Wednesday, 13 July 2016

የሐዋሳ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ፓርክ በ300 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን በውስጡም 37 ፋብሪካዎች ተገንብተዋል።

የሐዋሳ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ፓርክ በ300 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን በውስጡም 37 ፋብሪካዎች ተገንብተዋል።
እነዚህ ፋብሪካዎች በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ስመ ጥር በሆኑና በኢንዱስትሪ ፓርኩ ለማምረት በገቡ 15 ዓለም አቀፍ ታዋቂ ኩባንያዎች ተይዘዋል።
በዘርፉ የገዘፈ ስምና ዝና ካላቸው አለም አቀፍ ኩባንያዎች መካከል ጥቂቶቹን፦
የአሜሪካው ፒ ቪ ኤች ኩባንያ አንዱ ሲሆን ከ130 ዓመታት በላይ ልምድ ያለውና በምርቶቹ ይበልጥ የሚታወቅ ኩባንያ ነው።
የኩባንያው ምርቶች በአሁኑ ወቅት በዓለማችን በሽያጫቸውም ሆነ በዝናቸው ታዋቂ ከሆኑት መካከል በመጀመሪያዎቹ ተርታ ይገኛሉ።
የዚህ ኩባንያ መለያ ከሆኑት ውስጥ ካልቪን ክሌይን፣ ቶሚ ሂል ፊገር፣ ቫን ሂውሰን፣ ኢዞድ፣ አሮው፣ ስፒዶ፣ ዋርነርስ፣ ኦልጋና ሌሎችም ይገኙበታል፤
ኩባንያው በ2015 ዓመት የ8 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ዓመታዊ ሽያጭ ያስመዘገበ ሲሆን፥ ከ20 ዓመት በፊት ማምረት አቁሞ በዋናነትም በግዥና ማከፋፈል ላይ ተሰማርቶ ቆይቷል።
አለም አቀፍ መለያዎች ከሆኑት አንዱ ኬልቪን ክሌይን በሃዋሳ ይመረታል
በአሁኑ ወቅት ግን በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በዋናነትም የሙሉ ልብስ ሸሚዞችን ለማምረትና ወደ አሜሪካ ሃገር ለመላክ ዝግጅቱን አጠናቆ በግቢው ውስጥ 11 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ለማምረት ወስኗል።
በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ ከግማሽ በላይ ኩባንያዎች ከፒ ቪ ኤች ጋር የተሳሰሩ ሲሆን፥ ኩባንያው በሚፈልገው የጥራት ደረጃ አምርተው በስሙ ምርቶቹን ወደ አሜሪካ ለመላክም ተዘጋጅቷል።
የቻይናው ዉሺ ጂንማኦ ኩባንያም ከመነሻው ቻይና በተጨማሪ በአሜሪካ፣ ቬትናም፣ በባንግላዲሽና በካምቦዲያ የራሱ ፋብሪካዎች አሉት።
ፋብሪካዎቹ ለአሜሪካና አውሮፓ ገበያ የሚያመርቱ ሲሆን፥ ኩባንያው ምርቶቹን በተለይም ለፒ ቪ ኤች፣ ጋፕ፣ ጀ ሲ ፔኒ፣ ታርጌት፣ ቫኒቲ ፌር፣ ፔትኮ፣ ፔት ስማርትና ለኔክስት ያቀርባል።
የ2015 ሽያጩም ከ290 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ እንደነበር ተገልጿል።
ኩባንያው 20 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ኢንቨስት በማድረግ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ 40 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፉ ሶስት ፋብሪካዎችን ወስዷል፤ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን የሸሚዘ ጨርቆችን እንደሚያመርትም ይጠበቃል።
ከባህርዳር፣ ሐዋሳና ወሎ ዩኒቨርሲቲዎች በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የተመረቁ 30 ምሩቃንንም ቻይና ሃገር ወስዶ እያሰለጠነ ይገኛል።
አርቪንድ ሌላኛው በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የከተመና ዋና መስሪያ ቤቱን በህንድ ጉጅራት ያደረገ የ85 ዓመታት ዕድሜ ያለው ኩባንያ ነው።
ከጥጥ የተሰሩ ሸሚዞችና የጅንስ ጨርቆችን በማምረትና በማጠናቀቅ በዓለም ላይ ለታወቁ እንደ ረንግለር፣ ሊ፣ አሮው፣ ቶሚ ሂልፊገር ለመሳሰሉት ያቀርባል።
አርቪንድ የቶሚ ሂልፊገር መለያዎችን በስፋት ያመርታል
ድርጅቱ የጅንስ ጨርቅ በማምረት ከህንድ አንደኛ ከዓለም ደግሞ በአራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ነው።
በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ25 ሺህ በላይ ሰራተኞች ባለቤት የሆነው አርቪንድ ባለፈው ዓመት የ770 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ሽያጭ አስመዝግቧል።
በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ሲያመርት የቆየው አርቪንድ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክም ከ65 ሺህ 300 በላይ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ 7 ፋብሪካ ወስዷል።
የሚታወቅባቸውን ምርቶች እያመረተ ለአሜሪካና አውሮፓ ገበያዎች ለማቅረብም ዝግጅቱን አጠናቋል።
መሰረቱን ሆንክ ኮንግ ያደረገው ታል የተሰኘው ፋብሪካም እንዲሁ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምርቱን እያመረተ ወደ ውጭ ለመሸጥ ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ኩባንያ ነው።
በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ 26 ሺህ ሰራተኞች ያሉት ይህ ኩባንያ የ70 ዓመት ልምድ ያለው ሲሆን 1 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ዓመታዊ ሽያጭም አለው።
በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ 6 ፋብሪካዎችን ወስዷል።
በኩባንያው የሚመረተው ሳይተኮስ የሚለበስ፥ ሲታጠብም ቀለሙ የማይደበዝዝና የማይለቅ እንደሆነ የሚነገርለት የሙሉ ልብስ አላባሽ የሸሚዝ ምርቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኩባንያው መታወቂያ ነው።
በዚህ ምርትም ኩባንያው ለ20 ዓመታት ምርቱን እና መለያውን አስጠብቆ በገበያው ላይ እንደሚገኝ ይነገራል።
ታል ከ80 በላይ ምርቶቹን ወደ አሜሪካ የሚልክ ሲሆን፥ ብሩክ ብራዘርስ፣ በርበሪ፣ ጄሲ ፔኒ፣ ኤል ኤል ቢንም ዋና ዋናዎቹ የታል ገዢ መለያ (ብራንዶች) ናቸው።
በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክም ለዘመናት የሚታወቅበትን ምርት ለማምረት ከ18 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ኢንቨስት ለማድረግ 6 ፋብሪካዎችን ወስዷል።
ለምርት ሂደት የሚጠቅሙ ከ200 በላይ ኢትዮጵያውያንንም ኢንዶኔዢያ ወደ ሚገኘው ኩባንያው ወስዶ የማሰልጠን ዕቅድ አለው ተብሏል።
ሙሉ ልብስ በማምረት የሚታወቀው የህንዱ ራይሞንድ ከ95 ዓመታት በላይ የስራ ልምድ ያለው ሲሆን በአሁኑ ወቅት 27 ሺህ 500 ሰራተኞችን ያስተዳድራል።
በ2015 የ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ሽያጭ ያስመዘገበው ራይሞንድ፥ የህንድን 60 በመቶ የሙሉ ልብስ ገበያ የተቆጣጠረ ሲሆን 40 በመቶ ምርቶቹንም ወደ አውሮፓና አሜሪካ ገበያ ነው የሚልከው።
የህንዱ ራይሞንድ በመሰል ምርቶቹ በስፋት ይታወቃል
በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በወሰዳቸው 3 ፋብሪካዎች ሙሉ ልብስ እያመረተ ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብም ይጠበቃል።
ፒ ቲ ዩ የተሰኘው የኢንዶኔዢያ ኩባንያና ሃይድራማኒ የተሰኘው የሲሪላንካ ኩባንያዎችም እንዲሁ ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከገቡት ኩባንያዎች ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው።
ከአምራች ኩባንያዎች በተጨማሪም ቫኒቲ ፌር የተሰኘው የአሜሪካው ግዙፍ ገዥና አከፋፋይ ኩባንያና የስዊድኑ ኤች ኤንድ ኤም በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ በሁለት ፈረቃ ለ60 ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን፥ በአመት 1 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል።አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 6፣ 2008 (ኤፍ ቢ ሲ)

No comments:

Post a Comment