Thursday, 21 July 2016

የመዋቅር ለውጡ ጅማሮ…




ወንድይራድ ኃብተየስ
መንግሥት የከተሞችን ዕድገት ከኢንዱስትሪ ልማት ጋር ለማስተሳሰርና ለዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ልማቱን ማፋጠን የሚያስችሉ በመላ አገሪቱ በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን  በመገንባት ላይ ይገኛል።  በመላ አገሪቱ  መንግሥት በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት የአገሪቱን ዕድገት የተመጣጠነ እንዲሆን አቅዶ እየሰራ ነው። በመጀመሪያው ዙር ይገነባሉ ተብለው ከተያዙት መካከል በአዲስ አባባ (ለሚ አንድና ሁለት፣ ቂሊንጦ)፣ ሀዋሳ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ኮምቦልቻ፣ መቀሌ፣ ባህርዳርና ጅማ ናቸው።  ከእነዚህ ውስጥ የአዲስ አበባዎቹና የሐዋሳው ግንባታቸው ተጠናቆ ለባለሃብቶች ተላልፈዋል።
እነዚህ ፓርኮች  ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው የተገነቡና የሚገነቡ ከመሆናቸው ባሻገር ተመሳሳይ ምርት ሊያመርቱ የሚችሉ ፋብሪካዎች ለአብነት የጨርቃጨርቅ፣ የማቅለሚያ ኬሚካሎችን የሚያመርቱ በአንድ ክላስተር እንዲሁም ፋርማሲዩቲካልና ምግብ ነክ የሆኑ ውጤቶችን የሚያመርቱ በአንድ ላይ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው። በተጨማሪ ተመጋጋቢ የሆኑ ፋብሪካዎች በአንድ ላይ መሆናቸው ወጪንም ይቀንሳል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች በራሳቸው ከሚፈጥሩት የሥራ ዕድል ባሻገር፣ የኢንዱስትሪ  ፓርኮች   ከጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ጋር እንዲቀናጁ በማድረግም ተጨማሪ የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችል ሥራን  መንግሥት በማከናወን ላይ ይገኛል። አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማትን ለማስፋፋትና ለማጠናከርም መንግሥት የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ይገኛል። ለአብነት የማምረቻና መሸጫ ቦታ ማዘጋጀት፣ የገበያ ትስስር መፍጠር፣ ብድር ማቅረብ፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችንና የምክር አገልግሎት ወዘተ… በማድረግ ላይ ይገኛል።
አዳዲሶቹ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከቀድሞዎቹ የኢንደስትሪ ዞኖች ተብለው ይጠሩ ከነበሩት በበርካታ ነገሮች የተለዩ ናቸው። በቅድሚያ  አዳዲሶቹ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተደራጁት በመንግሥት ከፍተኛ ወጪ ነው። ሁሉም ፓርኮች ከአካባቢ እንዳይበክሉ ተደርገው የሚገነቡ በመሆናቸው ከአካባቢ ጋር ተስማሚ ቴክኖሎጂዎችን የተከተሉ ናቸው። 
በሁሉም ፓርኮች አስፈላጊ አገልግሎቶች ማለትም ጉምሩክ፣ ባንክ፣ መብራት፣ ውኃ፣ ወዘተ…የተሟሉላቸው በመሆናቸው ባለሃብቶች የሚፈልጉትን አገልግሎቶች በአንድ መስኮት  ማግኘት ያስችላቸዋል።
የሀዋሳ የጨርቃጨርቅና አልባሣት ኢንዱስትሪ ፓርክ 300 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ እጅግ ግዙፍ ሲሆን በውስጡም 37 ፋብሪካዎች ተገንብተዋል። በፓርኩ  በጨርቃጨርቅና አልባሣት ዘርፍ  ዓለም አቀፍ ታዋቂነትን ያተረፉ የሆኑ 15 ዓለም አቀፍባንያዎች ይካተታሉ። ለአብነት ከ130 ዓመታት በላይ ልምድ ያለው የአሜሪካው ኤች ኩባንያ  አንዱ ነው።
ይህ  ኩባንያ 2015 ዓመት ስምንት ቢሊዬን የአሜሪካ ዶላር ዓመታዊ ሽያጭ ያስመዘገበ ሲሆን፥ 20 ዓመት በፊት ማምረት አቁሞ በዋናነትም በግዥና ማከፋፈል ላይ ተሰማርቶ ቆይቷል። ይሁንና አሁን የሙሉ ልብስ ሸሚዞች መለያ የሆነውን ኬልቪን ክሌይን የተሰኘውን ዓለም አቀፍ ብራንድ በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለማምረትና ወደ አሜሪካ ለመላክ 11 ሺህ ካሬ ሜትር የፓርኩን ሥፍራ ተረክቧል። በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከሚከትሙት ከግማሽ በላይ ኩባንያዎች ከፒ ኤች ጋር የተሳሰሩና ኩባንያው በሚፈልገው የጥራት ደረጃ አምርተው ከፒ ኤች መለያ ወደ አሜሪካ ለመላክም ተዘጋጅቷል።
ሌላው በፓርኩ የከተመው የቻይናው ዉሺ ጂንማኦ ኩባንያ ሲሆን ይህ ኩባንያ ቻይና በተጨማሪ በአሜሪካ፣ቬዬትናም፣ በባንግላዲሽና በካምቦዲያ ፋብሪካዎች አሉት። ኩባንያው  ምርቶቹን በተለይም ለፒ ኤች፣ ጋፕ፣ ፔኒ፣ ታርጌት፣ ቫኒቲ ፌር፣ ፔትኮ፣ ፔት ስማርትና ለኔክስት ላሉ አከፋፋይ ኩባንያዎች ያቀርባል። የዚህ ግዙፍ ኩባንያ በ2015 ዓመታዊ  ሽያጭ  290 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ነው። አሁን በሀዋሣ ኢንዱስትሪ ፓርክ 40 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፉ ሦስት ፋብሪካዎች አቋቁሞ ጥራት ያላቸውን የሸሚዝ ጨርቆችን እንደሚያመርትም ታውቋል። ኩባንያው ከባህርዳር፣ ሀዋሣና ወሎ ዩኒቨርሲቲዎች በጨርቃጨርቅ ዘርፍ የተመረቁ 30 ምሩቃንንም ቻይና በመውሰድ በማሰልጠን ላይ ይገኛል።
በፓርኩ የሚከትመው ሌላኛው ኩባንያ ደግሞ አርቪንድ የተሰኘው ዋና መሥሪያ ቤቱን በህንድ ጉጅራት ያደረገውና የ85 ዓመታት በጨርቃጨርቅ ማምረት ረገድ  ልምድ  ያለው ኩባንያ ነው። ከጥጥ የተሰሩ ሸሚዞችና የጂንስ ጨርቆችን በማምረት ዓለም ላይ ለታወቁ እንደ ረንግለር፣ አሮው፣ ቶሚ ሂልፊገር ለመሳሰሉት ኩባንያዎች ያቀርባል። አርቪንድ የቶሚ ሂልፊገር መለያዎችን በስፋት ያመርታል። ድርጅቱ የጂንስ ጨርቅ በማምረት ከህንድ አንደኛ ከዓለም ደግሞ በአራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ግዙፍ ኩባንያ ነው። ይህ ኩባንያ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ 25 ሺህ በላይ ሠራተኞች አሉት። ባለፈው ዓመት ብቻ 770 ሚሊዬን የአሜሪካ ዶላር ሽያጭ አስመዝግቧል። አርቪንድ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ዞን ፋብሪካ አለው። አሁን ደግሞ በሀዋሣ ኢንዱስትሪ ፓርክም 65 ሺህ 300 በላይ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሰባት ፋብሪካ ያቋቁማል።
መሠረቱን ሆንክ ኮንግ ያደረገው ታል የተሰኘው ፋብሪካም እንዲሁ በሀዋሣ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመሰማራት የተመረጠ ሌላው ኩባንያ ነው።  ይህ ኩባንያም በዓለም አቀፍ ደረጃ 26 ሺህ ሠራተኞች በላይ የሚያስተዳድር ነው። በዘርፉ የ70 ዓመት ልምድ እንዳለው  ታውቋል። ኩባንያው ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ዓመት ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ዓመታዊ ሽያጭም አስመዝግቧል በሀዋሣ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስድስት ፋብሪካዎችን ለማቋቋም ቦታውን ተረክቧል
የኩባንያው ምርቶች ካውያ የማያስፈልጋቸው፣ ቀለማቸው የማይደበዝዝና የማይለቅ የሙሉ ልብስ አላባሽ ሸሚዞች እንደሆኑ ታውቋል። ኩባንያው ከ80 በላይ ምርቶቹን ወደ አሜሪካ የሚልክ ሲሆን፥ ብሩክ ብራዘርስ፣ በርበሪ፣ ጄሲ ፔኒ፣ ኤል ኤል ቢንም ዋና ዋናዎቹ የታል  መለያ (ብራንዶች) ናቸው። በሀዋሣ ኢንዱስትሪ ፓርክም ለዘመናት የሚታወቅበትን ምርት ለማምረት 18 ሚሊዬን የአሜሪካ ዶላር በላይ ኢንቨስት ለማድረግ ስድስት ፋብሪካዎችን ወስዷል።
ለምርት ሂደት የሚጠቅሙ 200 በላይ ኢትዮጵያውያንንም ኢንዶኔዥያ ወደሚገኘው ኩባንያው ወስዶ የማሰልጠን ዕቅድ እንዳለው ገልጿል
95 ዓመታት በላይ ሙሉ ልብስ በማምረት የሥራ ልምድ ያለው  የህንዱ ራይሞንድ ኩባንያም በሀዋሣ ከሚከትሙት ኩባንያዎች አንዱ ነው። ራይሞንድ የህንድን የሙሉ ልብስ ገበያ ከ60 በመቶ በላይ የተቆጣጠረ ሲሆን የምርቶቹንም 40 በመቶ  ለአውሮፓና አሜሪካ ገበያ ያቀርባል። በአሁኑ ወቅት 27 ሺህ 500 ሠራተኞችን የሚያስተዳድረው ኩባንያው  2015 አንድ  ነጥብ 5 ቢሊዬን ዶላር ሽያጭ አስመዝግቧል ራይሞንድ  በሀዋሣ ኢንዱስትሪ ፓርክ በወሰዳቸው ሦስት ፋብሪካዎች ሙሉ ልብስ እያመረተ ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብም ታውቋል።
በተመሳሳይ ፒ የተሰኘው የኢንዶኔዥያና ሃይድራማኒ የተሰኘው የሲሪላንካ ኩባንያዎችም  ሀዋሣ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከከተሙት ኩባንያዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።
ከአምራች ኩባንያዎች በተጨማሪም ቫኒቲ ፌር የተሰኘው የአሜሪካ እንዲሁም  የስዊድኑ ኤች ኤንድ ኤም ግዙፍ ገዥና አከፋፋይ ኩባንያናዎችም በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። ሀዋሣ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ በሁለት ፈረቃ 60 ሺህ ዜጎች  የሥራ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን ለአገሪቱም በዓመት አንድ ቢሊዬን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
የሀዋሣው ፓርክ የዘመኑን የረቀቁ ቴክኖሎጂዎች የሚጠቀም በመሆኑ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ  ነው።  ፓርኩ  85 በመቶ የሚሆን ውኃ መልሶመጠቀም አካባቢንም ከብክለት ከመጠበቅ ባለፈ የውኃ እጥረትን ያስወግዳል። በመሆኑም ለአካባቢ ተስማሚ በመሆን ረገድ  ከአፍሪካ ቀዳሚ ደረጃ ላይ ይገኛል። በፓርኩ የሚሰማሩ 15 የውጭና ስድስት የአገር ውስጥ ኩባንያዎችም ተለይተው ወደ ሥራ ሊገቡ ተዘጋጅተዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ  የሀዋሳውን  የኢንዱስትሪ ፓርክ ባስመረቁበት ወቅት  “የኢንዱስትሪ ልማት ፓርኮችን ማስፋፋት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ግቦችን ለማሳካት ዓይነተኛ መሣሪያ ናቸው” ብለዋል። 

No comments:

Post a Comment