Wednesday, 19 October 2016

አስተዛዛቢው የግብፆች ነገረ ስራ




ክፍል አንድ
/²ሰውን ማመን ቀብሮ ነው² አለች አሉ ቀበሮ!/
     ዴቪድ ላምብ የተባለ አሜሪካዊ ጋዜጠኛው ²አረቦችና እስራኤል² በሚል ርእስ የፃፈውን ድርሳን ላነበበ ሰው በተለይም የግብፃዊያንን የፖለቲካ ባህል መገመት አያዳግትም ማለት የሚቻል ይመስለኛል። ይህን የምልክት ምክንያት ደግሞ ላምብ በዚያ መፅሀፉ፤ አወዛጋቢውን የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጅኦ-ፖለቲካዊ እውነታ ከነታሪካዊ ዳራው ያተተበት አግባብ ይልቁንም ግብፅ ስለምታውቅበት ዲፕሎማሲያዊ ዘይቤ በተሻለ ስፋትና ጥልቀት እንድንገነዘብ የሚረዳ ሆኖ ስላገኘሁት ነው።
እናም ከዚህ የተነሳ የዴቪድ ላምብ ትንተና ለኔ እንደገባኝ ከሆነ ²በሀገራት መካከል የሚደረግ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሁሉ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ዘላቂ ወዳጅም፤ ዘላቂ ጠላትም ሊኖር እንደማይችል ያመለክት ይሆናል። ይህን መሰረተ ሃሳብ ወደ የአረቡ አለም ስናመጣው ደግሞ ምናልባትም በብዙ እጥፍ የባሰበት መሸዋወድ ተላብሶ የሚገለጽበት እውነታ ሊያጋጥመን ይችላልና አይግረማችሁ² የሚል ይዘት ነው ያለው። ፀሐፊው ለዚህ አስተያየቱ እንደዋነኛ ምክንያት አስርጎ ባቀረባቸው ነጥቦች ውስጥ በተለይም የቀጠናውን ጅኦ-ፖለቲካዊ ገፅታ የሚወስን ተፅእኖ ያሳድራሉ ከሚባሉት ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ግብፅ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች የፈፀመቻቸውን አስተዛዛቢ ዲፕሎማሲያዊ ክህደቶች የሚያወሱት በቁጥር በርከት ብለው ማግኘቴንም ልብ ትልሉኝ ዘንድ እጠይቃለሁ።
የመፅሐፉ ርዕስ ²አረቦችና እስራኤል² የሚል እንደመሆኑ መጠንም፤ በተለይም የአረብሊግን እንዲመሰረት ከማድረግ አንስቶ አባል ሀገራትን በፊትአውራሪነት እያስተባበረች የጋራ መድረኩን ስትመራ የቆየችው ግብፅ፤ ለዚያን አይነቱ ዓለም አቀፋዊ አመኔታን የሚጠይቅ ሃላፊነት የሚያበቃ የፖለቲካ ባህል ይኖሩታል ብሎ ማሰብ እንደሚያስቸግር ²በገደምዳሜ² ሊገልፅልን መፈለጉን የሚያመለክት እንድምታ ያለው ይመስላል ብንልም ተገቢ ሆኖ ይሰማኛል። እርሱ የግብጽ መንግስታት በተናገሩት ፀንተው ከመገኘት አኳያ እጅጉን ስር የሰደደ ችግር አለባቸው የሚል አንድ ምታ አዘል ትንተናው ላይ እንደምሳሌ ያወሳቸው የመካከለኛው ምስራቅ ጅኦ-ፖለቲካ ታሪካዊ እውነታዎች፤ በአብዛኛው ግብፃውያኑ የሚያስተባብሩት የአረብ ሊግና መሰል ቀጠናዊ ስብስብ ከአይሁዳዊቷ ሀገር ከእስራኤል ጋር፤ የ²ይለይልን² ዓይነት ፍጥጫ ውስጥ ገብቶ በተስተዋክባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ²ፈርኦኖቹ² ቶሎ የማፈግፈግ ወይም የመንሸራተት አዝማሚያ ስለማሳየታቸው የሚያስገነዝቡ ናቸው ማለት ይቻላል።
ለአብነት ያህልም፤ በዚያ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት አወዛጋቢ ታሪክ ውስጥ ²የስድስቱ ቀናት ጦርነት² እየተባለ የሚወሳውን የአረብ እስራኤል ደም አፋሳሽ ግጭትና እንዲሁም ሌሎች የሁለቱ ኃይሎች መንግስታት ጎራ ለይተው ወታደራዊ፤ ወይም ዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫው ውስጥ ሲገቡ የተስተዋሉባቸው ክስተቶች የግብፃውያን ፖለቲከኞችን ቃል አባይነት ያረጋገጡ እንደነበሩ ነው የዴቪድ ላምብ መፅሐፍ የሚያመለክተው። እንዲያውም ይህን እውነታ ከኔ በተሻለ መልክ ሳይገባው ያልቀረ አንድ አንባቢ ወዳጄ ባለፈው 2007 ዓ.ም አጋማሽ ላይ የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ወደ ኢትዮጵያ ለይፋዊ ጉብኝት ምምጣታቸውን ተከትሎ ምን ብሎኝ እንደነበር ማስታወስ ጉዳዩን ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ የሚረዳ ስለሚሆን እነሆ አሳጥሬ አካፍላችሁ ዘንድ ወድጃለሁ።
ነገሩ እንዲህ ነው፤ የአሁኑ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ፤ ገና የጦር ጀኔራልነት ወታደራዊ ማዕረጋቸውን አውልቀው በመጣል የርዕሰብሔርነቱን ስልጣን ከመጨበጣቸው ሀገራችንን ለመጎብኘት መጥተው ያሳዩን የወንድማማችነት መንፈስ ከጠበቅኩት በላይ ²ታሪካዊ ገፅታ የተላበሰ² ሆኖ ነበር ያስገኘሁት። እናም አልፈታህ በዚያ ጉብኝታቸው መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ለሚወከሉበት የፌዴራሉ መንግስት ፓርላማ አባላት ያደረጉትን አስደናቂ ንግግር ጨምሮ፤ በተለይም ሀገራችን በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ስላለው ታላቁ የህዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ አስፈላጊነት አኳያ ግብፅ ተባብሮ መስራትን እንደምትቀበል ሲገልጹ የተደመጡበት አግባብ እንደነሸጠኝ ያጫወትኩት አንዱ ጓደኛዬ ነው። ያኔ የዴቪድ ላምብን መጽሐፍ አስታውሶ ሊመክረኝ የሞከረው።
ስለዚህም እኔ በአልሲሲ የወዳጅነት መንፈስ እጅጉን ጎልቶ በተንፀባረቀበት ይፋዊ ጉብኝት ከመመሰጤ የተነሳ የኢትዮጵያ እና የግብፅ መንግስታት ግንኙነት ለወትሮው የሚታወቅበት ጤናማ ያልሆነ ገፅታ ሙሉ በሙሉ እየተቀየረ ነው የሚል እምነት ማሳደሬን ስገልጽለት ሃሳቤን ያልተቀበለው ወዳጄ እንዲህ ሲል የመከረኝን አስታውሳለሁ…
²ተው እንጂ ወዳጄ ቸኩለህ አትደምድም። ወይስ አረቦች እና እስራኤል የሚል ርዕስ ያለውን የዴቪድ ላምብ መጽሀፍ አላነበብከው ይሆን? መቼም ያን መፅሐፍ ያነበበ ሰው ግብፆችን እንዲህ በቀላሉ ሊያምን ይችላል ብሎ መገመት ያስቸግራልና ነው አንተንም መጠርጠሬ²
እንደእውነቱ ከሆነ ይህ የእርሰሱ አስተያየት በእርግጥም ስለግብፆች ቃል የማበል አባዜ የተጠናወተው ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ዘይቤ በስፋት የተተረከበትን ተጠቃሹ 3 የዴቪድ ላምብ መፅሐፍ ከእኔ ይልቅ በጥሞና አንብቦ ጠቃሚ ቁም ነገሮችን  እንደተገነዘበበት ነው የገባኝ። የዚያን ወዳጄን አስተዋይነት ይበልጥ እንዳደንቅ ያደረገኝ ሌላ ምክንያት ግን፤ በተለይም ከሰሞኑ አንዳንድ ግብፃዊያን ፖለቲከኞችና እንዲሁም ደግሞ ምሁራን ያረጀ ያፈጀውን ፈርኦናዊ አስተሳሰብ የሚያንፀባርቅ የፀብ አጫሪነት ፕሮፖጋንዳቸውን በኢትዮጵያ ላይ እንደ አዲስ ማስተጋባት ስለመጀመራቸው የሚያመለክት ዜና ከወደ ካይሮ ሲዘገብ የመደመጡ ጉዳይ ነው።
ስለዚህ  እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በትኩረት የምከታተለውን የአባይ ተፋሰስ ባለድርሻ ሀገራት ለፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ የመገዛት አለመገዛት ጉዳይ ግብፆች የምር ተቀብለውታል ወደሚል ቅን ድምዳሜ ለመድረስ የቃጣሁበት የካችአምናው ስሌቴ ስህተት እንደነበር መገንዘቤን በተለይም ለዚያ አስተዋይ ወዳጄ እገልጽለት ዘንድ እሻለሁ። ምክንያቱ ደግሞ ሰሞነኛው የካይሮ ሚዲያዎች ዘገባ እንዳረጋገጠልን ከሆነ፤ በእርግጥም ²ግብፆችን ማመን ቀብሮ ነው² የሚያሰኝ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ቅሌት ከመፈፀም አሁንም ድረስ አለመቆጠባቸውን የሚያመለክት ጥሬ ሀቅ ገሀድ ወጥቷልና ነው።
ስለሆነም ጉዳዩን ከዚህ ወቅታዊ ክስተት አኳያ ማጤን ግድ የሚል መስሎ እንደሚሰማኝና አሉታዊ አንድምታዎቹን በተመለከተ አንዳንድ ተጨማሪ ነጥቦችን ማንሳት እንደሚኖርብኝ ስለማምን አሁን በቀጥታ ወደዛው አልፋለሁ። በዚህ መሰረትም ሰሞኑን አንዳንድ የግብፅ ሚዲያዎች በስፋት ሲያራግቡት የተደመጠው የዚያች ሀገር የፖለቲካ ልሂቃን ኢትዮጵያን እንደታሪካዊ ጠላት ከመቁጠር የሚመነጭ መርዘኛ ፕሮፓጋንዳ ይዘት ምን አይነት አንድምታ ነው ያለው? የሚል ጥያቄ አንስቶ ሁነኛ ምላሽ መፈለግ እንደሚገባና እንዲሁም ደግሞ ከጉዳዩ በስተጀርባ ለሚዶለትብን ሴራ ተልዕኮ አስፈፃሚዎቹ ኃይሎች እነማን ናቸው? እውን ኦ.ነ.ግ ብቻውን ነውን? ወዘተ የሚሉ ተያያዠ ነጥቦችን በቅጡ መፈተሽ እንደሚጠቅም ከማመን የመነጨ የግል ምልከታዬን አሳጥሬ ለማቅረብ እሞክራለሁ።
እንግዲያውስ በቅድሚያ ለመሆኑ ይህን ሰሞነኛ የካይሮ ሚዲያዎች ያስደመጡንን ፀረ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ፕሮፖጋንዳ በማቀነባበር ረገድ የግብፅ መንግስት እጅ የለበትም ብሎ ማመን ይቻላልን? ለሚለው ጥያቄ የራሴን ስሌት መነሻ ያደረገ ምላሽ መስጠት የሚጠበቅብኝ ሆኖ ይሰማኛል። እና እንደእኔ እምነት ከሆነ በተለይም መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም የተከበረውን የኢሬቻ በዓል እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው የኦሮሚያ ክልልን ወደለየለት የሥርዓት አልበኝነት መፈንጫነት ሊያስገቡት ሲሞክሩ የተስተዋሉትን የጥፋት ኃይሎች ²ጎሽ አበጃችሁ! እኛም ከጎናችሁ ነን² እንደማለት የሚቆጠር ቅኝት ያለው ሆኖ ከተሰማኝ የግብጽ ሚዲያዎች ፀረ ኢትዮጵያ ዘገባ በስተጀርባ የፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ እጅ አይኖርበትም ብሎ ማመን ተራ የዋህነት ይመስለኛል።
ምንም እንኳን የግብፅ መንግስት በጉዳዩ እጁ እንደሌለበትና የካይሮውን ፀረ ኢትዮጵያ የምክክር መድረክ ያዘገጁት የዛች ሀገር ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እንደሆኑ የሚገልጽ ማስተባበያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ አማካኝነት ስለመስጠቱ ረቡዕ ጥቅምት 2 ቀን 2009 ዓ.ም ታትሞ የወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ ላይ የተዘገበውን ዜና ባነብም፤ ግን ደግሞ እውነታው ከማስተባበያው ይልቅ ጎልቶ እየወጣ መምጣቱን ደፍሮ መናገር ይቻላል። በግልጽ አነጋገር የግብጽ መንግስት ከኦነግና እንዲሁም ደግሞ ለአማራ ህዝብ ያሰቡ መስለው የአዞ እንባቸውን ሲያነቡ ከሚደመጡት ፅንፈኛ የትምክህት ኃይሎች ጋር ከመጋረጃው በስተጀርባ ተመሳጥሮ የዶለተው ፀረ ኢትዮጵያ ስራ ባይኖር ኖሮ ላለፉት በርካታ ወራት እቺን ሀገር ለማተራመስ የተሞከረበት የሁከት ተግባር ባለተስተዋለ ነበር ማለቴ ነው።
ወደ እንደዚህ አይነቱ ድምዳሜ እደርስ ዘንድ የሚያስገድዱኝ አሳማኝ ምክንያቶችን በተለይ እዚህ ሀገር ውስጥ ያሉት የኦነግና የግንቦት ሰባት ጉዳይ አስፈፃሚዎች አመጽ የመቀስቀስ ተልዕኮአቸውን ለመወጣት ሲሉ የሚየያደርጉት ግልጽና ህቡዕ እንቅስቃሴ ሁሉ ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል ለማማለል የሚያስችል በቂ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙበት አስተማማኝ ምንጭ ስለመኖሩ ያሳብቅባቸዋልና ነው። ለአብነት ያህልም በምዕራቡ ዓለም ሀገራት የሚኖሩትን አክራሪ ዲያስፖራ ተቃዋሚዎች ጨምሮ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኝነት ፅንፈኛ አመለካከት አቀንቃኝ ልሂቃን በተቀናጀ መልኩ አስተባብረው እንደሚያቀነባብሩት የሚነገርለትን ስነ ፅሁፋዊ የአስተሳሰብ ጦርነት በስርዓቱ ላይ የከፈቱበት ስፋትነናጥልቀት ሲታይ ከበስተጀርባቸው ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ሲባል የሚደረግ አስተማማኝ የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጡአቸው ኃይሎች እጅ እንዳለበት አምነን እንቀበል ዘንድ ያስገድዳል። ከዚህ አኳያ እኔ የታዘብኩትን ተጨባጭ እውነታ በዝርዝር ማተት አስፈላጊ መስሎ ባይታየኝም ቅሉ፤ ግን ደግሞ አስተያየቴን የሚጠራጠር አንባቢ ካለ ቢያንስ ላለፉት ጥቂት ዓመታት ታትመው የወጡ የአማርኛ መጽሐፍትን ብቻ እንኳን ተመልክቶ ጥሬ ሀቁን እንዲረዳ ልጠቁመው እወዳለሁ።
ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢና አንገብጋቢ መፍትሄ የሚሻ የሚያደርገው ምክንያት ደግሞ ምን መሰላችሁ? እነዚሁ ከባህር ማዶ እስከ ሀገር ቤት ድረስ በተዘረጋ ግልፅና ህቡዕ የመረጃ መረባቸው አማካኝነት የሚቀነባበር የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኝነት ፕሮፖጋንዳዊ ስብከታቸውን በመፅሐፍ መልክ እየጠረዙ የማሰራጨት ዘመቻ ላይ የተሰማሩ ወገኖች እነርሱ የሚፈልጉትን አመፅ ቀስቃሽ የስነ ፅሑፍ ስራ ከምኔው አዘጋጅተው እንደሚያሳትሙት ለማመን እስኪያዳግት በላይ በላዩ እያመጡ ግራ የሚያጋቡንን ያህል፤ የህዳሴው ዘመን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን የሚያንፀባርቅ አስተሳሰብ ያላቸው ዜጎች ድርሳን እንዳይፅፉም ጭምር የሚያደርጉበት ብርቱ አሉታዊ ተፅእኖአቸው ሲታይ ያስደነግጣል። እንዲያውም እንደነእርሱ አባባል ኢትዮጵያ በህዳሴ ጉዞ ላይ ያለች ሀገር ናት የሚል መሰረተ ሀሳብ፤ ወይም ደግሞ ጭብጥ የሚያነሳ ደራሲ ²ኢህአዴግ ኢህአዴግ የሚሸት አመለካከት የተጠናወተው አድር ባይ ፀሀፊ² ተደርጎ ይፈረጃል።
ከዚህ የተነሳም ኢትዮጵያ በህዳሴ ጉዞ ላይ የምትገኝ ሀገር ናት የሚል አቋሙን ለመግለጽ የሞከረበት የአስተሳሰብ ወገንተኝነቱ እንደነውር ተቆጥሮ ደራሲው ዜጋችን እንዲሸማቀቅና በተለይም ደግሞ ለማሳተም እንዳይችል ሲባል መንገዶች ሁሉ የእነርሱ ስውር መረብ በሚፈጽመው ፈርጀ ብዙ ፖለቲካዊ ደባ እንዲዘጉበት የማይፈነቅሉት የክፋት ድንጋይ የለም ማለት ይቻላል። በዚያው ልክም አፍቃሪ ህዳሴ ፀሀፍት ²ምን የሚሉት የሀገር ክህደት ወንጀል ፈፅሜ ነው የዚህን ያህል የተወሳሰበና ተደጋጋሚ ፈተና እጋፈጥ ዘንድ መገደዴ? እቺው እነርሱም እኔም የጋራ ቤታችን አድርገን የምንወስዳት ሀገረ-ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞው ታሪካዊ ከፍታዋ በማቅናት ላይ መሆኗን የሚያመለክት የህዳሴ ጉዞ ጀምራለች ብዬ ማመኔ እውን ለከፋ ውግዘት የሚዳርግ ስህተት ነው እንዴ?² ወዘተ እያለ የገዛ እራሱን እስከመጠየቅ የሚያደርስ ግራ መጋባትና ተስፋ ቆርጦ የክየና ጥረቱን እንዲያቆም የሚያስገድድም ጭምር ስሜት ሊሰማው ቢችል አያስገርምም።  

No comments:

Post a Comment