ኢብሳ ነመራ
ደቡብ
ሱዳናውያን ነፃነታቸውን ለማግኘት ግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ተዋግተዋል። በሱዳን ሕዝብ የነፃነት ንቅናቄ ወይም Sudan People Liberation Movement (SPLM) ታጋዮችና
በሱዳን ሪፑብሊክ መንግስት መካከል ለሃምሳ ዓመታት ያህል ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለበት ጦርነት ሲደረግ ቆይቶ እ. ኤ. አ.
በ2005 ዓ.ም. በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች መካከል የሰላም ስምምነት ተፈረመ። በዚህ የሰላም ስምምነት መሰረት የደቡብ ሱዳን ሕዝብ
እጣ ፈንታውን በሕዝበ ውሳኔ እንዲወስን መግባበት ላይ ተደርሶ ነበር። በዚህ መሰረት በ2011 በተካሄደ ሕዝበ ውሳኔ ደቡብ ሱዳን
ነፃ አገር ሆነች። አዲሷ የዓለማችን አገር ሆና የተመዘገበችው ደቡብ ሱዳን የተፋላሚው ፓርቲ የሱዳን ሕዝብ የነጻነት ንቅናቄ የወቅቱን
መሪ ሳልቫ ኪርን የመጀመሪያ ፕሬዝዳንቷ አደረገች።
ደቡብ
ሱዳን ነፃነቷን ለመቀዳጀት ያበቃት ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ መግባባት ላይ በተደረሰበት የ2005ቱ የሰላም ስምምነት ሌሎች ጉዳዮችም
በተመሳሳይ ሁኔታ በሕዝብ ውሳኔ ያገኛሉ የሚል መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር። ለምሳሌ፤ በነዳጅ የበለጸገችው የአቢዬ ግዛት እጣ ፈንታ
በሕዝበ ውሳኔ እንዲረጋገጥ ተበሎ የነበረ ቢሆንም ይህ ከመሆኑ በፊት አዲሱ የደቡብ ሱዳን መንግስት ከሱዳን ሪፑብሊክ ጋር ወደግጭት
ሊያመራ የሚችል አለመግባባት ተፈጠረ። ለነጻነት በተደረገው የትጥቅ ትግል ከደቡብ ሱዳን ጋር ሆነው የካርቱምን መንግስት ሲዋጉ ነበር
የሚባሉት የደቡብ ኮርዶፋን እና የብሉ ናይል ግዛቶችም ጉዳይ እልባት ስላልተበጀለት አሁንም የግጭት ስጋት መሆናቸውን የሚያመለከቱ ጥናቶች አሉ።
ደቡብ
ሱዳንና የሱዳን ሪፑብሊክ በነዳጅ በበለጸገችው አቢዬ ሳቢያ ፍጥጫ መግጠማቸውን ተከትሎ ፍጥጫው ወደለየለት ጦርነት እንዳያመራ ጉዳዩን
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይዞታል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አለመግባበቱ በሰላማዊ መንገድ እስኪፈታ ድረስ የይገባኛል
ጥያቄ በተነሳበት አካባቢ ሰላም አስከባሪ ሃይል እንዲሰፍር ይወስናል። በዚህ ጊዜ ሁለቱም መንግስታት ማለትም፤ የደቡብ ሱዳንና የሱዳን
ሪፑብሊክ መንግስታት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲሰፍር በአንድ አፍ ተስማሙ። በዚህ መሰረት በአቢዬ ግዛት የኢትዮጵያ
መከላከያ ሰራዊት የተመደ ሰላም አሰከባሪ ኃይል ሆኖ ሰፍሯል። አሁንም ይህን ሰላም የማስከበር ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል።
ኢትዮጵያ
በሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች በተመሳሰይ ውሳኔ የተመደ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት እንድታሰፍር መመረጧ ከምንም በላይ ለሰላም መከበር ያላትን
አቋም የሚያረጋግጥ ነው። የደቡብ ሱዳንም ሆነ የሱዳን ሪፑበሊክ መንግስታት “ኢትዮጵያ ለማንም ሳትወግን ሰላም የማስከበር ኃላፊነት
ትወጣለች” በሚል የጣሉባት እምነት ለራሷና በአጠቃላይ ለቀጣናው ሰላም መስፈንና መረጋጋት ያላትን ፅኑ ፍላጎትና ዝግጁነት ያሳያል።
እንግዲህ
በተመሰረተች በማግስቱ ከሱዳን ሪፑብሊክ ጋር አለመግባባት ውስጥ የገባችው ደቡብ ሱዳን ችግሯ በዚህ አላበቃም። ነፃ መንግስት በሆነች
በሁለተኛው ዓመት በ2013 በእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ገብታለች። ይህን የእርስ በርስ ግጭት አስመልክቶ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች፣
አዲሲቷ አገር ደቡብ ሱዳን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ ሁኔታዋ ገና ያልጠነከረች፤ እንዲሁም ስር በሰደደ ችግር የተተበተበች
እንደሆነች ይናገራሉ። በተለይ፤ የሱዳን ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ (SPLM) ከነፃ አውጪ ታጋይነት ወደገዢ ፓርቲነት ያደረገው ሽግግር
ችግር እንዳለበት ነው የሚናገሩት። ፓርቲው በአመዛኙ በ2005 ከተደረገው የሰላም ስምምነት በፊት የነበረውን ወታደራዊ የስልጣን
ተዋረድ የተከተለና የፓርቲውን አመራሮች ሥርዓት ማስያዝ የሚያስችል ራሱን በራሱ የሚቆጣጠረበት ወይም ቅሬታዎችን የሚፈታበት አሰራር
አልነበረውም። እንደተንታኞቹ አተያይ።
ደቡብ
ሱዳን በአንድ ፓርቲ የበላይነት ሥርዓት የምትመራ አገር ነች፤ ምንም ተቃዋሚ ፓርቲ የላትም። የሽግግር መንግስቱ ሕገመንግስትም በመንግስት
አካላት መካከል ያለውን የስልጣን ክፍፍል በግልፅ ያላስቀመጠ ከመሆኑ ባሻገር፣ ቅጥ ያጣ ሙስና ተነሰራፍቶ ነበር።
እነዚህ
ከላይ የሰፈሩ ሁኔታዎች በፓርቲው (SPLM) ውስጥና በመንግስት አመራሮች መካከል የሚፈጠር አለመግባባትን መፈታት እንዳይቻል፤ አለመግባባቶች
በቀላሉ ወደ ግጭት እንዲያመሩ በማድረግ ረገድ አስተዋፅኦ እንዲያመሩ ማድረጋቸውን ነው ተንታኞች የሚናገሩት። በደቡብ ሱዳን የተቀሰቀሰውና
እስካሁን የዘለቀው የእርስ በርስ ግጭት መንስኤ ከላይ የተጠቀሱት ፖለቲካዊ ሁኔታዎች መሆናቸውንም ተንታኞች ያምናሉ።
እንግዲህ አዲሲቷ አገር ደቡብ ሱዳን በውስጣዊ
አለመግባባት መናጥ የጀመረችው በተመሰረተች በሁለተኛው ዓመት በ2013 ላይ ነበር። በፓርቲውና በመንግስት ከፍተኛ አመራሮች አለመግባባት
አያደረ በፕሬዝዳንቱ ሳልቫ ኪርና በምክትላቸው ሪክ ማቻር መካከል የከረረ አለመግባባት አስከተለ። በ2013 ሚያዚያ ወር ላይ ሳልቫ
ኪር የማቻርን ስልጣን ገፈፉ። ሌሎች የፓርቲውን አመራሮችም አገዱ። ይሄኔ ተቃዋሚዎቻቻው ስልጣናቸውን ያለአግባብ እየተጠቀሙበት ነው
ብለው ወነጀሏቸው። ኪር በበኩላቸው ያገለሏቸው ባለስልጣናት ለመፈንቅለ መንግስት እየተዘጋጁ ናቸው ብለው ተናገሩ። ይህ ሁኔታ ተጋግሎ
ታህሳስ ላይ ወደመሳሪያ ግጭት ተሸጋገረ።
በሳልቫ ኪር የሚመራው የሱዳን ህዝብ የነፃነት
ንቅናቄ (SPLM) እና በሬክ ማቻር የሚመራው በዚሁ ፓርቲ ውስጥ የተፈጠረ ተቃዋሚ መካከል በጁባ የጀመረው ውጊያ ወደሌሎች የአገሪቱ
አካባቢዎችም ተዛመተ። ግጭቱ ቀደም ሲል በዚህ ፅሁፍ የተገለፀው ውስጣዊ ፓለቲካዊ ሁኔታ የፈጠረው ቢሆንም፣ አለመግባባቱ ወደመሳሪያ
ውጊያ ካደገ በኋላ ሁለቱም ወገኖች ደጋፊ ለማግኘት የብሄር መታወቂያቸውን አውጥተው የየራሳቸውን ብሄር አባላት አሰልፈው ግጭቱ መልኩ
ወደብሄር የእርስ በርስ ግጭት ተቀየረ። በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር በኩል የዲንካ ብሄር አባላት ሲሰለፉ፤ በሬክ ማቻር በኩል ደግሞ
ኑዌሮች ተሰለፉ። በአጭሩ በዚህ አኳኋን መልኩን ቀይሮ ወደአስከፊ የእርስ በርሰ ግጭትነት የተቀየረው የደቡብ ሱዳን አለመግባባት
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናውያንን ለሞት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ከመኖሪያ ቀዬአቸው ለመፈናቀል፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩትን
ደግሞ ለስደት ዳርጓል።
ይህ ደቡብ ሱዳናውያንን ለአስከፊ እልቂት፣
ለሰብአዊ መብት ጥሰትና ለእንግልት የዳረገ ግጭት ኢትዮጵያን ያሳሰበው ገና በጠዋቱ ነበር። ኢትዮጵያ በኢጋድ አማካኝነት ሁለቱ ተፋላሚ
ወገኖች ለሕዝባቸው ሰላምና ልማት ብለው አለመግባባታቸውን በውይይት
እንዲፈቱና ሰላምና መረጋጋት እንዲያሰፍኑ ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች። ይህ የኢትዮጵያ የሰላም ጥረት መነሻውም መድረሻውም፣ የደቡብ ሱዳናውያን ሰላም
የቀጠናው ሰላም አካል በመሆኑና በዚህ አካባቢ የሚከሰት የሰላም እጦት የአካባቢውን ልማትና የዜጎችን የመኖር ዋስትና ስለሚያናጋ
ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ብቻ ነበር።
ኢትዮጵያ በኢጋድ አማካኝነት ግንባር ቀደም
ሚና የተጫወተችበት በሁለቱ የደቡብ ሱዳን ቡድኖች መካከል የተፈጠረውን ግጭት አስቁሞ ሰላም እንዲሰፍን የማድረጉ ሂደት አስቸጋሪና
እልህ አስጨራሽ ነበር። ሁለቱ ወገኖች ግጭት ውስጥ ከገቡበት ወቅት ጀምሮ ወደመግባባት ለመምጣት ቢያንስ ሰባት ያህል ድርድሮች አካሂደው
ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ስምምነቶቹ ግን ገና የፊርማው ቀለም ሳይደርቅ፤ አንደኛው ወገን ሌላውን እየወነጀለ በማግስቱ የሚፈርሱ
ነበሩ። በመጨረሻም ሐምሌ 2015 ላይ ያደረጉት ስምምነት የረጋ መሰለ። በዚህ የሐመሌ ስምምነት ሁለቱ ወገኖች ተኩስ ለማቆም፣ ሬክ
ማቻር ወደምክትል ፕሬዝዳንትነት ቦታቸው እንዲመለሱ፣ ለ30 ወራት ያህል አገሪቱን የሚያስተዳደር የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት፣
የሽግግር መንግስቱ የቆይታ ጊዜ ሊያበቃ ጥቂት ሲቀረው የፕሬዝዳንት ምርጫ ተካሂዶ መንግስት እንዲመሰረት ነበር ተስማምተው የተፈራረሙት።
በዚህ መሰረት ሚያዚያ 2016 ላይ ማቻር ወደጁባ ገብተው የምክል ፕሬዝዳንትነት መንበራቸውን እንደገና ተረከቡ።
በዚህ የደቡብ ሱዳን ግጭት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን
በላይ የሚሆኑ ዜጎች በአገር ውስጥ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። ሶስት መቶ ሺህ የሚደርሱ ወደኢትዮጵያና ወደኡጋንዳ ተሰድደዋል። በአስር
ሺዎች የሚቆጠሩ ህይወታቸውን አጥተዋል። ይህን አስከፊ እልቂት ያስከተለ ግጭት እንዲቆምና በደቡብ ሱዳን ሰላም እንዲሰፍን በኢጋድ
አማካኝነት በተደረገው የሰላም ጥረት ውስጥ ኢትዮጵያ የማይተካ ሚና ተጫውታለች።
የደቡብ ሱዳን ጉዳይ በዚህ ሁኔታ እልባት አገኘ
ተብሎ የአገሪቱ ዜጎች ለሶስት ወራት እንኳን የሰላም አየር ሳይተነፍሱ ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ግጭቱ አገረሸ። እንደተለመደው በጁባ
በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርና በምክትላቸው ሪክ ማቻር ቡድኖች መካከል፤ በዚህ ግጭት ከ300 በላይ ሰዎች ሞተዋል፤ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ
ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል። አሁን ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ቢሆኑም ግጭቱ በማንኛውም ጊዜ እንደገና
ሊቀሰቀስ እንደማይችል መተማመኛ የለም። በመሆኑም ስጋት ሆኖ እንደቀጠለ ነው።
ይህን ያገረሸ የደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ
ግጭት አርግቦ ሰላም ማስፈን በተለይ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና፤ ብሎም ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ነው። በመሆኑም በቅርቡ በሩዋንዳ
ኪጋሊ በተካሄደ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎቸ ጉባኤ ላይ ጉዳዩ ተነስቷል። ህብረቱ በዚህ ስበሰባው በ2005 በሱዳን ሪፑብሊክና በሱዳን
ህዝብ የነጻነት ንቅናቄ (SPLM) መካከል የሰላም ስምምነት በተፈረመበት ወቅት በደቡብ ሱዳን የሰፈረው የተመድ ሰላም አስከባሪ
ኃይል ግጭት በተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች በሙሉ እየተዘዋወረ ሰላም ከማስከበር ይልቅ በካምፕ ተወስኖ የሚቀመጥ በመሆኑ፣ አስፈላጊ
በሆነበት ቦታ በሙሉ እየተንቀሳቀሰ ሰላም የሚያስከብር ከአፍሪካ ህብረት አባል አገራት የተውጣጣ የተባባሩት መንግስታት አዲስ የሰላም
አስከባሪ ኃይል መስፈር አለበት የሚል አቋም ይዟል። ከአፍሪካ ህብረት አባል አገራት የሚወከለው ሰላም አስከባሪ ኃይልም ከኢትዮጵያ፣
ከኬንያና ከሩዋንዳ የተወጣጣ እንዲሆን ተወስኗል። ይህ ጉዳይ ለውሳኔ ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ቀርቧል።
ከአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር
ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ላይ ከተመድ ዋና ፀሃፊ ባን ኪ ሙን ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱ በደቡብ ሱዳን እንደገና የተቀሰቀሰውን ግጭት ለመፍታት ኢትዮጵያ ስታደርግ የነበረውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ባን ኪ ሙን ጥሪ አቅርበዋል። የደቡብ ሱዳን ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመሆኑ የመንግስታቱ ድርጅት በትኩረት እንደሚከታተለው የገለፁት ባን ኪ ሙን፣ ኢትዮጵያም በደቡብ ሱዳን ሰላም እንዲሰፍን የምታደርገውን ያላሰለሰ ጥረት አጠናክራ እንድትቀጥል አጥብቀው ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም በበኩላቸው የደቡብ ሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ አሳሳቢና ከአገሪቱ መሪዎች ጋር በቅርበት መስራትን እንደሚጠይቅ ገልፀው፣ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ሊቀ መንበርነቷ ችግሩን ከጎረቤት አገራት ጋር ለመፍታት እየሰራች እንዳለችም አስረድተዋል።
እንግዲህ ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን
እንድታረጋግጥ ከማድረግ ጀምሮ ከነፃነት በኋላም ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ አጋር ሆና ቆማለች። ከሱዳን ሪፑበሊክ ጋር በአቢዬ ግዛት
የገጠማቸውን አለመግባባት ወደለየለት ጦርነት ሳያመራ በሰላማዊ መንገድ ብቻ ለማድረግ የበኩሏን ጥረት አድርጋለች። በደቡብ
ሱዳንና በሱዳን ሪፑብሊክ ጥያቄ እስካሁንም ድረስ የኢትዮጵያ ሰራዊት የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል አካል ሆኖ ሰፍሮ ይገኛል።
በ2013 በደቡብ ሱዳን መንግስት መሪዎች መካከል በተፈጠረ አለመግባበት ግጭት ሲቀሰቀስም ሁለቱ የደቡብ ሱዳን ወገኖች ለሕዝባቸው
ሲሉ ሰላም እንዲያሰፍኑ ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባን ኪ ሙን አሁንም ኢትዮጵያ
ያገረሸው የደቡብ ሱዳን ግጭት ሰላማዊ እልባት እንዲያገኝ እንድትሰራ ጥሪ ያቀረቡት የከዚህ ቀደሙን የሰላም ጥረቷን መነሻ
በማድረግ ነው። ኢትዮጵያ የጎረቤት አገራት ሰላም ለራሷም ሰላምና ልማት ስለሚጠቅም በደቡብ ሰላም ሰላም እንዲሰፍን
የምታደርገውን ጥረት አጠናከራ ትቀጥላለች።
No comments:
Post a Comment