Thursday, 27 October 2016

በአደርባይነትና በቲፎዞ የመንግስትን ስልጣን መቆናጠጥ አበቃለት !!




ስሜነህ
ባለፉት 25 ዓመታት ሃገራችን ጭልጥ ካለ ድህነት ውስጥ ወጥታ በእድገት ጐዳና ላይ ስለመገኘቷ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት በዓለም ፈጣን የሚባለውን እድገት በማስመዝገብ የአፍሪካ ቁንጮ ሆና መቆየቷም አያከራክርም፡፡ ከዚህ መሰረታዊ ስኬት በመነሳትም  መላው ዜጋ በሁሉም መስክ የተጀማመሩ መልካም ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ፍላጐቱ ጣራ የነካበት ወቅት ላይ የሚገኝ መሆኑን መገመት አይከብድም፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ሃገራችን ወደ ፊት በተራመደችባቸው በእነዚህ ዓመታት፣  ቀስ በቀስ እያደጉ የመጡ በርካታ ችግሮችም አሉ፡፡ መንግስት ባደረገው አጠቃላይ ግምገማና ጥልቅ ተሃድሶ እንዳረጋገጠውእነዚህ ችግሮች አንደኛው ምንጭ ሆኖ የተገኘው ከእድገታችን ጋር ተያይዘው የመጡ መሆናቸውን የተመለከተው ነው፡፡ በዋናነት ደግሞ በየደረጃው በሚገኙ የመንግስት አመራር አካላት ዘንድ በሚታዩ ድክመቶች፣ በተለይበምግባረ ብልሹነት ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮች በወቅቱና በአስተማማኝ ሁኔታ ባለመፈታታቸው የተከሰቱናቸውን የተመለከተውም ይገኝበታል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሮችም ሆነ የህዝቡን ተጠቃሚነት በተገቢው ደረጃ ያለማረጋገጥ ድክመት በዋነኛነት ከአመራር ብልሽት ጋር ተያይዘው የመጡ ችግሮች ናቸው፡፡ በመንግስት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የተቀመጡ ግለሰቦች የተረከቡትን ህዝባዊ አደራ ለማህበራዊና ሁለንተናዊ ሃገራዊ  ለውጥ ማምጫ በትጋት የሚሠሩበት መሣሪያ ማድረግን ወደጎን በመተው ስልጣንን የኑሮአቸው መሠረት የማድረግ አተያይና በዚህም ላይ የተመሰረተ ተጨባጭ ስህተት ከመፈፀማቸው ጋር ተያይዞ የተከሰተ ውጤት ነው፡፡ ይህ መታየት በጀመረበት ጊዜ ሁሉ የእድገታችን ፍጥነት መቀነሱም ሆነ የህዝብ ተጠቃሚነት ለአደጋ መጋለጡ አይቀርም፡፡
በተደጋጋሚ እንደተነገረው የችግሩ መንስኤ  ስርዓቱ በተፈጥሯዊ ባህርይው ለኪራይ ሰብሳቢነት የተጋለጠ ከመሆኑ የሚመነጭ ነው። ስለሆነም መፍትሄውም ከዚሁ የሚነሳ፤ ያላሰለሰና የማያባራ ውስጠ-ድርጅታዊ ዴሞክራሲና ትግል በድርጅቱ ውስጥ ማቀጣጠልና ጥልቀት ያለው ተሃድሶ ማካሄድ መሆኑ አያጠያይቅም።
በማንኛውም ሁኔታና ጊዜ፣ የሕዝቡን ጠያቂነትና ወትዋችነት በየጊዜው ማሳደግና የትግሉ አካል ማድረግ የመፍትሄው መነሻ መሆኑንም አመታዊ ስራውን በይፋ የጀመረው መንግስት በክቡር ፕሬዝዳንቱ በኩል አረጋግጧል ። 
ሀገሪቱ ከፍተኛ ሀብት እየፈጠረች በሄደች ቁጥር፣ ሀገሪቱን የሚመራው መንግስት የሚያዝበትና የሚወስንበት ሃብት እየጨመረ በመጣ መጠን፣ ኪራይ ሰብሳቢነት ስልቱን እየለዋወጠና መልኩን እየቀየረ፣ አቅሙን እያሳደገ ፈተና የመሆኑ ነባራዊ ዕውነታን በመሰረቱ በሚቀይር ማርሽ የሚነሳ መሆኑንም ማረጋገጡ ተገቢ ነው፡፡ በጠራ ሕዝባዊነትና በዓላማ ፅናት ብቻ ንፁህ አገልጋይ መሆን የሚጠበቅበትና የሚገባው የመሪው ድርጅት የኢህአዴግ አመራር፣ መስመሩ ሳይሆን ሃብት የሚያማልለው የመሆን አዝማሚያው በጨመረ ቁጥር፣ ሀገርን የሚንድ የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ ስጋት ከፍ ማለቱ አይቀሬ መሆኑን ባረጋገጠው ጥልቅ ተሃድሶ አግባብ የመንግስት የስልጣን ቦታዎች መያዝ አለባቸው፡፡  ምክንያቱም ከፍተኛ መጠን ባለው ሃብት ላይ የሚወስን አመራር፣ ውሳኔው ንፁህ ሕዝባዊነትና ሃገራዊ ዕድገት ላይ ካልተመሠረተ፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አረንቋ ውስጥ ሊዘፈቅ መቻሉ የሚጠበቅና የማያጠያይቅ ስለሆነ። በዚህ መልኩ ማርሹ ካልተስተካከለ ደግሞ አሁንም በገዛ ሃገር ላይ ባይተዋርነትን ይፈጥርና እርስ በእርስ ስለሚያናጨን  እና ብሶተኛው ሁሉ ህገወጥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እና በተነሱ ግርግሮች ሁሉ ተሳታፊ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎች ስለሚፈጥር፡፡ ይህም ባለፈው ሰሞን በኦሮሚያ ተነስቶ በነበረው ሁከትና በጎንደሩ የጥቂቶች አጀንዳ ላይ ተሳትፈው ከነበሩ ድንጋይ ወርዋሪዎች ተረጋግጧል።
እንዲህ አይነቱ ከድርጅቱ ውጪ ካለ ኪራይ ሰብሳቢ ጋር አብሮ በመጠቃቀም ሲወሰን የሚውለው አመራር ቁጥር ከፍ ባለ መጠን ሃገር የመፍረስ አደጋ ውስጥ መግባቷ የማይቀር መሆኑም በማያከራክር አግባብ ተረጋግጧልና ሹመቱም እድገትና ውረደቱም በዚሁ እና ህዝብን ማእከል ባደረገው ማእቀፍ ሊታይ ይገባዋል፡፡  
በእርግጥ ጥቅመኛው ሃይል በፈጠረው የጥቅም ሰንሰለት የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ዘመቻውን ለማኮላሸት የሚችለውን ሁሉ ያደረጋል፣ እያደረገም ነው። በተቻለው ሁሉ ከፍተኛ በጀት በመመደብ የዘመቻውን የመከላከያ አጥር ሲያጠብቅና ማኮላሻ መንገድ ሲጠርግ  ውሎ እያደረ መሆኑም የማያጠያይቅና ይልቁንም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማውጣት እስከሚያስገድድ ውድመት ውስጥም ገብቶ የነበረ በመሆኑም የሚገለጽ ነው፡፡
ይህ ደግሞ የድርጅትን መዋቅር ጭምር ተጠቅሞ ፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ሀይሉን እና ዘመቻውን ለማደናቀፍ ተረባርቦ የነበረ መሆኑን የሚያጠይቅ ነው፡፡ በከፍተኛ ደረጃ ሃብት ያካበተ ሃይል እንደመሆኑ፣ በገንዘቡ በመደለል እየመጣበት ያለውን ዘመቻ ለማምከን  የኪራይ ሰብሳቢነት ያልተቋጩ ሰነዶቹ የሚገኙበትን መዘጋጃ ቤቶችና ፍርድ ቤቶች በማቃጠል ዘመቻውም ተገልጧል። በዚህ ብቻ ሳይወሰን ዋናው ጐሬው ወደ ሆነው የጠባብነትና የትምክህተኝት ሼል ውስጥ በመግባት ባህሪውም ተገልጧል ። 
በመሆኑም የዚህን ሀይል እንቅስቃሴ በሁሉም አቅጣጫ መገደብና በሁሉም አማራጭ መዝጋት የጊዜው ቁልፍ ጥያቄ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ግቡን እንዲመታ በተመሳሳይ ትብብር ይህን ሃይልና መረቡን የማጋለጥ ተከታታይና የማያባራ ዘመቻ ውስጥ መግባት ነው፡፡ ከሕዝብ የሚደበቅ ነገር የለም፡፡ በመሆኑም ሕዝብ ሁሉንም ገልጦና ገላልጦ ማሳየት አለበት፡፡ በየስርቻው ሀብት ያካበተውን በዘመድ አዝማድ ስም ሀብት ያከማቸውን በመጠቃቀምና በጎሰኝነት የተከለለውን ይህ ሁሉ ሳይበቃው ሰነዱ የሚገኝባቸውን ቦታዎች ሁሉ በማቃጠልና ህዝባዊ አመጽ ለማስመሰል የበርካታ ሰዎች ህይወት እንዲጠፋ እና ንብረት እንዲወድም ምክንያት የሆነውን ሁሉ ከየጎሬው እያወጣ ማጋለጥ ከህዝቡ የሚጠበቅ ሃላፊነትና ግዴታ ነው ፡፡ ይህንን ንቅናቄ መንግስት ያለአንዳች መዘናጋት መምራት የሚያስችለውን ኮማንድ ፖስት አቋቁሟልና ወደኋላ ማለት እና ስጋት ውስጥ መግባት አይገባም፡፡   ንቅናቄው በዚህ መልኩ ከተጀመረ ማንም አያቆመውም፡፡ ራሱን እያጠናከረ መሄድ ይችላል፡፡ በሂደትም ኪራይ ሰብሳቢነት ላይ ወሳኝ ድል መጎናፀፍ ይችላል፡፡
ይህን የህዝብ ትግል መነሻ በማድረግና ጉዳዩን ከልብ በመቀበል መንግስት ባሳለፍነው ዓመት መጨረሻ ራሱን ከዚህ ዝንባሌ ለማፅዳት ቁርጠኛ እንቅስቃሴ ማካሄድ ጀምሯል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ቀደም ሲል የተጀመረውን አገራዊ ህዳሴ ከመቀዛቀዝ አውጥቶ ወደ ቀጣይ የለውጥ ሂደት ለማሸጋገር አንዱ ቁልፍ እርምጃ መንግስታዊ ስልጣንን ወደ ግል ኑሮ ማሻሻያ ለማሸጋገር የሚደረገውን ይህን ዝንባሌና ጥረት ማስቆምና መንግስት በርግጥም የህዝብና የአገር መገልገያ መሳሪያ መሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡ ለህዝቡም ብቁና ፍትሃዊ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል ማድረግ ነው፡፡
ስለሆነም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስራውን  የፌዴራል መንግስትን የአመራር ሥርዓት በአዲስ መልክና ቅኝት ለማዋቀር ተግባራዊ እርምጃ በመውሰድ ይጀምራል መባሉም ተገቢ ነው፡፡ የፌዴራሉ አካል የሆኑ ክልል መንግሥታትም ተመሳሳይ ቅኝት እንደሚከተሉም ይኸው በኦሮሚያ አሃዱ ተብሎ ተረጋግጧል፡፡ በዚህ መሰረት የመንግስት ስልጣንን ካላግባብ የመጠቀም ዝንባሌን የሚገታና ከእንግዲህ በውጤት አልባነት የመንግስት ስልጣን ላይ ተቀምጦ መቆየት የማይቻል መሆኑን የሚያረጋግጥ አዲስ የመንግስት ምክር ቤት የማደራጀት እንቅስቃሴ ውስጥ መገባቱ ተገቢና የህዝብን ሮሮ ታሳቢ ያደረገ ትክክለኛ እርምጃ ነው፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ የተቻለውን ያክል ብቃትና ቅንነት ያላቸውን ግለሰቦች በኃላፊነት ላይ በማስቀመጥ የመንግስት የስራ አፈፃፀም በውጤትና በውጤት ብቻ የሚመራ እንዲሆን ማድረግ ይጀመራል፡፡ ይህን ተከትሎ ውጤት ያላመጣ ማንኛውም ሰው በማንኛውም ሽፋን በመንግስት ስልጣን ላይ እንደማይቀጥል የሚያረጋግጥ ቋሚ የአሰራር ስርዓት ጥቅም ላይ እንዲውልም እድልና ምቹ ሁኔታዎች ስለሚፈጠሩ አካሄዱ ተመችቶናል፡፡

No comments:

Post a Comment