ሳህለ ማርያም
ወጣትነት በሕፃንነት
እና በጎልማሳነት ዕድሜ ክልል መካከል ያለ ዘመን ነው፡፡ የወጣትነት የዕድሜ ክልል በአብዛኛው ከ14
- 29 ዓመት የሚይዝ ሲሆን፤ ይህ የዕድሜ ክልል ወጣቶች ፍፁም ጎበዝ የሚሆኑበት፤ ታግለው የሚጥሉበት፤ ሮጠው የሚያመልጡበት ነው፡፡ ወጣትነት ዛሬ ላይ ሆኖ ለነገ መሠረት የሚጣልበት ጊዜ ነው፡፡
ሆኖም በደርግ መንግሥት እና ከእሱ በፊት በነበሩት
ሥርዓቶች ወጣቶች በወጣትነት ዕድሜያቸው ሊኖሩት የሚገባውን ጣፋጭ የትምህርት፣
የሥራ፣ የልማት ጊዜያቸውን በአግባቡ ማጣጣም አልቻሉም ነበር።
በእነዚያ ዘመናት ለወጣቶች ይቀርብላቸው የነበረው አማራጭ አንድ
እና አንድ ብቻ ነበር፡፡ “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” ፡፡ በመሆኑም ወጣቱ ባላመነበት እና ያለፍላጎቱ፤ በግድ በውትድርና ሙያ
ላይ ብቻ እንዲሰለፍ ይደረግ ነበር፡፡ በግዳጅ እና በአፈና ይመለመል የነበረው ያ ትኩስ ኃይል በቀጥታ ለጦርነት ይማገድ ስለነበር፤
በብዙ ሺህ የሚቆጠር ወጣት መስዋዕትነት ከፍሏል፤ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች አካል ጎድሏል፤ ለቁጥር የሚታክት
ዜጋ ደግሞ ለእስር እና እንግልት ተዳርጓል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በወቅቱ ተሸመድምዶ በነበረው ኢኮኖሚ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ለሥራ አጥነት በመዳረጋቸው
ዱር ገደሉን ቧጠው እና በረሐ አቋርጠው ወደ ተለያዩ ሀገራት ተሰደዋል፡፡ በተለያየ መስክ ሀገሪቱን ሊጠቅሙ የሚችሉ ወጣት ምሁራንም
ይፈጸም የነበረውን ግፍ እና በደል መሸከም አቅተቷቸው ወደ አውሮፓ፣ አሜሪካ እና የተቀረው ዓለም ክፍል እንደ ጨው ዘር ሊበተኑ
ችለዋል፡፡
ዛሬ ዛሬ
በኢትዮጵያ ውስጥ ሠርቶ መለወጥ የሚፈልግ ሁሉ የተለየ የንብረት እና የሕይወት ወይም የአካል መስዋዕትነት ሳያሳፈልገው መሥራት፣
ማግኘት፣ መለወጥ እንዲሁም የሀብት እና ዝና ጫፍ ላይ ለመቀመጥ ይችላል፡፡ ዛሬ ጦርነት የለም፤ ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር የሚል
መፈክር የለም፤ ቀይ ሽብር ነጭ ሽብር የሚል የሞት አዋጅ የለም፤ ወጣት በየስርቻው እንደአይጥ የሚሸጎጥበት ሁኔታም የለም፡፡ በዚህ
ምትክ ሁሉም ነገር ወደ ልማት፣ ሁሉም ነገር ወደ ዕድገት፤ ሁሉም ነገር ወደ ህዳሴ በሚል ተቀይሯል፡፡ ለዚህ ደግሞ መሠረቱ ያለው
መንግሥት የተከተለው የልማት አቅጣጫ ነው፡፡ ይህን እውነታ ለማረጋገጥ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መሠረት በማድረግ በመንግሥት የወጡትን
ዕቅዶች፣ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች እና መመሪያዎችን መመልከት በቂ ነው፡፡
እነዚህ ዕቅዶች፣
ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች መሠረታዊ ዓላማ ያደረጉት፤ የሀገሪቱን ቀጣይ ዕድገት ማረጋገጥ እና ዜጎችም በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን
ዕድል መፍጠር፤ ብሎም ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል የማስፈን አቅጣጫ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት በርካታ መሠረተ ልማቶች ተዘርግተዋል፣ የተለያዩ
ትላልቅ እና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ተቋቁመዋል፣ በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶችም ተገንብተዋል፡፡ እነዚህን ሁሉ ስናስብ የዚህ ሁሉ ሀገራዊ
ልማት አንቀሳቃሹ ወጣቱ ነው፡፡ ሁሉንም የሙያ ዘርፎች ወጣቶች ያንቀሳቅሰሷቸዋል፤
ገቢ በማግኘትም ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን በመርዳት በሀገር ዕድገት ላይ የራሳቸውን ድርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ።
ከዚህ በተጨማሪ
መንግሥት የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በአነስተኛ እና ጥቃቅን ልማት ዘርፍ ላይ ተሠማርተው ቤተሰቦቻቸውን ጭምር
በተመቻቸ የኑሮ ሁኔታ ላይ አስቀምጠዋል፡፡ ብዙዎችም ከጥቃቅን እና አነስተኛ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ባለቤትነት ተሸጋግረዋል፡፡
ለዚህ ማሳያ
የሚሆን ወጣት ላስተዋውቃችሁ። ናትርሼህ አሚን ይባላል፡፡ ዕድሜው በሰላሳዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ የሚኖረው በጅማ ከተማ
ነው፡፡ በጊቤ III የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት መሥራት ከጀመረ ሰባት ዓመታትን እንዳስቆጠረ ይናገራል፡፡ ይህ ወጣት ባለቤቱን
እና አራት ልጆቹን ጨምሮ የ8 ቤተሰብ አስተዳዳሪ ነው፡፡ እናት፣ አባቱ እና አንዲት የአሥረኛ ክፍል ተማሪ የሆነች ታናሽ እህቱ
ከእርሱ ጋር ይኖራሉ፡፡ ከሰባት ዓመት በፊት የነበረ ታሪኩን ሲተርክ ሁለቱም ዓይኖቹ እንባ እንዳንቆረዘዙ ነበር፡፡
ቀደም ሲል
አባቱ በግል ሥራ ይተዳደሩ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ እናቱ ምንም ዓይነት ገቢ የላቸውም፡፡ እሱ እና እህቱ በዚያው በጅማ ከተማ
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ይከታተሉ እንደነበር ይናገራል፡፡ ሆኖም አባቱ ባጋጠማቸው ሕመም ምክንያት የቤተሰቡ ገቢ ተቋረጠ፡፡
በቤት ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ ነገር ጠፋ፡፡ በመሆኑም የስምንተኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ ቤተሰቡን የሚያስተዳድርበት የእለት ገቢ
ማፈላለግ ነበረበት፡፡
በመሆኑም
በአንድ የአካባቢው ነዋሪ በሆነ ግለሰብ ዘንድ የአናፂ ረዳት ሆኖ ተቀጠረ፡፡ ናትርሼህ እንደሚለው ይህች የሚያገኛት ገቢ ቋት እንኳ
የምትሞላ አልነበረችም፡፡ ኑሮው እጅግ የተጎሳቆለ እና አሳዛኝ ነበር፡፡ ቤተሰቡን በዚህ ሁኔታ ማኖር እንደማይችል ስለተረዳ ግራ
ቀኙን መመልከት እና ሰዎችንም ማማከር ጀመረ፡፡
አንድ ቀን
ችግሩን ያወያየው አንድ ወዳጁ፤ የጊቤ III የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በርካታ ሠራተኞች እንደሚፈልግ እና በተለይ እንደ
እርሱ ዓይነት ሙያ ላላቸው ዜጎች ሠፊ ዕድል እንደሚሰጥ ነገረው፡፡
የቤተሰቡ
እና የእርሱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል እንቅልፍ የነሳው ወጣት ይህን ዕድል ለመጠቀም አላንገራገረም፡፡ ማቄን ጨርቄን
ሳይል ቋጥሮ ያስቀመጣትን ሁለት መቶ ብር ይዞ ወደ ደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ተጓዘ፡፡ እዚያም እንደደረሰ አካባቢውን
አጠያይቆ መደበኛ ሥራውን ጀመረ፡፡
ሥራውን በጀመረ
በወሩ ለቤተሰቦቹ አንድ ሺህ ብር ሲልክ እንደተዓምር እንደቆጠሩት ይናገራል፡፡ ከዚህ በኋላ ሥራውን በትጋት እና በታላቅ ፍቅር እያከናወነ
በርካታ ጥሪት መቋጠር እና በዚያው ተወልዶ በአደገበት ጅማ ከተማ 96 ቆርቆሮ የፈጀ ትልቅ ቤት መሥራት ችሏል፡፡ ትዳር እና የሞቀ
ጎጆ ሊመሠርት የቻለውም ይህን ሥራ ከጀመረ በኋላ እንደሆነ ናትርሼህ ይናገራል፡፡
ይህ ወጣት
እንደሚለው ቀደም ሲል ከተቀጠረበት ሙያ በተጨማሪ የግንበኝነት ሥራ መልመድ እንደቻለ እና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ማለትም ፕሮጀክቱ
እስከተጠናቀቀበት ወቅት ይህንኑ ተግባር ያከናውን እንደነበር ገልጿል፡፡ ይህ ወጣት እንደሚለው የውጭ ሀገር ዜጎችን ጨምሮ ወደ ስምንት
ሺህ የሚጠጉ ዜጎች የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት በወጣትነት ዕድሜ ክልል የሚገኙ
ናቸው፡፡ እንደእርሱ አባባል እነዚህ ወጣቶች የኢኮኖሚ አቅማቸው ማደጉ ብቻ ሳይሆን፤ የቴክኖሎጂ እና ዕውቀት ሽግግር መኖሩ እንዲሁም
ከተለያየ ክልል የተለያየ ባህል እና እሴቶቻቸውን መለዋወጥ መቻላቸው በምንም ነገር ሊተመን የማይችል ሀብት ነው፡፡
ወጣቶች የአፍላ
ጉልበት፣ ዕውቀት ባለቤት በመሆናቸው በሀገር ሁለንተናዊ ለውጥ ላይ የሚያበረክቱት ሚና ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ይህን ወሳኝ ኃይል
በተገቢው መንገድ አልምቶ ሥራ ላይ ማዋል ሀገሪቱ በ2017 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የያዘችውን ራዕይ ለማሳካት
የወጣቱ ድርሻ ወሳኝ ስለሆነ፤ መንግሥት ወጣቶችን ለማትጋት የያዘውን ዕቅድ መተግበር አለበት። ከዚህ በተጨማሪ ከወጣቶች ጋር በቀጥታም
ሆነ በተዘዋዋሪ ግነኙነት ያላቸው አካላት ሁሉ ሥኬታማ ወጣት ምሁር፤ ባለሀብት፣ ሥራ ፈጣሪ ለማነጽ የበኩላቸውን ድርሻ ባበርከት
ይጠበቅባቸዋል።
No comments:
Post a Comment