Tuesday, 3 January 2017

ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የተቀናጀ የወጣቶች ተሣትፎ ወሳኝ ነው!




ኃይለማሪያም ወንድሙ
 ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ጥንታዊት እና ራሷን ከውጪ ወራሪዎች ተከላክላ ከአፍሪካ ሀገሮች ሁሉ ነፃነቷን ጠብቃ የቆየች ሀገር ብትሆንም ዜጎቿ በተለይም ወጣቶችዋ ግን ለዘመናት እየተፈራረቁ ይገዟት በነበሩት አምባገነናዊ አገዛዞች መብቶታቸው እየተረገጠ ሲማቅቁ ኖረዋል። የኢትዮጵያ ወጣቶች ዘውዳዊዩን እና አምባገነናዊዩን አገዛዞች ለማስወገድ የተለያዩ አማራጮችን ለመጠቀም ሞክረዋል። በዚህም ምክንያት በርካታ ወጣቶች መስዋዕትነት ከፍለዋል።
ወጣቶች የሀገሪቱን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ለማስወገድ፣ መብታቸውን ለማስከበር እና የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ መብቶች፣ ፍትሐዊ የሀብት ተጠቃሚነት፣ በማንነታቸው እንዲኮሩ የማስቻል ክቡር ዓላማቸውን ለማሳካት በጋራ ሠርተዋል። ዘመናዊ የትምህርት ተቋማት የሉም ማለት በሚቻልበት በዚያን ዘመን ለውጥ ፈላጊ የሆኑት ወጣቶች በዕደ ጥበብ እና በግብርና ሥራ ተሠማርተው የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማንቀሳቀስ ከመጣራቸውም ባሻገር በተለያዩ ወቅቶች ሀገራቸውን ለመውረር ድንበር ጥሰው ከመጡ የውጪ ወራሪዎች በመከላከልም ረገድም ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክተዋል።
ከኢትዮጵያ ወጣቶች እንቅስቃሴ አንፃር ጎልቶ የሚነገረው በ1960ዎቹ የቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርሲቲ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ተማሪዎች አገዛዙን በመቃወም የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሣት ተንቀሳቅሰዋል። “መሬት ለአራሹ“ የሚለውን መፎክር በመያዝ ንጉሡ ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ ተደጋጋሚ የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል። በዚህም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘር፣ በሃይማኖት፣ በኢኮኖሚ ደረጃ ሳይከፋፈሉ አርሶ አደሮችን ጨምሮ በትግሉ እንዲሳተፉ እና ከጎናቸው እንዲሰለፉ አድርገዋል።
ይሁን እንጂ እየተደረጉ የነበሩ የወጣቶች፣ የታክሲ ሹፌሮች፣የምሁራን እና የአርሶ አደሮች ተቃውሞዎችን እንደምቹ አጋጣሚ ሲጠብቁ የነበሩ ከየሠራዊት ክፍሉ የተውጣጡ ጥቂት መለዮ ለባሾች ንጉሡን ገልብጠው አመራሩን ተቆጣጠሩ። ከዚያም በወጣቶች ተቃውሞ ሲነሱ የነበሩ የ“መሬት ለአራሹ” እና የከተማ ቦታ እና ትርፍ ቤት ለመንግሥት የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በመመለስ ለጊዜውም ቢሆን የወጣቶቹን ጥያቄ ለማደፋፈን ሞክረዋል።
ምንም እንኳን ራሱን ደርግ ብሎ የሰየመው የወታደራዊ መንግሥት የወጣቶቹ እና የሕዝቡ ጥያቄ ተጠቅሞ ዘውዳዊዩን አገዛዝ ቢያስወግድም “ትሻልን ትቼ ትብስን“ እንደሚባለው ሆኖ የወታደሮቹ አገዛዝ የባሰ አምባገነን እየሆነ መጣ። በመሆኑም የደርግ መንግሥት መጀመሪያ በሥልጣን ሽኩቻ እርስ በርስ ከተገዳደለ በኋላ ሥልጣኑን የተቆጣጠረው አካል በአብዮታዊ ርምጃ ሰበብ አምራች የሆነውን ወጣት በመግደል እንዲሁም በወቅቱ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለነበሩበት ጦርነቶች እና በአፈሳ ለጦርነት በመማገድ ደማቸው በከንቱ እንዲፈስ፣ ሕይወታቸው በከንቱ እንዲጠፋ አድርጓል። ይህም ሕዝቡ እንዲያዝን ወጣቱ ኃይልም ከቤተሰቡ ተለይቶ የተወሰነው ወደ ባዕዳን ሀገር ሲሰደድ ከፊሉ ከሥርዓቱ ጋር ተወዳጅቶ በወገኖቹ ላይ የሚደርሰው ግፍ እና መከራ መሣሪያ ሰሆን፤ ከፊሉም በወቅቱ በተለያየ አግባብ ተደራጅተው መሣሪያ አንስተው ወደነበሩ አማጽያን ኃይሎች በመቀላቀል ወታደራዊዩን አገዛዝ በትጥቅ ትግል በመፋለም እና ገርሥሦ በመጣል የበኩሉን አስተዋፅዖ አበርክቷል። 
ወጣቶች በዓለም ላይ ለሚካሄዱ የልማት እንቅስቃሴዎች ዋልታ እና ማገሮች ቢሆኑም፤ በየሀገራቱ በወጣቶች ላይ ያተኮሩ ፖሊሲ በማርቀቅ እና በማጽደቅ መተግበር የተጀመረው ግን እረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ አይደለም። በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1995 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ  “ የዓለም ወጣቶች የድርጊት መርሐ ግብር በ2ሺህ ዓመት እና ከዚያ በኋላ ” በሚል አፀደቀ። ይህን ተከትሎም ከሁለት አሥርት ዓመታት በኋላ በወጣቶች ፖሊሲዎች ላይ ያተኮረ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ፎረም በአዘርባይጃን ሀገር ባኩ ከተማ ተካሄደ። በፎረሙም ቀደም ሲል በወጣቶች ፖሊሲ ዙርያ የነበሩ አፈፃፀሞችን በመርመር የወጣቶች ፖሊሲዎችን ወደ ሚቀጥሉት ዘመናት ለማሸጋገር የሚያስችል ውይይት ተደርጓል። በወጣቶች ጉዳይ ላይ የተካሄደው ይህ ፎረም የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ተወካይ በተገኙበት በተመድ የልማት ፕሮግራም፣ በተመድ የሣይንስ የትምህርት እና የባህል ድርጅት በአውሮፓ ካውንስል እና በአዘርባይጃን መንግሥት አማካይነት ሲሆን፤ ከተለያዩ ሀገሮች የተውጣጡ ወጣቶች ኤክስፐርቶች ሠራተኞች፣ የመንግሥታት ተወካዮች እና ምሁራን ተካፍለውበት ነበር።
በወቅቱ የወጣቶች ፖሊሲ ወጣቶችን በማብቃት እና በማካተት መሥራት ተግዳሮት ወይም ውጣ ውረድ ቢኖረውም እንኳ ውጤታማ መሆኑ ተገልጿል። ይህን ለመፈፀም ቀጣይነት እና ሕጋዊነት ያለው አሠራር እንዲሰፍን ተጠይቆ ነበር።
የአፍሪካ ኅብረትም በበኩሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ “ የዓለም ወጣቶች የድርጊት መርሐ ግብር በ2ሺህ ዓመት እና ከዚያ በኋላ ” ካፀደቀው ፖሊሲ በመነሳት በሰኔ 2006 እ.ኤ.አ. የወጣቶችን ቻርተር አፅድቋል። የዚህም ቻርተር ግብ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የሚታየውን የወጣቶች የልማት ተሣትፎን ከፍ ለማድረግ እና ለመደገፍ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በኅብረቱ አማካይነት “የወጣቶች የአሥር ዓመት የድርጊት መርሐ ግብር 2009_2018 ” (road map) ማለትም ፍኖተ ካርታ በማርቀቅ በኅብረቱ የፀደቀውን የወጣቶች ቻርተር ዕውቅና ለመስጠት  እና ለመተግበር የሚረዳ ውሳኔ ተወስኗል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ120 በላይ ሀገሮች የወጣቶች ፖሊሲዎችን በማርቀቅ እና በማፅደቅ በመተግበር ላይ ይገኛሉ። በኢፌዴሪ መንግሥት 2004 ዓ.ም ላይ የፀደቀው የወጣቶች ፖሊሲ ለትምህርት፣ ለሥራ እና የሚያነሳሳ በሀገሪቱ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች እንዲሳተፉ እና በተሣተፉት ልክ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ የሚያበረታታ እና ፈር ቀዳጅ በመሆኑም ጭምር በቀድሞዎቹ ዘውዳዊ እና ወታደራዊ አገዛዞች ትኩረት እና ቦታ ያልተሰጠውን ወጣት ለማብቃት ብሎም ወደ ሥራ ለማሠማራት የሚያግዝ ነው።
ከደርግ ውድቀት በኋላ የወጣቶች ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት በተለያዩ ሚኒስትሮች አማካይነት (የባህል ወጣቶች እና ስፖርት በኋላም በሴቶች ሕፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር) አሁን ደግሞ ወጣቶች እና ስፖርት በሚል አደረጃጀት ተዋቅሮ በንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚስትር አቶ መለስ ዜናዊ በ1997 ዓ.ም. ከሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ለተውጣጡ ከ7ሺህ በላይ የሚሆኑ ወጣቶችን ሰብስበው በማወያየት እና ከወጣቶቹ የተነሱትን ጥያቄዎች በመመለስ በወቅቱ መንግሥት ለወጣቶች ሰጠውን ትኩረት አስረድተዋል። በዚሁ ጉባኤ ላይም ብሔራዊ የወጣቶች ካውንስል እንዲቋቋም ተደርጓል።
መንግሥት የወጣቶችን ፖሊሲ ካወጣ በኋላ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንፃር በጥቃቅን እና አነስተኛ ዘርፎች እንዲሠሩ ሥልጠናዎች በመስጠት እና የሥራ ቦታዎችን እና ለሥራዎቻቸው የመነሻ የሚሆን ብድር የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት እንዲሁም የገበያ ዕድላቸውን ሊያስተሳስሩ የሚችሉበትን ሁኔታ በማመቻቸት ረገድ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ ቆይቷል። በመሥራትም ላይ ይገኛል። በመሆኑም ዘርፉ ሀገራችን በተከታታይ እያስመዘገበችው ባለ ሁለት አሃዝ ኢኮኖሚዊ ዕድገት አዎንታዊ አስተዋፅዖ በማበርከት ላይ ይገኛል። በተለይ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በአነስተኛ እና በጥቃቅን የልማት ዘርፎች ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ አንቀሳቃሾች የገንዘብ ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከዚህ በተጨማሪም በዘርፉ የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎችን እና ልምዶችን በመቀመር፤ ግንዛቤያቸውን ለማሳደግ የሚያስችሉ የቴክኒክ ድጋፎችን በመስጠት ወጣቱን የማብቃት ተግባራት በመንግሥት እና ባለ ድርሻ አካላት ሲከናወን ቆይቷል። 
ከዚህ በተጨማሪ በኮንስትራክሽን ልማት ዘርፍም (የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ የአስፋልት መንገዶች ግንባታ እና በባቡር መንገድ ዝርጋታ ሥራዎች) በኢንቨስትመንት ማለትም የተለያዩ ፋብሪካዎች እና ከሀገር አቀፍ እስከ ባለ ኮከብ ሆቴሎች ግንባታዎች በዕደ ጥበብ እና በፈጠራ ሥራዎች እንዲሁም በግብርና ልማት ዘርፎች በከተሞች ጭምር ወጣቶች ተጠቃሚ በሚሆኑበት ዕድል በመመቻቸቱ በርካታ ወጣቶች ተጠቃሚ በመሆን ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ከመጥቀም ባሻገር በሀገር ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ የራሳቸውን አሻራ ማስቀመጥ የሚችሉ ሆነዋል።
ወጣቶች በኢንቨስትመንት ሆነ በመንገዶች ግንባታ በጌጠኛ መንገዶች (ኮብል ስቶን) በጊዚያዊነት ተቀጥረው ካደረጉት አስተዋፅዖ በተጨማሪ ግንባታዎቹ በተለይም ፋብሪካዎች እና ሆቴሎች አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ በኋላ ለብዙ ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል ከፍተዋል።
በመንግሥት ብቻ ሲሠራበት የነበረው የባንክ እና የመድህን ዘርፍ ለግል ባለ ሀብቶች በመፈቀዱም በሙያው ብቃት ያላቸው ብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል አግኝተው ተጠቃሚ ሆነዋል። ለሀገሪቱ ኢኮኖሚም አስተዋፅዖ ያለው ሥራ በመሠራት ላይ ይገኛሉ።
በተጠናቀቀው የመጀመሪያው የዕድገት እና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ዓቅም የሚያሳድጉ እና ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች ተሠተዋል። በልማት ዕቅዱ የወጣቶችን ፓኬጅ አጠናክሮ ተግባራዊ በማድረግ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ተሣትፎ እና ተጠቃሚነት ዕድሎች እንዲሰፉ እና እንዲጠናከሩ ተደርጓል። በሁለተኛው የዕድገት እና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመንም (2008-2012 ዓ.ም) የወጣቶችን አደረጃጀት በማጠናከር ሥራ አጥነትን ለመቀነስ ታቅዷል። ከዚህ አንፃር በመጀመሪያው ዕትዕ ዘመን ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ወጣቶች በጥቃቅን እና አነስተኛ የገቢ ማስገኛ ዘርፎች በመጀመሪያው ዕቅድ ተጠቃሚ ሆነዋል።
ምንም እንኳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ሁከቶች እና ግርግሮች ቢታዩም፣ መንግሥት ወቅታዊ የሀገሪቱን ትኩሳት ተመልክቶ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት ጥልቅ ተሐድሶ በማድረግ ላይ ይገኛል።
መንግሥት የሀገሪቱን ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ 10 ቢሊዮን ብር ተንቀሳቃሽ ፈንድ እንደሚመደብ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ም/ቤቶችን የመክፈቻ ንግግር በማድረግ የመንግሥት የ2009 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድን ባስተዋወቁበት ወቅት መግለፃቸው የሚታወስ ነው። ይህን የአሥር ቢሊዮን ብር ሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችል የአጠቃቀም መመሪያ ወይም የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑንም መንግሥት አሳውቋል።
በአጠቃላይ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የተቀናጀ የወጣቶች ተሣትፎ ወሳኝ ነው በሚል ርዕስ በቀረብኳት በዚች አጭር መጣጥፍ ለማለት የፈለግሁት ድህነትን ጥሎ ልማትን አንግቦ ለመጓዝ በሀገሪቱ ያሉ ወጣቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ነው። በመሆኑም ወጣቶች ሀገራቸውን ለማሳደግ እና ለመለወጥ ከሱሰኝነት ፀድተው በማኅበራዊ ሚድያ የሚሠራጩ አሉባልታዎችን እና ተጨባጭነት የሌላቸው ወሬዎችን አስወግደው ከመንግሥት ጋር እጅ ለእጅ ተያያዘው ለለውጥ ሊተጉ ይገባል።

No comments:

Post a Comment