Thursday, 28 July 2016

ጃስ ባዩም ከህግ ተጠያቂነት አያመልጥም!




ወንድይራድ ኃብተየስ
ቅሬታቸውን ለመግለጽ ወይም የተቃውሞ ድምፅ ለማሰማትና አቤቱታ ለማቅረብ፣  ወደ ወይም ድጋፍን ለመግለጽ አደባባይ መውጣት ህገመንግስታዊ መብት ነው። ይሁንና እንዲህ ያሉ መብቶች ተጠያቂነትም እንዳለባቸው  ማወቅ ተገቢ ነው። ግርግር ለሌባ ይመቻል እንደሚባለው አንዳንዶች የህዝብን ጥያቄዎች ከለላ በማድረግ ህገወጥ ተግባራትን ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ ታይተዋል። እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎችን  አሰፍስፈው የሚጠብቁ አካላት ቀላል የሚባሉ አይደሉም።

በተለያዩ  አገራችን ክፍሎች አንዳንድ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች በቅርቡ ደግሞ በሰሜን ጎንደር ዞን የህዝብን  ጥያቄዎች ከለላ በማድረግ ወይም ህዝብን በተሳሳተ ዓላማቸው ዙሪያ በማሰባሰብ የግል  ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ  በህገወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርተው የንጹሃን ህይወትና ንብረት ውድመትን አስከትለዋል። እንዲህ ያሉ ወራዳ ድርጊቶችን በመፈጸም ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨትና የግል ፍላጎታቸውን ለማሟላት  የሚሯሯጡ ቡድኖችንና ግለሰቦችን ህብረተሰቡ ሊቃወማቸውና ሊያወግዛቸው ይገባል።

እነዚህ ሃይሎች አገራችን እንድትረጋጋ አይፈልጉም። የህዝባችንን አብሮነትና አንድነት የሚሸረሽሩ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ አካላትን ከመንግስት ጎን ቆመን ልናወግዛቸው ወደ ህግ እንዲቀርቡና ለፈጸሙት እብደት እንዲጠየቁ ማድረግ  ይገባል። 

ትክክለኛ ተቃውሞ ያለው ሰልፈኛ የሰውን ሕይወትና ንብረት ለማውደም ፍላጎት የለውም። ይሁንና  በሰላማዊ ተቃውሞ መሃል ዝርፊያንና ጥቃትን ለመፈጸም  የሚሯሯጡ አካላት እንዳሉ በተደጋጋሚ ተመልክተናል። ይህ ድርጊት የህገመንግስቱን መርህ የሚቃረን ነው። ማንኛውም ግለሰብ በየትኛውም አካባቢ ሰርቶ የመኖር፣ ሃብት የማፍራትና በነጻነት የመኖር መብት አለው። ይህን መብት ማንም የሰጠው ማንም ሊነፍገው የማይችል የኢፌዴሪ ህገመንግስት ያረጋገጠለት መብት ነው። የፌዴራል ስርዓቱም ይህን መርህ መሰረት ያደረገ ነው። ይህን መርህ መቃወም ኢ-ህገመንግስታዊ አሰራር ነው።  በዚህ ህገወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት ሁሉ ከተጠያቂነት ሊያመልጡ አይችሉም።
የፌዴራል ስርዓታችን በአገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ በህዝቦች መካካል መተማመን እንዲፈጠርና የአገሪቱ  አንድነት እንዲጠበቅ  አድርጓል። ይሁንና እንዲህ ያሉ መልካም ነገሮችን ያስመዘገበ የፌዴራል ስርዓት ለመበጥበጥ አንዳንዶች ሲሯሯጡ ታይተዋል። የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ብሄርን ከብሄር፣ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚሯሯጡ አካላትን ወደ ህግ እንዲቀርቡ የማድረግ ስራ የሁላችንም ሰላም ወዳድ አካላት ተግባር መሆን ማሳየት መሆን መቻል አለበት።
የፌዴራል ስርዓታችንን  ለመቃወም በዋነኝነት ሁለት ፅንፎች እርስ በርስ ሲጓተቱ ይስተዋላሉ። የመጀመሪያዎቹ ጽንፈኞች የሞተንና የተቀበረውን "የቀድሞውን አህዳዊ ስርዓት መመለስ  አለበት፤ እኛ በምንለው መንገድ ይህች አገር ካልተመራች ወይም እኛ ካላስተዳደርናት “አንድነትና ኢትዮጵያዊነት” ሊኖር አይችልም፣ እኛ ብቻ አዋቂ፣ እኛ በቻ ኢትዮጵያዊ" የሚሉ ናቸው። እነዚህ አካላት አብረው የኖሩ ህዝቦችን በማጋጨት፤    ኢትዮጵያዊነትን በሃይል በሌሎች ላይ  ለመጫን የሚፈልጉ አካላት ናቸው። እነዚህ አካላት በቅርቡ በሰሜን ጎንደር የታየውን ሁከትና ብጥብጥ ሲመሩና ሲያደራጁ ነበር።

በሌላኛው  ጽንፍ  ደግሞ አብረው የኖሩ ህዝቦችን ለመነጣጠል፣ ኢትዮጵያ የሚለውን ስያሜ መስማት የማይፈልጉ፣  አብሮ የመኖር  ፈይዳ የማይታያቸው፣ ያለፈው ስርዓቶች አደረሱ የተባለውን በደል አሁን ላይ ለማወራረድ  ህዝቦችን የሚያነሳሱ፣ ጽንፍ የወጣ የብሄር አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ናቸው። እነዚህን አካላት በቅርቡ በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በተነሳ ሁከት ተመልክተናቸዋል።

እነዚህን ሁለት ጽንፎች አንድ የሚያመሰሳስላቸው ሁለቱም ሁከት ቀስቃሾች መሆናቸውና ንጹሃንን በማጋጨትና ደም በማፍሰስ፣ ጽጥታ ሃይሎች በመግደልና በማቁሰል፣ የመንግስትንና የንጹሃንን  ንብረት በማውደም፤ ወደ ስልጣን መሰላል መሰቀል የሚፈልጉ መሆናቸው ነው። እነዚህ ሁለት የሚጠፋፉ ጽንፎች በአንድ ላይ ገጥመው ዴሞክራሲያዊውን ስርዓት ለማፍረስ ሲሯሯጡ መመልከት እጅግ አስገራሚ ነገር ነው።

እነዚህ አካላት ስለመቻቻል፣ ስለእኩልነት፣ ስለአብሮ መኖር ወዘተ አይሰብኩም። እነዚህ አካላት ስለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጎልበት፣ ስለዕድገትና ልማት እንዲሁም ስለህዝቦች አብሮነት ሲናገሩ አይደመጡም። እነዚህ አካላት ህዝቦችን ለማጋጨት አበክረው ይሰራሉ።

እነዚህ ሁለት ጽንፎች ኢትዮጵያንና  ኢትዮጵያዊነትን የተለየ ትርጉም ይስጡት እንጂ፤ የእኛይቱ ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያዊነትም  በፍቃደኝነት እንጂ በሃይል የተጫነብን   ነገር  እንዳልሆነ በተግባር አሳይተናል። አገራችን አለምን ያስደመመ ላለፉት 13 ዓመታት ተከታታይ ባለሁለት አኃዝ ዕድገት ማስመዝገብ ችለናል። የህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ህገመንግስታዊ ዋስትና አገኝተዋል።   

ለአገራችን ሰላም መሰረቱ የአገራችን ህገ-መንግስት ነው። ህገ-መንግስታችን ለቆዩ ችግሮቻችን እልባትን አስገኝቷል።  የፌዴራሊዝም ስርዓታችን ያስተማረን ትልቅ ነገር መቻቻልና መከባበርን ነው። ይሁንና ይህን እሴታችንን የሚሸረሽሩ ድርጊቶች በየአካባቢው እያስተዋልን ነው። በቅርቡ በሰሜን ጎንደር ዞን የተደረገው ድርጊት አግባብነት የሌለው ግለሰቦችን ለመጉዳት አትኩሮ መንቀሳቀስ ኢትዮጵያዊ ባህል አይደለም። በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የለውም። በዚህ ድርጊት የተሰማራም ሆነ ያሰማራ ሃይል መጠያቅ ይኖርበታል።

የአገራችን ህገ-መንግስት የቡድንና የግለሰብን ሰባዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚያስከብር፣ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህሎችንና ኃይማኖቶችን  እኩልነት  ያረጋገጠ የአዲሲቷ  ኢትዮጵያ የህልውና መሰረት ነው፡፡ አገራችን  የህዝቦቿን ህብረ ብሔራዊነት ተቀብላ ማስተናገድ ከጀመረችበት ከ1983 ወዲህ  ህዝቦቿ ተከባብረውና ተደጋግፈው አንድ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት  የሚረባረቡባት አገር መሆን ችላለች። ይህን አለመቀበል ወይም የተለያ ሃሳብን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማራመድ ህገመንግስታዊ መብት ነው። ነገር ግን ልዩነትን በሃይል ለማራመድ መሞከር አግባብነት የጎደለው አካሄድ ነው።

በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች ተጨማሪ ጥናት የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም ፌደራሊዝም ስርዓታችን የፈጠራቸው ችግሮች እንዳልሆኑ  በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ በህግ መንግስቱ የተቀመጡ የፌደራሊዝም  መርሆዋችና እሴቶችን በአግባቡ በመፈፀም ላይ ውስንነቶች ቢታዩም እንዲህ ያለ ግለሰቦችን ለመጉዳት ታስቦ የሚደረግ እንቅስቃሴዎችን ግን  የፌዴራል ስርዓቱ ክፍተት ተደርጎ መወሰድ የለበትም። የፌዴራል ስርዓታችን የቡድኖችን መብት ብቻ ሳይሆን  የግለሰቦችንም ማንኛውንም መብት ማረጋገጥ የቻለ አገራችን ዘላቂ ሰላም እንድታገኝ ያስቻለ ስርዓት ነው።                       

ብዙህነት ዋጋ የሚከፈልለት እንደመሆኑ መጠን በአሁኑ ወቅት ብዙህነትን የሚሸረሽሩ አንዳንድ ለይቶ የማጥቃት ጅማሮዎች እየታዩ ነው። እንዲህ ያሉ ቅጥ ያጡ አካሄዶችን ገና በእንጭጩ መቅረፍ የመንግስት ስራ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ተግባር መሆን መቻል አለበት። ይህ ተግባር የህገመንግስቱን መርህ ይቃረናል። ለአገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጎልበትም ሆነ ከድህነት ለመውጣት ለምናደርገው ርብርብ የሚበጅ አይደለም።
Bottom of Form

የሰላማዊ ተቃውሞም ሆነ የድጋፍ ሰልፎች ህገመንግስታዊ መብቶች ናቸው። ይሁንና እነዚህ ነገሮች በህግ አግባብ መካሄድ ይኖርባቸዋል።  ንግስት በየትኛውም አካባቢ በየትኛውም ሰዓት የዜጎችን ሰባዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የማስጠበቅ ግዴታ አለበት። ይህን ማስጠበቅ የማይችል መንግስት መንግስት ሊባል አይችልም።  እኛስ መብቶቻችንን ስንጠይቅ በራሳችን አቅም ሰላማዊ ተቃውሞን ተገን አድርገው የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚያሯሩጡ አካላትን ለህግ አሳልፈን በመስጠት የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የማድረግ ስራ የሁላችንም ተግባር መሆን ይኖርበታል።

No comments:

Post a Comment