Friday, 15 July 2016

በጅምር እንዳይቀር


ብ. ነጋሽ
በአገሪቱ የተነሰራፋውን የመልካም አስተዳደር ችግርና ኪራይ ሰብሳቢነት መዋጋት “የህልውና ጉዳይ ነው፤ የሞት የሽረት ጉዳይ ነው …” የሚል አቋም በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና በኢፌዴሪ መንግሥት፤ እንዲሁም በዘጠኙም ክልል መንግሥታት በይፋ ከተገለፀ እነሆ አንድ ዓመት ሞላው። በኢፌዴሪ መንግሥትና በክልል መንግስታት እንዲሁም በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና አጋር ድርጀቶቹ የመልካም አስተዳደርን ችግር መዋጋት የሞት የሽረት ጉዳይ ነው የሚል መግለጫ መሰጠቱን ተከትሎ፣  የአገሪቱ የመልካም አስተዳደር ችግርና ኪራይ ሰብሳቢነት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚያሳይ በፌደራል የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩትና በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር  የተዘጋጀ ጥናት ይፋ ሆነ። በዚህ ሰነድ ላይ የሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት የተሳተፉበት የመልካም አሰተዳደር ሕዝባዊ ንቅናቄ ማቀጣጣያ ውይይት ተካሄደ። ይህ የሕዝባዊ ንቅናቄ ማቀጣጣያ ውይይት በየደረጃው ባሉ የመንግሥት የስልጣን እርከን የስራ ኃላፊዎችም ዘንድ ተካሂዷል።
ይህ በየደረጃው የተካሄደ የመልካም አስተዳደር ሕዝባዊ ንቅናቄ ማቀጣጣያ ውይይት በመልካም አስተዳደር እጦት፣ በብልሹ አሰራር መንሰራፋት፣ በኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊት ወዘተ. በተማረረውህዝብ ላይ ተስፋ ቢጤ ፈነጠቀ። ብዙም ሳይቆይ በተለያዩ ክልሎችየአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በብልሹ አሰራርና በኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊት ተጠያቂ ናቸው የተባሉ በሺዎች የሚቆጠሩ አስፈፃሚዎችና ባለሞያዎች ከሃላፊነት መነሳታቸው፣ ከደረጃ ዝቅ ብለው እንዲሰሩ መደረጋቸው ተገለጸ። ይህ መንግሥት መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያመለክት በመሆኑ በህዝቡ ወስጥ የተፈጠረውን ተስፋ አጠናከረው።
በዚህ ዙሪያ ያለውን እውነታ ለማስታወስየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ባካሄደው 3ኛ መደበኛ ስብሰባ  ከንቲባ ድሪባ ኩማ ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት የገለጹትን ልጥቀስ። በከተማዋየመልካምአስተዳደርንእናየአገልግሎትአሰጣጥንችግሮችለመፍታትየተለያዩተግባራትሲከናወኑቆይተዋልያሉትከንቲባድሪባ፣በዚህምበየደረጃውብልሹአሰራርውስጥየተገኙ 3 ሺህ 116 ፈጻሚዎችናአመራሮችላይእርምጃተወስዷል ብለዋል።በተለይምበመሬትወረራላይበተሳተፉአካላትላይአስተዳደሩየተለያዩእርምጃዎችንእየወሰደመሆኑንም አስታውቀዋል።ልብ በሉ፤ ሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ እርምጃዎችን ወስደዋል፤ አሁንም በመውሰድ ላይ ናቸው።
በዚህ ዓመት መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት መንግስትና ሕዝብ ዱብ ዱብ ያሉትን ያህል፣ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች የፈጠሯቸው ብሶቶች በመረረ ህዝባዊ ተቃውሞ መልክ የተገለጹበት ሁኔታዎችም ነበሩ።በበርካታ የኦሮሚያ አካባቢዎች፣ እንዲሁም በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ተቀስቅሰው የነበሩትን ተቃውሞዎች ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ተቃውሞዎች በኋላ መልካቸውን ቀይረው ቅጥ ወዳጣ ሁከትነት ተቀይረው ሰላም በማስከበረ ስራ ላይ የተሰማሩትን ጨምሮ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ህይወት መጥፋት፣ በብዙ ሚሊዮን ብር ለሚገመት የመንግስትና የግለሰቦች ንብረት፤ እንዲሁም የውጭ ሃገር ዜጎች ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ውድመት ምክንያት መሆኑ ይታወሳል። እነዚህ ሁከቶች የመልካም አሰተዳደር ችግርና ኪራይ ሰብሳቢነት ምን ያህል የስርአቱ አደጋ እንደሆኑ ቁልጭ አድርገው ያሳዩ ናቸው።
የመልካም አስተዳደር ሕዝባዊ ንቅናቄው በፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥም ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥሮ ነበር። በቅርቡ የአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እንዲሁም መድረሻቸው መገንባት እስኪመስል ለዓመታት የተጓተቱ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶችን ወዘተ. በተመለከተ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተነስተውየነበሩ ጥያቄዎች የዚህ ማሳያ ተደረገው ሊጠቀሱ ይችላሉ። ምክር ቤቱ ላቀረባቸው ጥያቄዎች የተሰጡ ምላሾችና ቃል የተገቡ  ተስፋዎች በትክክል በወቅቱ መፈፀማቸውን መከታተል ይኖርበታል። በዚህ ረገድ እስካሁን ይህ ነው የሚባል አርኪ ስራ አልታየም።
በዚህ አኳኋን ዓመቱን መልካም አሰተዳደርን ለማስፈን ስንባዝን፣ ተስፋ ስናደርግ፣ ያለፉትዓመታት የመልካም አሰተዳደር መጓደል ክምር ተንዶ በሁከቶች ስንናጥ ቆይተን እዚህ ደርሰናል። ከዚህ መልካም አስተዳደርን የማስፈን ሂደት ያተረፍነው ቢኖርም ገና የሚቀሩ በርካታ ተግባሮች መኖራቸው ግን ለክርክር የሚቀርብ አይደለም። ገና ብዙ መልካም አስተዳደርን የማስፈንና ኪራይ ሰብሳቢነትን የመድፈቅ ተግባራት ይጠብቁናል። መልካም አስተዳደርን የማስፈን ጉዳይ የአመለካከት ለውጥ፣ የባህል ግንባታ ጉዳይ በመሆኑ በአንድ ዓመት የሚሳካ ጉዳይ እንዳልሆነ ግልፅ ነው። መልካም አስተዳደርን ማስፈን ለብልሹ አሰራርና ለኪራይ ሰብሳቢነት ክፍተት የማይሰጥ፤ ማንም ተነስቶ በቀላሉ የማይበትነው የአሰራር ስርዓት የመዘርጋት ጉዳይም ነው። ጊዜ የሚወስደውም ለዚህ ነው።
ያም ሆነ ይህ የፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2008 ሥራውን አጠናቅቆየ2009ን በጀት ባፀደቀበት ስብሰባው ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ፤ የባለፈውንዓመትመልካም አስተዳደር የማሰፈን እንቅስቃሴና የተገኘውን ወጤት፣ እንዲሁም ቀሪውን ስራ የተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ መልካም አስተዳደርን የማስፈን ክንውኑ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ቀሪ ተግባራትንም ስለሚያሳይ ልጠቅሰው ወድጃለሁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የሰጡትን ማብራሪያ የጀመሩት የመልካም አስተዳደር ስራ ለልማታችን እንቅፋት እንዳይሆን በዚህ ዙሪያ ያሉ ችግሮችን የመቅረፍ ጉዳይ የሞት የሽረት ጉዳይ ተደርጎ እንዲወሰድ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን በማስታወስ ነበር። መልካም አስተዳደርን የማስፈንና ኪራይ ሰብቢነትን የማስወገዱ ትግል ሕዝብን ከመንግሥት ጎን በማሰለፍ በሕዝባዊ እንቅስቃሴ መልክ እንዲካሄድ ሰፊ የንቅናቄ እቅድ ተዘጋጅቶ በዚህ መሰረት እንቅስቃሴ መደረጉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በዚህ እንቅስቃሴ በዓመትጊዜ ውስጥ የተገኘውን ውጤት አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩም፤“ባደረግነው እንቅስቃሴ የመልካም አስተዳደር ችግር መስፋፋት እንዲገታ አድርገናል። በበርካታ አካባቢዎች ደግሞ ችግሩ እየተቃለለ መጥቷል። ይህንከሕዝብ ጋር በተደረጉ ውይይቶች ማረጋገጥ ችለናል።” ብለዋል። ይሁን እንጂ፤ እነዚህ ውጤቶች ስራ ለመስራት የሚያስችሉ፣ ተስፋ የሚሰጡ፣ ወደፊት አጠናከረን ከቀጠልን ሥር ነቀልና መሰረታዊ ለውጥ ልናመጣ እንደምንችል አመላካች ከመሆን አልፈው የሚያኩራሩ ውጤቶች ተብለው ሊወሰዱ እንደማይችሉ ገልጸዋል። በዚህ ምክንያት የመልካም አስተዳደርን ችግር አሁንም  የህልውና ጉዳይ አድርጎ የማየቱ  ነገር መዘንጋትእንደሌለበትም አሳስበዋል።
የመልካም አስተዳደር ችግር የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በሚሰራው ልክ መሰረታዊና ሥር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ የሚያደርግ ተጨማሪ ከፍተኛ ስራ እንደሚቀርም አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚደረግ ትግል በአጭር ግዜ ሊሳካ የማይችል መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል። ይህን አስመልክተው ሲናገሩ “የመልካም አስተዳደር ችግር ላይ አንድ ዓመት በሰራነው ሥራ የተወሰነ ርቀት መሄድ እንችል እንደሆን እንጂ መሰረታዊና ሥር ነቀል ለውጥ በሚያመጣ ደረጃ ውጤት ማምጣት ይቻላል ብሎ መጠበቅ ተገቢ አይደለም።” ብለዋል። የእስካሁኑ ሂደት በቀጣይ ዓመትም ትግሉን የበለጠ አጧጡፎ መቀጠል አለብን የሚል ድምዳሜ ላይ ከማድረስ ያለፈ የሚያኩራራ ወጤት እንዳልሆነ፤ በመሆኑም ሙስና፣ ብልሹ አሰራርና ውጤታማ ሥራ ያለመስራት ጉዳይ አሁንም መሰረታዊ ችግር ሆነው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማቃለል መንግሥትንና ህዝብን የሚጠብቅ ሥራ መኖሩን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም፣ ይህም አመለካከትን የመቀየር፣ የአገልጋይነት መንፈስን የማስረጽ፣ ባህልን የመቀየር ያለማቋረጥ የሚከናወንተግባር መሆኑን አመልክተዋል።
ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትንመታገልየህግ ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “የዚህ ትግል ዋና ጉዳይ መንግሥትና ህብረተሰብ በመተባባር ያለውን ብልሹ አሰራር የማስተካከል ጉዳይ ነው። ይህ ሊሆን የሚችለው ንቅናቄው ተሟሙቆ መቀጠል ሲችል ነው። ይህን ማረጋገጥ ማለት ደግሞ ዘላቂውን ውጤት ማረጋገጥ ማለት ነው።” ብለዋል። ለኪራይ ሰብሳቢነት ምቹ የሆኑ ሁኔታዎችንመቆለፍ እንደሚያስፈልግም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።ከዚህ ጋር በተያያዘ በበጀት አጠቃቀም ላይ ያሉትን ክፍተቶች ለመድፈን የበጀት አጠቃቀም ክትትልና ግምገማሥርአት መዘርጋቱንም አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የበጀት አጠቃቀምን ለመከታተልና ለመቆጣጠር የተዘረጋውን አዲስ አሰራርም አሳውቀዋል። ይህን ለማድረግ ከተዘረጋው አሰራር ውስጥ ቀዳሚው የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን እንዲቋቋም መደረጉ ነው። ባለፈው ዓመት የተቋቋመውና በዝግጅት ላይ የቆየው ይህ ተቋም በመንግስት በጀት አጠቃቀም ላይ ክትትልና ግምገማ በማድረግ እንደአግባብነቱ ማሻሻያዎችና እርምጃዎች እንዲወሰዱ የማድረግ ኃላፊነት አለበት።
ሁለተኛው አዲስ አሰራር ከውስጥ ኦዲት ጋር የተያያዘ ነው። ቀደም ሲል የውስጥ ኦዲተሮች ተጠሪነት ለሚሰሩበት መስሪያ ቤት ብቻ ነበር። ከሚቀጥለው በጀት ዓመት ጀምሮ ግን ይህ አሰራር ተቀይሮ የውስጥ ኦዲተሮች ለመስሪያ ቤታቸውና ለገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ጥምር ተጠሪነት እንዲኖራቸው ይደረጋል። ይህም የውስጥ ኦዲትንከአስተዳደር ጫና ነፃ ያደርጋል።
ሶስተኛው አዲስ አሰራር የክላስተር አደረጃጀት ነው። ይህ አሰራር በእያንዳንዱ ክላስተር ወይም ዘርፍ ውስጥ ክትትል በማድረግ የበጀትና የሀብት አጠቃቀም አጠቃላይ  ግምገማ ማከናወን ያስችላል።
አራተኛው አሰራር የተለመደው በዋና ኦዲተር አማካኝነት የሚከናወነው ተግባር ነው። በኦዲት የተገኘን ውጤት መሰረት በማድረግ የተሰጡ አስተያየቶችን ተግባራዊ የማድረግ አሰራር ይከናወናል። በዚህም መታረም ያለባቸው አሰራሮችና ጥፋቶች እንዲታረሙ፣ በህግ መጠየቅ ያለባቸው የስራ ሀላፊዎችም ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ጉዳይ ትኩረት ይሰጠዋል።
እንግዲህ በአገራችን የመልካም አስተዳደር ችግርና ኪራይ ሰብሳቢነት የሥርአት አደጋ እስከመሆን ተስፋፍቶ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ችግሩን ለማስወገድ ወይም ለማቃለል ህዝባዊ ንቅናቄ በተካሄደበት 2008 ዓ.ም ውጤት ሊያመጡ የሚችሉ መልካም ጅምሮች መኖራቸው እውነት ነው።እነዚህ ጅምሮች ከሚፈለገው ውጤት አኳያ ሲታዩ ገና ጫፍ የመያዝ ያህል ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያም በጉዳዩ ዙሪያ የተገኘው ውጤት የማያኩራራ ገና ጅምር መሆኑን ነው የገለፁት። እውነታቸውን ነው። እናም የተያዘውን ጫፍ ሳንለቅቅ ለከርሞ የተሻለ ወጤት ለማየት የተጀመረውን ተነሳሸነት ማስቀጠል የግድ ነው። አለበለዚያ  የውድቀት ትውስታ ሆኖ ገዢውን ፓርቲና መንግስትን ሲያሳፍር መኖሩ አይቀሬ ነው።


No comments:

Post a Comment