Friday, 30 September 2016

በጥልቀት የመታደስ ማለት ሹም ሽረት ማለት አይደለም!!




ስሜነህ
የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከነሃሴ 10-15/2008 . ድረስ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ያለፉትን አስራ አምስት ዓመታት የለውጥ ጉዞ በመገምገም በአንድ በኩል በእስካሁኑ ትግል የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ ለመቀጠል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን የሚፈታተኑ ችግሮችን በመቅረፍ የህዝብ መብትና ተጠቃሚነትን ለማጎልበት የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ማሳለፉና ጥቅል የሆኑትን የውሳኔ ሃሳቦች ለህዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡  
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በዚሁ ግምገማ የተረጋገጠውና ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት፤ ይልቁንም የውሳኔ ሃሳቦቹን ተግባር ላይ ለማዋል ይቻል ዘንድ ሊሰመርበት የሚገባው ነጥብ  አገራችን ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት በሁሉም መስኮች ከፍተኛ ለውጥ እያመጣች የተጓዘች መሆኑን የተመለከተው ነው፡፡ ህዝብና መንግስት መሪ ድርጅቱ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ተግባር ላይ ማዋል ይችሉ ዘንድ በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜህገ-መንግስት የተደገፈ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርዓት ግንባታ በመካሄድ ላይ መሆኑን ግልፅ ነው፡፡ ለቀጣዩ ተሃድሶ በዚህ የዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት የዜጎችና የልዩ ልዩ ማህበረሰቦች የፖለቲካ መብቶች ህጋዊ እውቅናና ዋስትና አግኝተው መከበራቸውንም ይብዛም ይነስ አምኖ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ የብሄር ብሄረሰቦችን ማንነት ያስከበረ አዲስ ዓይነት ፌደራላዊ የእኩልነት ስርዓት የተገነባና የሃይማኖት እኩልነት ተከብሮ መንግስትና ሃይማኖት መነጣጠላቸውንም በተመሳሳይ አምኖ መቀበል ግድ ይላል፡፡ የተጀመረውን እንዳልነበረ ወስዶ እና ከጉድለቱ ተምሮ መቀጠልን መሰረት ያላደረገ ለውጥን መሻት ትርጉም የለሽ ነው። በጥቅሉ  የዜጎችና የመላ ህዝባችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ቅድሚያ ሰጥቶ የተጀመረው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ህዝብ የሚጠቀምበት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓት በመገንባት ረገድ ረጅም ርቀት የተጓዘ መሆኑን መቀበል ለቀጣዩ ተሃድሶ ሁነኛ መደላድል ነው፡፡
የዚህ ተረክ መነሻም ይህን የተቀበለና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ይህንኑ መነሻ በማድረግ ባካሄደው ግምገማ በአሁኑ ጊዜ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ከሚፈታተኑት ችግሮች መካከል አንዱ የሆነውን የመንግስት ስልጣን የህዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ የግል ኑሮ መሰረት አድርጎ የመመልከትና በአንዳንዶችም ዘንድ የግል ጥቅም ከማስቀደም ጋር የተያያዘ እንደሆነ ማረጋገጡን መነሻ በማድረግ በተወሰደው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ያለውን እና እየታየ ያለውን ብዥታ ማጥራት ነው፡፡
ከላይ በተመለከተው አግባብ አገራዊ ለውጡ በስኬት ሲጓዝ የቆየው መንግስታዊ ስልጣንን ለህዝብ ጥቅም ማስከበሪያ ማድረግ በመቻሉ የሆነውን ያህል፣ ይህ ስልጣን ያለአግባብ ለመጠቀም ለሚሹ ግለሰቦች በመሳሪያነት ማገልገል ሲጀምር የተጀመረው ልማት የተደነቃቀፈ መሆኑና መልካም አስተዳደርም አደጋ ላይ መውደቁ ይታወቃል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ህዝብን በማስመረር ላይ ያለው ችግር ዋነኛ መንስዔ ይኸው እንደሆነ በማስመር ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ደረጃውና መጠኑ ምንም ይሁን ምን የመንግስት ስልጣንን ያለአግባብ ለግል ኑሮ መሰረት ለማድረግ የሚታየው ዝንባሌና ስህተት መታረምና መገታት እንዳለበት፣ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ተጨማሪ እርምጃም መውሰድ እንዳለበት ወስኗል፡፡ ዝንባሌው በሚታይባቸው ቦታዎች ሁሉ በአግባቡ እየተፈተሸ እንዲስተካከልና የድርጅቱ ጥራትና ጥንካሬ ተጠብቆ እንዲቀጥል አስፈላጊ የሆነው ርምጃ ሁሉ እንዲወሰድ መወሰኑም ይታወቃል፡፡  
ችግሩና የውሳኔው አፈጻጸም አካል የሚሆነው ህዝብና መላው የድርጅቱ አባላት እርምጃውን ወይም የተሃድሶውን እንደምታ ከሹም ሽረት ጋር ብቻ ያያያዙት መሆኑ በተለያዩ መልኮች መስተዋሉ ነው። ስለሆነም ከላይ ከተመለከተውና ድርጅቱም ካረጋገጣቸው ዋነኛ ችግሮች በመነሳት በጥልቀት የመታደስ ምንነትን፤ አዳሽና ታዳሽ የሆነውን ወገንና ዘርፎች እንዲሁም  የተገቢነቱን እንደምታ በዝርዝር መመልከት ስኬታማ ለሆነ ተሃድሶ እና ሃገራዊ ህዳሴ ተገቢ ይሆናል።
በጥልቀት የመታደስ  ትርጉም ከሹም ሽረት እጅግ የራቀና ይልቁንም ከአመለካከት ጋር የተያያዘ ነው። መሪ ድርጅቱ ከላይ በተመለከተው አግባብ ስለተሃድሶና መወሰድ ስለሚገባቸው የእርምጃ ውሳኔዎች ሲያወራ የመጀመሪያው እና ቁልፉ ጉዳይ ጎጂ ነገሮችን በድፍረት የመጋፈጥ ልምድና ተሞክሮ ያለውና በችግር ፈቺነቱ የሚታወቁት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና አባላቶቻቸው ማንኛውንም ህብረተሰባዊ ፈተና ተደብቀው ማለፍ የማይችሉ የመሆኑን  እውነታ በጥብቅ የመቀበል የአመለካከት ተሃድሶ ማድረግን በተመለከተ እየተናገረ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም በጥልቀት የመታደስ የመጀመሪያው ሚስጥር በዚህ ረገድ ያለው ችግር በተሟላ ደረጃ እስኪወገድ ድረስ ድርጅቱ እና አባላቱ ለአፍታም ቸል ሳይሉ  ጉዳዩን እያነሱ ሊጥሉና ሊፋጩበት የሚገባ መሆኑን የተመለከተ ነው፡፡
ድርጅቱ በተደጋጋሚ እንደሚገልጸውም ሆነ በተጨባጭ እንደሚስተዋለው ስርአቱ የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ የተጋረጠበት እንደሆነ በመገንዘብ ከተሃድሶ ሂደቱ ጀምሮ ለአስራ አራት አመታት ያህል በፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል መፋለሙ እሙን ነው፡፡ በዚሁም ልክ ነባራዊውን ሁኔታ ቀላል በማይባል ደረጃ ለልማታዊነት የተመቸ እንዲሆን ማደረጉም እሙን እና ሰሞንኛ የነበረው ግምገማም ከላይ በተመለከተው መልኩ ያረጋገጠው ነው፡፡ ይህ መሰረታዊ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ዛሬም ለኪራይ ሰብሳቢነት የሚያመቹ አረንቋዎች ጨርሶ አልተወገዱም፡፡ በተጨማሪም በነባራዊው ሂደትና ራሳቸው ኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች በሚፈጥሯቸው ቀዳዳዎች የተነሳ ዛሬም ለኪራይ ሰብሳቢ አዝማሚያና ተግባራት መበራከት ለም አፈር ሆነው የሚያገለግሉ ችግሮች ትንሽ አይደሉም፡፡ ሁለተኛው እና በጥልቀት የመታደስ ሚስጥር የድርጅቱና አባላቱ ድክመቶች ለዚህ አፍራሽ አዝማሚያ መከሰትና መስፋፋት ጉልህ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ማመንና ከዚህ የመውጫውን መንገድ ማበጃጀትን የተመለከተ እንጂ አንዱ አዳሽ ሌላኛው ታዳሽ ሆኖ የሚደረግ ሹም ሽር ነው ብሎ መውሰድ ከባድ ችግር ነው፡፡ ስለሆነም ትላንት ከትላንት ወዲያ ከነበረውም በላይ በፋይናንስ አቅሙና በጥገኛ መረቡ የጠነከረ ኪራይ ሰብሳቢነት አሁንም የስርዓቱ ፈተና ሆኖ መቀጠሉን እና ይህ በየትኛውም ዓይነት የድርጅቱ መልካም ስራ ሊሸፈን የማይችልና የማይገባው እውነታ መሆኑን ድርጅቱ እና አባላቱ ሊቀበሉ የሚገባ መሆኑን የተመለከተው ነጥብ በጥልቀት የመታደስ ምንነትን ፍንትው አድርጎ የሚገልጥ ነው፡፡
ስርዓታችንን የሚፈታተነው ኪራይ ሰብሳቢነት እንደአመቺነቱ በልዩ ልዩ መልኮች የሚከሰት ነው፡፡ አንዳንዴ በግብር ስወራ፣ ሌላ ጊዜ በንግድ ስርዓቱ ውስጥ የሞኖፖል አቅጣጫን ተከትሎ ሸማቹን በመዝረፍ፣ ሌላ ጊዜ መሬት በማግበስበስ ይከሰታል፡፡ ወይም ደግሞ የመንግስትን ፕሮጀክቶች ባልተገባ የጥገኛ መረብ ታግዞ ማግኘትና ጥራቱ የተጓደለ የፕሮጀክት አፈፃፀም በማሳየት ከህጋዊው በጀት በላይ ከመንግስት ገንዘብ በመውሰድና በመሳሰሉት መልክም ይገለፃል፡፡
አንዳንዴ ህብረተሰብ ውስጥ በተለይ በግሉ ሴክተር የተሰማራው ባለሃብት ዋናው የኪራይ ሰብሳቢ ኃይል ሆኖ በሚወጣበት፣ ሌላ ጊዜ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ተመሳሳይ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች በሚበራከቱበት ሁኔታም ሊገለፅ የመቻሉ ምክንያት የድርጅቱ እና አባላቱ የመታገል እና የማታገል ጥንካሬና ድክመት መሆኑንም አምኖ መቀበልን የተመለከተው ጉዳይ በጥልቀት የመታደስ ምንነትን የሚያጠይቅ ነው፡፡ በአንድ አካባቢ የሚካሄደው ትግል አይሎ ኪራይ ሰብሳቢነት እየተጠራቀመ ሲሄድ፣ ሌላ ቀዳዳ ፈልጎ በሆነ ሴክተርና መልክ የመገለፁ ምክንያት ከመታገልና ከማታገል ድክመትና ጥንካሬ የሚመነጭ እንጂ ሌላ መነሻ ስለሌለው ነው በጥልቀት መታደስ ማለት ከሹም ሽር የቀደሙ በርካታ እንደምታዎች አሉት የምንለው ፡፡
አንድ ኪራይ ሰብሳቢ ኃይል በትግሉ አስገዳጅነት ልማታዊ አቅጣጫ ሲይዝ፣ ሌላ ኪራይ ሰብሳቢ ኃይል በሌላ መልክና አጋጣሚ ብቅ የሚልበት ሂደት እንደነበር ድርጅቱ ባደረገው ግምገማ ያረጋገጠ መሆኑን ገልጦልናል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢ ትግሉ ሲዳከም ዝንባሌው እየሰፋ፣ ትግሉ ሲጠናከር ደግሞ ዝንባሌው እየቀነሰ በሚታይበት ሁኔታ ውስጥ ድርጅቱ ማለፉንም ግምገማውን ተከትሎ የወጣው መግለጫ አረጋግጧል፡፡ ስለሆነም ጥልቅ ተሃድሶ ማለት ይህን በመገንዘብ ህዝቡ፣ ድርጅቱ እና መንግስት በሚያካሂዱት የተቀናጀ ትግል ዝንባሌው እንደገና በቁጥጥር ስር የሚውልበትን ሁኔታ መፍጠር ማለት እንደሆነም መገንዘብ ያስፈልጋል ፡፡
ኪራይ ሰብሳቢነት በተንሰራፋ ቁጥር ልማታዊ ዴሞክራሲያዊነት መዳከሙ፣ በአንፃሩ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊነት በተጠናከረ ቁጥር ኪራይ ሰብሳቢነት መዳከሙ የታወቀ ነው፡፡ ይህ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የታየ ክስተት ነው፡፡ በብዙ ልማታዊ አገሮች ኪራይ ሰብሳቢነት ከቁጥጥር ውጭ እንዲሄድ ሲፈቀድለት ጅምር ልማታዊ ጥረቶችን ሁሉ በማጨናገፍ አገሮች ካሰቡት ሳይደርሱ እንዲቀሩ አድርጓል፡፡ በአንፃሩ የተዋጣለት ፀረ ኪራይ ሰብሳቢ ትግል ያካሄዱ አገሮች ሁሉ በአንድ ወይ በሌላ መልክ የተከሰተ ኪራይ ሰብሳቢነት ሳይደፍቃቸው ካሰቡበት ደርሰዋል፡፡ በጥልቀት መታደስ ማለት በእኛ ሁኔታም ከዚህ የተለየ ሊሆን እንደማይችል የህዳሴው እና የተሃድሶው አካላት በሙሉ በየደረጃቸው ሊገነዘቡ እና የአመለካከት ለውጥ ሊያመጡ ይገባል ማለትንም የሚጨምር እንጂ ድፍን ያለ ሹም ሽረት አድርጎ መውሰድን ብቻ የተመለከተ አይደለም፤ ሹም ሽረት የመጨረሻው አማራጭ ነው።

በጥልቀት መታደስን በተመለከተ ስናወራ ከሌላው ባለድርሻ በላቀ ደረጃ የድርጅቱ አባላትን ጨምሮ የመንግስት ፈጻሚና አስፈጻሚ አካላት  ከላይ የተመለከቱ እና ከአመለካከት ጋር የተያያዙትን ጉዳዮች በሚገባ ሊያስታውሱና ሊያጤኑት ይገባል። ይህ ከሆነ ደግሞ በአገራችን የተጀመረውን ፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል  ዳር ማድረስ ይቻላል። ይህ ከሆነ ደግሞ  ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የተመዘገቡት ውጤቶች ተጠብቀው ይበልጥ በአዳዲስ ድሎች ይጎለብታሉ፡፡ ኢኮኖሚያችን አሁንም ፈጣንና ህዝብ የሚጠቀምበት እድገት እያሳየ ሊጓዝ ይችላል፡፡ አገራችን ገና በቅጡ ያልተነካ ድልብ የልማት አቅም ያላት አገር ነች፡፡ የህዝብ ብዛቷ፣ መሬቷ፣ ውኃዋ፣ ኢነርጅ የማምረት አቅሟ፣ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን የማስፋፋትና በእነዚህ ሁሉ መስኮች ተወዳዳሪ የመሆን ብቃቷ እጅግ የሚያስጎመጅና በተነፃፃሪ ጠንካራ ትግል ወደውጤትነት ሊቀየር ይችላል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ መታደስን ከሹም ሽረት ጋር ብቻ አያይዘን የምንመለከት ከሆነ ኪራይ ሰብሳቢነት ከቁጥጥር ውጭ እንዲወጣ የበለጠ እድል ስለሚያገኝ የዚህ ተፃራሪ ውጤት ይመጣል፡፡ መጀመሪያ ላይ የእድገት መገታት፣ በሂደት ደግሞ እንደማንኛውም በጥገኝነት አቅሙ የተሰለበ አገር ያደርገናል፡፡ ከዚህም አልፎ በቅርቡ አንዳንድ አካባቢዎች የአገራችን ክፍል እንደተከሰተው ዓይነት ግጭትና አለመረጋጋት የሚያስከትል የመልካም አስተዳደር እጦትና ትርምስ ሊያስከትል ይችላል። ስለሆነም ስለውድቀታችንም ሆነ ትንሳኤያችን በጥልቀት የመታደስ ዋነኛና መሰረታዊ የሆነው ሚስጥር ከላይ ከተመለከቱ የአመለካከት ጉዳዮች ጋር የተያያዘው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ፡፡

የተሃድሶ ወግ



 

ዮናስ

ኪራይ ሰብሳቢነትን በስኬታማ መንገድ በመታገልና ባለመታገል፣ ውጤት በማምጣትና ባለማምጣት ረገድ ቁልፍ ሚና ከሚጫወቱ አካላት መካከል መንግስት የመንግስትን ስልጣን የያዘው አስፈጻሚ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በተለይ መንግስት በአንድ በኩል የኪራይ ሰብሳቢነት አረንቋን በማድረቅ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለልማታዊ ኃይሎች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር መሰረታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ለውጥ የሚያመጣውን ትግል የሚመራ አንድ ቁልፍ ኃይል መሆን እንዳለበት ተሰምሮበት ያደረ፤ ይህን መስመር በመከተልም ሲገነባ የቆየ ነው፡፡ ይህ መሰረታዊ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግስት በማያቋርጥ የኪራይ ሰብሳቢነትና የኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች ጥቃት ስር ለማለፍ የሚገደድ ተቋም ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች ከቻሉ ከውጭ በሚያካሂዱት ጥቃት ልማታዊ መንግስትን ለማዳከምና ለማሽመድመድ ይሞክራሉ፡፡ በንቃት፣ በታቀደና በተደራጀ አኳኋን ባይመለምሏቸውም በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያለውን የኪራይ ሰብሳቢነት ዝንባሌ ለእነርሱ በሚያመች ኪራይ ሰብሳቢ አቅጣጫ ሊቃኙ ይችላሉ፡፡ ኢህአዴግ ካደረጋቸው ግምገማዎችና የህዝብ መድረኮች መገንዘብ የተቻለውና የተረጋገጠው  በድርጅቱም ሆነ እርሱ በሚመራው መንግስት ውስጥ ህዝቡንና አገራቸውን በልማታዊ አቅጣጫና በታማኝነት ከሚያገልገሉ አባላትና አመራሮች ጎን፣ ከዚህ ህዝባዊ የአገልጋይነት መንፈስና አስተሳሰብ ርቀው መንግስትን የራሳቸው ግላዊ ጥቅም ማካበቻ ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች በደባልነት መኖራቸውን ነው፡፡
ስለሆነም ተሃድሶ ማድረግ  አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። አንዳንድ አካላት ግን ተሃድሶውን እና የተሃድሶውን አቅጣጫ በተለየ መንገድ በመረዳት የተቀረው ደግሞ አውቆ የኪራይ ሰብሳቢነት ከርሱን ለመሙላት ይረዳው ዘንድ የጉዳዩን አቅጣጫ በማሳት ላይ ይገኛሉ እና ተሃድሶ ማለት ሁለንተናዊ የሆነ የትራንስፎርሜሽን ጉዞ መሆኑን የሚያጠይቁ ጉዳዮችን ማውጋት ስለሃገራችን ህዳሴ ጠቃሚ ነው።
እጅግ አብዛኛው የመንግስት ሰራተኛ ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል ለለውጡ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳበረከተው ሁሉ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታዩ እና የሰው ህይወትና ንብረት ለወደመባቸው ግጭቶች ምክንያት የሆኑ የኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚያዎችን   በጥብቅ በመታገልና በማስተካከል መንግስት የህዝብ አገልጋይ እንደሆነ መቀጠሉን ማረጋገጥ የተሃድሶው መነሻና መድረሻ እንዲሁም የተሃድሶው ማጠንጠኛ መሆኑን ጠያቂያኖቹም ሆንን መልስ ሰጪዎቹ ልንረዳውና የጋራችን አመለካከት ሊሆን ይገባል፡፡ በዚህ መሠረት በየደረጃው ያሉ ኃላፊዎችና አባላት በተለይ ደግሞ ዛሬም እንደትላንቱ ህዝብን የማገልገል ዓላማ አንግበው ሌት ተቀን ለአገራቸው እድገትና ለህዝባቸው ተጠቃሚነት የሚባትሉ ታጋዮች ይህን ኃላፊነት በቅጡ መወጣት የሚችሉበትን መደላድል መፍጠርም ሌላኛው የጠያቂውና የተጠያቂው ወገኖች የጋራ አረዳድ ሊሆን ይገባዋል፡፡
በግምገማው የተረጋገጠው እና የተሃድሶውም አስፈላጊ መሆን የታመነው መንግሥት ልማታዊ ባህርዩን ጠብቆ ተልዕኮውን እያሳካ እንዲጓዝ የማድረግ ጉዳይ  በቅንነት ከሚታገሉ አባላትና የአመራር አካላት ትግልና ቁርጠኝነት ውጭ ሊሳካ የማይችል መሆኑ ስለተረጋገጠ እና ለነዚሁ አካላት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መሆኑ የመጀመሪያው ሲሆን፤ ራሳቸው በኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚያ የተበከሉ አባላት ደግሞ፣ ይህን አደገኛ የጥፋት መንገድ ትተው ወደቀና አቅጣጫ የሚያመሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንጂ የቂም በቀል ሂሳብ ለማወራረድና የጠሉትን መትቶ የወደዱትን በማንገስ ወደለየለት የኪራይ ሰብሳቢነት አቅጣጫ ለማምራት አይደለም፡፡
ከዚህ በመነሳት የተሃድሶው ግብ መንግስትን ከማንኛውም አይነት ድክመት የማፅዳትና ለተልእኮው የማብቃት ጉዳይ እንጂ የግለሰቦችን ሂሳብ የማወራረጃ ጉዳይ እንዳልሆነ መገመት አይከብድም፡፡ ይህ የሚወሰነው ከምንም ነገር በላይ መንግስትን የመቆጣጠረው ህዝብ  ከአሉባልታና ከተሃድሶው አቅጣጫዎች ውጪ ከሚራገቡ ወሬዎች በመጽዳት  በበጎ ተፅዕኖው መንግስት ከመልካም አቅጣጫው እንዳይወጣ ሲያደርገው ነው፡፡ በመሆኑም ተሃድሶ ማለት  በአንድ በኩል የመንግስትን ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ ባህርያት በከፍተኛ ትኩረት ማጎልበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በመንግስት ደረጃ የሚታዩ የኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚያዎችን በፅናት እየተፋለሙ የማስተካከል ተግባራትን በፅናት መፈፀም እና ለመፈጸም የሚያስችል ምህዳር መፍጠር ማለት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
ተሃድሶ ማለት ሌላ ሳይሆን መንግስት በእስካሁን ድሎች ሳይዘናጋ፣ ባጋጠሙት ፈተናዎች ክብደት ሳይደናገጥ በፅናትና ህዝባዊ ወገንተኝነት የተያያዘውን ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ትግል ወደ ሌላ ከፍታ ለማውጣት የሚያስችለውን ስርአት መዘርጋትና ለዚሁ የሚመጥን የሰው ሃይል ማሰማራት ማለት ነው፡፡
ተሃድሶ ማለት በፊት ያልነበሩና በአግባቡ ከተጠቀምንባቸው አገራችንን ለላቀ ዕድገትና ጥንካሬ የሚያበቁ የተከማቹ አዎንታዊ አቅሞችን በአግባቡ መያዝና ጥቅም ላይ በማዋል ለውጤት ማብቃትን የተመለከተ እንጂ ፍለጠው፣ ቁረጠው፣ አንሳው ወይም ጣለው ላይ የተመሰረተ እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
በየደረጃው የሚታዩት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዓይነተኛ ምንጭ ኪራይ ሰብሳቢነት ስለመሆኑና  በየአስተዳደር እርከኑና በየሴክተር መስሪያ ቤቱ የሚገኘውን አመራርና ፈፃሚ የአድሎና የመጠቃቀም ተግባር ውስጥ የሚያስገባውም ይኸው ኪራይ ሰብሳቢነት እንደሆነ በጥናትም ሆነ በግምገማ ተረጋግጧል፡፡ ሕዝብን በቅንነት የማገልገል ተነሳሽነት ጉድለት፣ ማመናጨቅና ማዋከብ ውስጥ የሚከተው የሕዝባዊነት ጉድለት ምንጭም ይኸው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት መዳበር መሆኑን በማስገንዘብ ከዚህ የማውጣት ወይም ደግሞ ሚናውን እንዲለይ ማድረግ ነው ተሃድሶ፡፡ ጥልቅ ተሃድሶ ማለት እላይ የተንጠለጠለ የካቢኔ ብወዛ ሳይሆን መንግስትና ሕዝብ ተባብረው እንዲህ ያለውን፣ ሕዝባዊነት የጐደለውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የሰፈነበትን አመራርና ፈፃሚ ከየተቋሙና ከየመዋቅሩ ማጥራት ማጥራት ማለት ነው፡፡ ተሃድሶ ማለት ይህን ለማድረግ የሚያስችል አደረጃጀትና አሰራርን መዘርጋትና ማዘመን ማለት እንጂ ግለሰቦችን ማፈራረቅ ማለት አይደለም ። በጥቅሉ ጥልቅ ተሃድሶ ማለት በተነሳሳ ሕዝባዊ የለውጥ ሀይል ቀልጣፋ፣ አርኪና አስተማማኝ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ በመፍጠር መልካም አስተዳደርን ማረጋገጥ ማለት እንጂ በሚናፈሰው ልክ ማንሳትና መጣል ብቻ አይደለም፡፡ 
ጥልቅ ተሃድሶ ማለት  በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የተገነቡት መሰረተ ልማቶች፣ ለሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስኬታማነት ትልቅ አቅም መሆናቸውን ያገናዘበ ስርአት የመዘርጋትና ለዚሁ የሚመጥን አመራር መሰየምን እንጂ ማሰርና መፍታትን ግቡ ያደረገ አካሄድ ማለት አይደለም።  
ጥልቅ ተሃድሶ ማለት ወጣቱ ትውልድን በገጠርና በከተማ ልማት በማሰማራት የስራ ዕድል ከመፍጠር ጎን ለጎን የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሃይል ለማድረግ የሚያስችል አሰራር መዘርጋት፣ በጀት መያዝና ለዚሁ የሚመጥን ፈጻሚና አስፈጻሚ ማብቃትና ማምጣትን የተመለከተ እንጂ ሊታረም፣ ሊቃና የሚችለውን ሁሉ በማባረር ያለጥናትና ሙሉ ዝግጅት ሌሎችን መተካት ማለትም እንዳልሆነም ማጤን ስለተሳትፏችን የግድ ይላል። ይህን ከመንግስት አወቃቀር ባህርያት አንፃር ለተመለከተው ደግሞ ሁሉም ነገር የበለጠ ግልፅ ይሆናል።
የሁለተኛውን ዙር እና የአንደኛውን ዙር አፈጻጸም መነሻ ያደረገው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የገጠሩን አጠቃላይ ገፅታ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚለውጠው ይታመናል፡፡ የመስኖ ግብርና፣ የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንደዚሁም የእንሰሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ስራ በከፍተኛ ደረጃ ማስፋፋትን ትኩረት ያደረገው ይህ ዕቅድ፣ ግብርናው በዕቅድ ዘመኑ ለልማቱና ለፈጣን ዕድገቱ የማይተካ አስተዋፅኦ ከማድረግ ባሻገር የዘመናዊ አምራች ዘርፍ ዕድገት ዋና ምንጭ ሆኖ እንዲቀጥል እንደሚያስችልና ሰፊ የስራ እድሎችን የሚፈጥር እንደሆነም ፖሊሲ ተንታኞችም ሆኑ የዘርፉ ልሂቃን ደጋግመው መስክረዋል ፡፡  ስለሆነም የገጠር ኢንዱስትሪ ማዕከላት በሂደት እየተፈጠሩ ከተሞቻችንም በዛው መጠን እያደጉ ሲሄዱ የህብረተሰቡ የኑሮ ደረጃ እየተቀየረ፣ የከተማና የገጠር ትስስር እየጠበቀ፣ ያደገ ህብረተሰብ ለመገንባት የሚያስችለን አቅም እየተፈጠረ የመሄዱን አይቀሬነት የተገነዘበ እና የበቃ ፈጻሚና አስፈጻሚ የማምጣትን እና በሂደትም ተተኪዎች የሚፈሩበትን ስርአት መዘርጋት ነው ጥልቅ ተሃድሶ ፡፡
የጥልቅ ተሃድሶው አቅጣጫና ግብም እንዲህ የሚሆነው ከእንግዲህ ያለው ሂደት በስኬት የተሞላና ለውጡ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያጎለብት እንዲሆን የማድረግ ጉዳይ የሚወሰነውም የመንግስትን ስልጣን በሚይዙ  ብቃት ያላቸው አመራሮችና ፈጻሚዎች ስለሆኑ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የሃገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በትክክል ገምግሞ፣ መልካም ዕድልና ፈተናዎችን በውል ለይቶ፣ በመልካም እድሎቹ በአግባቡ ለመጠቀም፣ ፈተናዎቹን ደግሞ በተገቢው አቅጣጫ ለመፍታት የሚችል  ብቁ አመራር ሰጪና ተቀባይ ፈጻሚ ሲኖር ብቻ ስለሆነ ነው፡፡
ህዝብን በተለይም ማህበራዊ መሰረቶቹ የሆኑትን ብዙኃን እንደተለመደው በትክክለኛው አቅጣጫና በብቃት በማደራጀት የለውጥ ሃሳቦቹን ተግባራዊ የማድረግ ብቃት እንዲጎናፀፉ አድርጎ የመምራትን አቅም መገንባትና ስርአት መዘርጋትም የተሃድሶው አካል ነው፡፡ ስለሆነም ስለተሃድሶ ያለንን ግንዛቤ ከሞላ ጎደል ከላይ በተመለከቱት ማእቀፎች ማስተካከል የህዝብና የአገርን ዘላቂና መሰረታዊ ጥቅሞች የማስከበር ትግሉን በአሉታዊ ተፅዕኗቸው ለማምከን የሚተጉ ሃይሎችን ለማጨንገፍ ይጠቅመናል፡፡ ለምን ቢሉ በኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ የተበከሉ ሰዎች ውስጣዊ ዴሞክራሲን በማጥበብ፣ ከስህተታቸው እንዲታረሙ ወይም እንዲወገዱ የሚደረገውን ትግል በማዳከም ስርአቱ ራሱን በራሱ የማረም የቆየ ችሎታውን እንዲያጣ በማድረግ የጥቅማችን ተጻራሪ ያደርጉናልና ፡፡
ባጠቃላይ፣ በአሁኑ ጊዜ ይህን ችግር ለመታገል የተጀመረው ጥረት የግምባሩ አባላትን ብቻ ሳይሆን በብዙ አካባቢዎች ህዝብን ባሳተፈ አኳኋን ጭምር እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ጥልቅ ተሃድሶ ማለት በዚህ ትግል በተለይ  ህዝቡ የሚታየውንና የገጠመውን ችግር ሁሉ በድፍረትና በግልፅነት እያነሳ መፋለም ማለት መሆኑንም ማስመር ተገቢ ነው፡፡ በዚህም አማካይነት ዘላቂ የሆነውን ሃገራዊ ህዳሴ በአስተማማኝ ደረጃ የማሳካት ጉዳይ የጊዜ ጉዳይ ብቻ እንደሚሆን አያጠያይቅም። የአጭር ጊዜ!!!!