Thursday, 28 July 2016

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፤ ሕዝባዊ ወገንተኝነት ያለው ትውልድ ለማፍራት!


ብ. ነጋሽ
የኢትዮጵያ ተማሪዎች ወይም ወጣቶች ታሪክ ለሕዝብ በማገለገልና በመታገል ገድል የተሞላ ነው። የኢትዮጵያ ተማሪዎች ከ1950ዎቹ ጀምሮ በአስከፊ ጭቆና ውስጥ የነበረው ጭሰኛ አርሶ አደር የራሱ መሬት እንዲኖረውና ከገባርነት ነፃ እነዲወጣ የ”መሬት ለአራሹ” መፈክር አንግበው በአደባባይ ድምፃቸውን አሰምተዋል። ንቅናቄያቸው አጋር አግኝቶና ፍሬ አፍርቶ ፊውዳላዊው የዘውድ ሥርዓት በ1967 ዓ.ም. ከተገረሰሰ በኋላ፣ ምንም እንኳን ድሉ በጥቂት ወታደራዊ መኮንኖች ቢእጅ ቢገባም በለውጡ ማግስት “በዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ” ወደገጠር በመዝመት በመሬት ለአራሹ አዋጅ የመሬት ባለቤት ለመሆን ያበቃውን አርሶ አደር አገልግለዋል። ዘመቻው ሲታሰብ በነበረው የዋህ ዓላማም መሰረት ተማሪዎቹ በመላው የኢትዮጵያ ገጠር በመሰማራት መይማኑን ጎልማሶች መሰረተ ትምህርት በማስተማር፣ ጭሰኞችን በማህበር በማደራጀት፤ የመሬት ባለቤት የሚሆኑበትን ሥርዓት በማበጀትና አጠቃላይ የገጠር የልማት ሥራዎችን በማከናወን ነበር አርሶ አደሩን ሲያገለግሉ የነበረው።
እርግጥ ይህ የእድገት በኅብረት ዘመቻ ከጀርባው አስገዳጅ አዋጅ የነበረ ቢሆንም፣ ዘመቻው የሚመለከታቸው ተማሪዎች ግን ወደ ገጠር ዘምተው አርሶ አደሩን ሲያገለግሉ የነበሩት  የመሬት ባለቤት እንዲሆን በታገሉበት ሥዝባዊ ስሜት ነበር። 60 ሺህ ገደማ የሚሆኑት የሁለተኛ ደረጃና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች/ወጣቶች ከጥር 1967 ዓ.ም. እስከ 1968 ዓ.ም. መጨረሻ ለሁለት ዓመታት ያህል በዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ ተሳትፈው ከላይ የተገለጹትን ማህበራዊና  የልማት አገልግሎቶች የሰጡት ያለምንም ክፍያ ነበር። ቀደም ሲል እነደገለፅኩት ይህ የእድገት በህብረት ዘመቻ በወታደራዊው ደርግ አስገዳጀ ሕግ የተመራ ቢሆንም፣ እንዲሁም ተማሪውን በማሸሽ ተቃውሞን ለማፈን የተደረገ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው ነው የሚሉ ወገኖች ቢኖሩም፣ ወጣቱ በዘመቻው ላይ የነበረው ተሳተፎ ግን ፍፁም ህዝባዊ ሰሜት የታየበት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተደርጎ መታየት ያለበት ነው የሚል እምነት አለኝ።

እርግጥ አብዛኛው ዘማች ወጣት ከተወሰኑ ወራት በኋላ ዘመቻውን አቋርጦ የተመለሰ/የተበተነ ቢሆንም ያቋረጠበት ምክንያት ግን የበጎ ፈቃድ አገልገሎት ለመስጠት  ፍላጎት ከማጣት የመነጨ አልነበረም። ይልቁንም ንጉሡን የተካውና የ1966ቱን አቢዮት የሕዝብ ድል መንተፎ የለየለት አምባገነንና ጨቋኝ ሆኖ የወጣውን ሥርዓት ለመታገል ነበር። የህይወት መስዋዕትነት ለሚሻ ሌላ ህዝባዊ ትግል ነበር።
በዚሁ በአምባ ገነኑ የወታደራዊ ደርግ ሥርዓት አሁንም ከጀርባው አስገዳጅ ሕግ ቢኖርም ለአስገዳጀነቱ በዙም ዋጋ ሳይሰጡ ወጣቶች በሕዝብ ወገንተኝነት ስሜት አገልግሎት የሰጡበት አጋጣሚም አለ። ይህም ከ1971 ዓ.ም. ክረምት ጀምሮ የተካሄደው የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ ነው። ይህ ማንበብ መፃፍ የማይችሉ ማይም ኢትዮጵያውያንን ማንበብና መፃፍ እንዲማሩ ለማድረግ በገጠርና በከተማ ከአስር ዓመታት በላይ የተካሄደ የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ በከፍተኛ ደረጃ ወጣቱን ከበጎ ፈቃድ አገልገሎት ጋር አስተዋውቆታል።
እነዚህ ከላይ ያነሳኋቸው የወጣቶች የሕዝባዊ አገልግሎት መርሃ ግብሮች በተደጋጋሚ እንደገለፅኩት አስገዳጀነት የነበራቸው ቢሆኑም በኢትዮጵያ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ ሕዝባዊ  አገልግሎት ታሪክ ውስጥ ሊጠቀሱ ይገባል እላለሁ።
እንግዲህ አምባ ገነኑ ወታደራዊ ደርግ የዛሬ ሃያ አምስት ዓመት ተወግዷል። ይህን አምባ ገነን ሥርዓት ለማስወገድ በተካሄደ ትግል ውስጥ የኢትዮጵያ ወጣቶች ትልቅ ድርሻ ነበራቸው። ዘውዳዊውን ሥርዓት ታግለው ያስወገዱትና በትግላቸው ያስገኙትን የሕዝብ ድል  የተነጠቁት ወጣቶች ናቸው አሁንም አርሶ አደሩን ከጎናቸው አሰልፈው ወታደራዊውን ደርግ ታግለውና አታግለው የገረሰሱት። በዚህ በተለያየ አቅጣጫ ወታደራዊውን ደርግ ለማስወገድ በተካሄደ ትግል የአንድ ትውልድ ወጣት መስዋእትነት ከፍሏል።
አሁን በአገራችን ያለው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር - መርጠው በወከሏቸው ሰዎች የመተዳደር፣ በቋንቋቸው የመንግሥት አገልግሎት የማግኘት፣ ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የማስተማር፣ ታሪካቸውን የመንከባከብ፣ ባህላቸውን የማስተዋወቅና የማጎለበት . . . መብትና ነፃነት የተረጋገጠበት፤ የአመለካከት ነጻነት፤ በአመለካከት የመደራጀት፣ አመለካከትን የማራመድ፣ የመግለፅ፣ በአመለካካት ለፖለቲካ ስልጣን የመፎካካር፣ በሕዝብ ድምፅ በሚገኝ ውክልና ስልጣን የመረከብ እና ሌሎች ፖለቲካዊና ሰብዐዊ መብቶች የተረጋገጡበት ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት የቀደመው ወጣት ትውልድ መስዋዕትነት ውጤት ነው። የኢትዮጵያን ህዝብ ለዘመናት ከኖረበት የድህነት አዘቅት በማውጣት የተሻለ ህይወት እንዲመራ ለማስቻል ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የተካሄደው ትግልና የተገኘው የእድገትና የልማት ሰኬትም የባለፈው ትውልድ ወጣቶች መስዋዕትነት ውጤት ነው።
ከላይ በመጠኑ የገለፅኩት የቀደመው ትውልድ ወጣቶች እስከ ህይወት መስዋዕትነት የዘለቀ ህዝብን የማገልገል ፈቃደኝነት አዲሲቱን ኢትዮጵያ በመፍጠር ሂደት ውስጥ ትልቅ ድርሻ አለው።
አዲሱ ወጣት ትውልድም ይህን የቀደሙትን ወጣቶች የሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ ሊወርስ ይገባል። የአሁኑ ወጣት ትውልድ በመስዋዕትነት የተገነባ ሌላ የህይወት መስዋዕትነት በማይጠይቅ የተደላደለ ሁኔታ ላይ ነው ያለው፤ ይህ ማለት ግን ምንም ኃላፊነት የለበትም ማለት አይደለም። ይልቁንም፤ ሕዝቡን ካለበት ድህነት አውጥቶ  ዋስትናው ወደተደጋገጠ ብልጽግና በማሸጋጋር የኢትዮጵያን ህዳሴ የማረጋጋጥ ታላቅ የትውልድ፤ የጊዜና የሞራል ኃላፊነት አለበት። ይህን ማድረግ ደግሞ፤ በየሞያ መስኩ ከራስ ጥቅም ባሻገር የሕዝብን የተሻለ ህይወት የማረጋገጥ፣ ፍፁም ሕዝብን በማገለገል ስሜት የታነፀ የፖለቲካ አመራር የመስጠት ተነሳሽነትን ይሻል። ይህም ደግሞ በሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ/ሞራል የተገነባ ትውልድን ይሻል። የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ይህን ሞራል ለመገንባት ያስችላል።
የበጎ ፈቃድ አገልገሎት መነሻውም መድረሻውም ሕዝብን ማገልገል የሆነ፤ ያለምንም ክፍያ ወይም ልዩ ጥቅማ ጥቅም የሚከናወን በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ዕውቀት የማሸጋገር ሥራ ነው። ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ወጣቶች በተለይ የትምህርት ተቋማት በሚዘጉበት የክረምት ወቅት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት ማድረግ ጀምረዋል። ይህ ዓይነቱ ተሳትፎ የወጣቱን ሰብዕና ዘላቂ በሆነ መንገድ የመቅረጽና ሕዝባዊ ወገንተኝነትንና ፍቅር የማዳበር፤ ግለሰባዊና ማህበራዊ ኃላፊነትን በተሟላ አግባብ የማላበስ አቅም አለው።    
የአገሪቱ ወጣቶች ባለፉት ዓመታት የጀመሩት ይህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰፋ መጥቶ በያዝነው ክረምት 12 ሚሊዮን ወጣቶች እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡ እነኚህ ወጣቶች ከዩኒቨርሲቲዎች፣ 2 ደረጃ ምህርት ቤቶችና ከተለያዩ አደረጃጀቶች የተውጣጡ ሲሆኑ፤ ክረምቱ እንደባተ በገጠርና በከተሞች ተሰማርተው ሕዝባዊ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡
ወጣቶቹ በገጠር ጎልማሶችን መሰረተ ትምህርት በማስተማር፣ በከተሞች 1 እና 2 ደረጃ ተማሪዎችን የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት የተማሪዎቹን ብቃት በማጎልበት ለአገሪቱ የትምህርት ጥራት የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። በገጠር የአርሶ አደሮችን የተሻሻለ የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ግንዛቤ በማዳበር ተግባር ላይ ተሰማርተዋል። በችግኝ ተከላና በአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ሥራም ላይ ይሳተፋሉ። በተለይ በችግኝ ተከላ፣ በአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ላይ የሚያከናውኗቸው ተግባራት በመገንባት ላይ ያለውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጨምሮ የአገሪቱ የኃይል ማመንጫ ግድቦች ከደለል ተጠብቀው በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት እንዲሰጡና የታቀደላቸውን እድሜ ያህል አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ ያለው ነው። በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩት ወጣቶች የአገሪቱን ከተሞችም አረንጓዴና ጽዱ ለማድረግ የተያዘውን እቅድ እያገዙ ይገኛሉ። ወጣቶቹ የደም ልገሳ በማድረግም ወገናቸውን ያግዛሉ።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ለዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም ዕውቀት በማካፈል እያበረከቱ ያሉት አስተዋጽኦ ልማቱን ከማገዝ በተጨማሪ፤ ወጣቶች በበኩላቸው ሕዝባዊ ወገንተኝነትንና ፍቅር እንዲቀስሙና እንዲያዳብሩ፤ ግለሰባዊና ማህበራዊ ኃላፊነትን መሸከምንና መወጣትን እንዲለማመዱ የሚያስችል መልካም ታሪካዊ አጋጣሚ ነው። ከሁሉም በላይ፤ ሕዝብን ለማገልገል ፈቃደኛ የሆነ አገር ተረካቢ ትውልድ ለመቀረፅ ዓይነተኛው መንገድ በመሆኑ ሊበረታታና ሊደነቅ ይገባል። ዛሬ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ 12 ሚሊዮን ወጣቶች የኢትዮጵያን ህዳሴ የማረጋገጥ ብቃት ያላቸው የነገ ሃገር ተረካቢዎች ናችውና።

No comments:

Post a Comment