የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 35 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በጀት አፀደቀ
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ለ2009 በጀት ዓመት የሚውል 35 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በጀት አፀደቀ።የአስተዳደር ምክር ቤቱ ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሦስተኛ መደበኛ ጉባዔውን በ2008 በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርትና በ2009 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ መክሯል።
ከአጠቃላይ በጀቱ 20 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል ሲሆን፣ ለመደበኛ ወጪዎች 12ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቧል።
ለመጠባበቂያ ደግሞ 2ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡን የአስተዳደሩ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ያቀረበው ሰነድ ይገልጻል።
ምክር ቤቱ የአስተዳደሩ ዋና ኦዲተር ያቀረበውን የ2008 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት አድምጧል።
ዋና ኦዲተር ወይዘሮ ፅጌወይኒ ካሳ ባቀረቡት ሪፖርት በዚህ በጀት ዓመት በስድስት ተቋማት 584 ሺህ 926 ብር የጥሬ ገንዘብ ሂሳብ ጉድለት መገኘቱን ገልጸዋል።
በተቋማቱ የገንዘብ ጉድለት የታየው የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓት ባለመጠናከሩ መሆኑንም አስረድተዋል።
ይህም ለመንግሥት ገንዘብ ብክነትና ምዝበራ ያጋለጠ በመሆኑ በጉድለት በታየው ጥሬ ገንዘብ ጉዳይ ህጋዊ እርምጃ መወሰድ እንደሚገባ ዋና ኦዲተሯ አሳስበዋል።
የገንዘብ ጉድለት በታየባቸው ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ለምክር ቤቱ እንደሚቀርብ ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ 367 ሺህ ብር የሚጠጋ ያልተመዘገበ የጥሬ ገንዘብ ገቢ እንዲሁም ከ3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ የጥሬ ገንዘብ ወጪ በኦዲት ወቅት መገኘቱን ወይዘሮ ፅጌወይኒ ጠቅሰዋል።
በኦዲት
ሪፖርቱ አንዳንድ ተቋማት በተጋነነ ዋጋ የቢሮ ዕቃዎችን መግዛታቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ ለአብነትም የአዲስ አበባ
መንገዶች ባለሥልጣን ለ17 ተሽከርካሪዎች ግዢ 34ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉ ተገልጿል።
በዚህ ዓመት በክትትልና ቁጥጥሩ የታዩት ክፍተቶች የህዝብን ጥቅም የሚያሳጡ በመሆናቸው በቀጣይ በጀት ዓመት እንደሚጠናከሩ ገልጸዋል።
በዚህም በግብረ መልስና በመስክ ምልከታ ችግሮችን በመለየት ፈጥነው ምላሽ በማይሰጡና ሪፖርት በወቅቱ የማይልኩ ተቋማት እንዲታረሙ ማድረግ ከምክር ቤቱ ይጠበቃል ብለዋል ዶክተር ታቦር።
ምክር ቤቱ በከተማ አስተዳደሩ የ2009 በጀት ዓመት አቅጣጫ ላይም መክሯል።
የከተማው ከንቲባ ድሪባ ኩማ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት በ2008 በጀት ዓመት የታዩ ውጤቶችን ለማጎልበትና የአፈጻጸም ችግር የታየባቸው ተቋማትን በማረም የተጀመረውን የልማት ሰራዊት ግንባታ ሥራዎች ወደ ላቀ ደረጃ የሚሸጋገርበት ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በ2009 በጀት ዓመት የሚከናወኑ ሥራዎችን በጥራትና በብቃት ለማስቀጠልና ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት በአመለካከት፣ክህሎትና ግብዓትን መሠረት ያደረጉ ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።
ለዕቅዱ ስኬታማነትም የህዝቡን ተሳትፎ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ሥራዎች፣አዲሱን የከተማ ፕላን የሚያስፈጽም አደረጃጀትና የህግ ማዕቀፍ መፍጠር ፣ሥራ አጥነትን መቀነስ፣ልማታዊ የመሬት ልማት አስተዳደር መፍጠርና ማጠናከር እንደሚተኮርባቸው ከንቲባው ጠቁመዋል።
No comments:
Post a Comment