Tuesday, 13 September 2016

ጥልቁ ተሃድሶ በቁርጠኝነት ሊታጀብ ይገባል!



                                                                           
                                                  ዘአማን በላይ
እነሆ አዲስ ዓመት ሊጠባ በጣት የሚቆጠሩ ቀናቶች ብቻ ቀርቶታል። ባለፈው ዓመት ሀገራችን ውስጥ የተለያዩ ችግሮች ተከስተዋል። የችግሩ ደርዝም አነጋጋሪ ሆኗል። እዚህና እዚያ የተፈጠሩ ችግሮች አላፊውን ዓመት መለያው ያደረጉት ይመስላል። እናም መጪው አዲስ ዓመት ከአሮጌው ዓመት አላስፈላጊ ጉዳዮች ለመራቅ ቃል የሚገባበት፣ ለአዲስ ግብ የሚታለምበት ብሎም ነባሩን ዓላማና ዕቅድ የምናስቀጥልበት ሊሆን ይገባል። እናም በዚህ ፅሑፍ መንግስት የግለሰቦች ስብስብ እንደ መሆኑ መጠን፤ በአዲሱ ዓመት በቅድሚያ በግለሰብ ደረጃ ለጥቆ ደግሞ በመንግስት ደረጃ ምን ዓይነት ግብ እንደሚያዝና እንደምን ተፈፃሚ መሆን እንደሚገባው ላመላክት እሞክራለሁ።  
እርግጥ እስከ በዓሉ ዋዜማ የመጨረሻዋ ሰከንድ ድረስ “በአዲሱ ዓመት ይህን ከውናለሁ” የሚል ዕቅድ በበርካታ ግለሰቦች ህሊና ውስጥ መመላለሱ አይቀርም። ታዲያ ይህ የዕቅድ ተስፋ፣ ተስፋ ብቻ ሆኖ መቅረት የለበትም። በተስፋው ውስጥ የግለሰቡ ቁርጠኝነት መታከል ይኖርበታል። በአንፃሩም ከቁመት በላይ ተሰቅሎ የተንጠለጠለውን ዳቦ ለማውረድ ሊገኝ የማይችልና የሌለን መሰላል ማሰብ አያስፈልግም። መሰላሉ እርግጥም ሊደረስበት የሚችልና ወደ መሰላሉ የመውጣት አቅም መኖሩም በቅድሚያ መረጋገጥ አለበት። ስለሆነም ተስፋው ምናባዊ ብቻ እንዳይሆን ግለሰቡ ተፈፃሚ ሊሆን የሚችል ነገርን ብቻ ማሰብ ያለበት ይመስለኛል።
ለነገሩ ተስፋ የሌለው ሰው በነሲብ ካልሆነ በስተቀር በታቀደና በሚታወቅ ግብ ሊኖር አይችልም። አንዳንድ ግለሰቦች “ስለ ነገ አታስብ፣ ቀኑ ለራሱ ሲል ያስባል” የሚሉት የጨለመና ራዕይ አልባ አባባል፤ የህይወት ጭላንጭል ተስፋን እንኳን በውስጡ ያልያዘ ነው። ከዚህ ባሻገርም የግለሰቦችን የ“ነገ“ ቀን “ህልም” የሌለው እንዲሆን የሚያደርግና “የነገ ሰውነትን” የሚያሳጣ ነው። ሰው በባህሪው ዛሬ ምሽት ወደ መኝታው ሲሄድ፣ ነገ የሚባል ቀንን ለማየት በውስጡ ተስፋን ሰንቆ ነው። ነገን በአዲስ ህይወት፣ በአዲስ የመኖር ጉጉት፣ በአዲስ ልማታዊ ትልምና ሰላም፣ በአዲስ ቀንነት በመናፈቅ። አዎ! ነገን አለመኖር በሰው ልጅ ሰብዓዊ ባህሪ ውስጥ በእንጥፍጣፊነት የሌለ የኑባሬው ዓለም ዕውነታ አንድ አንጓ ነው። ለነገ የማያስብ፣ ነገን በዛሬ ውስጥ የማያልም፣ የህይወትን ጣፋጭ ገፅታ አጮልቆ የማያይ እንዲሁም ነገን ሲያስብ ውስጡ በሐሴትና በፍሰሐ የማይሞላ ከቶ ማን ይኖር ይሆን?...አበው “የነገ ሰው ይበለን” የሚሉት ለዚህ ይመስለኛል።
ነገን “ማለም” ዛሬን በተስፋ ውስጥ ሆነን እንድንኖር ያደርገናል። ይሁንና “ህልሙ” በገሃዱ ዓለም ውስጥ ያለን ዕውነታ የሚያመላክት፣ ከወዲሁ የሚታይና የሚዳሰስ እንጂ፤ በህልምነቱ የምናውቀውን የማታውን ዓይነት እውነተኛ የጨለምተኞች እሳቤ መሆን የለበትም። በግለሰብ ደረጃ ስለ ነገ የምናስበው አዲስ “ህልም” በጨለምተኞች መደብዘዝ አይኖርበትም። “እዮሃ አበባዬ፣ መስከረም ጠባዬ” ተብሎ አዲሱን ዓመት “የከርሞ ሰው ይበለን” ብለን ስንቀበል፤ በግለሰብ ደረጃ የምናቅደው አዲሱ “ህልማችን” የሚደረስበትና ሰላማዊ እንዲሁም በአሮጌው ዓመት ያለፍናቸውን ችግሮቻችንን አሽቀንጥረን የምንጥልበት መሆን አለበት።  
ሰላማዊ ያልሆነና የህይወት መስመራችንን የሚያዘበራርቅ “ህልም” ቅዠቱ አያስተኛም። ውስጣዊ ቀውስንና ጥፋትን እንጂ ዕድገትንና ብልፅግናን አያመጣም። በመሆኑም በ2009 ዓ.ም የምናልመው “ህልም” ልኬቱና ስኬቱ ሰላማዊና ሰላማዊ መሆን ይኖርበታል። እንደ ግለሰብ በፖለቲካው፣ በማህበራዊውም ይሁን በምጣኔ-ሀብቱ መስክ የሚታሰቡ ጉዳዮች የስኬት ልኬታቸው የነገ ሰው የመሆን ህልምን ማንፀባረቅ ይኖርባቸዋል።
“ወደፊት የማይሄድ፣ ወደ ኋላ እየተራመደ ነው” እንዲሉ፤ በ2008 ዓ.ም ከነበርንበት የተመሰቃቀለ ቦታ በአዲሱ ዓመት ወደ ሰላማዊ ንፍቀ-ክበብ ፈቀቅ ማለት ይኖርብናል። ለምሳሌ በ2008 ዓ.ም በፖለቲካው ረገድ የታዩ የጠባብነትና የትምክህተኝነት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችና በስልጣን የማገልገል ሳይሆን የመገልገል አስተሳሰቦች፤ በ2009 ዓ.ም የቅኝታቸው ስልተ-ምት ራስን በመፈተሽና በቁርጠኝነት በመታደስ ስሜት እንዲሁም በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መለወጥ ያለባቸው ይመስለኛል።
አዎ! ያለፈው ዓመት የችግር ሰንኮፎች መደገም አይኖርባቸውም። በሸኘነው አሮጌ ዓመት በጠባቦች፣ በትምክህተኞችና በመንግስት ስልጣን የመገልገል ፍላጎቶችና ተግባሮች ሳቢያ የተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ በአዲሱ ዓመት እንዳይደገም ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል። በአንፃሩም በአዲሱ ዓመት ሁከትንና ብጥብጥን “እንጀራዬ” ብለው የያዙ ፅንፈኞችና የሀገራችንን ሁለንተናዊ ዕድገት ማየት የማይሹ አንዳንድ የውጭ ሃይሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገንዘብ ይገባል።
ይሁንና የእነዚህን ሃይሎች ህልምን ዘንድሮ ለማሳካት መጣር ውድቀትን እንጂ ሐሴትን እንደማያመጣ እንደ ግለሰብ መገንዘብ ያለብን ይመስለኛል። ምክንያቱም የሁከትና የብጥብጥ መንገድ ውድቀትን እንጂ ቀና የሚያደርግ ዕድገትን ሊያመጣ ስለማይችል ነው። አዎ! በሰላምና በልማት እንጂ በሁከትና በብጥብጥ ያደገ ሀገር የለም። ከሁከት የሚገኝ ነገር ቢኖር በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በሚደረጉ ተግባራት ላይ ተሳትፎ አሊያም በሌሎች ግፊት በብጥብጥ ላይ ተገኝቶ ተጎጂ መሆን ብቻ ነው።
እናም አዲሱን ዓመት ለሰላም እጅግ የጎላ ዋጋ በመስጠት ልንቀበለው ይገባል። ለዚህም በውስጣችን ሊኖሩ የሚችሉ የጥበትና የትምክህት ኃይሎችን በማጥራት ለመታገል ብሎም በውጭ እየኖሩ እዚህ ሀገር ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ለሚሹ ፅንፈኞች የማህበራዊ ሚዲያ የፈጠራ ውትወታዎች ፊት ላለመስጠት በግለሰብ ደረጃ ቃል መግባት ይኖርብናል። ከሰላም ከሚገኘው ጥቅም ግንባር ቀደም ተቋዳሾቹ እኛው በመሆናችን ይህን የምንከውነው ለራሳችን ስንል መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም። 
በመግቢያዬ ላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት መንግሰት የግለሰቦች ስብስብ ነው። እናም ግለሰቦች ስለ አዲሱ ዓመት ስናልም ህልማችን በመንግስትን ስልጣን ለመገልገል እንጂ ከመንግስት ስልጣን እየተገለገልን ኑሯችንን ለማደላደል መሯሯጥ አይኖርብንም። ግለሰቦች ይህን ሲከውኑ የመንግስት ስራ ተቃንቶ ለስልጣን ብልግና ምቹ ምህዳር እንዳይፈጠር ያደርጋሉ። ይህ ካልሆነ ግን ችግሩ መልሶ እኛኑ መጥለፉ አይቀርም።
እርግጥ ‘ነገ እናገኘዋለን’ ብለን የምናስበው ስኬት በራሳችን ወዝና ላብ ጥረን ግረን የምናገኘው የድካማችን ዋጋ ነው መሆን ያለበት። ሌላው የለፋበትን ሃብት በመቀማት ወይም የመንግስት ስልጣንን በመጠቀም የራስ ያልሆነን ሃብት በአንድ ጀንበር በአቋራጭ ለማግኘት መመኘት አደጋው የከፋ መሆኑ አይቀሬ ነው። የህግ የበላይነትን ለማስከበር በሚደረገው ስራ ራሳችንን ሌላ ቦታ ውስጥ ልናገኘው እንችላለንና። እናም አዲስ ዓመት ሲመጣ “ማለም” ያለብን ነገር በአሮጌው ዓመት የነበሩብንን ችግሮች የሚያቃልል፣ ጠንካራ ጎኖችን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል እንዲሁም በሰላማዊና ህጋዊ አስተሳሰብ ላይ ተመርኩዘን መሆን አለበት።
ገዥው ፓርቲ በአዲሱ ዓመት በጥልቀት እታደሳለሁ ብሏል። ይህ ጥልቅ ተሃድሶው ዕውን የሚሆነው በግለሰቦች አማካኝነት ነው። ግለሰቦች ደግሞ ቀደም ሲል ከጠቀስኳቸው ጉዳዩች አኳያ ራሳቸውን መፈተሽ ይኖርባቸዋል። እናም ጥልቁ ህዳሴ የገዥው ፓርቲ ዕቅድ ቢሆንም ቅሉ፤ ፈፃሚዎቹ ግለሰቦች ነንና በሁለት ጉዳዩች በጥልቀት ራሳችንን ማየት የሚኖርብን ይመስለኛል። አንደኛው ‘በጥልቀት ለመታደስ ራሴን ምን ያህል አዘጋጅቻለሁ?’ የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ‘በጥልቀት የመታደስ ሂደት ውስጥ የእኔ ድርሻ ምን መሆን አለበት?’ ብሎ ራስን መጠየቅ የሚገባ ይመስለኛል።
እርግጥ ገዝው ፓርቲና መንግስት በራሳቸው መንገድ በጥልቀት የመታደስ ሂደቱን ሊያስኬዱት ይችላሉ። እንደ ፈፃሚ ብሎም የዚህችን ሀገር ብሩህ ጊዜን እንደሚመኝ ዜጋ  በአዲሱ ዓመት የአሮጌውን ዓመት የችግር ሰንኮፎችን ለመንቀል ለሚደረገው ጥልቅ ርብርብ በቁርጠኝነት የበኩላችንን ገንቢ አስተዋፅኦ ማበርከት ይኖርብናል። ይህን ስናደርግም በእኛ ህይወት፣ ደምና አጥንት ለመኖር የሚሹ ፅንፈኞችንና ዕድገታችንን የማይሹ አንዳንድ የውጭ ሃይሎችን ስናሳፍር፤ በሌላ በኩል ደግሞ የህዳሴ ገዟችንን በአስተማማኝ ሰላም በማጀብ እያሳለጥን መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም። መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን!

No comments:

Post a Comment