ብ. ነጋሽ
በኢትዮጵያ
እያሰለሱ፣ በተለያዩ ሰበቦች ወደሁከትነት የተለወጡ ተቃውሞዎች ሲያጋጥሙ ቆይተዋል። በ1993 ብርሃኑ ነጋና ፕ/ር መስፍን የአዲስ
አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በብሄራዊ ሎተሪ አዳራሽ ሰብሰበው ማነጋገራቸውን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ ለሰዎች ህይወት መጥፋት፣
ለዝርፊያና የህዝብና የመንግስት ንብረት መውደም ምክንያት የሆነ ሁከት ተቀስቅሶ እንደነበረ እናስታውሳለን። ከዚያ በኋላ በ1997
ሀምሌና በ1998 ጥቅምት የቀደሞው ቅንጅት በህዝብ ውክልና ያገኘውን አዲስ አበባን የማስተዳደር፣ እንዲሁም በአማራ ክልልና በፌደራል
መንግስት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘውን በመቶዎች የሚቆጠር መቀመጫ አሻፈረኝ ብሎ ድምጽ የሰጠው ህዝብ በሃይል ህገመንግስታዊውን
ስርአት እንዲንድ ባስተላለፈው ጥሪ ምክንያት በአዲስ አበባና በአንዳንድ የሃገሪቱ ከተሞች ተቀስቅሶ የነበረውም ሁከት የሚረሳ አይደለም።
ከዚህ
በኋላ በውጭ ያሉ የኤርትራ መንግስት ስር የመሸጉ ተቃዋሚ ነን ባይ ቡድኖችና ሳይመች ህጋዊነትን፣ አመቺ ሁኔታ አለ ብለው ሲያስቡ
ደግሞ ህገወጥነትን እያጣቀሱ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በይፋና በስውር አጀንዳ እየተቀባበሉ ሁከት ለመቀስቀስ የማያቋርጥ ሙከራ
አድርገዋል። እንደየወቅቱ ሁኔታ ሁከት ለመቀስቀስ ያልተሞከረበት አጀንዳ የለም። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ሁከት የመቀስቀስ ሙከራዎች
ሳይሳኩ ቆይተው በ2003 ዓ/ም ተገቢ የሆኑ የሙስሊሙን ማህበረሰብ ጥያቄዎች አስታከው የተነሱ ቡድኖች በማህበራዊ ሚዲያ በመታገዝ
ለአንድ ዓመት ያህል የዘለቀ ሁከት መቀስቀስ ችለዋል። ይህ ሁከት አብላጫ ቁጥር ባላቸው ሙስሊሞች ባለመደገፉ እየተዳከመ ቢመጣም ህጋዊ ሆነው የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በውጭ ሃገር
ከሚገኙ ፅንፈኛ ተቃዋሚዎች ጋር በመተባበር እንዲያንሰራራ እድል ሰጥተውታል። ግንቦት 2005 ዓ/ም ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ
ከተማ የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ፣ በዚሁ ዓመት አንድነት ለዴሞከራሲና ለፍትህ በተለያዩ የሃገሪቱ ከተሞች በተለይ በደሴ ከተማ ጠርቶት
የነበረው ሰልፍ ለዚል በአስረጂነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።
የአክራሪነት
እንቅስቃሴ የቀሰቀሰው ሁከት በአንዳንድ ህጋዊ ሆነው በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና በውጭ ሃገራት ከኤርትራ ጋር አብረው ህገመንግስታዊ
ስርአቱን ለመናድ የሚፍጨረጨሩ ቡድኖች መንግስትን በሃይል አስወግደው ስልጣን ለመያዝ ያግዘን ይሆናል በሚል የአክራሪነትን አደጋ
ችላ በለው አብረውት ሲያቦኩ ቢቆዩም፣ አክራሪነት የሽብርተኝነት ርዕዮተ ዓለም በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፈጠረው ስጋት ወደኢትዮጵያም
ዘልቆ በብዙን ተቀባይነት ተነፍጎት እንደበጋ ጉም በኖ ጠፍቷል። የአክራሪነት እንቅሰቃሴ ግን አሁንም ውስጥ ውስጡን መኖሩን የሚያመለከቱ
ሁኔታዎች አሉ።
ከዚህ
በኋላ በ2006 ዓ/ም የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን ረቂቅ መነሻ በማድረግ በኦሮሚያ ውስጥ በሚገኙ
ዩኒቨረሲቲዎችና አንዳንድ ከተሞች ሁከት ብልጭ አለ። የክልሉ መንግስት ይህን ሁከት በተወሰነ ደረጃ በጉዳዩ ዙሪያ ከህዝብ ጋር ባካሄደው
ውይይት ለግዜው አዳፈነው። ይሁን እንጂ በ2008 ዓ/ም በሌሎች በክልሉ ውስጥ በሚፈፀሙ የኪራይ ሰብሳቢነተና የመልካም አስተዳደር
መጓደል በተፈጠሩ ብሶቶች ታጅቦ በ2008 ዓ/ም ድንገት ፈነዳ።
እነዚህንና
መናልባት ሌሎችም ያልጠቀስኳቸው ሁከቶች ጠለቅ በለን ስነመረምራቸው ጥቂትም ቢሆን ተገቢ የህዝብ ወይም የአንድ ማህበረሰብ ብሶትና ጥያቄ መኖሩን እንረዳለን። ይሁን እንጂ ብሶቶቹና ጥያቄዎቹ በህገመንግስት
የተረጋገጠውን ህጋዊና ሰላማዊ መንገድ እስከመጨረሻው አሟጦ ከመጠቀም ይልቅ በደአውዳሚ ሁከትነት የሚሸጋገሩት እውነተኛ የብሶቱ ባለቤት
በሆኑና ጥያቄ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አይደለም። ሁኔታው የፈጠረውን ሊገነፍል የሚችል ስሜት በመነካካት በሁከት መልክ እንዲፈነዳ
የሚያደረጉት ከሁከቱ የፖለቲካ ትርፍ እናገኛለን በለው የሚያሰቡ በውጭ ሃገራት የሚገኙ ፅንፈኛ ተቃዋሚዎችና በሃገር ውስጥ ያሉ አመቺ
አጋጣሚ ያገኙ ከመሰላቸው በህገወጥ መንገድ ስልጣን መመንተፍን እንደ አንድ የፖለቲካ ስልት ይዘው በህግ ስር ያደፈጡ ተቃዋሚዎች
ነው። ይህ የህዝብን ብሶት ያለወጉ በመቆስቆስ ወደሁከት የመውሰድ አካሄድ ለወደፊትም መሞከሩ የሚቀር አይመስለኝም። ይህ እንዳይሆን
ማድረግ የሚቻለው አይነተኛና ብቸኛ መንገድ የህዝብን ፍላጎት ማሟላትና
እርካታ መፈጠር ነው። ይህ በተለያየ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቶ ህዝበ ጥያቄ ማንሳት ሲጀምር ወዲያወኑ ህዝቡን አወያይቶ አፋጣኝ መላሽ
መስጠትም የግድ ነው። ይህ ካልሆነ ለወደፊትም በመጠላላት ቅስቀሳና በሁከት ስንታመስ መኖራችን አይቀሬ ነው።
ታዲያ
በየአጋጣሚው ከሚቀሰቀሱ ሁከቶች ጋር ተያይዞ የስርአት ለውጥ ይመጣል ብለው ተስፋ የሚያደረጉ፣ ግለሰቦቸና ቡደኖች በእነሱ አተያይ
የስርአት ለውጥ መቃረቡን ለማብሰር እግረመንገዳቸውንም ወደስልጣን ሊያወጣን ይችላል ብለው ያመኑበትን መንገድ ለማመቻቸት የተለያዩ
አስተያየቶች ይሰጣሉ፣ አቋም ይይዛሉ። ዜጎች በማንኛውም ጉዳይ ላይ ያመኑበትን አስተያየት የመስጠት አቋም የመያዝ፣ ይህን የማራመድ
ህገመንግስታዊ መብት እንዳላቸው አጥብቄ አምናለሁ። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የሚሰጧቸው አስተያየቶችና የሚይዟቸው አቋሞች የሃገሪቱን
ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘቡና ሊሆኑ የማይችሉ፣ ከእውነታ ሳይሆን እንዲሆን ከሚፈለግ የፈጠራ አቋም የሚነሱ ናቸው። ከእነዚህ መሃከል
የተወሰኑትን በአጭሩ እንመለከት።
የመጀመሪያው
ነባሩና የተለመደው ብሄራዊ እርቅ ይደረግ፤ በውጭና በሃገር ውስጥ ያሉ
ተቃዋሚዎችን፣ ታዋቂ ግለሰቦችን፣ የሃገር ሽማግሌዎችን . . . ያሳተፈ የሽግግር መንግስት ይቋቋም የሚል ነው። ሰሞኑንም
እየሰማነው ያለነው ይህንንና ይህን የመሳሰሉትን ነው። ሌላው የሁከት ሰሞን የተለመደ አቋም፣ ጥያቄው ተጠልፎ ወደሁከት የተገፋው
የህብረተሰብ ክፍል ህግን ባላከበረ ሁኔታ ሃይል የተቀላቀለበት የአደባባይ
ተቃውሞ ያካሄደው ድምጹ ስለታፈነ ነው፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማደረግ ስለተከለከለ
ነው የሚል ነው። ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየተለመደ የመጣው ደግሞ ለሁከት የወጣው ሰው ሃምሳም ይሁን አምስት መቶ “ገዢው ፓርቲ 99 በመቶ፣ 100 በመቶ ድምጽ አግኝቻለሁ ባለ ማግስት የገጠመው
ተቃውሞ፣ አገኘሁት ያለው ድምጽ የውሸት መሆኑን ያሳያል፣ ህዝብ ከዳር ዳር ተነስቶበታል፤ አንድ በመቶም የሚሆነው ህዝብ ድምጹን
አልሰጠውም” የሚል ነው። ይህ እስተያየት ሰሞኑን በኦሮሚያና
በአማራ አንዳንድ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ሁከቶችን ተከትሎ በውጭና በሃገር ውስጥ ባሉ ተቃዋሚዎች አመራሮች ሲነገር ይሰማል። እነዚህን
ከላይ የተነሱ ሶስት ጉዳዮች አንድ በአንድ እንመልከታቸው።
ብሄራዊ እርቅ ይደረግ፣ በውጭና በሃገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎችን፣
ታዋቂ ግለሰቦችን፣ የሃገር ሽማግሌዎችን . . . ያሳተፈ የሽግግር መንግስት ይቋቋም ከሚለው እንጀምር። ይህ ኮሽ ባለ ቁጥር ከውጭም ከሃገር ውስጥም የሚሰነዘር
አሰተያየት አንድ የዘነጋው ወይም ሊገነዘበው የማይፈልገው ትልቅ እውነት አለ። ይህም የሃገሪቱ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶችን ማንነት
ነው። የኢፌዴሪ ህገመንግስት አነቀፅ 8 “የህዝብ ሉዓላዊነት” በሚል ርዕስ ስር፤
·
የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና
ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው።
·
ይህ ህገመንግስት የሉዓላዊነታቸው
መገለጫ ነው።
·
ሉዓላዊነታቸው የሚገለጸው በዚህ ህገመንግስት
መሰረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደረጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት ይሆናል።
ተብሎ
ተደንግጓል።
በዚህ
የህገመንግስት ድንጋጌ መሰረት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዘጠኝ ክልሎችና ክልሎቹ በሚወከሉበት የፌደራል መንግስት
የተዋቀረው የሃገሪቱ የመንግስት ስርአት ባለቤቶች ናቸው። በሃገሪቱ ፌደራላዊ ስርአቱን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል አለመግባባት ከተፈጠረም፣
የሚፈጠረው በእነዚህ በአመዛኙ በብሄርና ብሄረሰብ ማንነት ላይ ተመስርተው በተዋቀሩ የሃገሪቱ ክልሎች መሃከል ነው። ይህ ሲሆን ክልሎቹ
የብሄራዊ እርቅ ፣ አብረው ለመኖር የተሰማሙበትን ህገመንግስት የመከለስ፣ በሁሉም ስምምነት ህገመንግስቱን የማሻሻል ጠያቄ ሊነሳ
ይችላል። ከዚህ ውጭ በህገመንግስት የተረጋገጠውን ዴሞከራሲና በብሄር ላይ በመመስረት የተዋቀረውን ፌደራላዊ ስርአት አልፈልግም ብሎ
አኩርፎ የሸሸ ሁሉ ብሄራዊ እርቅ የሚባል ጠያቄ ሊያነሳ አይችልም።
ይህ ጥያቄ ያልተጣላን ለማስታረቅ እንደመሞከር ነው የሚቆጠረው።
የሃገሪቱን
ፌደራላዊ ስርአት የማስቀጠል አለያም ፌደራላዊ ስርአቱ እንዲፈርስ የማድረግ መብትም አቅምም ያላቸው በህገመንግስቱ አንቀጽ 8 መሰረት
የሃገሪቱ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች የሆኑ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብቻ ናቸው። ማንም ተነስቶ የሃገሪቱ እጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን፣
የሽግግር መንግስት የማቋቋም ስልጣን የለውም። ይህ ታዋቂ ሰዎች፣ የሃገር ሽማግሌዎች ሰብስቦ የሽግግር መንግስት መመስረት የሚባለው
ሃሳብ በራሱ ትርጉም የለውም። ምክንያቱም የሃገሪቱ ስልጣን ያለው በብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እጅ በመሆኑ።
አናም
ይህ ሁከት በተቀሰቀሰ ቁጥር የሚቀርብ የብሄራዊ እርቅ እናድርግ፣ የሽግግር መንግስት እንመስርት ጥያቄ የሃገሪቱን ባለቤቶች ካለማወቅ
ወይም ለባለቤትነታቸው እውቅና ከመንፈግ የመነጨ ነው። በመሆኑም ከማውራት የማያልፍ ከንቱ ነው።
ከሁከት
ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው አጀንዳ ሃይል አዘል የአደባባይ ተቃውሞ
ያካሄደው ህዝቡ ድምጹ ስለታፈነ ነው፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ
ስለተከለከለ ነው የሚል ነው። ይህን የሚሉን ግን እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀምጠው በጋዜጣና በመጽሄት፣ በድረገጾች፣ ውጭሃገራት
በሚገኙ የሬድዮ ጣቢያዎች . . . አንድ ሳምንት እንኳን ሳያርፉ መረን የወጣ የተቃውሞ አስተያየት ሲሰጡ የቆዩ ግለሰቦች ናቸው።
ህዝብ በህገመንግስቱ የተረጋገጠለትን ድምጹን የማሰማት መብት ተነፍጎ ከሆነ እነርሱ የፈለጉትን የመናገር ነጻነት ከየት ይሆን ያገኙት?
እርግጥ
ነው በግልጽ በህግ በወንጀልነት የሰፈረን ድንጋጌ የተላለፉ የጋዜጣና የመጽሄት አዘጋጆች ክስ ተመስርቶባቸው ሊሆን ይችላል። የዚህ
ክስ ዓላማ ግን የዜጎችን ድምጻቸውን የማሰማት መብት ማፈን ሳይሆን፣ ጋዜጣዎቹና መጽሄቶቹ በህዝብ ሰላም ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን
ጉዳት መከላከል ነው። ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በየትም ሃገር የሚደረግ ነው። ሰሞኑን የብሄር ጥላቻንና ግጭትን ሲቀሰቅሱ
ከነበሩ የፌስቡክ ገጾች መሃከል የተዘጉ መኖራቸውን ልብ በሉ። ይህን ያደረገው የኢትዮጵያ መንግስት አይደለም፤ የፌስቡክ ባለቤት
ኩባንያ ራሱ እንጂ። በፌስቡክ ገፆቹ የሚተላለፉት መልዕክቶች ለእልቂትና ለሰብአዊ መብት ጥሰት ምክንያት ሊሆኑ ስለሚችሉ ተዘጉ እንጂ
ድምጻቸውን ለማፈን አይደለም። በኢትዮጵያም ተመሳሳይ እርምጃዎች መወሰዳቸው አይካድም። አናም ይህን እንደ መታፈን መቁጠር ለሀገር
እንዳለማሰብ ይቆጠራል።
አመራሮቻቸው፤ ህዝቡ ታፈነ፣
ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ተከለከለ . . . የሚል ወሬ የሚያወሩ ፓርቲዎችን ስንመለከት አብዛኞቹ በአንድ ዓመት ከአምስት ጊዜ
በላይ ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ሆነው እናገኛቸዋለን። ለምሳሌ አምስተኛው ዙር ሃገራዊ ምርጫ በተካሄደበትና የድምጾች መሰማት እጅግ
ይፈለግ በነበረበት 2007 ዓ/ም፣ በከተማው አስተዳደር ህጋዊ እውቅና በማግኘት አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ከ25 በላይ ሰላማዊ ሰልፎች
ተካሂደዋል። እነዚህን ሰልፎች ያካሄዱት ፓርቲዎች ከአራት አይበልጡም። አብዛኞቹ ሰልፎች በሰማያዊ ፓርቲ፣ በአንድነትና በመድረክ
የተካሄዱ ናቸው። እነዚህ ፓርቲዎች በተቀሩት የሃገሪቱ ክልሎች፤ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዘቦች፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ ከተሞችም
እውቅና የተሰጣቸው ሰልፎች አካሂደዋል። የሚገርመው ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ
ተከልክሏል እያሉ የሚያወሩት ግን እነዚሁ ፓርቲዎቸ ናቸው።
እኔ እንደታዘበኩት
እነዚህ ፓርቲዎች ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደው ድምጻቸውን ካማሰማት ይልቅ እንዲከለከሉ ነው የሚፈለጉት። ይህ የሆነው በሰልፉ ከሚያስተጋቡት
ድምፅ ይልቅ ተከለከልን ብለው የሚነዙት ወሬ የሚዲያንና የሰብአዊ
መብት ተሟጋች ነን የሚሉ ቡድኖችን ትኩረት ሰለሚስብ የበለጠ የፖለቲካ ትርፍ ያስገኛል በሚል የተሳሳተ ስሌት ነው። ሰላማዊ ሰልፍ
እንዲያካሂዱ ጠይቀው እውቅና ሲያገኙ፣ ሆነ ብለው ከተፈቀደላቸው አካባቢ ውጭ ካልተሰለፍን የሚል አምባጓሮ የሚያነሱት አንዳንዴም
እኛ ባልነው አካባቢ ካልሆነ አንሰለፍም ብለው የሚሄዱት ለዚህ እንዲመቻቸው ነው።
ያም ሆነ
ይህ በሃገሪቱ በርካታ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎች ሲካሄዱ ቢቆዩም ከዚህ ይልቅ ተከለከለ የሚለው በተደጋጋሚ ሲነገር ስለሚሰማ “እውሸት
ሲደጋገመ እውነት የመስላል” እንዲሉ በሰልፎቹ ላይ ሲሳተፉ የቆዩ ጭምር የሰልፍ ክልከላ አለ የሚለውን እነደእውነት ተቀብለው ሲያስተጋቡት ይሰማል። በተለየ እውቅና የሌላቸው ሃይል አዘል
ሰልፎች ተካሂደው ግጭት የተፈጠረ ሰሞን የግጭቱን መንስኤና በግጭቱ የደረሰውን ጉዳት መንግስት ላይ ለማላከክ፣ ሃይል የተቀላቀለበት ሰልፍ የተካሄደው መንግስት ሰልፍ ማደረግ ስለከለከለ
የታፈነ ድምጽ ፈንደቶ ነው እያሉ በውሸት ላይ የተመሰረተ ዲስኩር መስማት የተለመደ ነው። እርግጥ ሰልፎች ከቁጥጥር ውጭ ወጥተው
ለህግ ጥሰትና ለሰብአዊ ቀውስ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ ሲኖር ሁኔታዎች እስኪረጋጉ የሰልፍ ጥያቄዎች እውቅና ሊነፈጋቸው
ይችላል። ይህ የሚሆነው ሰlፎቹን ለመከልከል ሳይሆን የሚያስከትሉትን ቀውስ ለማስቀረት ነው። ከሁለት ሳምንት በፊት ሰማያዊ ፓርቲ
በባህርዳር ከተማ ጠርቶት የነበረውን፣ በቦምብ የሰው ህይወት የጠፋበትንና የህዝብ ንብረት የወደመበትን ሰልፍ ለዚህ አስረጂነት ማንሳት
ይቻላል። እንደእኔ እምነት ወቅቱ መረጋጋት ያልነበረበት በመሆኑ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ሰማያዊ ፓርቲ ላቀረበው የሰልፍ ጥያቄ
ማዘግየት ነበረበት። እርግጥ አንዳንድ የከተማ አስተዳደሮች ሰላማዊ ሰልፎችን በሙሉ የሚፈሩበትና አንጃ ግራንጃ እያበዙ እውቅና የመስጠቱን
ሂደት ያጓተቱበት ሁኔታ መኖሩ አይካድም። ይህ ለወደፊት መታረም ይኖርበታል። በአጠቃላይ ያለው ሁኔታ ግን መንግስት፣ ገዢው ፓርቲ በህገመንግስቱ የተረጋገጠውን ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ
ነፃነት ከልክሏል እየተባለ የአውዳሚ ሁከትን ተገቢነት ለማረጋገጥ የሚነዛውን ያህል የተጋነነ አይደለም።
በመጨረሻ የሁከትን ተገቢነት ለማረጋገጥ የሚነሳ ከምርጫ ውጤት ጋር የተያያዘ የውሸት
ወሬ እንመለከት። ይህም “ ገዢው ፓርቲ 99 በመቶ ድምጽ፣ 100 በመቶ
ድምጽ አግኝቻለሁ ባለ ማግስት የገጠመው ተቃውሞ፣ አገኘሁት ያለው ድምጽ የውሸት መሆኑን ያሳያል፣ ህዝብ ከዳር ዳር ተነስቶበታል፤
አንድ በመቶም የሚሆነው ህዝብ ድምጹን አልሰጠውም” የሚለው ነው። ይህን የሚናገሩት በምርጫው ላይ ተወዳድረው ያገኙትንና የተበለጡበትን የድምጽ ልክ፣ እንዲሁም ኢህአዴግ የተወዳደረባቸውን ክልሎች
የሚያውቁት ጭምር ናቸው።
በቅድሚያ
ኢህአዴግ በዘጠኙም ክልሎች አልተወዳደረም። ኢህአዴግ የሚወዳደረው በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ በትግራይ
ክልሎች፣ እንዲሁም በአዲስ አበባና በድሬደዋ ከተሞች ነው። አፋር፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሃራሪ (በከፊል)
ኢህአዴግ አይወዳደርባቸውም። በመሆኑም ኢህአዴግ በምክር ቤቱ ውስጥ ገዢ ፓርቲ መሆን የሚያስችለውን አብላጫ ድምጽ አግኝቷል እንጂ
የምክር ቤቱን መቀመጫዎች መቶ በመቶም ይሁን 99 በመቶ ተቆጣጥሮ አያውቅም። እርግጥ ኢህአዴግ በማይወዳደርባቸው ክልሎች ተወዳድረው
የሚያሸንፉት ፓርቲዎች በዓላማ ከኢህአዴግ ጋር ስለሚመሳሰሉ በአመዛኙ የኢህአዴግን አቋም ይደገፋሉ።
ኢህአዴግ
በተወዳደረባቸው ክልሎችም ቢሆን መቶ በመቶ የህዝብ ድምጽ አግኝቶ አያውቅም። በ50+1 አብላጫ ድምጽ ነው ያሸነፈው። ባለፈው ምርጫ
አዲስ አበባን ብንወስድ 15 በመቶ ያህሉ ድምጽ ሰጪ ኢህአዴግን አልመረጠም፣ በባህርዳርም ተመሳሰይ ሁኔታ ነበር። እናም ኢህአዴግ
በተወዳደረባቸው ሁሉም አካባቢዎች ማሸነፉ የመራጩን ሙሉ ድምጽ ማግኘቱን አያመለክትም። እናም ከተሞች ውስጥ ሁከት በተነሳ ቁጥር
ኢህአዴግ መንግስት ለመመስረት ያስቻለውን የስልጣን ውክልና ድምጽ ለማጣጣል
መቶ በመቶ ድምጽ አገኘሁ ያለው የውሸቱን ነው በማለት የሚነዛ ወሬ ሆን ተብሎ ፓርቲው በህዝብ ዘንድ ያለውን አመኔታ ለመሸርሸር
የሚነዛ ውዥንብረ ነው።
በአጠቃላይ
ተቃዋሚዎች በተጨባጭ እውን ሊሆን የሚችልና ህገመንግስቱን ያገናዘበ አቋም መያዝ ትተው በአንድ አጋጣሚ ሊገኝ ይችላል ብለው በሚያስቡት
የፖለቲካ ትርፍ መነሻነት የሚይዙት አቋም፣ ውሸት ሲደጋገም . .
. እንደሚባለው በሃሰተኛ መረጃ ህዝብን በማደናገር አጋጣሚዎችን
እየጠበቁ በፈለጉት መንገድ ለመንዳት በማሰብ የሚነዙት መሰረተ ቢስ ወሬ ለሃገሪቱ ዴሞክራሲ፣ ለተቃዋሚ ፓርቲዎችም ዘለቄታዊ ጥንካሬ
አይጠቅምም። ይህ የውዥንብር አካሄድ ጥቅም ያለው ቢሆን ኖሮ በዚህ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትልቅና ጠንካራ በሆኑ
ነበር። እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው። ከግዜ ወደግዜ በእርስ በርስ አለመግባበት እየታመሱ ውህደታቸው ሲፈርስ ነው የሚታየው።
ነባር አመራሮቻቸው ተሰናብተው ዳር ቆመው የመሰረቱትንና የመሩትን ፓርቲ ሲተቹና ሲወቅሱ ነው የሚሰማው። ፓርቲዎቹ ከዓመት ወደዓመት
እያነሱ ሄደው ድንገት በአንድ አጋጣሚ ብቅ ሲሉ “አሉ እንዴ?!” የሚባሉበት ደረጃ መድረሳቸው ነው የሚታወቀው። የኢትዮጵያ ህዝብ
አሁን ስልጣን ለመረከብ የሚበቃ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አለ በሎ ከቶም አያምንም፤ ኢህአዴግን አምርረው የሚቃወሙትም ጭምር። እናም
ተቃዋሚዎቻችን ከቅዠት ወጥተው ነባራዊው እውነታ በሚያዘው መሰረት ቢንቀሳቀሱ መልካም ነው። በኔ እምነት፣ የሚያዛልቀው ይህና ይህ
ብቻ ነው።
No comments:
Post a Comment