Sunday, 1 January 2017

የፅንፈኛው ዲያስፖራ የተሳሳተ ሥሌት…





ወንድይራድ ኃብተየስ 
የኢትዮጵያ የዲያስፖራ ኅብረተሰብ በአገሩ የፖለቲካ ሂደት የመሳተፍና ድጋፍ የመስጠት ሙሉ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ በዲያስፖራው የተፈጠረው አቅም በአገራችን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ ይውል ዘንድ ሁኔታዎች መመቻቸት አለባቸው፡፡ ይህን ለማሳካት በዲያስፖራው መካከል የፖለቲካ ዲያሎግ ማካሄድ ይጠይቃል፡፡

በዲያስፖራው ዘንድ የሚካሄደው የፖለቲካ ዲያሎግ በግል አመለካከት እና በአገራዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ያለውን አንድነትና ልዩነት የተሻለ ግንዛቤ በመፍጠር በአሁኑ ወቅት ያለውን መደበላለቅ ከተቻለ ማስወገድ ካልተቻለ ደግሞ ለመቀነስ ይረዳል፡፡

አንዳንድ ቡድኖችና ግለሰቦች በመንግሥትና በአገር መካከል ያለውን ልዩነትና አንድነት በተመከለተ ግልፅነት እንደሚጎደላቸው ከተግባራቸው ማየት ይቻላል፡፡ ገዥውን ፓርቲ ሲቃወሙ በአገራችን ዘላቂ ጥቅም ላይ ጉዳት ሲያደርሱ ይታያል፡፡ በዲያስፖራው መካከል የሚካሄደው የፖለቲካ ዲያሎግ ይህንን ነገር ለማስወገድ ይጠቅማል፡፡ በማንኛውም ቦታ፣ ጊዜና ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚካሄዱ ውይይቶች የመቻቻልና የዴሞክራሲያዊ እኩልነት መርሆዎችን የተከተሉ መሆን አለባቸው፡፡

ከፅንፈኞች ጋር የፖለቲካ ዲያሎግ ማካሄድ ስለመቻሉ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ፅንፈኞች የግለሰቦች ነፃነት እና መቻቻል የሚለው ነገር የሚዋጥላቸው አይደለም፡፡ ይህም ሆኖ ዴሞክራቶች ተስፋ ቆርጠው ስለማያውቁ ፅንፈኞችን በፖለቲካው መድረክ ለማሸነፍ የፖለቲካው ውይይት  ቀጣይ መሆን አለበት፡፡

በፖለቲካው ሂደት ቁም ነገሩ የመቻቻል እሴት ልዩነቶችን በሠላማዊ ውይይት እያስታረቁ ማስኬድ በመሆኑ ከዲያሎግ ማዕድ ጥሰው የሄዱትን ፅንፈኞች እግር በግር ተከትሎ የፖለቲካ ድንክዬዎች መሆናቸውን ማሳየት ያስፈልጋል፡

የዚህ ፅሑፍ ዓላማ በዲያስፖራው አካባቢ የፖለቲካ ውይይት በማቀጣጠል ዲያስፖራው ከአገሩ ጋር ያለውን ሠላማዊ ግንኙነት ለማጠናከር ነው፡፡ በዲያስፖራው የፖለቲካ ሱታፌ ታሪክ ሂደት ላይ እልባት ያላገኙ መሠረታዊ ጥያቄዎችን አንስቶ የሀሳብ ፍጭት ማካሄድ ተገቢ ነው፡፡

ተዘውትረው ከሚነሱና እስካሁን መግባባት ካልተደረሰባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋነኛው የዲያስፖራው የፖለቲካ ተሳትፎ የውኃ ልክ፣ ቁመትና ወርድ በማወቅ መስመር የማበጀት ጉዳይ ነው፡፡ ከአገር ቤት ርቆ በባዕድ አገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ በአገሩ ፖለቲካ የመሳተፍ መብቱ የተጠበቀ ቢሆንም አርባ ምንጭ ወይም ደሴ እንዳለው ዜጋ እኩል የፖለቲካ ተሳትፎ ለማድረግ ርቀት ይገድበዋል፡፡

ከአገር ቤት እየራቀ በሄደ ቁጥርም ከዕለታዊ ፖለቲካ መነጠሉ ነባራዊ ሁኔታ አይቀሬ ነው፡፡ የአሁኑ ዲያስፖራ እነዚህን ሁለት ተቃርኖዎች አቻችሎ ለማስኬድ የግድ የተሳትፎው ልኬት ላይ ግንዛቤ መያዝ አለበት፡፡ የስደት ዓለም ደራሲ፣ ፖለቲከኛ፣ ከያኒ ውሎ አድሮ እየቀዘቀዘ የመሄድ ተግዳሮት ይገጥመዋል፡፡

ከዲያስፖራ የፖለቲካ ተሳትፎ ታሪክ በመነሳት በባዕድ አገር የተቋቋሙ የፖለቲካ ቡድኖች እና በነሱ የተቀየሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራችን የለውጥ መሣሪያ ሆነው የማገልገል ዕድላቸው ምን ያህል ነው? የሚለው ጉዳይ ራሱን የቻለ ሌላ ጥያቄ  ነው፡፡

በአገራችን የተከሰቱ ለውጦች የተገኙት በአገር ቤት በሕዝብ መሀል በተወለዱ ድርጅቶች ነው፡፡ በዲያስፖራ የተመሩ ወይም የዲያስፖራ ጫና ያላቸው ቡድኖች በአገራችን የፖለቲካ ሂደት የነበራቸውን ሚና ገለልተኛ ሆኖ ትክክለኛ ብያኔ ለመስጠት ጥረት መደረግ አለበት፡፡

ይህ ፅሑፍ በዲያስፖራ የተቋቋሙ የፖለቲካ ቡድኖች በአገራችን ባለው ሂደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የነበራቸው መሆኑን በመጠቆም የአገር ቤት ፖለቲካ ከዲያስፖራ ጫና ነፃ መሆን እንዳለበት ይጠቁማል፡፡ የዲያስፖራው ሚና ከደጋፊነት ያለፈ የመሪነትና ውሣኔ የመስጠት ኃላፊነት ለመሸከም ሁኔታው የማይፈቅድለት መሆኑን ታሪክን በማጣቀስ መፈተሽ ይቻላል፡፡
ይህ ታሪክ ሰፊ ነው፡፡ የባለሙያ ጥናትና ምርምርም ይጠይቃል፡፡ ቢሆንም ከየራሳችን ልምድ እና ተሞክሮ አንፃር አንዳንድ ነጥቦች ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የፖለቲካ ስታፌ የተጀመረው 1960 የተማሪዎች ትግል ጋር ተያይዞ ነበር፡፡

በውጭ አገራት ለትምህርት የተላኩ ወጣቶች በአገር ቤት ሲቀጣጠል የነበረው የፖለቲካ ትግል አካል በመሆን መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበራት አቋቁመው የተሟሟቀ የፖለቲካ ትግል አካሂደዋል፡፡ በአገር ቤት ተማሪዎች  ያነሷዋቸውን መፈክሮች በመቀበል አስተጋብተዋል፡፡ በውጭ የነበሩ የተማሪዎች ማህበራት ከፖለቲካ ፓርቲ ባልተናነሰ የትግል መድረክ ሆነው አገልግለዋል፡፡ የተለያዩ መፅሔቶችን በማሳተም የርዕዮተ ዓለም ትግል ተካሂዷል፣ቻለንጅበመሳሰሉ መፅሔቶች ጥናታዊ ፅሑፎች እና ትንታኔዎች ቀርበዋል፡፡

በዚህም ሂደት ቀስ በቀስ በተማሪዎች መካከል የፖለቲካ ልዩነት ተከሰተ፡፡ የፖለቲካ ትግሉ እየተጠናከረ ሲሄድ አንዳንድ ምሁራንና ተማሪዎች ተጠራርተው ህቡዕ የፖለቲካ ቡድን ማቋቋማቸው ሲሰማ የነበረውን  ልዩነት ይበልጥ አጦዘው፡፡ ይህ ክስተት በተማሪው መካከል ቂምና ጥርጣሬ ፈጠረ፡፡ በመጀመሪያ መኢሶን የተባለ ድርጅት በህቡዕ ሲቋቋም ቆይቶም የኢሕአፓ አስኳል የሆነው ድርጅት በአውሮፓ ተመሠረተ፡፡ የዲያስፖራ ተማሪዎች በሁለት በመከፈል ወዳልሆነ ትንቅንቅ ገቡ፡፡

በየከተማውና በበየማህበሩ አንዱ ሌላውን ያሳድድ ያዘ፡፡ በሁለቱም ድርጅቶች መካከል የነበረው ልዩነትም ለብዙ ወገን ግራ አጋባ፡፡ የፓርቲዎቹ ድርሣናት እንዳስነበቡን የልዩነቱ ምክንያት በአገር ቤት በነበረው የፖለቲካ ቅራኔ አረዳድና አፈታት ላይ ነበር፡፡ ሆኖም አሁን መለስ ብለን ስናየው ሁለቱም ድርጅቶች የአገር ቤቱን ሁኔታ በአግባቡ ለመረዳት ሁኔታው የሚፈቅድላቸው አልነበረም፡፡

የአፄው ዘመን ሲያከትም የፖለቲካ ቡድኖች ቂምና ፀብ ሰንቀው አገር ቤት ገቡ፡፡ አገር ቤት እንደገቡም ቂምና ልዩነቱን ለማስፋፋት ቻሉ፡፡ መኢሶን ከደርግ ጋር በግልፅ ሲያብር ኢሕአፓም ሁለቱንም በእኩል ጠላትነት ፈርጆ ተፋለመ፡፡ ደርግም ቅራኔውን በመጠቀም በአሸናፊነት ወጣ፡፡

በሁለቱ የፖለቲካ ቡድኖች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ተከትሎ የተከሰተው አደጋ የዛሬው ትውልድ ድጋሚ ሊመለከተው ይገባል፡፡ በመጀመሪያ እነዚህ ቡድኖች የተመሠረቱት በውጭ አገራት በመሆኑ በአገር ቤት የነበረውን ነባራዊ ሁኔታ ውጭ አገር ሆነው ለመተንተን የሚያስችል መረጃ አልነበራቸውም፡፡ ሁለተኛ ፓርቲዎቹ ግለሰቦች በመጠራራት የፈጠሯቸው እንጂ በሕዝባዊ ተሳትፎና ድጋፍ የታጀቡ አልነበሩም፡፡ የልሂቃን የፖለቲካ ቡድኖች ነበሩ፡፡

ሦስተኛ በመካከላቸው የነበረውን የፖለቲካ ልዩነት በመቻቻል ለመፍታት የሚያስችል አቅም አልነበራቸውም፡፡ በፖለቲካ ቡድኖች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ክፍፍልም ከውጭ የተመለሱ ታጋዮች ተፅዕኖ ፈጥረው ነበር፡፡ በዲያስፖራ የተቀመረ የፖለቲካ ፕሮግራም ለአገር ቤት የፖለቲካ ትግል መሣሪያ ሆኖ እንዲያገለግል ነባራዊ ሁኔታው አይፈቅድም ነበር፡፡ ከዚሁ የታሪክ ዘመን የምንማረው ትልቁ ቁም ነገር ለአገር ቤት የለውጥ ፖለቲካ አገር በቀልና አገር በቀል ብቻ መሆን ያለበት መሆኑን ነው፡፡

በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረው ፀብ የተጀመረው በውጭ አገር መሆኑን አንርሳ፡፡ በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል በተፈጠረው ቂምና ጥላቻ ምክንያት ወደ እርስ በርስ መጠፋፋት አመራ፡፡ "ቀይ ሽብር" የሚባለውን የፖለቲካ ቃል ማድመጥ ጀመርን፡፡ በውድ ወንድሞቻችን ላይ "ቀይ ሽብር" የሚል ማሕተም አረፈባቸው፡፡

በመጨረሻም ሁለቱም ፓርቲዎች የደርግ ሰለባ ሆኑ፡፡ ከጥቂት የድርጅቶች መሪዎች በስተቀር ሁሉም አላስፈላጊ የህይወታቸው ዋጋ ከፈሉ፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ላይም ቂምና ቁርሾ ተተከለ፡፡ ደርግም በምሥራቅ አፍሪካ የማይቀመስ ኃይል መሆኑን በማመን "አድኃርያንን ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮንም ጭምር እንቆጣጠራለን" የሚል መፈክር አስተጋባ፡፡

የደርግ ሥርዓት ውድቀት እየተቃረበ በመጣበት ወቅት በዲያስፖራው አካባቢ የፖለቲካ ጫጫታ ተፈጠረ፡፡ ኮብላይ የደርግ መኮንኖች እና የኢሠፓ መሪዎች "ከቆራጡ መሪያችን ጋር ወደፊት!" እያሉ ጉሮሯቸው እስኪነቃ ድረስ እንዳልጮሁ ሁሉ ደርሰው የዴሞክራሲ ካባ ለመላበስ ሞከሩ፡፡

በዚህ ከተካኑት መካከልም እንደ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ የመሳሰሉት አዲስ ጉልበት ይዘው ከዋሽንግተን ነጋሪት እየጎሰሙ በነፃ አውጭነት አዲስ አበባ ለመመለስ ይዝቱ ጀመር፡፡ የኢትዮጵያ ዋና ችግር ደርግ ሳይሆን ሊቀመንበሩ ኮሎኔል መንግሥቱ እንደሆኑ በመቀስቀስ የቀዶ ጥገና ፖለቲካ እንዲካሄድ መፈንቅለ መንግሥት ሰበኩ፡፡ በአገር ቤት ሽንፈቱ እየተቃረበ መምጣቱን የተመለከቱ የጦር መኮንኖችም ያልተሳካ መፈንቅለ መንግሥት አካሄዱ፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት ኢሕአዴግ. ከፍተኛ ወታደራዊ ድሎችን በማስመዝገብ ትግራይን በሙሉ በመቆጣጠር "ወደ መሀል ግባ" እያለ ደርግን እየነዳ ወደ አዲስ አበባ ገሰገሰ፡፡ ይህን የተመለከቱ የዲያስፖራ ልሂቃንና ኮብላይ መኮንኖች ኢሕአዴግን ቀድመው አዲስ አበባ ለመግባት ተራወጡ፡፡

ደርግም ቢሆን ዕድሜው እያጠረ መሆኑን ተገንዝቦ ዕድሜውን ሊያስቀጥል ይችላል ብሎ የገመተውን "የአንድነት ኃይሎች ግንባር" ለመፍጠር መዘጋጀቱን በይፋ አወጀ፡፡ ይህ ሽንፈት የወለደው የፖለቲካ አጀንዳ ለእነ ጎሹ ወልዴ የልብ ልብ ሰጣቸው፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ኢሕአዴግ ከደርግ የባሰ ነው በማለት የፀረ ዴሞክራሲ ኃይሎችን ለማሰባሰብ ሞከሩ፡፡ አገር ወዳድ ወገኖችም በየከተማው ፎረሞችና የመሳሰሉትን ስብስቦች በመፍጠርና በመደራጀት ቀልባቸውን ለፖለቲካ ሰጡ፡፡

ኢሕአዴግ አዲስ አበባን በቅርብ ርቀት እያካበበ በመጣበት ወቅት የደርግ መኮንኖች፣ የአፄው ዘመን አዛውንቶች፣ የኢሕአፓና የመኢሶን ቅሪቶች ኢዴኃቅ የሚል ሕብረት ፈጥረው አንዴ ቶሮንቶ ሌላ ጊዜ ሌላ ቦታ እየተሰባሰቡ የአገራችን የመጪው ዘመን ፖለቲካ መሪዎች ለመሆን ቃጣቸው፡፡

በዚህ ወቅትም አገራችን ከደርግ ተገላገለች፡፡ አገሪቱን የተረከበው ኢሕአዴግ በርዕሰ ከተማይቱ ሠላም ለማስፈን ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ የደርግ መሪዎችም ከየቤታቸው ተኮልኩለው እጃቸውን ሰጡ፡፡ በዲያስፖራ ዙሪያ የነበሩት ዴሞክራቶችም የኢሕአዴግን ሠላማዊ ጥሪ ተቀብለው በሽግግሩ ዘመን ለመሳተፍ አገር ቤት ገቡ፡፡

ይህ ሲሆን የዲያስፖራ ፅንፈኞች ለሌላ የጦርነት አዙሪት ዝግጅት ጀመሩ፡፡ የተካሄደው ፖለቲካዊ ለውጥ ማህበራዊ ሽግሽግ አስከተለ፡፡ የቀድሞ ልሂቃን የነበራቸው ማህበራዊ ቦታ ለመልቀቅ ተገደዱ፡፡

የዲያስፖራው ፅንፈኞች አገር ቤት ቶሎ ለመግባት የነበራቸው ተስፋ እየራቀ ሲሄድ እነ ጎሹ ወልዴ ከፖለቲካው ዓለም ተሰናበቱ፡፡ ጎሹ ወልዴ ፖለቲካውን ሲለቅ ኢሕአዴግ ያበላሸውን ፖለቲካ ለማስተካከል እንደማይቻል በመግለፅ ነበር፡፡ ጎሹ ወልዴ የፖለቲካ ብልሽት ሲል የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እኩልነት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት ግንባታ ማለቱ ነበር፡፡ ሌሎች ፅንፈኞች ግን የፖለቲካቸውን ዕድሜ ለማስቀጠል የፖለቲካ ድርጅቶች፣ መፅሔቶች፣ ጋዜጦች፣ ራዲዮ ጣቢያዎች ፈጥረው ተንቀሳቀሱ፡፡

በአገር ቤት በተጀመረው የፌዴራል ዴሞክራሲ የፖለቲካ ሥርዓት በመጀመሪያ የእምቧይ ካብ ይመስላቸው ነበር፡፡ ሆኖም የሥርዓቱ ተቀባይነት እየተጠናከረ ሲመጣ እነዚህ መረን የለቀቁ ወገኖች ገዥ ፓርቲው ላይ ብቻ ሳይሆን በሕዝቦች ላይ ይሳለቁ ያዙ፡፡ የቀድሞ ልሂቃን የተጀመረው ዴሞክራሲ ቃር…ቃር አላቸው፡፡

ይህ ሲሆን በተለያየ ስም የተደራጁ የፖለቲካ ቡድኖች በፓሪስ በሠላምና በእርቅ ስም መሰባሰብ ጀመሩ፡፡ በፓሪስ የሠላምና የእርቅ ጉባዔ የተገኙ ቡድኖች ባለፉት 40 ዓመታት በፖለቲካው መድረክ የተሸነፉ ግለሰቦች ጥርቅም ነበሩ፡፡

በዚሁ ጉባዔ ከአገር ቤት የደቡብ ሕብረት እና ሌሎች ጥቃቅን ቡድኖች ተገኙ፡፡ ይህ በአገር ቤት የፖለቲካ ሂደት የተወለዱ ድርጅቶች በዲያስፖራ ቡድኖች ተፅዕኖ እንዲወድቁ ዕድል ፈጠረ፡፡ በቀጣዬቹ ዓመታት በአገራችን በተካሄዱ የፖለቲካ ሂደቶች ራሱን የቻለ ተግዳሮት ሆነ፡፡ ሽርክናው በአገር ሠላምና ፀጥታ ላይ ሥጋት ፈጠረ፡፡ አጋጣሚው የዲያስፖራ ፅንፈኞች በአገር ቤት ! የሚሉት ፈረስ ፈጠረላቸው፡፡

በአገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከተበሰረ በኋላ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ነፃ ሚዲያ የአገራችን የፖለቲካ ሥርዓት አካል ሆኑ፡፡ ሁለተኛ ዜጋ የነበሩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች የዴሞክራሲ ሥርዓት ዋልታና ማገር  ሆኑ፡፡  የፌዴራል የፖለቲካ ሥርዓት ልዩነትን በአንድነት የሚያስተናግድ በመሆኑ ተመራጭ ሆኖ በታሪካችን የነበረ የኃይል አሰላለፍም ተቀየረ፡፡ የዴሞክራሲ ኃይሎች የመሪነቱን ቦታ ሲይዙ ፅንፈኛው ከሥልጣን ተወግዶ ዴሞክራሲያዊውን ሥርዓት ለመናድ የተቃዋሚነት ቦታ ያዘ፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ መገለጫ በዴሞክራሲና በፀረ ዴሞክራሲ ኃይሎች መካከል የትግል መድረክ ሆነ፡፡

No comments:

Post a Comment