ወንድይራድ
ኃብተየስ
በአጼዎቹ ዘመን በአገራችን በኃይማኖትና በመንግሥት አሰራር መካከል ግልጽ ልዩነት ያልተደረገበት ወቅት በመሆኑ ኃይማኖት ለመጨቆኛ
መሳሪያናት ሲያገለግል ነበር። አገሪቱ የአንድ ሃይማኖት ርስት እስክትመስል ድረስ ንጉሰ ነገስቱ አንዱን ሃይማኖት አቅርበው ሌላውን ገፍተውት
ስለነበር በአገሪቱ የኃይማኖቶች እኩልነት መዛነፍን አስከትሎ ነበር።
የአጼውን ስርዓት የተካው የደርግ ስርዓት ደግሞ ለሁሉም ኃይማኖቶች እውቅና በማይሠጥ መንገድ አገሪቱን
ለመምራት ጥረት በማድረጉ ሌላ ታሪካዊ ስህተት ፈጸመ፡፡ በዚህም ምክንያት 1983 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያ የኃይማኖቶች እሥር ቤት ተደርጋ ትቆጠር ነበር፡፡
የኢፌዴሪ ህገመንግስት ከጸደቀ ቡኋላ ሁኔታዎች ተቀይረው በአገራችን ተዛንፈው የነበሩ የጭቆና
መድረኩች በሙሉ መቅረፍ ተችሏል። ሕገ-መንግሥቱ ለኃይማኖቶች እኩልነት ጽኑ መሠረት በመፍጠር የመንግስት አሰራርንና የኃይማኖት ጉዳይን በየፈርጁ እንዲታዩ አድርጓል። ሁሉም ኃይማኖቶች በሕግ ፊት ያላቸውን እኩልነት ያረጋገጠ እንዲሁም መንግሥታዊ የኃይማኖት ወይም ኃይማኖታዊ መንግስት በአገሪቱ ዳግም እንዳይኖር ተደርጓል። በመሆኑም በአገራችን በኃይማኖት ነጻነት መጓደል ሳቢያ ለሚነሱ
ችግሮች ህገመንግስቱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ሰጥቶታል። እነዚህ የሕገ-መንግሥት አንቀጾች በመንግሥት እና በኃይማኖቶች እንዲሁም በተለያዩ ኃይማኖቶች መካከልም የርስ በርስ ግንኙነት መጠናከርና መተማመን የፈጠሩ ለመሆናቸው የዛሬይቷ ኢትዮጵያ ጥሩ ማሳያ ናት።
በህገመንግስታችን የኃይማኖት
ነጻነት መብት በመረጋገጡ የትኛውም ኃይማኖት ተከታዮቹን በነጻነት የማስተማር በሰላማዊ መንገድ ተከታዮቹን
የማብዛት በተመሳሳይ ማንኛውም ግለሰብ የመረጠውን ኃይማኖት ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ በነጻነት የማራመድ መብት አለው። ይህ ኃይማኖት የጥንት ነው፣
ይህ መጤ ነው፣ ይህ መጥፎ ነው፣ ይህ እንዲህ ነው፣ ያ እንዲያ ነው ማለት አይቻልም። ሁሉም ኃይማኖች ለተከታዮቻቸው ትክክለኛና
የጽድቅ መንገዶች ናቸው። እኔ ኃይማኖቴ እንዲነካብኝ እንደማልፈልገው ሁሉ ሌላውም ሃይማኖቱ እንዲነካበት እንደማይፈልግ ማወቅ ይኖርብኛል።
“እንግዲህ
ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና (ማቴ. 7፡12)። ይህችን አባባል ከመጸሃፍ ቅዱስ ልውሰዳት እንጂ በተለያየ
አገላለጽ በሁሉም ኃይማኖቶች እንዳለች ለማረጋገጥ ችያለሁ። በአንተ ላይ እንዲደረግብህ የማትፈልገውን መጥፎ ነገሮች ሁሉ በሌሎች
ላይ አታድርግ፤ በተመሳሳይ ለአንተ እንዲደረግልህ የምትፈልገውን መልካም ነገሮች ሁሉ ለሌሎችም አድርግ። ይህ ድንቅ ጥቅስ ነው። ይህ ጥቅስ የአብሮነትንና የመቻቻል መርህን ያጎለብታል።
የኃይማኖት ነጻነት በተከበረበት አገር የሁሉም ኃይማኖቶች መብት እኩል ይታያል እንጂ በተከታዮች መብዛትና ማነስ
ላይ የተመሰረተ የነጻነት ገደብ የለም። አንዳንድ ሃይማኖቶች ጥቂት ተከታዮች ስላላቸው የሚያጡት መብት የለም
እንዲሁም አንዳንዶቹ ደግሞ በርካታ ተከታዮች ስላሏቸው ከሌላው በተለየ መልኩ የሚያገኙት መብት አይኖርም። ሁሉም ኃይማኖቶች እኩል
ናቸው።
የሃይማኖቶች ነጻነት በህገ-መንግሥቱ መረጋገጥ መቻሉ ለአገራችን
ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ አንዱ ዋስትና ሆኗል። ዛሬ የግል ፍላጎትን ሃይማኖት ሽፋን ለማራመድ የሚደረግ
መሯሯጥ ካልሆነ በአገራችን የኃይማኖት ነጻነት ሙሉ ለሙሉ ተጋግጧል። በኃይማኖት ነጻነት መጓደል ሳቢያ ሊነሳ የሚችል ምንም ቀዳዳ የለም። በህገመንግስቱ ማንም የመረጠውን ኃይማኖት የመከተል መብት እንደተጎናጸፈ ሁሉ ኃይማኖት የለሽም
የመሆን መብት ህገመንግስታዊ ዋስትና አለው። የእኔ የኃይማኖት ነጻነት
መብት የሚረጋገጠው የሌሎችን የሃይማኖት ነጻነት መብት ማክበር እስከቻልኩ
ጊዜ ድረስ ብቻ ነው። ይህ የሚያሳየው የኃይማኖት ነጻነት መብት የሚረጋገጠው የሌላውን ማክበር እስከተቻለ ጊዜ ድረስ ብቻ ነው። የአንዱ ወገን
መብት የሚከበረው የሌላውን መብት ማክበር ሲችል መሆኑን
መገንዘብ ተገቢ ነው።
ባለፉት ዓመታት በአገራችን አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች በጋራ ወይም በተናጥል
በኃይማኖት ነጻነት ስም ድብቅ አጀንዳቸውን ለማራመድ ሲነቀሳቀሱ ታይተዋል። አክራሪነት ለአገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታም ይሁን ለልማታችን የሚበጅ አይደለም።
ምክንያቱም አክራሪነት የመቻቻል ጥንጣን፤ የአብሮነት ጠንቅ ነው፤ እንዲህ ያለ እኩይ ተግባርን በእንጭጩ ማስቀረት
ካልተቻለ አሸባሪነትን ያስከትላል።
የእምነት ጉዳይ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን አክራሪዎች ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ለግል ፍላጎታቸው ማሳኪያ ኃይማኖትን
እንደሽፋን መጠቀምን ይመርጣሉ። አክራሪዎች ሃይማኖተኞች አይደሉም።
ለኃይማኖትም ቍብ የላቸውም። ለሰብዓዊም ሆነ ዴሞክራሲያዊ መብቶች አይገዳቸውም። ይልቁንም በየትኛውም መንገድ ይሁን በማንኛውም ሁኔታ ድብቅ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ወደ ኋላ አይሉም።
እነዚህ አከላት የኃይማኖት አብሮነት፣ የኃይማኖት መቻቻል የሚባል ነገር እንዲኖር
አይፈልጉም። እነዚህ ነገሮች የሚዳብሩ ከሆነ አክራሪዎች ህልማቸው ሊሳካ እንደማይችል ያውቁታል። በመሆኑም አክራሪዎች የኃይማኖት
አብሮነትንና መቻቻልን የሚሸረሽሩ፣ በአንድ ኃይማኖት ውስጥ ሳይቀር
ተከታዮችን እርስ በርስ በመከፋፈልና እንዳይተማመኑ በማድረግ፤ የኃይማኖት መሪዎችን
ስም በማጥፋት
ከተከታዮቻቸው ጋር እንዳይስማሙና እንዳይተማመኑ የማድረግ
የተለያዩ የፈጠራ ውንጀላዎችን ያናፍሳሉ።
የኃይማኖት አብሮነት ማለት የሌላውን ኃይማኖት ልዩነት መቀበል ወይም ሰዎች የመረጡትን ኃይማኖት እንዲከተሉ መፍቀድ ማለት ነው። የኃይማኖት አብሮነት
እና መቻቻል ከግለሰብና ከቤተሰብ የሚጀምር ጉዳይ ሲሆን ማንም የራሱን
እምነት መምረጥ እንደቻለ ሁሉ የሌላውንም የመምረጥ መብት የሚያከብርበት፣ የራሱን እምነት በፍቅርና በሰላም ለሌላው የሚያካፍልበት ሁኔታ ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ በርካታ ቤተሰቦች የተለያየ እምነት እየተከተሉ በአንድ ቤት
የሚኖሩበት፣ የሚበሉበትና የሚጠጡበት ሁኔታ ያለበት እጅግ ድንቅ የሆነ የኃይማኖት መቻቻልና አብሮነት በህል የሰፈነባት አገር ናት።
እነዚህንና ሌሎችንም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች ለተመለከተው፣ በህብረተሰቡ መካከል ያለው የኃይማኖት
አብሮነት እና ትብብር በአገራችን ምን ያህል ስር የሰደደ እንደሆነ
መረዳት አያዳግትም፡፡ አገራችን የያዘችው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና የልማት ስራዎች ቀጣይነት ለማረጋገጥ ሰላማችንን ሊያውኩ የሚችሉ ቀዳዳዎችን መድፈን የሁላችንም ስራ መሆን ይኖርበታል። ከእነዚህ ነገሮች መካከል አንዱ ደግሞ በየቤተእምነቱ
ያሉ አክራሪዎችን ማጋለጥና ማውገዝ የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ
መሆን መቻል አለበት። እያንዳንዳችን ለኃይማኖት አብሮነት እና ትብብር ዘብ መቆም ይኖርብናል፡፡ የኃይማኖት አብሮነት እና ትብብር
ካለ ዘላቂ ሰላም ይኖራል፡፡ ዘላቂ ሰላም ለልማታችን ቁልፍ ሚና አለው፤ ባለፉት 13 ዓመታት አገራችን ባለሁለት አሃዝ ዕድገት ማስመዝገብ የቻለችው ሰላም በማግኘታችን ነው።
ህብረተሰቡ በየቤተዕምነታችን የሚታዩ አክራሪነትንና ጽንፈኝነት መገለጫ የሆኑ ከመዋጋት ባሻገር የችግሮቻችን ሁሉ
ምንጭ የሆነውን ድህነትን መዋጋት አንዱና ቀዳሚው ስራችን መሆን ይኖርበታል።
ልማትን አጠናክሮ መቀጠል፣ ሕገ-መንግሥታዊና በሰላም አብሮ ተቻችሎ የመኖር
ባህላችንን ማጎልበት፣ የኃይማኖት ተቋማት ሚዛናዊ አስተሳሰብ እንዲጎለብት ተከታዮቻቸውን ማስተማር፣ አክራሪው ኃይል ሃይማኖታዊ ይሁንታን
እንዳያገኝ በተከታዮች ላይ የጠራ አመለካከት ለማስያዝ መንቀሳቀስ፣ የሃይማኖት ተቋማት የሠላምና የአብሮነት ተቋማት መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ መንግስትም የተጣለበትን
የህግ ማስከበር ስራ መስራት አክራሪነትንና ጽንፈኝነት ቦታ እንዳይኖራቸው
ያደርጋል።
የመንግስት አሰራርና ኃይማኖት ለየቅል ይሁኑ እንጂ አይነኬ አይደሉም። መንግስት ስርዓት የማስከበር
ሃላፊነት አለበት። ስርዓት ማስከበር የማይችል መንግስት፣ መንግስት
ሊሆን አይችልም። አገርም እንደአገር ልትቀጥል አትችልም። መንግስት በየትኛውም ስፍራ በማንኛውም ጊዜ የህግ የበላይነትን የማስከበር
ግዴታ አለበት። ይህ የመንግስት ተግባር ከጣልቃ ገብነት ሊወሰድ አይገባም።
ሁላችንም የህግ የበላይነት እንዲከበር የበኩላችንን አስተዋጽዖ ማድረግ
ይኖርብናል። አክራሪነት በኃይማኖት ሽፋን ለየሚፈፀም ፖለቲካዊ ቁማር ነው። አክራሪዎች የረጅም ጊዜ እቅድ አዘጋጅተው ራሳቸውን የኃይማኖት ተቆርቋሪ የኃይማኖት ደቀመዝሙር አድርገው በማቅረብ የግል ፍላጎታቸውን ለማሳከት ኃይማኖትን እንደሽፋን ይጠቀማሉ። ይህን የአክራሪዎች
መሰሪ አካሄድ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊያውቀውና ሊያወግዘው
ይገባል።
No comments:
Post a Comment