ታከለ አለሙ
እስከ ዛሬ በዘለቀው
ተጨባጭ ገፅታ የመንግሥትና የፓርቲ ሥራዎች በማይለዩበት ሁኔታ ተደበላልቀው ኖረዋል፡፡ ይህን በግምገማ የለየው ኢህአዴግ በሥር ነቀሉ
የተሀድሶ ለውጥ ውስጥ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከሚያስተካክለው መሠረታዊ አሠራሮች ውስጥ አንደኛው ይኸው ዘርፍ መሆኑን ገልጿል፡፡ መደበላለቁ
ይቆም ዘንድ ግድ ነው፡፡
የሀገሪቱ ሲቪል
ሰርቪስ ሠራተኛ በሙሉ ያለው በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ነው፡፡ የፓርቲና የመንግሥት ሥራ መደበላለቁ ሲቆም የመንግሥት መሥሪያ
ቤቶች በመያተኞችና በነጻነት ሲመሩ ከፍተኛ ለውጥ ይመዘገባል፡፡
ዋናውና የመንግሥት
ሥራዎች ሁሉ የጀርባ አጥንት ወይም አከርካሪ ተደርጎ የሚወሰደው ሲቪል ሠራተኛው ነው፡፡ ሙያተኛ ዜጎች ያለ ጣልቃ ገብነት በሙያቸው
በነጻነት መሥራትና ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ማገልገል ግዴታቸው መሆኑን ያምናሉ፡፡ አንዱም ኢህአዴግ መሠረታዊ ችግር ብሎ በቁርጠኝነት
ሊያርመውና ሊያስተካክለው የተነሳው ሙያተኞች በኃላፊነት፣ በተጠያቂነትና በግልፅነት መንፈስ ከሰሩ የበለጠ ውጤት ማስመዝገብ ይችላሉ፡፡ ያለጣልቃ ገብነት በነጻነት ሊሰሩ ይገባል ከሚል ጠንካራ እምነት በመነሳት
ነው፡፡
ሙያን የሚጠይቁ
ቦታዎች ሁሉ መሸፈን ያለባቸው በሙያተኞች ነው፡፡ በዚህ ረገድ በልምድ ከፍተኛ እውቀት ያካባቱ ዜጎች በትምህርት ክህሎቱን ያገኙ
ሰዎች ለአንድ ተቋም ትልቅ አቅምና ጉልበት ናቸው፡፡ በተለይም በአውሮፓ ሀገራት ልምድና ተሞክሮ ከወሰድን በአንድ መንግሥታዊ መሥሪያ
ቤት ውስጥ ረዥም ዘመን ያገለገሉና ልምድ ያካባቱ ሰዎች አዲስ ተተኪና ተመራቂ ወጣቶችን ከሥራቸው አድርገው ለተወሰነ ዓመታት እንዲለማመዱ
ያደርጋሉ፡፡
እውቀት፣ ልምድ፣
ብቃትና በራስ መተማመን የመወሰን ችግርን የመፍታት አቅምን እንዲያዳብሩ ታቅዶ የሚሰራ ሥራ ነው፡፡ እነዚህ ሙያተኞች እንደ ቅርስ
የሚታዩ የሀገር ሀብትም ናቸው፡፡ የሀገርና የዜግነት ግዴታቸውን በከፍተኛ ኃላፊነትና የተቆርቋሪነት ስሜት ይወጣሉ፡፡
ለሀገር ሀብትና
ለመንግሥት ንብረት ከፍተኛ ጠባቂ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ በርካታ ዓመታት በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት አገልግለው 30 ዓመትና
ከዚያም በላይ ጡረታ ሲወጡ የነበራቸውን የመሥሪያ ቤታቸውን ፍቅር እንዴት ለረዥም ዘመን በታማኝነት እንዳገለገሉ ሲናገሩ መስማት
መታደል ነው፡፡ ዛሬ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች የሉንም፡፡
ዛሬ ላይ አንድ
የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ አንድ ወጣት ግፋ ቢል አምስትና ስድስት ዓመት ከሰራ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሥራ ማማረጥ ያልተገላበጠ
ያራል የሚለው አማራጭ ለመፈለግ መሮጡ መብታቸው ቢሆንም ተቋማትን ደግሞ በእጅጉ ይጎዳል፡፡ መሥሪያ ቤቶች የሥራ ቦታቸው ለሠራተኛው
አመቺና ተስማሚ ከሆነ ጥሩ መሪና አስተዳዳሪ ካለ መብታቸው በአግባቡ ከተጠበቀ ለቀው የማይሄዱበት ሁኔታም አለ፡፡
ዋናው ነጥብ በአብዛኛው
የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በመንግሥት ሠራተኛው ዘንድ ጫና የሚፈጥረው አላስፈላጊ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲሆን ውሣኔ ሰጪ የሚሆነው
ሁሉንም መቆጣጠር አለብኝ የተለየ ኃላፊነት አለን በሚል ጣልቃ እየገቡ የሚያተራምሱት በተመሳሳይ ሁኔታም ለመልካም አስተዳደር ለፍትህ
እጦት ለአድልዎና ለመድልዎ ከፍተኛውን በር የሚከፍቱት የፖለቲካ አካላት ናቸው፡፡ በዚህ የመንግሥት ሠራተኛው ሲከፋ ኖሯል፡፡ ለእኔስ
ሀገሬ አይደለችም እንዴ ለእነሱ ብቻ ማን አደረጋት በሚል፡፡
የፖለቲካ አመራር
እንሰጣለን በሚል የመንግሥትና የፖለቲካ ድርጅትን ሥራ ያደበላለቁት ቅጥ አምባሩ እንዲጠፋ ያደረጉት የየድርጅቱ አባላት መሆናቸውን
ሠራተኛው ይናገራል፡፡ ይህ ሁኔታ በየመሥሪያ ቤቶቹ ግዢና ንብረት ጨረታ ኃላፊነት ላይ ባሉ መንግሥት ሠራተኞች ላይም ቀጥተኛና ሥውር
ጫና በማሳደር ሙስናና ምዝበራ እንዲስፋፋም ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ሠራተኞች ይናገራሉ፡፡
በሚያውቁትም በማያውቁትም
እየገቡ ዜጎችን የሚያስመርሩ በገዢው ፓርቲ ስም የሚነግዱ የመንግሥታዊ ሥራንና የፓርቲን ሥራ ለይተው የማያውቁ በመንግሥት ቢሮና
በጀት እንዳሻቸው ሲፈነጩ የነበሩና የሚፈነጩ የፖለቲካ ሹሞችን በየመሥሪያ ቤቱ ማየት የተለመደ መሆኑን ሠራተኛው በፍርሀት ተሸብቦ
ለመናገርም እድሉ እንደሌለው ይገልጻል፡፡
ይህንን ፀሐይና
አደባባይ የሞቀው በየመሥሪያ ቤቱ ያለን ችግር የመንግሥትን ሥራ ከፖለቲካ ሥራ በመለየት እንዲሰራ ለማድረግ ኢህአዴግ የደረሰበት
ድምዳሜ ተገቢ መሆኑን ሠራተኛው ይናገራል፡፡ ቀድሞም ቢሆን ፈጥኖ ማረም የሚገባው ራሱ ኢህአዴግ ብቻ ነበር፡፡ ዘግይቶም ቢሆን መገንዘቡ
ትልቅ ርምጃ ነው፡፡
ሀገሪቷ የሁሉም
ዜጎቿ የጋራ ቤት እንጂ ለተወሰኑ ሹሞች የግል ንብረት አድርጎ የሰጣቸው ሊሰጣቸውም የሚችል የለም፡፡ ሙያተኛው የበለጠ በፍላጎት
እንዲሰራ መበረታታት ነው የሚገባው፡፡ ተጽዕኖና ጫናን ሊሸከመው አይችልም፡፡ ሥራውን ለቆ ወደመረጠው ይሄዳል፡፡ ተጎጂዋ የፈረደባት
ሀገርና ህዝቡ ነው የሚሆነው፡፡ ይህ ያልሰለጠነና ያልተገራ አካሄድ ብሶትና ምሬትን ከማባበስ ውጭ የሚፈይደው ምንም ነገር የለም፡፡
ድርጅታዊ የፖለቲካ
ሥራ የፓርቲ ሥራ ሲሆን መንግሥታዊ ሥራ ደግሞ በፍጹም መለየት አለበት፡፡ አንድም የተሻለ ሀገራዊ የለውጥ አመለካከት ለሀገር ችግር
መፍትሄ የሚሆን ሀሳብ ማፍለቅ አማራጭ እይታዎችን ማመንጨት የማይችሉ በሹምነት ተሰይመው በሥራ ሳይሆን ነጋ ጠባ አዕምሮን በማደንዘዝ
በአታካችና እጅ እጅ በሚል አሰልቺ የስብሰባ ፍቅር ለተጠመዱት ኢህአዴግ እልባት ሊያበጅላቸው ይገባል፡፡ አሥረኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ
ጉባዔ ስብሰባን በተመለከተ ሲወያይ አጭር ስብሰባ ብዙ ሥራ በሚል የመከረበት መሆኑ ይታወቃል፡፡
ይኸው አሠራር በወረዳ፣
በክፍለ ከተማ፣ በክልል ሰፍኖና ገኖ በመንሰራፋቱ ነጋ ጠባ ስብሰባ ላይ ናቸው፤ የህዝቡን ችግር የሚያዳምጥ የለም የሚለው የመልካም
አስተዳደር ሙስናና የፍትህ እጦት መንገስ ችግርም ነው አንዱ በየደረጃው ኅብረተሰቡን አስመርሮ አሁን ያለውን ሀገራዊ ቀውስ የፈጠረው፡፡
ህዝቡም ብንሰበሰብ
ያው የተለመደውን አሰልቺ ወሬ ከመስማት በስተቀር ለውጥ አያመጡም፤ መሰብሰብም አንፈልግም እስከማለት የደረሰበትም ምክንያት ይኸው
ነው፡፡ ኢህአዴግ መንግሥታዊም ሆነ ድርጅታዊ አወቃቀሩን ሙሉ በሙሉ መፈተሽ መለወጥ ያለበትን መለወጥ፣ ማረም ያለበትን ማረምና ከህዝቡ
ፍላጎት ጋር በተጣጣመ መልኩ መራመድ የሚችልበትን አቅጣጫ ካልተከተለ ግንባር ሆኖ መዝለቅ የማይችልበት ወሣኝ ወቅት ላይ መገኘቱንም
መገንዘብ አለበት፡፡
ኢህአዴግ የበለጠ
ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ተተብትቦ ከተያዘበት በውስጡ መሽጎ አላሰራም ካለው ከህዝብ ጋር ሆድና ጀርባ ካደረገው ራሱን ወደከበርቴ
መደብነትና ወደ ከፍተኛ ንዑስ ከበርቴነት ካሸጋገረው ጥገኛ ኃይል ፈጥኖ ማፅዳት የነገ ሳይሆን የዛሬ የቤት ሥራው መሆን አለበት፡፡
ይህን በማድረግ
በሥር ነቀል ተሀድሶ ራሱን ለውጦ ከህዝቡ ጋር የተፈጠረውን መቃቃር በመፍታት ለመራመድ ካልበቃ ችግሩ ለሀገርም ለህዝብም ይተርፋል፡፡
የህዝቡ ጥያቄ እየገፋ መጥቷልና፡፡ መረጋጋት የሚያመጣው ከተፈጠረው ቀውስ ጀርባ ያሉትን ህዝብ የሚያውቃቸውን ዋነኛ ችግሮች አፋጣኝ
መልስ በመስጠት መፍታት ብቻ ነው፡፡ በሁሉም መስክ ያለው መደበላለቅ
መቆም አለበት፡፡
No comments:
Post a Comment