Tuesday, 3 January 2017

ሴቶች የራሳቸውን መብቶች ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም መብት መታገል ችለዋል!




  መሃመድ ሁሴን
ከኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች  ናቸው፡፡ እነዚህን የማህበረሰብ ክፍሎች በተገቢው ያላሳተፈ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከስኬት ይደርሳል ብሎ ማሰብ  ህልም ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአገራችን  የመንግስታት ታሪክ ለሴቶች ተገቢውን ሰብዓዊ  ክብርም ሆነ ተገቢውን እውቅና በመስጠት የሚያበረታታ እና ተሳትፏቸው እንዲጎለብት የሚያደርግ ምቹ ስርዓት  አልነበረም።  በደርግ ወቅት ቢሆን  የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት  የይስሙላ እንጂ እውነትም  ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረገ አልነበረም።       
በአጼዎቹ ስርዓት ሴቶች የሚያነሱት ሃሳብ ሚዛን የማይደፋና የማይደመጥ ተደርጎ ከመታየቱም በላይ በአደባባይ ሃሳቧን  የገለጸች እንስት ባለጌ እና ስርዓት የለሽ ተደርጋ ትታይ  እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ በነዚህ እና እነዚህን በመሳሰሉ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች ምክንያት ሴቶች  ለኃላፊነት የማይበቁና እምነት የማይጣልባቸው ተደርገው በመታየታቸው በቤት ውስጥ ስራ  እና ልጅ  በማሳደግ ብቻ ተወስነው እድሜያቸውን እንዲያሳልፉ ተደርገዋል፡፡ በሴትነታቸው ብቻ  ለድርብርብ እና ለከባድ የስነልቦና ችግር ተጋልጠው እንደነበረ  የሚረሳ ታሪክ አይደለም፡፡  በዚህም የተነሳ ከወንዶች በከፋ ደረጃ በርካታ የሰብዓዊ መብት፣ የማህበራዊ መብት እና የፖለቲካዊ መብት ጥሰት ደርሶባቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ መንግስታት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ በ1931 በተጻፈው ህገ-መንግስት ለይስሙላም ቢሆን  የመንቀሳቀስ መብት፣ የደህንነት መብት እና የንብረት ባለቤትነት መብት በህገ-መንግስቱ የተካተቱ ሲሆን  በሴቶች መብት እና ተጠቃሚነት ዙሪያ አንዳችም ጉዳይ የሚያነሳ አልነበረም፡፡
በተመሳሳይ ሁለተኛው ህገ-መንግስት እ.ኤ.አ በ1955 ዳግም በንጉሱ ስርዓት እንዲከለስ ተደርጎ ስለነጻነት ጥቂት ሃሳብ፣ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ እና የመደራጀት መብቶች ታክለውበት የተዘጋጀ ቢሆንም ሁሉም  በተግባር ላይ አለመዋሉ እንደተጠበቀ ሆኖ የሴቶች መብት እና የተጠቃሚነት ጉዳይ  ሳይነሳ የተዳፈኖ የቀረ ነበር፡፡
የሴቶች መብት እና የተጠቃሚነት ሁኔታ በአምባገነኑ ስርዓት ወቅትም የሚታሰብ ጉዳይ አልነበረም፡፡ ስለዚህ በሀገሪቱ ገዥ ስርዓቶች ታሪክ ስለሰብዓዊ መብት መከበር እና ስለዴሞክራሲያዊ መብት መከበር በተለይም  ስለሴቶች መብት መከበር እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሲነሳ  የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት በተገቢው አጽንኦት ስጥቶ በማካተት እና በተጨባጭ ተግባራዊ በማድረግ  መሰረት የጣለ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት የሀገራችን ሴቶች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተጠብቆ በሃገሪቱ ልማት እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ የሚችሉ ከህገመንግስቱ የመነጩ ስትራቴጂዎች እና ፖሊሲዎች   ተዘጋጀተው ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡
የሴቶች የማንነት፤ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ በሰላም ወጥቶ  የመግባት፣ የመማር፣ ወደሃላፊነት የመምጣት  በአጠቃላይ በእኩልነትና ሰላም የመኖር  መብታቸው  ተረጋግጧል። ሴቶች ይህን መብታቸውነ ለማረጋገጥ ከወንዶች እኩል ታግለዋል።  የዛሬዋን ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የሴቶች ድርሻ ጉልህ ነበር። 
የሀገራችን ሴቶች መሰዕዋትነት ከፍለው በተገኘው የቃልኪዳን ሰነድ መሰረት  አዲሲቷን ኢትዮጵያ  እውን ደድርገዋል። የኢፌዴሪ መንግስት  ለሴቶች  ልዩ ትኩረት  እንዲሰጥ  በማድረጉ ተጨባጭ  ለውጦች መታየት ጀምረዋል። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ በሁሉም ረገድ እኩልነት የተረጋገጠባት ናት። ሴቶች የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የኤኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው ተረጋግጧል። 
በኢፌዴሪ ህገ መንግስት  አንቀጽ 35 የሴቶች መብት በሚል ስር ከዘረዘራቸው ለሴቶች ልዩ ትኩረት እና ጉልበት ከሚሰጡ ንኡሳን አንቀጾች በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሴቶች የልማት እና የለውጥ ፓኬጅ (ሐምሌ 1998 ዓ.ም)፣ የኢትዮጵያ የገጠር ወጣቶች  የእድገት ፓኬጅ፣ እና የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ሴቶች  በሀገራዊ ግንባታ ሂደት ወሳኝ አካል መሆናቸውን  እና እኩል መሳተፍ እንደሚገባ ያመላከተ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እውቀት እና ክህሎታቸውን አዋጭ የሆኑ የስራ መስኮችን ለይቶ በማስቀመጥ በቡድን እና በተደራጀ መልኩ እንዲከናወን ስልት በማስቀመጥ ሴቶችን ያለስጋት ተግባር ውስጥ ማስገባት ችሏል፡፡
ዛሬ ሴቶች ከማጀት ወጥተዋል። መብቶቻቸውን መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች መብት መታገል የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቷል።  በዚህም የተነሳ በመላው የሀገሪቱ በኢኮኖሚዊና በፖለቲካዊ አቅማችው ለሞዴልነት የበቁ ሴት አርሶአደሮችንና ሴት አርብቶ አደሮችን፣ ሴት አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችን፣ ሴት የጥቃቅንና የመካከለኛ ኢንዱስትሪ አንቀሳቃሾችን፤ ሴት አስመጭና ላኪ ባለሃብቶችን፣ ሴት የእንስሳት ተዋጽኦ አምራችና አከፋፋዮችን፣ ሴት ሚኒስትሮችና ፖለቲከኞችን…ወዘተ  ማየት ዛሬ ላይ የተለመደ ተግባር ሆኗል፡፡  የሀገሪቱን የቀጣይ እጣ ፋንታም ሆነ የራሳቸውን የህይወት እጣ ፋንታ የመወሰን ስልጣኑ በእጃቸው መሆኑን የጋራ የቃልኪዳን ሰነዳቸው በፈቀደላቸው ልክ መተርጎምና መተግበር ችለዋል፡፡
ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ የፈጠረላቸውን ምቹ መደላድል ተመርኩዘው በየደረጃው የፈጠሯቸው በርካታ የሴት አደረጃጀቶች የውይይት መድረኮች ማንነታቸውን በመገንባትም ሆነ በማሳየት እንዲሁም ከፍተኛ በራስ የመተማመን ስሜትን በማጎልበት የተጫወቱት ሚና ወደር የለውም፡፡
ሴቶች በየጊዜው አቅማቸውን በማጎልበት እና ምርጥ አሰራራቸውን አጠናክረው  ልምድ በመለዋወጥና በማስፋት  መሰረታቸው የማይናወጥ ሴት ተኮር በርካታ አደረጃጀቶች መስርተው ተግባራዊ አድርገዋል፡፡  አደረጃጀቶቹ ሃሳባቸውን  በነጻነት በማንሸራሸር የወሳኝነት ሚናቸውን በሀገራዊ፣ በክልላዊ፣ በዞንና በወረዳም ሆነ በሚገኙበት አካባቢ ተጽኖ  መፍጠር  የሚችሉበት እድልና ጉልበት ሰጥቷቸዋል፡፡ በአንድ ዓላማ መሰባሰብና መመካከር፤ ፖለቲካዊ አሰተሳሰባቸውን ማጎልበትና ለመብትና ግዴታቸው መከበር በመድረክ መከራከር መቻላቸው በደማቸው የመሰረቱት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ፍሬ መሆኑን ሴቶች ትልቅ ድል ነው፡፡
ህገመንግስቱ የፈቀደላቸውን የመደራጀት እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ  መብት ተጠቅመው የሴት የልማት ቡድን  ከ25 እስከ 30 የሚደርሱ  ተመሳሳይ ፍላጎት እና ዓላማ ያላቸው  ሴቶች የሚመሰርቱት  ስብስብ ነው፡፡ እነዚህ ሴቶች የሰፈር ቅርበታቸውን መሰረት በማድረግ አንድ ለ አምስት (1 ለ 5)  የሚመሰርቱ ሲሆን በሳምንት አንድ ቀን ተሰባስበው ለራሳቸውና፣ ለአካባቢው ማህበረሰብ እና ለሀገር በሚጠቅም አጀንዳ ዙሪያ ይመካከራሉ፤ ይወስናሉ፡፡ በሰብሳቢያቸው አማካኝነት መሰረታዊ ድርጅት ተብሎ ለሚጠራ የበላይ አካል ውሳኔያቸውን ያሳውቃሉ፡፡
በዋናነት የሚያነሱትና የሚመካከሩበት  አጀንዳ በአካባቢያቸው አቅማቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት እና ጎልማሶች የትምህርት እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ፣ የአካባቢያቸውን የጸጥታ ጉዳይ መከታተልና ሰላም ማስፈን፤  በሰፈራቸው የሚኖር ሰው ሁሉም የጤና ኤክስቴንሽን አስራ ስድስቱን ፕሮግራሞች አውቆ እንዲተገብር ማድረግ፣  የኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ የሆኑ ሴቶችን በመለየት በጥቃቅንና አነስተኛ ፕሮግራም አማካኝነት ተደራጅተው እንዲለወጡ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እና የአካባቢ ጥበቃ በተለይ የተፋሰስ ልማት በመሳሰሉት ተግባራት ዙሪያ ሲሆን ስራዎች በመግባባትና በፍላጎትን  በፍቃደኝነት  የሚከናወኑ ናቸው፡፡ በዚህ ዙሪያ የመንግስት የፋይናንስ ተቋማት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ አበዳሪና ረጂ ድርጅቶች (ዩኒሴፍ፣ ሴቭዘ ችልድረን… ወዘተ) ያሉ አካላት ብድርና ቁሳቁስ በማቅረብና በማመቻቸት የማይናቅ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡
በጥቅሉ ለሴቶች መብት መረጋገጥ ፤ለሴቶች ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት እና ሃገር ወዳድነት የላቀ ስሜትና ተግባር ከዚህ ቡድን ድርጊት በላይ ምስክር ሊኖር አይችልም፡፡ ስለዚህ ለሴቶች መብት መረጋገጥና ተስማሚነት ከሚያበረክተው ፋይዳ ባልተናነሰ መንገድ የተሻለ አሰራርና የተሻለ ስራ ተለይቶ ለሌሎች በአስተማሪነት ይቀርባል፡፡ ይህ ሂደት ሀገር ወዳድ እና  ስራ ፈጣሪ ትውልድ በማፍራት አዲሲቷን ኢትዮጵያ በመገንባት ሂደት ውስጥ ለሚደረገው ርብርብ የላቀ ድርሻ አለው፡፡
የሴቶች የልማት ቡድን እና ሌሎች የልማት  አደረጃጀቶችን ለማፍረስ አሊያም ለማዳከም አንዳንድ  አካላት የተለያዩ ስልቶችን ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ ይሁን እንጂ ሴቶች ይህን እድል እና ስርዓት መሰረት ለማስያዝ የተከፈለው ዋጋ ቀላል አለመሆኑን ጠንቅቀው የሚያውቁ ከመሆናቸውም በላይ ተገቢውን ድጋፍ  ለአደረጃጀቶታቸው ማድረግ ይኖርባቸዋል።  እነዚህ አደረጃጀቶች በሴቶች ህይወትም ሆነ በአገራችን እድገት አዎነታዊ ለውጦችን ማምጣት የቻሉ በመሆናቸው ሁሉም አካል ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል።    
      
      

No comments:

Post a Comment