እየሩሳሌም
ደማሙ
በዚህ ፅሁፍ በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን የምናነሳ ይሆናል። ወደዋናዉ ጉዳይ ከመግባታችን በፊት ግን የህፃናት የእድሜ ጣሪያ ስንት ነው? ህጻናት
የሚባሉትስ እነማን ናቸው ከሚለው ጥያቄ ለመጀመር ያህል በህፃናት መብት ኮንቬንሽን ላይ የሚገኘው ስለህፃንነት እድሜ እንዲህ ሲል
ይገልፃል። የህጻናት እድሜን የሚገልጸው መደበኛ የሃገራችን ኢትዮጵያ ህግ 1952 ዓ.ም የፍትሃብሔር ህግ ነው፡፡ በዚህ ህግ ህጻን
የሚለው ቃል ጠቀሜታ ላይ የዋለው በቀጥታ ሳይሆን የህጉ አንቀጽ 198 እድሜያቸው ከአሰራ ስምንት አመት በታች የሆኑ ልጆችን የሚገልጸው
“አካለ መጠን ያልደረሱ” በሚል ሃረግ ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ ቢኖርም የፍትሐብሔር ሕጉን ጨምሮ ሌሎች የሃገሪቱ ህጎች ለአንዳንድ ጉዳዮች
የእድሜ ጣሪያውን ዝቅ ያደረጉታል፡፡ ለምሳሌ የፍትሃብሔር ህግ አንቀጽ 329 እና 581 ላይ ሴት ልጅ 15 አመት ከሞላት ማግባት
ስለምትችል 18 አመት ሳይሞላት ብታገባም እንደ አዋቂ ትቆጠራለች የሚል ነገር እናገኛለን፡፡እንዲሁም በዚሁ የፍትሃብሔር ሕግ ከአንቀጽ
330 እስከ 334 ላይ ወንድ ልጅም ቢሆን 15 አመት ከሆነውና ራሱን ይችላል ተብሎ ከታመነበት በወላጆቹ ፈቃድና በቤተ ዘመድ ውሳኔ
ከሞግዚት አስተዳደር ነጻ ይሆናል ሲል አስቀምጧል፡፡
በአንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች ስለ ህጻንነት ዘመን የተለያየ አመለካከት አለ፡፡ ይህም ሲባል
በከተማና በገጠር እንዲሁም በተለያዩ ብሔረሰቦች መካከልም ስለ ህጻናት የዕድሜ ክልል ያለው አመለካከት የተለያየ ነው፡፡
በአብዛኛው የገጠር አካባቢ ‘’ህጻን’’ ማለት አደጋን በራሱ መከላከልና መጠበቅ የማይችል ነው፡፡
እንደ አብዛኞቹ የገጠር አካባቢዎች አመለካከት ህጻን የሚባለው ከዕድሜ አለመብሰል የተነሳ ራሱን በራሱ መምራት የማይችልና የሌሎች
ድጋፍና ጥበቃ የሚያስፈልገው አካል ነው በአንፃሩ ደግሞ በከተማ አካባቢ ያለውን የህፃንነት የዕድሜ ዘመን አመለካከት ስናይ ህፃን
ማለት ከሰባት አመት በታች የሆነና መደበኛ ትምህርት ቤት መግባት ያልቻለ ብቻ ነው ሲል የህፃናት መብት ኮንቬሽን አስፍሯል፡፡
በአጠቃላይ ህፃናት እነማን ናቸው የሚለውን በተለያዩ ህጎች የተደነገገውን ለመግቢያ ያህል በአጭሩ
ካየን ወደ ዋናውና ለዚህ ፅሑፍ መነሻ ወደ ሆነው ጉዳይ ለመግባት እንሞክራለን፡፡
ይህንን ርዕሰ ጉዳይ ማንሳት የተፈለገበት ምክንያትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውና ህፃናት
ልጆችን ገና ቦርቀው ሳይጠግቡ በለጋ እድሜያቸው የጎዳና ህይወትን እያስመረጣቸው ያለው በአንድም ይሁን በሌላ በተለያዩ ምክንያቶች
በህፃናት ላይ የሚፈፅሙ ጥቃቶች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ህፃናት ልጆችን የጎዳና ህይዎትን እንዲኖሩ የሚያስገድዱ
የቤተሰብ መፍረስ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸዉን ማጣት፣ በእናስተምራቸዉ ሰበብ የዘመድ ልጆችን ከገጠር ወደ ከተማ በመውሰድ
ተለያዩ ህገወጥ የገንዘብ ማግኛነት መጠቀም ወዘተ የመሳሰሉ ምክንያቶችን መዘርዘር ይቻላል። በተለይ በመዲናችን አዲስ አበባ ህፃናት
የጎዳና ልጆች ቁጥራቸው የትየለሌ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ይህን ስልም ማንም አካል አይቶ ሊፈረደው የሚችል ጉዳይ ስለሆነ
ነው፡፡ በኢትዮጵያ የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናት ቁጥር በጥቂቱ ስንመለከት100 ሺህ ሕፃናት በአዲስ አበባ፣ በሌሎች ከተሞች ደግሞ
150ሺህ (600 ሺህ የሚል መረጃም አለ) ሕፃናት የጎዳና ተዳዳሪ ናቸው። ለመሆኑ በህፃናት ላይ የሚፈፅሙ ጥቃቶች ምን ምን ናቸው?
በምን መንገድ ይገለፃሉ? ጥቃት ፈፃሚው አካል ማንነው? ጥቃቱ የሚፈፅምባቸውስ እነማን ናቸው? ጥቃቱ የሚያስከትለው አካላዊና ስነ-ልቦናዊ
ችግሮች ምን ምን ናቸው? የሃገሪቱ ህጎች በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸው አቋም ምን ይመስላል? ጥቃቱ የሚፈፅምባቸው ቦታዎችና በህፃናት
ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ምን ምን መደረግ አለበት የሚሉትን ለማየት እንሞክራለን። ይህን ሃሳብ የሚያጠናክርልን የህፃናት
መብት ኮንቬንሽን ላይ የተገኘው መረጃ እንዲህ ይላል፡-
ህፃናት በወላጆቻቸው ወይም በአሳዳጊዎቻቸው
ወይም በሌሎች ሰዎች ቁጥጥር ስር በሚገኙበት ጊዜ ማንኛውም አይነት በአካላቸው ወይም በአዕምሮአቸው ላይ ጉዳት የሚያመጣ ድብደባ፣
ለጉዳት ወይም ለጉስቁልና የሚዳርግ አያያዝ፣ በቸልታ መጣል ወይም ማንገላታት ለሰው የሚገባ እንክብካቤ ማጣት ወይም የጥቅም ማግኛ
መሆን ፣ የግብረ ስጋ ግንኙነት ለማድረግ መገደድ ጭምር እንዲፈጸምባቸው ለማድረግ ተገቢውን የሕግ፣ የአስተዳደር፣ የማህበራዊና የትምህርት
እርምጃዎች ይወሰዳሉ፡፡ በአጠቃላይ ድብደባና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች፣ መሰረታዊ መብቶቻቸው መጣስ እና ለእንግልት መዳረግ፣ ወሲብና
ሌሎች የማህበራዊ ኑሮ ጥቃቶች፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የመሳሰሉት ሲሆኑ በህፃናት አካልም ሆነ ስሜት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ
ድርጊቶች በህፃናት ላይ የሚፈፅሙ ጥቃቶች ተብለው ይጠቃለላሉ ሲል አንቀጽ 19 ያስቀምጣል፡፡
ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በዕድሜ ለጋ ህፃናት ለአካላዊ ጥቃት የተጋለጡ ሲሆኑ ለአቅመ አዳም ወይም
ለአቅመ ሄዋንና ለወጣትነት የደረሱት ደግሞ ለፆታዊ ጥቃት ተጋላጭ ናቸው፡፡ ከሴት ህፃናት ይልቅ ወንድ ህፃናት ተጋላጭነታቸው አካላዊ
ጥቃት ሲሆን ሴት ህፃናት ደግሞ ለፆታዊ ጥቃት፣ ለግዳጅ ሴተኛ አዳሪነት የተጋለጡ ናቸው፡፡
በተለየ ሁኔታ ደግሞ አካል ጉዳተኛ ህፃናት፣ ትኩረት የተነፈጋቸው ሌሎች ህፃናት፣ የጎዳና ተዳዳሪ
ህፃናት፣ ስደተኛና ተፈናቃይ ህፃናት ለኃይል ጥቃት ተጋላጭ መሆናቸውን አንዳንድ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
በህፃናት ላይ የሚፈፅም ጥቃት የሚያሳድረው ተፅዕኖ አስከፊ ከመሆኑ ባሻገር ማህበራዊ፣ ስሜታዊና አዕምሮአዊ
እና ወደ ሱሰኝነት የሚወስዱ ችግሮችን ያስከትላል፡፡ ሊከሰቱ የሚችሉ ማሀበራዊ ችግሮችን ስናይ እንደ ፍርሃት፣ ቅዥት፣ መንፈሰ ደካማነት፣
የማስተዋል ችግር እንዲሁም ምግባረ ብልሹነትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ጥቃት ወደ ሚፈፅምባቸው ቦታዎች ስንመጣ በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች የሚጀምሩት ከቤት ዉስጥ
በቤተሰብ አማካኝነት ነዉ፡፡ በቤትና በቤተሰብ ውስጥ፣ በትምህርት ቤት፣ በህፃናት ማሳደጊያ ተቋማት በስራ ቦታና እንዲሁም በማህበረሰብ ውስጥ የመሳሰሉት
በህፃናት ላይ ጥቃት የሚፈፅምባቸው በታዎች ናቸው፡፡ በቤትና በቤተሰብ ውስጥ የሚፈፅሙ ጥቃቶች ከአደጋ አለመጠበቅ፣ አካላዊና ስሜታዊ
ፍላጎቶቻቸውን አለማሟላት ስነ-ምግባርን በማስጠበቅ ሰበብ ጭካኔ የተሞላባቸውና ሰብአዊ ክብርን የሚቀንሱ ድርጊቶችን እንዲሁም ሌሎች
አገልግሎቶችን አለማሟላት ያጠቃልላል፡፡ በቤት ውስጥ ጥቃት የሚፈፅሙ አካላትም ወላጆች፣ የአደራ ቤተሰቦች ወንድምና እህቶች እንዲሁም
ሌሎች የቤተሰብ አባላትና ተንከባካቢዎችንም ይጨምራል፡፡ በቤትና በቤተሰብ ውስጥ በህፃናት ላይ ከሚፈፅም ጥቃት በተጨማሪ አካላዊ
ቅጣት፣ ስነ-ልቦናዊ ቅጣቶች፣ ወሲባዊና ስርዓተ ፆታዊ ባህሪይ ያላቸው ቅጣቶች በትምህርት ተቋማት በመምህራን፣ በራሳቸው በተማሪዎች፣
በአስተዳደር አካላት ወዘተ የሚፈፅሙ ጥቃቶች ናቸው፡፡ ህፃናት በስራ ቦታ በአሰሪዎች፣ አብረዋቸው በሚሰሩ ሰራተኞች፣ በተገልጋዮች፣
በተቆጣጣሪዎች ወ.ዘ.ተ የተለያዩ ጥቃቶች እንደሚፈፅምባቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እንዲሁም ማህበረሰብ የህፃናት ጥበቃና የአብሮነት
ምንጭ ቢሆንም ጥቃት የሚፈፅምበት ጭምርም ነው፡፡ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚፈፅሙ ጥቃቶች በጓደኛ፣ በተደራጁ ቡድኖች የሚፈፅሙ እንደ
ጠለፋ፣ ሕገ-ወጥ የህፃናት ዝውውር፣ አካላዊና ወሲባዊ ጥቃቶችን ያካትታል፡፡ ህፃናት በማህበረሰቡ አባላት ለሚፈፅም ወሲባዊ ጥቃትና
ብዝበዛ ተጋላጭ ናቸው፡፡
የህፃናትን የጥቃት ተጋላጭነት ለመቀነስ ምን መደረግ አለበት? ሲባል ይህ ጉዳይ ጥናቶችን ማካሄድ የሚጠይቅ
ቢሆንም የተረጋጋ ቤተሰብ መኖር ህፃናቱ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የጥቃት ተጋላጭነታቸውን የሚቀርፍ መሰረት ሊሆን ይችላል፡፡ የወላጆች
የልጅ አስተዳደግ፣ በወላጆችና በልጆች መካከል ጠንካራ ግንኙነት መኖር፣ ኃይል ያልተቀላቀለበት የስነ-ምግባር መገንቢያ ስርዓት የመሳሰሉት
ተግባራት ህፃናትን በቤት ውስጥም ሆነ በሌሎች ሁኔታዎች ውስጥ ከጥቃት ለመጠበቅ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች ልንላቸው እንችላለን፡፡
በተጨማሪም መንግስት በተለያየ ምክንያት ለጥቃት የተዳረጉ ህፃናት ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። ህፃናት በቀላሉ ለችግር መጋለጣቸው፣
በታላላቆቻቸው ላይ ጥገኛ መሆናቸው ሊደርስባቸዉ ከሚችል ጥቃት የበለጠ ሊጠበቁ ይገባል። ምክንያቱም የአንድ ሃገር የወደፊት ህልውና
መሰረት የሚጣለዉ በህፃናት ላይ በመሆኑ ህፃናትን ከጥቃት መጠበቅ፣ በሚገባ መንከባከብና ሃላፊነትን መሸከም እንዲችሉ አድርጎ ማሳደግ
የእያንዳንዱ ቤተሰብና ማህበረሰብ ኃላፊነት ነው።
No comments:
Post a Comment