Friday, 30 September 2016

የተሃድሶ ወግ



 

ዮናስ

ኪራይ ሰብሳቢነትን በስኬታማ መንገድ በመታገልና ባለመታገል፣ ውጤት በማምጣትና ባለማምጣት ረገድ ቁልፍ ሚና ከሚጫወቱ አካላት መካከል መንግስት የመንግስትን ስልጣን የያዘው አስፈጻሚ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በተለይ መንግስት በአንድ በኩል የኪራይ ሰብሳቢነት አረንቋን በማድረቅ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለልማታዊ ኃይሎች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር መሰረታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ለውጥ የሚያመጣውን ትግል የሚመራ አንድ ቁልፍ ኃይል መሆን እንዳለበት ተሰምሮበት ያደረ፤ ይህን መስመር በመከተልም ሲገነባ የቆየ ነው፡፡ ይህ መሰረታዊ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግስት በማያቋርጥ የኪራይ ሰብሳቢነትና የኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች ጥቃት ስር ለማለፍ የሚገደድ ተቋም ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች ከቻሉ ከውጭ በሚያካሂዱት ጥቃት ልማታዊ መንግስትን ለማዳከምና ለማሽመድመድ ይሞክራሉ፡፡ በንቃት፣ በታቀደና በተደራጀ አኳኋን ባይመለምሏቸውም በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያለውን የኪራይ ሰብሳቢነት ዝንባሌ ለእነርሱ በሚያመች ኪራይ ሰብሳቢ አቅጣጫ ሊቃኙ ይችላሉ፡፡ ኢህአዴግ ካደረጋቸው ግምገማዎችና የህዝብ መድረኮች መገንዘብ የተቻለውና የተረጋገጠው  በድርጅቱም ሆነ እርሱ በሚመራው መንግስት ውስጥ ህዝቡንና አገራቸውን በልማታዊ አቅጣጫና በታማኝነት ከሚያገልገሉ አባላትና አመራሮች ጎን፣ ከዚህ ህዝባዊ የአገልጋይነት መንፈስና አስተሳሰብ ርቀው መንግስትን የራሳቸው ግላዊ ጥቅም ማካበቻ ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች በደባልነት መኖራቸውን ነው፡፡
ስለሆነም ተሃድሶ ማድረግ  አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። አንዳንድ አካላት ግን ተሃድሶውን እና የተሃድሶውን አቅጣጫ በተለየ መንገድ በመረዳት የተቀረው ደግሞ አውቆ የኪራይ ሰብሳቢነት ከርሱን ለመሙላት ይረዳው ዘንድ የጉዳዩን አቅጣጫ በማሳት ላይ ይገኛሉ እና ተሃድሶ ማለት ሁለንተናዊ የሆነ የትራንስፎርሜሽን ጉዞ መሆኑን የሚያጠይቁ ጉዳዮችን ማውጋት ስለሃገራችን ህዳሴ ጠቃሚ ነው።
እጅግ አብዛኛው የመንግስት ሰራተኛ ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል ለለውጡ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳበረከተው ሁሉ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታዩ እና የሰው ህይወትና ንብረት ለወደመባቸው ግጭቶች ምክንያት የሆኑ የኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚያዎችን   በጥብቅ በመታገልና በማስተካከል መንግስት የህዝብ አገልጋይ እንደሆነ መቀጠሉን ማረጋገጥ የተሃድሶው መነሻና መድረሻ እንዲሁም የተሃድሶው ማጠንጠኛ መሆኑን ጠያቂያኖቹም ሆንን መልስ ሰጪዎቹ ልንረዳውና የጋራችን አመለካከት ሊሆን ይገባል፡፡ በዚህ መሠረት በየደረጃው ያሉ ኃላፊዎችና አባላት በተለይ ደግሞ ዛሬም እንደትላንቱ ህዝብን የማገልገል ዓላማ አንግበው ሌት ተቀን ለአገራቸው እድገትና ለህዝባቸው ተጠቃሚነት የሚባትሉ ታጋዮች ይህን ኃላፊነት በቅጡ መወጣት የሚችሉበትን መደላድል መፍጠርም ሌላኛው የጠያቂውና የተጠያቂው ወገኖች የጋራ አረዳድ ሊሆን ይገባዋል፡፡
በግምገማው የተረጋገጠው እና የተሃድሶውም አስፈላጊ መሆን የታመነው መንግሥት ልማታዊ ባህርዩን ጠብቆ ተልዕኮውን እያሳካ እንዲጓዝ የማድረግ ጉዳይ  በቅንነት ከሚታገሉ አባላትና የአመራር አካላት ትግልና ቁርጠኝነት ውጭ ሊሳካ የማይችል መሆኑ ስለተረጋገጠ እና ለነዚሁ አካላት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መሆኑ የመጀመሪያው ሲሆን፤ ራሳቸው በኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚያ የተበከሉ አባላት ደግሞ፣ ይህን አደገኛ የጥፋት መንገድ ትተው ወደቀና አቅጣጫ የሚያመሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንጂ የቂም በቀል ሂሳብ ለማወራረድና የጠሉትን መትቶ የወደዱትን በማንገስ ወደለየለት የኪራይ ሰብሳቢነት አቅጣጫ ለማምራት አይደለም፡፡
ከዚህ በመነሳት የተሃድሶው ግብ መንግስትን ከማንኛውም አይነት ድክመት የማፅዳትና ለተልእኮው የማብቃት ጉዳይ እንጂ የግለሰቦችን ሂሳብ የማወራረጃ ጉዳይ እንዳልሆነ መገመት አይከብድም፡፡ ይህ የሚወሰነው ከምንም ነገር በላይ መንግስትን የመቆጣጠረው ህዝብ  ከአሉባልታና ከተሃድሶው አቅጣጫዎች ውጪ ከሚራገቡ ወሬዎች በመጽዳት  በበጎ ተፅዕኖው መንግስት ከመልካም አቅጣጫው እንዳይወጣ ሲያደርገው ነው፡፡ በመሆኑም ተሃድሶ ማለት  በአንድ በኩል የመንግስትን ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ ባህርያት በከፍተኛ ትኩረት ማጎልበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በመንግስት ደረጃ የሚታዩ የኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚያዎችን በፅናት እየተፋለሙ የማስተካከል ተግባራትን በፅናት መፈፀም እና ለመፈጸም የሚያስችል ምህዳር መፍጠር ማለት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
ተሃድሶ ማለት ሌላ ሳይሆን መንግስት በእስካሁን ድሎች ሳይዘናጋ፣ ባጋጠሙት ፈተናዎች ክብደት ሳይደናገጥ በፅናትና ህዝባዊ ወገንተኝነት የተያያዘውን ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ትግል ወደ ሌላ ከፍታ ለማውጣት የሚያስችለውን ስርአት መዘርጋትና ለዚሁ የሚመጥን የሰው ሃይል ማሰማራት ማለት ነው፡፡
ተሃድሶ ማለት በፊት ያልነበሩና በአግባቡ ከተጠቀምንባቸው አገራችንን ለላቀ ዕድገትና ጥንካሬ የሚያበቁ የተከማቹ አዎንታዊ አቅሞችን በአግባቡ መያዝና ጥቅም ላይ በማዋል ለውጤት ማብቃትን የተመለከተ እንጂ ፍለጠው፣ ቁረጠው፣ አንሳው ወይም ጣለው ላይ የተመሰረተ እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
በየደረጃው የሚታዩት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዓይነተኛ ምንጭ ኪራይ ሰብሳቢነት ስለመሆኑና  በየአስተዳደር እርከኑና በየሴክተር መስሪያ ቤቱ የሚገኘውን አመራርና ፈፃሚ የአድሎና የመጠቃቀም ተግባር ውስጥ የሚያስገባውም ይኸው ኪራይ ሰብሳቢነት እንደሆነ በጥናትም ሆነ በግምገማ ተረጋግጧል፡፡ ሕዝብን በቅንነት የማገልገል ተነሳሽነት ጉድለት፣ ማመናጨቅና ማዋከብ ውስጥ የሚከተው የሕዝባዊነት ጉድለት ምንጭም ይኸው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት መዳበር መሆኑን በማስገንዘብ ከዚህ የማውጣት ወይም ደግሞ ሚናውን እንዲለይ ማድረግ ነው ተሃድሶ፡፡ ጥልቅ ተሃድሶ ማለት እላይ የተንጠለጠለ የካቢኔ ብወዛ ሳይሆን መንግስትና ሕዝብ ተባብረው እንዲህ ያለውን፣ ሕዝባዊነት የጐደለውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የሰፈነበትን አመራርና ፈፃሚ ከየተቋሙና ከየመዋቅሩ ማጥራት ማጥራት ማለት ነው፡፡ ተሃድሶ ማለት ይህን ለማድረግ የሚያስችል አደረጃጀትና አሰራርን መዘርጋትና ማዘመን ማለት እንጂ ግለሰቦችን ማፈራረቅ ማለት አይደለም ። በጥቅሉ ጥልቅ ተሃድሶ ማለት በተነሳሳ ሕዝባዊ የለውጥ ሀይል ቀልጣፋ፣ አርኪና አስተማማኝ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ በመፍጠር መልካም አስተዳደርን ማረጋገጥ ማለት እንጂ በሚናፈሰው ልክ ማንሳትና መጣል ብቻ አይደለም፡፡ 
ጥልቅ ተሃድሶ ማለት  በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የተገነቡት መሰረተ ልማቶች፣ ለሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስኬታማነት ትልቅ አቅም መሆናቸውን ያገናዘበ ስርአት የመዘርጋትና ለዚሁ የሚመጥን አመራር መሰየምን እንጂ ማሰርና መፍታትን ግቡ ያደረገ አካሄድ ማለት አይደለም።  
ጥልቅ ተሃድሶ ማለት ወጣቱ ትውልድን በገጠርና በከተማ ልማት በማሰማራት የስራ ዕድል ከመፍጠር ጎን ለጎን የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሃይል ለማድረግ የሚያስችል አሰራር መዘርጋት፣ በጀት መያዝና ለዚሁ የሚመጥን ፈጻሚና አስፈጻሚ ማብቃትና ማምጣትን የተመለከተ እንጂ ሊታረም፣ ሊቃና የሚችለውን ሁሉ በማባረር ያለጥናትና ሙሉ ዝግጅት ሌሎችን መተካት ማለትም እንዳልሆነም ማጤን ስለተሳትፏችን የግድ ይላል። ይህን ከመንግስት አወቃቀር ባህርያት አንፃር ለተመለከተው ደግሞ ሁሉም ነገር የበለጠ ግልፅ ይሆናል።
የሁለተኛውን ዙር እና የአንደኛውን ዙር አፈጻጸም መነሻ ያደረገው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የገጠሩን አጠቃላይ ገፅታ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚለውጠው ይታመናል፡፡ የመስኖ ግብርና፣ የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንደዚሁም የእንሰሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ስራ በከፍተኛ ደረጃ ማስፋፋትን ትኩረት ያደረገው ይህ ዕቅድ፣ ግብርናው በዕቅድ ዘመኑ ለልማቱና ለፈጣን ዕድገቱ የማይተካ አስተዋፅኦ ከማድረግ ባሻገር የዘመናዊ አምራች ዘርፍ ዕድገት ዋና ምንጭ ሆኖ እንዲቀጥል እንደሚያስችልና ሰፊ የስራ እድሎችን የሚፈጥር እንደሆነም ፖሊሲ ተንታኞችም ሆኑ የዘርፉ ልሂቃን ደጋግመው መስክረዋል ፡፡  ስለሆነም የገጠር ኢንዱስትሪ ማዕከላት በሂደት እየተፈጠሩ ከተሞቻችንም በዛው መጠን እያደጉ ሲሄዱ የህብረተሰቡ የኑሮ ደረጃ እየተቀየረ፣ የከተማና የገጠር ትስስር እየጠበቀ፣ ያደገ ህብረተሰብ ለመገንባት የሚያስችለን አቅም እየተፈጠረ የመሄዱን አይቀሬነት የተገነዘበ እና የበቃ ፈጻሚና አስፈጻሚ የማምጣትን እና በሂደትም ተተኪዎች የሚፈሩበትን ስርአት መዘርጋት ነው ጥልቅ ተሃድሶ ፡፡
የጥልቅ ተሃድሶው አቅጣጫና ግብም እንዲህ የሚሆነው ከእንግዲህ ያለው ሂደት በስኬት የተሞላና ለውጡ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያጎለብት እንዲሆን የማድረግ ጉዳይ የሚወሰነውም የመንግስትን ስልጣን በሚይዙ  ብቃት ያላቸው አመራሮችና ፈጻሚዎች ስለሆኑ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የሃገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በትክክል ገምግሞ፣ መልካም ዕድልና ፈተናዎችን በውል ለይቶ፣ በመልካም እድሎቹ በአግባቡ ለመጠቀም፣ ፈተናዎቹን ደግሞ በተገቢው አቅጣጫ ለመፍታት የሚችል  ብቁ አመራር ሰጪና ተቀባይ ፈጻሚ ሲኖር ብቻ ስለሆነ ነው፡፡
ህዝብን በተለይም ማህበራዊ መሰረቶቹ የሆኑትን ብዙኃን እንደተለመደው በትክክለኛው አቅጣጫና በብቃት በማደራጀት የለውጥ ሃሳቦቹን ተግባራዊ የማድረግ ብቃት እንዲጎናፀፉ አድርጎ የመምራትን አቅም መገንባትና ስርአት መዘርጋትም የተሃድሶው አካል ነው፡፡ ስለሆነም ስለተሃድሶ ያለንን ግንዛቤ ከሞላ ጎደል ከላይ በተመለከቱት ማእቀፎች ማስተካከል የህዝብና የአገርን ዘላቂና መሰረታዊ ጥቅሞች የማስከበር ትግሉን በአሉታዊ ተፅዕኗቸው ለማምከን የሚተጉ ሃይሎችን ለማጨንገፍ ይጠቅመናል፡፡ ለምን ቢሉ በኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ የተበከሉ ሰዎች ውስጣዊ ዴሞክራሲን በማጥበብ፣ ከስህተታቸው እንዲታረሙ ወይም እንዲወገዱ የሚደረገውን ትግል በማዳከም ስርአቱ ራሱን በራሱ የማረም የቆየ ችሎታውን እንዲያጣ በማድረግ የጥቅማችን ተጻራሪ ያደርጉናልና ፡፡
ባጠቃላይ፣ በአሁኑ ጊዜ ይህን ችግር ለመታገል የተጀመረው ጥረት የግምባሩ አባላትን ብቻ ሳይሆን በብዙ አካባቢዎች ህዝብን ባሳተፈ አኳኋን ጭምር እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ጥልቅ ተሃድሶ ማለት በዚህ ትግል በተለይ  ህዝቡ የሚታየውንና የገጠመውን ችግር ሁሉ በድፍረትና በግልፅነት እያነሳ መፋለም ማለት መሆኑንም ማስመር ተገቢ ነው፡፡ በዚህም አማካይነት ዘላቂ የሆነውን ሃገራዊ ህዳሴ በአስተማማኝ ደረጃ የማሳካት ጉዳይ የጊዜ ጉዳይ ብቻ እንደሚሆን አያጠያይቅም። የአጭር ጊዜ!!!!

No comments:

Post a Comment