አሜን ተፈሪ
በዚህ ዓመት ጎላ ብለው ከታዩ ችግሮች መካከል ድርቅ እና ሰፊ
የጸጥታ መደፈርስ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የድርቁን ችግር በመከላከል እና በመቋቋም ረገድ የታየው መንግስታዊ የአፈፃጸም ስኬት በተስፋ
እንድንሞላ ያደረገንን ያህል፤ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የተመለከትነው የጸጥታ መደፍረስ አሳስቦናል፡፡ አጠቃላይ ስርዓቱን ለቀውስ
የሚዳርግ ችግር ሆኖ በመታየቱ በስጋት ተወጥረን ቆይተናል፡፡ ድርቁ ሰብአዊ ቀውስ ሳያስከትል መቋቋም መቻላችን ኢትዮጵያ ምን ያህል
እንደተለወጠች ያመለከተ ክስተት ሆኖ ሲያልፍ፤ ሁከቱ ደግሞ ሐገሪቱ ገና ብዙ መለወጥ እንደሚቀራት አሳይቶናል፡፡ አንዱ የስርዓቱን
ሁለንታዊ ጥንካሬ ሲገልጽ፤ ሌላው ብዙ መሠረታዊ ድክመቶች መኖራቸውን ተናግሯል፡፡ አንዱ የስርዓቱ ተስፋ፤ ሌላው ለስርዓቱ ዳፋ ሲሆን
በውል አይተናል፡፡ አሁንም እሣት እና አበባ ከፊታችን አለ፡፡ አሳሳቢው እሣቱ ነው፡፡ ይህ እሣት ህገ መንግስቱን አመድ ሊያደርገው
ዙሪያ - ዙሪያውን ይንቀለቀላል፡፡ ይህ በእጅጉ ያሳስባል፡፡
ህገ መንግስቱን የሁከት እሣት ከበላው ባዶ እጅ እንቀራለን፡፡
ግራ እንጋባለን፡፡ መታፈር የጀመረችውን ኢትዮጵያ እናዋርዳታለን፡፡ የጠላቶቻችን መጫወቻ እንሆናለን፡፡ ሰላም እናጣለን፡፡ ሐገር
እናፈርሳለን፡፡ እርስ በእርስ እንተላለቃለን፡፡ የዓለም ህዝብ፤ ‹‹ኢትዮጵያውያን ያገኙትን መልካም ዕድል ያስቀጥሉታል ወይስ ተመልሰው
ከመጥፎ አዙሪታቸው ጥለው ያበላሹታል?›› ብሎ በአንክሮ ይመለከተናል፡፡ የልማት ጉዞአቸው ይቀጥላል ወይስ ተሰናክሎ ይቀራል? እያለ
በትዝብት ያስተውለናል፡፡ የተስፋ አበባቸውን ረግጠው፤ ህገ መንግስታቸውን በአመጽ እሣት አቃጥለው፤ በሐገራቸው ሁከት አንግሰው ወደተለመደ
ትርምሳቸው ይገቡ ይሆን? እያለ ሲያየን ይውላል፡፡
ኢትዮጵያውያን እርምጃቸውን በእጃቸው በያዙት ህገ መንግስት
እየለኩ ካልተራመዱ የምንፈራው ይደርሳል፡፡ ሆኖም በቃል ኪዳን ሰነዳቸው (በህገ መንግስታቸው) ያሰፈሩትን ነገር ተከትለው ከተራመዱ
መንገዳቸው ይቃናል፡፡ አሁን የያዝነው ህገ መንግስት የአንድ ቡድን ህገ መንግስት አይደለም፡፡ ይህ ህገ መንግስት፤ አሟልተው የማይቀበሉትን
ወገኖች እንኳን በልበ ሰፊነት የሚቀበል ህገ መንግስት ነው፡፡ ይህ ህገ መንግስት የደጋፊዎቹ ብቻ ሳይሆን፤ የተቃዋሚዎቹም ነው፡፡
ህገ መንግስቱ መለወጥ አለበት ብለው የሚያስቡ ሰዎች ህገ መንግስት ጭምር ነው፡፡
ስለዚህ ኢትዮጵያውን መንገዳቸው ሁሉ በህገ መንግስቱ በኩል መሆን አለበት፡፡ ይህ ህገ መንግስት የተቃዋሚዎቹም የደጋፊዎቹም ነው፡፡ ስለሆነም፤ አሁን ጸንቶ
ያለውን ስርዓት የሚቃወሙ ወይም እንዲለወጥ የሚፈልጉ ሰዎች ጭምር ይህን ህገ መንግስት መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ህገ መንግስት
የሰው ህይወት ሳይጠፋ፤ ንብረት እና ሐብት ለውድመት ሳይዳረግ በሰላማዊ ጎዳና ዓላማን ማሳካት የሚያስችል መሣሪያ ነው፡፡
ህገ መንግስቱ የሰላማችን ካስማ ነው፡፡ ከፋም - ለማም ልማት
ማምጣት ያስቻለ ሰነድ ነው፡፡ የሰላማችን እና ሁሉንም አርኪ ከሆነ ደረጃ ያልደረሰው ልማታችን ምንጭ እርሱ ነው፡፡ አንዳንዶች፤
የልማቱ ምንጭ ‹‹ትክክለኛ ፖሊሲ፣ ምቹ ዓለማዊ ሁኔታ፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ያልተማከለ አስተዳደር›› ወዘተ ሊሉ ይችላሉ፡፡
ጉዳዩን ከዚህ አኳያ ለማየት የጀመረ ሰው፤ ከተጠቀሱት ነገሮች በተጨማሪ ብዙ ዝርዝር ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ሆኖም ነገሩ ያለ ሐተታ
በአንድ ቃል ሊገለጽ የሚችል ነው፡፡ ይህ ቃል ከዓለም ህዝቦች አንደበት የማይጠፋ፤ የደፈረሰ ህሊናን የሚያጠራ፤ የሁሉም በጎ ነገሮች
ምንጭ የሆነ ክቡር ቃል ነው፡፡ ለፍጥረታት ሁሉ አለኝታ እና መከታ የሆነ የሦስት ሆሄያት ስሪት ነው፡፡ ይህ ንዑድ -ክቡር ቃል ‹‹ሰላም›› ነው፡፡ ሁሉንም አርኪ ከመሆን ደረጃ ያልደረሰው ልማታችን ምስጢር ‹‹ሰላም›› ነው፡፡ የሰላሙ ምንጭ ደግሞ ህገ መንግስታችን ነው፡፡
ትናንት እንደ ጠላት የሸሸን፤ ዛሬ ደግሞ በጸጋው የሚባርከን፣
ነገንም በተስፋ አሻግሮ እያሳየ በፍቅር የሚያሳድረን ሰላም ነው፡፡ በእጅ ያለ ወርቅን ከመዳብ የመቁጠር መጥፎ ሰብኣዊ ዝንጋኤ፤
ሁል ጊዜ የሰላም እና የጤንነትን ዋጋ አሳንሶ ያሳያል፡፡ አረቦች፤ ‹‹ጤንነት ስውር ዘውድ ናት›› ይላሉ፡፡ የጦርነትን ገፈት ለምዕተ
ዓመታት እስኪያንገሸግሻቸው የተጋቱ ኢትዮጵያውያን ደግሞ፤ ‹‹ሰላም ስውር ዙፋን ነች ይላሉ›› ማለት ይኖርባቸዋል፡፡ ‹‹ሰላም ስውር
ዙፋን ናት፡፡›› የሰው ልጆችን ሁሉ የክብር በትረ ሙሴ አስጨብጣ የምታነግስ ሰላም ናት፡፡ ይሁንና፤ ነገሩ ‹‹ሰው ካልሄደ ወይም
ካልሞተ አይመሰገንም›› እንዲሉ ሆኖ፤ አንዳንዴ የሰላም ዋጋ የሚታወቀን፤ ከእኛ ርቃ በሄደች ወይም በሞተች ጊዜ ነው፡፡ ‹‹ሰላም
ካልሄደች ወይም ካልሞተች አትመሰገንም፡፡›› ዋጋዋ አይታወቅም›› ፡፡
አበው ‹‹ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ›› ይላሉ፡፡ እኔም
‹‹ሰላም ካለ በሰማይ መንገድ አለ›› እያልኩ ነው፡፡ እውነተኛ የሰው ልጆች ገንዘቦች ሰላም እና ጤንነት ናቸው፡፡ በዚሁ አገባብ
‹‹ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ›› የመባሉ ምስጢር ‹‹ሰላም ካለ በሰማይ መንገድ አለ›› በሚል አንድምታ መሆኑን መናገር ይቻላል፡፡
አሁን በእጃችን የያዝነው ሰላም ዋጋው ዝቅ ብሎ ታይቶናል፡፡ አሁን የሰላም ዋጋ ብቻ ሳይሆን የሰላሙ ምንጭ ምን እንደሆነ ጠፍቶብናል፡፡
የሰላማችን ምንጭ ህገ መንግስቱ ነው፡፡ የልማታችን ምንጩ ሰላም ነው፡፡ ስለዚህ የልማታችን ምንጭ ህገ መንግስቱ ነው፡፡ የሰላማችን
ምንጭ ህገ መንግስቱ ነው፡፡
ስለዚህ ህገ መንግስቱ ከመካከላችን ሲጠፋ፤ እኛንም ይዞ ይጠፋል፡፡
አሁን ይህ እውነት ተሰውሮብናል፡፡ አሁን የቆምነው በህገ መንግስቱ መሠረት ነው፡፡ ብንጣላም ብንዋደድም እስካሁን አንድ አድርጎ
በሰላም ያኖረን ህገ መንግስቱ ነው፡፡ በፖለቲካ ስሌት ከታሰበ፣ አሁን ያለን የጋራ ነገር ህገ መንግስት ብቻ ነው፡፡ በዚህች ሐገር
ምንም ዓይነት ጥያቄ ወይም ቅሬታ አለኝ የሚል ዜጋ፤ ጥያቄው ሊመለስ እና ቅሬታው ሊቀረፍ የሚችለው የጸና ስርዓት ሲኖር ብቻ ነው፡፡
በአሁኑ ተጨባጭ የሐገራችን ሁኔታ የጸና ስርዓት ሊገኝ የሚችለው በህገ መንግስቱ ብቻ ነው፡፡ ሁላችንም ይህን ነገር መነሻ አድርገን
መውሰድ አለብን፡፡
ይህ ህገ መንግስት፤ ቀደም ሲል ሐገሪቱን የጦርነት አውድማ
ሊያደርጓት የሚችሉ የታጠቁ ኃይሎችን ወደ ሰላም ጠረጴዛ በመጥራት ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል ማድረግ የሚችሉበትን ሁኔታ አመቻችቷል፡፡
የብሔር ጥያቄ ያነሱ ኃይሎችን ፍላጎት በማክበር እና የመረጋጋትን መንፈስን በመፍጠር፤ የመገንጥል ጥያቄ ላነሱ ወገኖች የሚያረካ
ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ በቋንቋቸው የመጠቀም (የመዳኘት እና የመማር)
እንዲሁም ባህል እና ታሪካቸውን የማሳደግ መብት አጎናጽፎአቸዋል፡፡ በዚህ ዓይነት በወቅቱ የተፈጠረውን የፖለቲካ ውጥረት አርግቧል፡፡
ሆኖም ዕድሜ የፈቀደልን ዜጎች እንደምናስታውሰው፤ ኢህአዴግ
የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መብት እንዲከበር ሲያደርግ እና ለዚህ የተመቸ የፖለቲካ ስርዓት እንዲፈጠር ሲያደርግ፤ በቀላል
ቁጥር የማይገመቱ ኢትዮጵያውያን ጥረቱን ሐገር የማፈራረስ ፕሮጀክት አድርገው ይመለከቱት ነበር፡፡ አሁንም ተመሳሳይ ስሜት ያላቸው
ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ይህ ስሜት የመጥፋት አዝማሚያ ሲከተል ቆይቶ፤ አሁን (እንደ ድሮው የሴራ ትንታኔ ያለው አቀራረብ የተከተለ ባይሆንም)
የተለየ ቅርጽ እና ይዘት ይዞ ብቅ ማለት ጀምሯል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሚታዩ መጥፎ አዝማሚያዎች በተጨማሪ፤ በተለይ በዩኒቨርሲቲ
ተማሪዎች ዘንድ በሰፊው የሚታዩ አንዳንድ ባህርያትን እና የተለያዩ የማህበራዊ ኑሮ አጋጣሚዎችን በመጥቀስ ስርዓቱ አደጋን ያረገዘ
ስርዓት መሆኑን የሚናገሩ ሰዎች ዳግም እየተበራከቱ የመጡበት ሁኔታ ያለ ይመስለኛል፡፡
እዚህ ላይ መነሻ መደረግ የሚገባው አንድ ነገር አለ፡፡ ዴሞክራሲ ተኝተው የሚያድሩበት
ሥርዓት አይደለም፡፡ ሁሌም ነቅቶ መኖርን የሚጠይቅ ስርዓት ነው፡፡ የተለያዩ ጥቅሞች ዘወትር የሚሻኮቱበት ስርዓት ነው፡፡ በተመሳሳይ፤
ፌደራሊዝም ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል ምቹ ሁኔታን የያዘ ስርዓት እንጂ፤ ግጭት የማይፈጠርበት ስርዓት አይደለም፡፡
ሆኖም ጦርነት የመግጠም እንጂ የተለያዩ ፍላጎቶችን የማገጣጠም ብዙ ልምድ ለሌለው እንደኛ ያለ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፌደራላዊ ስርዓቱ
ማደናገሩ የማይቀር ነው፡፡
በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሁልጊዜ ከተለያየ ጥግ የሚመጣ ጉንተላ ይኖራል፡፡ ዴሞክራሲ
እረፍት የሚነሳ የክፉ ጎረቤት ዓመል አለው፡፡ በዴሞክራሲ ላይ ፌደራሊዝም፤ በፌዴራሊዝም ላይ የብሔር ጉዳዮች ሲጨመሩ ይከብደናል፡፡
ፈተናውን ማለፍም ይጠበቅብናል፡፡ ለኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም የሰላም አማራጭ ነው፡፡ ሆኖም፤ ፌደራሊዝም የግጭት መፍቻ ያለው ስርዓት እንጂ ግጭት አስወጋጅ ስርዓት አይደለም፡፡
በኢትዮጵያ ግጭቶች የብሔር መልክ የመያዝ ሰፊ ዕድል ይኖራቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ
የብሔር ማንነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ አደረጃጀት የሚያሰጋቸው ሰዎች እውነት አላቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች የሚያቀርቡትን አስተያየትም፤
ከጠቅላይ ግዛት የፖለቲካ ዝንባሌ ጋር ብቻ አያይዞ ማየት ተገቢ አይሆንም፡፡ ስለዚህ በብሔር ፖለቲካ ላይ ጥርጥሬ ያላቸውን ሰዎች
አቋም ከጠቅላይ ግዛት የፖለቲካ ዝንባሌ ጋር ብቻ ማያያዝ አይቻልም፡፡ በዚሁ ሚዛን፤ የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦችን መብት ለመቀበል መወሰንን ሐገር ከማፍረስ ጋር ማያያዝ ትክክል አይሆንም፡፡
ዛሬ ታላቁ መምህር ኑሮ፤ በዕድሜ ፊደል እና በታሪክ ክርታስ አስተምሮኝ
የሐሳብ ለውጥ አደረግሁ እንጂ፤ የእኔም የአስተሳሰብ ጎጆ ዛሬ ‹‹አስገራሚ›› ብዬ በምፈርጀው የአቋም ቅጽር ውስጥ የቆመ ነበር፡፡
ቀደም ሲል፤ ከኢህአዴግ እና ከደርግ ለኢትዮጵያ አንድነት የታገለው ማንኛው ነው?›› የሚል ጥያቄ ቢቀርብልኝ፤ ለአፍታም ሳላመነታ
‹‹ደርግ ነዋ!›› የምል ሰው እንደ ነበርኩ አውቃለሁ፡፡ አሁን እንደዚያ ሆኖ አይታየኝም፡፡
እዚህ ላይ፤ ነገሩን ከጥንተ ጉዳዩ ጀምሬ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ኢህአዴግ
አዲስ አበባ ከመግባቱ ከአንድ ወር በፊት፤ ምናልባትም ሚያዚያ 14፣ 1983 ዓ.ም ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማርያም የተናገሩትን
አንድ ነገር ማስታወስ ይቻላል፡፡ የሐገር አንድነትን ለማስከበር መቆማቸውን የሚያምኑት እና ብዙዎችም በዚሁ ዓይን የሚያዩዋቸው ኮሎኔል
መንግስቱ ከሸንጎው ፊት ተቀምጠው እንደሚከተለው ተናግረው ነበር፡፡
‹‹ጓዶች ተፈተንን፣
ተቸገርን፤….ልጄ ውትድርና ሄደብኝ፣ መሬቴ ተቀማብኝ ያለ አማራ ጫካ ግብቷል፡፡ ትግሬ ድሮም ሽፍታ ነበር፡፡ ሸፍቷል፡፡ ኦሮሞ ነጸ
ካልወጣሁ እያለ እየወጋን ነው፡፡ አፋር ብረት አንስቶ ለነጻነቴ እታገላለሁ ይላል፡፡ ዛሬ እኮ ይህን መንግስት የሚወጉ ነጻ አውጪ
ነን የሚሉ ድርጅቶች ወደ አርባ ተጠግተዋል፡፡ ማንን ነው ከማን ነጻ የሚያወጡት? እዚህ ውስጥ ኦሮሞ የለም፤ አማራ የለም፤ ትግሬ
የለም? ይህን ምን እንደምናደርግ ነው ግራ የገባን?›› ብለው ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ አደባባይ
በወጣ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ተውጠው፡፡
በወቅቱ የኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ የነበረውን የኃይል አሰላለፍ ሲገልፁ፤
‹‹በአንድ ወገን፤ የሐገራችሁን ህዝብ አንድነት፣ ዕድገት እና ብልጽግና
በደማችሁ የምትዋጁ፤ አጥንታችሁን የምትከሰክሱ፤ መተኪያ የሌላት ህይወታችሁን የምትሰዉ፤ እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች እና ጀግኖች፡፡
በሌላ ወገን፤ ለወገናችሁ ሞት፣ ስቃይ እና ስደት በአንደበታችሁ የምትመርዙ፣ በብዕራችሁ የምትደልዙ፣ በጠብመንጃ አፈሙዝ የምትገዘግዙ፤
እንዲሁም ራሳችሁን ብቻ ሳይሆን የወለዷችሁን እናት እና አባቶቻችሁን ጭምር የካዳችሁ፤ የዘመኑ የኢትዮጵያ እንቆቅልሾች……›› ብለው ነበር፡፡
ኮሎኔሉ፤ የብሔር፣ የብሔረሰቦች እና ህዝቦች መብት መከበር አለበት የሚል
አቋም የያዙትን ‹‹የኢትዮጵያ እንቆቅልሾች›› ወይም ‹‹ከሃዲዎች››፤
በተቃራኒው በኃይል የሐገሪቱን አንድነት እናፀናለን የሚል አቋም የሚያራምዱትን ‹‹እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች-ጀግኖች›› አድርጎ ይፈርጃሉ፡፡ ይህም መንግስታቸው ጨርሶ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል
ቁመና እንዳልነበረው ያመለክታል፡፡
የብሔር፣ የብሔረሰቦች እና ህዝቦች መብት መከበር አለበት ብሎ የሚጠይቅ
ወገን ሲመጣ፤ ‹‹ምን አልክ አንተ ጎሰኛ?! አሁን ከዚህ ግድም አትሄድም!›› እያለ ሐገሪቱን በሁሉም አቅጣጫ የጦር አውድማ ያደረገው
ያ መንግስት፤ የኃይል አንድነት መፈክሩን እንደያዘ ከመንበሩ ተፈነገለ፡፡ የተከተለው ጎዳና የሐገሪቱን ሰላም አደፍርሶ አንድነቷን
ለባሰ አደጋ እንዲጋለጥ አደረገ እንጂ የፈጠረው ለውጥ አልነበረም፡፡
ደርግ በጦርነት ከተሸነፈ በኋላ ሐገሪቱን የተቆጣጠረው ኢህአዴግ የብሔር፣
የብሔረሰቦች እና ህዝቦች መብት እውቅና እንዲያገኝ ማድረጉ፤ ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ ነጻ መንግስት ከመመስረት ውጪ ሌላ አማራጭ መኖሩን
ለማየት ፈቃደኛ ያልሆኑ ወገኖች ትንሽ እንዲረጋጉ እና የህዝቦችን ዘላቂ ጥቅም ከማረጋግጥ አንጻር መተኪያ የሌለውን፤ (በኢህአዴግ
አገላለጽ) ‹‹የዴሞክራሲያዊ አንድነት›› አማራጭን ለመሞከር ዝግጁ እንዲሆኑ ለማድረግ አስችሏል ብዬ አስባለሁ፡፡
በወቅቱ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የተጋረጠውን
አደጋ ገለል ለማድረግ የሚያስችል ሌላ አማራጭ ያለ አልመሰለኝም፡፡ ለሐገር አንድነት ቆምኩ የሚለው መንግስት ‹‹ለዘማች አሞራ››
ጥሎት የሄደውን የሐገር አንድነት ጉዳይ፤ ከእሳት አውጥቶ በክብር ለማኖር በኢህአዴግ ከቀረበው አማራጭ የተሻለ ሌላ መንገድ ሊታየኝ
አልቻለም፡፡ ይህን ሳስብ የደርግ መንግስት ለአንድነት የቆመ መስሎ መታየቱ አስገራሚ ይሆንብኛል፡፡ የደርግ መንግስት በዚሁ መልክ
የመታየት ሰፊ ዕድል ማግኘቱ ይደንቀኛል፡፡ ፕሮጅክቱ ገና አልተጠናቀቀም እንጂ አሁን-አሁን ከደርግ ይልቅ ኢህአዴግ ለአንድነት ታግሏል
ለማለት እየዳዳኝ ነው፡፡ በርግጥ፤ ደርግ እና ኢህአዴግ ስለኢትዮጵያ አንድነት የሚናገሩትን የሰማ ሰው፤ ኢህአዴግ ለሐገር አንድነት
ደንታ የሌለው ድርጅት መስሎ ሊታየው እንደሚችል አልጠራጠርም፡፡ ነገሩን በገጽታው ብቻ የተመለከተ ሰው ከዚህ የተለየ አቋም ሊይዝ
አይችልም፡፡
እንዲያውም የአንዳንድ ሰዎችን የነገር አያያዝ ስመለከት፤ የኢትዮጵያ ብሔር፣
ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በኢህአዴግ የተፈጠሩ መስሎ እየተሰማቸው የሚናገሩ ይመስለኛል፡፡ ለነገሩ እንደዚያ ዓይነት ስሜት መያዛቸው
ሊያስገርም አይገባም፡፡ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በፖለቲካ ሐቲቱ (Political Discourse) ‹‹የዘወትር ጸሎት›› ሆኖ ብቅ ያለው ኢህአዴግ ከመጣ ወዲህ በመሆኑ፤ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በኢህአዴግ
የተፈጠሩ መስሎ ቢታየን አስገራሚ አይሆንም፡፡
ይሁንና ደርግ ዋና የፖለቲካ ፕሮግራሙ ትኩረት አድርጎ ባይዘውም፤ እከተለዋለሁ
ይል በነበረው ሶሻሊስታዊ መርህ መነሻ፤ ወይም በኢትዮጵያ ተማሪዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ግፊት (አለያም በሁለቱም ጣምራ ስበት)፤
ለብሔር - ብሔረሰቦች ጉዳይ ‹‹ከሥራ ሰዓት ውጪ›› የሆነ ትኩረት
መስጠቱ ግልጽ ነው፡፡ ቢያንስ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጥናት ተቋም›› የተባለ መንግስታዊ መሥሪያ ቤት እንዲቋቋም አድርጎ ነበር፡፡
ሆኖም ደርግ የቡድንም ሆነ የግለሰብ መብቶችን ለማክበር የሚችል ወይም የማክበር ፈቃደኝነት ያለው መንግስት አልነበረም፡፡ ስለዚህ
የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ለማስከበር ያደረገው ጥረት አልነበረም፡፡
የደርግን ነገር ትተን፤ ‹‹ለመሆኑ ቡድን የሚባለው ነገር ምንድነው?››
የሚል ጥያቄ እናንሳ፡፡ ቡድን በበርካታ በግለሰቦች ስብስብ የሚፈጠር ነገር ነው፡፡ ቡድኖቹም በማህበር የተደራጁ ወይም ያልተደራጁ
ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ቡድኖች በፍላጎት፣ በመጠን (Size) እና በአደረጃጀት ይለያያሉ፡፡
በውስጣቸውም በርካታ ንዑስ ቡድኖችን ወይም አንጃዎችን ሊይዙ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶች እነዚህ ቡድኖች የመብት ባለቤቶች መሆናቸውን
ሲቀበሉ፤ ሌሎች ‹‹የቡድን መብት የሚባል ነገር የለም›› ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ስለዚህ የቡድን መብትን ለመቀበል ይቸገራሉ፡፡
ሆኖም ሰዎች ሰው በመሆናቸው ብቻ ሊከበሩላቸው የሚገቡ መብቶች መኖራቸውን
ሁሉም ወገን ይቀበላል፡፡ ሰዎች ሰው በመሆናቸው የሚኖራቸው መብት የሰብአዊ ወይም ተፈጥሮአዊ በሚል ሲጠቀሱ፤ ሰዎች እንደ ዜጋ የሚኖራቸው
መብቶች ደግሞ ‹‹የሲቪል መብቶች›› ይባላሉ፡፡ የሰዎችን ሰብአዊ እና የሲቪል መብቶች በተመለከተ ልዩነት ባይኖርም፤ አክራሪ የግለሰብ
መብት አቀንቃኞች (Liberal Individualists) ሰዎች የዚህ ወይም
የዚያ ቡድን አባል በመሆን የሚያገኙትን ‹‹የቡድን መብት›› ለመቀበል አይፈልጉም፡፡ እንዲያውም በመብት ስም፤ መብቶች እንዲጣሱ
ያደርጋል በሚል የቡድን መብት መከበርን ይቃወማሉ፡፡ ፍትሐዊ ተደርጎ የሚታሰብ ኢ-ፍትሓዊ ተግባር ለመፈጸም መንገድ ይከፍታል፤ በሰዎች
መካከል ልዩነትን ማድረግን ያስከትላል ይላሉ፡፡ መብቶች የጭቆና መከላከያ ጋሻዎች መሆናቸው ቀርቶ ልዩነት መፍጠሪያ ይሆናሉ በማለት
የቡድን መብት መከበርን ይነቅፋሉ፡፡
ሆኖም ‹‹ኢትየጵያ የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች እስር ቤት ሆና ቆይታለች››
ብሎ የሚያምነው ኢህአዴግ የሚያቀርበው የታሪክ ትንታኔ ትክክል ሆኖ ታይቶኝ ባያውቅም፤ ‹‹ወደድክም ጠላህም በኢትዮጵያ አንድነት
ሥር ትኖራለህ›› የሚል አቋም የተሳሳተ መሆኑን ሲናገር ትክክል መሆኑን መቀበሉ ከብዶኝ አያውቅም፡፡ ይህን አቋሙን ሐገር ከማፍረስ
ዓላማ ጋር የሚያያይዙት ወገኖችም የተሳሳቱ ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ ትልቅ ጥያቄ አድርጎ ከፊታችን የደቀነውን ይህን
ጥያቄ ለመመለስ ደፋር ውሳኔ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን አንድነት ለማስቀጠል የሚያስችል ደፋር አማራጭ መውሰዱን አደንቃለሁ፡፡
ስለዚህ ኢህአዴግ ታሪክ ከፊታችን የደቀነውን ከባድ እና ወሳኝ ጥያቄ መልሷል፡፡ አሁን ሌላ ጥያቄ ከፊታችን ተደቅኗል፡፡ ይህንም
ጥያቄ መመለስ ይኖርብናል፡፡ የሰላም እና የብልጽግና ዘመን ይሁንልን፡፡
No comments:
Post a Comment