Tuesday, 13 September 2016

ሚኒስትርነት የስራ ቦታ እንጂ መታደል አይደለም


ስሜነህ
ከአስራ 15 አመታት በፊት በተደረገው የተሃድሶ መስመር ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ልማትንም ሆነ ዴሞክራሲን ማረጋገጥ የፍላጎት ጉዳይ አይደለም፤ የህልውና እንጂ። ይህ የሚረጋገጠው ልማት ደግሞ ከዴሞክራሲ ውጪ ትርጉም የሌለው መሆኑ ተመልክቷል። ዴሞክራሲውንም ለብቻው ማረጋገጥ ከልማት ውጪ የማይሞከር ነው።
በአንፃሩ ግን ኪራይ ሰብሳቢው ሃይል እነዚህን የህልውና መሠረቶች እንዳይረጋገጡ ተግቶ የሚሰራ መሆኑም ተመልክቶ ነበር። ይህ ሃይል ተሰግስጎባቸው በህዝቦች ጥቅሞችና ፍላጎቶች ላይ እየተረማመደ ወደ ትርምስ ለማምራት ከሚጠቀምባቸው ስልቶች አንዱ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶቸ እንዲፈጠሩ ማድረግ፣ በተፈጠሩት ላይ ደግሞ የማባባስን ስልት መከተል ስለመሆኑ ተመልክቶ የነበረው ጉዳይ ይኸው በተግባር ታይቶ ሲያፋጀን ከርሟል።
የመልካም አስተዳደር ጉደለት የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርአቱ ፈተና ሆኖ የተደቀነው አንድም መንግስታዊ አገልግሎትን ለሁሉም ወገን በፍትሃዊነት፣በጥራትና በብቃት ለማዳረስ የሚደረገው ጥረት የአቅም፣ የክሂሎትና የህዝባዊ ውግንና ጉድለቶች በፈፃሚው አካል ላይ ጎልቶ መንፀባረቁ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ሚንስትርነትን የስራ ቦታ ሳይሆን የግል ጥቅም ማካበቻ አድርገው የሚመለከቱ በርካታ ሹማምንት መፈልፈላቸው መሆኑንም ሰሞንኛው እና ካለፈው ባስ ባለ መልኩ የተደረገው ግምገማ አረጋግጧል።
መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚያስችሉ በተሃድሶ መስመሩ አማካይነት የተነደፉ የአገልግሎት አሰጣጥ ሪፎርሞች፣ አሠራሮችና አደረጃጀቶችን በቁርጠኝነትና በብቃት መፈፀም የሚችል የአመራር ሃይል በበቂ ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ የነበረ ቢሆንም ሚንስትርነትን በይገባኛል መንፈስ የሚመለከቱ ሃይሎች የወረሩት መሆኑም ሰሞኑን በከፈልናቸው ዋጋዎች ተረጋግጧል።
በመሬት አቅርቦትና አሰጣጥ፣ በንግድ ፍቃድ አሰጣጥ፣ በግብር አሰባሰብና በማዘጋጀ ቤታዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታየው አድሏዊ አሠራር፣ ንቅዘትና ዝቅጠት የመልካም አስተዳደር ጉዳይ የጦዘ አጀንዳ እንዲሆን ያስቻለውም የማእከላዊ ኮሚቴ አባልነትን የአቋራጭ ሹመት ማካማቻ አድርጎ የሚመለከተው ሃይል ስለበዛ ነው።
መልካም አስተዳደርን ማስፈን የመስመሩን ቀጣይነት ከማረጋገጥ ባለፈ በዜጎች ውስጥ የባይተዋርነት መንፈስ እንዳይፈጠር፣ ዜጎች በአገራቸው እጣ ፋንታ ላይ የመወሰን አቅማቸው እንዳይነጠቅ እና በማያቋርጥ የእድገት ጉዞ ውስጥ እየተመመች ያለች አገር ግስጋሴ እንዳይስተጓጎል ማድረግ  ነው።
ያም ሆኖ ግን በከተሞች ገዝፎ የሚታየው የመልካም አስተዳደር ችግር/ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በገጠሩም ተመሳሳይ ዝንባሌዎችና ተግባሮች እየጎለበቱ መታየት ጀምረዋል/ ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች፣ አስቻይ ፕሮግራሞችና አሠራሮች ቢዘረጉም ችግሩን መሻገር ያልተቻለው የሹመት ቦታዎች በችግር ፈቺዎች ሳይሆን በችግር አባባሾች ስለተወረሩ ነው። በየደረጃው የሚገኘው አመራር ቁርጠኝነት መጓደል፣ ከህዝባዊ ውግንና መንሸራተትና ከህዝብ ጥቅም በፊት የራስን ጥቅም ማስቀደም ባህል እየሆነ መምጣቱንም ሰሞንኛው ግምገማ በተጨባጭ አረጋግጧል። በተወሰነው የአመራር ክፍል በኩል የሚታየው ዳተኝነት፣ ከችግሮቹ ተቆራርጦ አለመገኘትና በአድርባይነት አዙሪት ውስጥ መዳከር ሌላኛው ለመፋጀት ያበቃን ጉዳይ ነው። ከኔ ጥቅም በፊት የህዝባችን ጥቅሞችና መብቶች መቅደም አለበት ብሎ ለዚህ መታገልና ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል የቆረጠ አመራር ሲጠበቅ ለግል ጥቅሙ የቆረበ አመራር በመበራከቱም መክፈል የነበረብንን ዋጋ እንድንከፍል ምክንያት ሆኖናል ።
ይህ ከህዝብ ያልወገነ አመራር የተሃድሶን መስመር ታምር ፈጣሪነት እየሰበከ፣ በጎን ደግሞ የህዝብ መሬት የሚዘርፍ፣ አርሶ-አደሩን በልማት ስም ከመሬቱ እያፈናቀለ ከኪራይ ሰብሳቢው ሃይል ጋር የሚዘምር፣ ልማታዊ ባለሃብቱን እየደቆሰ ጥገኛውን የሚያጀግን፣ የኪራይ ሰብሳቢውን ሃይል የሚታገል አመራርንም ሆነ ፈፃሚ ሃይል እንዲሁም አንድን የህበረተሰብ ክፍል ነጥሎ እየመታ ትግሉን የሚያቀዘቅዝ እና ሰልፉን ከጥገኛው ሃይል ጋር አስማምቶ ስርአቱን ከውስጥ የሚንድ ሃይል ሆኖ ስለመገኘቱም ምክር ቤቱ ባደረገው ግምገማ አረጋግጧል። ስለሆነም እዚህ ሰልፍ ውስጥ የገባን አመራር ማጥራትና ማስወገድ፣ ችግሩን ሊፈታ በሚችል መንገድ ተመጣጣኝ ርምጃ መውሰድ ግድ ይላል።
ምክንያቱም እዚህም እዚያም ቅሬታዎች በበዙና መፍትሄዎች የሌሉ በመሰሉ ቁጥር ቅሬታ የሚይዘው ሃይል እየበዛ መምጣቱ ብቻ ሳይሆን ወደለየለት ሁከትና ብጥብጥ መሄዱ አይቀሬ መሆኑን ሰሞኑን በሚገባ አይተናልና።  ሚንስትርነት የስራ ቦታ መሆኑን በዘነጉ አመራሮች እንደተወረረ ከቀጠ ሀገራዊ መተራመስና መበላላትን ይፈጥራል። ምክንያቱም ኪራይ ሰብሳቢው ሃይል ከህዝባዊ ውግንናው የተነሸራተተው ከፍተኛ የሆነውን የአመራር ሃይል አጥብቆ በመያዝ ነውና።
ሚንስትርነትን በይታደሉታል የተቆናጠጠው ሃይል ሌላው ችግር ያው በመታደል አግኝቶታልና የሚጠበቀው የአቅም፣ የልምድና የክሂሎት ችግር ነው። በዚህም ምክንያት የተፈጠረው ጉድለት ቀላል እንዳልሆነ ከግምገማው ውጤት ማረጋገጥ ተችሏል። የአመራር አቅም ክፍተትና የልምድ ጉድለት ያለበት የአመራር ሃይል ሙሉ በሙሉ በራስ መተማመኑ ስለሚከዳው በአማካሪነት ወይም በባለሙያነት በዙሪያው የሰበሰባቸው ሰዎች መሠረታዊ ህዝባዊ ውግንና ከሌላቸው፣ ይህን የአመራር ሃይል ለኪራይ ሰብሳቢነት ፍላጎታቸው ማስፈፀሚያ መሣሪያ አድርገው የሚጠቀሙበት መሆኑን መገመት አይከብድም። በዚህም ምክንያት ውሳኔዎቹ ወይም የአገልግሎት አሰጣጡ የህዝቡን እርካታ ያላረጋገጡ ይሆናሉ። እዚህም ላይ ኪራይ ሰብሳቢው ሃይል ጉድለቶችን ለቅሞ በመቀመር ለትርምስ ማነሳሻ ይጠቀምበታል።
ከላይ የሚገኘውና ሚንስትርነትን በይገባኛል የተቆናጠጠው አካል በዚህ መልኩ ሲጓዝ በተመሳሳይ  የአገልግሎት ዘርፎች ላይ የተሰማራው ፈፃሚ ሃይል ከአገልጋይነት ይልቅ በተገልጋይነት አስተሳሰብ ይጠለፋል። ስለሆነም ህዝቡ ከቀበሌ ጀምሮ ባሉ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ሰፊ የሆነ ቅሬታ በተደጋጋሚ ያቀረበው ለዚህ ነው። አመራሩም ፈፃሚውን ሃይል በአመለካከትም ሆነ በአስተሳሰብ ቀርፆ ልማታዊ ማድረግ የሚጠበቅበት ቢሆንም ለይስሙላ እና እየሰራሁ ነው ስለማለት ብቻ ሲመቸው በስብሰባ የመገሰጥ፣ የማይመቸው ሲሆን በደብዳቤ ከማስጠንቀቅ ባለፈ የረባ ርምጃ አይወስድም። አንዳንዴ ከፈፃሚው ሃይል ጋር ትሰስር ፈጥሮ ህዝብን ወደ ከፋ ጫፍና ብሶት የሚመራ አመራርም ስለመሆኑ ግምገማው በሚገባ አረጋግጧል።
ስለዚህ፣ እንደሃገር ልንቀጥል ካስፈለገ ሚንስትርነት በይገባኛልና በመታደል የሚይዙት  ሳይሆን የስራ ቦታ መሆኑን እንደመንግስት ተከታታይ በሚሆኑ እርምጃዎች ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

No comments:

Post a Comment