታ በአካባቢዎቹ የሚኖረው ህዝብ በመንግስት
አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እርካታው ምን ያህል የተጓደለ መሆኑን ያሳየ ክስተት ይመስለኛል። ነገሩ “ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው”
እንዲሉ በመሆኑ፤ ህዝቡ በሁከት ፈጣሪዎቹ የቅጥፈት አጀንዳ ምክንያታዊ ሳይሆን እንዲያዳምጣቸው ምክንያት ሆኗል። ይህም በመንግስት
በኩል የውስጥ ተጋላጭነትን በመቀነስና የህዝቡን እርካታ በማረጋገጥ ረገድ መከናወን የሚገባቸው ብዙ የቤት ስራዎች እንዳሉ የሚያሳይ
ነው።
እርግጥ መንግስትና ገዥው ፓርቲ በያዝነው የበጀት ዓመት ከመልካም አስተዳደርና
የመንግስት ስልጣንን የግል ኑሮ መደጎሚያ ከማድረግ አኳያ የሚታዩ ጉድለቶችን እንዲሁም ህዝቡን ለምሬት የሚዳርጉ አሰራሮችንና ተግባሮችን
በቁርጠኝነት እንደሚያስተካክሉ ቃል ገብተዋል።
ለዚህም በቅርቡ የብአዴን፣ የደህዴንና የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ማዕከላዊ
ኮሚቴዎች ያሉትን ችግሮች በጥልቀት ከገመገሙ በኋላ፣ ከየክልሎቻቸው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ያወጧቸው የአቋም መግለጫዎች አስረጅዎች
ይመስሉኛል። ይህን መጣጥፍ እያጠናቀርኩ በነበርኩበት ወቅት ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጉባዔውን አላካሄደም ነበር።
ሆኖም በቅርቡ ድርጅቱ በሚያካሂደው የማዕከላዊ ኮሚቴ ጉባዔው ከክልሉ የመልካም አስተዳደር ተጨባጭ ችግሮች አኳያ የራሱን አቋም የሚይዝ
ይመስለኛል።
እንግዲህ ይህ ሀገራዊ ችግርን የመፍታት ርብርብ ገዥው ፓርቲና አባል ድርጅቶቹ
ህዝቡን ለምሬት የዳረገውን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት የህዝቡን እርካታ ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መሰለፋቸውን የሚያሳይ ይመስለኛል።
እርግጥ ከገዥው ፓርቲ መሰረታዊ ባህሪ አኳያ በአባል ድርጅቶቹ ውስጥ እየታዩ ያሉት መነሳሳቶች ተገቢነት ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ ኢህአዴግ
ለህዝብ ያለውን ወገንተኝነት የሚያሳዩ ጭምርም ናቸው። ይህም ድርጅቱ ሀገር ውስጥ የተፈጠረውን ችግር በሰላም ለመፍታትና የሀገራችን
ህዝቦችም የጀመሩት ዕድገት ያለ አንዳች ሳንካ ሳይስተጓጎል እንዲቀጠል ያለውን ቁርጠኛ አቋም የሚያረጋግጥ ይመስለኛል።
ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ያሉት ችግሮች መንስዔዎችን ለይቷል። ይኸውም በአንድ
በኩል የመንግስትን ስልጣን የህዝብ ጥቅም ማስከበሪያ መሳሪያ የማድረግ ሁኔታ መቀነሱን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ስልጣን የኑሮና የጥቅም
መሰረት የመሆን ዝንባሌ መናሩን ገምግሟል። ይህም በአሁኑ ወቅት በህብረተሰቡ ውስጥ የተፈጠሩትብን ብሶቶች ማባባሱን አረጋግጧል።
የስልጣን ዋነኛው ግብ የህዝብን መብትና ጥቅም ለማስከበር ሆኖ ሳለ፣ የግለሰቦች ኑሮ ማደላደያ በመሆኑ ሳቢያ በጅምር ላይ ያለው የለውጥ ጉዞ ችግሮችን በማባባስ የህዝብ ቅሬታን ከፍ ሊያደርግ
ችሏል። በተለይም በየደረጃው ያለ አመራር የወጣቶችን ጥያቄዎች በተገቢው ሁኔታ ማስተናገድ ባለመቻሉ ለቅሬታዎቹ አሁን ያሉበት ደረጃ
መድረስ ምክንያት ሆኗል። እንግዲህ እነዚህ ሃቆች ድርጅቱ የደረሰባቸው መሰረታዊ ጉዳዩች በመሆናቸው የህዝቡን ቅሬታዎች ለመፍታት
እየተንቀሳቀሰ ነው።
ሰሞኑን በተለያዩ ደረጃዎች እየተከናወኑ ያሉት ህዝባዊ ውይይቶች የዚህ አባባሌ
አስረጅዎች ናቸው። በውይይቶቹ ገዥው ፓርቲና መንግስት በቀጣይ ሊከናወኑ የሚገባቸውን ከፍተኛ ግብዓቶችን እያገኙ ነው። የውይይቱ
ተሳታፊ የሆነው ህዝብም፣ ላለፉት 25 ዓመታት የተገኘውን ሰላምና መረጋጋት ለመጠበቅ እንዲሁም እየተመዘገበ ባለው ልማት ላይ የሚቃጣን
ማናቸውንም አደጋ ለመመከትም ዝግጁ መሆኑን ሲገልፅ እየሰማን ነው። በተለይም በሁከት ኃይሎች አማካኝነት ግጭት በነበረባቸው አንዳንድ
አካባቢዎች የሰው ህይወት መጥፋቱን በፅኑ ኮንኗል።
በእኔ እምነት ይህ የህዝቡ አቋም የሚያሳየው ሁለት ነገሮችን ነው። አንድም
ህዝቡ የተከሰተው ችግር የተገኘውን ሰላም የኋሊት የሚቀለብስ መሆኑን መረዳቱን፣ ሁለትም የሁከት ኃይሎች የግጭት አጀንዳ በሂደት
ቦታ የሚያጣ መሆኑን ነው። አዎ! ከገዥው ፓርቲና ከመንግስት ጋር ውይይት እያደረገ ያለው ህዝብ ችግሮችን መጠለያ በማድረግ እንዲሁም
የተከሰተውን ቅሬታና አለመግባባት እንደመልካም አጋጣሚ ቆጥረው ህገ-መንግስቱንና ስርዓቱን ለማፍረስ የተነሱ የሁከት ኃይሎች መኖታቸውን
በሚገባ ተገንዝቧል።
እነዚህ ኃይሎች አንዱን ብሔር ከሌላው ጋር በመለያየት በጥርጣሬና በጥላቻ
እንዲተያዩና በዚህም ለዘመናት የተጋመደውን የአብሮነት ክር ለመበጠስ በተቀናጀ ሁኔታ ሲሰሩ እንደነበር በውይይቶቹ ሲገልፅ ተስተውሏል።
ይህ የህዝቡ የተከሰተውን ችግር የመረዳት ሁኔታ የሁከት ኃይሎቹን ማንነት ይበልጥ ግልፅ ያደረገ ብቻ ሳይሆን፣ አጀንዳቸውም በሂደት
ቦታ እንደማይኖረው ያረጋገጠ ይመስለኛል። ይህም ኃይሎቹ ይዘው የተነሱትን የብጥብጥ ዓላማ መና የሚያስቀረው ብቻ ሳይሆን፣ ሀገራችን
ውስጥ የተጀመረው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ይበልጥ እንዲያብብ የሚያደርገው ይመስለኛል።
ይሁንና ይህን የህዝቡን ፍላጎት ገቢራዊ ለማድረግ በገዥው ፓርቲም ይሁን በመንግስት
በኩል መከናወን ያለባቸው ጉዳዩች ጊዜ ሳይሰጣቸው ሊተገበሩ ይገባል። ለምሳሌ የሁከቱ ዓላማ ምን እንደሆነ ሳይገባቸው ወደ በሁከት
ፈጣሪ ኃይሎች አማካኝነት ወደ ችግር ውስጥ የገቡ ወጣቶችን ግልፅ በሆነ መንገድ ማወያየት፣ በህገ መንግሱ ዙሪያ ማስተማርና ስለ
ሰላማዊ ትግል አካሄድ የማሳወቅ ስራ መተግበር ያለበት ይመስለኛል። ከዚህ በተጨማሪም የሁከት ኃይሎቹን የጥፋት አሉባልታዎችን ለማምከን
በማህበራዊ ሚዲያዎችና በሌሎች የመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት የሚነዙ ወሬዎችን ፈጣን በሆነ ሁኔታ የአፀፋ ምላሽ በመስጠት ወጣቱን
በትክክለኛ መረጃ የተሟላ ቁመና እንዲኖረው ማድረግ የሚገባ ይመስለኛል። ይህም የሰላምን በር በማስፋት የበኩሉን ሚና ይጫወታል።
እርግጥ እዚህ ሀገር ውስጥ ያለውን የዕድገት መስመር የቀየሰው፣ ዜጎችን በየደረጃው
ተጠቃሚ ያደረገውና የኢትዮጵያን ቀደምት አሳፋሪ “ማንነትን” በመቀየር አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ ያደረገን ኢህአዴግና
መንግስት እንጂ፤ ውጭ በሆነው በፈጠራ ወሬዎች ሁከት በመፍጠር የትርምስ አውድማ ሊያደርጉን የሚሹ ኃይሎች አይደሉም። የችግሮች መፍትሔ
የሚገኘው ከኢህአዴግና ከመንግስት እንጂ ከእነርሱ አይደለም። እናም አሁን በተጀመሩት ህዝባዊ ውይይቶች የሁከት ኃይሎቹን አጀንዳ
እያሳጣ በመሆኑ፤ ከድርጅቱና ከመንግስት ጋር ሆነን የሰላምን በር አጥብቀን ልንይዝ ይገባል እላለሁ።
No comments:
Post a Comment