በወርቅነሽ ደምሰው
ሕጻናት ሀገር ተረካቢ ትውልድ ስለሆኑ የተሟላ ስብዕና ይዘው የሀገሪቱ ተተኪ የሰው ኃይል ምንጭ እንዲሆኑ ሁሉም ሰው ግዴታን መውጣት ይጠበቅበታል።
በዓለም አቀፍ የሕጻናት ኮንቬንሽን እና የኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ መሠረት ‹‹ሕጻን›› የሚለው
ቃል ዕድሜው ወይም ዕድሜዋ 18 ዓመት እና ከዚያ በታች የሆነ ሲሆን፤ ከሀገራችን ሕዝብ ብዛት 52 በመቶ የሚሆኑት ሕጻናት መሆናቸውን
የሀገሪቱ የማዕከላዊ ስታትስቲክ መረጃ ይጠቁማል ፡፡
ሕጻናት ላይ የሚደረጉ ያልተገቡ አካላዊ እና ሥነ-ልባናዊ አያያዞች፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ በቸልተኝነት፣የገንዘብም
ሆነ ሌሎች ጥቅሞችን ለማግኘት የሚፈጸም የጉልበት ብዝበዛ በሕጻናት ላይ ከሚፈፀሙ ጥቃቶች ጥቂቶቹ ናቸው። እነዚህ ጥቃቶች መፈፀማቸው
በተለያየ ደረጃ ሊገለፅ የሚችል በሕጻናቱ ጤና፣ ዕድገት እና ስብዕና ላይ ጉዳት እንዲደርስ ያደርጋል። ይህ ደግሞ በልጆች አስተዳደግ
ላይ ኃላፊነት ያለባቸው ግለሰቦች የሚፈጽሙት ድርጊት መሆኑን መረጃው ያሳያል፡፡ ስለዚህ በወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ጥቃት በመፈጸም
ወይም ከጥቃት ባለመከላከል ምክንያት በሕጻናት ላይ ጉዳት ሊደርስ
ይችላል፡፡ ጥቃቱ በቤተሰብ አባላት፣ በተለያዩ ማዕከላት ወይም የማኅበረሰብ አካላት በሆኑ እና በአብዛኛው በሕጻናት በሚታወቁ አልፎ
አልፎም በማይታወቁ ሰዎች ሊፈጸም ይችላል፡፡
በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ አሳሳቢ ከሆኑት በሕጻናት ላይ ከሚደርሱ ጥቃቶች አንዱ አስከፊ የሕጻናት
ጉልበት ብዝበዛ ነው፡፡ እንደ የዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት መረጃ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወንዶች እና ሴቶች ልጆች በቂ
ትምህርት፣ ጤና፣ እረፍት እና መሠረታዊ ነጻነቶችን በሚያሳጧቸው የሥራ መስኮች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።
እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ባስጠናው
ጥናት መሠረት በሀገራችን ዕድሜያቸው ከ5-14 ዓመት ክልል ውስጥ ከሚገኙ ልጆች መካከል 28 በመቶ የሚሆኑት በሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ
ሥራ የተሰማሩ መሆናቸውን ያሳያል። በሠነዱ ዕድሜያቸው ከ5-11 ዓመት
ከሚሆኑት ሕጻናት መካከል 18 ከመቶ፣ ዕድሜያቸው ከ12-14 ከሆኑት
ሕጻናት መካከል ደግሞ 40 ከመቶ የሚሆኑት በሣምንት ከ28 ስዓታት በላይ እንደሚሰሩ ተረጋግጧል። ይህም በክልሎች ሲታይ (በትግራይ
42 በመቶ፣ በአማራ 32 በመቶ ፣ በኦሮሚያ 22 በመቶ፣ በደቡብ 31 በመቶ፣፣በኢትዮ-ሶማሌ 23 በመቶ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ
20 በመቶ፣ በጋምቤላ 14 በመቶ ፣በሐረሪ 11 በመቶ) እንዲሁም በአዲስ አበባ የከተማ አስተዳደር 7 በመቶ እና በድሬ ዳዋ የከተማ
አስተዳደር 14 በመቶ መሆኑ የችግሩን አሳሳቢነት የሚያሳይ ነው፡፡
የሕጻናት የጉልበት ብዝበዛ በሕጻናት የሚሠራ ሥራ ሲሆን፤ ከሥራው ዓይነት እና ባህሪይ አኳያ
ሲታይ ለሕጻናቱ አካላዊ እና አዕምሯዊ አስተዳደግ ጎጂ የሆነ፣ ለተለያዩ የሥራ ላይ አደጋዎች እና የጤና ጉዳቶች የሚያጋልጥ፣ የትምህርት
ዕድል የሚያጣብብ ሲከፋም የሚዘጋ ፣ለረዥም ሰዓት በዝቅተኛ ክፍያ የሚወሰን የብዝበዛ ባህሪያት ያለው እና የቅጥር ግንኙነትን የሚንፀባረቅበት
ሥራ ነው፡፡ ይህም ሕጻናትን ለተለያዩ አካላዊ፣ሥነ-ልቦናዊ እና ፆታዊ ጥቃት የሚዳርጉ ሥራዎችን የሚያካትት ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ
ለዚህ ችግር የሚጋለጡት ደግሞ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ደላሎች አማካይነት ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ከገጠር ወደ ከተማ እንዲኮበልሉ
የተደረጉ ሕጻናት ናቸው፡፡
በዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት (ILO) ፍረጃ መሠረት የሕጻናት የጉልበት ብዝበዛ ማለት፤ ከ11
ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት የሚያከናውኗቸውን ማንኛውም ዓይነት ኢኮኖሚ ነክ ሥራ፣ ከኮንቬንሽኑ ድንጋጌ ውጭ የሆኑ ከ12 እስከ
14 ዓመታት ያሉ ሕጻናት የሚያከናውኗቸው ማንኛውም ዓይነት ኢኮኖሚ ነክ ሥራ፣ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 17 በሆኑ ሕጻናት የሚከናወኑ
ማንኛቸውም ለአደጋ የሚያጋልጡ ሥራዎች እንዲሁም አደገኛ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛን የሚያስከትሉ ከ18 ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት
የሚያከናውኗቸውኑት የኢኮኖሚ ሥራዎችን ያጠቃልላል።
ይህ ችግር በተለይ በታዳጊ ሀገራት በስፋት የሚታይ ክስተት በመሆኑ በድህነት ሁኔታ፣ በጦርነት
በመፈናቀል፣ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ወረርሽን ፣ በተሳሳተ የማኅበረሰብ አመለካከት፣ በቂ የሕግ ጥበቃ ሥርዓት አለመኖር እና የሕገ
ወጥ የሕጻናት ዝውውር መበራከት ለችግሩ መስፋፋቱ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡
በሀገራችን ለሕጻናት የጉልበት ብዝበዛ መስፋፋት እና ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በምክንያትነት
ከሚጠቀሱት መካከል የደላሎች መበራከት እና የወላጆች በሞት መለየት የትዳር መፍረስ ዋናዎቹ ናቸው። ሕጻናት ከሚሰማሩባቸው የጉልበት
ብዝበዛ ሥራዎች መካከል የተለያዩ ባህላዊ የሽመና ሥራዎች ፣ የአበባ ሥራ፣ የአትክልት እና ፍራፍሬ እርሻዎች ፣ በከተሞች የደረቅ
ቆሻሻ የመሰብሰብ ፣ በወሲብ ንግድ እና በሆቴል አገልግሎት ሥራ፣ በኮንስትራክሽን ሥራዎች ፣ በቡና እና በሻይ ምርት ለቀማ ፣ የአነስተኛ
እና መካከለኛ የማምረቻ ድርጅቶች፣ በአገልግሎት ሰጪዎች እና በቤት ውስጥ ሥራዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ።
በእነዚህ የሥራ ዘርፎች በሚደርሱ የጉልበት ብዝበዛ በርካታ ሕጻናት ለድህነት እና ለመሃይምነት
ተዳርገዋል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ሕጻናት የትምህርት ዕድል ካለገኙ እና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚፈልገ ዕውቀት እና ክህሎት ከሌላቸው
ለሀገሪቱ ልማት የሚያደርጉት አስተዋፅኦ ውስን ስለሚሆን ሀገሪቱን በኢኮኖሚ ረገድ የሚጎዳ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሕጻናቱን
ከተለያዩ የጤና እክሎች ለመታደግ መንግሥት፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶም ሆኑ የተለያዩ የኅብረተሰቡ ክፍሎች
የሚያወጡት ገንዘብ ለሌሎች ምርታማ ለሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች ቢውል ሀገሪቱ እያስመዘገበች ላለው ዕድገት የበኩሉን ድርሻ ያበረክት
ነበር።
ይህን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት የአሠሪ እና ሠራተኛ አዋጅ በማውጣት የሕጻናትን ትምህርት፣ ጤና
እና ድህንነት እንዲሁም አካላዊ ዕድገት የሚጎዳ እና አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሥራዎች ላይ ክልከላን አስቀምጧል፡፡
ሕጻናት የዛሬ ቡቃያዎች የነገፍሬዎች ናቸው፡፡ ቡቃያ በእንክብካቤ ካልተያዘ ፍሬ እንደማያፈራ
ሁሉ ሕጻናት በአግባቡ ተይዘው ካልታነጹ በለጋነታቸው ለማይወጡበት ችግሮች ይጋለጣሉ። ይህም በለጋነታቸው ሞታቸውን በማፋጠን ሀገር ተረካቢ ትውልድ ያሳጣል። ስለዚህ
ከዚህ ትውልድን ከሚያኮላሽ ችግር ለመውጣት የራስን አስተሳሰብ በመለወጥ ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ በሕጻናት ላይ የሚደርሰውን የጉልበት
ብዝበዛ ማስቆም ያስፈልግል፡፡ በተለይም የተማረው የሀገሪቱ ዜጋ ራሱን ለለውጥ ዝግጁ በማድረግ የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ረገድ
ብዙ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡
ሕጻናትን ለጉልበት ብዝበዛ የሚዳርጉ ሕገ ወጥ የሕጻናት አዘዋዋሪዎች በተለያዩ ማታለያ በመጠቀም
ከወላጅ፣ ከአካባቢያቸው በማፈናቀል የራሳቸውን ፍላጎት የሚወጡ በመሆናቸው እና ይህን ድርጊት ሲፈጽሙም ከኅብረተሰቡ ዕይታ ውጭ ስላልሆኑ፤ኅብረተሰቡ በማጋለጥ
ለሕግ አሳልፎ በመሰጠት ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረግ ይገባዋል፡፡ ለሕጻናት ልጆች አስተዳደግ ምቹ ሁኔታዎችን በመፈጠር
ተምረው ሀገራቸውን የሚጠቅሙ ትውልድ እንዲሆኑ፤ የዳበረ አስተሳሰብ እና አመለካከት እንዲኖራቸው በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን
በሰፋት በመሥራት ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡
ዓለም አቀፍ ተቋማት መንግሥታዊ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ አጋር ድርጅቶች እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ለሕጻናት ትኩረት በመስጠት ተባብረው ለሕጻናት
ተስፋ በመሆን የሀገር ተረካቢ ትውልድ ማፍራት ይገባቸዋል፡፡
በአጠቃላይ ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ሕጻናትን በመልካም አስተዳደግ እና የሥራ ባህል፣ የሚያንጽ፣
ጠቃሚ ክህሎት እና ዕውቀት ለማስተላለፍ የሚረዳ ገንቢ የሥራ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ በማድረግ ፤ የመማር ሁኔታ የማይገድብ እና
ለጤና ጉዳት የማይዳርግ ሥራ በማሠራት ግዴታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡
ይህ ሲሆን ሕጻናት በሚፈለገው መንገድ አደገው የሀገሪቱ ተስፋ ትውልድ በመሆን ለሀገርም ሆነ ለወገን የሚጠቀሙ ይሆናሉ፡፡ ለዚህ
ትልቅ ዓላማ ደግሞ ሁሉም ዜጋ የራሱን ኃላፊነት መወጣት ይገባዋል፡፡
No comments:
Post a Comment