ታከለ አለሙ
ለአንድ ሀገር ትልቁና ወሳኙ ሀብት ሰላም ነው፡፡ ሰላም በገንዘብ አይገዛም፡፡
ሰላም በምድራችን ባሉ ውድና እንቁ ነገሮች ሁሉ አይተመንም፡፡ የሰላም ዋጋ ቀመርና ስሌት የለውም፡፡ ሰላም የሁሉም ገዢና የበላይ
ነው፡፡ ለአንድ ሀገር ሰላም ማለት ጤናማ ህይወትና እስትንፋስዋ መሆኑ
አያከራክርም፡፡ የሰላም መደፍረስ የጸጥታ መታወቅ በሰላም ወጥቶ ሰርቶ በሰላም ወደቤት ወደ ልጆች መመለስ አለመቻል የሰላም መታጣትን
ያሳያል፡፡ ሰላም ከሌለ ሀገር ታማለች ታውካለች ማለት ነው፡፡ መስራት መትጋት ያለብን የሀገር ሰላም ሁሌም ተጠብቆ እንዲኖር ነው፡፡
ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል እንዳይሆን አርቆ ማስተዋል ይገባል፡፡
የሰላምና የመረጋጋት አለመኖር እጦት ይህን ተከትሎ የሚመጣው ሁከትና ግርግር
ሰላማዊ የነበሩ ብዙ ሀገራትን አፈራርሶአል፡፡ በዚህ ሁኔታ ተጠቃሚ የሆነ ህዝብና ሀገር እስከአሁን አላየንም፡፡ የነበሩት ሁሉ እንዳልነበሩ
ሁነው ወድመዋል፡፡ ይህንን አደገኛ ሁኔታ ማየት ደግሞ ማንም አይፈቅድም፡፡
አክራሪና ጽንፈኛ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የህዝቡን ብሶትና ቅሬታ በመጠቀም
ቀዳዳውን አስፍተን የከፋ ትርምስ እንፈጥራለን በሚል የሚሄዱበት መንገድ ሀገራትን መመለሻ ለሌለው ውድቀት ዳርጎአቸዋል፡፡ ህዝባቸው
አልቆአል፡፡ ኢኮኖሚቸው ወድቆአል፡፡ በአንድ ዘመን ገናና የነበሩ ሀገራት እንዳልነበር ሁነው ጠፍተዋል፡፡ እንዲህ አይነቶቹ የሀገርና
የህዝብ ጠንቆች ለምንም አይበጁም፡፡ ልንከላከለው የሚገባን ከወዲሁ ነው፡፡ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ፡፡
ሰላም ከሌለ ስለሀገር ደህንነት ስለህዝብ ሰላማዊ ህይወትና ኑሮ ስለኢኮኖሚ
ልማትና እድገት ማሰብ አይሞከርም፡፡ በአለማችን ያሉ መንግስታት አይነታቸው የተለያየ ቢሆንም በህዝባቸው ውስጥ መጠነ ሰፊ ቅሬታዎች
አሉ፡፡ የህዝብ ብሶት እሮሮ የስራአጥነት የመኖሪያ ቤት የመንግስታዊ ቢሮክራሲ የፍትህ የታላቅ ሙስና በስልጣን ያለአግባብ የመጠቀም
ችግሮች በሰፊው አሉባቸው፡፡ ሞልተው ተርፈዋል፡፡ በድሀም ሆነ በአደጉና በበለጸጉ ሀገራት፡፡
በተለይም ሙስናን በተመለከተ አለም አቀፉ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል
የሀገራትን ደረጃ በየግዜው ያወጣል፡፡ በአለም ደረጃ ያሰራጫል፡፡
በቀዳሚነት የሚገኙት ያደጉ የአውሮፓ የኤሽያና የአፍሪካ ሀገራት ዝርዝራቸው በቅደም ተከተል ይወጣል፡፡ የትም ሀገር ላይ የተባሉት
ችግሮች ሞልተው ተትረፍርፈዋል፡፡ በእርግጥም የአፈታቱ መንገድ ይለያያል፡፡ ዋናው ነጥብም እንዴት ይፈታል የሚለው ነው፡፡
መንግስት በራሱ መንገድ አጣርቶ የተጠቀሰውን ችግር ለህዝብ በይፋ አሳውቆ
ተጠያቂ የሚሆኑትን በህግ አግባብ እንዲጠየቁ የሚያደርግበት ወይም በፓርቲዎች ከሆነ የሚመራው ፓርቲው ሙሉ ሀላፊነቱን ወስዶ የራሱን
ማጥራት በውስጥ በማካሄድ ከሃላፊነት የሚያነሳበት በህግ እንዲጠየቁ የሚያደርግበት ሁኔታም በተደጋጋሚ ታይቶአል፡፡ ከዚህም ባለፍ
የሙስና ደረጃው እጅግ የገዘፈ ሁኖ ሲገኝ ስርአቱን ይዞ የሚጠፋበትም ሁኔታ ይከሰታል፡፡ በሙስና የወደቁ መንግስታት በርካታ ናቸው፡፡
ፈጥነው እርምት በማድረግ ሁኔታውን ለማስተካከል እርምጃ የሚወስዱት በዚህ
መልኩ ለህዝቡ ተቃውሞ ለመብቱ መከበር ላቀረበው ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ ምላሹ በቂና ተገቢ አይደለም ብሎ ህዝቡ ሲያምን ተቃውሞውን
ደግሞና ደጋግሞ በሰላማዊ መንገድ የሚገልጽበት ሁኔታም አለ፡፡ ይህንን አይነቱን አጋጣሚ የተለያዩ የተደራጁ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመጠቀም
ለፖለቲካ ስልጣን ተፎካካሪነት ሲሉ ህዝቡን ወደ አልተፈለገ ሁከትና ብጥብጥ የመሩበት በዚህም ከፍተኛ የህይወትና የንብረት ውድመት
የደረሰበት አልፎም ሀገር እስከማጥፋት፣ እስከመበተን የዘለቀበት የታሪክ ክስተት በሊቢያ፣ በሶርያ፣ በየመንና በግብጽም ታይቶአል፡፡
ዛሬም ሀገራቱ የተረጋጋ ሰላም የላቸውም፡፡ በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ
በመግባት ተቃዋሚውን በመደገፍና በማደራጀት የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ግርግር ሁከት አመጽ በህዝቡ ውስጥ እንዲቀጣጠል በማድረግ
የሚመሩት የተለያዩ ሀገራት የደህንነት ሀይሎችና የውስጥ አክራሪ ጽንፈኞች ናቸው፡፡ አስቀድመው ከየሀገራቱ ሰዎችን እየመለመሉ ስልጠና በመስጠት ሁከቱንና አመጹን እንዴት እንደሚመሩት
ያዘጋጃሉ፡፡ ሁኔታው አመቺ ነው በስሎአል ባሉበት የመረጃ ትንተናቸው ሰአት ስምሪት በመስጠት በህዝቡ ውስጥ የተከሰተው ተቃውሞና
አመጽ ከመንገድ እንዲወጣ ይሰራሉ፡፡ ያስተባብራሉ፡፡ አልተሳካላቸውም እንጂ ይህ ድርጊት በእኛም ሀገር ተሞክሮአል፡፡ ላለመሳካቱ
ዋናው ምክንያት ህዝቡ ስለተከላከለውና ምንም አይነት ክፍተት ስላልሰጠው
ነው፡፡ የአሁኑም ጥፋትና ውድመት የነዚህ ሀይሎች ሴራ ነው፡፡
ግብጽን፣ ኢራቅን፣ ሶርያንና የመንን በዚህ መልኩ ነው ያተረማመሱዋቸው፤
ያወደሙዋቸው፡፡ አክራሪና ጽንፈኛ አሸባሪ እስላማዊ ሀይሎች በአንድ ወገን የቀለም አብዮት አራማጆች በሌላ ወገን በመሆን በየፊናቸው
የህዝቡ ተቃውሞ እንዳይበርድ ያቀጣጥሉታል፡፡ የተቃውሞው አድማስ በተለያዩ አካባቢዎች እንዲስፋፋ እምቢተኝነት እንዲነግስ፣ ሁሉም
ነገር ከህግና ከስርአት ውጭ እንዲሆን በማቀድ ስርአተ አልበኝነትን በማስፈን ንብረት እንዲወድም ያደርጋሉ፡፡ ይህ ሆን ተብሎ ታቅዶ
የሚሰራ፤ ሀገር የማፍረስ አደገኛ ሴራ ነው፡፡ መቼም ሆነ መቼ የማይበጅ
በመሆኑ ህዝቡ ሀገሩን ከጥፋት ነቅቶ መጠበቅ አለበት፡፡
አክራሪና ጽንፈኛ ተቃዋሚ ሀይሎች በውጭ ሀይሎች በመታገዝና በመረዳት የጎዳና
ነውጥን አመጽና ትርምስን እንደሰደድ እሳት እያቀጣጠሉ ሀገራቱ ሰላማቸውን አጥተው ህዝቡም ታይቶና ተሰምቶ ለማይታወቅ ዘግናኝና አሰቃቂ
ችግር ላይ እንዲወድቅ አድርገውታል፡፡ ሰላሙን ማጣቱ ብቻ ሳይሆን በነገሰው ስርአተ አልበኝነት ሀብትና ንብረቱ ተዘርፎአል፡፡ ህይወቱን
በዘራፊዎች ተነጥቆአል፡፡ የህግና ስርአት አለመኖር የስርአተ አልበኝነት መንገስ ሀገርና ህዝብን የሚያስከፍለው ዋጋ አጅግ የከበደ፤ ማካካሻም ሆነ መመለሻ የሌለው
ነው፡፡ መጠንቀቅም ይገፈባናል የምንለውም በነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ምክንያት ነው፡፡
በእኛ ሀገር በቅርቡ የተከሰተው የህዘብ ተቃውሞ የመብቴ ይከበርልኝ ጥያቄ
ሲሆን የቀረበውም በህዝቡ ነው፡፡ይህንን ተገቢ ጥያቄ መንግስት መልስ እንደሚሰጥበት ለታዩት ከፍተኛ ችግሮች የመንግስትን ሀላፊነት
ይዘው ለግል ጥቅም መክበሪያ ያደረጉትን ተጠያቂ እንደሚያደርግ በአብዛኛው ህዝብን ያስከፉና ያስመረሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን
እንደሚፈታ ለዚህም ጥልቀታዊ ተሀድሶ በማድረግ ላይ መሆኑን ለህዝብ አሳውቆ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ሁኔታው ይህን የመሰለ መልክ ይዞ ባለበት ሁኔታ በኦሮሚያና በአማራው ክልል
የተከሰተው የሀገርና የህዝብ ሀብትና ንብረትን ፋብሪካዎችን እርሻዎችን የተለያዩ ከባድና ቀላል መኪናዎችን የግለሰቦች ቤቶችን በእሳት
ማቃጠልና ማውደም ሊኮነን፣ ሊወገዝ የሚገባው የወንጀል ድርጊት ነው፡፡ በዚህም መሰረት የአካባቢው ሰላም ደፍርሶ የህዝቡም ህይወት
ታውኮ ከርሞአል፡፡ በህዝቡ የእለት ተእለት ህይወት ላይም ከፍተኛ ችግር ከመፍጠሩም በላይ በማህበራዊ መስተጋብሩ በንግድ ልውውጡ
በግብይቱ በትምህርት ስርአቱ ላይም ከፍተኛ መስተጓጎል ፈጥሮ ቆይቶአል፡፡
ቀደም ሲል እንዳልነው፣ የሰላም ማጣትና መደፍረስ በህዝቡ ውስጥ ከፍተኛ
አለመረጋጋትን ያስከትላል፡፡ ለስርአተ አልበኞች ለዘራፊዎችና ለቀማኞች እንዳሻቸው እንዲፈነጩ በርና ቀዳዳ ይከፍታል፡፡ በኦሮሚያ
እንደታየው የውጭ ሀይሎች ግብጽን የመሰሉ ከኦነግ ጋር በመሰለፍ የሀገርን ሰላም ለማናጋት የልማት ፕሮጀክቶችን ለማደናቀፍ ብሎም
ለማውደም የሄዱበት ርቀት በባህላዊ የሀይማኖት ስርአትና ክብረ በአል ጭምር ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ህዝብን ለአደጋ አጋልጠው የህይወት
መስዋእትነት እንዲከፈል ያደረጉበትን አሳዛኝ ሁኔታም በተጨባጭ አይተናል፡፡ ይህ ሁኔታ እንዲቀጥል የሚፈቅድ ህዝብም ሆነ መንግስትም
ደግሞ የለም፡፡
እነዚሁ ጽንፈኛ ሀይሎች የፖለቲካ አጀንዳቸውን ፍጹም ሰላማዊ ሁኖ በኖረው
የህዝቡ ባህላዊና ሀይማኖታዊ መንፈሳዊ ስነስርአት ላይ ለመጫን በማቀድ
በህዝቡ የተከበሩትን አባገዳዎች በመናቅ የፈጸሙት ህዝብንና እምነቱን የመርገጥ የወንጀል ድርጊታቸው ከባድ ጥፋት አስከትሎአል፡፡
ይህ ከጀርባ በግብጽ የተመራው የኦነግ ተልእኮ ህዝብና መንግስትን ሆን ብሎ ለማጋጨት የተጠነሰሰ ሴራ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኦነግ በኦሮሚያ
የተፈጠረውን ማንኛውም እንቅስቃሴ የመራሁት እኔ ነኝ ሲል ሀላፊነቱን ወስዷል፡፡ ኦነግና ግብጾች በጋራ የነበራቸው ትብብርና ምክር
በተጨባጭ በቪዲዮ ማስረጃ ሊክዱትም ሆነ ሊያስተባብሉት በማይችሉበት ደረጃ ይፋ ወጥቶአል፡፡ እንዲያውም ግብጾች ለኦነጎች በሚቀጥለው
አመት የራሳችሁን መንግስት ትመሰርታላችሁ እስከ ማለት መድረሳቸው ሲታይ ምን ያህል ርቀት እንደሄዱ ተጨባጭ ማረጋገጫ ነው፡፡
በሌላም ወገን የኤርትራው መንግስት ሻእቢያ፣ የተለያዩ አክራሪና አሸባሪ
እስላማዊ ድርጅቶች፣ ዋሀቢና ሰለፊያ፣ በምስራቅ ኢትዮጵያም አልሻባብና ተከታዮቹ ሰላም እንዳይኖር ሀገሪቱና ህዝቡ ሁከትና ትርምስ
ውስጥ እንድትገባ ብጥብጦች እንዲፈጠሩ በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ሰላማዊ ህይወት እንዲናጋ በማቀድ በሰፊው እየሰሩ
ይገኛሉ፡፡ ይህን ሴራ መመከት፣ ማምከንና ማድረቅ የእኛና የእኛ ብቻ ሀላፊነትና ድርሻ ነው፡፡
እዚህ ላይ ትኩረት የሚሻው ትልቁ ጉዳይ የህዝቡን የመብቴ ይጠበቅልኝ ይከበርልኝ
ጥያቄና ተቃውሞ በመጥለፍ የሁከት አድማሱን በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለማስፋት ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ እንዲሆኑ ለህዝብና ለሀገር
የሚጠቅሙ ተቋማትን ድርጅቶችን የመንግስትና የህዝብ ንብረቶችን የማውደሙ ተግባር እየተመራ ያለው በህዝቡ ውስጥ ህዝብን መስለው ሰርገው
በገቡ የኦነግ፣ የሻእቢያና የግብጽ ሌሎችም አክራሪ እስላማዊ ሀይሎች ወኪሎች የጋራ ትብብርና ቅንጅት እንጂ በህዝቡ እንዳልሆነ በግልጽ
መታወቅ አለበት፡፡
ለዚህ ተግባር ተፈጻሚነት አስቀድመው በከፍተኛ የገንዘብ ሀይል በየአካባቢዎቹ
በምስጢር የመለመሉዋቸውን ወጣቶችና ተባባሪዎች በማሰማራት ቀድመው ባዘጋጁት ዝርዝር መሰረት ጥፋቱንና ውድመቱን እንደሚያካሂዱ ህዝቡ
በቂ ግንዛቤ አግኝቶአል፡፡ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ከዚህ አንጻር እጅግ የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው ህዝቡ እየገለጸ ይገኛል፡፡ ህዝብ
ራሱ የሚገለገልበትን፣ የሚሰራበትን፣ የወር ገቢ በማግኘት ቤተሰቡን የሚያስተዳድርበትን ድርጅትና ንብረት ፋብሪካዎች፣ መኪኖች፣ አምቡላንሶች በምንም መንገድ ቢሆን
ለእሳት አይዳርግም፡፡ ይሄ በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡
በደረሰው ውድመት በአሁኑ ሰአት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ለስራ አጥነት
ተጋልጠዋል፤ የወር ገቢያቸው ተቋርጦአል፤ ለእለት የሚሆን ገንዘብ ያጡበት ሁኔታ ተፈጥሮአል፡፡ ቤት ኪራይ የሚከፍሉት፣ ለቀለብ ለልጆች
ትምህርት ቤት የሚሆን ገንዘብ ያጡበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ የእነዚህ ጸረ ሀገርና ጸረ ህዝቦች ሴራና ወንጀል እዚህ ድረስ ህዝቡን
ዋጋ አስከፍሎታል፡፡ ይህን ድርጊት የሚፈጽም ማንኛውም ሀይል በምንም መልኩ ለህዝብ አሳቢ ተቆርቓሪ ነኝ ሊል አይችልም፡፡ የለየለት
ሀገርና ህዝብን ለማጥፋት የተሰማራ ወንጀለኛና ጸረ ህዝብ ቅጥረኛም ሀይል ነው፡፡ በፍጥነት ሊገታ ይገባል፡፡
ትላንት ሰራተኛ የነበሩት ወገኖቻችን ዛሬ ደግሞ ጸረ ህዝቦች በፈጸሙት
ፋብሪካዎችን ድርጅቶችን ወዘተ በእሳት የማጋየት ተግባር የሚሰሩበት ቦታ አገልግሎት ለመስጠት ባለመቻሉ ለስራ አጥነት ተዳርገው የእለት
ኑሮአቸውን ማሸነፍ ተስኗቸዋል፡፡
አንዱ የሴራው አካል ድርጅቶችንና ፋብሪካዎችን ካወደምን የተቃዋሚውን ሀይል
ቁጥር እናበዛለን የሚል ደካማና ተራ ስሌት ነበር፡፡ እንዳሰቡት ማድረግ አልተሳካላቸውም፡፡ ሀገር ማውደም ሀገር ማልማት አይደለምና
እነዚህ ሀይሎች የለውጥ ሳይሆን የጥፋት ሀይሎች ናቸው፡፡
ያቀዱት ሰላምን የማደፍረስ፤ ስርአተ አልበኛነትን የማስፈን፤ መንገድ የመዝጋት፤
በየቦታው ንብረቶችን የማውደም የመዝረፍ ወዘተ ድርጊቶች ለተወሰነ ግዜ ቢሄዱበትም ህዝቡ ማንነታቸውን በውል በመረዳቱ የተነሳ አሁን
ሁኔታውን መቆጣጠርና መግታት ተችሎአል፡፡ ሰላሙንና መረጋጋቱን በየአካባቢው ህዝቡ በራሱ ተነሳሽነት ከመንግስት ጎን ቆሞ በማስከበር
ላይ ይገኛል፡፡ በሌሎች ሀገራት የታየው ስርአተ አልበኝነት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲደገም የሚፈቅድ ህዝብ የለም፡፡
የከፋ ሀገራዊ ትርምስና ጥፋት ምስቅልቅል እንዲፈጠር የሄዱበት መንገድ
ውድቀት እንጂ ለህዝቡም ሆነ ለሀገሪቱ የሚያስገኘው የተሻለ ለውጥ የለም፡፡ በአክራሪነትና አሸባሪነት የተሰለፉት ሀይሎች ስመ ብዙ
ናቸው፡፡ አጀንዳቸው የተለያየ ከመሆኑም በላይ በህግና በስርአት የሚመሩ አይደሉም፡፡ በፉክክር የተቀየዱ ስለሆነ አንድ ሊሆኑም አይችሉም፡፡
በሰላማዊ ውይይት በመነጋገር በሰላማዊ ምርጫ በውድድር በተረጋጋና በሰከነ
ሁኔታ ለውጥ እንዲመጣ የሚሰራ ባሀርይና መስመር የላቸውም፡፡ ዋነኛ አላማቸው የግብጽ አጀንዳ አስፈጻሚ በመሆን የአባይ ግድብ ግንባታና
ሌሎችም የተጀመሩ ለዛሬውም ለነገውም ትውልድ የሚበጁ ሀገራዊ የልማትና የእድገት ፕሮጀክቶች እንዲቆሙ ህዝቡ እርስ በእርስ ግጭት
ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ነው፡፡ ይሄም አልተሳካላቸውም፡፡
የውስጥ ችግሮቻችንን መፍታትና መፍትሄ ማበጀት ያለብን ህዝብና መንግስት
በጋራ በመነጋገር ሲሆን ከዚህ ውጭ ያለው የውጭ ሀይሎች ጣልቃ ገብነት ለሀገሪቱ ሰላምና ደህንነት መቼም አይበጅም፡፡ መማር የቻለ
ከነሶርያና ሌሎች በርካታ ሀገራት ሀገራዊ ውድቀት መማር ይገባዋል፡፡ የሀገር ሰላምና ደህንነት በምንም መልኩ ለውይይትና ለድርድር
የሚቀርብ አይደለም፡፡
ሰላሙን የሚጠብቀውና የሚያስከብረው ህዝብ ነው፡፡ ለሀገሩ ሰላምና መረጋጋት
ዋነኛው ባለቤትና ባለድርሻው ህዝብ ነው፡፡ የሰላም አለመኖርና መደፍረስም የሚጎዳው ይህንኑ ህዝብ ነው፡፡ ተጽእኖውም ፈርጀ ብዙ
ነው፡፡ ከቤተሰብ፣ ህብረተሰብ፣ መንደር፣ ሰፈር፣ ክልል ሲል አስከ
ሀገር ይደርሳል፡፡ የውስጥ ችግሮችን በሰላምና መረጋጋት ተደማምጦ መፍታት ይቻላል፡፡ በዚህ ቀዳዳ ለመጠቀም አሰፍስፈው ለሚገኙ የውጭ
ሀይሎች በር መክፈት ሀገሪቱን ለከፋ አደጋ ማጋለጥ ከመሆኑም በላይ ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል እንዳሉት እንዳይሆን ሁሉም ወገን
ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግበት ይገባል፡፡
No comments:
Post a Comment