Friday, 9 September 2016

ተግባራዊ ምላሽ!!




                                                     ታከለ አለሙ
                                                                                                                      ሀገራችን ከድህነትና ከኋላቀርነት  ለመውጣት ሰፊና እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ የተጓዘችውን ያህል ብትራመድም ዛሬም ገና  ብዙ ትግል፣ ፈተናና ውጣ ውረድ ይጠብቃታል፡፡ ብዙ መድከም፣ መሥራትና መልፋት ግድ ይላል፡፡ በእርግጥም ባለፉት 25 ዓመታት ታላላቅ የሆኑ ሀገራዊ ፋይዳቸው የጎላ የኢኮኖሚና መሠረተ ልማት ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ ባለው ላይ ለመጨመር የህዝቡን ችግር ፈጥኖ በመቅረፍም ረገድ ከመንግሥትም ሆነ ከድርጅቱ የበለጠ ተግባራዊ ምላሽ ይጠበቃል፡፡
በሚነሳ የህዝብ ተቃውሞና አመጽ ለህዝብና ለሀገር የሚጠቅሙ ንብረቶችን የግለሰብም ይሁን  የመንግሥት ማቃጠል፣ በእሣት ማጋየት፣ ማውደምና ማፈራረስ ከሁሉ በላይ የሚጎዳው ራሱን የአካባቢውን ነዋሪ ህዝብ ነው፡፡ ተቃውሞን በህጋዊ መንገድ ማቅረብና ማሰማት ይቻላል፡፡ ነገም ከነገ ወዲያም ወደፊትም የሚጠቅመውን ንብረት ማውድም ለህዝብም ለሀገርም አለማሰብ ነው፡፡ ዘግናኝ ድርጊትም ነው፡፡
ያንን የወደመ ንብረት ለመተካት ምን ያህል ጊዜ ልፋትና ድካም እንደሚጠይቅ መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ከንብረቱም በላይ በህጉና በሥርዓቱ ሊመለሱ የሚገባቸው ጥያቄዎች ከመንገድ ወጥተው ክቡሩን ሰው ህይወት አስከፍለዋል፡፡ ንብረቱ ሊተካ ሊሰራ ይችላል፡፡ የማይተካው የወደቀው የሰው ህይወት ነው፡፡ አሳዛኙም ይኼ ነው፡፡
በየአካባቢው በተጀመረው ግንባታ በነበረውም ላይ መጨመር ሲገባ ያለውን ማውደም የአካባቢውን ህዝብ ክልሉን ምን ያህል በዕድገትና በልማት ወደኋላ እንደሚመልሰው አጠያያቂ አይደለም፡፡ መንግሥት መጣ መንግሥት ሄደ የሀገር፣ የህዝብና የግለሰብም ንብረት ሀብት ቢሆን ሊጠብቀው የሚገባው ህዝቡ ነው፡፡ ነገም ተመልሶ የሚያገለግለው ህዝቡን ነውና፡፡
አንዳንዶች የህዝብ ተቃውሞና ቁጣ መልስ ሳይሰጠው ሲቀር እንዲህ ዓይነት ግብታዊና ስሜታዊ ርምጃዎችን ይወስዳል፤ በሥርዓቱ መቆጣጠርም አይቻልም የሚል መከራከሪያ ያሰማሉ፡፡ ይህ ክስተት በሌሎች ሀገራትም ሲታይ የኖረና ያለ ቢሆንም ሀብትና ንብረት ማውደም መልሶ የሚጎዳው ራሱን ኅብረተሰቡን ነው፡፡ ጠቀሜታ የለውም፡፡ ከቀደሙት ጊዜያትም ከሌሎች ሀገራትም ጥፋትና ውድመት ውድቀትም መማር ይገባል፡፡
በሁሉም አቅጣጫ ቀድሞ ያልነበሩ ለሀገሪቷ አዳዲስ የሆኑ ህዝብን ማዕከልና ተጠቃሚ ያደረጉ በስኬት የታጀቡ ሥራዎች በጤናው፣ በትምህርት፣ በከተማና መንገድ ግንባታው፣   በኢንቨስትመንት፣ በግብርናው፣ በግድብ ግንባታው፣ በኮንዶሚኒየም ወዘተ…መስኮች ይህ ቀረው የማይባል ዓለምን ያስደመመ ዕድገትና ለውጥ ተመዝግቧል፡፡ እየተሰራም ነው፡፡ መሠረታዊው የህዝብ ጥያቄና ችግር ትኩረትና ቅድሚያ ተሰጥቶት ጎን ለጎን ቢፈታ ኖሮ አሁን የተፈጠረው ቀውስ ላይከሰት ይችል ነበር፡፡
ትልቁና ዋናው ኅብረተሰቡን ያማረረው ችግር የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህ እጦት፣ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የሙስናና የመሬት ቅርምት ዘረፋ በመንግሥት ወንበር ተቀምጠው  የግል ጥቅማቸውን ሲያሳድዱና ሲዘርፉ የነበሩ ግለሰቦች የሚፈጽሙት ዓይን አውጣ ህገ ወጥ ድርጊትና ሌሎችም እየተባባሱ በመሄዳቸው መንግሥትም ሆነ ኢህአዴግ ወቅታዊ ርምጃ ለመውሰድ ባለመቻሉ የተፈጠረ ለመሆኑ ሁሉም ወገን ይስማማል፡፡
ይህንን በህዝቡ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለመጠቀም የሚጥሩ የሚሞክሩ በተገኘው ቀዳዳ ውስጥ በመግባት አድማሱን ለማስፋት የሚንቀሳቀሱ የውጭ ኃይሎች እጅ እንደሚኖር ይታወቃል፡፡ ቁልፉ ጉዳይ የጥያቄው ባለቤት ህዝቡ እንጂ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የመሩትና ያስተባበሩት አይደለም፡፡ ህዝቡም አትግቡብን ጉዳዩ የእኛ ነው ያቀረብነው ህጋዊና ሠላማዊ ጥያቄ ስለሆነ በህጉ መሠረት ምላሽ ሊሰጠን ይገባል ሲል በተደጋጋሚ በተለያዩ አጋጣሚዎች ገልጿል፡፡
እያደገ የመጣው ኅብረተሰብ በትምህርትም በብስለትም ደረጃ ከፍታን ያሳየ በመሆኑ አዳዲስ ጥያቄዎችን ማንሳቱ ተገቢና የሚጠበቅም ነው፡፡ ይህንን አዳጊ ኅብረተሰብና ተለዋዋጭ የዕድገት አቅጣጫዎች የሚመጥን አመራር ፈጥሮ በወቅቱ ለሚነሱት ማንኛቸውም የህዝብ ችግሮች ፈጣን መልስ ለመስጠት አለመቻሉ የአመራሩን ጉልህ ድክመት በገሀድ ያሳያል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ሲነሱ የነበሩ ተደጋጋሚ አይነታቸው የተለያየ ችግሮች ተደምረውና ተንከባለው አሁን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ቢፈጥሩም የሰው ህይወትና የንብረት መውደም ሳያስከትል በህጋዊና በሠላማዊ መንገድ መጠየቅና መፍትሄ እንዲያገኝም ከጥፋት ባሻገር ሠላማዊ ጫና መፍጠር ይቻል እንደነበር ኢህአዴግ ይገልጻል፡፡ ምን ዓይነት ሠላማዊ ጫና የሚለውም ያነጋግራል፡፡
በመንግሥት አመራሮች፣ ኃላፊዎችና አስተዳዳሪዎች በተለያዩ ከህዝቡ ጋር በሚያገናኙ  የመሬት፣ የቦታ፣ የማስተር ፕላን የካሣና ምትክ ወዘተ…ጉዳዮች ግልፅነትና ተጠያቂነት አለመኖር ጉዳዩን  ከህዝቡ ጋር አለመወያየት፣ ህዝቡን አለማዳመጥ፣ ከጀርባም የአንዳንድ ባለሀብቶችና በኃላፊነት የነበሩ ያሉ ሰዎች እጅና ግፊት መኖር ሁኔታውን እንዳወሳሰበው ትናንትም ህዝቡ ሲገልጽ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ላይ በመደጋገም የሚደመጡ እውነቶች ሆነዋል፡፡
በራሱ በመንግሥትና በድርጅቱ ውስጥ መንግሥታዊ ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማግኚያ አድርጎ የመመልከት አዝማሚያና ዝንባሌ እያደገ መምጣቱ በወቅቱ ሊታረም አለመቻሉ ችግሩን እያደር እያገዘፈው ሄዶ አሁን ያለውን ሁኔታ እስከመፍጠር ለመረማመድ መቻሉን  ሁሉም ወገን ይስማማበታል፡፡
ችግሩ የህዝቡ ሳይሆን  የመንግሥት አመራር ድክመትና ፈጥኖ ውሣኔ ለመስጠት ያለመቻል ነው፡፡ በአመራሩ በራሱ ውስጥ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ችግር ፈጣሪውና የኪራይ ሰብሳቢው ኃይል በውስጥ መሽጎ አላሰራና አላንቀሳቅስ ያለበት ፈታኝ ሁኔታም እንደነበር እውነት ነው፡፡ ይህ ሥር የሰደደ ችግር ህዝቡን ሲያማርር ህዝቡ ለመብቱ መከበር መታገሉ፣ ድምጽ ማሰማቱና ተቃውሞውን መግለጡ ተገቢ መሆኑን የድርጅቱ ግምገማ ይገልጻል፡፡
የእኛን ሀገር በመሰለ ታዳጊ ኢኮኖሚ ውስጥ የተሰሩ ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅሙ የመሠረተ ልማቶችን የግለሰቦችንም የህዝብንም ንብረት መጠበቅና መንከባከብ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የህዝቡም ግዴታ ነው፡፡ የሀገር ሀብትና ንዋይ ፈሶባቸው የተሰሩ ናቸው፡፡ ለዛሬውም ለቀጣዩም ትውልድ በተሸጋጋሪነት የሚጠቅሙ እየጨመርንባቸው መሄድ የበለጠ መገንባት የሚገባን እንጂ ሊጠፉና ሊወድሙ አይገባም፡፡
ተጎጂው ከማንም በላይ ህዝብ ነው የሚሆነው፡፡ በኦሮሚያም ሆነ በአማራውም ክልሎች በተከሰተው ተቃውሞ የበርካታ ዜጎች የወጣቱም የፀጥታ አስከባሪውም ህይወት አልፏል፡፡ ከፍተኛ ንብረት ወድሟል፡፡ በእጅጉም ያሳዝናል፡፡ በንግድና ቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡
በህዝቡ የእለት ተእለት ሠላማዊ ህይወትና መስተጋብር በትራንስፖርት እንቅስቃሴውም ላይ ጫናና ሥጋት ደቅኖም ነበር፡፡ ግብይቱ የታወከበት የፍርሀት ድባብ የሰፈነበት ስሜትም ፈጥሯል፡፡ ይህንን መልሶ ማረጋጋትና ወደ መደበኛው ሠላማዊ እንቅስቃሴ መመለስ የሚቻለው በራሱ በህዝቡ ተሳትፎ ብቻ ነው፡፡ የሀገሩ ባለቤት ወሣኙ ህዝብ ብቻ ነው፡፡
ህዝቡ ጥያቄዎቹ ፈጥነው እንዲመለሱለት ይፈልጋል፡፡ መፍጠን ያለበትም ገዢው ፓርቲ ነው፡፡ ለመፍጠንም ለይቶ ያስቀመጣቸውን መሠረታዊ ችግሮቹን መቅረፍ ይጠበቅበታል፡፡ የችግሩ አድማስና ተጽዕኖ በቀላሉ የሚሰላ አይደለም፡፡
ሥር ነቀል የተሀድሶው እንቅስቃሴ በበርካታ መስኮች ለሚያመጣው ለውጥ የህዝቡን ችግሮች በመሠረታዊነት ለመፍታት የተጀመረውንም ሀገራዊ ልማትና ዕድገት ወደላቀ ደረጃ ለማስፈንጠር እንደሚያስችለው ነባር አመራሮቹ  ሲናገሩ ተደምጧል፡፡
ከዚህ በፊት በርካታ ጊዜያት ህዝቡን ባስመረሩት ችግሮች ላይ ርምጃ እንደሚወስድ ኢህአዴግ ሲገልፅ የቆየ ቢሆንም ቃሉን ወደመሬት አውርዶ ለህዝቡ አላሳየውም የሚለው ሰፊ የህዝብ አስተያየት አሁን የታሰበው የተሀድሶ ለውጥ የምር ነው? እውነትስ ያደርጉታል? የሚል ጥያቄም ያነሳል፡፡ ለህዝቡ ጥያቄ ተግባራዊ ምላሽ መስጠት የሚጠበቀው ከኢህአዴግ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment