ስሜነህ
የአዲስ
አበባ ከተማ አስተዳደር አሥረኛውን ማስተር ፕላን በይፋ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅቱን ስለማጠናቀቁ ሰሞኑን ገልጾልናል፡፡
አስተዳደሩ የተዘጋጀውን ማስተር ፕላን በተመለከተ በሰጠው መግለጫ፤የመኖሪያ
ቤቶችን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ 1.2 ሚሊዮን ቤቶች እንደሚገነቡ አስታውቋል፡፡ በመንግሥት
ከሚገነቡት ከእነዚህ ቤቶች በተጨማሪ በግሉ ዘርፍ የሚገነቡ የንግድ ተቋማት (ቅይጥ) ከንግድና ከአገልግሎት መስጫዎች ጋር
አፓርታማዎችን መገንባት እንዳለባቸው በማስተር ፕላኑ ምክረ ሐሳብ ላይ ቀርቧል፡፡
ይህ ትርክት ደግሞ ይህንኑ ማስተር ፕላን ከመሬት ወረራ ጋር
ተያይዞ በአገሪቱ በየወቅቱ በልቀቅ አልለቅም የሚከሰቱትን ግብግቦችና በዚህም የሰውን ህይወት ጨምሮ የሚደርሱ ጥፋቶችን
ከማስቀረት አኳያ ያለውን ፋይዳ ይቃኛል። የመሬት ጉዳይ በአገራችን በነበሩ መንግስታት ሁሉ የጠብ እና በሕዝቦች መካከል
የልዩነት መንስኤ ሆኖ ለዘመናት የዘለቀ መሆኑና በዚህ መንግሥት ህገ መንግሥታዊ መፍትሄ ተሰጥቶትም የውዝግብ መንስኤ እየሆነ
ማየት የተለመደ ነው። ካለፉት መንግሥታት የሚለየው የአሁኑ መሬት ነክ ውዝግብ ከየከተሞቻችን መሪ ፕላን ማጣት ጋር ተያይዞ
የሚከሰት የኪራይ ሰብሳቢነት አጀንዳ መሆኑ ብቻ ነው።ስለሆነም መሬትን በአግባቡ ለመጠቀምና የህዝብ መሆኑን ለማረጋገጥ ከሚወሰዱ
እርምጃዎች ሁሉ፤ ይልቁንም ከወረራው ኋላ ለሚነሱ ውዝግቦች መቋጫ ለመስጠት ብቸኛው መደላድል እንዲህ ዓይነት ዘመናዊ እና
ዘላቂነት ያለው መሪ ፕላን መሆኑ አያጠያይቅም።
ሌላውንም በዚህ ቅኝት እያሰላን ተደጋጋሚ ውዝግቦች በማስተናገድ
ላይ ያለችውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሪ ፕላን መመልከቱ ከፋይዳ አንጻር ጥሩ ግንዛቤ ይሰጠናል። አዲስ
አበባ ብቻ ሳትሆን ሌሎች ከተሞችም ሆኑ የገጠር ቀበሌዎች ያላቸውን መሬት በቁጠባ መጠቀም አለባቸው፡፡ በዚህ መርህ
መሠረት በከተሞች ከመሬት እጥረት ጋር ተያይዞ ያለውን መሬት
በማብቃቃት ሁሉም ዜጋ እንደዜግነቱ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት እንዲችል ለቅይጥ አገልግሎት ቦታ የሚወስዱ ባለሀብቶች ለመኖሪያ
ቤት የሚሆን አፓርታማ በመገንባት ችግሩን ለመቅረፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ የሚኖርባቸው መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ማስተር
ፕላን መሆኑ የመጀመሪያው ወደመፍትሄ የሚያደርስ ሁነኛ አቅጣጫ
ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሚያስተዳድረው
54 ሺሕ ሔክታር መሬት ውስጥ ለማስፋፊያ የተመደበው መሬት አልቋል የሚባልበት ደረጃ ላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡ይህ ደግሞ
በእርግጥም በህጋዊ መንገድ የተወሰደ እንዳልሆነ መገመት ይቻላል።ኪራይ ሰብሳቢው ኃይል በምስጢር እንዲህ ማስፋፊያውን ሁሉ
እንዲጨርስ ምክንያት ከሆኑት ውስጥ ደግሞ ግንባር ቀደም የሚሆነው የከተማው ባለቤት ንብረቱን ሊቆጣጠር የሚያስችለውን ምንም
አይነት የዘመነ መረጃ በእጁ ላይ የሌለው መሆኑ ይገመታል። እናም ይህ ማስተር ፕላን በቶሎ ወደመሬት መውረድ ይገባዋል።ለዚህም
ከመንግስት ብቻ ሳይሆን በልማታዊ አስተሳሰብ ከታነጸ ዜጋ ሁሉ የተጠናከረ ተሳትፎ ይጠበቃል።
ከመቶው እጅ አሥሩብቻ የሚተገበረው ማስተር ፕላን ትኩረቱን ሙሉ
በሙሉ በመካከለኛው የከተማው ክፍል (መልሶ ማልማት) ላይ ማድረጉ ያለችውን መሬት ሁሉም ዜጋ በፍትሃዊ መንገድ መጠቀም እንዲችል
መሆኑ የሚያመላክት ነው፡፡
በዚህ መካከለኛ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ፋብሪካዎች እንዲሁም ሰፋፊ
ቦታ የያዙ ኢንዱስትሪዎች ከከተማ ክልል እንዲወጡ እንደሚደረግም በማስተር ፕላኑ ላይ መመልከቱ ስለፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል
ተገቢነት ያለውና የመንግስትን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ከከተማ ከሚወጡ ተቋማት መካከል በልደታ ክፍለ ከተማ ሜክሲኮ
አካባቢ የሚገኘው የቢጂአይ (ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ)፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኘው አምቼ የከባድ ተሽከርካሪዎች አስመጪና
መገጣጠሚያ የመሰሉት ናቸው ፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው አስተዳደሩ ያለውን ለመኖሪያ እና ለንግድ የሚሆኑ መሬቶች በአግባቡ መምራትና
ማስተዳደር እንዲቻለውና ህገወጥነትን በላቀ ደረጃ መከላከል እንዲያስችለው መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል።
ማስተር ፕላኑ እንደሚገልጸው አዲስ አበባ እንድታድግ የሚጠበቀው
በኢንዱስትሪ ሳይሆን በአገልግሎት ዘርፍ ነው፡፡ ሆኖም ግን ለኢንዱስትሪ ቦታ የሚሰጠው ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለሚሆኑና ቦታ
ለማይፈጁ፣ እንዲሁም ለአዳጊ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ነው ይላል፡፡
በዚህ መሠረት አሁን ያለው የቦታ አሰጣጥና የኢንዱስትሪ ልማት
ከዚህ ሐሳብ ጋር እንዲሄድ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የማስተር ፕላኑ ማብራሪያ ይጠቅሳል፡፡ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ
ቀርቦ ይፀድቃል ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ ማስተር ፕላን፣ በከተማ ደረጃ አሥር ማዕከላት እንደሚኖሩት ይገልጻል፡፡
ከእነዚህ ማዕከላት መካከል ግዮን ሆቴል፣ ፍልውኃና ብሔራዊ ቤተ
መንግሥት አንድ ላይ አንድ ማዕከል እንደሚሆኑ ፕላኑ ያስቀምጣል፡፡ ግዮን ሆቴል የሆቴል አገልግሎት መስጠቱ ቀርቶ የፓርክ
አገልግሎት፣ ቤተ መንግሥት ደግሞ ሙዚየም ሆኖ ከፍልውኃ ጋር በተናበበ መንገድ እንደሚለማ ማስተር ፕላኑ ያስቀምጣል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የመከላከያ ሚኒስቴር ህንፃና የቸርችል ጎዳና
ከብሔራዊ ቴአትር ጋር በተናበበ መንገድ ከብሔራዊ ቴአትር እስከ ቸርቸር ጎዳና ድረስ ከተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ነፃ ሆኖ ከኢትዮ
ኩባ ፓርክ ጋር አንድ ላይ የሕዝብ መዝናኛና የእግረኛ መንገድ ይሆናል ተብሏል፡፡እነዚህ አሥር ማዕከላትና የተመረጡ ፕሮጀክቶችን
ለማልማት በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ በአጠቃላይ 289.4 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ከአስተዳደሩ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በአጠቃላይ አዲስ አበባ ከተማ በአዲሱ ማስተር ፕላን ወደ ጐን
መለጠጡን አቁሞ ወደ ላይ እንዲያድግ እንደሚሠራና፣ ለዚህም አገልግሎት ከፍተኛ ድርሻ የሚኖራቸው የውኃና የፍሳሽ መሠረተ ልማቶች
ግንባታ እንደሚከናወን በማስተር ፕላኑ ተመልክቷል። በዚህም የወደፊቷ አዲስ አበባ ጽዱና ከወረራ የጸዳች ለኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች
የሚሆን አንዳች ምሽግ የማይኖራት ከተማ እንደምትሆን መገመት
አይከብድም፡፡
አዲስ አበባ ከምስረታዋ ጀምሮ ዘጠኝ
ማስተር ፕላኖችን አሳልፋለች። የመጀመሪያው የሚባለው የእቴጌ ጣይቱ የ1879 የአሰፋፈር እቅድ ነበር። ከዚያ በጣሊያናውያን
የተሰራ ነበር። በ1996 ዓ.ም ፀድቆ ሲሰራበት የቆየው የከተማዋ ማስተር ፕላን የአስር ዓመት ጊዜውን ያጠናቀቀው በ2006
ዓ.ም ሲሆን ከዚያ በኋላ እየሰራ ያለው አዲሱ ማስተር ፕላን
ነው። በአዲሱ ማስተር ፕላን መሰረት ከተማዋ ወደ ጎን እንድትሰፋ ከማድረግ ይልቅ እድገቷ ወደ ላይ የሚደረግ መሆኑም
ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ስለማስተር ፕላኑ በተዘጋጁ መድረኮች
ላይ በተደረጉ ገለፃዎች ተመልክቷል። በከተማዋ ያለው መሬት አነስተኛ ከመሆኑ ጋር በተያያዘና ሀብቱንም በጋራና በቁጠባ መጠቀም
ስለሚገባ በረጃጅም ፎቆች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ማስተር ፕላን ነው ተግባራዊ የሚሆነው ። ይህም ሰፊ የሆነ አቅምና ቴክኖሎጂ
የማይጠይቅ መሆኑም ተመልክቷል። ረጃጅም ፎቆች ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃና የውሃ ግፊት ስለሚጠይቁም ለዚህም ልዩ ትኩረት
ይሰጠዋል ።
“አዲሱ ማስተር ፕላን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጉዳይ የአዲስ አበባ ነዋሪ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን
የኢትዮጵያ ህዝብም ጭምር ነው” እንዲል ቢሮው ፤ አዲስ አበባ
የአፍሪካ መዲና በመሆኗ ፕላኑ የአፍሪካ ህብረትን ሳይቀር ይመለከታል። ፕላኑ መሬት
ላይ ወርዶ ሲተገበር የእያንዳንዱን ሰው እንቅስቃሴ የሚነካ ስለሚሆን የሕዝብ ውይይቶች እና ተሳትፎ አስፈላጊ መሆናቸው
አያጠያይቅም።
ይህ ማስተር ፕላን ወረራን በመመከት ብቻ
ሳይሆን በተለያዩ ጊዜያት አዲስ አበባን ለአፍሪካ ህብረት መቀመጫነት አትመጥንም በሚል በአንዳንድ ወገኖች ሲነሱ
የነበሩትን ቅሬታዎች በሚመልስ መልኩ የተዘጋጀ ነው።
ከአስር የከተማዋ ማስተር ፕላኖች ውስጥ
ከግማሽ በላይ የሆኑት የከተማዋ ማስተር ፕላኖች በውጪ ዜጎች የተዘጋጁ መሆኑ የተመለከተ ሲሆን፤ እነዚህም የቀደሙ ማስተር
ፕላኖች ብዙም የሕዝቡን ፍላጎት፤ ባህልና የአኗኗር ዘይቤ ታሳቢ ያላደረጉከመሆኑ ጋር ተያይዞ የነበሩ ችግሮችም በዚህ ማስተር
ፕላን መልስ ያገኛሉ ። አዲሱ ማስተር ፕላን በአገር ውስጥ ባለሙያዎች እንዲዘጋጅ ተደርጓልና።
ከዚህ ቀደም በነበረው የከተማዋ ማስተር
ፕላን መሰረት አንድ ሰው ቦታ ወስዶ ግንባታ ሲያከናውን ከይዞታው ገባ ብሎ እንዲሰራ
ይደረግ የነበረ ሲሆን፤ በአዲሱ ፕላን ግን የቦታ ቁጠባ ስለሚያስፈልግ ቀደም ሲል የነበረው አሰራር አይተገበርም። በዚህም
መሰረት ባለቦታው በቦታው ላይ ሙሉ ግንባታን ያሰፍራል ማለት ነው። ቀደም ባለው የግንባታ ፈቃድ መሰረት አንድ ለግንባታ ሁለት ሜትር ከወሰን መራቅ ይጠበቅበት የነበረው ጉዳይም
በማስፋፋትና በመጠቅለል አስባብ ለኪራይ ሰብሳቢነትና ዘረፋ ሲያጋልጥ ነበርና በዚህ ማስተር ፕላን የእርሱም ጉዳይ አበቃለት
ማለት ነው።
በመንግሥት በተያዙ ቦታዎች ግንባታዎችያለፈቃድ ስር በሰደደ መልኩ ሲገነቡ መቆየታቸውም ለኪራይ ሰብሳቢው ወራሪ ሽፋን
ሆነው ዓመታትን ማስቆጠራቸው ይታወሳል። ከዚህ በኋላ ግን ማንኛውም የመንግሥት አካል ግንባታ ሲያከናውን በፈቃድ ብቻ እንደሚሆን በማስተር ፕላኑ ተመልክቷልና ውልፍት የለም። የግንባታ ፈቃድ ጠይቆ
ግንባታ ማከናወንን በተመለከተ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ሳይቀሩ ከሚመለከተው አካል የግንባታ ፈቃድ ሳያገኙ የሚገነቡበት ሁኔታ የለም።ይህም የመሬት ወረራን ነገር ቀዳዳ እንደሚያሳጣው ይጠበቃል
እና ተግባራዊነቱን ብንናፍቅ እውነት ስላለን ነው ። የግንባታን ፈቃድ በተመለከተ ወጥ የሆነ አሰራር አለመኖሩም በውይይቶቹ
ተገልጿል። ብዙ ጊዜ የሚተገበረው አዲስ ተሻሽሎ የወጣው ህግ ሳይሆን በተለያዩ ጊዜያት የወጡ ህጎችና ሰርኩላሮችም ጭምር
በመሆናቸውለሸ የፕላኖቹን አተገባበር ውስብስብ አድርጐት የቆየ መሆኑ አያጠያይቅም።
መሪ ፕላኑን በማስፈፀም ረገድ
እስከዛሬ በነበረው አሰራር መሰረት የፕላኑን አተገባበር የሚቆጣጠረው አካል በፈፃሚው አካል ስር ሆኖ ሲሰራ እንደነበር
ተመልክቷል። ይሁንና ይህ አሰራር ችግሮች ሲፈጥር የቆየ መሆኑ ተመልክቶ፤ በቀጣዩ መሪ ፕላን አተገባበር ላይ ይህ አካል ተጠሪነቱ በቀጥታ
ለከንቲባው ሆኖ ፕላኑን ከማዘጋጀት ጀምሮ ክትትል እስከማድረግ ድረስም ኃላፊነቱን በሙሉ ወስዷል። የስፖርት ማዘውተሪያን
በተመለከተ በእያንዳንዱ ክፍለ ከተማ አንድ አንድ ስታዲየም ማሰራት የሚያስችሉ ሜዳዎች ታሳቢ
ተደርገው በክፍት ቦታነት የተያዙ በመሆኑም ወራሪዎች ውልፍት የሚሉባት ቀዳዳ አያገኙም።
No comments:
Post a Comment