Sunday, 1 January 2017

ጥልቅ ተሃድሶው የበፊቱን የሚያጠናክር ነው!




                                                         
                                                        ዘአማን በላይ
አንዳንዴ ቆም ብዬ ሳስብ ኢህአዴግ ራሱን እንደ ተማሪ የሚቆጥር ይመስለኛል። አዎ! የድርጅቱን የትናንት ጉዞ ከዛሬ ጋር አጣምሮ የሚመለከት ማንኛውም ሰው ኢህአዴግ ከራሱና ከዓለም ወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር እያጣመረ በመመማር ዛሬ ላይ መድረሱን መገንዘቡ የሚቀር አይመስለኝም። በዚህ የድርጅቱ ሂደት ውስጥ ሊጠቀስ የሚችለው ዋነኛው ጉዳይ የተሃድሶ መስመሩ ነው።
ትናንትን ከዛሬ ጋር ስናንሰላስለው መታደስ ለኢህአዴግ አዲስ አለመሆኑን መረዳት ብዙም የሚከብድ አይደለም። በዚህ ፅሑፌ ላይ ብዙም ሳንርቅ የድርጅቱን ሁለት ተሃድሶዎችን በድርበቡ ለማንሳት እሞክራለሁ— በ1993 ዓ.ም እና በአሁኑ ወቅት እያካሄደ ያለውን ጥልቅ ተሃድሶዎችን። እዚህ ላይ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው ጥልቅ ተሃድሶ ያለፈውን ማጠናከር መገንዘብ ይገባል።
እንደሚታወቀው በሀገራችን ረጅም የፖለቲካ ሂደት ወስጥ የብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን ፍትሐዊ የዘመናት ጥያቄዎችን አንግቦና ከአምባገነኖች ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ እንዲሁም የህይወትና የአካል መስዕዋትነትን ከፍሎ በአሸናፊነት የድል ፅዋን ያነሳው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ታሪክ በተሃድሶ ውስጥ ያለፈ ነው።
የዛሬ 16 ዓመት ገደማ ድርጅቱን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ሊያመሩ የሚችሉ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የትምክህትና የጠባብነት የዝቅጠት አደጋዎችን በተካሄደው ተሃድሶ ችግሩን መቅረፍ ችሏል። የህዝቡን ሁለንተናዊ ዕድገት ሊያሳልጡ የሚችሉ ዙሪያ መለስ ስትራቴጂዎችም በመንደፍም ዛሬ ለምንገኝበት አስተማማኝ ሰላም፣ ዘላቂ ልማትና ስር የሚሰድ ዴሞክራሲ ዕውን እንዲሆን ተደርጓል።
በእኔ እምነት ይህ የድርጅቱ ተሃድሶ ሀገራችንን አሁን ላለችበት የዕድገት ጎዳና ያበቃት ነው። በወቅቱ በአንድ በኩል ስልጣንን የኢኮኖሚያዊ ሃብትና የብልፅግና መሳሪያ በማድረግ ፀረ-ዴክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት በሚሹ ወገኖች፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስልጣን የሃብት ምንጭ እንዳይሆን፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ እንዲያብብና እንዲዳብር ብሎም የጥገኝነት አስተሳሰብ የበላይነት እንዳያገኝ በሚተጉ ኃይሎች መካከል ከፍተኛ ግምገማና የመድረክ ትግል መካሄዱን እናስታውሳለን።
ታዲያ በድርጅቱ ውስጥ ተፈጥረው በነበሩት በእነዚህ ሁለት ፅንፍ አመለካከቶች ዙሪያ በተካሄዱ ግምገማዊ የሃሳብ ፍጭት፤ ስልጣን የጥቂቶች የሃብት ማካበቻ እንዳይሆን እንዲሁም ዴሞክራሲና ዴክራሲያዊ አንድነት እንዲጎለብት ብሎም የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ውስጥ የበላይነት እንዳያገኝ የታገለው ወገን ነጥሮ በመውጣት ተሃድሶው ግቡን መትቷል፤ ውጤትም አምጥቷል።
እንደ እውነቱ ከሆነ በወቅቱ እንዲህ ዓይነቱ የተሃድሶ ርምጃ በድርጅቱ ውስጥ ባይካሄድ ኖሮ፤ ሀገራችን የምትመራባቸው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም ስልቶች ባልተነደፉ ነበር። በድርጅቱ ውስጥ አቆጥቁጦ የነበረው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብም በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ ጋር አብሮ ባልከደሰመ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም በአንደኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕድገት የተገኘው ሁለንተናዊ እመርታ አይታሰብም ነበር። ሁለተኛ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕድገት ዕቅድም ሊታለም አይችልም። ከሁሉም በላይ ለህዳሴያችን ጉዞ የመረባረብ ሃሳቡም አይኖረንም ነበር። እናም በወቅቱ የተካሄደው ተሃድሶ ውጤታማ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ ላለንበት ሀገራዊ ቁመና ፈር የቀደደ ነው ማለት ይቻላል። ይህም ራሱን በራሱ እያረመ ለሚሄደው ኢህአዴግ ጠንካራ ትምህርት የሰጠው ይመስለኛል።
ኢህአዴግ በዚህ የተሃድሶ ዘመን የቀመረው ትምህርት ለወቅቱ ብቻ አልነበረም። ከትናንት ዛሬ የሚማርበት መድረክ እንጂ። ኢህአዴግ ተሃድሶን ለታይታ የሚያደርግ ድርጅት አይደለም። የዛሬ 16 ዓመት ገደማ የተካሄደው የተሃድሶ መስመር የዚህ አባባሌ ሁነኛ አስረጅ ነው። በወቅቱ ከነበረው ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የተካሄደው ግምገማ ለሀገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት ዋነኛ እንቅፋት የነበሩትን አስተሳሰቦች ማስወገድና አዲስ እሳቤን  ማረጋገጥ ተችሏል።
ይህ ሁኔታም ድርጅቱ በውስጡም ይሁን እንደ ገዥ ፓርቲነቱ በሀገር ላይ ተጋርጦ የነበረውን አደጋ በአስተማማኝ ሁኔታ በማስወገድ ፊቱን ወደ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲያዞር ያደረገው ነው። በተሃድሶው ውጤትም መላው የሀገራችን ህዝቦች ተጠቃሚ ከመሆናቸውም በላይ፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፊት በበጎ ገፅታ ይበልጥ ጎልታ እንድትታይ ያደረጋት ይመስለኛል። የምትከተለው በሳል የዲፕሎማሲ መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነቷን ከማረጋገጥ ባሻገር፤ ለጎረቤቶቿ ህዝቦች የሰላም ጠባቂ፣ መጠጊያና መጠለያ ሆናለች። ከራሷ አልፋ ለሌላው ተርፋለች።
እርግጥ በ1993 ዓ.ም ከተካሄደው ተሃድሶ ኢህአዴግ ውጤታማነትን አትርፏል። ይህ ውጤት ግን አሁንም በሂደት ሊጎለብቱ በሚችሉ ጉዳዩች ሳቢያ በብዙ ጥረቶች መታጀብ ይኖርበታል። ዛሬም እንደ ትናንቱ የመንግስት ስልጣንን ለግል ጥቅም የማዋል ዝንባሌና አስተሳሰብ ብሎም የህብረተሰቡን እርካታ ያለመፍጠር ችግር ብርቱ ችግር ሆነዋል። እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም ገዥው ፓርቲ በጥልቅ ተሃድሶ መስመር የመጓዙ ትክክለኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይመስለኝም። እናም ከ16 ዓመት በኋላ ጥልቀት ባለው ሁኔታ እታደሳለሁ ማለቱ ከሂደት እንደሚማርና ውጤቱም ምን ሊሆን እንደሚችል ስለሚያውቅ ይመስለኛል።
ኢህአዴግ ዳግም በመታደስ ሂደት ውስጥ ራሱንና የመንግስት አሰራሮችን ሲፈትሽ መነሻውም ሆነ መድረሻው ስር ነቀል ለውጥን ማዕከል ያደረገ መሆኑን ብግልፅ እየተናገረ ነው። አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት “አለባብሰው ቢያርሱ፤ በአረም ይመለሱ” ዓይነት አይደለም። በእኔ እምነት መንግስት ከህዝቡ ጋር የተጀመራቸው የውይይት መድረኮች ለዚህ ትግበራ ዓይነተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው።
እነዚህ መድረኮች መንግስትንና ህዝቡን በቀጥታ ፊት ለፊት የሚያገናኙ እንዲሁም ያሉትን ችግሮች ከዋነኛ ተዋናዩ ማግኘት የሚያስችሉ በመሆናቸው ለስር ነቀል አፈታቱ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ በመሆናቸው መቀሜታቸው የጎላ ነው። የችግሮቹን ትክክለኛ መንስኤዎች በተገቢው መንገድ ለማወቅ፣ አውቆም ለመረዳትና የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት መንግስት ወደ ታች ወደ ህብተሰቡ ውስጥ የሚያወርዳቸው መድረኮችም ይጠናከራሉ። የውይይቶች መጠናከር ደግሞ የታሰበውን የተሃድሶ ንቅናቄ ከግቡ የሚያደርሰው መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ይመስለኛል።
እርግጥ ውይይቶች ሁከትንና ብጥብጥን ለራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ መጠቀሚያ ለማድረግ ለሚሹ ኃይሎች የራስ ምታት ይሆናሉ። እናም ውይይቶቹንና ለውይይቶቹ መነሻ የሆነውን ጥልቅ ተሃድሶ በሁከት ሃይሎቹ አማካኝነት “አይሳካም” በማለት የሚነዛው አሉባልታ ብዙም የሚደንቅ አይሆንም። ያም ሆኖ የሁከት ኃይሎቹ በህዝቡ ውስጥ ውዥንብርና አሉባልታ በመንዛት ውይይቶቹን ለማደናቀፍ ለመጣር ቢሞክሩም ህዝቡ ራሱ የሰላሙ ባለቤት በመሆኑ ለቅጥፈታቸው ቦታ አልሰጣቸውም።
ምናልባት ‘ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል’ የሚባለው እውነት የሚመስላቸው ወገኖች ካሉ ነገር ገዥው ፓርቲ ዛሬም እንደ ትናንቱ ቃሉን የማያጥፍና ሁሌም የሚያካሂደው ተሃድሶ በውጤት የሚታጀብ መሆኑን ማስረዳት የሚገባ ይመስለኛል። ይህ ዕውነታም ለህዝቡ በጥልቅ ተሃድሶው ውይይትች ላይ በግልፅ መብራራት ያለበት ይመስለኛል። የሁከትና የትርምስ ኃይሎች የሀገራችንን ዕድገትና ብልፅግና የማይሹ አንዳንድ የውጭና የውስጥ ሃይሎች እንጂ ከየትኛውም ብሔርና ህዝብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው መሆኑንም ህዝቡ አሁን ካለው ግንዛቤ በላይ ይበልጥ ማስረፅ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።
እርግጥ በአሁኑ ወቅት መንግስት እያካሄደ ባለው ጥልቅ ተሃድሶ ሳቢያ ዘና ብሎ ተግባሩን እያከናወነ ነው። በአማራና በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በተከናወኑ አጥፊ ተግባራት ላይ የተሳተፉ ጥቂት ወጣቶች በኮማንድ ፖስቱ አማካኝነት ተገቢው የተሃድሶ ትምህርት ተሰጥቷቸው ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉ የዚህ ተጨባጭ ሁኔታ መገለጫ ይመስለኛል። በሁከት ሃይሎች የውሸት የተቀናጀ ፕሮፖጋንዳ አማካኝነት የተካሄደው ተግባር ህዝቡን መልሰው የሚጎዱ መሆናቸውን የተሃድሶ ትምህርቱን የወሰዱት ወጣቶች ሲናገሩ ተደምጧል። እናም ይህ መሰሉ ተግባር ዳግም እንዳይፈጸም ጥልቅ ተሃድሶው ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ሊካድ አይገባም።
ኢህአዴግ ትናንትም ይሁን ዛሬ ያከናወናቸውና የሚያከናውናቸው ተሃድሶዎች ተጨባጭ ውጤቶችን ያመጡ ናቸው። ገዥው ፓርቲ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው የተሃድሶ ሂደት የመንግስት መዋቅሮችን የህዝቡን እርካታ በሚፈጥሩ መንገድ እያከናወነ ነው። ይህ ሁኔታም ከዚህ ቀደም በነበሩ የተሃድሶ መንገዶች የተከናወኑ ተግባራትን የሚያጠናክርና ይበልጥ የሚያሰርፅ ነው። ገዥው ፓርቲ ለያዘው ቁርጠኛና ውጤት ሊያመጣ የሚችለው ጥልቅ ተሃድሶ ሁሉም የበኩሉን ጠጠር ቢወረውር የሚፈለገው ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል ባይ ነኝ።

No comments:

Post a Comment