ታከለ አለሙ
የሀገር
ሠላም የህዝብ ኑሮና ህይወቱ እንዲታመስ እንዲናጋ በየቦታው ሁከትና ረብሻ እንዲነግስ ህዝቡ አይፈቅድም፡፡ የተሰሩት ታላላቅ ሀገራዊ
የልማት ሥራዎችም ሆኑ በሥራ ላይ ያሉትና ለመገባደድ ጥቂት የሚቀራቸው ፕሮጀክቶች እንዲስተጓጎሉ ማንም አይሻም፡፡ ዛሬም ነገም የኢትዮጵያ
ሠላም ውሎ ማደር ከምንም በላይ ቀዳሚ አጀንዳ ነው፡፡ በትርምስ ሀገር አይቀናም፡፡ ሀገር ተመካክሮ ተደማምጦ ልዩነትን አቻችሎ በጋራ
የሚኖሩባት ነች፡፡ ለዚህም ወሣኙ ሠላም ነው፡፡
ከባህር
ማዶ ሆነውም ሆነ ከሀገር ቤት በመንግሥት ደጋፊነትም ሆነ ተቃዋሚነት ስም እጅግ አስከፊ በሆነ ፀያፍ ቃላትና ነውረኛ በሆነ ስድብና
ዘለፋ ጥላቻና ማንቋሸሽ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨትና ለማባላት ዘረኛ መርዛቸውን የሚረጩት መረን አደጎች ጨዋውን ሥነ ምግባርና ፈሪሀ
አምላክ ያለውን ተከባብሮ ለዘመናት የኖረውን የኢትዮጵያ ህዝብ አይወክሉም፡፡
እውነተኞቹ
የኢትዮጵያ ልጆች ሁሉንም ወንድሜ እህቴ ብለው በእኩልነት የሚያዩ አብረው የሚኖሩ ያገኙትን በጋራ ተካፍለው በደስታውም በሀዘኑም
የማይለያዩ የአንዱን ችግር ሌላው የሚጋራው በአቅሙ የሚረዳው ቢታመም የሚጠይቀው ቢራብ የሚያበላው ቢታረዝ የራሱን አውልቆ የሚያለብሰው
ዘርና ጎሣ የሚባል ልዩነትና መከፋፈልን አጥብቆ የሚጠላ የሚሸሽም ነው፡፡ የተጋባ የተዋለደ በብዙ የማይበጠስ ሰንሰለት የተቆራኘ
ነው፡፡
በሰለጠነ
ዘመን ይህን የዘረኝነትና የጎሣ እጅግ ኋላ ቀር አስተሳሰብ የሚያራምዱ ግለሰቦች በኅብረተሰቡ ውስጥ ተቀባይነት የላቸውም፡፡ በዚህ
አስተሳሰብ የተቃኙ የተሞረዱ ሁሉ የሰው ልጆች ሁሉ እኩል ናቸው የሚለውን የተባበሩት መንግሥታትን ሰብዓዊ መብት ድንጋጌ የኢትዮጵያንም
ህገ መንግሥት ጭምር የሚፃረሩ የሚቃወሙ ናቸው፡፡ እንወክለዋለን ለሚሉትም ህዝብ የሚያተርፉለት ወሰን የሌለው ችግር ነው፡፡
አብሮነታችን
ፍቅራችን መዋለዳችን አብረን አብረን ብዙ ሺህ ዘመናትን በደጉም በክፉውም ማሳለፋችን ምን አለን? አሁን እስቲ ዙሪያችንን በጠላት
ተከበን የምንኖር መሆኑ ቢታወቅም ማን የውጭ ጠላት መጣብንና ነው በር የምንከፍተው?
ተመካክረን
ሀገራችንን ጠብቀን መኖር ማሳደግ ሲገባን በዘረኝነት ክፉ ደዌ እየተናጥን እርስ በእርስ መናቆሩን ምን አመጣው? ገፊ ምክንያቶች
የሉም አይባልም፡፡ እነዚህን መሠረታዊ ለሀገርና ለህዝብ አደጋ የሚሆኑ ችግሮች በቅድሚያ በውስጥ መፍታትና ማረም ማስተካከል የሚገባው
ምሣሌም መሆን ያለበት መሪው ኢህአዴግ ነው፡፡
በመንግሥት
ኃላፊነት በተለያየ ደረጃ የተቀመጡ ደጋፊ ነን የሚለትም በተቃዋሚውም ያሉት አክራሪ ጽንፈኞች ይህ ክፉ የዘረኝነት ልክፍትና ደዌ
የተቆራኛቸው ክፍሎች አሉ። በአስተሳሰብ እጅግ ደካማ የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክና ባህል የህዝቡን ለብዙ ሺህ ዘመናት የኖረ ቢበጥሱት
የማይበጠስ ታሪካዊ ቁርኝትና ትስስር ጠንቅቀው የማያውቁ ግልብ ግለሰቦች ናቸው፡፡ ማንም ሊከተላቸው አይችልም፡፡
በኢትዮጵያ
ውስጥ የተፈጠረ ብሄር ብሄረሰብ ሁሉ እኩል ነው፡፡ ሀገሩ ነች፡፡ መብቱም ሊከበርለት የተገባ ነው፡፡ የበላይም የበታችም የለም፡፡
ችግር የሚፈጠረው የእኩል ተጠቃሚነት መብት ሲጣስ ሲነፈግ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ለሀገርም ሆነ ለአብሮነት የማይበጅ የከፋፋይነት
ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ ዘመን ያስቆጠረ መርዝ ሲረጩ የኖሩ ሁሉ ለሀገርም ለህዝብም ሠላምና ዕድገት የማይበጁ ጠንቆች ናቸው፡፡
ዘረኝትና
ጎጠኝነት በዚህ የሰለጠነ ዘመን በየትኛውም የዓለም ህዝብ ዘንድ የማይታሰብ የሰውኛ ሳይሆን አውሬያዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ አሜሪካ
የዓለምን ህዝብ ሰብስባ የያዘች ሀገር ነች፡፡ የዓለም ብሄር ብሄረሰቦች ሁሉም በአሜሪካ ይኖራሉ፡፡ የእኛዎቹንም ጨምሮ፡፡ ሰው ሰው
በመሆኑ ብቻ ከየትም ሀገር ይሂድ ከየትም የሰውነት መብቱ በህግ ፊት ተከብሮ ይኖራል፡፡ ዘረኛነት ጎጠኛነት እጅግ የተወገዘ ወንጀል
ነው፡፡ ሀገርን ህዝብን በእጅጉ ይጎዳል፡፡
ዘረኝነትና
ጎጠኝነት ከአስተሳሰብ ድህነት ዘቅጦ ከማሽቆልቆል ወርዶ ከመንከባለል የሚመጣ ፈውስ የሌለው በሽታ ነው፡፡ ለታላቋ ሀገር ኢትዮጵያና
ለህዝቦቿ አይመጥንም፡፡ ዘረኝነትና ጎጠኛነት በዓለም ውስጥ በተለያዩ ሀገራት ታላቅ ጥፋትና ውድመት አስከትሏል፡፡ ከነበሩበት ደረጃ
ተንከባለው ወድመዋል፡፡ ህዝባቸው የከፋ ጥላቻ በሰፈነበት ዘረኛ የእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት አልቋል፡፡
ይህ ዓይነቱ
ዘግናኝ ታሪክ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ የሚሹ የሚመኙ መንግሥትን እንደግፋለን በሚል ሽፋን ዘረኝነትን የሚረጩና በጽንፈኛው ጎራ ተሰልፈው
በየፌስ ቡኩ በየማህበራዊ ሚዲያው በየሰዓቱ የሚያሰራጩ ዋልጌዎች ይህንኑ ነውረኛ ድርጊት ሥራዬ ብለው የተሰማሩበት ሲሆን ታላቁንና
ጨዋውን የኢትዮጵያ ህዝብ አይወክሉም፡፡ መንግሥትንም ሊወክል አይችልም፡፡
ኢትዮጵያዊነት
ከዘረኝነትና ከጎጠኝነት በላይ የላቀ የመጠቀ ታላቅ እሴት ነው፡፡ ይህንን ጨዋና ተከባብሮ ለዘመናት የኖረና ወደፊትም በአብሮነቱ
የሚኖር ህዝብ በግብጽና በሻዕቢያ አጀንዳ በመመራት ኢትዮጵን ለማፍረስና ለመበታተን የተጠነሰሰው ሴራ አባሪና ተባባሪ በመሆን እርስ
በእርሱ ለማባላት የሚደረገውን እኩይ ድርጊት ማስቆም የሁሉ ዜጋ ግዴታ መሆን አለበት፡፡ የህዝቡ ጥያቄ ተገቢና መሠረታዊ በመሆኑ
ኢህአዴግ ውሎ ሳያድር አፋጣኝ መልስ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡
የህዝብን
ጥያቄ በመንተራስ ቀዳዳ አገኘን ብሎ የሚክለፈለፈው የቀለም አብዮት ህልመኛም ሆነ ባልመራው ትግል እኔ ነኝ የመራሁት በሚል እየተኮፈሰ
ያለውም ስመ ብዙ ተቃዋሚ ባልዋለበት በሌለበት ባለቤት ሊሆን አይችልም፡፡ ሠላማዊ ሀገራዊ መፍትሄ ሊያስገኝ የሚችል ሀሳብ ማቅረብ
ቢችል ሀገሪቱንና ሠላሟንም ለመታደግ ይበጃል፡፡
ችግሮቹ
በሙሉ በሠላማዊ ውይይት በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ማድረግ ነው ለዛሬውም ለቀጣዩም ትውልድ የሚበጀው፡፡ ህዝብን ለመምራት ኃላፊነትን
ለመሸከም የማይመጥኑ የመንግሥትንም ህዝባዊ አካሄድና ሁሉንም በእኩልነት የማገልገል ራዕይና ህልም የሚያጨናግፉ ስብስቦች ኢህአዴግ
በጀመረው የሥር ነቀል ተሀድሶ ለውጥ የሚራገፉ እንጂ የሚቀጥሉ አይሆኑም ተብሎ ይታመናል፡፡ እያመጡት ያለው ብሄራዊ አደጋ በገሀድ
እየታየ ስለሆነ፡፡
በኢህአዴግ
ውስጥ የሚካሄደው መሠረታዊ ሥር ነቀል ለውጥ ለጎጠኝነት ለዘረኝነት ቦታ የሌለው የህዝቡን መሠረታዊ ጥያቄ የሚፈታ ብቻ ሳይሆን ሙሉ
በሙሉ አዲስ መስፈንጠርና ሽግግርን የሚያካሂድ ይሆናል ተብሎ ይታመናል፡፡ በመላው ሀገሪቱ ባለው አሠራርና አደረጃጀት ላይ ሥር ነቀል
ለውጥ ይካሄዳል፡፡ አሁን ያሉት ሹሞች በሙሉ በሚባል መልኩ ከቦታቸው ይነሳሉ ወይም ይቀየራሉ፡፡
ከቀበሌ
ወረዳ ክፍለ ከተማ ክልል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያሉ ሹሞች የመንግሥትና የፓርቲ ሥራ ሙሉ በሙሉ ስለሚለያይ ካድሬዎች ወደፖለቲካ
ሥራቸው ሙያተኛ ሲቪል ሠራተኞች ደግሞ በሙያዊ ነጻነት በብቃትና በችሎታቸው በአስተዋጽኦቸው በክህሎታቸው ሀገራቸውንና ህዝባቸውን
የሚያገለግሉበት እንደሚሆንም ይገመታል፡፡
ኢህአዴግንና
በውስጡ ያሉ ድርጅቶችን ሽፋን በማድረግ ስም በየቦታው እያንዳንዱ የየራሱን ቡድንና መረብ በመዘርጋት ሲያካሂደው የነበረው ህዝብንና
ሀገርን የጎዳ የገደለ መከፋፈልን የፈጠረ ነውረኛ የሆነ በድርጅት አባልነት ስም ሲሰራ የነበረ ድርጊት በተሀድሶው ለውጥ ከሥሩ ተነቃቅሎ
ተበጣጥሶ ይወገዳል የሚል ተስፋም አጭሯል፡፡
ያለእውቀታቸው
ያለሙያቸው በአመራር ወንበር ተኮፍሰው ሲመፃደቁ ሲያምሱና ሲያተራምሱ የነበሩ ዕድገትን ሳይሆን ውድቀትን ያመጡ በጎጠኝነትና የዘረኝነት
መንፈስ ጠባብ አጥር ውስጥ ተሸጉጠው ህዝቡን ሲያስመርሩ የነበሩ ትናንሽ ግልገል አምባገነኖች ከእንግዲህ በተሀድሶው ሥር ነቀል ለውጥ
ውስጥ ቦታና ሥፍራ አይኖራቸውም፡፡ እንደተባለው ተግባራዊ ከተደረገ ለኢህአዴግ ታላቅ የመስፈንጠር ዕርምጃ ነው ሊባል ይችላል፡፡
አዲሱ
የኢህአዴግ ሥር ነቀል የተሀድሶ የለውጥ እርምጃ የፓርቲ አባላትን ብቻ ሳይሆን በዋነኛነት ዜጎችን ሁሉ በሙያቸውና በብቃታቸው ለሀገራቸውና
ለህዝባቸው እውቀታቸውን ልምዳቸውን ችሎታቸውን በነጻነት እንዲያካፍሉ እንዲሰሩ የሚያስችል ነው፡፡ ለሌብነት ለምዝበራ በኢህአዴግ
አባልነት ስም እንዲዘርፉ ዜጎችን እንዲያስፈራሩ በህግ ስም ተጠቅመው ወንጀል እንዲሰሩ ቀዳዳና ክፍተት አይሰጥም፡፡ ካለፉት ስህተቶች
ሰፊ ሀገራዊ ልምድ በመቀመር እጅግ በገዘፈ ሁኔታ ሀገራዊ ለውጥ ለማምጣት የሀገሪቷንም ዕድገትና ልማት የበለጠ ቀጣይ እንዲሆን በማድረግ
ረገድ ወሣኝ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ለዚህ
ነው ኢህአዴግ ራሱን ሥር ነቀል በሆነ ለውጥ ውስጥ አሳልፎ የተሸከመውን ኪራይ ሰብሳቢና የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ፀር የሆኑትን
የሀገርና የህዝብ ኋላፊነት የማይሰማቸውን ጥገኞች አስወግዶ እውነተኛ የህዝብ አገልጋዮችን በማቀፍ ዳግም ታላቅ ሀገራዊ ለውጥና ዕድገት
ያስመዘግባል የሚል ጠንካራ እምነት የተፈጠረው፡፡ ይህም በተግባር የሚታይ ይሆናል፡፡
የአዲሱ
ዓመት አዲስ እመርታዊ የተሀድሶ ለውጥ የሀገሪቱን የዴሞክራሲ አውድ ማስፋት ሁሉንም የሀገራችን ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎችን ማሳተፍ
በጎና ገንቢ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ማስቻል ሀገርንና ህዝብን ሠላሟንና ህዝቧን መጠበቅ የተጀመሩትን ሀገራዊ የልማትና የዕድገት
ፕሮጀክቶች በስኬት ማጠናቀቅ ማስቀጠል የሚሉትን ዐቢይ ነጥቦች ያካተተ እንደሆነም ይታመናል፡፡
የኢትዮጵያ
ጠላቶች የተመኙትን የሀገራችንን ውድቀት ሳይሆን ታላቅ ድል አድራጊነትና ስኬትን ደግመን ደጋግመን ማረጋገጥ የእኛ የኢትዮጵያውያን
ሁሉ ታላቅ ሀገራዊ ግዴታና ኋላፊነት ነው፡፡ ለዚህም ቁልፍ ሆነው የተከሰቱት የህዝቡ ችግሮች መፈታት ወሣኝነት አለው፡፡
የህዝቡን
መሠረታዊና ህጋዊ ጥያቄዎች በመንተራስ ሀገራዊ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነግስ መደማመጥ እንዲጠፋ የእርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጠር የሚሰሩትን
የግብጽና የሻዕቢያ ተላላኪዎች የቀለም አብዮት ናፋቂዎችን መሰሪ ሴራ ህዝቡ ራሱ ከሥሩ ነቅሎ ይጥለዋል፡፡ ያመክነዋል፡፡ ችግሩን
ፈትቶ በአብሮነቱ ይቀጥላል፡፡
ኢትዮጵያ
ልጆቿ መደማመጥና መግባባት ተስኗቸው እርስ በርሳቸው እንዲናቆሩ ታሪካዊ ጠላቶቿ የሸረቡትን ደባ በልጆቿ ርብርብ ታመክነዋለች፡፡
የትርምስ የሁከት ማዕከል አትሆንም፡፡ አትፈርስም፡፡ አትበታተንም፡፡ ይልቁንም ኃያልና ተፈሪ ሀገር ሆና ትቀጥላለች፡፡ ለዚህ ነው
ሀገራዊ ሠላምና መረጋጋት ወሣኝ የሚሆነው፡፡
No comments:
Post a Comment