Wednesday, 13 July 2016

የኢንዱስትሪ ልማት ፓርኮችን ማስፋፋት ለአገሪቱ እቅድ ስኬት አይነተኛ መሳሪያ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ

የኢንዱስትሪ ልማት ፓርኮችን ማስፋፋት ለአገሪቱ እቅድ ስኬት አይነተኛ መሳሪያ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ

የኢንዱስትሪ ልማት ፓርኮችን ማስፋፋት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ግቦችን ለማሳካት አይነተኛ መሳሪያ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ተናገሩ።

የሀዋሳ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ፓርክ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ፓርኩ የወጪ ንግድ ላይ ያተኮረ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ለመገንባት አገሪቱ ለምታደርገው የለውጥና የእድገት ግስጋሴ የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።

"አገራዊ ራዕያችን ሰፊ የስራ እደል የሚፈጥር እንዲሁም ጉልበትን በሰፊው የሚጠቀም የማምረቻ ኢንዱሰትሪ በመገንባት በአፈሪካ ቀዳሚ መሆን ነው" ብለዋል።

ላለፉት ዘጠኝ ወራት ግንባታው የተከናወነው የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በይፋ ተመርቆ ሥራውን ጀመረ።

ኢንዱስትሪ ፓርኩ በ300 ሺህ ሜትር ስኩዌር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ከ250 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ ተደርጎበታል።

ፓርኩ የውኃና የቆሻሻ ማስወገጃ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ሲሆን ይህም 85 በመቶ የሚሆን ውኃን መልሶ መጠቀም ያስችላል፤ አካባቢንም ከብክለት ከመጠበቅ ባለፈ የውኃ እጥረትን ያስወግዳል።

ይህም ለአካባቢ ተሰማሚ የኢንዱስትሪ ፓርክ በመሆን ከአፍሪካ ቀዳሚው ያደርገዋል።

በፓርኩ 15 የውጭና 6 የአገር ውስጥ ኩባንያዎችም ፋብሪካዎችን ከፍተው ወደ ሥራ ለመግባት ተለይተዋል።

የሀዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ በ 300 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን በውስጡም 37 ፋብሪካዎች ተገንብተዋል።

ፓርኩ ሙሉ በሙሉ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርት ላይ የሚያተኩር ሲሆን በተገነቡት ሼዶች የሚሰማሩ ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸውና በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ 15 የውጭ ኩባንያዎችም ተለይተዋል።

ኩባንያዎቹም ከአሜሪካ፣ ከህንድ፣ ከስሪላንካ፣ ከሆንግኮንግ የመጡ ሲሆን ጥራትና አቅም ያላቸውና በዓለም አቀፍ ደረጃ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ቀዳሚውን ሥፍራ የያዙ ናቸው።

ከ20 ዓመት በፊት ምርት አቁሞ በሽያጭ ላይ ተወስኖ የቆየውና ካልቪን ክሌን፣ ቶሚ ሂል ፊገር፣ ቫን ሂውሰን፣ ኢዞድ፣ አሮው፣ ስፒዶ፣ ዋርነርስ በተባሉት የምርት መለያዎች የሚታወቀው የአሜሪካው ፒ.ቪ.ኤች ኩባንያ በፓርኩ ከሚሰማሩት መካከል ተጠቃሽ ነው።

የኢንዶኔዢያው ፒ.ቲ.ዩ የሲሪላንካው ሃይድራማኒ፣ የህንዱ ራይሞንድና የቻይናው ውሺ ጂንማኦ ኩባንያዎችም እንዲሁ ወደ ሀዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ የገቡ ናቸው።

ኩባንያዎቹ ሰፊ የገበያ አቅም ያላቸው፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር አቅምና የአስተዳደር ክህሎት የዳበሩ መሆናቸውም ዘርፉን ይበልጥ ተወዳዳሪ ያደርገዋል።

ኩባንያዎቹ ካላቸው ሰፊ የገበያ ድርሻ አንፃር የውጭ ምንዛሪን በፍጥነት የማምጣት ዕድላቸው ሰፊ መሆኑንም ነው የጠቅላይ ሚንስትሩ ልዩ አማካሪ ሚኒስትር ዶክተር አርከበ ዑቑባይ የተናገሩት።

የኩባንያዎቹ ዓመታዊ የሽያጭ ሪከርድም ከ200 ሚሊዮን የአሜሪካ እስከ 8 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚደርስ ነው።

ይህም በዓመት አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስገኝ ለሚጠበቀው ለሀዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ አቅም ይሆነዋል ነው የተባለው።

የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችም ከእነሱ ጋራ በምርት ስለሚተሳሰሩ የዕውቀት ሽግግሩን ውጤታማ ያደርጉታል።

ሰፊ መዋዕለ ነዋይ፣ ጠንካራ የአስተዳደር ሥርዓትና የቴክኖሎጂ አቅም ለሚያሰፈልገው የማምረቻ ዘርፍ ይህንን የሚያሟሉ ኩባንያዎች መግባታቸው መዋቅራዊ ለውጡን ያፋጥነዋልም ነው የሚሉት።

ለአልባሳት ምርት የሚያስፈልጉ የጨርቃጨርቅ አቅራቢ ፋብሪካዎችና እንደ የሸሚዝ፣ ቁልፍና ዚፕ የመሳሰሉ ግብዓቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎችም ወደ ፓርኩ ገብተዋል።

ፓርኩ በጨርቃጨርቅ ዘርፍ ምን ለውጥ ያመጣል

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የጨርቃጨርቅ ዘርፍ ሰፊ የገበያ ፍላጎት ያለው በመሆኑ የሀዋሳ ፓርክ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ላይ እንዲያተኩር ተደርጓል።

በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ዘርፉ ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጠው የአገሪቱ የኢንዱስትሪ መሪ ዕቅድ ያመላክታል።

በአሁኑ ወቅት በኢኮኖሚው ከ5 በመቶ በላይ አስተዋጽኦ የሌለው የማምረቻው ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ድርሻ በየዓመቱ 25 በመቶ ለማድረስና በቀጣይ አሥር ዓመታት ለ2 ሚሊዮን ሰዎች የሥራ ዕድል እንዲፈጥር እየተሰራ ነው።

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የአምራች ኢንዱስትሪ ማዕክል ለመሆን ላስቀመጠችው ግብ ስኬታማነት ፈር ቀዳጅ ነውም ተብሏል።

በፓርኩ ተመሳሳይ ዘርፍ እንዲሆን የተደረገውም ለዘርፉ የሚስማማ መሰረተ ልማት፣ ፍሳሽ ማስወገጃና የክህሎት ሽግግሩን ለማፋጠን ታሰቦ ነው።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ኢኮኖሚ የማምረቻው ዘርፍ ድርሻ ከአምስት በመቶ የማይበልጥ ሲሆን በወጪ ንግድ ዘርፍም የዘርፉ ድርሻ ከ12 በመቶ በታች ነው።

አገሪቱ እስካሁን ከጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ የምታገኘው ገቢም ከ200 ሚሊዮን ዶላር በታች ነው።

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻውን በዓመት አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያስገኝ ሲሆን ይህም ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ በአሥር እጥፍ የሚያሳድገው ይሆናል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ለ55 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።

ፓርኩ በሙሉ አቅሙ ወደ ምርት ሲገባ በሁለት ፈረቃ ለ60 ሺህ ዜጎች ሥራ ይፈጥራል፤ ይህም በዘርፉ የተፈጠረውን የሥራ ዕድል ወደ 115 ሺህ ከፍ የሚያደርገው ይሆናል።

ቀጣይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት

በእስካሁኑ ሂደት በመንግሥትና በግል አልሚዎች የተገነቡ እንደ ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን እና ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ዞን የመሳሰሉ ግንባታቸው ተጠናቆ በምርት ላይ ይገኛሉ።

በቀጣይ በኮምቦልቻ፣ መቐለ፣ ድሬዳዋ፣ አዳማና በሌሎች አካባቢዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገነቡ ሲሆን በፈረንጆቹ 2016ትም ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ዶክተር አርከበ ተናግረዋል።

ከእነዚህ መካከል የአማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በቀጣይ ሳምንት የሚጀመር ሲሆን 125 ሚሊዮን ዶላር ለግንባታው ወጪ ይሆናል።

ይህ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንደ ሀዋሳው ሁሉ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርት ላይ የተሰማሩ ባለኃብቶች የሚገቡበት ሲሆን በቀጣይ ዘጠኝ ወራት ግንባታው ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባም ታውቋል።

ግንባታውን የሚያከናውነውም የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን የገነባው የቻይናው ሲ.ሲ.ኢ.ሲ.ሲ ኮስትራክሽን ድርጅት ነው።ሀዋሳ 6/2008ኢዜአ

No comments:

Post a Comment