Tuesday, 3 January 2017

የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን ለመከላከል የተወሰዱ ጥረቶች





                                          ምንይችል አለማየሁ
ትውልድ አለምን ለሰው ልጅ አኗኗር ይበልጥ እንዲመች አድርጎ ከመለወጥና ስልጣኔ ከማምጣት አኳያ አሻግሮ የሰነቀው ራዕይ የሚተገበረው በዛሬዎቹ ህጻናት የመሆኑ ጉዳይ አያጠራጥርም፡፡ የነገውን ማህበራዊ ኃላፊነት የሚወጡ፣ ፖለቲካዊውን ለሃገር በሚበጅ አቅጣጫ የሚመሩና የኢኮኖሚ ምህዋርን ዘመኑ በሚጠይቀው  በቃት የሚያሽከረክሩ የዛሬዎቹ ህጻናት መሆናቸውን ለመረዳት የምድረን ተፈጥሮአዊ ኡደት ማስተዋል ብቻ በቂ ነው፡፡ ከዚህ እንደምንረዳው ዛሬ ላይ ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ ሃገራት ስራቸውን ትናንት በነበሩ ህጻናት ላይ ሰርተዋል፡፡
ነገን ሊረከቡ የሚችሉ ህጻናት ዛሬ በተመቻቸ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መደላድል ውስጥ ማለፍ አለባቸው፡፡ ህጻናት ከእድሜያቸው ለጋነት አንጻር አዕምሯቸው በሚፈልገው ደረጃ የጎለመሰ ባለመሆኑ  ነገሮችን ከተለያዩ አቅጣጫ በመመልከት ጠቃሚና ጎጅውን አመዛዝኖ የመወሰን ችሎታቸው በአብዛኛው ብስለት የተላበሰ አይደለም፡፡ በተጨማሪም  አካላቸው በቅጡ የዳበር ባለመሆኑ ሊደርሰባቸው ከሚችል ጥቃትና አደጋ የመከላከል አቅማቸው ደካማ ነው፡፡ በመሆኑም ህፃናት ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል በተለየ ለተለያዩ ጥቃቶችና ጉዳቶች የመጋለጥ እድላቸው የሰፋ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
በህፃናት ላይ ከሚደረሱ ጥቃቶች መካከል የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን በዓለማችን በተለይም በማደግ ላይ ባሉ ሃገራት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ህጻናት የድርጊቱ ሰለባ እንደሆኑና ከጊዜ ወደ ጊዜም ሁኔታው እየተባባሰ እንደመጣ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ከዚህ ጋር ተያይዞ ሃገራት የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ለመከላከል  የህግ ማዕቀፎችንና ኮንቬንሽን በማፅደቅ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ የተፈለገውን ደረጃ ያህል ባይሆንም በችግሩ ተጎጂ የሆኑ ህፃናት ቁጥርን  መቀነስ ተችሏል፡፡ ለአብነትም  ከስድሰት ዓመት በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ በጉልበት ብዝበዛ ችግር ውስጥ የነበሩ ህፃናት ቁጥር ከ215 ሚሊዮን በላይ የነበሩ ሲሆን ከዚያ ወዲህ ባሉት ጊዜያት ወደ 168 ሚሊዮን ዝቅ ማለቱንና ከዚህ መካከል 85 ሚሊዮን ህጻናት አስከፊ በሆነ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ ውስጥ መገኘታቸውን የዓለም ስራ ድርጅት (ILO) እ.ኤ.አ በ2015 ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ ይህ አሃዝም በ2020 ዓ.ም ወደ 107 ሚሊዮን እንዲወርድ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡
በሃገራችን ኢትዮጵያም ምንም እንኳን ወጥነት ባለው መልኩ የዳሰሳ ጥናት ተካሂዶ በአግባብ የተደራጀ መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ ቢሆንም በአንዳንድ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ግብረሰናየ ድርጅቶች የተካሄዱ የክትትለትና ቁጥጥር ስራወች እንደሚያሳዩት በአንዳንድ የግል ንግድ ተቋማት የሐጻናት ጉልበት ብዝበዛ ይፈጸማል። ለምሳሌ የሰራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2008 ዓ.ም ሪፖርት እንደሚሳየው እንደ ጋራዥ፣ ሸማ ስራ ማህበራት የመሳሰሉ ድርጅቶች ውስጥ ድርጊቱ ሲፈጸም ተስተውሎ እርምጃ ተወስዷል።
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ1991 የፈረመችው የህፃናት መብቶች ኮንቬንሽን ፣ የአፍሪካ የህጻናት መብትና ደህንነት ቻርተር እንዲሁም የኢፌድሪ ሕገ-መንግስት የህፃናት ደህንነትን በሚመለከት በግልጽ የሰፈሩ አንቀጾች አሉ፡፡
የዓለም አቀፍ የህጻናት መብት ኮንቬንሽን አንቀጽ 16፣27 እና 29 ብሎም የአፍሪካ ህፃናት መብትና ደህንነት ቻርተር አንቀጽ ከ34-36 ህጻናት ከማንኛውም ወሲባዊ ጥቃትና ጉልበት ብዝበዛ ነጻ የመሆን መብት እንዳላቸው ያስቀምጣል፡፡በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት ህፃናትን ጨምሮ ማንም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት ኢ-ሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብርን ከሚያዋርድ አያያዝ እንዲሁም ከባርነት ወይም ከግዳጅ ስራና ከሕገወጥ ዝውውር የመጠበቅ መብት እንዳላቸው አስቀምጧል፡፡ ለተቀመጠው መብት ተፈጻሚነት ይረዳ ዘንድ አገሪቱ የተለያዩ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች እና ህጎችን ከመቀየስ ባለፈ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዷ የህፃናት መብትና ደህንነት እንዲከበርና ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው በመደንገግ ስተገብር ቆይታለች፡፡
ኢትዮጵያ በተለይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰራተኛ ህጻናቷን ለመቀነስ  ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር በጋራ አየሰራች ሲሆን አገሪቱ የአለም አቀፍ ሰራተኞች ድርጅት (ILO) ስምምነትን በመቀበል ዝቅተኛው የስራ ዕድሜ 15 ዓመት እንዲሆን ወስናለች፡፡ ከ14 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን ከስራ ለመጠበቅ እንዲሁም የእድሜ ክልላቸው ከ14-18 ዓመት ያሉ ህፃናትን የስራ ሁኔታ ለመወሰን የሕግ  ማዕቀፍ በመቅረጽ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ በሰራተኛ አዋጅም ህፃናት ለደህንነታቸው አስጊ በሆነ ስራ ላይ እንዳይሰማሩ ከልክላለች፡፡ በተጨማሪም ህፃናትን ከአስከፊ የጉልበት ብዝበዛ ለመከላከል የሚረዳ ብሔራዊ የድርጊት መርሃ ግብር ያወጣች ሲሆን መሰል ድርጊቶችን የሚከላከሉና የህጻናትን ማህበራዊ ደህንነት የሚያረጋግጡ የሕግ ሰነዶች ተዘጋጅተው በስራ ላይ እንደዋሉ ከኢፌዴሪ የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በመገናኛ ብዙሃን ስለጉዳዩ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ በመፍጠር  ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በስፋት እየተከናወነ ሲሆን የጉልበት ብዝበዛ የደረሰባቸው ህጻናትን በመደገፍ  ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡በተለይ ወጣቶች ራሳቸውን ችለው ቤተሰቦቻቸውን እንዲደግፉ የሚረዱ የሙያ ስልጠናዎችን በማመቻቸት እና የገበያ ሁኔታ በመፍጠር የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን ለመከላከል የሚያግዙ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
አብዛኛውን ጊዜ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ የሚከናወነው ህጻናትን ከቦታ ቦታ በሕገወጥ መልኩ በማዛወር ነው፡፡ በተለይም  ወላጅ አልባ ወይም ቤተሰቦቻቸው በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ህፃናትን ለዚህ ሐገወጥ ተግባር ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው፡፡


መንግስት ይህን አስከፊ ድርጊት ከምንጩ ለማድረቅ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፣ በማከናወንም ላይ ይገኛል። ከነዚህም መካከል አንዱና ዋናው ህፃናትን በህገ-ወጥ መልኩ ከቦታ ቦታ ማዘዋወር በድንበር ያልተከለለ ህጋዊ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ወንጀል መሆኑን መደንገግ ነው፡፡ ለሐጉ ስኬታ ማ ተፈጻሚነትም ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከል በአውቶቢስ መነሐሪያዎች የህጻናት የሕገወጥ ዝውውር መከታተያ ክፍል እንዲሁም ችግሩ በስፋት ይስተዋልባቸዋል ተብለው በተለዩ አካባቢዎች    የመፈተሻ ጣቢያዎችን አቋቁሞ በዚሁ መልኩ ሊዘዋወሩ ሲሉ የተገኙ ህፃናትን በመያዝ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም ለጉልበት ብዘበዛ በሕገ-ወጥ መልኩ ከቦታ ቦታ ስለሚዘዋወሩ ህጻናትን አስከፊ ገጽታ በተመለከተ ለሕግ ባለሙያዎች ፣ ፖሊስ ፣ ለህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ሹፌሮችና ረዳቶች እንዲሁም ለአውቶቢስ መናህሪያ ሰራተኞች እና ደላሎች ቀጣይነት ያለው ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ለአብነት ያህል በ2008 በጀት ዓመት በተለያዩ ጊዜ በተፈጠሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች 8,144,666 ሰዎች እንዲሳተፉ በማድረግ 96,943 ህጻናትን ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊት 115,914 ህጻናትን ከሀይል ጥቃት እና ጉልበት ብዝበዛ መታደግ ተችሏል፡፡
በተጨማሪም በተለያዩ ጊዜያት በሚወጡ ሃገራዊ መዋቅሮች ፣የምልመላ መስፈርቶች፣ የቅጥር ሁኔታ ወ.ዘ.ተ ህፃናት ለጉልበት ብዝበዛ እንዳይዳረጉ  ክትትል በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ በሃገሪቱ የጦር ሰራዊት አባል የመሆኛ እድሜ 18 ሲሆን ከዚህ እድሜ ክልል ወጪ የሆኑ ህፃናት በፍቃደኝነት እንኳ ቢሆን የሰራዊት አባል መሆን አይችሉም፡፡ ህፃናት በትጥቅ ትግሎች እንዳይሳተፉ የሚያደርግ፣ ህፃናት ለጦርነታ ምልመላ የሚከለክል እና ሌሎች መብቶቻቸውን የሚያስጠብቁ አህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ስምምነቶችን ፈርማለች፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከህብረተሰብ፣ ከተለያዩ ሃገር በቀልና የውጪ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት፣ ከሲቪክ ማህበራት ፣ ከአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ጋር በመሆን እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የህጻናትን ጉልበት ብዝበዛ እና የነገ ሃገር ተርካቢ ትውልዶችን ሁለንተናዊ ኑሮ በማሻሻል ረገድ አበረታች ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች፡፡ ይህም የህፃናትን መብትና ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ አገሪቱ በትክክለኛ መስመር እየተጓዘች መሆኑን ማሳያ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ገና ያልተሻገረቻቸው እና የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚጠይቁ መሰናክሎች ስላሉ መልካም ጅምሮችን በማጠናከርና ጉድለቶችን ለይቶ በመሙላት  በተለየ ትጋት መስራት ይኖርባታል፡፡

No comments:

Post a Comment